የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
በአሮጌው የውኃ ጕድጓድ አጠገብ

ምዕራፍ 21 · 6 ደቂቃ ንባብ · 7 ደቂቃ ማዳመጥ

በአሮጌው የውኃ ጕድጓድ አጠገብ

ከፋሲካ በኋላ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ባለው አውራጃ ወይም የምድሪቱ ክፍል በይሁዳ መንደሮች እያስተማረ ዞረ። ይሁዳ ከአምስቱ አውራጃዎች ትልቁ ስለ ነበረ ስሙን ለምድሪቱ ሁሉ ሰጠ፤ ምድሪቱም «ይሁዳ» እና «የእስራኤል ምድር» ተብላ ትጠራ ነበር። መጥምቁ ዮሐንስ አሁንም ይሰብክና ያጠምቅ ነበር፤ ሊሰሙት የሚመጡት ሕዝብ ግን እንደ ቀድሞው ብዙ አልነበሩም። ዮሐንስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሳለ ኢየሱስ ሕዝቡን ከዮሐንስ ሊያርቅ የሚሞክር እንዳይመስላቸው በይሁዳ ተቀመጠ።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ኢየሱስ መጥምቁ ዮሐንስ በገሊላና በፔሪያ ክፉ ገዢ በሄሮድስ አንቲጳስ እንደ ታሰረ ሰማ። ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን ወስዶ ከእርስዋ ጋር ይኖር ነበር። ዮሐንስም እንዲህ አለው፦

«የወንድምህን ሚስት መውሰድ በሙሴ ሕግና በእግዚአብሔር ፊት አልተፈቀደልህም።»

ይህም ሄሮድስን በዮሐንስ ላይ አስቈጣው፤ ሄሮድያዳም ከእርሱ ይልቅ ተቈጣች። ስለ ድፍረት ቃሉ ዮሐንስ እንዲገደል ፈለገች፤ ሄሮድስ ግን ምንም እንኳ ደግ ሰው ባይሆን ዮሐንስ እንዲገደል አልወደደም፤ በከፊልም ከሚስቱ ጥላቻ ሊጠብቀው ወደ ወኅኒ እንዲገባ አዘዘ። በምድረ በዳ ነጻ ኑሮ ለለመደ፥ በከተማ ወይም በመንደር ለመኖር እንኳ ላልፈለገ እንደ ዮሐንስ ላለ ሰው በአራት ግንብ መካከል በወኅኒ ክፍል ተዘግቶ የውጭውን ዓለም በብረት በተዘጉ መስኮቶች ብቻ ማየት እጅግ ከባድ ሳይሆንበት አልቀረም።

ኢየሱስ መጥምቁ ዮሐንስ በወኅኒ እንደ ተዘጋበት ባወቀ ጊዜ በይሁዳ የነበረውን ሥራውን ጨረሰ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር በሰሜን ወዳለው ወደ ቀድሞ አገሩ ወደ ገሊላ ጕዞ ጀመረ። በዚህ ጕዞ በዮርዳኖስ ወንዝ መንገድ አልሄደም፤ ይልቁንም በሰማርያ ምድር የሚያሳልፈውን ቀጥተኛውን መንገድ ያዘ። በዚያች ምድር የሚኖሩት ሳምራውያን አይሁድን እንደሚጠሉና በአገራቸው ሲያልፉ ብዙ ጊዜ እንደሚዘርፉአቸው ያውቅ ነበር። ቢሆንም ኢየሱስ በሰማርያ በኩል ሊያልፍ ቈረጠ።

ጥቂቶቹን ተከታዮቹን እየመራ ከኢየሩሳሌም ወደ ሰሜን ተጓዘ፤ ከብዙ ዘመን በፊት ያዕቆብ በድንጋይ ትራስ ላይ ተኝቶ እስከ ሰማይ የደረሰ መሰላል ያየበትን ያን ድንቅ ሕልም ያለመባትን ቤቴልን አለፈ፤ በሳሙኤል ዘመን ቅዱሱ የእግዚአብሔር ታቦት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ተቀምጦበት የነበረውን ሴሎን አለፈ፤ ጦርነቶች የተደረጉባቸውንና ድሎች የተገኙባቸውን ተራሮችም ተሻገረ።

