ምዕራፍ 3 · 7 ደቂቃ ንባብ · 10 ደቂቃ ማዳመጥ
እግዚአብሔር ለቅድስና ያዘጋጀው
ሁለተኛ ቀን።
«በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት፥ ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት።»—1ኛ ቆሮ. 1፥2።
«በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ቅዱሳን ሁሉ። ለቅዱሳን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ሰላምታ አቅርቡ።»—ፊልጵ. 1፥1፤ 4፥21።
ቅዱስ! በክርስቶስ! በእነዚህ በሁለቱ አገላለጾች ምናልባት በመጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ ውስጥ እጅግ አስደናቂ የሆኑት ቃላት አሉን።
ቅዱስ! ሱራፌል ፊታቸውን ሸፍነው የሚናገሩት፥ ጥልቀቱ የማይመረመር ቃል። ቅዱስ! የእግዚአብሔር ፍጹምነቶች ሁሉ የሚያተኩሩበት፥ ክብሩም ከእርሱ የሚፈልቅ ጅረት ብቻ የሆነለት ቃል። ቅዱስ! እግዚአብሔር ከዘላለም ስለ ሰው ያሰበበትን ዓላማ የሚገልጥ፥ በሚመጣውም ዘላለም የሰው ከፍተኛ ክብር ምን እንደሚሆን የሚናገር ቃል፤ ይኸውም የቅድስናው ተካፋይ መሆን ነው!
በክርስቶስ! የእግዚአብሔር ጥበብና ፍቅር ሁሉ የተገለጠበት ቃል! አብ ከእኛ ጋር አንድ ይሆን ዘንድ ልጁን ሰጠ! ወልድ ከራሱ ጋር አንድ ሊያደርገን በመስቀል ላይ ሞተ! የአብ መንፈስ ቅዱስ ያንን አንድነት ሊያጸናና ሊጠብቅ በእኛ ያድራል! በክርስቶስ! ቤዛነት ያደረገውን ሁሉ፥ የእግዚአብሔር ልጅ እንዲኖርበት የተፈቀደለትንም ሊታሰብ የማይቻል የተባረከ ሕይወት እንዴት ያለ ያጠቃልላል! በክርስቶስ! በምድር ላይ ልናጠናው የሚገባን ብቸኛ ትምህርት። ለፍላጎታችንና ለጸሎታችን ሁሉ የእግዚአብሔር ብቸኛ መልስ። በክርስቶስ! የዘላለም ክብር ዋስትናና ቅምሻ።
በሁለቱ ቃላት ኅብረት እንዴት ያለ የትርጉምና የበረከት ባለጠግነት አለ፤ በክርስቶስ ቅዱሳን! እግዚአብሔር ለቅድስናችን ያዘጋጀው፥ «እንዴት ቅዱሳን እንሆናለን?» ለሚለው ጥያቄያችን የእግዚአብሔር መልስ ይኸው ነው። «እናንተ ቅዱሳን ሁኑ፥ እኔ ቅዱስ እንደ ሆንሁ» የሚለውን ጥሪ ደጋግመን ስንሰማ፥ በእግዚአብሔርና በሰው ቅድስና መካከል ታላቅ ገደል ያለ፥ ሁልጊዜም የሚኖር ይመስላል። በክርስቶስ! ገደሉን የሚያሻግር ድልድይ ነው፤ ይልቁንም ሙላቱ ገደሉን ሞልቶታል። በክርስቶስ! እግዚአብሔርና ሰው ይገናኛሉ፤ በክርስቶስ! የእግዚአብሔር ቅድስና አግኝቶናል፥ የራሱም አድርጎናል፤ ሰው ሆኖአል፥ በእውነትም የገዛ ራሳችን ሊሆን ይችላል። በኢየሱስ አምነው ሳሉ እንዴት ቅዱሳን እንደሚሆኑ ለማያውቁ በሺህ የሚቆጠሩ የተጠሙ ነፍሳት የጭንቀት ጩኸትና የልብ ናፍቆት የእግዚአብሔር መልስ ይኸው ነው፤ እናንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ቅዱሳን ናችሁ። ቢያደምጡና ቢያምኑ፥ እነዚህን የመለኮት ቃላት ይዘው ቢያስፈልግ ሺህ ጊዜ ቢደጋግሟቸው፥ «አዎን፥ አሁን አየሁት። በክርስቶስ ቅዱስ! በክርስቶስ ኢየሱስ የተቀደስሁ!» ብለው መልሰው ሲያስተጋቡአቸው የእግዚአብሔር ብርሃን እንዴት ባበራ፥ ልባቸውንም በደስታና በፍቅር በሞላ ነበር!
እነዚህን አስደናቂ ቃላት ለማጥናት ስንነሣ፥ ቅድስና በእውነት ምን እንደ ሆነ ሊገልጥልን የሚችል እግዚአብሔር ራሱ ብቻ እንደ ሆነ እናስብ። የገዛ አሳባችንን እንፍራ፥ የገዛ ጥበባችንንም እንስቀል። በመንፈስ ቅዱስ በእኛ በሚሠራው በእግዚአብሔር ሕይወት ኃይል፥ ከሰው አሳብ ይልቅ የጠለቀውንና እውነት የሆነውን፥ ቅድስናችን የሆነውን ክርስቶስን ራሱን ለመቀበል ራሳችንን እንስጥ። በዚህ በቅድስና መንፈስ ትምህርት በመደገፍ፥ መጽሐፍ ቅዱስ በፊታችን የሚያኖረውን በቀላሉ ለመቀበል እንፈልግ፤ የጥንቱ የቅዱሱ መገለጥ እጅግ ዝግተኛና ቀስ በቀስ የሆነ እንደ ነበረ፥ እንዲሁ እኛም በቃሉ ውስጥ የሚያበራውን የብርሃን መንገድ ደረጃ በደረጃ በትዕግሥት ለመከተል እንርካ፤ ፍጹም ቀን እስኪሆን ድረስ እየበራ ይሄዳል።
በመጀመሪያ «ቅዱስ» የሚለውን ቃል በብሉይ ኪዳን ማጥናት ይኖርብናል። አሁን በክርስቶስ ቅዱሳን ለሆንነው ለእኛ ምሳሌ በሆነው በቅዱሱ ሕዝብ በእስራኤል፥ እግዚአብሔር እንዲሆኑ የሚወደውን በመጠኑ እንዲያስተውሉ በሕዝቡ አቋም ውስጥ ለማስረጽ በምን ያህል የምሳሌ ሙላት እንደ ፈለገ እናያለን። በሕጉ ውስጥ «ቅዱስ» ሕጉ ሊያገለግለውና ሊያዘጋጅለት ለታሰበው ቤዛነት ታላቅ ቍልፍ ቃል እንደ ሆነ እናያለን። በነቢያት ደግሞ የእግዚአብሔር ቅድስና የሚመጣው ቤዛነት የሚፈልቅበት ምንጭ ሆኖ እንዴት እንደ ተገለጠ እንሰማለን፤ የሚናገሩት ስለ ቅድስና ሳይሆን ይልቁንም ስለ ቅዱሱ ነው፤ እርሱም በሚቤዥ ፍቅርና በሚያድን ጽድቅ ራሱን የሕዝቡ አምላክ አድርጎ የሚገልጥ ነው።
የቃሉም ትርጉም በመጠኑ ሲከፈት፥ የበረከቱም ጥልቅ ፍላጎት በብሉይ ኪዳን ሲገለጥ፥ ያ ፍላጎት እንዴት እንደ ተፈጸመ ለማግኘት ወደ አዲስ ኪዳን እንመጣለን። በእግዚአብሔር ቅዱስ በክርስቶስ፥ መለኮታዊ ቅድስና በሰው ሕይወትና በሰው ባሕርይ ይገኛል፤ እውነተኛ ሰብአዊ ፈቃድ ፍጹም ሆኖ በመታዘዝ ከእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ሁሉ ጋር ወደ ሙሉ አንድነት አደገ። በመስቀል ላይ ራሱን በሠዋ ጊዜ፥ ያ ቅዱስ ባሕርይ እንደ ስንዴ ቅንጣት በሞት በኩል እንደ ገና ሕያው ሆኖ በእኛ ራሱን እንዲያበዛ ራሱን ለሞት አሳልፎ ሰጠ። የማይታየውን ክርስቶስ የሚወክለው፥ የሚገልጠውና የሚያካፍለው የእግዚአብሔር የቅድስና መንፈስ ከዙፋኑ ሲሰጥ፥ የክርስቶስ ቅዱስ ሕይወት ወርዶ ሕዝቡን ይይዛል፥ እነርሱም ከእርሱ ጋር አንድ ይሆናሉ። ብሉይ ኪዳን «ቅዱስ» ከሚለው የበለጠ ከፍ ያለ ቃል እንዳልነበረው፥ አዲስ ኪዳንም «በክርስቶስ» ከሚለው የበለጠ ጥልቅ ቃል የለውም። በእርሱ መሆን፥ በእርሱ መኖር፥ በእርሱ ሥር መስደድ፥ በሁሉ ነገር በእርሱና ወደ እርሱ ማደግ፥ በእኛና በመድኃኒታችን መካከል ያለው አስደናቂና ፍጹም አንድነት የሰው ቋንቋ በሚችለው መጠን ወደ እኛ የሚቀርብባቸው መለኮታዊ አገላለጾች ናቸው።
ብሉይና አዲስ ኪዳን እያንዳንዳቸው መልእክታቸውን ሲሰጡ፥ አንዱ ቅዱስ ምን ማለት እንደ ሆነ፥ ሌላው በክርስቶስ ምን ማለት እንደ ሆነ ሲያስተምሩን፥ ሁለቱን በሚያዋሕደው በእግዚአብሔር ቃል የእግዚአብሔር ፍቅር ያዘጋጀውን ታላቁን ቤዛነት እጅግ ፍጹም በሆነ መንገድ ተጠቃልሎ እናገኘዋለን። እግዚአብሔር በልጁ ያዘጋጀልን የቅድስና የዘላለም እርግጠኝነት፥ አስደናቂው በቂነቱ፥ ወሰን የሌለው ኃይሉ ሁሉ በዚህ በተባረከ «በክርስቶስ ቅዱሳን» በሚለው ተገልጦአል።
«በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉ ቅዱሳን!» የተወደዳችሁ አብረን የምናምን ወንድሞች ሆይ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ፥ በመንፈስ ቅዱስ ቋንቋ የምንጠራበት ስም ይህ ነው። በክርስቶስ ቅዱሳን መሆናችን የትምህርት መግለጫ ብቻ አይደለም፤ እንድንገባበት የተጋበዝነው ጥልቅ የሥነ መለኮት ክርክርም አይደለም፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር አፍቃሪ ልብ ጥልቀት የተወደዱ ልጆቹን እንዲህ ብሎ የሚጠራ ድምፅ ይወጣል። አብ ልጆቹን የሚጠራበት ስም ነው። ያ ስም እግዚአብሔር ቅዱሳን እንድንሆን ያዘጋጀውን ይነግረናል። እግዚአብሔር የሰጠንን፥ አሁንም የሆንነውን፥ እግዚአብሔር በእኛ ሊሠራ የሚጠብቀውን፥ በግልና በተግባርም የእኛ ሊሆን የሚችለውን መግለጥ ነው። ያ ስም በምስጋና ሲቀበሉት፥ በደስታ ሲመሰክሩት፥ በመታመን ሲለምኑበት፥ ወደ ተጠራንበት ቅድስና የምንደርስበት መያዣና ኃይል ይሆናል።
ስለዚህ እየገፋን ስንሄድ ጥናታችን ሁሉና የእግዚአብሔር ትምህርት ሁሉ በሦስት ታላላቅ ትምህርቶች እንደሚጠቃለል እናገኛለን። የመጀመሪያው መገለጥ ነው፤ «እኔ ቅዱስ ነኝ፤» ሁለተኛው ትእዛዝ ነው፤ «ቅዱሳን ሁኑ፤» ሦስተኛው በሁለቱ መካከል ያለው ማገናኛ የሆነ ስጦታ ነው፤ «በክርስቶስ ቅዱሳን ናችሁ።»
