የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ወጣቱ አናጢ

ምዕራፍ 14 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

ወጣቱ አናጢ

ቤተ መቅደሱን ከጎበኘ በኋላ ለዐሥራ ስምንት ዓመታት ኢየሱስ ከብላቴናነት ወደ ወጣትነት እያደገ በናዝሬት ኖረ። የአይሁድ ልጅ ብዙውን ጊዜ ትምህርት ቤቱን የሚተወው በዐሥራ ሦስት ዓመቱ ገደማ ነበር፤ ከዚያም በአንድ ሙያ ወይም ሥራ መሥራት ይጀምር ነበር። ኢየሱስ ወደ ዮሴፍ የሥራ ቤት ገብቶ ማረሻዎችንና የመጥረቢያ እጀታዎችን፥ መሰቅሰቂያዎችንና ለቤቶች የሚሆኑ ቀላል የቤት ዕቃዎችን በመሥራት በሥራው ረዳ። ኢየሱስ የሠራው ሁሉ በሚገባ የተሠራ ነበር፤ በሙያውም ብዙ ሳይቈይ የተዋጣለት ሠራተኛ እንደ ሆነ አንጠራጠርም። የሠራቸው የመጥረቢያ እጀታዎችና ማረሻዎች ከምርጦቹ የማያንሱ ነበሩ፤ የእህል መስፈሪያ ቢሠራም ትክክለኛ ነበረ፤ ኢየሱስ ሊታመን የሚችል ልጅ ነበርና።

በብላቴናነቱ እንደ ሌሎች ልጆች ነበረ፤ በመጫወቻ ጊዜ በደስታ ይጫወት፥ በሥራ ጊዜም በሙሉ ልቡ ይሠራ ነበር። አንዳንድ ልጆች እያነበቡ፥ እያሰቡና እያለሙ ብቻቸውን መሆን ይወዳሉ፤ ኢየሱስ ግን ከእንደዚህ ያሉት አልነበረም። በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ሰዎች በዙሪያው እንዲሆኑ ይወድ ነበር፤ በብላቴናነቱም በሌሎች ልጆች መካከል ብዙ ወዳጆች እንደ ነበሩት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ብርቱና ጤናማ ነበረ፤ መሮጥ፥ መዝለልና ዛፍ መውጣት ይችል ነበር። ከብላቴና ወዳጆቹ ጋር በተራሮች መካከልና ከከተማው ኮረብቶች ማዶ ባለው በታላቁ ሜዳ ላይ ይዘዋወር ነበር። የገሊላ ባሕር ሃያ ማይል ብቻ ይርቅ ነበር፤ ኢየሱስም ከወዳጆቹ ጋር በሰማያዊ ውኆቹ ዓሣ ለማጥመድ እንደ ሄደና ያጠመደውን ዓሣ ለእናቱ ወደ ቤት እንዳመጣ አንጠራጠርም።

ከጊዜ በኋላ የማርያም ባል ዮሴፍ ሞተ፤ ኢየሱስም እናቱንና ብዙ ልጆቿን የመንከባከብ ኀላፊነት ቀረበት። ገና ከብላቴናነት ለሚወጣና ጐልማሳ መሆን ለሚጀምር ሰው ለእናቱና ቢያንስ ለስድስት ታናናሽ ወንድሞቹና እኅቶቹ ምግብ የሚገዛበትን በቂ ገንዘብ የማግኘት ሸክም መጣል ቀላል ነገር አይደለም፤ ወጣቱ ኢየሱስ የተሸከመውም ይህን ሸክም ነበር። አባት ሆኖለት የነበረው ዮሴፍ ቢሄድም ኢየሱስ የሰማዩ አባቱ አሁንም ከእርሱ ጋር እንዳለና በችግሩ ሁሉ ለርዳታ ሊጠራው እንደሚችል ያውቅ ነበር።

