ምዕራፍ 17 · 5 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ
በምድረ በዳ ብቻውን
ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ በእርሱ ላይ ስለ መጣው ስለዚያ ታላቅ ለውጥ ለማሰብ ለጥቂት ጊዜ ብቻውን መሆን እንዳለበት ተሰማው። ትናንት በናዝሬት አናጢ ነበረ፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ልጅና የእስራኤል ንጉሥ እንደ ሆነ አወቀ! እንዲህ ያለ ድንገተኛና ታላቅ ለውጥ ሊያስብና ሊጸልይ፥ ስለ ራሱና ስለሚሠራው ሥራ የአባቱንም ፈቃድ ሊረዳ ወደሚችልበት ጸጥ ወዳለና ሰው ወደሌለበት ስፍራ መሄድ እንዳለበት እንዲሰማው አደረገው።
ኢየሱስ ከዮሐንስ ጋር አንዲት ቃል እንኳ ሳይነጋገር በወንዙ ዳር ከነበረው ሕዝብ መካከል ቀስ ብሎ ወጣ። ወደ ደቡብም አቀና፤ ወደ ኢየሩሳሌም በዓላት ሲሄድ ብዙ ጊዜ በተጓዘበት በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው በታወቀው መንገድ አልሄደም፤ ይልቁንም ከሰዎች ጋር ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ስለ ፈለገ ሰዎችን በማያገኝበት በተራራው ጎን ባሉት መንገዶች መረጠ።
በመጨረሻም በኢያሪኮና በኢየሩሳሌም መካከል ወዳለ እጅግ ብቸኛ ስፍራ ደረሰ፤ ማንም ሰው ወደማይኖርበት፥ የበረሃ ዓረቦች እንኳ እምብዛም ወደማይንከራተቱበት ስፍራ ነበር። በዚያ ባድማ ምድር የሚኖሩት ሕያዋን ፍጥረታት የዱር አራዊት፥ ተኵላዎችና ቀበሮዎች ብቻ ነበሩ፤ ጩኸታቸውም በሌሊት ይሰማ ነበር። በዚያም በዓለቶች በተከበበ በአንድ ኮረብታ ራስ ላይ ሊያርፍ ተቀመጠ። አእምሮው በታላቅ መነሣሣት ይዞር፥ ልቡም በብርቱ ስሜት ይመታ ስለ ነበረ የሚበላው ምግብ ይዞ መሄድን ፈጽሞ አላሰበም ነበር። ብዙ ቀንና ሌሊት ብቻውን እየጸለየና ከእግዚአብሔር ጋር እየተነጋገረ፥ አንድ ጊዜ እንኳ ስለ መብላት ሳያስብ ቈየ። የረሀብ ስሜት በእርሱ ላይ ከመምጣቱ በፊት ከአንድ ወር በላይ፥ አርባ ቀን እንኳ፥ አለፈ።
ከዚያም ድንገት በሰውነቱ ውስጥ የሚቦረቡር ብርቱ ሕመም ተሰማው፤ በረሀብ እየደከመ እንደ ሆነም አወቀ። አንዳች ካልበላ እግዚአብሔር የጠራውን ታላቅ ሥራ ሳይፈጽም በዚያ በበረሃ እንደሚሞት ተሰማው። በዙሪያውም የምድረ በዳው ሻካራ ድንጋዮች ነበሩ፤ እነርሱንም ሲመለከት ይህ ሐሳብ ወደ አእምሮው መጣ፦
«በዚህ በረሃ በረሀብ መሞት አያስፈልገኝም። ከሰማይ የመጣው ድምፅ እንደ ተናገረ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንሁ አንዲት ቃል ብቻ መናገር ይበቃኛል፤ እነዚህም ድንጋዮች እንጀራ ይሆናሉ!»
