ምዕራፍ 24 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ
የተጠሩት አራቱ ዓሣ አጥማጆች
ኢየሱስ ከናዝሬት ከተባረረ በኋላ መኖሪያው አድርጎ የመረጠው ስፍራ ቅፍርናሆም ነበረች። ይህች በገሊላ ባሕር በሰሜን ምዕራብ ዳርቻ የምትገኝ ታላቅ ከተማ ነበረች። በባሕሩ አጠገብ ከእርሷ የምትበልጥ አንዲት ከተማ ብቻ ነበረች፤ እርሷም ጥብርያዶስ ናት። ይህች የገሊላ ገዥ በነበረው በሄሮድስ የተሠራችና በሮም በነበረው በንጉሠ ነገሥቱ በጢባርዮስ ስም የተሰየመች አዲስ ከተማ ነበረች። ጥብርያዶስ ግን የአይሁድ ከተማ አልነበረችም። በውስጧ የጣዖት መቅደሶች ነበሩ፤ ሕዝቧም መጻተኞች ነበሩ፤ በቅጥሮቿም ውስጥ ለመኖር የሚፈቅዱ አይሁድ እጅግ ጥቂቶች ነበሩ። ደግሞም ሄሮድስ አንቲጳስ በዚያ ራሱ በሠራው ቤተ መንግሥት ይኖር ነበር፤ ኢየሱስም ወደ ሄሮድስ መቅረብ አልፈለገም።
ቅፍርናሆም ግን የአይሁድ ከተማ ነበረች፤ ኢየሱስም ሥራው በአይሁድ መካከል እንደ ሆነ ተሰማው። ከኢየሱስ የመጀመሪያ ተከታዮች ቢያንስ አራቱ በቅፍርናሆም ይኖሩ ነበር፤ እነርሱም ሁለት ጥንድ ወንድማማቾች ነበሩ፤ የዮና ልጆች ስምዖንና እንድርያስ፥ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ። እነዚህ አራት ሰዎች በዓሣ ማጥመድ ሥራ ከዘብዴዎስ ጋር ተባባሪዎች ነበሩ። ብዙ የዓሣ ማጥመጃ ታንኳዎች ነበሯቸው፤ የሚሠሩላቸውም ሰዎች ነበሯቸው። ባሕሩ በዓሣ የተሞላ ነበረ፤ በዙሪያውም ያሉ ብዙ ሰዎች በዓሣ ማጥመድ ይተዳደሩ ነበር። የገሊላ ባሕር ዓሣ መልካም ምግብ ነበረ፤ በአቅራቢያ ወዳሉት ከተሞች ሁሉም ይላክ ነበር። ከዚህ ዘመን ብዙም ሳይቈይ በሮም የነበረ አንድ ንጉሠ ነገሥት በቤተ መንግሥቱ ለማዕዱ በየሳምንቱ ከገሊላ ባሕር አንድ በርሜል ሙሉ ዓሣ ይላክለት እንደ ነበረ ይነገራል።
የቅፍርናሆም ሰዎች ስለ ኢየሱስ ሰምተው ነበር፤ በኢየሩሳሌም ወደሚከበሩት በዓላት የወጡ ሁሉ ስለዚህ ድንቅ መምህርና ድውዮችን ስለሚፈውሰው ሰው ወሬ ወደ ቤታቸው ይዘው መጥተው ነበርና። ኢየሱስ በሄደበት ሁሉ ቃሉን ለመስማት፥ ይልቁንም ከድንቅ ሥራዎቹ አንዱን ያደርግ እንደ ሆነ ለማየት በመጓጓት ብዙ ሕዝብ በዙሪያው ይሰበሰብ ነበር።
አንድ ቀን ጠዋት ኢየሱስ በባሕሩ ዳር ሲመላለስ ከተከታዮቹ አንዳንዶቹን አገኘ። እነዚህ ሰዎች አሁን ወደ ገዛ ቤታቸው ስለ መጡ እንደ ቀድሞው ወደ ዓሣ ማጥመድ ሥራቸው ተመልሰው ነበር፤ ታንኳዎቻቸውም በባሕሩ ዳር ቆመው ነበር። ሰዎቹ ባለፈው ሌሊት ዓሣ ሲያጠምዱ አድረው አሁን በባሕሩ ዳር መረቦቻቸውን ያጥቡ ነበር። ኢየሱስም ከተከታዮቹ አንዱን ስምዖን ጴጥሮስን ታንኳውን ከምድር ጥቂት ፈቀቅ አድርጎ ወደ ውኃው እንዲገፋት ነገረው። እርሱም እንዲሁ አደረገ፤ ኢየሱስም