ምዕራፍ 2 · 7 ደቂቃ ንባብ · 9 ደቂቃ ማዳመጥ
እግዚአብሔር ወደ ቅድስና መጥራቱ
«የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ ቅዱሳን ሁኑ፥ እኔ ቅዱስ ነኝና ተብሎ ተጽፎአልና።»—1ኛ ጴጥ. 1፥15, 16።
የእግዚአብሔር ጥሪ የዘላለም አሳቡ በጊዜ ውስጥ መገለጡ ነው፤ «አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው።» አማኞች «እንደ አሳቡ የተጠሩት» ናቸው። በጥሪው ስለ እኛ ያለው አሳቡና ፈቃዱ ምን እንደ ሆነ፥ የሚጋብዘንም ወደ ምን ዓይነት ሕይወት እንደ ሆነ ይገልጥልናል። በጥሪው የመጠራታችን ተስፋ ምን እንደ ሆነ ግልጥ ያደርግልናል፤ ይህንንም በመንፈስ ተረድተን ወደ እርሱ ስንገባ፥ በምድር ያለው ሕይወታችን በዘላለም ያለው አሳቡ ነጸብራቅ ይሆናል።
መጽሐፍ ቅዱስ የመጠራታችንን ዓላማ ወይም ግብ ለማመልከት ከአንድ በላይ ቃል ይጠቀማል፤ ነገር ግን ጴጥሮስ እዚህ ከሚናገረው የበለጠ ደጋግሞ የሚጠቀምበት የለም፤ እግዚአብሔር እርሱ ቅዱስ እንደ ሆነ ቅዱሳን እንድንሆን ጠርቶናል። ጳውሎስ አማኞችን ሁለት ጊዜ «ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ» ብሎ ይጠራቸዋል (ሮሜ 1፥7፤ 1ኛ ቆሮ. 1፥2)። «እግዚአብሔር ጠርቶናልና» ይላል፥ «ለርኵሰት ሳይሆን በቅድስና» (1ኛ ተሰ. 4፥7)። «የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ» ብሎ ሲጽፍ፥ «የሚጠራችሁ የታመነ ነው፥ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል» ብሎ ይጨምራል (1ኛ ተሰ. 5፥24)። መጠራቱ ራሱ «ቅዱስ አጠራር» ተብሎ ተነግሮለታል። ጥሪው ፍሬው የሆነለት የዘላለም አሳብም ዘወትር ከቅድስና ጋር ግቡ ሆኖ ተያይዞአል። «በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን» (ኤፌ. 1፥4)። «እግዚአብሔር እንደ በኵራት መርጦአችኋልና፥ በመንፈስ መቀደስ ለመዳን» (2ኛ ተሰ. 2፥12)። «በእግዚአብሔር አብ አስቀድሞ ማወቅ የተመረጣችሁ፥ በመንፈስ መቀደስ» (1ኛ ጴጥ. 1፥2)። ጥሪው አብ ከዘላለም ልቡን ያኖረበትን አሳብ መግለጥ ነው፤ ይኸውም ቅዱሳን እንድንሆን ነው።
እግዚአብሔር ወደ ምን እንደ ጠራን በትክክል ማወቅ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ማስረጃ አያስፈልገውም። እዚህ ላይ መሳሳት የሚያጠፋ ፍሬ ሊያመጣ ይችላል። እግዚአብሔር ወደ መዳን ወይም ወደ ደስታ፥ ይቅርታን እንድትቀበል ወይም መንግሥተ ሰማያትን እንድታገኝ እንደሚጠራህ ሰምተህ፥ እነዚህ ሁሉ ከሌላ ነገር በታች እንደ ሆኑ ፈጽሞ ሳታስተውል ቀርተህ ይሆናል። ጥሪው «በመቀደስ ለመዳን» ነበር፤ በመጀመሪያ ደረጃ ወደ ቅድስና ነበር፤ ይኸውም መዳንና መንግሥተ ሰማያት የሚገኙበት ስፍራ ነው። ብዙ ክርስቲያኖች ስለ ደስታና ስለ ኃይል ማጣት፥ ስለ ውድቀትና ስለ እድገት ማጣት የሚያሰሙት ሮሮ ምክንያቱ ይህ ብቻ ነው፤ እግዚአብሔር በጥሪው ለቅድስና የሰጠውን ስፍራ እነርሱ በመልሳቸው አልሰጡትም። እግዚአብሔርና እነርሱ በዚህ ነገር ገና አልተስማሙም።
