የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
በናዝሬት የአንድ ልጅ ሕይወት

ምዕራፍ 12 · 6 ደቂቃ ንባብ · 8 ደቂቃ ማዳመጥ

በናዝሬት የአንድ ልጅ ሕይወት

ትንሹ ኢየሱስ ወደ ናዝሬት በመጣ ጊዜ ዕድሜው ከሁለት እስከ አምስት ዓመት ሳይሆን አይቀርም፤ ከሕፃንነት ወጥቶ ትንሽ ልጅ መሆን እየጀመረ ነበር። ናዝሬትም ቢያንስ ለሀያ አምስት ዓመታት፥ በልጅነቱ፥ በወጣትነቱና በጕልምስናው መጀመሪያ ሁሉ፥ መኖሪያው ነበረች።

በኮረብታው ጎን በነበረችው አንድ ፎቅና አንድ ክፍል ብቻ ባላት በዚያች ትንሽ ነጭ ቤት የሚኖረው ልጅ ኢየሱስ ብቻ አልነበረም። ብዙም ሳይቈይ ሌላ ወንድ ሕፃን ተወለደ፤ ስሙም ያዕቆብ ተባለ። እርሱም አድጎ ታላቅ ሰው ሆነ፤ ከብዙ ዓመታት በኋላም ከመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አንዱን፥ የያዕቆብን መልእክት፥ ጻፈ። ከዚያም አንዱ ከሌላው በኋላ ሦስት ተጨማሪ ወንዶች ልጆች ተወለዱ፤ እነርሱም ዮሳ፥ ስምዖንና ይሁዳ ናቸው። «ይሁዳ» የሚለውን ስም ስናነብ ጌታ ኢየሱስን በጥቂት ብር የሸጠውን ክፉውን ይሁዳን እናስብ ይሆናል። ያ ግን ሌላ ይሁዳ ነበር። ይህ ይሁዳ እንደ ወንድሙ እንደ ያዕቆብ ከብዙ ዘመን በኋላ ሌላውን የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ፥ የይሁዳን መልእክት፥ ጻፈ። ከልጆቹም መካከል ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩ፤ ከሁለት በላይም ሊሆኑ ይችላሉ፤ የሴቶቹ ቍጥርና ስማቸው ግን አልተጠበቀም።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ ልጆች አንዱ ከሌላው በኋላ እየተወለዱ፥ ሁልጊዜም የሚጠበቅ ሕፃን እያለ ያች ትንሽ ቤት ብዙ ጊዜ ጠባብ ሆና ሳትሆን አትቀርም። ደግሞም አብዛኛውን ጊዜ አባት ዮሴፍ የአናጢነት ሥራውን የሚሠራባት መሥሪያ ቤትም ነበረች። የጡብ ወይም የጭቃ ወለሉ ብዙ ጊዜ በፋቅ ይሞላ ነበር፤ የሠራተኛውም መሣሪያዎች በጠረጴዛው ላይ ይገኙ ነበር።

ቤቱ ዕቃ እምብዛም አልነበረውም፤ ወንበር፥ ፍራሽ ያለበት አልጋ፥ ምድጃ፥ በግድግዳ ላይ የተሰቀለ ሥዕል አልነበረም። በአንዱ ማዕዘን ምግብ ለማብሰል ትንሽ እሳት ይነድድ ነበር፤ ነፋሱ ወደ ክፍሉ መልሶ ካልነፋው በቀር ጢሱ በጣሪያው ባለው ቀዳዳ ይወጣ ነበር። በክረምት ቤቱን ለማሞቅ እሳት አያነድዱም ነበር፤ ሲበርድ ግን ፀሐይ እስክትወጣ ድረስ ብቻ ይጠብቁ ነበር። አንዳንድ ጊዜ በረዶ ይወርድ ነበር፤ በረዶው ግን ከሁለት ወይም ከሦስት ቀን በላይ እምብዛም አይቈይም ነበር። የዮሴፍ ልጆች በበረዶ ላይ በተጎታች ተሳፍረው ፈጽሞ አያውቁም፤ በገደላማ ኮረብቶችም ላይ በሸርተቴ አልተንሸራተቱም።

ለምግብ የሚሆን ጠረጴዛ ቢኖር እንኳ ከሁለት ጫማ በታች ቁመት ያለው እጅግ ዝቅተኛ ነበር፤ በዙሪያውም በትንንሽ ትራሶች ላይ ተቀምጠው እጃቸውን ወይም ቍራሽ እንጀራቸውን በአንድ የጋራ ሳሕን ውስጥ እያጠቀሱ ይበሉ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ጠረጴዛው የተገለበጠ ክብ መስፈሪያ ብቻ ነበር፤ አንዳንድ ጊዜም እኛ በሽርሽር ጊዜ በሣር ላይ ምግብ እንደምናቀርብ ምግቡ በወለሉ ላይ ይቀርብ ነበር።

