የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
የሹሙ ልጅ

ምዕራፍ 22 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

የሹሙ ልጅ

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በያዕቆብ የውኃ ጕድጓድ አጠገብ ባለችው መንደር በሲካር ሁለት ቀን ከቈዩ በኋላ ወደ ሰሜን ወደ ገሊላ ምድር መንገዳቸውን ቀጠሉ። በጥንት ዘመን ብዙ ጦርነቶች የተደረጉበትን ታላቁን ሜዳ አቋርጠው ሄዱ፤ ከእርሱም ባሻገር ያሉትን ተራሮች ወጡ። ኢየሱስ ለብዙ ዓመታት የኖረባት ናዝሬት በመንገዱ ላይ ነበረች፤ ኢየሱስ ግን ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ሊጎበኛት በልቡ አስቦ ስለ ነበረ በዚህ ጊዜ በዚያ አልቆመም። ከተከታዮቹም ጋር ከጥቂት ወራት በፊት ውኃውን የወይን ጠጅ ወዳደረገባት ስፍራ ወደ ቃና ለሁለተኛ ጊዜ መጣ።

ኢየሱስ መጀመሪያ ቃናን በጎበኘ ጊዜ ስሙን የሰሙ ሰዎች እጅግ ጥቂቶች ነበሩ። አሁን ግን ሰው ሁሉ ስለ እርሱ ይነጋገር ነበር፤ ከፋሲካ በዓል ወደ ቤታቸው የተመለሱት ሁሉ በኢየሩሳሌም ሲሰብክ ስለ ነበረው፥ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ከቤተ መቅደስ ስላስወጣው፥ ድውዮችንም በመፈወስ ድንቅ ስላደረገው ስለ አስደናቂው ወጣት ነቢይ ለወዳጆቻቸውና ለጎረቤቶቻቸው ነግረዋቸው ነበርና።

ከቃና ሃያ ማይል ገደማ ርቃ በገሊላ ባሕር ዳር ቅፍርናሆም የምትባል ከተማ ነበረች። በቅፍርናሆም የንጉሥ ሄሮድስ አንቲጳስ ባለሥልጣን የሆነ አንድ ከፍተኛ ማዕረግ ያለው ሰው ይኖር ነበር። ይህ ሹም በታላቅ ጭንቀት ውስጥ ነበረ፤ ልጁ በብርቱ ንዳድ እጅግ ታሞ ለሞት ተቃርቦ ተኝቶ ነበርና። ኢየሱስ እንደ ገና በገሊላ እንዳለና ሃያ ማይል ብቻ ርቆ እንደሚገኝ የሰማው ወሬ፥ ምናልባት ይህ ነቢይ ከቃና ወደ ቅፍርናሆም ወርዶ ልጁን ሊፈውስ ይፈቅድ ይሆናል የሚል ተስፋ ለሹሙ አመጣለት።

ወዲያውም ወደ ኢየሱስ ሄዶ መጥቶ እንዲረዳው ሊለምነው ቈረጠ። ከቅፍርናሆም ወደ ቃና የሚወስደው መንገድ ሃያ ማይል ተራራ መውጣት ስለ ሆነ አስቸጋሪ ጕዞ ነበረ፤ ይህ የተጨነቀ አባት ግን በማለዳ ተነሥቶ ከቀኑ በሰባት ሰዓት ገደማ ቃና ደረሰ። ኢየሱስንም አግኝቶ ልጁ ምን ያህል እንደ ታመመ ነገረው፤ ወደ ቅፍርናሆም መጥቶ እንዲፈውሰውም ለመነው። ኢየሱስ ግን ለመሄድ ብዙም የፈቀደ አይመስልም ነበር። ሹሙንም እንዲህ አለው፦

«እናንተ ሰዎች ድንቅ ሥራ ሳደርግ ሁልጊዜ ካላያችሁ በእኔ አታምኑም።»

«ጌታ ሆይ፥» አለ የተጨነቀው አባት እየለመነ፥ «ልጄ እንዳይሞት እባክህ ፈጥነህ ውረድ!»

«እኔ መምጣት አያስፈልገኝም፤» አለ ኢየሱስ። «ወደ ቤትህ ሂድ፤ ልጅህ በሕይወት ይኖራል፤ ይድናልም።»

ይህ ቃል የዚህን ሰው በኢየሱስ ላይ ያለውን እምነት በብርቱ የሚፈትን ነበረ። ኢየሱስ ምንም ምልክት ሳይሰጠው ልጁ እንደሚድን እንዴት ሊያውቅ ይችላል? ኢየሱስስ ያላየውንና ሃያ ማይል ርቆ ያለውን ሰው በአንድ ቃል ሊፈውስ እንደሚችል እንዴት ሊረዳ ይችላል? አባትየው ግን የኢየሱስን ተስፋ ወዲያው አመነ። ልጁ መዳኑን ለማየት ወደ ቤቱ እንኳ አልቸኰለም፤ ነገር ግን ጕዞውን ለመጀመር እስከ ማታ ድረስ ቈየ።

በማግሥቱም ወደ ቤቱ በቀረበ ጊዜ ባሮቹ ተገናኝተው የደስታውን ወሬ ነገሩት፦

«ልጅህ በሕይወት አለ፤ እጅግም ተሻሎታል።»

«መሻል የጀመረው በስንት ሰዓት ነው?» አለ ሹሙ።

«ትናንት ነው፤» አሉት፤ «በሰባት ሰዓት ገደማ ንዳዱ ለቀቀው።»

ሰውዬው አልተደነቀም፤ ልክ እንደ ጠበቀው ሆኖአልና። ያቺ ሰባት ሰዓት ኢየሱስ «ልጅህ በሕይወት ይኖራል» ያለበት ሰዓት ራሷ ነበረች።

ይህ ተአምር፥ ማለትም ድንቅ ሥራ፥ ሰዎች ብዙ ተነጋገሩበት፤ ይህንንም ሹም ብቻ ሳይሆን ቤተ ሰቡን ሁሉ ከእርሱ ጋር ኢየሱስ ለረጅም ዘመን ተስፋ የተሰጠበት መድኃኒትና የእስራኤል ንጉሥ እንደ ሆነ እንዲያምኑ አደረጋቸው።


ቀዳሚ ቀጣይ