ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈው የቀሌምንጦስ የመጀመሪያ መልእክት
ከጻድቃን ጋር እንተባበር፤ ክርክራችሁ ጎጂ ነው

ምዕራፍ 46 · 1 ደቂቃ ንባብ · 1 ደቂቃ ማዳመጥ

ከጻድቃን ጋር እንተባበር፤ ክርክራችሁ ጎጂ ነው

ወንድሞች ሆይ፥ እንግዲህ እንደነዚህ ያሉትን ምሳሌዎች መከተል ይገባናል፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፦ «ከቅዱሳን ጋር ተባበሩ፤ ከእነርሱ ጋር የሚተባበሩ [ራሳቸው] ይቀደሳሉና።» ደግሞም በሌላ ስፍራ [መጽሐፍ] እንዲህ ይላል፦ «ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤ ከምርጥ ሰው ጋር ምርጥ ትሆናለህ፤ ከጠማማ ሰው ጋርም ጠማማ ሆነህ ትገለጣለህ።» እንግዲህ ከንጹሓንና ከጻድቃን ጋር እንተባበር፤ እነዚህ የእግዚአብሔር ምርጦች ናቸውና። ስለ ምን በመካከላችሁ ክርክርና ሁከት፥ መለያየትና መከፋፈል፥ ጦርነትም ይሆናል? [ሁላችንም] አንድ አምላክና አንድ ክርስቶስ የለንምን? በላያችን የፈሰሰ አንድ የጸጋ መንፈስ የለምን? በክርስቶስስ አንድ መጠራት የለንምን? ስለ ምን የክርስቶስን ብልቶች እንከፋፍላለን፥ እንገነጣጥላለንም? ስለ ምንስ በገዛ አካላችን ላይ ክርክርን እናስነሣለን? «እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን» የሚለውን እስክንረሳ ድረስ ስለ ምን ወደዚህ ያህል እብደት ደረስን? የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል አስቡ፤ እንዲህ ብሎአልና፦ «[በእርሱ ጠንቅ ማሰናከያ ለሚመጣበት] ለዚያ ሰው ወዮለት! ከምርጦቼ አንዱን ከሚያሰናክል ይልቅ ባልተወለደ ይሻለው ነበር። አዎን፥ ከታናናሾቼ አንዱን ከሚያሰናክል ይልቅ የወፍጮ ድንጋይ [በአንገቱ] ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ቢሰጥም ይሻለው ነበር።» መለያየታችሁ የብዙዎችን [እምነት] ገለበጠ፤ ብዙዎችን ተስፋ አስቈረጠ፤ በብዙዎች ዘንድ ጥርጣሬን አስነሣ፤ ሁላችንንም አሳዘነ። ዓመፃችሁም ገና አልቆመም።

ገጽ 1 / 1 · 1 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