ኢየሱስ ረጅሙን ቀን ሁሉ በትጋት ይሠራ ነበር፤ በአይሁድ ዘንድ ቅዳሜ የሆነው የሰንበት ቀን በመጣ ጊዜ ግን የሥራ ቤቱ ይዘጋ ነበር፤ እርሱም በመንደሩ ምኵራብ ወለል ላይ ተቀምጦ የብሉይ ኪዳንን ንባብ ያዳምጥና በምስጋና መዝሙሮች ይተባበር ነበር። በተራውም በንባብ ማቅረቢያው አጠገብ አንባቢ ይሆን ነበር፤ ከኢሳይያስ ወይም ከሚክያስ ወይም ከሆሴዕ ትምህርቱን ሲያነብ ሌሎች ሊያዩት ያልቻሉትን ትርጕም በጥቅሶቹ ውስጥ ያይ ነበር፤ በሥራ ቤቱ ረጅም ሰዓታት ውስጥ ያስብ፥ ይጸልይና የእግዚአብሔርን ድምፅ ያዳምጥ ነበርና።

ኢየሱስ ይህን ጸጥ ያለ ሕይወት በቤትና በሥራ ቤት እየኖረ ሳለ በምድሪቱ ላይ አንዳንድ ለውጦች እየሆኑ ነበር። በገሊላ ገዥ የነበረው በቤተ ልሔም ሕፃናትን ሁሉ የገደለው የዚያ የክፉው ሄሮድስ ልጅ ሄሮድስ አንቲጳስ ነበረ፤ እርሱም ከአባቱ እጅግ የተሻለ አልነበረም። በኢየሩሳሌም ዙሪያ ባለው የምድሪቱ ክፍል በይሁዳ ሌላው የሄሮድስ ልጅ አርኬላዎስ እጅግ በክፋት ስለ ገዛ ሕዝቡ ሁሉ እንዲያስወግደው በሮም ወዳለው ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ጢባርዮስ ላኩ። አይሁድ ከዚያ በኋላ ከወገናቸው የሆኑ ገዦች እንደሚኖሩአቸው ተስፋ አደረጉ፤ ንጉሠ ነገሥቱ ግን የማይወዱትን ነገር ግን ሊያስቈጡት የማይደፍሩትን የሮማ አገረ ገዥ ላከላቸው። በምድሪቱ ውስጥ በብዙ ስፍራዎች፥ በተለይም ኢየሱስ ይኖርበት በነበረው በገሊላ፥ ከሕዝቡ አንዳንዶቹ ለሮም መንግሥት ግብራቸውን ለመክፈል እምቢ ብለው ከገዦቹ ጋር መዋጋት ጀመሩ። ከሮማውያን ሠራዊት ጋር ሊዋጉ አልቻሉም፤ ስለዚህ በዱርና በዋሻ በተራራም ተሸሸጉ፤ ነገር ግን በቡድን እየወጡ በመንገድ ላይ ሕዝቡን ይዘርፉ ነበር። በምድሪቱ ሁሉ፥ በሰሜንም በደቡብም፥ ፍርሃትና መከራ ነበረ። ሕዝቡ በገዦቻቸው አልረኩም፤ ሁሉም የእግዚአብሔር መንግሥት የምትመጣበትና የሮማ ሹማምንቶቻቸውና ቀራጮቻቸው የሚባረሩበት ጊዜ እንደ ቀረበ ተስፋ ያደርጉ ነበር። ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት ዳዊት እንደ ነገሠባት ያለች መንግሥት፥ ሠራዊትና በጠላቶቿ ላይ ድል ለንጉሡም ቤተ መንግሥት ያላትን መንግሥት ይጠባበቁ ነበር።

ነገር ግን በናዝሬት ኮረብታ ላይ ባለችው በዚያች አንድ ክፍል ብቻ ባላት ትንሽ ቤት ውስጥ ንጉሡ ወጥቶ እውነተኛይቱን የእግዚአብሔር መንግሥት እንዲያመጣ የሚጠራበትን ጊዜ እየጠበቀ እንደ ነበረ አላወቁም።


ቀዳሚ ቀጣይ