በታንኳይቱ ውስጥ ተቀመጠ፤ ብዙ ሕዝብም ድምፁ በሚደርስበት ርቀት በባሕሩ ዳር ቆመው ነበር። ከዚያም ኢየሱስ ታንኳይቱን እንደ መድረክ አድርጎ በባሕሩ ዳር ላሉት ሰዎች ተናገረ። በዚያን ጊዜ የተናገረው አልተጻፈም፤ ነገር ግን በማቴዎስ ወንጌል በአምስተኛው፥ በስድስተኛውና በሰባተኛው ምዕራፍ በሚነበበው በተራራው ስብከት ውስጥ ካለው ትምህርቱ ጋር እጅግ ይመሳሰል ነበር። ኢየሱስ በብዙ ስፍራ ለልዩ ልዩ ሕዝብ ሲናገር ያንኑ ትምህርት ደጋግሞ ይሰጥ እንደ ነበረ ምንም ጥርጥር የለም።
ኢየሱስ ለሕዝቡ መናገሩን ከጨረሰ በኋላ ከሌሎቹ ዓሣ አጥማጆች ጋር በአጠገቡ ቆሞ የነበረውን ስምዖንን እንዲህ አለው፦
«ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል፤ ዓሣም ለማጥመድ መረቦቻችሁን ጣሉ።»
«መምህር ሆይ፥» ብሎ ስምዖን መለሰ፤ «ሌሊቱን ሁሉ ደከምን፤ አንድ ዓሣ ስንኳ አልያዝንም። ነገር ግን እንደ ገና እንድንሞክር ብትነግረን መረቦቹን እጥላለሁ።»
እንዲሁም አደረጉ፤ አሁንም መረቦቻቸው እጅግ ብዙ የዓሣ መንጋ ያዙ፤ ብዛቱም መረቦቹ መቀደድ እስኪጀምሩ ድረስ ነበረ። በሌላይቱም ታንኳ የነበሩትን ጓደኞቻቸውን መጥተው እንዲያግዙአቸው ጠቀሷቸው። እነርሱም መጥተው መረቦቹን በመሳብና ዓሣውን ወደ ታንኳዎቹ በመገልበጥ ረዱ። ዓሣውም እጅግ ብዙ ስለ ነበረ ሁለቱንም ታንኳዎች ሊሰጥሙ እስኪጀምሩ ድረስ ሞሉአቸው። ስምዖን ጴጥሮስም ይህን ሁሉ ባየ ጊዜ ይህ በእግዚአብሔር ኃይል እንደ ተደረገ ተሰምቶት በመደነቅና በፍርሃት ተያዘ። በታንኳይቱም ውስጥ በኢየሱስ ፊት በጕልበቱ ወድቆ እንዲህ አለ፦
«ጌታ ሆይ፥ እኔ ኃጢአት የሞላብኝ ነኝ፤ ለዚህ ሁሉ የተገባሁ አይደለሁም! ጌታ ሆይ፥ ከእኔ ተለይ!»
ኢየሱስ ግን እርሱንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሦስቱን ሰዎች እንዲህ አላቸው፦
«አትፍሩ፤ ተከተሉኝ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምዱ ትሆናላችሁ።»
ይህን ሲል አሁን መረቦቻቸውንና ታንኳዎቻቸውን ትተው ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ ማለቱ ነበረ፤ ከእርሱም ከተማሩ በኋላ ወጥተው ሰዎችን ከኃጢአት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚያወጣውን መንገድ እንዲያሳዩ ነበረ።
ስለዚህ መረቦቻቸውንና ዓሣቸውን ወደ ምድር እንዳደረሱ ወዲያው ከያዕቆብና ከዮሐንስ አባት ከዘብዴዎስና ከቅጥር ሠራተኞቹ ጋር ተዉአቸው።
ከዚያ ቀን ጀምሮ እነዚህ አራት ሰዎች ቃሉን እየሰሙ ከኢየሱስ ጋር ኖሩ፤ በጕዞውም ሁሉ አብረውት ሄዱ፤ ብዙ ጊዜ ከመስማታቸውም የተነሣ ቃሉን አጥንተው ለሌሎች ሊደግሙት ቻሉ።