በክርስቶስ ቅዱሳን
መቅድም

ምዕራፍ 1 · 3 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

መቅድም


በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመነሻውና በትርጉሙ «ቅዱስ» ከሚለው ቃል የበለጠ በግልጥ መለኮታዊ የሆነ ቃል የለም። ወደ መለኮት ምሥጢር ከፍ አድርጎ የሚያወጣን፥ ወደ እግዚአብሔር ልጆች መብትና ብፅዕና ጠልቆ የሚያስገባን እንደ እርሱ ያለ ቃል የለም። ይሁን እንጂ ብዙ ክርስቲያኖች ይህን ቃል ፈጽሞ አላጠኑትም፥ አልተረዱትምም።

ባለፉት ሀያ ዓመታት «ቅዱሳን ሁኑ» የሚለው መፈክር በብዙ አብያተ ክርስቲያናትና በክርስቲያን ማኅበራት ከቀድሞው ይልቅ በላቀ ትጋት በመያዙ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ ጥቂቶች አይደሉም። በመጻሕፍትና በመጽሔቶች፥ በጉባኤዎችና በስብሰባዎች፥ በአማኞች ምስክርነትና ሕይወት፥ የቅድስና እንቅስቃሴ ተብሎ የሚጠራው ነገር እውነተኛ መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ምልክቶች አሉን።

ሆኖም ገና ምን ያህል ይጎድላል! ቅድስና ምን እንደ ሆነ እጅግ ከደበዘዘ አሳብ በቀር ሌላ የሌላቸው አማኝ ክርስቲያኖች እንዴት ብዙ ናቸው! ከሚፈልጉትም መካከል ይህን የክርስቶስንና የእግዚአብሔርን ምሥጢር ክፍል ብቻውን ሊገልጥ ለሚችለው ትምህርት ወደ እግዚአብሔር ቃልና ወደ እግዚአብሔር ራሱ መምጣት ምን ማለት እንደ ሆነ ገና ያልተማሩ ስንቶቹ ናቸው! ለብዙዎች ቅድስና፥ ቃሉ በእውነት ምን ማለት እንደ ሆነ ብዙ ሳይታሰብበት፥ ይበልጥ ትጉህ ለሆነው የክርስቲያን ሕይወት የተሰጠ ጠቅላላ መጠሪያ ብቻ ሆኖአል።

ይህችን ትንሽ መጽሐፍ ስጽፍ ዓላማዬ እግዚአብሔር ቃሉን በምን ትርጉም እንደሚጠቀምበት መርምሮ ማግኘት ነበር፤ ይኸውም ለእርሱ ያለው ትርጉም ለእኛም እንዲኖረው ነው። ቃሉ በሚገኝባቸው እጅግ አስፈላጊ በሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በአንዳንዶቹ ውስጥ ተከትዬ፥ በዚያ የእግዚአብሔር ቅድስና ምን እንደ ሆነ፥ የእኛስ ምን ሊሆን እንደሚገባ፥ ወደ እርሱም የምንደርስበት መንገድ የትኛው እንደ ሆነ ለመማር ሞክሬአለሁ። በተለይም የክርስቲያን ሕይወት በሙላቱና በፍጹምነቱ ሁሉ መለኮታዊ መገለጫ የሆነውን እውነተኛ ቅድስና የሚያስገኙት ክፍሎች ምን ያህል ብዙና ልዩ ልዩ እንደ ሆኑ ለማመልከት እጅግ ተግቻለሁ። በዚያው ጊዜም በኢየሱስ አካል ላይ ያተኮረ በመሆኑ በውስጡ ያለውን አስደናቂ አንድነትና ቀላልነት ሁልጊዜ በልቤ ለመያዝ ታግያለሁ። ሥራዬን እየቀጠልሁ ስሄድ፥ ሌሎችን ወደ ልዑል ቅዱስ ስፍራ የውጭ አደባባዮች እንኳ ለመምራት መነሣቴ ምን ያህል ከፍ ያለ ተግባር እንደ ሆነ ይበልጥ በጥልቅ ተሰማኝ። ሆኖም የተግባሩ አስቸጋሪነት ራሱ ምን ያህል አስፈላጊ እንደ ሆነ አሳመነኝ።

