ምዕራፍ 24 · 8 ደቂቃ ንባብ · 10 ደቂቃ ማዳመጥ
ቅድስናና ሰውነት
ሃያ ሦስተኛ ቀን።
«የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ። ሥጋ ለጌታ ነው፥ ጌታም ለሥጋ ነው። ሥጋችሁ በእናንተ ያለ የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።»—1ኛ ቆሮንቶስ 3፥16፤ 6፥13, 19።
«ያልተጋባች ሴትና ድንግል በሥጋም በነፍስም እንዲቀደሱ የጌታን ነገር ያስባሉ።»—1ኛ ቆሮንቶስ 7፥34።
«ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ።»—ሮሜ 12፥1።
የተባረከው ጌታችን ወደ ዓለም ሲገባ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ «ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤ እነሆ፥ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ።» ከዚህ ዓለም ዳግመኛ ሲለይም ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ የተሸከመው በራሱ ሥጋ ነበር። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያደረገው በነፍስና በመንፈስ ብቻ ሳይሆን በሥጋም ጭምር ነበር። ስለዚህም «በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል» ተብሎአል።
ጳውሎስ ስለ ተሰሎንቄ ሰዎችና ስለ መቀደሳቸው ሲጸልይ እንዲህ ይላል፦ «የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ።» ስለ ራሱም ሲናገር «የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን። የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋን የሆንን ከኢየሱስ የተነሣ ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለንና» ብሎ ነበር። ልባዊ ናፍቆቱና ተስፋውም «በህይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን ደግሞ በስጋዬ ይከብራል» የሚል ነበር። በሥጋና በመንፈስ መካከል ያለው ግንኙነት እጅግ የቀረበ ስለ ሆነ፥ በመንፈስ ያለው የኃጢአት ኃይል በአብዛኛው በሥጋ በኩል ስለሚመጣ፥ ሰውነትም የክርስቶስ ቤዛነትና የመንፈስ ቅዱስ መታደስ ግልጥ ዓላማ ስለ ሆነ፥ መጽሐፍ ቅዱስ በሰውነት ስላለው ቅድስና የሚያስተምረውን ካልተቀበልን የቅድስና ጥናታችን እጅግ የጎደለ ይሆናል።
ሰውነት በውስጡ ለሚኖሩትና ለሚሠሩት ለነፍስና ለመንፈስ እንደ ከተማ ቅጥር ነው ተብሎ በመልካም ተነግሮአል። ጠላት የሚገባው በእርሱ በኩል ነው። በጦርነት ጊዜ ሁሉ ነገር ለቅጥሩ መከላከያ ይሰጣል። አማኙ ነፍሱና መንፈሱ ያለ ነቀፋ ተጠብቀው እንዲኖሩ የሚያቅተው ብዙ ጊዜ ቅጥሩን መከላከልን፥ ይኸውም ሰውነቱን ተቀድሶ መጠበቅን፥ አስፈላጊነት ስለማያውቅ ነው። ወይም በቅድስና ያለው እድገቱ እጅግ ደካማ የሚሆነው፥ ሰውነትን በክፍሎቹ ሁሉ መጠበቅና መቀደስ ልክ እንደ ውስጣዊው ሕይወት መታደስ ግልጥ የእምነት ሥራ፥ በቀጥታም በኢየሱስ ታላቅ ኃይልና በመንፈስ በውስጥ መኖር የሚፈጸም መሆን እንዳለበት ስለማያስተውል ነው። የከተማውን አስተዳደር ለኢየሱስ አደራ እንሰጣለን፤ የቅጥሩን መከላከያ ግን በገዛ እጃችን እንይዛለን፤ ንጉሡም እንደ ጠበቅነው አይጠብቀንም፥ የውድቀታችንንም ምሥጢር ማግኘት አንችልም። ሁለንተናችንን የሚቀድሰው፥ መንፈስንና ነፍስን ሥጋንም ያለ ነቀፋ ፈጽሞ ሊጠብቅ የሚገባው የሰላም አምላክ ራሱ ነው። እንጨት ያለው የመገናኛው ድንኳን፥ ድንጋይ ያለው ቤተ መቅደስ በቅጥራቸው ውስጥ እንዳለው ሁሉ ቅዱሳን ነበሩ፤ የእግዚአብሔር ቅዱሳንም ሰውነታቸው ቅዱስ ሊሆን ያስፈልጋቸዋል።
የዚህን ሙሉ ትርጉም እንድናስተውል ኃጢአት የገባው በሰውነት በኩል እንደ ሆነ እናስታውስ። «ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ አየች»፤ ይህ በሥጋ የመጣ ፈተና ነበር፤ በዚህም በኩል ነፍስ ተነካች፥ «ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ»፤ ከነፍስም ወደ መንፈስ አለፈ፥ «ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ»። ዮሐንስ በዓለም ያለውን በገለጠበት ቃል (1ኛ ዮሐንስ 2፥15) ያንኑ ሦስት እጥፍ ክፍፍል እናገኛለን፤ «የሥጋ ምኞት፥ የዓይን አምሮት፥ የሕይወትም ትዕቢት»። ሰይጣን ኢየሱስን የፈተነባቸው ሦስቱ ፈተናዎችም ከዚህ ጋር ፍጹም ይስማማሉ፤ በመጀመሪያ እንጀራን በማድረግ ራቡን እንዲያስታግሥ በሚያቀርበው ሐሳብ በሰውነቱ በኩል ሊደርስበት ፈለገ፤ ሁለተኛው (ሉቃስ 4 ተመልከት) በዚህ ዓለም መንግሥታትና በክብራቸው ራእይ ነፍስን ሊስብ ሞከረ፤ ሦስተኛው ራሱን ወደ ታች በመወርወር መለኮታዊ ልጅነቱን እንዲገልጥና እንዲያረጋግጥ በሚጠራው ጥሪ መንፈስን ነካ። ለእግዚአብሔር ልጅ እንኳ የመጀመሪያው ፈተና ለአዳምና በዓለም ላሉት ሁሉ እንደ መጣው ሆኖ መጣ፤ እንደ ሥጋ ምኞት፥ ተፈጥሮአዊውንና የተፈቀደውን የራብ ፍላጎት ለማርካት እንደ መሻት። የሰው የመጀመሪያ ኃጢአት የተሠራው ለመብላት መልካም መስሎ የታየውን በመብላት ጉዳይ እንደ ሆነ፥ ያም ራብን ለማስታገሥ የመብላት ጉዳይ ታዳጊው ከሰይጣን ጋር የመጀመሪያውን ግጥሚያ ያደረገበት የጦር ሜዳ እንደ ሆነ እጅግ በጥንቃቄ ልናስተውል ይገባናል። ከሚያውቁት በላይ ብዙ ክርስቲያኖች በሰይጣን የሚሸነፉት መልካምና የተፈቀደውን በመብላትና በመጠጣት ጉዳይ ነው። የሰውነትን ፍላጎት ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ አገዛዝና ሥርዓት ሥር ማድረግ ለአንዳንዶች አላስፈላጊ፥ ለሌሎች ደግሞ እጅግ አስቸጋሪ ይመስላቸዋል። ነገር ግን ሰውነት እንደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ሊሆን፥ እኛም በሥጋችንና በመንፈሳችን ልናከብረው ከሆነ ይህ ሊሆን ግድ ነው። የኃጢአት የመጀመሪያ አቀራረቦች በሰውነት በኩል ናቸው፤ ፍጹሙም ድል በሰውነት ይገኛል።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰውነትና ስለ መንፈስ ግንኙነት መቀራረብ የሚያስተምረውን የሰውነት ሳይንስ ያረጋግጣል። በመጀመሪያ ሥጋዊ ብቻ የሚመስሉ መተላለፎች በነፍስ ላይ እድፍ ይተዋሉ፥ የሚያዋርድም ተጽእኖ ያደርጉባታል፥ በእርሷም በኩል መንፈስን ወደ ታች ይጎትታሉ። በሌላ በኩል ደግሞ መንፈሳዊ ኃጢአቶች፥ የሐሳብና የምናብና የዝንባሌ ኃጢአቶች፥ በነፍስ በኩል ወደ ሰውነት ያልፋሉ፤ በነርቭ ሥርዓት ውስጥ ሥር ይሰዳሉ፥ በፊት ገጽታና በሰውነት ልማዶችና ዝንባሌዎች እንኳ ይገለጣሉ። ኃጢአትን መዋጋት ያለብን በመንፈስ ክልል ብቻ አይደለም፤ ቅድስናን ፍጹም ልናደርግ ከሆነ ሥጋንና ደግሞ መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን ማንጻት ይገባናል። «በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ።» በእውነት ከኃጢአት ልንነጻና ለእግዚአብሔር ቅዱሳን ልንሆን ከሆነ፥ ሰውነት እንደ ውጫዊ ምሽግ ከሰይጣንና ከኃጢአት ኃይል በተለየ ሁኔታ መጠበቅ አለበት።