በአንድ ቀን ማለዳ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ሌሊቱን ሙሉ ከተጓዙ በኋላ ከሴኬም ከተማ ሁለት ማይል ያህል ርቆ ወዳለ አንድ አሮጌ የውኃ ጕድጓድ ደረሱ። በአጠገቡ ከጕድጓዱ የምትታይ ሲካር የምትባል ትንሽ መንደር ነበረች፤ የሳምራውያን መንደር ብትሆንም የኢየሱስ ተከታዮች ምግብ ሊገዙ ወደ እርስዋ ሄዱ። ይህ ጕድጓድ እጅግ አሮጌ ነበረ። ኢየሱስ ወደዚያ ስፍራ ከመምጣቱ ከአንድ ሺህ ስምንት መቶ ዓመት በፊት የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ አባት የሆነው ያዕቆብ ቈፍሮት ነበር። እስከ ዛሬም በዚያ አለ፤ ከጠንካራ ዓለት የተቈፈረ፥ መቶ ጫማ የሚያህል ጥልቀት ያለው ጕድጓድ ነው፤ ዛሬም በዓመት አሥር ወር ውኃ ይገኝበታል፤ በበጋ ግን ይደርቃል። ያ ጕድጓድ አሁን አራት ሺህ ዓመት ሊሆነው ጥቂት ቀርቶታል፤ ቢሆንም የሚጎበኘው መንገደኛ ሁሉ ወደ ጥልቁ ቍልቍል ሊመለከት፥ ባልዲ ውኃ ሲቀዳ ሊያይና ከእርሱም ሊጠጣ ይችላል።

በዚያ ዘመን ጕድጓዱ ውኃ የሚያወጣ ፓምፕ አልነበረውም፤ ወደ ውስጡ የሚወርድ ገመድ እንኳ አልነበረም፤ ውኃ ሊቀዳ የሚመጣ ሁሉ፥ ብዙውን ጊዜም ሴት ነበረች፥ ገመድና እንስራ ይዞ ይመጣ ነበር። ኢየሱስ እጅግ ደክሞ፥ ተርቦና ተጠምቶ በጕድጓዱ አጠገብ ሲቀመጥ ውኃ የሚቀዳበት ምንም አልነበረውም። በምድር ላይ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መሆኑ ውኃው ወደ እርሱ እንዲመጣ ማድረግ ይችል ነበር፤ ነገር ግን አላደረገውም፤ በምድረ በዳ ኢየሱስ ለራሱ ፍላጎት ብቻ ምንም ድንቅ ሥራ ወይም ተአምር እንደማያደርግ ታስታውሳላችሁና።

ኢየሱስ ድንገት የአንድ ሰው መምጣት ድምፅ ሰማ። ቀና ብሎ ሲመለከት አንዲት ሴት እንስራዋንና ገመድዋን ይዛ በጕድጓዱ አጠገብ ቆማ አየ። ከአለባበስዋም አይሁዳዊት ሳትሆን ሳምራዊት እንደ ሆነች አወቀ፤ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆኑም ከዚህ የበለጠ አየ። መልካም ያልነበረውን ሕይወትዋን ሁሉ ወዲያው አወቀ። ነገር ግን ልብዋን ተመልክቶ እግዚአብሔርንና መልካሙን የምትናፍቅ እንደ ሆነች አየ። እንዲህም አላት፦

«ከዚህ ጕድጓድ ውኃ ታጠጪኛለሽን?»

ሴቲቱም ኢየሱስን ተመለከተች፤ ከአለባበሱና ከአነጋገሩም አይሁዳዊ እንደ ሆነ አውቃ እንዲህ አለችው፦

«አንተ አይሁዳዊ ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ?»