መጽሐፉ ለአንዳንዶች ተስፋ የሚያስቆርጥ ይሆንባቸው ይሆናል ብዬ እፈራለሁ። ወደ ቅድስና ሕይወት መግቢያው ብዙ ጊዜ አንድ እርምጃ ብቻ እንደ ሆነ ሰምተዋል። የቅድስናን አስደናቂ ምሥጢር በእምነት ካገኙ ወዲህ በሕይወታቸው ስለ መጣው የተባረከ ለውጥ መናገር የሚችሉ አማኞችን ሰምተዋል ወይም አይተዋል። አሁንም ይህን ምሥጢር ይፈልጋሉ። ምሥጢሩ የሚመጣው እርሱን ለማይፈልጉ፥ ኢየሱስን ብቻ ለሚፈልጉ እንደ ሆነ ሊገባቸው አይችልም። ስለ ቅድስናና ወደ እርሱ ስለሚያደርሰው መንገድ ማወቅ የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ለመማር፥ ለማስታወስና ለመለማመድ ቀላል በሆኑ ጥቂት ትምህርቶች የተሰበሰበበትን መጽሐፍ ቢያገኙ ደስ ባላቸው ነበር። ይህን ግን አያገኙም። ለኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ዛሬም ጴንጤቆስጤ የሚባል ነገር አለ፤ ነገር ግን የሚመጣው ኢየሱስን ብቻ ለመከተል ሁሉን ለተወ፥ በፍጹምም እየተከተለ መምህሩ እንዲገሥጸውና እንዲያስተምረው ለፈቀደ ሰው ነው። በእልፍኝ ውስጥም ሆነ በቅዱሳን ስብሰባዎች ክርስቶስ ከኃጢአት የሚያድን መድኃኒት ሆኖ የሚገለጥባቸው እጅግ የተባረኩ መገለጦች ብዙ ጊዜ አሉ፤ ነገር ግን እነዚህ የሚሰጡት ለተዘጋጀላቸውና ለመቀበል ለተዘጋጁ ነው። ልምዳቸው እንደ ተመኙት ባይሆን እንኳ ሁሉ በኢየሱስ መታመንንና በእርሱ ደስ መሰኘትን ይማሩ። እርሱ ቅዱሳን ያደርገናል። ነገር ግን ኢየሱስ መቀደሳችን በሆነበት በተባረከው የእምነት ሕይወት ውስጥ ገብተንም ሆነ ገና ከሩቅ እየናፈቅነው፥ ሁላችንም አንድ ነገር ያስፈልገናል፤ እርሱም አምላካችን የተናገረውን እያንዳንዱን ቃል በቀላል ልብ፥ በእምነትና በመታዘዝ መቀበል ነው። በተባረከው ቃሉ እንደ ተጻፈ በዘመናት ሁሉ የተገለጠውን አስደናቂውን የእግዚአብሔርን ቅድስና መገለጥ ከወንድሞቼ ጋር አብሬ ለመከተል ስሞክር የእምነታቸው ረዳት እንድሆን ልባዊ ምኞቴ ነበር። የተጻፈውን ተጠቅሞ እግዚአብሔር በልጆቹ ውስጥ ቅዱሳን መሆን እንዳለብን ያለውን እርግጠኝነት፥ እንዴት ቅዱሳን እንደምንሆን ያለውን እውቀት፥ ቅዱሳን ልንሆን እንደምንችል ያለውን ደስታ፥ ቅዱሳንም መሆን እንደምንችል ያለውን እምነት እንዲያበዛ የዘወትር ጸሎቴ ነበር። ክርስቲያንና ቅዱስ የሚሉት ስሞች አንድ ትርጉም እንዲኖራቸው፥ እያንዳንዱም አማኝ የተቀደሰና ለጌታው የሚጠቅም ዕቃ እንዲሆን፥ በሕዝቡ ሁሉ ላይ የቅድስና መንፈስና ኃይል እንዲጎበኝ ሁላችንም ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ እንድንጮኽ ያነሣሣን።

አ. ሙ.

ዌሊንግተን፥ 16 ኖቬምበር 1887።

ቀጣይ