በክርስቶስ ቅዱሳን
ቅድስናና መለየት

ምዕራፍ 11 · 8 ደቂቃ ንባብ · 10 ደቂቃ ማዳመጥ

ቅድስናና መለየት


አሥረኛ ቀን።

«ከአሕዛብ የለየኋችሁ አምላካችሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ። እኔ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና ለእኔ ቅዱሳን ሁኑ፤ የእኔም ትሆኑ ዘንድ ከአሕዛብ ለይቻችኋለሁ።»—ዘሌዋውያን 20፥24, 26።

«ለእግዚአብሔር ራሱን የሚለይበት ወራት እስኪፈጸም ድረስ ቅዱስ ይሆናል…. በተለየበት ወራት ሁሉ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ነው።»—ዘኍልቍ 6፥5, 8።

«ስለዚህ ኢየሱስ ደግሞ በገዛ ደሙ ሕዝቡን እንዲቀድስ ከበር ውጭ መከራን ተቀበለ። እንግዲህ ነቀፌታውን እየተሸከምን ወደ እርሱ ወደ ሰፈሩ ውጭ እንውጣ፤»—ዕብራውያን 13፥12, 13።

መለየት ቅድስና አይደለም፤ ነገር ግን ወደ እርሱ የሚያደርስ መንገድ ነው። ያለ መለየት ቅድስና ሊኖር ባይችልም፥ ወደ ቅድስና የማያደርስ መለየት ሊኖር ይችላል። መለየትን ብቻ ቅድስና አድርጎ ከመቍጠር ከቀኙ ስሕተት፥ ደግሞም ያለ መለየት ቅድስናን ከመፈለግ ከግራው ስሕተት እንጠበቅ ዘንድ ልዩነታቸውንም ግንኙነታቸውንም መረዳት እጅግ አስፈላጊ ነው።

የዕብራይስጡ የቅድስና ቃል መለየት ከሚል ሥር የመጣ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በትርጉማችን «መለየት» ወይም «መከፋፈል» ወይም «ለብቻ ማድረግ» ባለበት ስፍራ ፍጹም ሌሎች ቃላት አሉን። ቅዱስ የሚለው ቃል ያን ልዩ ሐሳብ ለመግለጥ ብቻ ይሠራበታል። የቅዱስ ሐሳብ ሁልጊዜ መለየትን የሚጨምር ቢሆንም፥ እርሱ ራሱ እጅግ ወሰን በሌለው መጠን ከፍ ያለ ነገር ነው። ይህን በሚገባ መረዳት እጅግ አስፈላጊ ነው፤ ለእግዚአብሔር መለየት፥ ለጥያቄው ራስን መስጠት፥ ለአገልግሎቱ መወሰን ወይም ራስን መቀደስ ብዙ ጊዜ ቅድስና እንደ ሆነ ተደርጎ ይነገራልና። ይህ መጀመሪያ፥ ቅድመ ሁኔታ ብቻ እንደ ሆነ የሚለውን ሐሳብ እጅግ አጥብቀን ልናሳስብ አንችልም፤ ቅድስና ራሱ ወሰን በሌለው መጠን ይበልጣል፤ ቅድስና እኔ የሆንሁት ወይም የማደርገው ወይም የምሰጠው አይደለም፥ ነገር ግን እግዚአብሔር የሆነው፥ የሚሰጠኝና የሚያደርግልኝ ነው። የሚቀድሰኝ እግዚአብሔር እኔን መያዙ ነው፤ በእውነት የሚቀድሰው የእግዚአብሔር ሕልውናና ክብሩ ነው። እግዚአብሔር ለእስራኤል የተናገረውን ቃል በጥንቃቄ ማጥናት ይህን ግልጥ ያደርግልናል። በዘሌዋውያን «እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ» የሚለውን አነጋገር ስምንት ጊዜ እናገኛለን። ቅድስና ከእስራኤል ጋር ያለውን ግንኙነቱን ብቻ ሳይሆን ማንነቱንና ባሕርዩን፥ ወሰን የሌለውን የሥነ ምግባር ፍጽምናውን የሚገልጥ የእግዚአብሔር ከፍተኛው ባሕርይ ነው። ይህ ምን ማለት እንደ ሆነ ሥጋዊውንና የጨለመውን የሰው አእምሮ ማስተማር የሚችለው እጅግ በዝግታና ቀስ በቀስ ቢሆንም፥ ገና ከመጀመሪያው እንደ ራሱ እንዲሆኑ፥ እርሱ ቅዱስ ስለ ሆነ እርሱም ቅዱስ እንደ ሆነ ቅዱሳን እንዲሆኑ ዓላማው እንደ ሆነ ለሕዝቡ ይነግራቸዋል። እግዚአብሔር ራሱን ለእነርሱ እንደሚሰጥ ሰዎችን የእርሱ ይሆኑ ዘንድ ለራሱ እንደሚለይ መንገር ስላለው ግንኙነት ይነግረኛል፤ ነገር ግን ስለዚህ ቅዱስ አምላክ እውነተኛ ባሕርይ ወይም ለእኔ ስለሚያካፍለኝ ቅድስና ዋና ዋጋ ምንም አይነግረኝም። መለየት የሚነጻውንና የሚሠራበትን ዕቃ ለብቻ ማድረግና መያዝ ብቻ ነው፤ እውነተኛ ዋጋውን የሚሰጠው በውስጡ በምናኖረው የከበረ ይዘት መሙላቱ ነው። ቅድስና መለኮታዊ ሙላት ነው፤ ያለ እርሱ መለየት ባዶዎች አድርጎ ይተወናል። መለየት ቅድስና አይደለም።