ይህስ እንዴት ይደረጋል? እግዚአብሔር ለዚህ እጅግ ልዩ ዝግጅት አድርጎአል። ቅዱሱ መጽሐፍ ስለ መንፈስ ቅዱስ፥ ቅድስናን ስለሚያካፍለው መንፈስ፥ ከሰውነት ጋር አያይዞ እጅግ ግልጥ አድርጎ ይናገራል። በመጀመሪያ ሲታይ ሰውነታችሁ የሚለው ቃል እናንተ ራሳችሁ ከሚለው ጋር እኩል ሆኖ ብቻ የተነገረ ይመስላል። ነገር ግን በሰውነት ስላለው የኃጢአት ኃይልና በተለይ በዚያ ስለሚያስፈልገው መዳን ጥልቅ ማስተዋል አእምሮአችንን ሲያነቃው፥ ሰውነት የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ነው ሲባል ምን ማለት እንደ ሆነ እናያለን። ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሚያረክሱ አድርጎ የሚናገረው በተለይ በሰውነት ስለሚሠሩ ኃጢአቶች እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርንም እንድናከብር የሚፈልገው በሰውነት ባለው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንደ ሆነ እናስተውላለን። «ሥጋችሁ የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? እንግዲያስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።» መንፈስ ቅዱስ የሰውነት ፍላጎቶችና እርካታቸው በልክና በራስ መግዛት እንዲሆኑ የሚከለክልና የሚያስተካክል ተጽእኖ ብቻ ማድረግ የለበትም፤—ይህ አሉታዊው ጎን ብቻ ነው፤—ነገር ግን የተፈጥሮ ተግባራትን መፈጸም ለእግዚአብሔር ክብር የቅዱስ ደስታና የነጻነት አገልግሎት የሚያደርግ በእርግጥ መንፈሳዊ የሆነ ነገር ሊኖር ይገባል፤ ይህም ለመታዘዝና ለኅብረት ሕይወት የሚያሰጋ እንቅፋት መሆኑ ቀርቶ የጸጋ መንገድ፥ ለመንፈሳዊ ሕይወትም እውነተኛ እርዳታ ይሆናል። ይህ የሚሆነው በቅዱሱ ሕይወት በተሞላ፥ በእግዚአብሔርም መንፈስ ፈጽሞ በተያዘ ሰውነት ብቻ ነው።
ይህስ እንዴት ሊገኝ ይችላል? በእውነተኛው የክርስትና ሕይወት ራስን መካድ ወደ ደስታ፥ መተው ወደ ማግኘት፥ ሞትም ወደ ሕይወት የሚያደርስ መንገድ ነው። በልክ ብቻ ብናደርገው በትክክል ልንጠቀምበት ወይም ልንደሰትበት ነጻነትና ኃይል አለን ብለን የምናስበው ነገር እስካለ ድረስ፥ የራሳችንን ቅድስና ማጣት ወይም የመንፈስ ቅዱስን ፍጹም መታደስ አስፈላጊነት ገና አላየንም፥ አልተናዘዝንምም። «እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነውና፥ ከምስጋናም ጋር ቢቀበሉት የሚጣል ምንም የለም» ማለት ብቻ አይበቃም፤ ተጨማሪውን «በእግዚአብሔር ቃልና በጸሎት የተቀደሰ ነውና» የሚለውን ማስታወስ አለብን። የፍጥረትን ሁሉና የአጠቃቀሙን መቀደስ እንደ ራሳችን መቀደስ እውነተኛና የተከበረ ነገር ነው። ይህም የሚሆነው፥ አስፈላጊ ሲሆን፥ እግዚአብሔር ለክብሩ ብቻ በእውነት እንድንጠቀምበት ኃይል እስኪሰጠን ድረስ ስጦታውንና በእርሱ የመጠቀምን ነጻነት በምንሠዋበት ብቻ ነው። ከመለኮታዊ ሥርዓቶች እጅግ ስለ ተቀደሰው ስለ ጋብቻ፥ ማግባትን የሚከለክሉትን አጥብቆ የሚነቅፈው ጳውሎስ፥ በፈቃድ ሳያገቡ መኖር «በሥጋም በመንፈስም ቅዱስ» ለመሆን እጅግ የተረጋገጠና ተቀባይነት ያለው መንገድ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ በግልጥ ይናገራል። እግዚአብሔር ቅዱስ እንደ ሆነ ቅዱስ መሆን በእውነት የሕይወት ታላቅ ምኞትና ዓላማ ሲሆን፥ ሁሉ ነገር ዋናውን ግብ እንደሚያራምድ መጠን ይወደዳል ወይም ይተዋል። በሰውነት ሕይወት ውስጥ ያለው የመንፈስ ቅዱስ እውነተኛና ሕያው መገኘት በመሠዊያው ላይ ዘወትር የሚነድድ እሳት ይሆናል።
