የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
አናጢው መሥሪያ ቤቱን ተወ

ምዕራፍ 16 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ

አናጢው መሥሪያ ቤቱን ተወ

ከጥቂት ወራት በኋላ መጥምቁ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ሽቅብ መጥቶ ከገሊላ ባሕር በስተ ደቡብ 12 ማይል ያህል ርቆ በሚገኝ ስፍራ እየሰበከ ነው የሚል ወሬ ወደ ናዝሬት ደረሰ። ዮሐንስ ይሰብክበት የነበረው ስፍራ ሁለት ስሞች ነበሩት። በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ሌላ ቢታንያ ስለ ነበረች «በዮርዳኖስ ማዶ ያለችው ቢታንያ» ተብሎ ይጠራ ነበር፤ ደግሞም «ቤተ ራባ» ይባል ነበር፤ ትርጓሜውም «ሰው ወንዙን በእግሩ የሚሻገርበት ስፍራ» ማለት ነው፤ በዚያ የዮርዳኖስ ወንዝ ጥልቀት ስላልነበረው ሰዎች በውኃው ውስጥ እየሄዱ ይሻገሩት ነበር። ዮሐንስ ይህን ስፍራ የመረጠው በወንዙ አጠገብ ያለው ተዳፋት ዳርቻ ብዙ ሕዝብ ተቀምጦ ስብከቱን እንዲሰማ የተመቸ ስለ ነበረ፥ ጥልቀት የሌለውም ውኃ ሕዝቡን ለማጥመቅ በአጠገቡ ስለ ነበረ ነው።

ቤተ ራባ ወይም ቢታንያ ከናዝሬት 25 ማይል ያህል ይርቅ ነበር፤ ከኮረብታውም ማዶ ባለው ሜዳ ላይ ወደዚያ ስፍራ ወደ ወንዙ የሚወርድ መንገድ ነበረ፤ ሰዎች ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳሉት ወደ ዲካፖሊስና ወደ ፔሪያ ምድር ሲሄዱ በዚያ ወንዙን ይሻገሩ ነበር። ሕዝቡ ሁሉ ማለት ይቻላል የዮሐንስን ስብከት ሰምተው ነበር፤ አብዛኞቹም ከክፉ ተመልሰው መልካም ሊያደርጉና በቅርቡ የሚመጣውን ንጉሥ ሊጠባበቁ ቃል እንደ ገቡ ምልክት እንዲሆን በእርሱ ተጠምቀው ነበር።

ኢየሱስም እግዚአብሔር የጠራውን ሥራ የሚጀምርበት ጊዜ አሁን እንደ ደረሰ ተሰማው። ሐሳቡን ለማንም፥ ለእናቱ እንኳ፥ አልነገረም ነበር፤ አንድ ቀን ግን የአናጢነት መሥሪያ ቤቱን አሁን ጎልማሶች ለሆኑትና እናታቸውን መጦር ለሚችሉት ታናናሽ ወንድሞቹ ትቶ ሄደ። በሸለቆዎቹ ወርዶ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ደረሰ፤ ውኃውንም በእግሩ ተሻገረ፤ በቤተ ራባም ከአገሩ ሁሉ በመጡ ብዙ ሕዝብ ፊት መጥምቁን ዮሐንስን ለመጀመሪያ ጊዜ አየው። ማርያም ስለ መልአኩ በመሠዊያው አጠገብ መታየት፥ ስለ ዮሐንስ መወለድና ስለ ልጅነቱ ታሪኩን ሁሉ ለልጅዋ ነግራው እንደ ነበረ አያጠራጥርም፤ ይሁን እንጂ በእነዚያ ዓመታት ሁሉ ኢየሱስና ዮሐንስ ተገናኝተው አያውቁም ነበር።

ኢየሱስ የዮሐንስን ቃል ሰማ፤ ከዚያም ከሌሎቹ ጋር ሊጠመቅ ወደ ፊት ቀረበ። ዮሐንስም ወደ እርሱ የሚቀርበውን ይህን እንግዳ ወጣት ተመለከተ፤ ሲመለከተውም በውስጡ ያለው ድምፅ እንዲህ አለው፦

«ከጥንት ጀምሮ ተስፋ የተሰጠበት ንጉሥ መጥቶአል! እርሱ ይህ ሰው ነው!»

