በነዶዎች መካከል የተለቀመ
በድካም ውስጥ ያለ ብርታት

ምዕራፍ 5 · 2 ደቂቃ ንባብ

በድካም ውስጥ ያለ ብርታት

በድካም በኩል የሚገኝ ብርታት

በክርስቶስ ብርቱ የምትሆንበት መንገድ በራስህ ደካማ መሆን ነው። የሰው ኃይል ሁሉ ተጨልፎ እስኪያልቅ ድረስ እግዚአብሔር በሰው ልብ ውስጥ ኃይልን አያፈስስም። የክርስቲያን ሕይወት በእግዚአብሔር ጸጋና ብርታት ላይ በየዕለቱ የመደገፍ ሕይወት ነው።

የብርታት ምሥጢር

አማኝ ሆይ፥ ለቤተ ክርስቲያን ስለ ጠቀምህና በዘመንህ ጥቂት አገልግሎት ስለ ፈጸምህ ትታበያለህን? አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? በጨለማው ላይ ጥቂት ብርሃን አብርተሃልን? አሃ! መብራትህን ያበራው ማን ነው? አሁንም እንድታበራ የሚያደርግህና እንዳትጠፋ የሚጠብቅህ ማን ነው? ፈተናን አሸንፈሃልን? ሰንደቅህን አትስቀል፤ ደረትህንም በክብሩ አታስጌጥ፤ በውጊያው ብርቱ ያደረገህ ማን ነውና? ሰይፍህን የሳለው፣ ጠላትን ለመምታትም ክንድህን ያበረታው ማን ነው? አስታውስ፤ በራስህ ምንም ነገር አላደረግህም። ዛሬ ያጌጥህና በወርቅ የተለበጥህ የክብር ዕቃ ብትሆን፣ አሁን እጅግ ጣፋጭ በሆነ ሽቱ የተሞላህ ውድ ማሰሮ ብትሆን፣ ራስህን እንዲህ ያደረግህ አንተ አይደለህም። አንተ ጭቃ ነህ፤ ሸክላ ሠሪው ግን ማን ነው? የክብር ዕቃ ብትሆንም ለራስህ ክብር የሆንህ ዕቃ ሳትሆን ለሠራህ ለእርሱ ክብር የሆንህ ዕቃ ነህ። መላእክት ከወደቁት መናፍስት በላይ ከፍ ብለው እንደሚቆሙ አንተም ከሰዎች መካከል ተለይተህ እንደ ተመረጠ ሰው ብትቆም፣ እንድትመረጥ ያደረገህ በአንተ ያለ አንዳች መልካምነት እንዳልሆነ አስታውስ፤ ከረግረጉ ጭቃ አውጥቶ እግርህን በዓለት ላይ ያቆመውና አረማመድህን ያጸናው የአንተ ጥረት ወይም የአንተ ኃይል አልነበረም። ዘውዱን ከትዕቢተኛ ራስህ አውርድ፤ ክብርህንም በሰጠህ በእርሱ እግር ሥር አኑር። ከኪሩቤልና ከሱራፌል ጋር ፊትህን ሸፍነህ «ለእኛ አይደለም፥ ለእኛ አይደለም፤ ነገር ግን ክብር ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ለስሙ ይሁን» ብለህ ጩኽ።

እንዲህ በትሕትና ስትጐነበስም ይህን ሌላ ትምህርት ለመማር ተዘጋጅ፦ ዳግመኛ በራስህ ፈጽሞ አትደገፍ። የምትሠራው ነገር ቢኖር በሥጋ ክንድ ተደግፈህ ልትሠራው አትውጣ። አስቀድመህ ጕልበትህን አንበርክክ፤ ብርቱ ከሚያደርግህ ከእርሱም ኃይልን ለምን፤ ከዚያም ከሥራህ ደስ እያለህ ትመለሳለህ። በራስህ ኃይል ብትሄድ ግን ማረሻህን በዓለት ላይ ትሰብራለህ፤ ዘርህን በጨዋማው ባሕር አጠገብ በምድረ በዳ አሸዋ ላይ ትዘራለህ፤ በሚመጡትም ዓመታት ባዶውን እርሻ ትመለከታለህ፤ ልብህንም ደስ የሚያሰኝ አንዲት ቡቃያ እንኳ አይሰጥህም። «ለዘላለም በእግዚአብሔር ታመኑ፤ በጌታ በእግዚአብሔር የዘላለም ብርታት አለና።» በራስህ በማናቸውም ኃይል እስካረፍህ ድረስ ያ ብርታት ለአንተ አይገኝም። ድካምህን ብትናዘዝ ይረዳሃል፤ በራስህ ብርቱ ብትሆን ግን የራሱን ኃይል ከአንተ ይወስዳል፤ አንተም ትሰናከላለህ፤ ትወድቃለህም። እንግዲያስ በየዕለቱ በእግዚአብሔር የመደገፍን ጸጋ ተማር፤ እንዲሁ ተገቢ የሆነውን ትሕትና ትለብሳለህ።

የብርታት መጨመር

እግዚአብሔር በቀኙ የተከላቸው ተክሎች ገና ችግኞች ሳሉ የሚደርሱባቸው ችግሮች፣ እንደ ዝግባ ጠንክረው ሥር ከሰደዱ በኋላ በዙሪያቸው ከሚነፍሱት ጋር ሲነጻጸሩ እጅግ ጥቃቅን ናቸው። ስንበረታ፣ ብርታታችን በጨመረ መጠን ሥቃያችን፣ ፈተናዎቻችን፣ ድካማችን ወይም ወደ ኃጢአት የሚስቡን ፈተናዎች በእርግጥ ይበዛሉ። የእግዚአብሔር ኃይል ለማንም ሰው ተከማችቶ እንዲቀመጥ ፈጽሞ አይሰጥም። እንድንበረታ የሚሰጠን ምግብ እስራኤላውያን በምድረ በዳ እንደ ለቀሙት መና ወዲያውኑ ጥቅም ላይ እንዲውል የታሰበ ነው። ጌታ በቃል ኪዳኑ ተስፋ የሰጠንን የብረት ጫማ በእግራችን ሲያጠልቅልን፣ እንድንሄድበት ነው እንጂ በቤተ መዘክራችን አስቀምጠን እንደ ልዩ ዕቃ እንድንመለከተው አይደለም። ብርቱ እጅ ቢሰጠን፣ የምንዋጋው ብርቱ ጠላት ስላለን ነው። ከጥንት ለኤልያስ እንዳደረገው ታላቅ መብል ቢሰጠን፣ በዚያ መብል ኃይል የአርባ ቀን መንገድ እንድንሄድ ነው።

ገጽ 1 / 1 · 2 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል