የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ጌታ በቤተ መቅደሱ

ምዕራፍ 20 · 5 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ

ጌታ በቤተ መቅደሱ

ከምድሪቱ ክፍሎች ሁሉ የመጡ ሕዝብ ታላቁን የፋሲካ በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም የሚወጡበት የዓመቱ የፀደይ ወራት ደረሰ።

ይህ በዓል የሚከበረው ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ባሪያዎች ከነበሩባት ከግብፅ እንዴት እንዳወጣቸው ለማስታወስ እንደ ነበረ ታስታውሳላችሁ። የፋሲካ በዓል የተባለውም በወጡበት ሌሊት የሞት መልአክ በግብፃውያን ቤቶች ላይ ሞትን ባመጣ ጊዜ የእስራኤላውያንን ቤቶች «ስላለፈ» ነበር። በዚያችም ሌሊት ከግብፅ በችኮላ ስለ ወጡ ሴቶቹ ሊጡ እስኪቦካ ድረስ ሳይጠብቁ ጋገሩ፤ በዚያን ጊዜ የተበላውም እንጀራ ሁሉ «ቂጣ»፥ ማለትም ያለ እርሾ የተጋገረ እንጀራ ነበረ።

እስራኤል ራሱን የሚገዛ ሕዝብ የሆነባትን ያችን ታላቅ ቀን ለማስታወስ በየዓመቱ በፀደይ ሕዝቡ ሁሉ በኢየሩሳሌም ይሰበሰቡ ነበር፤ ለአንድ ሳምንትም ቂጣ፥ ማለትም ያለ እርሾ የተጋገረ እንጀራ ይበሉ ነበር። በዚህ በዓል በየቀኑ በቤተ መቅደስ ታላላቅ አገልግሎቶች ይደረጉ ነበር፤ በአንዲትም ምሽት እስራኤላውያን በግብፅ ምድር የበሉትን የመጨረሻ ማዕድ ለማስታወስ የተጠበሰ በግ ልዩ እራት ሰው ሁሉ ይበላ ነበር፤ ያን ጊዜ ለመሄድ ተዘጋጅተው ባርኔጣቸውን በራሳቸው፥ መጐናጸፊያቸውን በትከሻቸው፥ ጫማቸውንም በእግራቸው አድርገው ነበር።

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወይም ተከታዮቹ የሆኑት ጥቂቶቹ ሰዎች ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ እንዳደረጉት በእግር በዮርዳኖስ ሸለቆ ወደ ኢያሪኮ ወርደው ከዚያም ኮረብቶቹን ወጥተው ወደ ቅድስቲቱ ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ። ኢየሱስ ለብዙ ዓመታት ወደ ፋሲካ በዓል ይመጣ ነበር፤ ነገር ግን እንደ አሁኑ በመንፈስ ኃይል፥ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ከዚህ በፊት መጥቶ አያውቅም ነበር።

በእግዚአብሔር ቤት ዙሪያ የአሕዛብ አደባባይ የሚባል ታላቅ ሜዳ ነበረ፤ አይሁድ ወይም እስራኤላውያን ብቻ ወደ ውስጠኛዎቹ አደባባዮች ይገቡ ስለ ነበር፥ አይሁድ ያልሆኑ የውጭ ሰዎች በዚያ ለመጸለይ ይመጡ ነበር። አይሁድ ግን አሕዛብን ወይም የውጭ ሰዎችን ሁሉ ይንቁ ነበር። የውጭ ሰዎች የሚጸልዩበትን የቤተ መቅደሱን ክፍል እንደ ቅዱስ አይቈጥሩትም ነበር፤ ይህንም የአሕዛብ አደባባይ የገበያ ስፍራ አደረጉት። ኢየሱስም በዚያ በየስፍራው ለሽያጭ የመጡ በጎችንና በሬዎችን፥ ለድሆች በመሠዊያው ላይ መባ እንዲሆኑ የሚሸጡ ርግቦችን የሞሉ ጎጆዎችን፥ የሌሎች አገሮችን ሰዎች ገንዘብ በይሁዳ ገንዘብ የሚለውጡ ሰዎች የተቀመጡባቸውን ገበታዎች አገኘ። የጸሎት ቤት ሊኖረው የሚገባ ጸጥታና ሰላም ምንም አልነበረም፤ ሁሉ ጩኸትና ሁከት ነበረ፤ የበሬዎች ግሳት፥ የሚገዙና የሚሸጡ ሰዎች ድምፅ፥ በገበታዎቹ ላይ የብሩ ቅጭልጭል።

