ምዕራፍ 18 · 7 ደቂቃ ንባብ
ከዚህ በላይ ምን እላለሁ?
«እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና። እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ።
ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ። እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ ስላሰበ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም» (ዕብራውያን 11:32-40)።
ምዕራፉን የሚደመድሙት እነዚህ ዘጠኝ ቍጥሮች የእኔን መነሻ ሐሳብ በግልጽ ያረጋግጣሉ። በእምነት ብዙዎች ታላላቅ ሥራዎችን ሠሩ፣ ታላላቅ ተአምራትንም አዩ፤ በእምነትም ሌሎች በታላቅ ሥቃይና ጭንቀት ውስጥ አለፉ። ይህ የሆነው በማመናቸው ምክንያት ሳይሆን፣ በመከራም ውስጥ እንኳ በሕዝቡ ይከበር ዘንድ የእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ስለ ነበረ እንደ ሆነ እርግጥ ነው። ከኀዘኑና ከሥቃዩ እንዲያመልጡ የማይፈቅድላቸው የእውነት ውስጣዊ ምስክርነት ስለ ነበራቸው ፈቃደኞች ሆኑ። አሳዳጆቻቸው እንደ ጠየቋቸው ጌታቸውን ክደው ቢሆን ኖሮ ሊያመልጡ በቻሉ ነበር።
ቅዱሱ ጸሐፊ ነጥቡን በዚህ ምዕራፍ ቀደም ባሉት ምሳሌዎች አስረድቶአል። አሁን ግን ብዙ ስሞችን በአንድነት ይደረድራል፤ በዘመን ቅደም ተከተልም እንኳ አይደለም፤ ይህ ግን አንባቢዎቹን አያስጨንቃቸውም፤ የእያንዳንዱን አዲስ ስም ታሪክ በሚገባ ያውቃሉና። እነዚህ ስሞችና ሥራዎች በፍጥነት ሲወረወሩብን የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ልናጣው እንችላለን፤ ለአይሁድ ግን እያንዳንዱ ሐረግ ሕያው ትዝታ ያስነሣ ነበር።
የጥንቱ የታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ ዳዊት እንዴት «መንግሥታትን ድል እንደ ነሣ» ሲገልጽ ጸሐፊያችን የተጠቀመበትን ያንኑ የግሪክ ሐረግ ተጠቅሞአል።
ሰብዓ ሊቃናት — የብሉይ ኪዳናችን የግሪክ ትርጉም — ዳዊት እንዴት «ጽድቅን እንዳደረገ»፣ እምነት ለዳንኤል እንዴት «የአንበሶችን አፍ እንደ ዘጋ»፣ ለሲድራቅ፣ ለሚሳቅና ለአብደናጎም እንዴት «የሚነድደውን እሳት እንዳጠፋ» ለመናገር ያንኑ ቃል ይጠቀማል።
«ከሰይፍ ስለት ማምለጥ» የሚለው አባባል የአንባቢዎቹን ሐሳብ ኤልያስና ኤልሳዕ ከኤልዛቤልና ከሶርያውያን ወደ ዳኑበት ታሪክ ይመልሰው ነበር። ሌሎች ምሳሌዎች በብሉይ ኪዳናችን ውስጥ ካልተመዘገቡ፣ ነገር ግን የአዋልድ መጻሕፍትን በተለይም ሁለተኛውን የመቃብያን መጽሐፍ ለሚያነቡ ሰዎች በሚገባ ከሚታወቁ የታማኞች ሕይወት የተወሰዱ ናቸው። «በጦርነት ኃይለኞች መሆን» እና «የባዕድ ጭፍሮችን ማባረር» የሚሉት ሐረጎች የመቃብያንን ዘመን የማይረሳ ክብር ወዲያውኑ እንደሚያሳስቧቸው ጥርጥር የለውም።
ነገር ግን የእምነት ታሪኮች በሰው ዓይን ሲታዩ ሁልጊዜ የድል ታሪኮች አይደሉም። ምዕራፉ በቍጥር 34 ቢያበቃ ኖሮ፣ በእግዚአብሔር ለሚያምኑ መልካም ነገሮች ብቻ — ጤና፣ ሀብትና ብልጽግና — ይደርሳሉ ብለን ለማመን እንፈተን ነበር፤ ይልቁንም ሞት፣ ስደትና መከራ ይገኛል። ይህስ በእምነት ሊሆን ይችላልን? አዎን! አዎን! አዎን! እግዚአብሔር በዚህ የሚከበር ከሆነ፣ አዎን! እርሱም በሕዝቡ መከራ ተከብሮአል።
