የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
የኢየሱስ የመጀመሪያዎቹ ተከታዮች

ምዕራፍ 18 · 4 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ

የኢየሱስ የመጀመሪያዎቹ ተከታዮች

ኢየሱስ በበረሃ ከቈየባቸው አርባ ቀናት በኋላ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የመማረኩን ሥራ ጀመረ። ዕቅዱም በመጀመሪያ ከሰዎች ጋር አንድ በአንድ መነጋገር ነበረ፤ ይህንም ያደረገው እንደ መምህር ቃሉን የሚያምኑና እንደ መሪያቸው የሚከተሉትን ጥቂት ሰዎች በዙሪያው እስኪሰበስብ ድረስ ነው። የመጀመሪያዎቹ ተከታዮቹ ለመሆን ይበልጥ የተዘጋጁት ቀደም ብሎ በመጥምቁ ዮሐንስ የተማሩት አንዳንዶቹ ነበሩ። ስለዚህ ኢየሱስ ከምድረ በዳው እንደ ገና ወደ ሰሜን ተመለሰ፤ ከሁለት ወር ገደማ በፊት ወደ ተጠመቀበት ወደ ቤተ ራባ በሚወስደው በብዙ ሰው በተረገጠው መንገድ ሽቅብ ሄደ።

በቤተ ራባ ከመጥምቁ ዮሐንስ ጋር የዮሐንስ «ደቀ መዛሙርት» የሚባሉ የወጣቶች ቡድን ነበሩ፤ ይኸውም ሕዝቡ ወደ ቤታቸው ከሄዱ በኋላ ትምህርቱን ለመማር ከእርሱ ጋር የሚቈዩ ሰዎች ማለት ነው። ከእነዚህም አንዳንዶቹ ዮሐንስን ለመስማት መረባቸውንና ሥራቸውን ትተው የመጡ የገሊላ ባሕር ዓሣ አጥማጆች ነበሩ።

ዮሐንስ ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹን በዙሪያው አድርጎ ቆሞ ሳለ አንድ እንግዳ ሰው ከሩቅ በመንገዱ ሽቅብ ሲሄድ ታየ። እነዚህ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ይህ ሰው ማን እንደ ሆነ አላወቁም ነበር፤ ዮሐንስ ግን አስታወሰው፤ በተጠመቀበት ቅጽበት በፊቱ ላይ ከሰማይ ያበራው ብርሃንና ከሰማያት የመጣው ድምፅ ኢየሱስን በልቡ አትመውበት ነበርና። ወደ ኢየሱስም እያመለከተ እንዲህ አለ፦

«እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ! ያውና! ‹ከእኔ በኋላ ከእኔ የሚበልጥ ሰው ይመጣል፤ እርሱም በውኃ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃል› ብዬ የተናገርሁለት ይህ ነው። መንፈስ እንደ ርግብ በዚህ ሰው ላይ ሲወርድና በእርሱ ላይ ሲያርፍ አየሁ። ይህም ሰው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ለሁላችሁ እነግራችኋለሁ።»

ዮሐንስ ይህን ቃል ሲናገር ሳለ ኢየሱስ ከዓይናቸው ተሰወረ፤ ዮሐንስና ደቀ መዛሙርቱም በዚያ ቀን ዳግመኛ አላዩትም። በማግሥቱ ግን ዮሐንስ ከተከታዮቹ ከሁለቱ ጋር ቆሞ ሳለ ኢየሱስ እንደ ገና በዚያ አለፈ፤ ዮሐንስም ዳግመኛ ተመልክቶት ለወጣቶቹ እንዲህ አለ፦

«እነሆ የእግዚአብሔር በግ!»

ሁለቱ ወጣቶች ይህን ቃል በሰሙ ጊዜ ወዲያው ዮሐንስን ትተው ወደ ኢየሱስ ሄዱ። በቀረቡም ጊዜ ኢየሱስ ዞር ብሎ እንዲህ አላቸው፦

«ለምን ትከተሉኛላችሁ? የምትፈልጉት ምንድር ነው?»