እነዚህ የሚታዩና የሚሰሙ ነገሮች የኢየሱስን ልብ አነሣሡት። በዙሪያው የሚደረገው ያ ሥራ ለእግዚአብሔር አምልኮ በተለየ ስፍራ የማይገባና ክፉ እንደ ሆነ ተሰማው። ከወለሉ ላይ ቍራጭ ገመድ አንሥቶ ጅራፍ እስኪመስል ድረስ ክሮቹን ፈታታ። ከዚያም በገዢዎቹና በሻጮቹ ፊት ቆሞ ንግዳቸውን እንዲያቆሙ አዘዛቸው። እነርሱም ፊቱ እንደ ንጉሥ በኃይል የሚያበራውን ይህን እንግዳ በመገረም ቀና ብለው ተመለከቱት።

ማንም ሳይረዳው ብቻውን እነዚህን ሰዎች ሁሉ ከአደባባዩ አስወጣቸው። በጎቹንና በሬዎቹን እንዲነዱ አዘዛቸው፤ ርግብ ሻጮቹ ጎጆዎቻቸውን እንዲያወጡ አዘዘ፤ የገንዘብ ለዋጮቹን ገበታዎች ገለበጠ፥ ብራቸውንም በወለሉ ላይ አንከባለለ።

«ይህን ሁሉ ከዚህ ውሰዱ» ብሎ ጮኸ። «ይህ የአባቴ ቤት ነው፤ የንግድ ቤት አታድርጉት።»

ጥቂቶቹ ደቀ መዛሙርቱ እንኳ፥ ጴጥሮስ፥ ዮሐንስ፥ እንድርያስና ሌሎቹም፥ መምህራቸው ብቻውን ቍራጭ ገመድ ብቻ ይዞ ይህን የሰው ብዛት ከበሩ ሲያስወጣ እያዩ በመደነቅ ቆሙ፤ ሰዎቹም በመልኩ ንጉሣዊነት ፈርተው ከፊቱ ሸሹ፥ ፈቃዱንም ለአንድ አፍታ እንኳ ለመቃወም አልደፈሩም።

ብዙም ሳይቆይ ግን የቤተ መቅደሱ ካህናትና አለቆች መጡ። እነዚህ ሰዎች በቤተ መቅደሱ አደባባይ እንዲነግዱና የገበያ ስፍራ እንዲያደርጉት መፍቀድ አይገባቸውም ነበር። ነገር ግን ከእነርሱ አንዳንዶቹ በዚያ ስፍራ ከሚገኘው ገንዘብ ድርሻ ይወስዱ ነበር። አንድ ሊቀ ካህናት በቤተ መቅደሱ ለሽያጭ የሚቀመጡትን የርግብና የዋኖስ ጎጆዎች ሁሉ የራሱ አድርጎ ነበር ይባላል። እነዚህ አለቆች ንግዱ በመቆሙና ትርፋቸው በመወሰዱ እጅግ ተቈጡ።

ኢየሱስንም «ወደዚህ መጥተህ ሁከት የምታነሣው በምን መብት ነው?» አሉት። «በዚህ ስፍራ ልትገዛ የምትሞክር አንተ ማን ነህ? የዚህ ስፍራ ጌታ እንደ ሆንህ ምልክት ወይም ማስረጃ አሳየን!»

ኢየሱስም «የኃይሌን ምልክት የማሳያችሁ ጊዜ ይመጣል፤ አሁን ግን አይደለም፤ ያም ምልክት በመጣ ጊዜ አታምኑበትም» አለ።

ከዚያም ወደ ራሱ እንደሚያመለክት በእጆቹ ምልክት አድርጎ እንዲህ ብሎ ጨመረ፦

«ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ።»

አይሁድ በዚህ ቃል እጅግ ደነገጡ፤ በሞሪያ ተራራ ላይ ስላለው ሕንፃ የሚናገር መስሎአቸው ነበርና፤ እግዚአብሔር የሚኖርበትን ቤት ስለ ማፍረስ መናገርም በአሳባቸው አስፈሪ ነገር ነበረ። ኢየሱስ ግን የሚናገረው የእግዚአብሔር መንፈስ በሥጋው ስለሚያድርበት የእግዚአብሔር ልጅ ስለ ራሱ ነበር። ሰዎች ስለሚያታልሉበትና ክፉ ስለሚሠሩበት ከዚያ ሕንፃ እጅግ ይልቅ ኢየሱስ ራሱ የእግዚአብሔር ቤት ነበረ። አለቆቹም እንዲህ አሉ፦

«ይህ ቤተ መቅደስ በአርባ ስድስት ዓመት ተሠርቶአል፤ ገናም አላለቀም፤ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን?»