ነገር ግን መለየት ለቅድስና አስፈላጊ ነው። «ከአሕዛብ ለይቻችኋለሁ፥ ቅዱሳንም ትሆናላችሁ።» አንድን ዕቃ ከአጠገቡ ካሉት መርጬ እስካልለየሁት፥ ቢያስፈልግም እስካላነጻሁት ድረስ፥ ልሞላው ወይም ልጠቀምበት አልችልም። በእጄ ሊኖረኝ፥ ለጊዜውም ሙሉና ብቸኛ ሥልጣን ሊኖረኝ ይገባል፤ ያለዚያ የከበረውን ወተት ወይም የወይን ጠጅ ወደ ውስጡ አላፈስስም። እንዲሁም እግዚአብሔር ከግብፅ ባወጣቸው ጊዜ ሕዝቡን ለየ፤ ኪዳኑንና ሕጉን በሰጣቸው ጊዜ፥ ቅዱሳን የማድረግ ዓላማውን ይፈጽም ዘንድ በቍጥጥሩና በኃይሉ ሥር እንዲሆኑ ለራሱ ለያቸው። ለብቻ እስኪያደርጋቸው ድረስ፥ በፍጹም እርሱ ብቻ የእርሱ የሆኑ ልዩ ሕዝብ መሆናቸውን በውስጣቸው እስኪያነቃ ድረስ፥ እንዲሁም ራሳቸውን ለእርሱ እንዲለዩ እስኪያስተምራቸው ድረስ ይህን ሊያደርግ አልቻለም። መለየት ለቅድስና አስፈላጊ ነው።

የናዝራዊ ሥርዓት ይህን ያጸናል፤ መለየት ምን ማለት እንደ ሆነም እጅግ ግልጥ አድርጎ ያሳያል። እስራኤል ቅዱስ ሕዝብ ይሆን ዘንድ ነበረ። ቅድስናው በተለይ በካህናቱ ተመስሎ ነበረ። ስለ እያንዳንዱ እስራኤላዊ ግን ቅዱስ እንደ ሆነ በሙሴ መጻሕፍት የትም አናነብም። ነገር ግን ፈጽሞ ቅዱስ ለመሆን ያለውን ምኞት ሊያሳይ የሚወድ እስራኤላዊ ይህን የሚያደርግባቸው ሥርዓቶች ነበሩ። በዙሪያው ካለው ሕዝብ ተራ ኑሮ ራሱን ለይቶ የናዝራዊን፥ የተለየውን ሰው ኑሮ ሊኖር ይችል ነበር። በዚያ በጥላና በምሳሌ ዘመን ይህ መለየት እንደ ቅድስና ተቈጠረ። «በተለየበት ወራት ሁሉ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ነው።»