በመጀመሪያ «እኔ ቅዱስ ነኝ» የሚለው መገለጥ ይመጣል። ጥናታችን በአምልኮ መንፈስና በጥልቅ ትሕትና በተንበረከከ ጉልበት መሆን አለበት። ቅዱስ ምን እንደ ሆነ እናውቅ ዘንድ ከሆነ እግዚአብሔር ራሱን ሊገልጥልን ይገባል። የባሕርያችንና ከባሕርይ የሆነው ሁሉ ጥልቅ ርኵሰት ሊገለጥልን ይገባል፤ ቅዱሱ ለሙሴና ለኢሳይያስ ራሱን በገለጠላቸው ጊዜ እንደ ሆነው፥ እኛም ልንፈራና ልንንቀጠቀጥ፥ ያለ እሳት መንጻት ለመገለጡ ወይም ለኅብረቱ ምን ያህል ፈጽሞ የማንበቃ እንደ ሆንን ልንናዘዝ ይገባናል። እግዚአብሔርን ለማወቅ የገዛ ጥበባችን ወይም ማስተዋላችን ፈጽሞ አቅመ ቢስ እንደ ሆነ ተገንዝበን፥ ነፍሳችን በመጸጸትና ከራሳችን፥ ከኃይላችንና ከጥረታችን ተሰብራ፥ እግዚአብሔርን እንደ ቅዱሱ ይገልጥ ዘንድ ለእግዚአብሔር መንፈስ፥ ለቅድስና መንፈስ ልትገዛ ይገባታል። እርሱንም ወሰን በሌለው ጽድቁ፥ ኃጢአት በሆነው ሁሉ ላይ በሚነድደው በእሳታዊ ቅንዓቱ፥ ኃጢአተኛውን ከኃጢአቱ ነጻ ሊያወጣና ወደ ራሱ ፍጹምነት ሊያመጣው ራሱን በሚሠዋው ወሰን የሌለው ፍቅሩ ማወቅ ስንጀምር፥ በዚህ ክቡር አምላክ መደነቅንና እርሱን ማምለክን፥ ከእርሱ ጋር ያለንን አስፈሪ አለመመሳሰል መሰማትንና ማዘንን፥ በዚህ ቅድስና መለኮታዊ ውበትና ብፅዕና የተወሰነ ድርሻ ለማግኘት መናፈቅንና መጮኽን እንማራለን።
ከዚያም «እኔ ቅዱስ እንደ ሆንሁ ቅዱሳን ሁኑ» የሚለው ትእዛዝ በአዲስ ትርጉም ይመጣል። ወንድሞቼ ሆይ! የአምላካችሁን ትእዛዛት እንታዘዛለን የምትሉ እናንተ፥ ለዚህ ከሁሉ ለሚበልጠውና ሁሉን ለሚያጠቃልለው ትእዛዝ በልባችሁና በሕይወታችሁ የሚገባውን የመጀመሪያ ስፍራ ስጡት። የእግዚአብሔርን ቅድስና በመምሰል ቅዱሳን ሁኑ። እርሱ ቅዱስ እንደ ሆነ ቅዱሳን ሁኑ። ይበልጥ ባሰላሰላችሁና ባጠናችሁ መጠን ይህን ወሰን የሌለውን ቅድስና ለመያዝ አቅማችሁ እያነሰ እንደሚሄድ፥ አልፎ አልፎም ይበልጥ በያዛችሁ መጠን እንዲህ ያለውን መለኮታዊ ቅድስና ለማግኘት ተስፋ እንደምትቆርጡ ብታገኙ፥ እንዲህ ያለው መሰበርና ተስፋ መቁረጥ ትእዛዙ ሊሠራው የታሰበው ይኸው እንደ ሆነ አስቡ። ከገዛ ቸርነታችሁ ብቻ ሳይሆን ከገዛ ጥበባችሁም መተውን ተማሩ፤ የሚጠይቀው ቅድስና ከሰው እውቀት ወይም ከሰው ኃይል ምን ያህል ፈጽሞ በላይ እንደ ሆነ ቅዱሱ ያሳያችሁ ዘንድ በመንፈስ ድሆች ሆናችሁ ቅረቡ፤ ከራስዋ ለምታርፍና በሥጋ ለማትታመን ነፍስ ወደ እርሱ የጠራንን ቅድስና ያሳያታል፥ ይሰጣታልም።
