በክርስቶስ ቅዱሳን
ቅድስናችን በሆነው በክርስቶስ

ምዕራፍ 23 · 7 ደቂቃ ንባብ · 9 ደቂቃ ማዳመጥ

ቅድስናችን በሆነው በክርስቶስ


ሃያ ሁለተኛ ቀን።

«እናንተስ ከእግዚአብሔር ሆናችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ናችሁ፤ እርሱም ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም ሆነልን፤ ይኸውም፦ የሚመካ በጌታ ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈ ይሆን ዘንድ ነው።»—1 ቆሮ. 1፥30፣ 31።

እነዚህ ቃላት አሁን ወደ እግዚአብሔር የቅድስና መንገድ መገለጥ ማዕከል ይመሩናል። ወደዚህ የሚያደርሰውን መንገድ ደረጃዎች እናውቃለን። እርሱ ቅዱስ ነው፤ ቅድስናም የእርሱ ነው። በመቅረብ ይቀድሳል። መገኘቱ ቅድስና ነው። በምሳሌና ለሚመጣው መልካም ነገር ተስፋ ሆኖ ብቻ ተገልጦ የነበረው ቅድስና በክርስቶስ ሕይወት በእውነት የሰውን ፈቃድ ይዞ ከእውነተኛ የሰው ባሕርይ ጋር አንድ ሆኖ ነበር። በሞቱ ያ ቅዱስ ባሕርይ ወደ እኛ እንዳይተላለፍ ሊከለክል የሚችል መሰናክል ሁሉ ተወግዶ ነበር፤ ክርስቶስ በእውነት ቅድስናችን ሆኖ ነበር። በመንፈስ ቅዱስም የዚያ ቅድስና በእውነት መሰጠት ተፈጸመ። አሁንም መንፈስ ቅዱስ የሚሠራው ሥራ ምን እንደ ሆነ፥ ይህንንም ቅዱስ ባሕርይ እንዴት እንደሚያካፍለን ልናስተውል እንወዳለን፤ ቅድስናችን ከሆነው ከክርስቶስ ጋር ያለን ግንኙነት ምን እንደ ሆነ፥ ቅድስናው በሙላቱና በኃይሉ ሥራውን በእኛ ይሠራ ዘንድ በእርሱ ፊት ልንይዘው የሚገባን አቋም ምን እንደ ሆነ ልናስተውል እንወዳለን።

ለዚህ ጥያቄ መለኮታዊው መልስ «ከእግዚአብሔር ሆናችሁ በክርስቶስ ናችሁ» የሚል ነው። ልናስተውለው የሚገባን አንድ ነገር በክርስቶስ ያለን ይህ አቋምና ሕይወት ምን እንደ ሆነ፥ ያም አቋምና ሕይወት በእኛ በኩል እንዴት ሊቀበልና ሊጠበቅ እንደሚችል ነው። ይህ ከፍ ያለና ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር እንዳልሆነ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። «ማን ወደ ሰማይ ይወጣል? ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው» በማለት የሚያደክም ጥረት ወይም ተስፋ የሌለው ትካዜ አያስፈልግም። ለኃጢአተኞችና ለደካሞች፥ ለማይገባቸውና አቅም ለሌላቸው የታሰበ ሕይወት ነው። የአብ ፍቅር ስጦታ የሆነ፥ እርሱ ራሱም እንደ ሕፃን በመታመን ወደ እርሱ በሚመጣ ሁሉ የሚገልጠው ሕይወት ነው። በሚለዋወጠው ሁኔታና አጋጣሚ ሁሉ ቅዱሳን የሚያደርገንና የሚጠብቀን፥ ለዕለት ተዕለት ኑሮአችን የታሰበ ሕይወት ነው።

«ከእግዚአብሔር ሆናችሁ በክርስቶስ ናችሁ።» የተባረከው ጌታችን ዓለምን ከመተዉ በፊት፦ እነሆ፥ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ ብሎ ተናገረ። ስለ እርሱም፦ «ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው» ተብሎ ተጽፎአል። «ቤተ ክርስቲያን አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት።» ጌታ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ በምድር ላይ ከሕዝቡ ጋር ነው። ባይታይም በሥጋም ባይሆንም፥ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በተመላለሰበት ጊዜ እንደ ነበረው ሁሉ የግል መገኘቱ በምድር ላይ እውነተኛ ነው። አማኝ ዳግመኛ በመወለድ ከቀድሞ ስፍራው «ከሥጋ» ይወጣል፤ ከእንግዲህ በሥጋ አይደለም፥ በመንፈስ እንጂ (ሮሜ 8፥9)፤ በእውነትና በርግጥ በክርስቶስ ነው። ሕያው ክርስቶስ በቅዱስ መገኘቱ ይከብበዋል። የትም ቢሆን ምንም ቢሆን፥ ስለ አቋሙ የቱንም ያህል የማያውቅ ወይም ለእርሱ የቱንም ያህል ታማኝ ያልሆነ ቢሆን፥ እዚያ በክርስቶስ ነው። በመለኮታዊና ሁሉን በሚችል ጸጋ ሥራ በክርስቶስ ተተክሎአል፤ ሁሉን በሚሞላው፥ ሙላቱም በተለይ በዚህ በምድር ባለው አካሉ በቤተ ክርስቲያን በሚኖረው በእርሱ ኃይልና ፍቅር በሁሉ አቅጣጫ ተከብቦአል።

ክርስቶስን ቅድስናው አድርጎ በሙላት ለማወቅ የሚናፍቅ ሰው፥ እግዚአብሔር በዚህ—«በክርስቶስ» በሚለው—ያሰበውንና ያዘጋጀውን በኑሮው እንዴት ሊገልጠው ይችላል? መታሰብ ያለበት የመጀመሪያ ነገር ይህ የእምነት እንጂ የስሜት ጉዳይ አለመሆኑ ነው። ቅዱሱ በውስጥ ሊኖርና ሕያው ሊያደርግ የሰጠው ተስፋ ለትሑታንና ልባቸው ለተሰበረ ነው። ቅዱስ እንዳልሆንሁ፥ ራሴንም ቅዱስ ለማድረግ ምንም ማድረግ እንደማልችል በጥልቅ በሚሰማኝ ጊዜ፥ በራሴ በማፍርበት ጊዜ፥ ልክ ያን ጊዜ ከራሴ ዘወር ብዬ በጸጥታ፦ እኔ በክርስቶስ ነኝ ማለት የሚገባኝ ጊዜ ነው። እነሆ፥ እርሱ በዙሪያዬ ሁሉ ነው። እንደሚከብበኝ አየር፥ እንደሚበራልኝ ብርሃን፥ ጌታዬ ኢየሱስ በተሰወረው ነገር ግን መለኮታዊና እጅግ እውነተኛ በሆነው መገኘቱ ከእኔ ጋር ነው። እምነቴ ከእርሱ በሆንሁበትና በብርቱ ጸጋው በክርስቶስ ባለሁበት በአብ ፊት በጸጥ ያለ ዕረፍትና መታመን ልትሰግድ ይገባታል፤ እርሱ ይህን ዘወትር በሚያድግ ግልጽነትና ኃይል ይገልጥልኛል። ይህን የሚያደርገው ሳምን፥ በማመንም ነፍሴን ሁሉ በዚህ ውስጥ ያለውን ለመቀበል ስከፍት ነው፤ የኃጢአተኝነትና የቅድስና ማጣት ስሜት የመታመኔና የመደገፌ ኃይል ሊሆን ይገባዋል። በእንዲህ ያለ እምነት በክርስቶስ እኖራለሁ።

ነገር ግን ከእምነት ስለ ሆነ ስለዚህ ከመንፈስ ቅዱስ ነው። ከእግዚአብሔር ሆናችሁ በክርስቶስ ናችሁ። እግዚአብሔር በክርስቶስ አኑሮንና ተክሎን፥ አንድነቱን መጠበቅ አሁን ለእኛ የተወው አይደለም። አይደለም፤ እግዚአብሔር ዘላለማዊ ነው፤ ለአንዲት ቅጽበት እንኳ በማያቋርጥ ኃይል በየቅጽበቱ የሚሠራ የዘላለም ሕይወት አምላክ ነው። እግዚአብሔር የሚሰጠውን በማያቋርጥ መስጠት ይቀጥልበታል። ይህን በክርስቶስ ያለውን ሕይወት በልቡናችን የተባረከ እውነት የሚያደርገው እርሱ በመንፈስ ቅዱስ ነው። «ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ ተቀበልን።» እምነት የሚቀበለውን ስጦታ ብቻ ሳይሆን የመቀበልንም ኃይል ከእግዚአብሔር ይጠብቃል። እምነት ወልድን እንደ ሙላቱና እንደ ምግቡ ብቻ አይሻም፤ ለመቀበልና ለመያዝ ኃይሉ እንዲሆን መንፈስንም ይሻል። ስለዚህ ቅድስናችን በሆነው በክርስቶስ መሆን ማለት ያለውን ሁሉ የተባረከ ርስት የምናገኘው ለመንፈስ ብርቱ ሥራ በእምነት ጸሎት በእግዚአብሔር ፊት መስገድን ስንማር፥ እርሱም ያለንበትን ይህን ክርስቶስ ቅድስናችንን በእኛ እንደሚገልጥና እንደሚያከብር በጥልቅ የሕፃን መታመን ስንታመን ነው።