መለየቱ በተለይ በሦስት ነገሮች ነበረ፤ ከወይን ፍሬ በመከልከል ራስን መግዛት፤ ጠጕሩን ባለመቈረጡ ወይም ባለመላጨቱ ትሕትና («ወንድ ጠጕሩን ቢያስረዝም ነውር እንደ ሆነ»)፤ አባቱ ወይም እናቱ በሞቱ ጊዜ እንኳ ስለ እነርሱ ራሱን ባለማርከሱ ራስን መሠዋት። በተለይ ልናስተውለው የሚገባን መለየቱ ከተከለከሉ ነገሮች ሳይሆን ከተፈቀዱ ነገሮች መሆኑን ነው። አብርሃም በአባቱ ቤት በመኖሩ ወይም እስራኤል በግብፅ በመቀመጡ በራሱ ኃጢአት የሆነ ነገር አልነበረም። የመለየት መንፈስ የሚገለጠው ኃጢአት መሆኑ ሊረጋገጥ የሚችለውን ብቻ ሳይሆን፥ ይቀድሰን ዘንድ በእግዚአብሔር እጅ ራሳችንን በሙሉ ጽናት መስጠታችንን ሊያደናቅፍ የሚችለውን ሁሉ በመተው ነው።

ይህ እውነት የሚያመለክተንን ትምህርቶች እንማር። ለመለየት ያለውን አስፈላጊነት ማወቅ ይገባናል። ይህ የእግዚአብሔር የዘፈቀደ ጥያቄ አይደለም፥ ነገር ግን በነገሮች ባሕርይ ውስጥ መሠረት አለው። አንድን ነገር መለየት ለመረጠው ሰው ፈቃድ በማይከፋፈል ኃይል ይፈጽምና ዕድሉንም ያገኝ ዘንድ ለአንድ ልዩ ጥቅም ወይም ዓላማ ነጻ ማድረግ ነው። ይህ በሥራ ክፍፍል ሁሉ ሥር ያለው መርሕ ነው፤ ለአንድ የትምህርት ወይም የሥራ ዘርፍ ፈጽሞ መለየት ወደ ስኬትና ወደ ፍጽምና የሚያደርስ መንገድ ነው። በፊቴ ዛፎቹ ሁሉ ቀጥ ብለው እርስ በርሳቸው ተጠጋግተው የበቀሉበት የወርካ ደን አለ። በዳርቻው ከባልንጀሮቹ የተለየ አንድ ዛፍ አለ፤ ከባዱ ግንዱና በሰፊው የተዘረጉ ቅርንጫፎቹ መለየቱ፥ ሥሮቹና ቅርንጫፎቹ የሚዘረጉበት ሰፊ መሬት ለራሱ ጥቅም ተለይቶ መኖሩ የእድገቱና የታላቅነቱ ምስጢር እንደ ሆነ ያስረዳሉ። ሰብአዊ ኃይላችን ውሱን ነው፤ እግዚአብሔር ፈጽሞ ሊይዘን ከሆነ፥ እኛም በእርሱ ፈጽመን ልንደሰት ከሆነ፥ ለእርሱ መለየት ቀላል፥ ተፈጥሮአዊና የማይቀር አስፈላጊ ነገር ብቻ ነው። እግዚአብሔር ራሱን ሁሉ ይሰጠን ዘንድ እኛን ሁላችንን ለራሱ ይፈልገናል።

