የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
በግብፅ ተጠብቆ

ምዕራፍ 11 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ

በግብፅ ተጠብቆ

ማርያምንና ሕፃንዋን ከጎበኙ በኋላ በዚያች ሌሊት ጥበበኞቹ ሕልም አዩ። በሕልማቸውም የእግዚአብሔር ድምፅ እንዲህ ሲላቸው ሰሙ፦

«ንጉሡን ሄሮድስን ለመገናኘት ዳግመኛ አትሂዱ። እርሱ የዚህ ልዑል ሕፃን ወዳጅ አይደለም። በሌላ መንገድ ወደ አገራችሁ ተመለሱ፤ ሄሮድስም እንዲያውቅ አታድርጉ።»

ጥበበኞቹም የጌታን ድምፅ ታዘዙ። የሚሄዱበትን መንገድ ለማንም ሳይነግሩ በጸጥታ ከቤተ ልሔም ወጡ፤ በሄሮድስ ከተማም ሳያልፉ ወደ አገራቸው፥ ወደ ሩቂቱ ጳርቴ፥ ተመለሱ።

ጥበበኞቹ እንደ ሄዱ በዚያች ሌሊት ዮሴፍም ሕልም አየ። በአልጋው አጠገብ መልአክ አየ፤ መልአኩም ዮሴፍን እንዲህ አለው፦

«ፈጥነህ ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ በተቻለህ ፍጥነት ወደ ግብፅ ምድር ውረድ፤ እንድትወጣ እስክነግርህም ድረስ በዚያ አገር ተቀመጥ፤ ንጉሡ ሄሮድስ በቅርቡ ይህን ሕፃን ሊገድለው ይሞክራልና።»

ዮሴፍም አንዲት ቅጽበት ሳይቈይ ማርያምን ከእንቅልፍዋ ቀሰቀሳት፤ የተኛውን ሕፃን ይዘውም በሌሊት ከቤቱ ወጡ። በጨለማው የቤተ ልሔም መንገዶች በጸጥታ አልፈው ወደ ግብፅ የሚወስደውን መንገድ አገኙ። አንዳንድ ጊዜ ማርያም የተወደደ ልጅዋን ይዛ በአህያ ላይ ተቀምጣ ትሄድ ነበር፤ አንዳንድ ጊዜም ዮሴፍ ጓዛቸውን የተሸከመውን እንስሳ ሲመራ እርስዋ በእግርዋ ትሄድ ነበር። ወደ ግብፅ የሚወስደው መንገድ ከመቶ ማይል የሚበልጥ ነበር፤ ነገር ግን ንጉሡ ሄሮድስ ሳያውቅ በሰላም ደረሱ።

ግብፅ የሄሮድስ መንግሥት ክፍል ስላልነበረች በዚያ በሰላም ሊኖሩ ይችሉ ነበር። ብዙ አይሁድ በዚያ ይኖሩ ነበር፤ ዮሴፍም የተዋጣለት የእንጨት ሠራተኛ ስለ ነበረ በመካከላቸው በሙያው ሊተዳደር ይችል ነበር። በግብፅ ምን ያህል ጊዜ እንደ ቈዩ አናውቅም፤ ጥቂት ወራት ወይም ጥቂት ዓመታት ሊሆን ይችላል።

ሄሮድስ ጥበበኞቹን እንደ ገና ለማየትና ሕፃኑ ንጉሥ የት እንደሚኖር ለማወቅ ለተወሰነ ጊዜ ጠበቀ። ነገር ግን ቀናት እያለፉ ምንም ሳይሰማ ሲቀር፥ በመጨረሻም መጥተው እንዲያዩት የሰጣቸውን ትእዛዝ ሳይፈጽሙ ወደ አገራቸው እንደ ሄዱ በተረዳ ጊዜ እጅግ ተቈጣ። ቢኖር መንግሥቱን ከእርሱ ወይም ከቤተሰቡ ሊወስድ የሚችለውን ይህን ሕፃን ለመግደል ግን ቈርጦ ነበር።