ጳውሎስ ኤፌሶን ሰዎች «ቅዱሳን እንዲሆኑ የተመረጡ» እንደ ሆኑ በተናገረበት በዚያው ምዕራፍ፥ «የመጠራታቸውን ተስፋ» ያውቁ ዘንድ እርሱን በማወቅ የጥበብና የመገለጥ መንፈስ ለአማኞች እንዲሰጣቸው መጸለዩ አያስደንቅም (1፥17, 18)። ወደ ቅድስና እንደ ተጠራን እጅግ ጥቂት እንዳስተዋልን የሚሰማን ሁላችን ይህን ጸሎት እንጸልይ። የሚያስፈልገን ይህ ነው። የጠራን እርሱ ራሱ ቅዱስ እንደ ሆነ እኛም ደግሞ እንዴት ቅዱሳን ልንሆን እንደሚገባ እግዚአብሔር እንዲያሳየን እንለምነው፤ መጠራታችን ቅዱስ መጠራት ነው፥ ከሁሉ በፊትና ከሁሉ በላይ ወደ ቅድስና የተደረገ ጥሪ ነው። ቅድስና ምን እንደ ሆነ፥ በመጀመሪያ የእርሱን ቅድስና ቀጥሎም የእኛን ቅድስና እንዲያሳየን እንለምነው፤ የራሱ መልክና ምሳሌ ስለ ሆነ በእኛ ሊያየው የሚወደው ብቸኛ ነገር አድርጎ እንዴት ልቡን እንዳኖረበት እንዲያሳየን፤ ደግሞም ከክርስቶስ ጋር በቅድስናው መካፈል ያለውን የማይነገር ብፅዕናና ክብር እንዲያሳየን እንለምነው። ኦ! እርሱ ቅዱስ እንደ ሆነ ቅዱሳን እንድንሆን መጠራታችን ምን ማለት እንደ ሆነ እግዚአብሔር በመንፈሱ ቢያስተምረን! ይህ እንዴት ያለ ታላቅ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር በቀላሉ መገመት እንችላለን።
«የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ ቅዱሳን ሁኑ።» ይህ የእግዚአብሔር ጥሪ ወደ ቅድስና የሚያደርሰውን እውነተኛ ምክንያት እንዴት ያሳየናል! «እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ።» እግዚአብሔር እንዲህ ያለ ይመስላል፤ ቅድስና ብፅዕናዬና ክብሬ ነው፤ ያለ እርሱ በነገሮች ተፈጥሮ ልታዩኝ ወይም በእኔ ደስ ልትሰኙ አትችሉም። ቅድስና ብፅዕናዬና ክብሬ ነው፤ ከእርሱ የበለጠ ሊታሰብ የሚችል የለም፤ በእርሱ ከእኔ ጋር እንድትካፈሉ እጋብዛችኋለሁ፥ እኔን እንድትመስሉ እጋብዛችኋለሁ፤ «እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ።» ከእኔ ጋር የመሆን፥ የቅድስናዬም ተካፋዮች የመሆን ተስፋ አይበቃችሁምን? አይስባችሁምን? በኃይልስ አያነቃቃችሁምን? አይጎትታችሁምን? ከዚህ የሚሻል የማቀርብላችሁ የለኝም፤ ራሴን አቀርብላችኋለሁ፤ «እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ።» ነፍሳችን ለዚህ አስደናቂ ጥሪ መልስ ሁሉን ለመስጠት ፈቃደኛ እንድትሆን፥ የቅድስናውን ክብር እንዲያሳየን ወደ እግዚአብሔር አጥብቀን አንጮኽምን?