እነርሱም፦ «መምህር ሆይ፥ እንድናይህና ከአንተ ጋር እንድንነጋገር የምትኖርበትን ልናውቅ እንወዳለን» አሉት።

ኢየሱስም፦ «መጥታችሁ እዩ» አላቸው፤ በእንግድነት ወደሚኖርበትም ቤት ወሰዳቸው። በዚያ ዘመን አይሁድ በጕዞ ላይ ሆነው ለጥቂት ቀናት ማረፊያ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ወደ ቤታቸው በደስታ ይቀበሉ ነበር። እነዚያ ሁለት ሰዎች ከኢየሱስ ጋር በቤቱ ውስጥ የተቀመጡት ከጠዋቱ አራት ሰዓት ገደማ ነበረ፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ሲነግራቸውም እያደመጡ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ ቀኑን ሙሉ ከእርሱ ጋር ቈዩ። ቃሉም በቀጥታ ወደ ልባቸው ገባ፤ በዚያም ቀን እነዚያ ሁለት ወጣቶች ኢየሱስን መሲሕ-ክርስቶስ ብለው አመኑበት፤ ይኸውም በብሉይ ኪዳን ነቢያት ከጥንት ተስፋ የተሰጠበትና የእስራኤል ሕዝብ ለረጅም ዘመን ሲጠባበቁት የነበረው የእስራኤል ንጉሥ ማለት ነው። መሲሕና ክርስቶስ የሚሉት ሁለቱ ቃላት አንድ ናቸው። አንዱ በዕብራይስጥ ቋንቋ፥ ሌላው በግሪክ ቋንቋ ነው፤ ሁለቱም «የተቀባው» ወይም «የእስራኤል ንጉሥ» ማለት ናቸው።

እንዲህም ኢየሱስ በማስተማሩ በመጀመሪያው ቀን ሁለት ተከታዮችን አገኘ። ሁለቱም ብዙ ማይል ከማይርቀው ከገሊላ ባሕር የመጡ ዓሣ አጥማጆች ነበሩ። አንዱ ዮሐንስ የሚባል ሰው ነበረ፤ እርሱም በኋላ «ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር» ተባለ፤ ከተከታዮቹ ሁሉ ይልቅ ለኢየሱስ የቀረበው ዮሐንስ ነበረና። ከብዙ ዘመን በኋላ ዮሐንስ በመጽሐፍ ቅዱስ ካሉት እጅግ ውድ መጻሕፍት አንዱን፥ «የዮሐንስ ወንጌልን»፥ ጻፈ፤ ይህም መጽሐፍ ከሌላው መጽሐፍ ሁሉ ይበልጥ የኢየሱስን ውስጣዊ ልብ ያሳየናል።

ሌላው ወጣት እንድርያስ ይባል ነበር። እርሱም ወዲያው የመጥምቁ ዮሐንስ ተከታይ የነበረውን ታላቅ ወንድሙን ስምዖንን አሰበ። ስምዖንንም ፈልጎ አግኝቶ እንዲህ አለው፦

«ነቢያት የተናገሩለትን መሲሕን አግኝተናል!»

የተናገረው የሕዝቡ ቋንቋ በነበረው በዕብራይስጥ ነበረ። አዲስ ኪዳን መጀመሪያ በተጻፈበት በግሪክ ቋንቋ ተናግሮ ቢሆን ኖሮ «ክርስቶስን አግኝተናል» ይል ነበር፤ ይኸውም ንጉሡን ማለት ነው። እንድርያስም ወንድሙን ስምዖንን ወደ ኢየሱስ አመጣው፤ ኢየሱስም እንዳየው፥ እንድርያስ ስሙን ከመናገሩ በፊት፥ እንዲህ አለው፦

«ስምህ ስምዖን ነው፤ አንተም የዮና ልጅ ነህ። እኔ ግን አዲስ ስም እሰጥሃለሁ። ወደ ፊት ‹ዓለት› ትባላለህ።»

በዕብራይስጥ ቋንቋ «ዓለት» ማለት «ኬፋ» ወይም «ኬፋስ» ነው። በግሪክ ደግሞ «ጴጥሮስ» ነው። ከዚያ በኋላ ስምዖን አንዳንድ ጊዜ ኬፋ፥ ብዙውን ጊዜ ግን ጴጥሮስ ተብሎ ተጠራ። እርሱም በኢየሱስ ተከታዮች መካከል መሪ ሆነ፤ ከብዙ ዓመታት በኋላም ከአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አንዱን፥ ምናልባትም ሁለቱን፥ ጻፈ።