ከሃምሳ ዓመት ገደማ በፊት ንጉሡ ሄሮድስ በዘመኑ አርጅቶና ፈርሶ የነበረውን ቤተ መቅደስ እንደ ገና መሥራት ጀምሮ ነበር። ጥገናው በጣም በዝግታ ይሠራ ነበር፤ በኢየሱስ ዘመንም ሕንፃው ገና ከመፈጸም እጅግ የራቀ ነበር። ያለቀውም ከሀያ ዓመት በላይ ቈይቶ ነበር።

ኢየሱስ በዚያ ቃል ምን ማለቱ እንደ ነበረ እኛ እናውቃለን፤ ከሦስት ዓመት በኋላ እነዚያው ሰዎች ሥጋው የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነውን የእግዚአብሔርን ልጅ እንደሚያስገድሉት፥ እርሱም ከሞቱ በኋላ በሦስት ቀን ውስጥ ዳግመኛና ለዘላለም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ይሆን ዘንድ ከመቃብሩ እንደሚነሣ ነው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህን ቃል ሰሙ፤ በዚያን ጊዜ ግን ትርጓሜውን አላወቁም ነበር።

ኢየሱስ ለጥቂት ጊዜ በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፤ ለሕዝቡም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ተናገረ። ድውያንን መፈወስን የመሰሉ ድንቅ ሥራዎችንም አደረገ፤ እነዚህን ሥራዎች ያዩ ሰዎችም ቃሉን እግዚአብሔር ወደ ሰዎች ከላከው የመጣ እንደ ሆነ አመኑ። ካህናቱና አለቆቹ ግን ኢየሱስ በክፉ ኑሮአቸው ላይ ስለ ተናገረ ጠሉት፤ ሕዝቡንም ከእርሱ ለማራቅ የቻሉትን ሁሉ አደረጉ።

ነገር ግን ከአለቆቹ መካከል ኢየሱስን የሰሙና ቃሉን ያመኑ ጥቂት ሰዎች ነበሩ። ከእነዚህም አንዱ ኒቆዲሞስ የሚባል ሰው ነበረ። ከኢየሱስ ጋር ተነጋግሮ ስለ ትምህርቱ የበለጠ ለማወቅ ፈለገ። ነገር ግን ሌሎቹ አለቆች ኢየሱስን እጅግ እንደሚቃወሙት ስለሚያውቅ በቀን ከኢየሱስ ጋር መታየትን ፈራ። ስለዚህ በአንዲት ሌሊት ማንም ሳያውቅ በጸጥታ ሄዶ ከኢየሱስ ጋር ተገናኘ። ኒቆዲሞስም እንዲህ ብሎ ጀመረ፦

«መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ኃይል ሊሰጠው ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ድንቅ ነገሮች ሊያደርግ የሚችል የለምና ልትነግረን ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ተላክህ ሁላችን እናውቃለን።»

ኢየሱስም እንዲህ አለው፦

«ለአንተና ለሕዝብህ ሁሉ አንድ ነገር ልንገርህ። ሰው ከእግዚአብሔር ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር በእግዚአብሔር መንግሥት ምንም ድርሻ ሊኖረው አይችልም።»

ኒቆዲሞስም ይህ ምን ማለት እንደ ሆነ አላወቀም፤ «ሰው ካደገ በኋላ እንዴት ዳግመኛ ሊወለድ ይችላል?» አለ።

ኢየሱስም አለ፦ «ሰው ሁሉ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ ቢወድ አዲስ ሰው ሊሆንና የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ሊያድርበት ያስፈልገዋል። ‹ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል› ስላልሁህ አታድንቅ። ልታስተውላቸው የማትችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ነፋሱ ሲነፍስ ስማ! ድምፁን ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንደሚሄድ አታውቅም። ከእግዚአብሔር መንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።»

ኢየሱስ በዚህ ቃል ማለት የፈለገው የክርስቶስ ተከታይ ሊሆን የሚወድ ሁሉ አዲስ ልብ ሊኖረውና አዲስ ሕይወት ሊኖር እንደሚያስፈልገው ነው፤ ይህን አዲስ ልብና አዲስ ሕይወት ሊሰጠው የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው።

በዚያን ጊዜ ኢየሱስ አንድ ታላቅ ቃል ተናገረ። እነሆ፦

«በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።»


ቀዳሚ ቀጣይ