መንፈስ ያለንበትን ይህን ክርስቶስ እንዴት ይገልጣል? በተለይ እንደ ሕያው፥ እንደ ግል ወዳጅና ጌታ አድርጎ ይገልጠዋል። ክርስቶስ ምሳሌያችንና ዓላማችን ብቻ አይደለም። በጽሑፎቹ በብርቱ ስለሚነካን ሰው እንደምንናገር፥ ሕይወቱ ከባቢና መነሣሣት ብቻ አይደለም። ክርስቶስ መንፈስ የሚመራን የጸጋና የኃይል ግምጃ ቤትና ሙላት ብቻ አይደለም። ነገር ግን ክርስቶስ እጅግ በርኅራኄ ሰብአዊ ሆኖ ሳለ መለኮታዊ በሆነ ፍቅር የሚመታ ልብ ያለው ሕያው አዳኝ ነው። በዚህ ፍቅር ይቀርባል፤ አብ በእርሱ ሲተክለን በዚህ ፍቅር ይቀበለናል። በግል ፍቅር ኃይል ተጽዕኖ ሊያደርግና ከራሱ ጋር ሊያቆራኘን ይወዳል። በዚያ ፍቅሩ ቅድስናው ወደ እኛ እንደሚገባ ዋስትና አለን፤ በዚያ ፍቅር የሚገባበትም ታላቅ ኃይል አለ። መንፈስ የምንኖርበትን፥ በክርስቶስና በፍቅሩ መሆኑን፥ ይህም ክርስቶስ ሕያው ጌታና አዳኝ መሆኑን ሲገልጥልን፥ ፈጽሞ የእርሱ የሚያደርገን የግል ቁርኝት ቅንዓትና የፍቅር ታማኝነት ትጋት በውስጣችን ይነሣል። ቅዱሳን መሆን እንደምንችልም ማመን ይቻለናል፤ በቅድስና መንገድ ከኃይል ወደ ኃይል መሄድ እንደምንችል እርግጠኞች እንሆናለን።

በእርሱ በመሆናችን ከክርስቶስ ጋር ስላለን ግንኙነት እንዲህ ያለ የእምነት ማስተዋል፥ ወደ ፍቅሩ ለተቀበለንና በዚያም ለሚያኖረን ለእርሱ እንዲህ ያለ የግል ቁርኝት የአዲስ መታዘዝ ምንጭ ይሆናል። የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ሕይወትና በፍቅሩ ብርሃን ወደ እኛ ይመጣል፤ እያንዳንዱ ትእዛዝ አስቀድሞ በእርሱ ተፈጽሞ፥ ከዚያም ከአብና ከቅድስናው ጋር ለበለጠ ፍጹም ኅብረት እርግጠኛና እጅግ የተባረከ ረዳት ሆኖ ለእኛ ይተላለፋል። ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በነፍስ ውስጥ ጌታና ንጉሥ ይሆናል፤ ፈቃድን ወደ እግዚአብሔር ፍጹም ፈቃድ ሁሉ ይመራል፤ የነፍስንም መታዘዝ በእግዚአብሔር መገኘትና ቅድስና ዘወትር በሚበዛ መፍሰስ ሲያቀዳጅ፥ ቅድስናዋ እንደ ሆነ ያሳያል።

በቅዱስ ኑሮ ሁሉ እንዴት ያለ ሰው ሊሆን እንደሚገባው ሲያስብ ልቡ ሊዝል የሚያዘነብል ውድ የእግዚአብሔር ልጅ ቢኖር፥ አይዞህ እንዲል እጠራዋለሁ። እግዚአብሔር እንደነዚህ ላሉ ኃጢአተኞችና አቅም የሌላቸው ፍጥረታት ከዚህ የሚበልጥ ድንቅ ወይም ውብ ነገር ሊያዘጋጅ ይችል ነበርን? እስቲ አስብ፤ የእግዚአብሔር የገዛ ልጁ ክርስቶስ ቅድስና ሆኖልሃል። ኃያሉ፥ አፍቃሪው፥ ቅዱሱ ክርስቶስ፥ ከአንተ ጋር ይራራ ዘንድ በመከራ የተቀደሰው፥ ቅዱስ ሊያደርግህ ተሰጥቶአል። ከዚህ ሌላ ምን ልትመኝ ትችላለህ? አዎን፥ ከዚህ የሚበልጥ አለ፤ «ከእግዚአብሔር ሆነህ በእርሱ ነህ።» ብታስተውለውም ባታስተውለውም፥ የቱንም ያህል በደካማ ብትረዳው፥ እነሆ አለ፤ እጅግ መለኮታዊ እውነትና እውነተኛ ነገር ነው። በእግዚአብሔር የገዛ ብርቱ ኃይል ሥራ በክርስቶስ ነህ። በዚያም፥ በክርስቶስ፥ እግዚአብሔር ራሱ እስከ ፍጻሜ ሊያጸናህና ሊያረጋግጥህ ይናፍቃል። ከሁሉም የሚበልጥ ድንቅ፥ በክርስቶስ ለአንተ ያለውን ሁሉ እንድታውቅ፥ እንድታምንና እንድትቀበል የሚያስተምርህ መንፈስ ቅዱስ በውስጥህ አለ። በአንተ ውስጥ ለቅድስና የሚሆን ጥበብ ወይም ኃይል ፈጽሞ እንደሌለ ብትመሰክር፥ «የእግዚአብሔር ጥበብና የእግዚአብሔር ኃይል» የሆነው ክርስቶስ በውስጥህ ባለው በመንፈስ ቅዱስ ወደ ፊት እንዲመራህ፥ ምን ያህል በፍጹም፥ ምን ያህል በታማኝነት፥ ምን ያህል በብርቱ ቅድስናህ ሊሆን እንደሚችል እንዲያሳይ ብትፈቅድለት፥ እጅግ በክብር ያደርገዋል።

ወንድሜ ሆይ! ና፥ ለእግዚአብሔር የቅድስና መንገድ የበለጠ በሙላት እሺ በል። ክርስቶስ ቅድስናህ ይሁን። የምትመለከተው የራቀ ክርስቶስ ሳይሆን፥ እጅግ ቅርብ የሆነ፥ በዙሪያህ ሁሉ ያለ፥ አንተም በእርሱ ያለህበት ክርስቶስ። በሥጋ የሆነ ክርስቶስ፥ ያለፈው ዘመን ክርስቶስ ሳይሆን፥ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ያለ የአሁን ክርስቶስ። በጥበብህ ልታውቀው የምትችለው ክርስቶስ ሳይሆን፥ መንፈስ የሆነው፥ ለሥጋና ለራስ ስትሞት በውስጥህ ያለው መንፈስ በኃይል የሚገልጠው የእግዚአብሔር ክርስቶስ። ትንሹ ሐሳብህ ሊገምተው የሚችለው ዓይነት ክርስቶስ ሳይሆን፥ እንደ እግዚአብሔር ልብና ፍቅር ታላቅነት የሆነ ክርስቶስ። ኦ፥ ና፥ ይህን ክርስቶስ ተቀበል፥ በእርሱም ደስ ይበልህ! ከምታስበው በላይ እንደሚያደርግልህ በጸጥ ያለ መተማመን፥ ድካምህን፥ ሞኝነትህንና አለማመንህን ሁሉ ለእርሱ ለመተው አሁን እሺ በል። ከእንግዲህም እንደ ተጻፈው እንዲሁ ይሁን፤ የሚመካ በጌታ ይመካ።

እኔ ቅዱስ እንደ ሆንሁ ቅዱሳን ሁኑ።

እጅግ ብፁዕ አባት ሆይ! በመለኮታዊ ፍቅርህ ቅዱስ ምሥጢር ፊት ቃል በሌለው ስግደት እሰግዳለሁ….