ይህስ እንዴት ይደረስበታል? ስለ መንፈስ እንደ ሆነ ስለ ሰውነትም ጠባቂያችንና ቀዳሻችን እግዚአብሔር፥ በክርስቶስ ያለው እግዚአብሔር ነው። የከተማውን ቅጥር መጠበቅ በውስጥ ለሚገዛው አደራ ሊሰጥ ይገባል። «የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ሊጠብቅ እንዲችል ተረድቼአለሁ»፥ ማለትም ለእርሱ የሰጠሁትን ሊጠብቅ እንደሚችል፥ ለመዳን አደራ ስለ ሰጠነው ነፍስ እውነት እንደ ሆነ ሁሉ፥ ስለ ሰውነትና ጥርጥር ወይም መሰናከል ምክንያት እንደ ሆነ ስለምናውቀው ስለ እያንዳንዱ ተግባሩ እንዲሁ በግልጥ እውነት ሊሆን ይገባል። በባንክ ውስጥ የተቀመጠ ቋሚ ተቀማጭ በዚያ እንዲጠበቅ ከእጄ ተሰጥቶ የወጣ ገንዘብ ነው፤ ቅዱስ ሊሆን የሚያስፈልገው ሰውነት ወይም የትኛውም ክፍሉ በኢየሱስ ዘንድ የተቀመጠ አደራ ሊሆን ይገባል። እምነት እርሱ እንደ ተቀበለውና እንደሚጠብቀው ሊታመን ይገባል፤ ጸሎትና ምስጋና በየዕለቱ እንደ ገና ማረጋገጫውን ሊያድሱ፥ አደራ መስጠቱን ሊያጸኑ፥ ከኢየሱስም ጋር ያለውን ኅብረት ሊጠብቁ ይገባል። እንዲህ በእርሱና በቅድስናው ስንኖር፥ ቅድስና ሆኖ በተሰጠን በእርሱ ምን ያህል ሙሉና ፍጹም እንደ ሆንን፥ የእግዚአብሔርም ቅድስና በሕዝቡ ውስጥ ምን ያህል እውነተኛ እንደ ሆነ በሰውነት እንኳ የምናረጋግጥበትን ኃይል በመታመንና በደስታ ሕይወት እንቀበላለን።
እኔ ቅዱስ እንደ ሆንሁ ቅዱሳን ሁኑ።
ቅድስናዬ የሆንህ የተባረክህ ጌታ ሆይ! አሁን እጅግ ልዩ በሆነ ልመና ወደ አንተ እመጣለሁ። በራስህ ሥጋ ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ የተሸከምህ፥ ስለ አንተም «በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል» ተብሎ የተጻፈልህ አንተ ሆይ፥ ሰውነቴ የአንተን ድንቅ ቤዛነት ኃይል እንዴት በሙላት ሊለማመድ እንደሚችል ትገልጥልኝ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን። በነፍስም በሥጋም ለጌታ ቅዱስ ልሆን እናፍቃለሁ።
ጌታ ሆይ! ሰውነቴ የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ፥ በእርሱም ውስጥ ግድ የማይሰጥ ምንም ነገር እንደሌለ፥ እያንዳንዱ ሁኔታውና ተግባሩም ለጌታ ቅድስና ሊሆን እንደሚገባው እጅግ ጥቂት አስተውያለሁ። ይህ እንዲህ ሊሆን እንደሚገባ ባየሁበትም ጊዜ፥ እነዚህን የከተማውን ቅጥሮች ከጠላት አቀራረብ በራሴ ለመጠበቅ አሁንም ፈለግሁ። ይህ የማንነቴ ክፍል ደግሞ ሊጠበቅና ሊቀደስ የሚችለው በእምነት ብቻ፥ እምነት ለአንተ አደራ የሰጠውን አንተ በመቀበልህና በመጠበቅህ ብቻ እንደ ሆነ ረሳሁ።
