የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ውኃው ወደ ወይን ጠጅ ተለወጠ

ምዕራፍ 19 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ

ውኃው ወደ ወይን ጠጅ ተለወጠ

ኢየሱስ የመጀመሪያ ተከታዮቹ የሆኑትን ሰዎች ካገኘ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከዮርዳኖስ ወንዝ ተነሣ፤ ከእነዚህም ሰዎች ጋር በእግር ወደ ገሊላ ምድር፥ ከናዝሬት በስተ ሰሜን ስድስት ማይል ያህል ርቃ ወደምትገኘው ወደ ቃና መንደር ሄደ። ይህች ከኢየሱስ የመጀመሪያዎቹ አምስት ተከታዮች አንዱ የሆነው ናትናኤል የሚኖርባት ከተማ ነበረች።

በቃና ሰርግ ሊደረግ ነበር፤ ኢየሱስም ከተከታዮቹ ሁሉ ጋር ተጠራ። በዚያች ምድር በሰርግ ጊዜ ሁልጊዜ ግብዣ ይደረግ ነበር፤ የአዲሶቹ ሙሽሮች ወዳጆች ሁሉ ከወዳጆቻቸውም ጋር፥ የመንደሩም ሰው ሁሉ ማለት ይቻላል፥ እንዲመጡ ይጠበቅ ነበር። ግብዣው፥ ጭፈራውና ደስታውም ብዙ ጊዜ አንድ ሳምንት ሙሉ ይቆይ ነበር።

ግብዣው ገና ሳያልቅ፥ በዚያ ዘመን ሰው ሁሉ በብዛት ይጠጣው የነበረው የወይን ጠጅ እንዳለቀ አወቁ፤ ግብዣውን ያዘጋጁትም ለእንግዶቻቸው የሚያቀርቡት የወይን ጠጅ አልነበራቸውም። ይህም እጅግ አስደነገጣቸው፤ በእንዲህ ያለ ጊዜ የወይን ጠጅ በብዛት እንዲቀርብ ይጠበቅ ነበርና፤ በግብዣ ላይ ለታዳሚዎቹ የወይን ጠጅ ማጣትም እንደ ውርደት ይቈጠር ነበር።

የኢየሱስ እናት የቤተሰቡ ወዳጅ ሆና በዚያ ነበረች። ግብዣውን ያዘጋጁትን የምትረዳበትን መንገድ አሰበች፤ ልጅዋንም ከሕዝቡ መካከል ለብቻው ጠርታ በጣም በለሆሳስ እንዲህ አለችው፦

«የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም።»

ጥቂቶች ብቻ የሚያውቁትን፥ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነና ኃይልም ሁሉ በእጁ እንዳለ ታውቅ ነበር። ከጊዜ በኋላ ብዙ ጊዜ ያደረጋቸውን ድውያንን መፈወስን፥ ዕውሮችን ማሳየትንና ደንቆሮዎችን ማሰማትን የመሰሉትን ድንቅ ሥራዎች ገና አንዱንም አላደረገም ነበር፤ ማርያም ግን ቢፈቅድ ሊያደርጋቸው እንደሚችል አመነች። ምናልባት የሚያስፈልገውን የወይን ጠጅ ለመስጠት ኃይሉን ይጠቀም ይሆናል ብላ አሰበች። «የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም» ያለችውም በዚህ ተስፋ ነበር።

ኢየሱስ የሰጣት መልስ በቃሉ የሚያበረታታ አልነበረም።

«አንቺ ሴት፥ በዚህ ነገር ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም» አላት።

እናቱን በእኛ ዘንድ አንድ ወጣት እንደሚለው «እናቴ» ከማለት ፈንታ «አንቺ ሴት» ብሎ መጥራቱ አክብሮት ማጣት አልነበረም። በዚያ ዘመን ልጅ «እናቴ» ሳይሆን «አንቺ ሴት» ማለት ልማድ ነበረ። እርስዋም የተናገረችው በከንቱ እንዳልሆነ የሚያሳያትን ምልክት በፊቱ ላይ አየች። ስለዚህ በአጠገብ ቆመው ወደ ነበሩት አገልጋዮች ዘወር ብላ «የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ» አለቻቸው።

