ምዕራፍ 13 · 7 ደቂቃ ንባብ · 9 ደቂቃ ማዳመጥ
የጠፋውና የተገኘው ልጅ
ኢየሱስ ዐሥራ ሁለት ዓመት እስኪሞላው ድረስ በመንደሩ ምኵራብ ባለው ትምህርት ቤት ተማረ። በዚያን ጊዜ ማንበብና መጻፍ ይችል ነበር፤ ብዙ ጥቅሶችንም በቃሉ ያውቅ ነበር። የንባብ መጽሐፉ፥ የፊደል መጽሐፉ፥ የጽሕፈት መለማመጃው፥ በቃል የሚያጠናቸውም ጥቅሶች ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ነበሩ፤ በምኵራቡ አምልኮ ጊዜም ከመጻሕፍቱ ረጅም ንባብ ይሰማ ነበር፤ ስለዚህ ከመጻሕፍት ሁሉ የሚበልጠው በዚያ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን መልካም ነገሮች ሁሉ በሚገባ እንዳወቃቸው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ለዚህም አንዱ ማስረጃ ይህ ነው፤ በኋለኞቹ ዓመታት አንድ ሰው በከባድ ጥያቄ ሊያስቸግረው በሞከረ ጊዜ ብዙ ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ በተወሰደ ቃል ወዲያውኑ ይመልስ ነበር።
አንድ የአይሁድ ልጅ ብዙውን ጊዜ ትምህርት ቤትን የሚተወው በዐሥራ ሁለት ዓመቱ ነበር፤ ረቢ ለመሆን ካልፈለገ በቀር፤ ረቢ በአይሁድ ዘንድ የሕጋቸው መምህር የሚጠራበት ስም ነበር። ይህ ምኞቱ ወይም የወላጆቹ ዓላማ ከሆነ ግን ጻፎች ወይም መምህራን በቤተ መቅደስ በሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት እንዲማር ወደ ኢየሩሳሌም ይላክ ነበር። ከኢየሱስ በአራት ዓመት ያህል የሚያንሰው የጠርሴሱ ሳውል፥ እኛ ሐዋርያው ጳውሎስ ብለን የምናውቀው፥ በቤተ መቅደሱ ትምህርት ቤት ተማሪ ነበረ፤ ኢየሱስ ግን አልነበረም። ወጣቱ ሳውል በኢየሩሳሌም ሲማር ሳለ ወጣቱ ኢየሱስ በናዝሬት በአናጢነት ቤት ይሠራ ነበር።
ኢየሱስ ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ ታላቁን የፋሲካ በዓል ለማክበር ለመጀመሪያ ጊዜ ከናዝሬት ወደ ኢየሩሳሌም ተወሰደ። በዓመት ውስጥ ሦስት ታላላቅ በዓላት ይከበሩ ነበር። የፋሲካ በዓል በጸደይ መጀመሪያ ላይ ነበር፤ እስራኤላውያን ባሪያዎች መሆናቸው ቀርቶ ነጻ ሰዎች ሆነው ከግብፅ የወጡበትን ታላቅ ቀን ያሳስብ ነበር። የበዓለ ሃምሳ በዓል በጸደይ መጨረሻ፥ ልክ ከፋሲካ በኋላ በኀምሳኛው ቀን ይከበር ነበር፤ «ጴንጤቆስጤ» የሚለው ቃል «ኀምሳ ቀን» ማለት ነውና፤ አባቶቻቸው ከግብፅ ከወጡ ከኀምሳ ቀን በኋላ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ በመብረቅና በነጐድጓድ መካከል ሕጉን እንደ ሰጣቸው ሕዝቡን ያሳስብ ነበር። የዳስ በዓል ወይም «የድንኳን በዓል» (የቃሉ ትርጕም ይህ ነውና) በመከር ይከበር ነበር፤ በዚያን ጊዜ ሕዝቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር ወደ ከነዓን ሲጓዙ በምድረ በዳ በጥንት ዘመን ያሳለፉትን የሜዳ ኑሮ ለማሳየት ከለመለሙ ቅርንጫፎች ዳሶችን ሠርተው ለአንድ ሳምንት በውስጣቸው ይበሉና ይተኙ ነበር። እነዚህ ሦስቱ ታላላቅ በዓላት በኢየሩሳሌም ይከበሩ ነበር፤ ሕዝቡም ሊያከብሩአቸው ከምድሪቱ ክፍል ሁሉ ወደ ከተማዪቱ ይወጡ ነበር።
ብላቴናው ኢየሱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን ጕዞ ወደ ኢየሩሳሌም ማድረጉ ታላቅ ነገር ነበር። ትንንሾቹ ልጆች በአንድ ወዳጅ ጥበቃ ሥር በቤት ቀሩ፤ ልጅ እነዚህን በዓላት ማክበር የሚጀምረው ዐሥራ ሁለት ዓመት ሲሞላው ነበርና። ዮሴፍና ማርያም ግን ይህን ጕዞ ብዙ ጊዜ አድርገውት ስለ ነበር ሁሉን ያውቁት ነበር። ከዐሥራ ሁለት ዓመት በፊት ወደ ቤተ ልሔም ሲሄዱ የያዙትን መንገድ ተከትለው ከናዝሬት ከተነሣው የመንገደኞች ቡድን ጋር ሄዱ። ማርያም በአህያ ላይ ተቀምጣ፥ ዮሴፍና ብላቴናው ኢየሱስ በአጠገቧ እየሄዱ ሲጓዙ ስለሚያልፉባቸው ስፍራዎችና ስለ እነርሱ ስለሚነገሩት የጥንት ታሪኮች ይነጋገሩ ነበር። ኢየሱስ እነዚያን ታሪኮች ሁሉ ያውቅ ነበር፤ የአይሁድ ልጅ ሁሉ ደጋግሞ ሰምቶአቸው ነበርና።
ከናዝሬት አጠገብ ባለው ኮረብታ ጫፍ ላይ በቆሙ ጊዜ ታላቁ የኤስድራሎን ሜዳ ከበታቻቸው ተዘርግቶ ነበር፤ እንዲህም ይሉ ይሆናል፦ «በምዕራብ በኩል በታላቁ ባሕር አጠገብ ያለው ያ ተራራ የቀርሜሎስ ተራራ ነው፤ ኤልያስ መሠዊያውን የሠራበትና ታላቁን መሥዋዕቱን ያቀረበበት፥ ለጸሎቱም መልስ እሳት ከሰማይ ወርዶ በመሠዊያው ላይ የተቀመጠውን ወይፈን ያቃጠለበት ስፍራ ነው። ሜዳውን አቋርጦ የሚሄደውን ያን መንገድ ታያለህን? ከረጅሙ ድርቅ በኋላ ዝናቡ ሲመጣ ኤልያስ በዚያ መንገድ ላይ በንጉሡ በአክዓብ ሰረገላ ፊት ሮጠ። ደግሞም ይህ ሜዳ! በግራ በኩል ካለው ከታቦር ተራራ ተነሥተው ዲቦራና ባርቅ የሚሸሹትን ከነዓናውያን በዚህ ሜዳ ላይ አሳደዱ። ከታቦር ባሻገር ያለውን ሁለተኛውን ተራራ ታያለህን? እርሱ የጊልቦዓ ተራራ ነው፤ በእግሩም ጌዴዎን ከሦስት መቶ ጀግኖቹ ጋር የምድያምን ሠራዊት በሌሊት አስደንግጦ ታላቅ ድል አገኘ።»
ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ ወርደው የዮርዳኖስን ወንዝ ተከትለው በሮማውያን መንገድ ወደ ደቡብ ሄዱ። በአንድ ስፍራ በግራና በቀኝ ያሉት ተራሮች ወደ ወንዙ ተጠግተው ይወርዱ ነበር፤ በአንድ በኩል በሚያረፋው ወንዝና በሌላው በኩል በገደላማው ዓለት መካከል ለመንገዱ የሚበቃ ቦታ ብቻ ነበረ።
ዮሴፍም፦ «ተመልከት፤ አባቶቻችን በኢያሱ መሪነት ከዚህ ሠላሳ ማይል በታች ወንዙን ሊሻገሩ ሲሉ ውኆቹ ተነሥተው እንደ ክምር የቆሙበት ስፍራ ይህ ነው» አለ።
ወደ ወንዙ የሚገባውን አንድ ፈፋ ተሻገሩ፤ ዮሴፍም፦ «ይህን ፈፋ ታያለህን? ይህ የኮራት ፈፋ ነውና በዚያ በተራሮቹ መካከል ነቢዩ ኤልያስ በቁራዎች የተመገበበት ስፍራ ነበረ» አለ።
ከኢያሪኮ ጥቂት ከፍ ብሎ እስራኤላውያን በኢያሱ ዘመን በደረቁ የወንዝ ወለል ላይ የተሻገሩበት ስፍራ ደረሱ፤ በዚያን ጊዜ ካህናቱ ቅዱሱን ታቦት ተሸክመው በፊት ይሄዱ ነበር፤ ሕዝቡም በረጅም ሰልፍ ይከተሉ ነበር። በዚያ ወንዙ እጅግ ሰፊና ጥልቀት የሌለው ስለ ሆነ ሰዎች በእግር ይሻገሩታል፤ በጸደይ መጀመሪያ ግን በዝናብና በሰሜን በኩል ርቀው ባሉት ከፍተኛ ተራሮች ላይ በሚቀልጠው በረዶ ይሞላል።
በዚያም ከወንዙ ማዶ ያለውን ሙሴ ቆሞ ምድሪቱን የተመለከተበትንና ከዚያም ብቻውን ተኝቶ የሞተበትን የናባው ተራራ ያሳዩት ይሆናል። በኢያሪኮም ለማረፍ ቆሙ፤ በዚያም እስራኤላውያን በዙሪያቸው ሲዞሩና ካህናቱ የአውራ በግ ቀንደ መለከታቸውን ሲነፉ ስለ ፈረሱት ቅጥሮች የሚነገሩ ታሪኮች ነበሩ። ምናልባትም ነቢዩ ኤልሳዕ ውኃውን ባነጻበት በኢያሪኮ አጠገብ ባለው በታላቁ ምንጭ ቆመው ጠጥተው ይሆናል። ወደ ተራሮቹም ከወጡ በኋላ በስድስተኛው ቀን ወይም በሳምንቱ መጨረሻ የጕዞአቸው መድረሻ ወደሆነችው፥ ሕዝቡ «ቅድስቲቱ ከተማ» ወደሚሏት ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ።
ከዚያም የእግዚአብሔር ግሩም ቤተ መቅደስ በዚያ ነበረ! ብላቴናው ከጽዮን ተራራ ወደ ሞሪያ ተራራ በሚወስደው ድልድይ ላይ ሲሄድ ልቡ እንዴት ተነካ! ወደ ታላቁ የውጪ አደባባይ፥ ወደ አሕዛብ አደባባይ ገቡ፤ ይህ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ባዕዳን እንዲገቡ የተፈቀደበት ብቸኛ ስፍራ ነበር፤ ብላቴናው ኢየሱስም ይህ ስፍራ ከብትና በግ ርግብም ወደሚሸጥበት፥ የባዕድ አገር ገንዘብን በአይሁድ ሰቅል የሚለውጡ ሰዎች ገበታዎችም በዙሪያው ወደ ቆሙበት ገበያ ተለውጦ ባየ ጊዜ ደነገጠ።
