የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
በወንዙ አጠገብ የተሰማው ድምፅ

ምዕራፍ 15 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ

በወንዙ አጠገብ የተሰማው ድምፅ

ኢየሱስ ገና በናዝሬት እየኖረ በአናጢነት ቤቱ ሲሠራ ሳለ፥ ከኢየሩሳሌም ብዙ በማይርቀው በይሁዳ ምድረ በዳ አንድ እንግዳ ሰው እየሰበከ እንደ ሆነና ሕዝቡ ሁሉ እርሱን ለመስማት ከከተሞችና ከመንደሮች እየወጡ እንደ ሆነ የሚገልጽ ወሬ በድንገት በምድሪቱ ሁሉ ተሰማ።

ይህ ሰው የሽማግሌው ካህን የዘካርያስና የሚስቱ የኤልሳቤጥ ልጅ ዮሐንስ ነበረ። ዘካርያስ በቤተ መቅደስ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ መልአክ መጥቶ ወንድ ልጅ እንደሚወልድና ስሙም ዮሐንስ እንደሚባል እንደ ነገረው ታስታውሳላችሁ። ዮሐንስ አሁን አድጎ ሠላሳ ዓመት ገደማ የሆነው ጐልማሳ ነበረ። ብቻውን ሆኖ እንዲያስብ፥ እንዲጸልይና የእግዚአብሔርን ድምፅ እንዲያዳምጥ ከከተሞችና ከሕዝባቸው ርቆ በምድረ በዳ ስፍራዎች ኖሮ ነበር። እግዚአብሔርም በምድረ በዳ ተናግሮት ነበር፤ ለሕዝቡ እንዲሰብክና በቅርቡ ለምትመጣው ለእግዚአብሔር መንግሥት እንዴት እንደሚዘጋጁ እንዲነግራቸው አዝዞት ነበር።

ዮሐንስ በተራሮቹ እግር በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ይሰብክ ነበር፤ ሕዝቡም ቃሉን ለመስማት ከየከተማውና ከየመንደሩ ወደ እርሱ ሄዱ። ዮሐንስ በዘመኑ እንደ ነበሩት ሰዎች አልነበረም። ጠጕሩ ፈጽሞ ተቈርጦ አያውቅም ነበር፤ ረጅምና ጥቁር ሆኖ በትከሻው ላይ ተንዘርፍፎ ነበር። ጥቁር ጢሙም ፈጽሞ ተከርክሞ ስለማያውቅ እጅግ ረጅም ነበር። ልብሱ ከአውሬ የተገፈፈ ቍርበት ወይም ከሻካራውና ከጐፋሩ የግመል ጠጕር የተሠራ መጐናጸፊያ ነበር፤ በወገቡም የጠፍር መታጠቂያ ታጥቆ ነበር። በፀሐይ፥ በነፋስና በዝናብ ውስጥ ከቤት ውጭ ኖሮ ስለ ነበር ፊቱ፥ ክንዶቹ፥ ባቶቹና ባዶ እግሮቹ ሁሉ ቡናማና ጠንካራ ሆነው ነበር። ምግቡም በሜዳና በዱር የሚለቅማቸው አንበጣዎችና በዛፎች ጕድጓድ ውስጥ የሚገኝ ማር ነበረ። ሕዝቡ ባዩት ጊዜ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ዮሐንስ ይሰብክበት ከነበረው ስፍራ አጠገብ በእሳት ሰረገላ ወደ ሰማይ ያረገውን ታላቁን ነቢይ ኤልያስን አሰቡ፤ እየተደነቁም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦

«ይህ ወደ ምድር የተመለሰው የእሳቱ ነቢይ ኤልያስ መሆን አለበት።»

