የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ከተነሣው ክርስቶስ ጋር የተደረገ ጕዞ

ምዕራፍ 101 · 3 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

ከተነሣው ክርስቶስ ጋር የተደረገ ጕዞ

ኢየሱስ ከመቃብሩ ከተነሣ በኋላ በታየ ጊዜ ለአንድ ሰው ስለ ተገለጠ ያ «መገለጥ» ተብሎ ተጠራ። እንዳነበባችሁት የመጀመሪያው መገለጡ ለመግደላዊት ማርያም ነበር፤ ሁለተኛው መገለጡ ለሌሎቹ ሴቶች ነበር፤ ሦስተኛው መገለጡም በዚያ በመጀመሪያው የትንሣኤ ጠዋት ወደ ገጠር ይሄዱ ለነበሩ ለሁለት ሰዎች ነበር።

እነዚያ ሁለት ሰዎች ከኢየሱስ ዐሥራ ሁለት ደቀ መዛሙርት አልነበሩም፤ ነገር ግን እርሱ ክርስቶስ፥ የእስራኤል ንጉሥ እንደ ሆነ አምነው ነበር። ከእነርሱ አንዱ ቀለዮጳ ይባል ነበር፤ የሌላው ስም ግን ይህ ታሪክ በተነገረበት በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል አልተጻፈም። ሁለቱ ሰዎች በዚያ ጠዋት ከኢየሩሳሌም ወጥተው ከከተማይቱ ስድስት ወይም ሰባት ማይል ያህል ወደሚርቀው ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር። ሲሄዱም ስለ ኢየሱስ፥ ስለ ሞቱ፥ ስለ መቀበሩና እንደ ገና ሕያው ሆኖአል ብሎ አሁን ስለ ደረሳቸው ወሬ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር።

እየሄዱና እየተነጋገሩ ሳሉ ድንገት ሌላ ሰው ከእነርሱ ጋር ሲሄድ አዩ። ይህ እንግዳ ኢየሱስ ነበረ፤ ነገር ግን መግደላዊት ማርያም ኢየሱስን በመጀመሪያ ባየችው ጊዜ እንዳላወቀችው እነርሱም አላወቁትም። እንዲህም አላቸው፦

«እየሄዳችሁ የምትነጋገሩበት ነገር ምንድር ነው?»

እነርሱም ፊታቸው አዝኖ ቆሙ፤ ቀለዮጳም ለዚህ እንግዳ መለሰለት።

«እንዴት!» አለ ቀለዮጳ፥ «በእነዚህ ጥቂት ቀኖች በኢየሩሳሌም የሆነውን ነገር ያልሰማህ ትመስላለህና በዚያ ለብቻህ ትኖራለህን?»

«ምን ነገር ነው የምትሉት?» ብሎ ጠየቀ እንግዳው።

«ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ ነዋ፤» ብለው መለሱለት። «ስለ እርሱ ፈጽሞ አልሰማህምን? በሕዝቡ ሁሉ ፊት እግዚአብሔር በቃሉና በሥራው ኃይል የሰጠው ድንቅ ነቢይ ነበረ። ነገር ግን የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን ያዙት፥ የሞት ፍርድም እንዲፈረድበት አሳልፈው ሰጡት፥ ሰቀሉትም። እኛ ግን እስራኤልን ከጠላቶቹ ነጻ የሚያወጣና ንጉሣችን ሆኖ የሚገዛ እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር። አሁንም ከሞተ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው፤ በዚህም ጠዋት ከእኛ ወገን የሆኑ አንዳንድ ሴቶች እጅግ ያስገረመንን ወሬ አመጡልን። ማልደው ወደ መቃብሩ ሄዱ፤ ተከፍቶም አገኙት፥ ሥጋውን ግን በውስጡ አላገኙም። ኢየሱስ ሕያው ነው ያሉአቸውን መላእክት እንዳዩ ነገሩን! ወዲያውም ከእኛ ሰዎች አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ ሄዱ፤ ሴቶቹም እንደ ተናገሩት መቃብሩ ተከፍቶ ሥጋውም ጠፍቶ አገኙት፤ ኢየሱስን ግን አላዩትም።»

«እናንተ የማታስተውሉ፥ ነቢያት በቅዱሱ መጽሐፍ የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ!» አለ የተነሣው ኢየሱስ የሆነው እንግዳ። «ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ወደ ክብሩ ከመግባቱ በፊት ይህን ሁሉ መከራ ሊቀበል እንደሚገባው አታውቁምን?»

ከዚያም በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ፥ ሙሴ በሕጉ፥ ዳዊት በመዝሙራቱ፥ ነቢያትም ሁሉ በጽሑፎቻቸው ክርስቶስ በመጣ ጊዜ በእርሱ ላይ የሚሆነውን ነገር እንዴት አስቀድመው እንደ ተናገሩ ያሳያቸው ጀመር፤ ይህም ሁሉ በኢየሱስ ላይ እንደ ተፈጸመ፥ የናዝሬቱ ኢየሱስም በእውነት የእግዚአብሔር ልጅና የእስራኤል ንጉሥ እንደ ሆነ አሳያቸው።

እየተነጋገሩ ሲሄዱ ሁለቱ ሰዎች ወደሚሄዱበት ወደ ኤማሁስ መንደር ቀረቡ። ማንነቱ ያልታወቀው ኢየሱስ ወደ ፊት የሚሄድ መሰለ፤ እነርሱ ግን እንዲያርፍ ለመኑት።

«ከእኛ ጋር እደር፤» አሉት፥ «ማታ ቀርቦአልና፤ ፀሐይም ልትጠልቅ ነው።»

ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ወደ መንደሩ፥ ወደ ቤቱም ገባ። ለእራትም ተቀመጡ፤ እንግዳውም እንጀራውን አንሥቶ ባረከው፥ ቈርሶም ሰጣቸው። በዚያው ቅጽበት ዓይናቸው ተከፈተ፥ ማን እንደ ሆነም አወቁ፤ መምህራቸው ኢየሱስ ነበረ! በዚያው ቅጽበት ግን ከዓይናቸው ተሰወረ።

«በመንገድ ሲናገረን በቅዱሱ መጽሐፍ የተባለውንም ሲያስረዳን ልባችን እንዴት ይቃጠልብን ነበር!» ተባባሉ።

ወዲያውም ከማዕዱ ተነሥተው ፈጥነው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የመጨረሻውን እራት በበላበት በኢየሩሳሌም ባለው በሰገነቱ ክፍል አንዳንድ ደቀ መዛሙርትንና ሌሎችን አገኙ። ቀለዮጳና ወዳጁ ታሪካቸውን ለመናገር ዕድል ሳያገኙ በክፍሉ የነበሩት እንዲህ አሉአቸው፦

«ጌታ በእውነት ተነሥቶአል፤ ለስምዖን ጴጥሮስም ታይቶአል!»

ከዚያም ሁለቱ የኤማሁስ ሰዎች እንግዳው በመንገድ ከእነርሱ ጋር እንዴት እንደ ሄደና ከብሉይ ኪዳን ብዙ ነገር እንደ ነገራቸው፥ እንጀራውንም ሲባርክና ሲቈርስ ድንገት ኢየሱስ መሆኑን እንዴት እንዳወቁ ተረኩ።

እነዚህ የኢየሱስ ሦስተኛውና አራተኛው መገለጦች ነበሩ፤ ሦስተኛው ለስምዖን ጴጥሮስ ነበረ፥ ኢየሱስ ያለው ግን አልተጻፈም፤ አራተኛውም ወደ ኤማሁስ በሚወስደው መንገድ ለቀለዮጳና ለወዳጁ ነበረ።


ቀዳሚ ቀጣይ