ጥሪውን ስናዳምጥ የእውነተኛ ቅድስናን ባሕርይ ደግሞ ያሳየናል። «እርሱ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተም ደግሞ ቅዱሳን ሁኑ።» ቅዱስ መሆን እግዚአብሔርን መምሰል ነው፤ እንደ እግዚአብሔር ያለ ዝንባሌ፥ ፈቃድና ጠባይ መያዝ ነው። «ቅዱሳን እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን» የሚለውን እንደ ገና እስክንሰማ ድረስ፥ አሳቡ የስድብ ያህል ይመስላል። በክርስቶስ የእግዚአብሔር ቅድስና በሰው ሕይወት ተገለጠ፤ በክርስቶስ ምሳሌ፥ በአሳቡና በመንፈሱ፥ የማይታየው አምላክ ቅድስና ወደ ሰው ሕይወትና አካሄድ ተተርጕሞ እናገኘዋለን። ክርስቶስን መምሰል እግዚአብሔርን መምሰል ነው፤ ክርስቶስን መምሰል እግዚአብሔር ቅዱስ እንደ ሆነ ቅዱስ መሆን ነው።
ጥሪው ደግሞ የቅድስናን ኃይል ይገልጣል። «እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለም፤» እርሱ ካለው፥ ይልቁንም እርሱ ከሆነውና ከሚሰጠው በቀር ቅድስና የለም። ቅድስና የምናደርገው ወይም የምንደርስበት ነገር አይደለም፤ የመለኮት ሕይወት መሰጠት፥ የመለኮት ባሕርይ እፍ መባል፥ በእኛ ላይ ያረፈ የመለኮት መገኘት ኃይል ነው። ቅዱሳን የምንሆንበትም ኃይላችን በእግዚአብሔር ጥሪ ውስጥ ይገኛል፤ ቅዱሱ እርሱን በመያዝ ቅዱሳን እንድንሆን ወደ ራሱ ይጠራናል። «እኔ ቅዱስ ነኝ» ብቻ ሳይሆን «የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ» ይላል። የቅድስና ጥሪ ወሰን ከሌለው ኃይልና ፍቅር አምላክ የሚመጣ ስለ ሆነ፥ ቅዱሳን መሆን እንችላለን የሚል መተማመን ሊኖረን ይችላል።
ጥሪው ደግሞ የቅድስናን መለኪያ ይገልጣል። «እርሱ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ ራሳችሁ»፥ ወይም (በእንግሊዝኛው የተሻሻለ ትርጉም ኅዳግ እንደ ተጻፈው) «የሚጠራችሁን ቅዱሱን መስላችሁ እናንተ ደግሞ ራሳችሁ ቅዱሳን ሁኑ።» ለእግዚአብሔር አንድ የቅድስና መለኪያ፥ ለሰው ደግሞ ሌላ የለም። የብርሃን ባሕርይ በፀሐይም ይሁን በሻማ ብናየው አንድ ነው፤ የቅድስና ባሕርይም የሚያድርበት እግዚአብሔርም ይሁን ሰው ሳይለወጥ ይኖራል። ጌታ ኢየሱስ «እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ» ከማለት ያነሰ ሊናገር አልቻለም። እግዚአብሔር ወደ ቅድስና ሲጠራን ወደ ራሱና ወደ ገዛ ሕይወቱ ይጠራናል፤ ድምፁን በጥንቃቄ ባዳመጥንና ወደ ልባችን እንዲሰርጽ በፈቀድን መጠን፥ የሰው መለኪያዎች ሁሉ ይበልጥ ይወድቃሉ፥ «እኔ ቅዱስ እንደ ሆንሁ ቅዱሳን» የሚለው ቃል ብቻ ይሰማል።