የዮሐንስን ወንጌል ሳነብ ኢየሱስ ስለሚመጣው ክብሩ ብዙ ጊዜ እንደሚናገር አገኛለሁ። «ክብር» የሚለውን ቃል ስታነብ ምን ታስባለህ? ለመተርጐም ሞክሬ በመጨረሻ የተገለጠ የእግዚአብሔር ሙላት ነው ብዬ ደመደምሁ። ኢየሱስ በዮሐንስ 17:1 ላይ «አባት ሆይ፥ ሰዓቱ ደርሶአል፤ ልጅህ ደግሞ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው» አለ፤ ወደ መስቀልም ሄደ። በእርግጥም በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ስለ ክብር የሚናገር እያንዳንዱ ቃል ከኢየሱስ ሞት ጋር የተያያዘ ነው! ክብር የሚመጣው በመከራ በኩል ነው!
የመቃብያን ታሪክ በክፉው ሶርያዊ በአንጥያኮስ ኤጲፋንስ ዘመን ስለ ታማኝ አይሁድ መከራና ሰማዕትነት በሚናገሩ መዛግብት የተሞላ ነበር። እነዚህ የዕብራውያን አንባቢዎች ከላይ ካሉት ሐረጎች ጋር በሚገባ ሊያዛምዷቸው የሚችሏቸው ታሪኮች ናቸው፤ ከሐዋርያትና ከዕብራውያን ጸሐፊ ዘመን ጀምሮ ያለው የቤተ ክርስቲያን ታሪክም ብዙ ተመሳሳይ ዘገባዎች አሉት።
እንዲህ ብለን ልንጽፍ እንችላለን፦ «በእምነት እስጢፋኖስ ‹ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው!› እያለ ጮኾ ተገደለ»። በዚህ የእምነት ተግባር የጠርሴሱን ሳውልን ከእግዚአብሔር ኵነኔ ፈታው፤ በዚህም እግዚአብሔር ሳውልን ወደ ሐዋርያው ጳውሎስ ታላቅ አገልግሎት እንዲጠራው መንገድ ከፈተ። እስጢፋኖስ ለጭንቀቱ የእግዚአብሔርን ቍጣ በሳውል ላይ በመጥራት ምላሽ ሰጥቶ ቢሆን ኖሮ (እኔ ብሆን እንዲህ ለማድረግ እንደምፈተን እመሰክራለሁ!)፣ ሳውል ታላቁ ሐዋርያ ይሆን ነበርን ብዬ አስባለሁ።
በእምነት ጳውሎስ በሮም ታሰረ፤ ይህም ለቍጥር ለሌላቸው አማኞች እጅግ የብርታትና የምሪት ምንጭ የሆኑትን ታላላቅ መልእክቶች የሚጽፍበት ጊዜ እንዲያገኝ ነው።
በእምነት የቀደሙት አማኞች ተሰደዱ፤ ይህም ከአሳዳጆቻቸው ሲሸሹ ወንጌል በመላው የሮም ዓለም እንዲስፋፋ ነው።
በእምነት ክራንመር፣ ሪድሊና ላቲመር በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በእንጨት ላይ ታስረው በእሳት ተቃጠሉ፤ ይህም «በእንግሊዝ ፈጽሞ የማይጠፋ ብርሃን እንዲበራ» ነው (ሂው ላቲመር)።
በእምነት ሚስዮናውያን በሃያኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ከቻይና እንዲወጡ ታዘዙ፤ ይህም በቻይና ባህል ውስጥ የምዕራባውያን ቤተ ክርስቲያን ቅጂ ያልሆነች ንጹሕ የአማኞች ቤተ ክርስቲያን እንድታድግ ነው። በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው የምዕራባውያን የቤተ ክርስቲያን አስተሳሰብ ብቻ ነው የሚል የተጣመመ አመለካከት ላለን ለብዙዎቻችን ይህ ከባድ ነገር ነው። በጉዞዎቼ የእኛ «የምዕራባውያን» ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ዘንድ ከሁሉ ያነሰ ተቀባይነት ያላት ናት ወደሚለው የተጠራጣሪ አቋም ልደርስ ምንም አልቀረኝም!