አይሁድ ሳምራውያንን ይንቁ ነበር፤ ምንም ውለታ አይለምኑአቸውም ነበር፤ ሳምራዊ በእጁ የነካውን ጽዋ ወይም ማንቈርቈሪያ ተጠቅመው አይጠጡም ነበር። ሴቲቱ ይህን ታውቅ ነበር፤ ስለዚህ ይህ የአይሁድ ወገን የሆነ እንግዳ ወጣት ስላናገራት እጅግ ተገረመች። ኢየሱስም መለሰላት፦

«የእግዚአብሔርን ነጻ ስጦታና ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑን ብታውቂ፥ አንቺ በተራሽ ትለምኚው ነበር፤ እርሱም የሕይወት ውኃ ይሰጥሽ ነበር።»

ኢየሱስ ይህን ቃል በጥልቅ አሳብ ሲናገር ሴቲቱ እየተመለከተችና እየሰማች ይህ ተራ ሰው እንዳልሆነ ተሰማት። ምናልባት ነቢይ፥ ማለትም ብርቱ ሥራ እንዲሠራና የእግዚአብሔርን ቃል እንዲናገር እግዚአብሔር የላከው ሰው ይሆናል ብላ አሰበች። በታላቅ አክብሮትም እንዲህ አለችው፦

«ጌታ ሆይ፥ መቅጃ የለህም፤ ጕድጓዱም እጅግ ጥልቅ ነው። የሕይወት ውኃህን ከወዴት ታገኛለህ? ይህን ጕድጓድ ቈፍሮ ከሰጠን፥ ራሱም ከልጆቹና ከበጎቹ ከበሬዎቹም ጋር ከውኃው ከጠጣው ከአባታችን ከያዕቆብ አንተ ትበልጣለህን?»

ኢየሱስም መለሰላት፦

«ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ከቶ አይጠማም። እኔ የምሰጠው ውኃ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል።»

ሴቲቱም «ጌታ ሆይ፥ እንዳልጠማ ይህንንም መንገድ ሁሉ ውኃ ልቀዳ እንዳልመጣ ከሕይወት ውኃህ ስጠኝ» አለች።

ኢየሱስ የሴቲቱን ፊት አጥብቆ ተመለከተ፤ ከዚያም እንዲህ አላት፦

«ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ተመለሺ።»

የሴቲቱ ፊት ጨለመ፤ ዓይኖችዋን ዝቅ አደረገች፤ ያፈረች መሰለች፤ በለሆሳስም «ባል የለኝም» ብላ መለሰች።

ኢየሱስም ትኵር ብሎ ተመለከታትና እንዲህ አለ፦

«እውነት ተናገርሽ። ባል የለሽም። ነገር ግን አምስት ባሎች ነበሩሽ፤ አሁን አብረሽው የምትኖሪው ሰውም ባልሽ አይደለም። በዚህ ቃል እውነት ተናገርሽ።»

ሴቲቱ እንግዳው ሲናገር ስትሰማ በድንቅ ተሞላች። ይህ ሁሉን የሚያውቅ ሰው እንደ ሆነ ወዲያው አየች። እግዚአብሔር ለዚህ ሰው እንደ ተናገረውና ስለ እርስዋ ይህን እውቀት እንደ ሰጠው ተረዳች። «ጌታ ሆይ» አለች፥ «አንተ የእግዚአብሔር ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ። እንግዲህ ንገረኝ፤ ትክክል የሆኑት ወገኖቻችን ናቸው ወይስ አይሁድ? አባቶቻችን በዚህ ተራራ ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ አይሁድ ግን ሰው ሁሉ ለእግዚአብሔር ሊሰግድ የሚሄድበት ስፍራ ኢየሩሳሌም ነው ይላሉ።»

ይህንም ስትናገር በአጠገቡ ወደ ቆመው ተራራ፥ በራሱ ላይ የሳምራውያን ቤተ መቅደስ ወደ ነበረበት ወደ ገሪዛን ተራራ አመለከተች።

ኢየሱስም «አንቺ ሴት፥ እመኚኝ» ብሎ መለሰ፤ «ሰዎች ከዚህ ተራራና ከኢየሩሳሌም ሌላ በሌሎች ስፍራዎች ለእግዚአብሔር የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። በየስፍራው ያሉ እውነተኞች ሰጋጆች ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚጸልዩበት ጊዜ ቀርቦአል፥ አሁንም ሆኖአል። እግዚአብሔር በሁሉ ስፍራ የሚኖር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።»