ከአይሁድ ልማዶች አንዱ ለመብል ከመቀመጣቸው በፊት እጃቸውን መታጠብ ነበረ። ይህ መታጠብ እጅን ለማንጻት ብቻ አልነበረም፤ የሃይማኖት ሥርዓት ዓይነት ነበረ፤ አይሁድም በዚህ እጅግ ጥብቅ ነበሩ። ይህን ያህል ብዙ ሕዝብ ለግብዣ በተሰበሰበ ጊዜ ብዙ ውኃ ያስፈልግ ነበር። በአዳራሹም ውስጥ ስድስት ትልልቅ የውኃ ጋኖች ቆመው ነበር፤ እያንዳንዱም ሀያ ጋሎን የሚያህል ይይዝ ነበር። እንግዶቹ ሁሉ በግብዣው ከመቀመጣቸው በፊት እጃቸውን ታጥበው ስለ ነበር ጋኖቹ ባዶ ሊሆኑ ጥቂት ቀርቶአቸው ነበር። ኢየሱስም ወደ እነዚህ ጋኖች አመልክቶ አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፦

«እነዚያን ጋኖች ሁሉ ውኃ ሙሉአቸው።»

እነርሱም ታዘዙለት፥ ጋኖቹንም ሁሉ እስከ አፋቸው ሞሉአቸው። ኢየሱስም ደግሞ እንዲህ አለ፦

«አሁን ከጋኖቹ ቀድታችሁ የቀዳችሁትን ለግብዣው አሳዳሪ ውሰዱለት።»

አገልጋዮቹም እየተደነቁ ከጥቂት ጊዜ በፊት ውኃ በሞሉአቸው በትልልቆቹ ጋኖች ውስጥ ማንቈርቈሪያዎቻቸውን ነከሩ። እያንዳንዱ ማንቈርቈሪያ ቀይ የወይን ጠጅ ሞልቶ ሲወጣ ባዩ ጊዜ እንዴት ተገረሙ! ወደ ግብዣው አሳዳሪም ወሰዱት። እርሱም ቀመሰው፤ እጅግ ምርጥ የወይን ጠጅ እንደ ሆነም አየ። እንዴት እንደ ተሠራ አላወቀም፤ ነገር ግን ከአንድ የወይን ጠጅ ነጋዴ ድንገት የመጣ መሰለው። ያገባውን ወጣትና ግብዣው በክብሩ የተደረገለትን ሙሽራ ጠርቶ እንዲህ አለው፦

«ሰው ሁሉ በግብዣው መጀመሪያ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፤ ሰዎች ለጊዜው ከጠጡ በኋላ ግን መናኛውን ያመጣል፤ አንተ ግን መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል!»

አዲሱ የወይን ጠጅ ከወዴት እንደ መጣ የሚያውቁት አገልጋዮቹ ብቻ ነበሩ። እነርሱ ግን ብዙም ሳይቆዩ ለሌሎች ነገሩ፤ የማርያም ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ድንቅ ሥራ እንዳደረገ ወሬው በታዳሚዎቹ መካከል ተዛመተ። ከኢየሱስ ጋር ወደ ሰርጉ ግብዣ የመጡት አምስቱ ወይም ከዚያ የሚበልጡት ተከታዮቹ ደቀ መዛሙርቱ፥ መምህራቸው ከተራ ሰው የሚበልጥ እንደ ሆነ፥ የእግዚአብሔር ኃይል በእርሱ ላይ እንዳለና የሚናገረውም ሁሉ የእግዚአብሔር ቃል እንደ ሆነ ከበፊቱ ይልቅ አጥብቀው አመኑ።

ውኃን ወደ ወይን ጠጅ እንደ መለወጥ ያለ፥ ማንም ሰው ያለ እግዚአብሔር ኃይል ሊያደርገው የማይችል ሥራ «ተአምር» ይባል ነበር። ያደረገው ሰው ከእግዚአብሔር የተላከ፥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግና የእግዚአብሔርን ቃል የሚናገር እንደ ሆነ ያሳይ ነበር። ይህ ኢየሱስ ያደረገው የመጀመሪያው ተአምር ወይም ድንቅ ሥራ ነበር፤ ከዚህ በኋላ ግን ስለ ብዙ ተአምራት እናነባለን።

ኢየሱስ ከሰርጉ ግብዣ ተነሥቶ የገሊላን ተራሮች ወርዶ በገሊላ ባሕር ሰሜን ምዕራብ ዳርቻ ወደምትገኘው ወደ ቅፍርናሆም ከተማ ሄደ። በዚህ ወደ ቅፍርናሆም ባደረገው ጕብኝት እናቱ፥ አንዳንድ ታናናሽ ወንድሞቹና ተከታዮቹ ከእርሱ ጋር ነበሩ።


ቀዳሚ ቀጣይ