በምሥራቁ ቅጥርና በወርቁ በር ባሻገር በዚያን ጊዜ እስከ ጫፉ ድረስ በወይን ቦታዎች፥ በወይራ ዛፎችና በአትክልት ስፍራዎች የተሸፈነውን ደብረ ዘይትን አዩ። ደረጃዎችን ወጥተው «ውብ» በተባለው ደጅ በኩል ልክ እንደ ውጪው አደባባይ ጣራ ወደሌለው ወደ አንድ ትንሽ አደባባይ ገቡ። ይህም «የሴቶች አደባባይ» ተብሎ ይጠራ ነበር፤ ሴቶቹ በዐይነ ርግብ ከተሸፈነው ሰገነት ወደ መሠዊያውና ወደ አምልኮው ሥርዓት ይመለከቱ ነበርና። ኢየሱስ በዚህ በሴቶች አደባባይ ብዙ የወጣቶች ክፍሎች በክብ ተቀምጠው መምህራኖቻቸውን እያዳመጡ ሲማሩ ተመለከተ። በመካከላቸው ተቀምጦ እነዚህን ጠቢባን ሊቃውንት ለማዳመጥ እንዴት ተመኘ! ገና ብላቴና ቢሆንም ስላነበባቸው ብዙ ነገሮች በጥልቅ አስቦ ነበርና፤ መልስ እንዲያገኝላቸው እጅግ የሚመኛቸው ብዙ ጥያቄዎችም ወደ አእምሮው መጥተው ነበር። መለከቶች እየተነፉ፥ የዕጣን ጥናዎች እየተወዛወዙ፥ ካህናቱም የዳዊትን መዝሙሮች እየዘመሩ የመሥዋዕቱ ቍርባን በመሠዊያው ላይ ሲቀመጥና ሲቃጠል አየ።
ቤተሰቡ በኢየሩሳሌም በነበሩበት ጊዜ የሚያርፉበት ወዳጆች አገኙ፤ የፋሲካውንም ራት በቤታቸው በሉ። እርሱም እጅግ ቀላል ማእድ ነበር፤ የተጠበሰ በግ፥ ጥቂት አትክልትና እንደ ብስኩት ቀጭንና ከእርሱ ግን ሰፋ ያለ ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ብቻ ነበር። ማእዱንም በገበታው ዙሪያ ባሉ መደቦች ላይ ተጋድመው፥ ራሳቸውን ወደ ገበታው እግራቸውንም ከእርሱ ወደ ውጭ አድርገው በሉ። በዚህ በዓል የመጀመሪያውን ፋሲካ ታሪክ መናገር የአይሁድ ልማድ ወይም ሥርዓት ነበር። ምናልባት ዮሴፍ ኢየሱስን እንዲህ ብሎት ይሆናል፦
«ልጄ ሆይ፥ ይህ ፋሲካ ለመጀመሪያ ጊዜ በተበላ ጊዜ የሆነውን ታውቃለህ። ታሪኩን ንገረን።»
ብላቴናው ኢየሱስም በግብፅ ምድር ላይ ስለ ወረዱት አስፈሪ መቅሠፍቶች ተናገረ፤ ስለ መጨረሻውና ስለ ታላቁ ኀዘን፥ በየቤቱ ስለ ሞተው የበኵር ልጅ፤ እስራኤላውያን የታረደውን በግ ደም በመቃኖቻቸው ላይ እንዴት እንደ ረጩና የሞት መልአኩ እንዴት እንዳለፋቸው፤ በዚያችም ሌሊት ለጕዞ ተዘጋጅተው በጉን እንዴት እንደ በሉ፤ ከግብፅም እንዴት እንደ ወጡና በቀይ ባሕር መካከል እንዴት እንደ ተሻገሩ ተረከ።
ቤተሰቡ ለአንድ ሳምንት በኢየሩሳሌም ቈዩ፤ ኢየሱስም በአምልኮው ለመሳተፍና ከመምህራኑ የሚችለውን ለመማር በየቀኑ ወደ ቤተ መቅደስ ይወጣ ነበር። የጕብኝታቸው የመጨረሻ ቀን ደረሰ፤ በመጨረሻውም ወደ ገሊላ የሚሄዱት ቤተሰቦች ወደ ቤታቸው ለመመለስ በአንድነት ተሰበሰቡ። ቀንደ መለከት ተነፋ፤ የመንገደኞቹም ቡድን ወደ ሰሜን ተነሣ። ማርያም ልጅዋን አጣችው፤ ነገር ግን በእኩዮቹ ልጆች መካከል እያወራ በሕዝቡ ውስጥ ያለ መሰላት። ሌሊት በሆነ ጊዜ ግን መንገደኞቹ ለማረፍ ቆሙ፤ ኢየሱስም አልታየም። ማርያም ደነገጠች። ሕዝቡን ሁሉ ፈለጉ፤ ኢየሱስ ግን አልተገኘም።