አንዳንዶች ሚስዮናውያኑ ከወጡ ወዲህ በቻይና ያለችው ቤተ ክርስቲያን እጅግ ብዙ ሚሊዮኖች መድረሷን አይቀበሉም። ሐሳቤ በተሳሳተ መንገድ እንዳይረዳ እዚህ ላይ ልጨምር፤ በሚስዮን ሥራና በሚስዮናውያን አጥብቄ አምናለሁ። አንዳንድ ጊዜ ግን የአሠራር ዘዴዎቻችንንና የአንድነታችንን ጕድለት መቀበል ይከብደኛል። ጌታ ይመስገን፣ ይህ በቅርብ ዘመናት የሚስዮን ታሪክ ውስጥ እየቀነሰ መጥቶአል።
በእምነት አምስት አሜሪካውያን ወጣቶች የኦካ ሕንዶችም ከእኛ ጋር የወንጌል ባለ ጠግነት ወራሾች እንዲሆኑ ጃንዋሪ 8 ቀን 1956 በኢኳዶር ጫካዎች ውስጥ ሞቱ። የዓለም ጋዜጦች ርዕሰ አንቀጾች ይህን የአሜሪካውያን ወጣቶች ሕይወት ታላቅ ብክነት ብለው ጠሩት፤ ነገር ግን ከእነርሱ አንዱ ጂም ኤሊየት ከመሞቱ ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ በማስታወሻ ደብተሩ እንደ ጻፈው፦ «ሊያጣው የማይችለውን ለማግኘት ሊያቆየው የማይችለውን የሚሰጥ ሰው ሞኝ አይደለም!» (ጂም ኤሊየት)። ይህ በእምነት ለመመላለስ የሚሹ ሁሉ መመሪያ ቃል ሊሆን ይገባዋል።
የፒት ፍሌሚንግ፣ የሮጀር ዩደሪያን፣ የኤድ ማካሊ፣ የኔት ሴንትና የጂም ኤሊየት ስሞች ከሚስቶቻቸው ስሞች ጋር በሰማይም በሲኦልም በሚገባ የታወቁ ናቸው። በደረሰባቸው ሞትና ሥቃይ አማካይነት የኦካ ሕንዶችን በኃጢአት ምርኮ ውስጥ አስሮ በያዛቸው የወኅኒ ቅጥር ላይ ሰፊ ክፍተት ተከፍቶአልና።
ዛሬ ከእነዚያ ውድ ሰዎች ብዙ ሺዎች በዚያ ክፍተት አልፈው በክርስቶስ ብቻ ወደሚገኘው ነጻነት በመግባታቸው ደስ ሊለን ይችላል።
አንባቢዬ ሆይ፣ ይህን ታሪክ የማታውቀው ከሆነ፣ የጂም ባልቴት ኤሊዛቤት ኤሊየት የጻፈችውን «በክብር በሮች በኩል» የተሰኘውን መጽሐፍ እንድታነብ አበረታታሃለሁ።
የሰማዕታት ሞት የቤተ ክርስቲያን የሕይወት ደም ሆኖአል በሚለው አባባል በእውነት ልንስማማ እንችላለን። ዛሬ፣ በሃያኛው ክፍለ ዘመን፣ ምናልባት በታሪክ ከማንኛውም ጊዜ የበለጠ ሰማዕትነትና ስደት አለ፤ ሆኖም ቤተ ክርስቲያን አልተሸነፈችም፤ እጅግ በፈጠነ ሁኔታም ማደጓን ቀጥላለች።
አንዳንዶች በውኆች፣ አንዳንዶች በጐርፍ፣ አንዳንዶች በእሳት፣ ሁሉም ግን በደሙ፤ አንዳንዶች በታላቅ ኀዘን፣ እግዚአብሔር ግን ዝማሬን ይሰጣል፣ በሌሊት ወራት ቀኑንም ሙሉ።
(ጂ. ኤ. ያንግ) በእምነት (ስምህ) አብ ይበልጥ እንደ ሌላው ልጁ እንደ ኢየሱስ ሊያደርገው ስለ ወደደ ወደ አዲሱ የሥቃይ ሸለቆ ገባ ብለንስ ልንጽፍ አንችልምን?
«እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ ስላሰበ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም» (ዕብራውያን 11:39-40)።
እነዚህ የእምነት ወንዶችና ሴቶች ሁሉ ለእኛ ምሳሌ እንዲሆኑ ተመዝግበዋል። በዚህ ሕይወት ስለ ታማኝነታቸው ምንም ዋጋ አልተቀበሉም። በእግዚአብሔር እምነት ነበራቸው። ታመኑበት፤ ለእነርሱና በውስጣቸው የተናገረውንም ቃል ታዘዙ፤ ሆኖም ዛሬ የእኛ የሆነውን «የሚበልጥ ነገር» አልተቀበሉም ነበር።
የታማኝነታቸው ዋጋ ለእያንዳንዱ ሰው እንደሚገባው በሚሰጠው በአዳኙ በክርስቶስ ዘንድ ይገኛል — በዓለም ወይም በቤተ ክርስቲያን ዓይን ስላለው ታላቅነቱ ሳይሆን ስለ እምነቱ። ከዚህም በላይ የአብ የተስፋ ቃል የሆነው (የሐዋርያት ሥራ 1:4) በውስጣችን የሚኖር መንፈስ ቅዱስ ተሰጥቶናል፤ «የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእኛ ዘንድ» ነው፤ ወደ እውነትም የሚመራን እርሱ ነው። ለውስጣዊ መገለጡ ራሳችንን ስናስገዛ በእምነት እንድንመላለስ የሚያስችለን የእርሱ ውስጣዊ ምስክርነት ነው። ወደ የሚያድን እምነት ያመጣን እርሱ ነው፤ በሕያው ውኃ ምንጮች አጠገብ ስንቆምም በውስጣችን የእምነትን ፍሬ ያፈራል። ከሕያው ውኃ ወንዞች አብዝተን ስንጠጣ በጊዜው ፍሬ እናፈራለን።
አቤቱ ጌታ ሆይ፣ በፈቃድህ ልመላለስ እናፍቃለሁ። ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፥ እንዲሁ ልቤ ወደ አንተ ይናፍቃል። በፈቃድህ ምራኝ። ፈቃድህን ለማወቅም ሆነ በእርሱ ደስተኛ ለመሆን አልለምንም። በጥልቅ ሸለቆዎች ውስጥ ብትመራኝ ለመሄድ ፈቃደኛ ነኝ፤ በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ እንኳ አጽናኜ ትሆናለህና። ምን ያህል ሞኝና እልኸኛ መሆን እንደምችል አውቃለሁ፤ ስለዚህ ከፈቃድህ በወጣሁ ጊዜ ሁሉ ገርፈህ ወደ መስመሩ እንድትመልሰኝ ሙሉ ፈቃድ ሰጥቼሃለሁ። የምለምነው አንድ ነገር ብቻ ነው፤ በዚህ ጕዞ መጨረሻ «መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ!» ስትለኝ እንድሰማ ነው።
የእምነት ሥዕል በእኔ ዘንድ ይህ ነው፤ የሰማዩን አባቴን እጅ የያዝሁ ትንሽ ልጅ ብቻ ነኝ።
ዛሬ እንደ ሕይወት «ከረሜላ መሸጫ ሱቅ» ወዳሉ ደስ ወደሚያሰኙ ስፍራዎች ይወስደኝ፣ ወይም በምትኩ ወደ «ጥርስ ሐኪም» ሥቃይ ይወስደኝ እንደ ሆነ አላውቅም። ወደ መጀመሪያው ብዙ ጊዜ ብሄድ ወደ ሁለተኛው ሊወስደኝ ግድ እንደሚሆንበት ግን አውቃለሁ!