ጥሪውም ወደ ቅድስና የሚያደርሰውን መንገድ ያሳየናል። የእግዚአብሔር ጥሪ እጅግ ብርቱ የሆነ፥ የሚፈጽም ጥሪ ነው። ኦ! እርሱን ብቻ እንስማ፥ እርሱን ብቻ እናዳምጥ፥ ጥሪውም በመለኮት ኃይል የሚያቀርበውን ይፈጽማል። የሌሉትን እንዳሉ አድርጎ ይጠራል፤ ጥሪው ለሙታን ሕይወትን፥ ሕያዋን ላደረጋቸውም ቅድስናን ይሰጣል። ስለ ቅድስናው፥ እርሱንም ስለሚመስለው ስለ ቅድስናችን ሲናገር እንድናዳምጥ ይጠራናል። ቅድስናውን እንድናጠና፥ እንድንፈራ፥ እንድንወድና የእኛ እንድናደርግ ወደ ራሱ ይጠራናል። መለኮታዊ ቅድስና ሰብአዊ ቅድስና ወደ ሆነበት ወደ ክርስቶስ፥ ሁሉ ለእኛ የሆነውን እንድናይና እንድናደንቅ፥ እንድንመኝና እንድንቀበል ይጠራናል። በክርስቶስ የእኛ የሆነውን ወደ ልባችን እንዲያደርስና በውስጣችን እንዲተነፍስ ራሳችንን እንድንሰጥ፥ የቅድስና መንፈስ ወደሚያድርብንና ወደሚያስተምረን ይጠራናል። ክርስቲያን ሆይ! እግዚአብሔር ወደ ቅድስና ሲጠራህ አድምጥ። ቅድስናው ምን እንደ ሆነ፥ የአንተስ ምን እንደ ሆነና ምን ሊሆን እንደሚገባ ና ተማር።
አዎን፥ እጅግ ጸጥ ብለህ አድምጥ። እግዚአብሔር አብርሃምን በጠራው ጊዜ «እነሆኝ» ብሎ መለሰ። እግዚአብሔር ሙሴን ከቍጥቋጦው በጠራው ጊዜ «እነሆኝ» ብሎ መለሰ፤ ወደ እግዚአብሔርም ለማየት ፈርቶ ነበርና ፊቱን ሸፈነ። እግዚአብሔር ቅዱስ ያደርግህ ዘንድ ወደ ቅድስና፥ ወደ ራሱ ወደ ቅዱሱ ይጠራሃል። ነፍስህ ሁሉ «ጌታ ሆይ፥ እነሆኝ! ጌታ ሆይ፥ ተናገር! ጌታ ሆይ፥ ራስህን ግለጥ! እነሆኝ» ብላ ትመልስ። ስታዳምጥ ድምፁ ይበልጥ እየጠለቀና እየረጋ ይሰማል፤ እኔ ቅዱስ እንደ ሆንሁ ቅዱስ ሁን። እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱስ ሁን። ከታላቁ ዘላለም፥ ከቤዛነት የምክር አዳራሽ የሚወጣ ድምፅ ትሰማለህ፤ የሩቅ ሹክሹክታውንም ስትይዝ «ቅዱስ ሁን፥ እኔ ቅዱስ ነኝ» ይሆናል። ፈጣሪ ለፈጠረው ሰው ሰባተኛውን ቀን ሲቀድስና «ቅዱስ ሁን» ሲል ከገነት የሚወጣ ድምፅ ትሰማለህ። በነጐድጓድና በመብረቅ መካከል ከሲና የሚወጣውን ድምፅ ትሰማለህ፤ አሁንም «እኔ ቅዱስ እንደ ሆንሁ ቅዱስ ሁን» ነው። ከቀራንዮ የሚወጣ ድምፅ ትሰማለህ፤ በዚያም ከሁሉ በላይ «እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱስ ሁን» ነው።
የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ፥ አባታችን እርሱ ቅዱስ እንደ ሆነ ቅዱሳን እንድንሆን ወደ ራሱ እንደሚጠራን ተገንዝበህ ታውቃለህን? ከቅድስና ይልቅ ደስታ፥ ከመቀደስ ይልቅ መዳን እንደ በለጠብን መናዘዝ አይገባንምን? ኦ! ስሕተቱን ለማረም ገና አልረፈደም። የሚጠራውን ድምፅ ለማዳመጥ፥ ለመቅረብ፥ ቅድስና ምን እንደ ሆነ ለማግኘትና ለማወቅ፥ ይልቁንም ቅዱሱን ራሱን ለማግኘትና ለማወቅ አሁን በአንድነት እንተባበር። ወደ እርሱ የመጀመሪያው መቅረብ በኀፍረትና በውርደት ቢሞላን፥ ቢያስፈራንና ወደ ኋላ ቢያሸሸን እንኳ፥ «እኔ ቅዱስ እንደ ሆንሁ ቅዱሳን ሁኑ» የሚለውን ድምፅና ጥሪ ማዳመጣችንን እንቀጥል። «የሚጠራችሁ የታመነ ነው፥ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል።» ፍርሃታችንና ጥያቄያችን ሁሉ ከእርሱ ጋር እንድንካፈለው በዚህ አንድ ዓላማ ቅድስናውን በገለጠው በቅዱሱ መልስ ያገኛል። የሚጠራንን ቅዱስ ድምፅ ለማዳመጥ በነፍስ ጥልቅ ጸጥታ ራሳችንን ስንሰጥ፥ በውስጣችን አዲስ ምኞትና ጠንካራ እምነት ያነቃቃል፤ ከተስፋዎችም ሁሉ እጅግ የከበረው ይህ የመለኮት ትእዛዝ ቃል ይሆንልናል፤
እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ።
አቤቱ ጌታ ሆይ! ብቻህን ቅዱስ የሆንህ፥ አንተ ቅዱስ እንደ ሆንህ ቅዱሳን እንድንሆን ጠርተኸናል። ጌታ ሆይ! ቅድስናህን ካልገለጥህልን እንዴት እንችላለን? እንዴት ቅዱሳን እንደምንሆን፥ ምን ያህልስ ቅዱሳን ልንሆን እንደሚገባ እናውቅ ዘንድ፥ እንዴት ቅዱስ እንደ ሆንህ፥ ምን ያህል ቅዱስ እንደ ሆንህ፥ ቅድስናህ ምን እንደ ሆነ እንድታሳየን እንለምንሃለን። የቅድስናህ መታየት ምን ያህል ቅዱሳን እንዳልሆንን ይበልጥ ብቻ ሲያሳየን፥ ለዚሁ ወደ አንተ የሚመጡትን የገዛ ቅድስናህ ተካፋዮች እንደምታደርጋቸው አስተምረን።
አቤቱ አምላክ ሆይ! ወደ አንተ ወደ ቅዱሱ እንመጣለን። ነፍስ ቅድስናን የምታገኘው አንተን በማወቅና በማግኘት፥ አንተንም በመያዝ ነው። አሁን ወደ አንተ ስንመጣ፥ የጠራኸንና ወደ አንተ የምንመጣበት ብቸኛ ዓላማ ቅድስና እንደ ሆነ በልባችን አሳብ አጽናልን ብለን እንማልድሃለን። አንተን እንድንመስል፥ የቅድስናህም ተካፋዮች እንድንሆን ትወዳለህ። ልባችን ከፍ ያለ እንደ ሆነ ቢፈራ፥ ወይም ከቅድስና ባነሰ መዳን ቢረካ፥ የተባረክህ አምላክ ሆይ! «ቅዱሳን ሁኑ፥ እኔ ቅዱስ ነኝ» እያልህ እንደ ገና ስትጠራን ድምፅህን እንስማ። የሚጠራው የታመነ ስለ ሆነ እርሱም ደግሞ ስለሚያደርገው፥ ያ ጥሪ ምክንያታችንና ኃይላችን ይሁን። ያ ጥሪ መለኪያችንንና መንገዳችንን ያመልክት፤ ኦ! ሕይወታችን አንተ ልታደርገው እንደምትችል ይሁን።
ቅዱስ አባት ሆይ! በፊትህ በትሕትና ሰግጄ ዝም እላለሁ። አሁን «እኔ ቅዱስ እንደ ሆንሁ ቅዱስ ሁን» እያለ የሚጠራኝ የገዛ ድምፅህ በልቤ ጥልቀት ይሰማ። አሜን።
1. የዚህችን ትንሽ መጽሐፍ አንባቢ ሁሉ አጥብቄ የምለምነው ይህን ነው፤ ቅድስናን ለመፈለግ ትረዳው ዘንድ ከፈለገ በእግዚአብሔር በራሱ መጀመር አለበት። ወደሚጠራህ ወደ እርሱ መሄድ አለብህ። «ቅዱሳን ሁኑ» የሚለው ትእዛዝ ሕይወት ወይም ኃይል ሊኖረው የሚችለው «እኔ ቅዱስ ነኝ» ብሎ ሲናገር እግዚአብሔር በግል ለአንተ ሲገለጥ ብቻ ነው።
2. አማኝ እንደ መሆንህ ሙሉ በሙሉ ባትረዳውም እንኳ የእግዚአብሔርን ጥሪ አስቀድመህ ተቀብለሃል። የጥሪው ትርጉም ሆኖ የምታየውን ሁሉ ወዲያውኑ ለመቀበልና ለመፈጸም የወሰንኸው ነገር ይሁን። እግዚአብሔር ቅዱስ እንድሆን ከጠራኝ ቅዱስ እሆናለሁ።
3. ይህን ቃል አጥብቀህ ያዝ፤ «የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ የሚጠራችሁ የታመነ ነው፥ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል።» በዚያ እምነት እግዚአብሔር ሲጠራህ አድምጥ።
4. አሁን ጸጥ በል፥ አባትህ ሲጠራህም አድምጥ። ይህን ቅዱስ ጥሪ እንድትረዳ ልብህን ይከፍት ዘንድ መንፈስ ቅዱስን፥ የቅድስናን መንፈስ ለምን፤ በእርሱም ተማመን። ከዚያም ለዚህ ጥሪ የምትሰጠውን መልስ ተናገር።