ጌታ ኢየሱስ ሆይ! ይህን ሰውነት ከፍላጎቶቹ ሁሉ ጋር በእጅህ አሳልፌ ልሰጥ አሁን እመጣለሁ። በድካምና በጭንቀት፥ በመነቃቃትና በደስታ፥ በራብና በችግር፥ በጤናና በብልጽግና፥ ቅዱስ አዳኜ ሆይ፥ ሰውነቴ በየደቂቃው በአንተ ጥበቃ ይሁን። «ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ብልቶቻችሁ ሊቀደሱ ለጽድቅ ባሪያዎች አድርጋችሁ አቅርቡ» ብለህ ትጠራናለህ። አዳኝ ሆይ! በአንተ ያለኝን ከኃጢአት አርነት በማመን የሰውነቴን ብልቶች ሁሉ ለአንተ አቀርባለሁ፤ በአንተ ያለው የሕይወት መንፈስ በብልቶቼ ካለው ከኃጢአት ሕግ አርነት እንደሚያወጣኝ አምናለሁ። በሕይወትም ብኖር ብሞትም አንተ በሥጋዬ ክበር። አሜን።
1. በመገናኛው ድንኳንና በቤተ መቅደሱ ውስጥ ቁሳዊው ክፍል በውስጡ ከሚኖረው ቅድስና ጋር የሚስማማና የእርሱም መገለጫ ሊሆን ይገባው ነበር። ስለዚህ ሁሉ በተራራው ላይ እንደ ታየው ምሳሌ ተሠራ። በዘፀአት የመጨረሻዎቹ ሁለት ምዕራፎች «እግዚአብሔር እንዳዘዘ» የሚለውን አሥራ ስምንት ጊዜ እናገኛለን። ሁሉ ነገር፥ በውጫዊው እንኳ፥ የእግዚአብሔር ፈቃድ መገለጫ ነበረ። እንዲሁም ሰውነታችን እንደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሁሉ ነገር በእግዚአብሔር ቃል ሊመራ፥ በመንፈስ ቅዱስም ሕያው ሊሆንና ሊቀደስ ይገባዋል።
2. በሰውነት ካለው ከዚህ ቅድስና አንዱ ክፍል አድርጎ መጽሐፍ ቅዱስ አለባበስን ይጠቅሳል። ጴጥሮስ «ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት» «የዋህና ዝግተኛ መንፈስ» ካለው ልብስ ጋር የማይስማማ መሆኑን ሲናገር እንዲህ ይላል፦ «እንዲህ በቀድሞ ዘመን በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉት ቅዱሳት ሴቶች ደግሞ ተሸልመው ነበርና።» ቅድስና በአለባበሳቸው ይታይ ነበር፤ ሰውነታቸው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ነበረ።
3. «በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ።» ሕያው የሚያደርገው ኃይሉ በሁለንተናው ሊነግሥ ይገባል። መንፈሳዊውን ከሐሳባዊውና ከማይታየው ጋር ማያያዝ እጅግ ስለ ለመድን፥ ሥጋዊውና በስሜት የሚታወቀው መንፈሳዊ ሕይወታችንን እንዴት እንደሚነኩ፥ በእግዚአብሔርም መንፈስ ገዥነትና መነሣሣት ሥር ሊሆኑ እንደሚገባቸው ለማስተዋል ጊዜና አሳብ እምነትም ያስፈልገናል። ጳውሎስ እንኳ «ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ» ይላል።
4. እግዚአብሔር ከመሬት በተሠራው በአዳም ሰውነት ውስጥ መንፈሱን በእውነት እፍ ካለ፥ መንፈስ ቅዱስ አሁንም ሰውነታችንን በሚቀድሰው ኃይሉ ሕያው ቢያደርግ እንግዳ ነገር ሆኖ አይቈጠር።
5. «ሥጋዊነት የእግዚአብሔር መንገዶች ፍጻሜ ነው።» ይህ የአንድ የጥንት የሃይማኖት ሊቅ ጥልቅ አባባል እጅግ ቸል ስለ ተባለ እውነት ያሳስበናል። የእግዚአብሔር መንፈስ ታላቅ ሥራ ራሱን ከቁስ ጋር ማዋሐድና ለእግዚአብሔር ማደሪያ የሚሆን መንፈሳዊ አካል አድርጎ መሥራት ነው። መንፈስ ቅዱስ ፍጹም ገዥነትን ካገኘ ይህን በሰውነታችን ያደርገዋል።
6. የእምነት ፈውስ የሚባለው የተመሠረተው በሰውነት ውስጥ ስላለው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በዚህ እውነት ላይ ነው። በዘመናት ሁሉ፥ በልዩ መንፈሳዊ መነቃቃት ጊዜያት፥ ክርስቶስ እዚህም እንኳ ሰውነትን የመንፈስ ሕይወትና ኃይል ተካፋይ እንዴት እንደሚያደርገው እንዲያዩ እግዚአብሔር ለአንዳንዶች ሰጥቶአል። ይህን ለሚያዩት፥ ጌታ ኢየሱስ ሰውነትን ለራሱ ገንዘብ ሲያደርግ፥ በቅድስናና በፈውስ መካከል ያለው ማያያዣ እጅግ የቀረበና የተባረከ ነው።