ዮሐንስ ይህ ሰው የሚተወው ኃጢአት እንደሌለበትና የእግዚአብሔርንም ፈቃድ አስቀድሞ ፍጹም አድርጎ እንደሚፈጽም ስላወቀ ጥምቀት የማያስፈልገው ሰው በፊቱ እንዳለ ተሰማው። ሊያጠምቀውም አልወደደም፤ እንዲህም አለ፦

«በእግዚአብሔር ፊት እንደ አንተ ያለውን እጅግ ቸርና ታላቅ ሰው እኔ ላጠምቅ አይገባኝም። እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል፤ አንተስ ወደ እኔ ትመጣለህን?»

ኢየሱስ ግን እንዲህ ብሎ መለሰለት፦

«እንዲህ ቢሆን ይሻላል። ለሌሎች ሰዎች የሚገባው ሁሉ ለእኔም ይገባኛል። ይህን ለእግዚአብሔር እንደሚገባኝ ግዴታ ላድርገው።»

ዮሐንስም ለኢየሱስ ፈቃድ እሺ ብሎ አጠመቀው። ኢየሱስም ከውኃው በወጣ ጊዜ አንድ ድንቅ ነገር ሆነ። ሲጸልይ ሳለ ከሰማይ ብርሃን ብልጭ አለ፤ እንደ ነጭና አንጸባራቂ ርግብ በእርሱ ላይ ወርዶ በኢየሱስ ራስ ላይ ያረፈ መሰለ፤ የነጐድጓድ ድምፅ የሚመስልም ድምፅ ተሰማ። በዳርቻው ላይ ቆመው የነበሩት አንዳች ቃል እንደ ተነገረ ተሰማቸው፤ ሊያስተውሉት ግን አልቻሉም። የሰማውና ያስተዋለው ዮሐንስ ብቻ ነበረ። ይህ የእግዚአብሔር ድምፅ ነበረ፤ ዮሐንስም በኋላ የተነገሩት ቃሎች እነዚህ እንደ ነበሩ ለሕዝቡ ነገራቸው፦

«በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው።»

በዚያን ቅጽበት ታላቅ ኃይል በኢየሱስ ላይ መጣ። የእግዚአብሔር መንፈስ ሁልጊዜ ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ጌታም ለአንድ ታላቅ ሥራ እያዘጋጀው እንደ ሆነ እንዲሰማው አድርጎት ነበር። ነገር ግን የሰማዩ ብርሃን በእርሱ ላይ በወደቀበትና የእግዚአብሔር ድምፅ በተሰማበት በዚያ ጊዜ ኢየሱስ ከእርሱ በፊት ማንም ሰው፥ ከነቢያት ታላቁ እንኳ፥ ባልተሞላው መጠን በእግዚአብሔር መንፈስ ተሞላ። አሁን የእግዚአብሔርን ድምፅ የሚሰማና የእግዚአብሔርን ቃል የሚናገር ነቢይ ብቻ እንዳልሆነ አወቀ፤ ከነቢይ የሚበልጥ፥ እርሱ ራሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ። እግዚአብሔር በምድር ላይ ስለሚያቆመው መንግሥቱ ያለውን ዕቅድ እንደ መብረቅ ብልጭታ በአንድ ጊዜ አየ፤ ይህም መንግሥት የአይሁድ ሕዝብ ከሚጠብቁት እጅግ የተለየ መሆኑን አስተዋለ። እስከዚያች ሰዓት ድረስ የናዝሬት እንጨት ጠራቢ የነበረው እርሱ ከዚያች ሰዓት ጀምሮ የሰማያዊው መንግሥት አለቃ እንደሚሆን አወቀ። ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር ሊመራና ሰዎች እንዴት መኖር እንደሚገባቸው በገዛ ሕይወቱ ሊያሳይ ነበረ። እግዚአብሔርን ወደ ሰዎች ሊያወርድ፥ ሰዎችንም ወደ እግዚአብሔር ሊያመጣ ነበረ። በዮርዳኖስ ዳር የእግዚአብሔር ብርሃን በፊቱ ላይ አብርቶ በቆመ ጊዜ ይህ ሁሉና እኛ ልናስተውለው የማንችለው ከዚህ የሚበልጥ ነገር ወደ ኢየሱስ ነፍስ መጣ።


ቀዳሚ ቀጣይ