ምዕራፍ 43 · 1 ደቂቃ ንባብ · 1 ደቂቃ ማዳመጥ
ሙሴ ስለ ክህነት ክብር የተነሣውን ክርክር ጸጥ አሰኘ
እንግዲህ በክርስቶስ ሆነው ከእግዚአብሔር ዘንድ እንዲህ ያለ አደራ የተሰጣቸው ሰዎች ቀደም ብለን የጠቀስናቸውን [አገልጋዮች] ቢሾሙ ምን ያስደንቃል? ብፁዕ ሙሴ ደግሞ «በቤቱ ሁሉ እንደ ሎሌ የታመነ» ሆኖ የተሰጡትን ትእዛዛት ሁሉ በቅዱሳት መጻሕፍት ጽፎአቸዋልና፤ ሌሎቹም ነቢያት እርሱን ተከትለው እርሱ ለሠራው ሥርዓት በአንድ ልብ መስክረዋልና። ስለ ክህነት ፉክክር በተነሣ ጊዜ፥ ነገዶቹም ያን የከበረ ስም የሚጐናጸፈው ከመካከላቸው የትኛው እንደ ሆነ እርስ በርሳቸው በተከራከሩ ጊዜ፥ እርሱ የነገዶቹን አሥራ ሁለት አለቆች እያንዳንዳቸው የነገዳቸው ስም የተጻፈበትን በትራቸውን እንዲያመጡለት አዘዛቸው። እርሱም ወስዶ [በአንድነት] አሰራቸው፤ በነገዶቹም አለቆች ቀለበቶች አተማቸው፤ በምስክሩም ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ገበታ ላይ አኖራቸው። የድንኳኑንም ደጆች ዘግቶ በትሮቹን እንዳተመ እንዲሁ መክፈቻዎቹን አተመ፤ እንዲህም አላቸው፦ ወንድሞች ሆይ፥ በትሩ የሚያብብለትን ነገድ፥ እርሱን እግዚአብሔር የክህነትን ሥራ እንዲፈጽምና እንዲያገለግለው መርጦታል። በነጋም ጊዜ እስራኤልን ሁሉ፥ ስድስት መቶ ሺህ ሰዎችን፥ ሰበሰበ፤ ማኅተሞቹንም ለነገዶቹ አለቆች አሳየ፤ የምስክሩንም ድንኳን ከፍቶ በትሮቹን አወጣ። የአሮንም በትር ያበበ ብቻ ሳይሆን ፍሬም ያፈራ ሆኖ ተገኘ። ወዳጆች ሆይ፥ ምን ይመስላችኋል? ሙሴ ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ አላወቀምን? በእርግጥ ያውቅ ነበር፤ ነገር ግን በእስራኤል መካከል ዓመፅ እንዳይነሣ፥ የእውነተኛውና የብቻውም አምላክ ስም እንዲከበር እንዲህ አደረገ፤ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።
ምዕራፍ 43 ተጠናቋል
ሙሴ ስለ ክህነት ክብር የተነሣውን ክርክር ጸጥ አሰኘ