ሌሊት ሲመጣ ቀን ቀን ተጠቅልለው በግድግዳ ላይ የሚቆሙትን ምንጣፎች ይዘረጉ ነበር፤ በወለሉም ላይ አንጥፈው ይተኙባቸው ነበር፤ ቀኑን ሙሉ የላይ ልብሳቸው የነበረውንም ረጅም መጐናጸፊያ በላያቸው ይደርቡ ነበር። በሩ ሲዘጋ ቤቱ ጨለማ ይሆን ነበር፤ ብቸኛው መስኮቱ በግድግዳው ላይ ያለች ትንሽ ቀዳዳ ነበረችና። ቤቱንም በረጅም መቆሚያ ወይም በትንሽ መደርደሪያ ላይ በሚቀመጥ የዘይት መብራት ያበሩት ነበር።

ነገር ግን ሰው ሁሉ በፊት ለፊት ባለው ግቢ፥ በመንገዶችና በዙሪያው ባሉት ኮረብቶች ውጭ ይኖር ስለ ነበር ቤቱ በቀን ብዙም አያገለግልም ነበር። ደስ በሚሉ ቀናት ዮሴፍ መሣሪያዎቹን ወደ ግቢው አውጥቶ እንጨት ይሠራ ነበር። በእኛ ዘመን የአናጢ ዋና ሥራ ያ ስለ ሆነ ዮሴፍን ቤት ሲሠራ እናስበው ይሆናል። ነገር ግን ቤቶቹ ከጭቃ ወይም ካልተጠረበ ድንጋይ ይሠሩ ነበር፤ አናጢውም በእነርሱ ላይ የሚሠራው እጅግ ጥቂት ነበር። ዋናው ሥራው የእንጨት ማረሻዎችን፥ ለበሬዎች ቀንበርን፥ ትንንሾቹን ጠረጴዛዎችንና በየቤቱ የሚገኘውን፥ በጠረጴዛም ፋንታ የሚያገለግለውን መስፈሪያ መሥራት ነበር።

አንድ እጅግ ጠቃሚ ዕቃ በቤቱ ወይም በግቢው ውስጥ ነበረ፤ እርሱም ከሁለት ክብና ጠፍጣፋ ድንጋዮች የተሠራው እህል የሚፈጭበት የእጅ ወፍጮ ነው። የእኛ ዱቄት ከታላላቅ ፋብሪካዎች ይመጣልናል፤ በዚያ አገር ግን እያንዳንዱ ቤተሰብ የራሱ ትንሽ ወፍጮ ነበረው። እህሉን በላይኛው የወፍጮ ድንጋይ ቀዳዳ ውስጥ ያፈሱ ነበር፤ ከዚያም እህሉ ተፈጭቶ ዱቄት እስኪሆን ድረስ ድንጋዩን በእጀታው እያዞሩ ያሽከረክሩት ነበር። ይህ ከባድ ሥራ ነበር፤ ሁልጊዜም የሚሠራው በሴቶች ነበር። ብዙ ጊዜ ሁለት ሴቶች የላይኛውን የወፍጮ ድንጋይ እጀታ ለማዞር ይረዳዱ ነበር። ማርያም ለብዙው ቤተሰብዋ የሚያስፈልገውን ዱቄት ስትፈጭ ብዙ ጊዜ ክንድዋ ይዝል ነበር። ሴቶች ልጆችዋ በበረቱ ጊዜ በዚህ ሥራ ይረዱአት ነበር።

ኢየሱስ የስድስት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ ከሌሎቹ ወንዶች ልጆች ጋር ወደ ትምህርት ቤት ተላከ። እኛ እስከምናውቀው ድረስ በአይሁድ ዘንድ ለሴቶች ልጆች ትምህርት ቤት አልነበረም። ትምህርት ቤቱ የሚካሄደው ምኵራብ ብለው በሚጠሩት በመንደሩ የጸሎት ቤት ነበር። መምህሩ ሁልጊዜ ወንድ ነበረ፤ አብዛኛውን ጊዜም ሕንጻውን በሥርዓት የሚጠብቀው የጸሎት ቤቱ ጠባቂ ነበር።