የመለየትን ዓላማ ማወቅ ይገባናል። ይህም እግዚአብሔር፥ «እኔ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና ለእኔ ቅዱሳን ሁኑ፤ የእኔም ትሆኑ ዘንድ ከአሕዛብ ለይቻችኋለሁ» ባለው ውስጥ ይገኛል። እግዚአብሔር በጥልቁ የቃሉ ትርጉም ለራሱ ለይቶናል፤ ወደ እኛ ይገባ ዘንድ፥ ራሱንም በእኛ ይገልጥ ዘንድ። ቅድስናው የፍጽምናዎቹ ሁሉ ድምርና ማእከል ነው፤ የለየን እንደ ራሱ ቅዱሳን ያደርገን ዘንድ ነው። መለየት በራሱ ምንም ዋጋ የለውም፤ እጅግ የተሳሳተ ወይም ጎጂ ሊሆን ይችላል፤ ሁሉ በታሰበው ዓላማ ላይ የተመሠረተ ነው። እግዚአብሔር እኛን ፈጽሞ ሲያገኘንና ሲይዘን፥ በክርስቶስ ያለው የዘላለም ሕይወት ሕልውናችንን ሁሉ ሲገዛ፥ መንፈስ ቅዱስ በሙላትና በነጻነት በእኛ ሲፈስስ፥ በእግዚአብሔር እንድንኖር እግዚአብሔርም በእኛ፥ ያን ጊዜ መለየት የሥርዓትና የልማድ ነገር ሳይሆን መንፈሳዊ እውነት ይሆናል። ይህም የእግዚአብሔር ዓላማ ሲታይ፥ ሲቀበሉትና ሲከተሉት፥ ከምን መለየት እንዳለብን፥ መለየትም ምን ያህል መሥዋዕት እንደሚጠይቅ የሚሉት አስቸጋሪ ጥያቄዎች ቀላል መልስ ያገኛሉ። እግዚአብሔር ወደ ቅድስናውና ወደ ኅብረቱ ከማያደርሰን ሁሉ ይለየናል።

ከሁሉ በላይ የመለየትን ኃይል፥ በምኞትና በደስታ፥ በነጻነትና በፍቅር መንፈስ ወደ እርሱ የሚመራንን ኃይል ማወቅ ያስፈልገናል። በሰው ቋንቋ ታላቁ የሚለይ ቃል የእኔ የሚለው ቃል ነው። በዚህ ውስጥ የጥረትና የደስታ ታላቅ ምንጭ አለን፤ በሕፃኑ ከመጫወቻዎቹ ጋር፥ በሠራተኛው ከትርፉና ከደመወዙ ጋር፥ ስለ አገሩ በሚሞተው አርበኛ፥ ከሌላው ሁሉ በሚለየው ላይ እጁን የሚጭነው ይህ የእኔ የሚለው ነው። ፍቅር የሚጠቀምበት ታላቅ ቃል ነው። ለእናቱ፥ የእኔ እናቴ ብሎ፥ የእኔ ልጄ የሚለውን መልስ የሚያስገኘው ሕፃን ቢሆን፤ ልጂቱን ከምትወደው ቤትዋና ከወላጆችዋ የእርሱ ትሆን ዘንድ የሚስባት ሙሽራ ቢሆን፤ ወይም «የእኔ ትሆኑ ዘንድ ከአሕዛብ ለይቻችኋለሁ» ብሎ የሚናገረው ቅዱሱ አምላክ ቢሆን፤ ፍቅር ታላቁን ኃይሉን የሚያሳየውና ከሌላው ሁሉ ወደ ራሱ የሚስበው ሁልጊዜ በዚያ የእኔ በሚለው ቃል ነው። እግዚአብሔር ራሱ ከዚህ የበለጠ ብርቱ ማስረጃ አያውቅም፥ «የእኔ ትሆኑ ዘንድ» ከሚለው የበለጠ ኃይለኛ መሳብ ሊያቀርብ አይችልም። ያን ቅዱስ ዓላማ ለማጥናትና ለመረዳት፥ ያን ድንቅ የእኔ የሚለውን ለመስማትና የራሳችን ለማድረግ፥ በዚያ ሁሉን በሚችል ፍቅርም ለመያዝ ራሳችንን በሰጠን መጠን የመለየት ኃይል ወደ እኛ ይመጣል በእኛም ይሠራል።