በክርስቶስ ያለው ታላቁ የቅድስና ስጦታ የሚገባውና የሚወደደው ለእንደነዚህ ላሉት ነው። ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ቅድስና በሰው አካሄድና ግንኙነት በማሳየት ያቀርበዋል። በእርሱና በእኛ መካከል፥ በእግዚአብሔርና በእኛ መካከል ያለውን ግድግዳ በማስወገድ ያቀርበዋል። ከራሱ ጋር አንድ ስለሚያደርገን ያቀርበዋል። «በክርስቶስ ቅዱሳን፤» ቅድስናችን በእርሱ ስለ ሆንን ለእኛ የተያዘ፥ ለእኛ የሚሰጥ፥ በእኛም በብርቱ የሚሠራ መለኮታዊ ስጦታ ነው። «በክርስቶስ!» ኦ፥ ያ አስደናቂ በ! ሕይወታችን ራሱ በክርስቶስ ሕይወት ውስጥ ሥር ሰድዶአል። በምድር ላይ በፍቅርና በመታዘዝ ሕይወቱ ውብ የሆነው፥ ስለ እኛ ራሱን የቀደሰው ያ የአብ ቅዱስ ልጅና ባሪያ፥ ያ የክርስቶስ ሕይወት፥ እኔ የተተከልሁበትና ሥር የሰደድሁበት መሬት፥ እያንዳንዱን ጠባዩንና ባሕርዩን እንደ ምግቤ የምቀዳበት አፈር ነው። ያ ቃል «እኔ ቅዱስ ነኝ» በሚለው መገለጥና «እኔ እንደ ሆንሁ ቅዱሳን ሁኑ» በሚለው ትእዛዝ ላይ እንዴት ብርሃኑን ያበራል፥ ሁለቱንም እንዴት በአንድ ያስተሳስራቸዋል! በክርስቶስ የእግዚአብሔር ቅድስና ምን እንደ ሆነ፥ የእኔም ቅድስና ምን እንደ ሆነ አያለሁ። በእርሱ ሁለቱም አንድ ናቸው፥ ሁለቱም የእኔ ናቸው። በእርሱ ቅዱስ ነኝ፤ በእርሱ እየኖርሁና እያደግሁ፥ እግዚአብሔር ቅዱስ እንደ ሆነ በኑሮዬ ሁሉ ቅዱስ መሆን እችላለሁ።
እኔ ቅዱስ እንደ ሆንሁ ቅዱሳን ሁኑ።
እጅግ ቅዱስ አምላክ ሆይ! ወደ ቅድስና መጥራትህ ብቻ ሳይሆን «በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉ ቅዱሳን» በሚለው በዚህ ስም መጥራትህ ምን ማለት እንደ ሆነ ለልጆችህ ግለጥላቸው ብለን እንማልድሃለን። ኦ፥ የአንተ ልጅ ሁሉ ይህን ስም እንደሚሸከም፥ ትርጉሙ ምን እንደ ሆነ፥ ስሙ የሚጠራውን እንዲሆን ሊያደርገው በውስጡ ምን ኃይል እንዳለ ቢያውቅ! ቅዱስ ጌታ አምላክ ሆይ! ኦ፥ የመጎብኘትህ ጊዜ ፈጥኖ ቢመጣ፥ በምድር ያለ የአንተ ልጅ ሁሉ ቅዱስ ሆኖ ቢታወቅ!