አይሁድ ለመንደሩ ትምህርት ቤት ያወጡለት ያማረ ስም ነበር። ልጆቹ በፀሐይ ለመብሰል የሚያድጉ የትንንሽ ወይን ዘለላዎች እንደ ሆኑ አድርገው «የወይን ቦታ» ብለው ይጠሩት ነበር። በዚህ የወይን ቦታ ትምህርት ቤት ለጥናት የሚሆን አንድ መጽሐፍ ብቻ ነበር፤ እርሱም መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። አዲስ ኪዳን ገና ስላልተጻፈ አይሁድ ብሉይ ኪዳን ብቻ ነበራቸው። ከትልልቆቹ መጻሕፍት እያንዳንዱ ረጅም የብራና ጥቅልል ሆኖ ለብቻው ይገኝ ነበር፤ ብራናም ተለስልሶ ቃላቱ የሚጻፉበት ከበግ ቆዳ የተሠራ ሉህ ነው። ከትንንሾቹ መጻሕፍት ብዙዎቹ በአንድ ጥቅልል ላይ ይጻፉ ነበር። በትምህርት ቤቱ ለተማሪዎቹ ሁሉ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ብቻ ነበረ፤ እያንዳንዱ ልጅ ግን ሰሌዳና ጠመኔ ነበረው፤ በእርሱም ከመጽሐፍ ቅዱስ ዓረፍተ ነገሮችን ጽፎ በቃሉ ያጠናቸው ነበር። ጥቅሱን ካጠና በኋላ እያንዳንዱ ተማሪ ሰሌዳውን አጽድቶ አዲስ ትምህርት ይጽፍበት ነበር። በአይሁድ ትምህርት ቤት ትምህርቱ ሁሉ ከብሉይ ኪዳን ነበር።

በትምህርት ቤቱ የነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ አብዛኛውን ጊዜ እስኪያረጅና እስኪያልቅ ድረስ በምኵራብ ሲያገለግል የኖረ ነበር። ለምኵራቡ አገልግሎት አዲስ የመጻሕፍት ስብስብ ሲያገኙ አሮጌዎቹን ቅጂዎች ለትምህርት ቤቱ ይሰጡ ነበር።

ኢየሱስ ልጅ በነበረበት ዘመን እንደ ነበሩት ያሉ ልጆች የሚማሩበትን ትምህርት ቤት ዛሬም በዚያው አገር ልታይ ትችላለህ። ልጆቹ በወለሉ ላይ በክብ ይቀመጣሉ፤ መምህሩም ከክቡ አንዱ ሆኖ ይቀመጣል። ጥቅሶቻቸውን ለማጥናት ሲደጋግሙ ሁሉም በአንድ ጊዜ ጮክ ብለው ስለሚናገሩ ትምህርት ቤቱ እጅግ ጫጫታ ይበዛበታል። እኛ በእንዲህ ያለ ጩኸት ማጥናት አንችልም፤ እነርሱ ግን ግድ የሚሰጣቸው አይመስሉም።

በዚያ አገር ትምህርት ብዙም አስቸጋሪ አልነበረም። የእኛ ልጆች በየሳምንቱ ከትምህርት ነጻ የሆነ አንድ የዕረፍት ቀን አላቸው፤ ኢየሱስ በተማረበት ትምህርት ቤት ግን ከሰንበት በተጨማሪ በየሳምንቱ ሁለት የዕረፍት ቀናት ነበሩአቸው። ከእነዚህ የዕረፍት ቀናትም በተጨማሪ በየቀኑ እኩለ ቀን ላይ የሦስት ሰዓት ረጅም ዕረፍት ነበር፤ ቀኑ እጅግ ሞቃት ከሆነም ትምህርት ፈጽሞ አይኖርም ነበር።

ኢየሱስ ትንሽ ልጅ በነበረ ጊዜ አባቱ ዮሴፍ ወደ ጸሎት ቤቱ፥ እንደምታስታውሱት ምኵራብ ወደሚሉት፥ ይወስደው ነበር። ወንዶችና ወንዶች ልጆች በወለሉ ላይ በምንጣፍ ወይም በሰሌን ላይ ይቀመጡ ነበር፤ ሴቶችና ሴቶች ልጆች ግን ቁልቁል እያዩአቸው በሰገነት ላይ ይሆኑ ነበር። ወንዶችና ወንዶች ልጆች ሁሉ በጸሎት ቤቱ ውስጥ ራሳቸውን ተሸፍነው ይቀመጡ ነበር፤ መሸፈኛቸውም በራሳቸው ላይ የሚጠመጠም የጨርቅ ጥምጥም ነበር። ነገር ግን እያንዳንዱ በበሩ ሲገባ ጫማውን ወይም ነጠላ ጫማውን ያወልቅ ነበር፤ በአምልኮውም ሰዓት በጸሎት ቤቱ ውስጥ በባዶ እግሩ ይሆን ነበር። በአምልኮ ሰዓት በዚያ አገር ወዳለው የእስላሞች የጸሎት ቤት፥ መስጊድ ወደሚሉት፥ ብትሄድ ጫማዎቹ ሁሉ በበሩ ውጭ ቆመው ታያለህ።