በእስራኤላውያን ዘንድ ነቢይ ማለት እግዚአብሔር እንዲናገረው የሰጠውን ቃል ወደ ሕዝቡ የሚያመጣ ሰው ነበረ። ሕዝቡ ሁሉ በቃል ከሞላ ጐደል የሚያውቋቸው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ስለ ብዙ ነቢያት ይናገሩ ነበር፤ ለምሳሌ ዓለቱን መትቶ ለሕዝቡ ውኃ ያወጣው ሙሴ፤ ጸሎቱ ሕዝቡን ከጠላቶቻቸው ያዳነው ሳሙኤል፤ ለንጉሡ ለዳዊት የድፍረት ቃል የተናገረው ናታን፤ የምንጩን መራራ ውኃ ጣፋጭ ያደረገው፥ ለምጻሙን ንዕማንን የፈወሰውና ብዙ ድንቅ ሥራዎችን ያደረገው ኤልሳዕ። ከነቢያት ሁሉ ኤልያስን ታላቅ አድርገው ይቈጥሩት ነበር፤ በብሉይ ኪዳን የመጨረሻ መጽሐፍ በነቢዩ በሚልክያስ መጽሐፍ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈም ያስታውሱ ነበር፦

«እነሆ፥ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ።»

ሕዝቡም በወንዙ አጠገብ የሚሰብከውን ይህን እንግዳ ሰው ባዩት ጊዜ የጌታ ቀን በእርግጥ እንደሚመጣና ተስፋ የተሰጠበት ነቢዩ ኤልያስ ይህ እንደ ሆነ አሰቡ።

ዮሐንስ በስብከቱ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበችና ሰው ሁሉ ለእርሷ ተዘጋጅቶ መቆየት እንዳለበት ለሕዝቡ ተናገረ። ለመዘጋጀትም ኃጢአታቸውን መናዘዝ፥ ክፉ ማድረግን መተውና መልካም ማድረግ መጀመር ነበረባቸው። ከክፋት ለመራቅና ጌታን ለማገልገል መፍቀዳቸውን ለማሳየት ምልክት እንዲሆን በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ ተጠመቁ። ዮሐንስም እንዲህ አላቸው፦

«እኔ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ከእናንተ ከራሳችሁ ወገን የሆነ፥ እናንተ የማታውቁት፥ ከእኔ የሚበልጥ አንድ በመካከላችሁ አለ፤ ጐንብሼ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ እስከ ሆንሁ ድረስ ከእኔ እጅግ ከፍ ያለ ነው። እርሱ በቅርቡ ይመጣል፤ በመጣም ጊዜ እንደ እኔ በውኃ አያጠምቅም። እርሱ በእሳትና በእግዚአብሔር መንፈስ ያጠምቃችኋል።»

በቅርቡ ስለሚመጣው ስለዚህ ታላቅ ሰው ደግሞ ተናገረ፤ እንዲህም አለ፦

«ገበሬ በአውድማው ላይ እህሉን እንደሚያደርግ እርሱም ሕዝቡን እንዲሁ ያደርጋል። አውድማውን ፈጽሞ ያጠራል፤ ስንዴውን በጎተራው ይከታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።»

ሕዝቡም ወደ ዮሐንስ መጥተው እንዲህ አሉት፦

«ለዚህ ታላቅ ንጉሥ መምጣት ለመዘጋጀት ምን እናድርግ?»

ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦

«እያንዳንዱ የተቸገሩትን ለመርዳት የሚችለውን ያድርግ። ከእናንተ ሁለት ልብስ ያለው ቢኖር አንዱን ልብስ ለሌለው ለአንድ ድሀ ይስጥ፤ ስንዴና ገብስ ያላችሁም ለተራቡት የሚበሉትን ስጡ።»

ለሮማ ገዦች ከሕዝቡ ግብር የሚሰበስቡ አንዳንድ ሰዎችም ወደ ዮሐንስ መጥተው እንዲህ አሉት፦

«ለንጉሡ መምጣት ለመዘጋጀት ምን እንድናደርግ ትፈልጋለህ? ከእንግዲህ ግብር እንዳይከፍሉ ለሕዝቡ እንንገራቸውን?»