ኦ፥ ሊታወቅና ሊታመን እንደሚገባው መጠን ጥቂት ብቻ ስላወቅሁትና ስላመንሁት ይቅር በለኝ።

ከመለኮታዊ ብፅዕናው ስላየሁትና ስለ ቀመስሁት ምስጋናዬን ተቀበል። ጌታ አምላክ ሆይ! አንተን በትክክል ፈጽሞ ማመስገን እንደማይችል ብቻ የሚያውቅ ደስተኛና አፍቃሪ ልብ ምስጋናን ተቀበል።

አባቴ ሆይ! በውስጤ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስህ ኃይል፥ ቅድስናዬ በሆነው በክርስቶስ የሰጠኸኝን ዕለት ዕለት እንድቀበልና በሙላት እንድኖረው ጸሎቴን ስማ። በእርሱ ያለው የማይመረመር ባለ ጠግነት ለፍላጎቴ ሁሉ የዕለት ስንቅ ይሁን። ቅድስናው፥ በፈቃድህ ደስ መሰኘቱ፥ በእውነት የእኔ ይሁን። ሁሉን በሚችለው ሕያው በሚያደርገው ኃይልህ ሥራ በእርሱ ስለ ሆንሁ፥ በአንተም በዚያ ስለ ተጠበቅሁ፥ ይህ እንዴት በእርግጥ ሊሆን እንደሚችል ከሁሉ በላይ አስተምረኝ። አባቴ ሆይ! እምነቴ ይጮኻል፤ ቅዱስ መሆን እችላለሁ፤ ጌታዬ ኢየሱስ ይባረክ!

ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ንጉሤና ጌታዬ፥ ፈቃድህን ብቻ አደርግ ዘንድ በዚህ እምነት ራሴን ለአንተ እሰጣለሁ። ታላቅም ይሁን ትንሽ በማደርገው ሁሉ፥ በኢየሱስ እንደ ተቀደሰ፥ በእርሱም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር እንደ ተዋሐደ ሰው ልሠራ እወዳለሁ። ይህን ማድረግ ልታስተምረኝ፥ ለመፈጸምም ኃይል ልትሰጠኝ የምትችል አንተ ብቻ ነህ። ነገር ግን በአንተ እታመናለሁ፤ ቅድስናዬ ክርስቶስ አንተ አይደለህምን? ብፁዕ ጌታ ሆይ! በእውነት በአንተ እታመናለሁ። አሜን።

1. በምድር እንደ ኖረና እንደ ሞተ ክርስቶስ ቅድስናችን ነው። ሕይወቱ፥ የሕይወቱ መንፈስ፥ ቅድስናችን የሆነው ነው። ከክርስቶስ ጋር ፍጹም መስማማት፥ የእርሱን ልብ ማግኘት፥ ቅዱስ መሆን ነው።

2. የክርስቶስ ቅድስና ሁለት ገጽታ ነበረው። እግዚአብሔር በመንፈሱ ቀደሰው፤ ክርስቶስም የመንፈስን አመራር በመከተል፥ በሁሉ ፈቃዱን ለእግዚአብሔር በመስጠት ራሱን ቀደሰ። እንዲሁም እግዚአብሔር በክርስቶስ ቅዱሳን አድርጎናል፤ እንዲሁም ራሳችንን ለእግዚአብሔር መንፈስ በማስገዛት፥ ፈቃዳችንን በመተውና በእግዚአብሔር ፈቃድ በመኖር ቅድስናን እንከተላለን፥ እንፈጽማለንም።

3. እግዚአብሔር በቃሉ ስለ ቅድስና የገለጠውን እያንዳንዱን ገጽታ መቀበላችን መልካም ነው። ነገር ግን ሁሉን ፈጽሞ ለመያዝ በመሞከር ራሳችንን ፈጽሞ አናድክም። እንዲያውም በኢየሱስ ወዳለው ቅንነት እንመለስ። በእግሩ ሥር መስገድ፥ የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደሚያውቅ፥ ሁሉም እንዳለው፥ ሁሉንም መስጠት እንደሚወድ ማመን ዕረፍት ነው። ቅድስናም የእግዚአብሔርን ዕረፍት በኢየሱስ ማረፍ ነው። ሐሳባችን ሁሉ ወደዚህ ወደ አንዱ ይሰብሰብ፤ ኢየሱስ፥ ብፁዕ ኢየሱስ።

4. ይህ በክርስቶስ ያለ ቅዱስ ሕይወት ለዛሬ ነው፥ ይህን ለምታነብበት ጊዜ። ዛሬ ከእግዚአብሔር ቅድስና ሆኖልሃልና፤ ዛሬ በእውነት ቅድስናህ ይሆናል። ስለዚህ በእርሱ እመን፤ ታመንበት፥ አመስግነው። አስታውስም፤ በእርሱ ነህ።

ጨርሰዋል፦ ቅድስናችን በሆነው በክርስቶስ

ቀዳሚ ቀጣይ