ሴቲቱም ኢየሱስን እንዲህ አለችው፦

«ንጉሣችን ሊሆን ከእግዚአብሔር የተላከው ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ። እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይገልጥልናል።»

ኢየሱስም «አሁን የምናገርሽ እኔ እርሱ ክርስቶስ ነኝ!» አላት።

በዚያችም ቅጽበት የኢየሱስ ተከታዮች፥ ዮሐንስና ጴጥሮስ ሌሎቹም፥ የገዙትን ምግብ ይዘው ከመንደሩ ተመለሱ። መምህራቸው ከአንዲት ሴት ጋር ሲነጋገር አግኝተውት ተገረሙ፤ ነገር ግን ምንም አላሉም።

ሴቲቱ ወደ ጕድጓዱ የመጣችው ውኃ ልትቀዳ ነበር፤ ነገር ግን በዚህ ድንቅ እንግዳ ስለ ተማረከች የመጣችበትን ጉዳይ ፈጽሞ ረሳች። እንስራዋንም ትታ ወደ መንደሩ ሮጣ ተመለሰች፤ ያገኘችውንም ሰው ሁሉ እንዲህ አለች፦

«በሕይወቴ ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑ ከእኔ ጋር እዩ! እንጃ ይህ ሰው የምንጠብቀው ክርስቶስ አይደለምን?»

ሴቲቱ ወደ ቤትዋ ከሄደች በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን ካመጡት ምግብ እንዲበላ አጥብቀው ለመኑት። ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በፊት ተርቦ ነበር፤ አሁን ግን ከሴቲቱ ጋር ሲነጋገርና አእምሮዋን ወደ እውነት ሲመራ የራሱን ፍላጎት ረስቶ ነበር።

«እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል አለኝ» አለ።

እርስ በርሳቸውም እየተያዩ እንዲህ ተባባሉ፦

«የሚበላው አንዳች ሰው አምጥቶለት ይሆንን?»

ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፦ «የእኔ መብል ወደ ዓለም የላከኝን የአባቴን ፈቃድ አደርግ ዘንድ፥ እንዳደርገው የሰጠኝንም ሥራ እፈጽም ዘንድ ነው። መከር እስኪመጣ ገና አራት ወር ቀርቶአል ትላላችሁን? እነሆ እላችኋለሁ፥ እርሻውን ተመልከቱ፤ አሁንም ለመከር እንደ ነጣ ታገኙታላችሁ። ታጭዳላችሁ፥ ብዙ መከርም ታገኛላችሁ፤ ለዘላለም ሕይወት ፍሬን ትሰበስባላችሁ።»

ኢየሱስ ማለት የፈለገው ይህች ሴት ከዚህ በፊት ኃጢአተኛ ብትሆንም አሁን ቃሉን ለመስማትና ወደ እግዚአብሔር ለመምጣት እንደ ጓጓች ነው። እንዲሁም ደቀ መዛሙርቱ ብዙም ሳይቆዩ በየስፍራው የሰዎችን ልብ እንደ በሰለ የእህል እርሻ፥ ሊማረክና ሊድን የተዘጋጀ ሆኖ ያገኙታል።

ብዙም ሳይቆይ ሴቲቱ ከብዙ የአገርዋ ሰዎች ጋር ወደ ጕድጓዱ ተመለሰች። ሁሉም ኢየሱስን ወደ መንደራቸው መጥቶ እንዲያስተምራቸው ለመኑት። እርሱም ወደ ሲካር ከተማ ሄዶ በዚያ ሁለት ቀን ተቀመጠ፤ ለሕዝቡም ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና እንዴት ሊገቡበት እንደሚችሉ ተናገረ። በዚያ ስፍራና በአካባቢው የነበሩ ብዙ ሰዎችም ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ከእግዚአብሔር የተላከ ንጉሥ እንደ ሆነ አመኑ፤ እንዲህም አሉ፦

«አሁን እኛ ራሳችን ሰምተነዋል፤ እርሱም በእውነት የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን።»


ቀዳሚ ቀጣይ