ነገ ወደ ጥልቅ ሸለቆ ይመራኝ እንደ ሆነ አላውቅም፤ ነገር ግን ባለፈው ሕይወቴ ከእርሱ ጋር ወደ ተራራ ጫፎች ከመውሰዱ በፊት እንደዚህ ያሉ ሸለቆዎች ሁልጊዜ እንደ ነበሩ አውቃለሁ።
ለእኔ ያለው ፈቃዱ ምን እንደ ሆነ አላውቅም (መጽሐፍ ቅዱስ ለሁላችንም ከሚገልጠው በቀር)፤ ነገር ግን ከፊት ያለውን መንገድ እርሱ እንደሚያውቀው አውቃለሁ።
ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ አላውቅም፤ ነገር ግን ነገን የሚይዘውን አውቃለሁ፤ እርሱም እጄን ይዞአል!
«ስለ እኔ የሞትኸው ውድ መለኮታዊ ጌታዬ ሆይ፣ ሕይወቴ ሁሉ ለአንተ በሚሆን ምስጋና እንዲሞላ እወዳለሁ።
ፈቃዴ ሁሉ የአንተ ይሁን፣ በመለኮታዊ ፍቅር ይገዛ፤ ኃያል አዳኝ ሆይ፣ ሕይወትህን በእኔ ውስጥ ኑር።
አዝማች፦ ውድና መለኮታዊ ፈቃድህን በደስታ የራሴ አደርገዋለሁ፤ ልቤ ዙፋንህ ይሆናል፣ የአንተ ብቻ።
የምሄድበትን መንገድ አንተ ምረጥልኝ፣ ወደምመራበትም ስፍራ፤ ኃያል አዳኝ ሆይ፣ ተከትዬ እንድሄድ እርዳኝ።
ዳግመኛ የተወለድሁ መንገደኛ፣ አልፎ ሂያጅ እንግዳ ነኝ፤ የአንተ ስለ ሆንሁ ከዚህ ዓለም አይደለሁም።
ከሚያልፈው ትርኢቱ ተለይቼ፣ ፍቅርህን ለማወቅ ተለውጬ፣ ኃያል አዳኝ ሆይ፣ እጄን በእጅህ ያዝ።
ክፉ ጠላቶች ሲያጠቁኝና ሊያሸንፉኝ ሲቃረቡ፣ በዚያች የጨለማ ሰዓት ኃይሌና ጋሻዬ ሁን።
በዚያን ጊዜ ብርቱ እቅፍህን ስጠኝ፣ በጸጋህ ደግፈኝ፤ ኃያል አዳኝ ሆይ፣ በድካሜ ኃይሌ ሁን።
አዎን፣ በዚህ መንገድ ልትመራኝ የወደድህበትን ምክንያት ባላይም፣ መንገዴን አንተ ምረጥልኝ።
አድካሚው መንገድ ወደ ብርሃን ቀን ግዛት እንደሚያደርስ አውቃለሁ፤ ኃያል አዳኝ ሆይ፣ በዚያ ከአንተ ጋር እኖራለሁ።»
(ኤች. ቲ) — ፈቃድ ተጠይቆአል።
ፍጻሜ
ምዕራፍ 18 ተጠናቋል
ከዚህ በላይ ምን እላለሁ?