ሄሮድስ እጅግ የሚያስፈራ ክፉ ሥራ አቀደ፤ ፈጸመውም፤ ይሁን እንጂ ቀደም ብሎ ከሠራቸው ከብዙዎቹ ሥራዎች የከፋ አልነበረም። በመንደሩ ወዳለው ቤት ሁሉ እንዲገቡ፥ ሁለት ዓመት የሆነውንና ከዚያም በታች የሆነውን ሕፃን ሁሉ ፈልገው ሁሉንም እንዲገድሉ አዝዞ የወታደሮች ጭፍራ ወደ ቤተ ልሔም ላከ። ወታደሮቹም ይህን አሰቃቂ ነገር አደረጉ፤ ልጆቻቸው በክፉው ንጉሥ ትእዛዝ ከተገደሉባቸው እናቶችና አባቶችም ታላቅ ልቅሶ ወደ ሰማይ ወጣ።

ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር ለመዋጋት የሚደረግ ሙከራ ሁሉ ከንቱ እንደሚሆን፥ ሄሮድስ ሕፃናቱን መጨፍጨፉ ከንቱ ሆነ። ሄሮድስ ይህ ንጉሣዊ ሕፃን በቤተ ልሔም ከሞቱት ከእነዚያ ትንንሽ ሬሳዎች መካከል በእርግጥ ይገኛል፤ ዙፋኔም ተጠብቋል ብሎ አሰበ። በዚያን ጊዜ ግን ትንሹ ኢየሱስ በግብፅ ነበረ፤ በዓባይ ወንዝ አጠገብ ከዘንባባ ዛፎችዋ በአንዱ ሥር ተኝቶ፥ ወይም በጥንት ዘመን ከድንጋይ የተቀረጹትን ድንቅ ሥራዎች ፒራሚዶችንና ስፊንክስን በሕፃን ዓይኖቹ አፍጥጦ እየተመለከተ ነበር።

ሄሮድስ ከዚህ በኋላ ብዙ አልኖረም። በዕድሜ ጠግቦ፥ በክፋት ተሞልቶ፥ ታላቅ ሥቃይም እየተሰቃየ ሞተ። ከዚያም ዮሴፍ በግብፅ እንደ ገና ሕልም አየ። ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ ያየው መልአክ ዳግመኛ መጥቶ እንዲህ አለው፦

«ዮሴፍ ሆይ፥ ሕፃኑን ሊገድሉ የፈለጉት ሞተዋልና፥ ምንም ሊያደርጉበትም አይችሉምና፥ አሁን ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ አይሁድ ምድር ልትመለስ ትችላለህ።»

ዮሴፍም እንደ ቀድሞው በአህያው ላይ ኮርቻ አስሮ ጓዛቸውን በጀርባው ላይ ጫነ። ትንሹ ቤተሰብም ወደ ይሁዳ ምድር ለመመለስ ጕዞውን ጀመረ። የዮሴፍና የማርያም አሳብ ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ቤተ ልሔም ተመልሰው፥ አንድ ቀን በዳዊት ዙፋን ላይ የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ ይቀመጣል ብለው የሚጠብቁትን ይህን ሕፃን በዚያ ማሳደግ ነበር። በመንገድ ላይ ግን ሌሎች መንገደኞችን አግኝተው እንዲህ ብለው ጠየቁአቸው፦

«ሄሮድስ ስለ ሞተ አሁን በይሁዳ የሚነግሠው ማን ነው?» እነርሱም ዮሴፍን እንዲህ አሉት፦

«አሁን በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ የነገሠው የአረጋዊው ንጉሥ የሄሮድስ ልጅ አርኬላዎስ ነው፤ እርሱም ከእርሱ በፊት እንደ ነበረው እንደ አባቱ ክፉና ጨካኝ ነው።»

ይህ ወሬ ዮሴፍንና ማርያምን ወደ ቤተ ልሔም ለመሄድ አስፈራቸው። «ምናልባት ንጉሡ አርኬላዎስ ስለ ሕፃኑ ስለ ኢየሱስ ሰምቶ ሊገድለው አጋጣሚ ይጠባበቅ ይሆናል» ብለው አሰቡ።

ስለዚህ ወደ ቤተ ልሔምም ሆነ ወደ ኢየሩሳሌም ላለመቅረብ፥ አርኬላዎስ ከሚገዛው ምድርም ርቀው ሁለቱም ከመጋባታቸው በፊት ይኖሩባት ወደ ነበረችው ወደ ናዝሬት ለመመለስ ቈረጡ። እንዲህም በይሁዳ ቤተ ልሔም የተወለደው ኢየሱስ በገሊላ ናዝሬት አደገ።


ቀዳሚ ቀጣይ