መለኮታዊ ፍቅር የመለየት ሥራውን የሚሠራበትን ድንቅ መንገድ ደረጃ በደረጃ እናጥና። በቤዛነት መንገዱን ያዘጋጃል። እስራኤል በበጉ ደምና በሚመራው የእሳት ዓምድ ከግብፅ ይለያል። «ውጡ ተለዩም» በሚለው ትእዛዙ ሰውን ለሥራ ያነቃዋል፤ «አምላካችሁ እሆናለሁ» በሚለው ተስፋው ምኞትን ያነሣሣል እምነትንም ያጸናል። በእግዚአብሔር ቅዱሳንና አገልጋዮች ሁሉ፥ በመጨረሻም ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ በሆነው በእርሱ መንገዱን ያመለክታል። በመንፈስ ቅዱስ፥ በቅድስና መንፈስ ኃይል፥ በሚያድረው አምላክ ሕልውና መለየቱን ያትማል። ይህ በእውነት የመለየት ኃይል ነው። የእግዚአብሔር ሕልውና የሚለይ ኃይል፤ ማወቅ የሚያስፈልገን ይህ ነው። ሙሴ፥ «እኔና ሕዝብህ በፊትህ ሞገስ እንዳገኘን በምን ይታወቃል? ከእኛ ጋር በመሄድህ አይደለምን? እንዲሁ እኔና ሕዝብህ በምድር ፊት ካሉ አሕዛብ ሁሉ እንለያለን» አለ። ከዓለምና ከመንፈሱ፥ ከራሳችንና ከፈቃዳችን እውነተኛውን መለየት የሚሠራው፥ የገዛ ራሱ አድርጎ የሚያደርገንና የሚጠብቀን፥ የእግዚአብሔር በእኛ የሚያድር ሕልውና ንቃት ነው። ይህንም መለየት በተቀበልነውና ባከበርነው በጸናንበትም መጠን የእግዚአብሔር ቅድስና ይገባል ይይዘንማል። የጌታ ገንዘብ፥ የራሱ ሕዝብ መሆን የእርሱ ተብሎ ከመቈጠር ወይም ከመታወቅ ብቻ እጅግ ወሰን በሌለው መጠን እንደሚበልጥ፥ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና ማደር ሕልውናችንን፥ ፍቅራችንን፥ ፈቃዳችንንም በራሱ ሕይወትና ቅድስና ከመሙላት ያነሰ ምንም ማለት እንዳልሆነ እንረዳለን። ለራሱ ይለየናል፥ ማደሪያውም እንድንሆን ይቀድሰናል። ክርስቶስ በልብ በማደሩ በገዛ ራሱ ሊይዘን ራሱ ይመጣል። ያን ጊዜም በውስጣችን ባለው በእግዚአብሔር ሕልውና በእውነት የተለየን ነን፥ ተለይተንም እንጠበቃለን።

እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ።

ለራስህ የለየኸኝ አምላኬ ሆይ! ይህን መለኮታዊ መለየት በታላቁ ኃይልህ ለእኔ ሥራና እውነት እንድታደርገው እለምንሃለሁ። በውስጥ በመንፈሴ ጥልቅ፥ በውጭም በግንኙነቴ ሁሉ የአምላኬ የመለየት አክሊል በእኔ ላይ ይሁን።

አምላኬ ሆይ፥ በተለይ ከራስ መለየትን በኃይል እንድትፈጽም እለምንሃለሁ! በጌታዬ በኢየሱስ ማደር ያለው ሕልውናህ ራስን ከዙፋን የሚያባርር ኃይል ይሁን። በጥላቻ ከእርሱ ተመልሻለሁ፤ አባቴ ሆይ፥ ልጅህን በእኔ ፈጽመህ ግለጠው! እርሱ ራሱ በእኔ ስፍራ ሲቆም የአንተ አድርጎ ሊጠብቀኝ የሚችለው በልቤ መንገሡ ነው።

አቤቱ፥ ለክብርህና ሕዝብህ ለሚያስፈልገው፥ ሁሉን ለእግዚአብሔር ፈጽሞ መተው ስላለው ብፅዕና፥ እርሱ ብቻ የእርሱም ብቻ እሆን ዘንድ ምንም ስለማያስቀር መለየት እመሰክር ዘንድ ማወቅን አገኝ ዘንድ፥ በውጭው ኑሮዬ መለኮታዊ ጥበብን እጠብቅ ዘንድ ጸጋን ስጠኝ።