ኢየሱስም እንደ ገና አሰበና በልቡ እንዲህ አለ፦ «አዎን፥ እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ፤ እነዚህን ድንጋዮች የምበላው እንጀራ የማድረግ ኃይልም አለኝ። ነገር ግን ይህ ኃይል የተሰጠኝ ከሰማያዊ አባቴ ነው፤ የተሰጠኝም ለራሴ እንድጠቀምበት ሳይሆን የተቸገሩትን ሌሎችን እንድረዳበት ነው። ለራሴ ከድንጋይ እንጀራ እንዳደርግ የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለም።»
ከዚያም ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ቃል ወደ ኢየሱስ አእምሮ መጣ፤ እንዲህም አለ፦ «ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል።»
ኢየሱስ በበረሃ ብቻውን ያለ ይመስል ነበር፤ ነገር ግን ሳይታይ የሚመለከተው አንድ ነበረ። እርሱም ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅና የዓለም መድኃኒት መሆኑን አውቆ የሚጠላው ክፉ መንፈስ ሰይጣን ነበረ። ድንጋዮችን እንጀራ የማድረግንና እግዚአብሔር የሰጠውን ኃይል ለራሱ ብቻ የመጠቀምን ሐሳብ በኢየሱስ አእምሮ ያስገባው እርሱ ነበረ። ኢየሱስ ግን የሰይጣንን ዓላማ ፈጥኖ አይቶ ከእርሱ ዞር አለ።
ከዚያም ሌላ ሐሳብ ወደ ኢየሱስ አእምሮ መጣ። በልቡም እንዲህ አለ፦ «ሕዝቡ እጅግ ብዙ ዘመን ሲጠባበቁት የነበረው መሲሕ፥ የእስራኤል ንጉሥ፥ እኔ እንደ ሆንሁ አውቃለሁ። ነገር ግን ሕዝቡ እኔ ንጉሣቸው መሆኔን እንዲያውቁ እንዴት አደርጋለሁ? በእኔ እንዲያምኑ ምን ላድርግ?»
በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ሥራውን የሚጀምርበትንና የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ለሕዝቡ የሚያሳውቅበትን የተሻለ ዕቅድ ሊያስብ ሲሞክር ሳለ፥ ክፉው መንፈስ ሰይጣን ሌላ ቃል አዘጋጅቶ ነበር። እንዲህም አለ፦ «ይኸውልህ መልካም ዕቅድ። ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት በአንድ የበዓል ጊዜ በኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መቅደስ ሂድ፤ በሕዝቡም ሁሉ ፊት ከግንቦቹ ከአንዱ ላይ ዝለል። ኃይል ሁሉ የአንተ ነውና በምድር ላይ አትወድቅም፤ በአየር ላይ እየተንሳፈፍህ ትወርዳለህ እንጂ። ሕዝቡም ባዩህ ጊዜ በፊትህ በግንባራቸው ይወድቃሉ፤ ለረጅም ዘመን ተስፋ የተሰጠበት ንጉሥ እንደ ሆንህም ያምኑብሃል። አንተ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ፥ እግዚአብሔርም እንደሚጠብቅህ ታውቃለህ። ከመዝሙራቱ በአንዱ ‹መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል› ተብሎ እንደ ተጻፈ አታስታውስምን?»
ኢየሱስ ይህ የሰይጣን ዕቅድ እንጂ የእግዚአብሔር ዕቅድ እንዳልሆነ ወዲያው አየ። ይህ በእግዚአብሔር መታመን አይሆንም፤ ኢየሱስ ራሱ ምን ማድረግ እንደሚችል ለማሳየት የእግዚአብሔርን ኃይልና ጥበቃ መፈታተን ይሆናል። ይህን የሞኝነት ሥራ ወይም እንዲህ ያለውን ማንኛውንም ነገር በገዛ ፈቃዱ አያደርግም። እግዚአብሔር የሚያደርገውን እስኪነግረው ድረስ ይጠብቃል፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን እስኪያረጋግጥም አንዳች አያደርግም። ደግሞም ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ቃል ወደ አእምሮው መጣ፤ እንዲህም አለ፦
«‹ጌታን አምላክህን አትፈታተነው› ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል።»
ይህ ማለት በእግዚአብሔር መታመናችንን ለታይታ ማድረግ ወይም ባልተፈለገ ሥራ እግዚአብሔር እኛን ለመርዳት ምን እንደሚችል ለሌሎች ማሳየት ፈጽሞ አይገባንም ማለት ነው። እግዚአብሔር ከአደጋ እንዴት እንደሚያወጣን ለማሳየት ብለን ራሳችንን ወደ አደጋ መጣል የለብንም።
ኢየሱስ አሁን ሁለት ታላላቅ ጥያቄዎችን ፈትቶ ነበር። ተአምር የማድረግ ኃይሉን ለራሱ፥ የገዛ ሕይወቱን ለማዳን እንኳ፥ አይጠቀምበትም፤ ለታይታ ብቻ ብሎም አንዳች አያደርግም፤ በነገር ሁሉ የአባቱን ፈቃድ ብቻ ይፈጽማል። የሚቀረው አንድ ጥያቄ ነበረ፤ እርሱ የእስራኤል ንጉሥ ሊሆን ነበረ፤ ነገር ግን መንግሥቱ ምን ዓይነት መንግሥት ትሆናለች?
