የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ከተነሣው ክርስቶስ ጋር የነበሩ ሁለት የእሑድ ምሽቶች

ምዕራፍ 102 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

ከተነሣው ክርስቶስ ጋር የነበሩ ሁለት የእሑድ ምሽቶች

ኢየሱስ በመስቀል ላይ ከሞተ በኋላ በእርሱ ያመኑ ሁሉ የሚሰበሰቡበት ስፍራ ኢየሱስ የመጨረሻውን እራት የበላበት የሰገነቱ ክፍል የነበረ ይመስላል። በዚያ ከቀን ወደ ቀን ይገናኙ ነበር፤ ሁለቱ ሰዎችም ከኤማሁስ ከኢየሱስ ጋር የተገናኙበትን ወሬ ይዘው የመጡት ወደዚሁ ስፍራ ነበር። በእሑድ ማታ፥ በመጀመሪያው የትንሣኤ ቀን፥ የኢየሱስ ተከታዮች በዚህ ክፍል ተሰብስበው ነበር። ከክርስቶስ ዐሥራ አንድ ደቀ መዛሙርት ዐሥሩ በዚያ ነበሩ፥ ቶማስ ግን አልነበረም፤ ከእነርሱም ጋር ሴቶቹና በኢየሱስ ያመኑ ሌሎች ብዙ ሰዎች ነበሩ።

የአይሁድን አለቆችና ሕዝቡን ስለ ፈሩ ወደዚህ ክፍል የሚያስገቡት ደጆች ተዘግተውና ተቈልፈው ነበር። ኢየሱስ ስለ መነሣቱና ስለ መታየቱ ስለ ደረሳቸው ስለ እነዚህ ወሬዎች እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ ሳሉ ድንገት ኢየሱስ ራሱ በክፍሉ መካከል ቆሞ አዩት። እንዲህም አላቸው፦

«ሰላም ለእናንተ ይሁን!»

መጀመሪያ ባዩት ጊዜ ደነገጡ፤ ያዩት ሕያው ኢየሱስን ሳይሆን የሞተውን የኢየሱስን ጥላ ወይም መንፈስ መሰላቸውና።

«ስለ ምን እንዲህ ትደነግጣላችሁ?» አላቸው ኢየሱስ፥ «ስለ ምንስ ጥርጥር ወደ ልባችሁ ይመጣል? እጆቼንና እግሮቼን እዩ። እኔ ራሴ ነኝ። ዳስሳችሁ እዩኝ፤ በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና!»

ይህንም ብሎ በመስቀል ላይ የተቸነከረባቸው የችንካሮቹ ቀዳዳዎች ገና ያሉባቸውን እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። አሁንም ቢሆን ኢየሱስን ማየታቸው እውነት ለመሆን እጅግ መልካም ነገር መሰላቸው፤ ሕያው ሆኖ ያዩት ጌታቸው እንደ ሆነም ለማመን አቃታቸው። እንዲህም አላቸው፦

«በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁን?»

እነርሱም የተጠበሰ ዓሣ ቁራጭ አመጡለት፤ እነርሱም እያዩ በላው። ይህን ያደረገው ተርቦ ምግብ ስላስፈለገው አልነበረም፤ ከእንግዲህ ምንም አያስፈልገውም ነበርና፤ ነገር ግን በእውነት ሕያው መሆኑን ሊያሳያቸው ብቻ ነበር።

ከዚያም በኋላ ከእንግዲህ አልፈሩም፤ ጌታቸው ሕያው ሆኖ ከእነርሱ ጋር እንዳለ ፈጽመው አመኑ፤ ልባቸውም በደስታ ተሞላ። ኢየሱስም ዳግመኛ እንዲህ አላቸው፦

«ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ።»

ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና እንዲህ አለ፦ «የእግዚአብሔርን መንፈስ ቅዱስ ተቀበሉ! የሰዎችን ኃጢአት ብታስወግዱ እኔ ራሴ ይቅር እንዳልኋቸው ከእነርሱ እንዲወገድላቸው ሥልጣን እሰጣችኋለሁ፤ ኃጢአታቸውን ባታስወግዱ ግን የኃጢአታቸው በደል በላያቸው ይኖራል።»

በዚያ ማታ ኢየሱስ ከተከታዮቹ ጋር ለጥቂት ጊዜ ከተነጋገረ በኋላ እንደ መጣው ድንገት ተሰወረ። ይህም ከመቃብሩ በተነሣበት በዚያ ቀን አምስተኛው መገለጡ ነበር።

ነገር ግን እንዳየነው ከኢየሱስ ዐሥራ ሁለት ደቀ መዛሙርት አንዱ ቶማስ በዚያ ማታ ከሌሎቹ ጋር አልነበረም፤ ስላልነበረም የተነሣውን ኢየሱስን አላገኘውም። ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት እንዲህ አሉት፦

«ጌታን አይተነዋል!»

ቶማስ ግን አላመናቸውም። ሁሉም እንደ ተሳሳቱ አሰበና እንዲህ አለ፦

«በመስቀሉ ላይ የተቸነከረበትን የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ፥ ጣቴንም በዚያ በችንካሩ ምልክት ካላገባሁ፥ በጎኑም በጦሩ የተወጋውን ቍስል እጄን ካላገባሁ፥ ሕያው መሆኑን አላምንም!»

ከሳምንት በኋላ በሚቀጥለው እሑድ ማታ ሁሉም እንደ ገና በሰገነቱ ክፍል ተሰበሰቡ፤ በዚህ ጊዜም ቶማስ በዚያ ነበረ። ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ ዳግመኛ መጥቶ በመካከላቸው ቆመ፤ እንደ ቀድሞውም «ሰላም ለእናንተ ይሁን!» አላቸው።

ቶማስንም ተመልክቶ እንዲህ አለው፦

«እጆቼን እይ፥ ጣትህንም በዚያ አግባ፤ ጎኔንም እይ፥ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው። ሕያው መሆኔን ለማመን ከእንግዲህ እምቢ አትበል፥ ነገር ግን በእኔ እመን።»

ቶማስም መልሶ «ጌታዬ አምላኬም!» አለው።

«ስላየኸኝ ነውን በእኔ ያመንኸው?» አለ ኢየሱስ። «ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው!»

የተወደደው ደቀ መዝሙር ዮሐንስ ኢየሱስን ሕያው ሆኖ ከማየቱ በፊት ወደ ባዶው መቃብር በተመለከተ ጊዜ ኢየሱስ እንደ ተነሣ እንዳመነ ታስታውሳላችሁ።

ይህ በሁለተኛው እሑድ ማታ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የተደረገው ስብሰባ ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ስድስተኛው መገለጡ ነበር።


ጨርሰዋል፦ ከተነሣው ክርስቶስ ጋር የነበሩ ሁለት የእሑድ ምሽቶች

ቀዳሚ ቀጣይ