ኢየሱስ አሁን ጌታቸውና ንጉሣቸው አድርገው የሚያምኑበት ሦስት ተከታዮች ነበሩት፤ በማግሥቱም አራተኛውን አገኘ። ይህ ሰው ፊልጶስ ይባል ነበር፤ በገሊላ ባሕር በሰሜን ዳርቻ ካለችው ቤተ ሳይዳ ከምትባል ስፍራ የመጣ ነበረ። ኢየሱስም ፊልጶስን እንዲህ አለው፦

«ተከተለኝ።»

እርሱም ደግሞ ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ወይም ተከታዮች ትንሽ ማኅበር ጋር ተባበረ። ፊልጶስም ወዲያው የኢየሱስ ተከታይ ለመሆን ከእርሱ ጋር በመተባበር ደስ ይለዋል ብሎ ያሰበውን እጅግ ደግና ንጹሕ የሆነ አንድ ወዳጁን አሰበ። ሊፈልገውም ሄደ፤ ከበለስ ዛፍ በታች ቆሞም አገኘው። እንዲህም አለው፦

«ሙሴ በሕግ የጻፈለትን፥ ነቢያትም የተናገሩለትን ክርስቶስን አግኝተነዋል። ስሙ ኢየሱስ ይባላል፤ የዮሴፍ ልጅ ነው፤ የመጣውም ከናዝሬት ከተማ ነው።»

የናትናኤል የትውልድ ከተማ ከናዝሬት ጥቂት ማይል ብቻ የምትርቀው ቃና ነበረች። ናትናኤል ናዝሬትን እንደ ተናቀች ስፍራ ይቈጥራት ነበር። ታላቁ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ ከእንደዚህ ያለች መንደር ይወጣል ብሎ ማመን አልቻለም። ከታላቅ ከተማ፥ ከኢየሩሳሌም፥ ወይም ከዳዊት ከተማ ከቤተ ልሔም ይመጣል ብሎ ይጠብቅ ነበር። ኢየሱስ በቤተ ልሔም እንደ ተወለደ አላወቀም፤ እንዲያውም ስለ ኢየሱስ ፈጽሞ ሰምቶ አያውቅም ነበር፤ እንዲህም አለ፦

«ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላል ትለኛለህን?»

ፊልጶስ በኢየሱስ ያመነበትን ምክንያት ለናትናኤል ሊያስረዳው የሚችል ብልህ አልነበረም። ጥልቅ የሆነውን አንዳንድ ሐሳባችንን በቃል መግለጽ አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ለናትናኤል እጅግ ጥበበኛ መልስ ሰጠው።

ፊልጶስም፦ «እንግዲያስ መጥተህ ኢየሱስን ራስህ እይ» አለው።

ኢየሱስ ናትናኤልን ከዚያ በፊት አይቶት አያውቅም ነበር፤ ሲቀርብ ግን በአጠገቡ ቆመው ለነበሩት እንዲህ አለ፦

«እዩ! እውነተኛ እስራኤላዊ፥ የእግዚአብሔር ሰው፥ በልቡ ክፋት የሌለበት ሰው ይኸው ይመጣል።»

ናትናኤልም በዚህ በኢየሱስ ቃል እጅግ ተደነቀ። እንዲህም አለ፦

«እንዴት ታውቀኛለህ?»

ኢየሱስም፦ «ፊልጶስ ሳይነግርህ፥ ከበለስ ዛፍ በታች ቆመህ ሳለህ፥ አየሁህ» ብሎ መለሰለት።

ናትናኤልም፦ «መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ» አለው።

ኢየሱስም እንዲህ አለው፦

«‹ከበለስ ዛፍ በታች አየሁህ› ስላልሁህ ታምናለህን? ከዚህ የሚበልጥ ነገር ገና ታያለህ። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ።»

ኢየሱስ «የሰው ልጅ» ሲል ራሱን ማለቱ ነበረ። እነዚህን ቃላት የተጠቀመው «የእግዚአብሔር ልጅ» ሆኖ ሳለ በሰዎች መካከል ያለ ሰውም እንደ ሆነ ለማሳየት ነው።

ኢየሱስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ለጥቂት ሰዎች ሲሰብክ ወይም ሲነግራቸው ቈይቶ ነበር፤ ቀድሞውንም አምስት ተከታዮችን አግኝቶ ነበር። ሌሎችም ኖረው ይሆናል፤ ብዙም ሳይቈይ የዮሐንስ ወንድም ያዕቆብ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል እናገኘዋለንና።


ቀዳሚ ቀጣይ