በይሁዳና በገሊላ ብቻ ሳይሆን በአገሮች ሁሉ ያሉት የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ንጉሠ ነገሥቱ ጢባርዮስ በሮም እንደሚገዛ በኢየሩሳሌም የሚገዛ ንጉሥ እንደሚጠብቁ በሚገባ ያውቅ ነበር። ሠራዊት የሚሰበስብ፥ ሮማውያንን የሚያባርር፥ ጦርነት የሚዋጋ፥ ድል የሚያደርግና መንግሥቱን በዓለም ላይ ገዢ ኃይል የሚያደርግ ንጉሥ ተስፋ ያደርጉ ነበር። ሮማውያን ከእግራቸው በታች የሚሆኑበትን፥ ሌሎቹም አገሮች ሁሉ ግብር የሚከፍሉበትንና በኢየሩሳሌም ያለውን ንጉሣቸውን የሚያገለግሉበትን ዘመን ይጠባበቁ ነበር።
ኢየሱስ ይህን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ክፉው መንፈስ ሰይጣንም ሳይታይ በአጠገቡ ቆሞ እንዲህ አለው፦
«ምክሬን ተቀበል፤ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ እሰጥሃለሁ፤ የእኔ ናቸውና ለምወደው ልሰጣቸው እችላለሁ።»
ኢየሱስ ሕዝቡ የሚፈልጉት ሰይጣን የሚፈልገውን እንደ ሆነ አወቀ፤ ይኸውም በጦርነትና በደም፥ ለእርሱ የማይገዙትንም ሁሉ በመግደል የሚቆም ዓለማዊና ክፉ መንግሥት ነው። ያ ግን የእግዚአብሔር መንግሥት አይሆንም። በቀድሞ ዘመን ብዙ መንግሥታትና ሕዝቦች እንደ ነበሩ የሰይጣን መንግሥት ይሆናል። ሰይጣን የፈለገውን ማድረግ ለሰይጣን ሰግዶ እንደ ጌታውና እንደ አለቃው ከማምለክ ጋር አንድ ይሆናል። ይህን አያደርግም፤ ለፈታኙም የተናገረው የመጨረሻ ቃል ይህ ነበረ፦
«ከእኔ ሂድ፥ ሰይጣን! ‹ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ› ተብሎ ተጽፎአልና!»
ኢየሱስ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ይህን ታላቅ ምርጫ በመምረጡ የገዛ ሕዝቡን አይሁድን ደስ እንደማያሰኝ በግልጽ አየ። አለቆቹ፥ ካህናቱና ጻፎቹ፥ በዚያ ዘመን የነበሩት መሪዎች፥ እንደሚቃወሙት፥ ሊከተሉትም እንደማይወዱ፥ ሕዝቡን በእርሱ ላይ ሊያነሣሡና ሊገድሉትም እንደሚሞክሩ አወቀ። ኢየሱስ ግን የሰይጣንን ፈቃድ እያደረገ ከመኖር ይልቅ እግዚአብሔርን እያገለገለ ለመሞት ዝግጁ ነበረ።
ክፉው መንፈስ ሰይጣንም ኢየሱስን ፈቃዱን እንዲያደርግ ሊያባብለው እንዳልቻለ ባየ ጊዜ ተወው። ከዚያም በኋላ በአባቱ የተላኩ የሰማይ መላእክት በበረሃ ወደ እርሱ መጥተው የሚያስፈልገውን ምግብ ሁሉ ሰጡት።
የዚህን ከሰይጣን ጋር የነበረውን ግጥሚያና የኢየሱስን ድል ታሪክ የሚናገሩት የማቴዎስና የሉቃስ ወንጌሎች የሆነበትን ትክክለኛ ስፍራ አይናገሩም። የምናውቀው በ«በረሃ» ወይም በ«ምድረ በዳ» እንደ ሆነ ብቻ ነው። ነገር ግን በኢያሪኮ አጠገብ አንዳንዶች ኢየሱስ በእነዚያ አርባ ቀናት የቈየበት ነው ብለው የሚያስቡት ተራራ አለ። ስለዚህም ይህ ተራራ «አርባ ቀን» የሚል ትርጓሜ ባለው ስም ቋራንታንያ ተራራ (ገዳመ ቆሮንቶስ) ተብሎ ይጠራል።