የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
አናጢው በገዛ ከተማው

ምዕራፍ 23 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ

አናጢው በገዛ ከተማው

ኢየሱስ ቃናን ከጎበኘና የሹሙን ልጅ ከፈወሰ በኋላ ብዙም ሳይቈይ ስድስት ማይል ብቻ ወደምትርቀው ወደ ቀድሞ መኖሪያው ወደ ናዝሬት በእግሩ ሄደ። በዚያች ከተማ ያሉትን፥ አሁን የራሳቸው ልጆች ያሏቸው ሴቶች የሆኑትን እኅቶቹን አሰበ፤ ሊያያቸውም ናፈቀ። ደግሞም በቀድሞ ዘመን አብሮአቸው የተጫወተውንና በትምህርት ቤት አብሮአቸው የተቀመጠውን፥ አሁን ግን ቤተ ሰብ ያላቸው ሰዎች የሆኑትን ልጆች አሰበ፤ አንድ ዓመት ያህል ያላያቸውንም የቀድሞ ጎረቤቶቹን አሰበ። ልቡ ለገዛ ወገኖቹ በፍቅር የተሞላ ነበረ፤ እግዚአብሔር ከሰጠው ኃይል የተነሣ የሚጠቅማቸውን ቃል ሊነግራቸው እንደሚችልም ተሰማው።

የናዝሬት ሰዎች ስለ ቀድሞው የከተማቸው ሰው አስደናቂ ወሬ በእርግጥ ሰምተው ነበር፤ ይኸውም ድንገት ከዚህ በፊት ፈጽሞ ያልተሰማ እውነትን የሚናገር ታላቅ መምህር ሆኖ እንደ ተገለጠ፥ ይልቁንም በቃናና በቅፍርናሆም ድውዮችን በመፈወስ ድንቅ ሥራ እንዳደረገ ነበረ። ይህ ወሬ ሁሉ የናዝሬትን ሰዎች አስገረማቸው፤ ኢየሱስ በመካከላቸው ሳለ ምንም የታላቅነት ምልክት አሳይቶ አያውቅም ነበርና። በጸሎት ቤቱ በስፍራው ይቀመጥ ነበር እንጂ በመድረኩ ላይ ሆኖ ተናግሮ አያውቅም፤ ለሁሉ ደግና ገር የሆነ መልካም ወጣት፥ በሙያውም ታማኝና ብልህ ሠራተኛ እንደ ሆነ ያውቁት ነበር። ነገር ግን እንደ መምህር፥ ወይም ከእግዚአብሔር መልእክት እንደሚያመጣ ነቢይ፥ ወይም በቃናና በቅፍርናሆም እንዳደረገ እንደ ሰሙት ድንቅ እንደሚያደርግ ሰው አድርገው አስበውት አያውቁም ነበር።

ኢየሱስ በሰንበት ቀን በናዝሬት የጸሎት ቤት እንደሚናገር ይጠበቅ ነበር (የጸሎት ቤታቸውን «ምኵራብ» ይሉት ነበር፤ ትርጓሜውም «የሕዝብ ጉባኤ» ማለት ነው)፤ ሊያዩትና ሊሰሙትም ሰው ሁሉ በዚያ ተገኘ። በአንድ ወገን ባለው ሰገነት እኅቶቹ ሳይታዩ እየተመለከቱና እያደመጡ ነበሩ፤ በአይሁድ የጸሎት ቤቶች ሁሉ የሴቶች ሰገነት በፍርግርግ የተሸፈነ ነበረና። ከታች በወለሉ ላይ በምንጣፍ ወይም በሰሌን ላይ ተቀምጠው ጎረቤቶቹና ከልጅነቱ ጀምሮ ሰው እስኪሆን ድረስ ሲያድግ ያዩት ሰዎች ነበሩ። የተገኙትም ለመማር ሳይሆን ቃሉን ሊሰሙና ሊፈርዱበት፥ ይልቁንም ምን ታላቅ ነገር እንደሚያደርግ ለማየት ነበረ።

ኢየሱስ ወደ መድረኩ ወጣ፤ ኃላፊው አገልጋይም የዕለቱ ንባብ የተጻፈባቸውን ጥቅልሎች ሰጠው። ይህ አገልጋይ በአንድ ጊዜ የሕንጻው ጠባቂና በሳምንቱ ቀናት በዚያ የሚሰጠው ትምህርት መምህር ነበረ። ይህ ሰው ምናልባት ኢየሱስን በልጅነቱ ማንበብ ያስተማረው መምህር ሊሆን ይችላል። ለዚያ ቀን ከተመደቡት ንባቦች አንዱ በነቢዩ ኢሳይያስ መጽሐፍ በስድሳ አንደኛው ምዕራፍ ውስጥ ነበረ። ከእርሱም አንዱ ክፍል እንዲህ ይላል፦

«የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥
ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ለይቶኛልና።
እስረኞች ነጻ እንደሚወጡ እናገር ዘንድ ልኮኛል፥
ዕውሮችም ዳግመኛ እንደሚያዩ፥
ድሆችና መከራ የሚቀበሉም ነጻነት እንደሚሰጣቸው፥
ከእግዚአብሔርም የሞገስ ዘመን እንደ ደረሰ።»

ኢየሱስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሲያነብ ቆሞ ነበር፤ በዚያም የነበሩት ሁሉ ደግሞ ቆሙ፤ አይሁድ መጽሐፍ ቅዱስ በተነበበ ቁጥር በመቆም ለእርሱ ያላቸውን አክብሮት ያሳዩ ነበርና። ንባቡንም ከጨረሰ በኋላ ጥቅልሉን ጠቅልሎ ለአገልጋዩ መለሰለትና ተቀመጠ፤ ሕዝቡም እንዲሁ ተቀመጡ። በምኵራብ ወይም በጸሎት ቤት የሚሰብክ ሰው ብዙ ጊዜ ተቀምጦ ይናገር ነበር። ኢየሱስም እንዲህ ብሎ ጀመረ፦

«ዛሬ ይህ የነቢዩ ቃል በጆሮአችሁ ተፈጸመ።»

ለድሆች እንዲሰብክ፥ እስረኞችን ነጻ እንዲያወጣ፥ ለዕውሮች ማየትን እንዲሰጥና የእግዚአብሔርን ቸርነት የምሥራች ለሰዎች እንዲያመጣ እንዴት እንደ ተላከ በቀላልና በገር ቃል ይነግራቸው ጀመር። በመጀመሪያ ሕዝቡ በታላቅ ጕጕት አደመጡ፤ ልባቸውም በደግና በርኅሩኅ ቃሉ ተነካ።

ብዙም ሳይቈዩ ግን እርስ በርሳቸው ይንሾካሾኩ ጀመር። አንዱ «ይህ አናጢ እኛን ሊያስተምር ለምን ይሞክራል?» አለ። ሌላውም «ይህ ሰው መምህር አይደለም! እርሱ የአናጢው የዮሴፍ ልጅ ብቻ ነው! ወንድሞቹን እናውቃቸዋለን፤ እኅቶቹም እዚህ ይኖራሉ» አለ። አንዳንዶቹም «በሌሎች ስፍራዎች አድርጓቸዋል ከሚባሉት ድንቅ ነገሮች አንዳንዱን ለምን እዚህ አያደርግም? ድውዮችን የሚፈውስበትን አስደናቂ ሥራውን ልናይ እንወዳለን!» ይሉ ጀመር።

ኢየሱስ አሳባቸውን ያውቅ ነበር፤ ነገር ግን በሰዎች ዘንድ ለመታየት ብቻ ድንቅ ሥራ አያደርግም ነበር። እንዲህም አላቸው፦

«‹በቅፍርናሆም በሹሙ ልጅ ላይ እንደ ተደረገው ያለ ድንቅ ሥራ እስኪ እንይ› እንደምትሉ አውቃለሁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ነቢይም ሆነ መምህር በገዛ ወገኑ ዘንድ ክብር የለውም።»

«በነቢዩ በኤልያስ ዘመን ሰማይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ተዘግቶ ዝናብ ባልዘነበ ጊዜ በምድሪቱ ታላቅ ራብና የእንጀራ እጦት እንደ ነበረ ታስታውሳላችሁ። በዚያን ጊዜ በእስራኤል ምድር ብዙ መበለቶች ነበሩ፤ ኤልያስ ግን በሲዶና አገር ወዳለችው ወደ ሰራፕታ፥ መጻተኛና ከአሕዛብ ወገን ወደ ሆነች ወደ አንዲት መበለት እንጂ ከእነዚህ ወደ አንዲቱም አልተላከም። ከኤልያስም በኋላ በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመን በእስራኤል ምድር ብዙ ለምጻሞች ነበሩ፤ ነገር ግን ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር ከእነርሱ አንድ ስንኳ ከለምጹ አልነጻም።»

እግዚአብሔር ድንቅ ሥራውን ለማድረግ ከእስራኤላውያን ይልቅ መጻተኞችን እንዴት እንደ መረጠ የሚናገረው ይህ ቃል በጸሎት ቤቱ የነበሩትን ሰዎች እጅግ አስቈጣቸው፤ ለኢየሱስ ቃል ግድ አልነበራቸውም፤ የፈለጉት ተአምር ወይም ድንቅ ሥራ ሲያደርግ ማየት ብቻ ነበረና። ሊሰሙትም አልወደዱም፤ በቍጣና በንዴት ተሞልተው ከመቀመጫቸው ዘለው ተነሡ፤ ወደ መድረኩ ሮጠው ወጡ፤ ኢየሱስንም ይዘው ወደ ውጭ ጐተቱት። ከከተማይቱ በላይ ወዳለው ኮረብታ ራስ ወሰዱት፤ ከገደሉም ቍልቍል ጥለው ሊገድሉት ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ የሚሞትበት ጊዜ ገና አልደረሰም ነበር። በእግዚአብሔር ኃይል ኢየሱስ በጸጥታ ከእጃቸው አምልጦ ሄደ። የእግዚአብሔርን የበረከት የምሥራች ከሁሉ አስቀድሞ ለገዛ ወገኖቹ ሊያመጣ ናፍቆ ነበርና ከናዝሬት በታላቅ ኀዘን ተለይቶ ሄደ።


ቀዳሚ ቀጣይ