ዮሐንስም «አይደለም» ብሎ መለሰ፤ «ሕዝቡ እንደ ቀድሞው ግብራቸውን ይክፈሉ፤ እናንተ ግን ከሚገባው አብልጣችሁ እንዳታስከፍሏቸውና እንዳትዘርፏቸው ተጠንቀቁ።»

ከእነዚህ ግብር ሰብሳቢዎች (ቀራጮች ይባሉ ከነበሩት) ብዙዎቹ ሊወስዱት ከሚገባቸው አብልጠው ከሕዝቡ ይወስዱና የሕዝቡን ገንዘብ ለራሳቸው ይጠቀሙበት ነበርና። ሕዝቡን በመዝረፍ ራሳቸውን ያበለጽጉ ነበር። ሕዝቡ በየስፍራው እነዚህን ቀራጮች ይጠሉአቸውና «ኃጢአተኞች» ብለው ይጠሩአቸው ነበር።

ወታደሮችና ጠባቂዎችም ወደ ዮሐንስ መጥተው «እኛስ ምን እናድርግ?» አሉት።

ዮሐንስም እንዲህ አላቸው፦

«በሕዝቡ ላይ ጨካኞችና ኃይለኞች አትሁኑ። ሰውን ሁሉ በደግነት ያዙ። ደመወዛችሁ ይብቃችሁ፤ ልትጠይቁት መብት የሌላችሁን ገንዘብ እንዲሰጧችሁ ሕዝቡን አታስገድዱ።»

ዮሐንስ ለሕዝቡ ከተናገራቸው ብዙ ነገሮች እነዚህ ጥቂቶቹ ነበሩ። ቃሉ ሁሉ ወደዚህ ይጠቃለል ነበር፦ «ክፉ እያደረጋችሁ ከሆነ ተዉት፤ መልካም ማድረግም ጀምሩ። ራስ ወዳዶች አትሁኑ፤ ባልንጀሮቻችሁን ውደዱ፤ መልካምም አድርጉላቸው። ንጉሡም ሲመጣ ልትታዘዙት ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ።»

ዮሐንስ ትምህርቱን ለመከተል ቃል የገቡትን ሁሉ በዮርዳኖስ ወንዝ ያጠምቅ ስለ ነበር «መጥምቁ ዮሐንስ» ተባለ።

በኢየሩሳሌም የነበሩት የሕዝቡ መሪዎች የዮሐንስን ቃል አላመኑም፤ በእርሱም አልተጠመቁም። ስለ እርሱ ምን እንደሚያስቡ በትክክል አላወቁም ነበር፤ ስለዚህ እንዲያዩት አንዳንድ ካህናትንና ሌሎችንም ላኩ። እነዚህ ሰዎችም መጥተው እንዲህ ብለው ጠየቁት፦

«አንተ ማን ነህ? ተስፋ የተሰጠበት ንጉሥ ክርስቶስ አንተ ነህን?»

ዮሐንስም «አይደለሁም፤ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም» ብሎ መለሰ።

እነርሱም «እንኪያስ ምንድን ነህ?» አሉ። «አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት እንደ ገና ወደ ምድር የመጣው ነቢዩ ኤልያስ ነህን?»

ዮሐንስም ደግሞ «አይደለሁም፤ እኔ ኤልያስ አይደለሁም» ብሎ መለሰ።

እነርሱም «እንግዲያስ ለላኩን ገዦች መልስ እንድንሰጥ ማን እንደ ሆንህ ንገረን» አሉት።

ዮሐንስም እንዲህ አለ፦

«በነቢዩ በኢሳይያስ መጽሐፍ ‹በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤ የጌታን መንገድ አዘጋጁ፥ ጥርጊያውንም በፊቱ አቅኑ› ተብሎ ተጽፎአል። ለሕዝቡ እንድናገርና ለንጉሡ እንዳዘጋጃቸው ያ ድምፅ እኔ ነኝ፤ ንጉሡም ባታውቁትም አሁን እንኳ በመካከላችሁ ነው፤ በቅርቡም ራሱን ይገልጣል።»


ቀዳሚ ቀጣይ