ቅዱስ ጌታ አምላክ ሆይ! ሕዝብህን ጎብኝ። አቤቱ፥ ከዓለምና ከእርሱ ጋር ከመመሳሰል አውጣቸው። አቤቱ፥ ለይ፥ የአንተ የሆኑትን ለራስህ ለይ። አቤቱ፥ ስንዴውን ከገለባው ለይ፤ እንደ እሳት ወርቁን ከዝገቱ ለይ፤ የጌታ የሆኑት፥ ቅዱሳኑም እነማን እንደ ሆኑ ይታይ ዘንድ። አሜን።

1. ፍቅር በእውነት ይለያል። ባል ሚስቱን፥ እናት ልጆችዋን፥ ንፉግ ሀብቱን በምን ያለ ቅናት ይጠይቃል! የእርሱ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር እንዴት ወደ ራሱ እንዳመጣህ መንፈስ ቅዱስ ያሳይህ ዘንድ ጸልይ። «እርሱ ቅዱስ አምላክ ነው፤ ቀናተኛ አምላክ ነው።» በልብ የፈሰሰ የእግዚአብሔር ፍቅር መለየትን ቀላል ያደርጋል።

2. ሞት በእውነት ይለያል። በክርስቶስ በእውነት እንደ ሞትሁ ራሴን ብቈጥር፥ በክርስቶስ ሞት ኃይል ከራሴ ተለይቻለሁ። ሕይወት ደግሞ ይበልጥ በብርቱ ይለያል። «እኔ አይደለሁም፥ ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል» ስል ከራስ ኑሮ ወደ ላይ እነሣለሁ።

3. መለየት ሊገለጥ ይገባዋል፤ ለሌሎችና ለራሳችን ምስክር ይሆን ዘንድ የታሰበ ነው፤ በውስጥ እውነተኛና ብርቱ ሊሆን ከሆነ በውጭ መገለጫ ሊያገኝ ይገባዋል። የምሳሌያዊ ድርጊት ጠባይ ስሜትን መግለጡ ብቻ ሳይሆን የሚስማማውን ስሜት መመገቡና ማበርታቱ ነው። ነፍስ ወደ እግዚአብሔር ኅብረት ስትገባ፥ አንዳንድ ጊዜ ለሌሎች ምንም ጉዳት የሌለው ከሚመስለው እንኳ ውጫዊ መለየት እንደሚያስፈልጋት ይሰማታል። ለእግዚአብሔር በትሕትና ራስን በመቀደስ መንፈስ ከተነሣሣ፥ ውጫዊው ነገር እውነተኛውን መለየት እጅግ ሊያበረታ ይችላል።

4. ለእግዚአብሔር መለየትና በእርሱ መያዝ አብረው ይሄዳሉ። ይህ ለሰማዕታት፥ ለአማኞች፥ ለሚስዮናውያን፥—ሁሉን ስለ መተው ግልጥ መግለጫ ለሰጡ ሁሉ የመጣ በረከት ነው።

5. መለየት በፍቅር ይጀምራል በፍቅርም ይፈጸማል። የመለየት መንፈስ ራስን የመሠዋት፥ ለእግዚአብሔር ፍቅር ራስን የመስጠት መንፈስ ነው፤ በእውነት የተለየው እጅግ አፍቃሪና ፍቅርን የሚስብ፥ እግዚአብሔርንና ሰውን ለማገልገል ራሱን የሰጠ ይሆናል። ኢየሱስን ከሌሎች ሁሉ የሚለየው፥ የሚያስታውቀውስ፥ ራሱን የሚሠዋው ፍቅሩ አይደለምን? ይህ እንደ እርሱ ልንሆንበት የሚገባን መለየቱ ነው።

6. የእግዚአብሔር ቅድስና መለየቱ ነው፤ ከዓለም ወደ ተለየው ወደ እርሱ መለየት እንግባ፤ ያ ቅድስናችን ይሆናል። ራስህን ከእግዚአብሔር ጋር አንድ አድርግ። ያን ጊዜ የተለየህና ቅዱስ ነህ። እግዚአብሔር ለራሱ የሚለየው ከውጭ በሚሠራ ድርጊት ሳይሆን ፈቃዱና ሕልውናው ሲይዙን ነው።

ጨርሰዋል፦ ቅድስናና መለየት

ቀዳሚ ቀጣይ