በጸሎት ቤቱ አገልግሎቱን የሚመራና ስብከት የሚሰብክ አገልጋይ አልነበራቸውም። ወንዶቹ እየተፈራረቁ አምልኮውን ይመሩ ነበር። አንዱ ከብሉይ ኪዳን አንዱን ክፍል፥ ሌላውም ሌላውን ክፍል ያነብ ነበር። ጥሩ አንባቢ የሆነ ልጅ ካገኙ በአገልግሎቱ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነብ ብዙ ጊዜ ይጠሩት ነበር። ሁልጊዜ ከመጽሐፍ የሚነበቡ ጸሎቶች ነበሩአቸው፤ ከመዝሙረ ዳዊትም በአንድነት ይዘምሩ ነበር፤ መናገር የሚፈልግ ሁሉ ሊናገር ይችል ነበር።

ነገር ግን ሕፃኑ ኢየሱስ ሁልጊዜ በትምህርት ቤት ወይም በጸሎት ቤት ብቻ እንደ ነበረ ማሰብ የለብንም። እርሱ ብርቱ፥ ደስተኛና ጤናማ ልጅ ነበረ። የውጭ ሕይወትን ይወድ ነበር፤ በሜዳ የሚበቅሉትን አበቦችና በአየር የሚበርሩትን ወፎች ያውቅ ነበር። ከሌሎች ልጆች ጋር ይጫወት ነበር፤ ጨዋታዎቻቸውንም ሁሉ ያውቅ ነበር። ከእነዚህ ጨዋታዎች ሁለቱን ከብዙ ዘመን በኋላ ሲያስተምር በአጋጣሚ ጠቅሶአቸዋል። አንዱ ጨዋታ ሰርግ ነበረ፤ በእርሱም ይዘምሩና ይዘፍኑ ነበር፤ ሌላው ለቅሶ ነበረ፤ በእርሱም በታላቅ ድምፅ እያለቀሱ የሐዘን ዋይታ ያሰሙ ነበር። በዚያ ዘመን ልጆች ኳስና ጠጠር፥ እንዲሁም እንደ ቦሊንግ ያለ ጨዋታ ይጫወቱ እንደ ነበር ደግሞ እናውቃለን።

ኢየሱስ ተለይቶ ለብቻው የሚኖር ብቸኛ ልጅ አልነበረም። ሌሎች በዙሪያው እንዲሆኑ ሁልጊዜ ይወድ ነበር። ሰው በሆነ ጊዜ በምድሪቱ ሁሉ እየተዘዋወረ ሲያስተምር ሁልጊዜ ከእርሱ ጋር የነበሩ የመረጣቸው አሥራ ሁለት ወዳጆች ነበሩት፤ ስለዚህ በልጅነቱም ከሌሎች ልጆች ጋር መሆን ይወድ እንደ ነበረ፥ የመንደሩ ልጆችም በተራቸው ይወዱት እንደ ነበረ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።

ደግሞም በቤት፥ በትምህርት ቤትና በጨዋታ ሁልጊዜ ትክክል የሆነውን ለማድረግ የሚጥር መልካም ልጅ ሆኖ እንዳደገ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። በቤት ዮሴፍን በመሥሪያ ቤቱ፥ እናቱንም በሥራዋ ወይም ታናናሾቹን ልጆች በመጠበቅ ይረዳ ነበር፤ በትምህርት ቤት የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅሶች እንዳጠና እናውቃለን፤ በኋለኞቹ ዓመታት ሁልጊዜ ሊያስታውሳቸውና ሊናገራቸው ይችል ነበርና፤ በጨዋታም ሁልጊዜ ቅን፥ ደግ ልብ ያለውና ፈቃደኛ ነበረ። በዕውቀትና በእግዚአብሔር በሰውም ሁሉ ዘንድ በሞገስ ያድግ እንደ ነበረ ተነግሮናል። በሌላ አነጋገር ሰው ሁሉ የሚወደው ልጅ ነበረ።


ቀዳሚ ቀጣይ