ለዚህም ቅድስናህ ምን እንደ ሆነ ለቅዱሳንህ እንድትገልጥ እንለምንሃለን። «እኔ ቅዱስ ነኝ» የሚለውን ቃልህን በመለኮት ኃይል ለነፍሳችን እስክትናገር ድረስ እንድንሰግድና እንድንጠብቅ አስተምረን። ኦ፥ ይመርምረን፥ ስለ ርኵሰታችንም ይውቀሰን!
አንተ የምትበላ እሳት እንኳ ሆነህ ቅዱስ እንደ ሆንህ፥ እንዲሁ ትእዛዝህም ቅዱሳን ሊያደርገን ባለው ቍርጥና ወደ ኋላ በማይል ዓላማው ቅዱስ እንደ ሆነ እንድትገልጥልን እንለምንሃለን። አቤቱ አምላክ ሆይ! ማምለጫ በሌለው ኃይል ድምፅህ በማንነታችን ጥልቀት ይሰማ፤ ቅዱሳን ሁኑ፥ ቅዱሳን ሁኑ።
እንዲሁም በአንድ በኩል ወሰን በሌለው ቅድስናህና በሌላ በኩል በርኵሰታችን መካከል ሆነን፥ ክርስቶስን መቀደሳችን አድርገን እንድንቀበል፥ አንተ እንድንሆን የምትወደውን ለመሆን ሕይወታችንና ኃይላችን አድርገን በእርሱ እንድንኖር እንገፋና እንሳብ፤ «በክርስቶስ ኢየሱስ ቅዱሳን።»
አባት ሆይ! መንፈስህ ይህን የከበረ ቃል በውስጣችን ሕይወትና እውነት ያድርገው። አሜን።
1. የመለኮትን ምሥጢር ለማጥናት እንደ ገና እየገባህ ነው። «በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤» የእውነትን መንፈስ ትምህርት ጠብቅ።
2. በክርስቶስ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ እንዲህ ይላል፤ «አገላለጹ ሁለት ግብረ ገባዊ እውነታዎችን ያመለክታል፤ የመጀመሪያው ሰው ክርስቶስን የሚይዝበት የእምነት ተግባር፥ ሁለተኛው በዚህ እምነት አማካይነት ከእርሱ ጋር የተመሠረተው የሕይወት ኅብረት ነው።» ከሁሉ የሚበልጥ ሌላ እውነታ ደግሞ አለ፤ ይኸውም በክርስቶስ የሆንሁትና በእርሱ የምጠበቀው በመለኮት ኃይል ተግባር መሆኑ ነው። ልገነዘበው የምፈልገው ይህን ነው፤ በኢየሱስ ያለኝ ስፍራ መለኮታዊ መሆኑን።
3. የእውነቱን ሁለት ገጽታዎች ያዝ። በክርስቶስ በመለኮታዊ ቅድስና ቅዱስ ነህ። በዚያ እምነት ቅዱስ ልትሆን፥ በሰብአዊ ቅድስና ቅዱስ እየሆንህ ልትሄድ ይገባሃል፤ ይኸውም በሰው ሕይወት አካሄድ ሁሉ የተገለጠ መለኮታዊ ቅድስና ነው።
4. ይህ ክርስቶስ ሕያው አካል፥ አፍቃሪ መድኃኒት ነው፤ ፈጽሞ ሊይዝህና ሥራውን ሁሉ በአንተ ሊሠራ እንዴት ደስ ይለዋል! እየገፋን ስንሄድ ይህን ሁልጊዜ አጥብቀህ ያዝ፤ ቅዱስ ሊያደርግህ በክርስቶስ፥ በፍቅሩና በኃይሉ ላይ መብት አለህ። የተቤዠው እንደ መሆንህ፥ ምንም ብትሆን የትም ብትሆን በዚህ ሰዓት በእርሱ ነህ። ቅዱስ መገኘቱና ፍቅሩ ከብበውሃል። በእርሱ ነህ፤ በቅዱስ መገኘቱ ሁልጊዜ በሚከብብህ በዚያ ርኅሩኅ ፍቅር ቅጥር ውስጥ ነህ። በተቀበልኸውና በተገነዘብኸው በዚያ መገኘት ቅድስናህ አለ።