ዮሴፍና ማርያምም በታላቅ ጭንቀት ልጃቸውን እየፈለጉ ወደ ኢየሩሳሌም ፈጥነው ተመለሱ። ባረፉበት ቤት ባሉት ወዳጆች ዘንድ ጠየቁ፤ እርሱ ግን በዚያ አልነበረም። በጠባቦቹ መንገዶች ላይ ወዲያና ወዲህ ተንከራተቱ፤ ብዙ የልጆች ቡድኖችን ቢያዩም ልጃቸው በመካከላቸው አልነበረም። በመጨረሻ በሦስተኛው ቀን በቤተ መቅደስ ፈለጉት። ከአደባባዮቹ በአንዱ ብዙ ሕዝብ ከአንድ ሰው ጋር የሚነጋገሩ የሚመስሉትን መምህራን ያዳምጡ ነበር። ቀረቡ፤ ማርያምም ከሕዝቡ መካከል የአንድ ብላቴና ድምፅ በድንገት በሰማች ጊዜ ልቧ ይመታ ጀመር። ያን ጥርት ያለ፥ ደማቅና ቅን ድምፅ ታውቀው ነበር! ተጋፍታ ገባች፤ እነሆም ልጅዋ በሊቃውንቱ መካከል ቆሞ ነበር። እነዚህን ሰዎች ይጠይቃቸው ነበር፤ እነርሱም በመልሳቸው በተራቸው ይጠይቁት ነበር፤ በዙሪያቸውም ያሉ ሰዎች እያዳመጡ በዚህ ብላቴና የእውነት ጥልቅ እውቀት ይደነቁ ነበር።
ማርያም ወደ ኢየሱስ ፈጥና ሄዳ እንዲህ አለችው፦
«ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ሦስት ቀን ስንፈልግህ ነበርን!»
ኢየሱስም በመደነቅ ቀና ብሎ የእናቱን ፊት ተመለከተና እንዲህ አለ፦
«ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?»
በጕብኝታቸው የመጨረሻ ቀን ቤተ መቅደሱን አንድ ጊዜ ደግሞ ለመጎብኘት ሾልኮ እንደ ሄደ ግልጽ ነው፤ በዚያም ከደረሰ በኋላ አእምሮውና ልቡ እጅግ ስለ ተሞሉ ወደ ቤት የመመለስ ሐሳብ ፈጽሞ አልመጣለትም። ስለ ውጪው ዓለም ምንም ሳያስብ በጌታ ቤት አደባባዮች ውስጥ ብቻ ቈየ።
በእነዚያ ሁለት ሌሊቶች የት ተኛ? በእነዚያ ሦስት ቀኖች ምግብ የሰጠው ማን ነው? በበዓሉ ወቅት በሺህ የሚቈጠሩ ሰዎች እንዳደረጉት በደብረ ዘይት ላይ ከወይራ ዛፎች ሥር ተኝቶ ይሆናል። አንድ እንግዳ ሰው አይቶት ወደ ምግብ ጋብዞት ይሆናል። ነገር ግን በጥልቅና በሙሉ ልቡ በያዘው ጕዳይ ተመስጦ ምግብን ፈጽሞ ሳያስብ በእነዚያ ሦስት ቀኖች ምንም ባይበላ የሚያስደንቅ አይሆንም።
ነገር ግን ምንም ቃል ሳይናገር የእናቱን እጅ ይዞ ከቤተ መቅደስ ወጣ። ያየውንና የሰማውን ሁሉ እያሰላሰለ፥ ጥቂት እየተናገረ ግን ብዙ እያሰበ ወደ ቤቱ ወደ ናዝሬት ተጓዘ። ቢያንስ አንድ ታላቅና ክቡር እውነት ወደ ልቡ ገብቶ ነበር። የእስራኤል አምላክ ጌታ እግዚአብሔር የራሱ አባት እንደ ሆነና በአባቱ በእግዚአብሔር ፈጽሞ ሊታመን እንደሚችል ተሰማው።