ምዕራፍ 34 · 1 ደቂቃ ንባብ · 1 ደቂቃ ማዳመጥ
በእግዚአብሔር ዘንድ የመልካም ሥራ ዋጋ ታላቅ ነው
ደግ ባሪያ የድካሙን እንጀራ በድፍረት ይቀበላል፤ ሰነፉና ሀኬተኛው ግን ቀጣሪውን ቀና ብሎ ሊያየው አይችልም። ስለዚህ መልካም በማድረግ ፈጣኖች ልንሆን ይገባናል፤ ሁሉ ከእርሱ ነውና። እርሱም እንዲህ ብሎ አስቀድሞ ያስጠነቅቀናል፦ «እነሆ፥ ጌታ [ይመጣል]፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው ሊከፍል ዋጋው በፊቱ ነው።» ስለዚህ በማናቸውም መልካም ሥራ ሰነፎችና ሀኬተኞች እንዳንሆን ይህን በሙሉ ልባችን እንድንጠብቅ ይመክረናል። ትምክህታችንና መታመናችን በእርሱ ይሁን። ለፈቃዱ እንገዛ። የመላእክቱን ሠራዊት ሁሉ፣ ፈቃዱን ለማገልገል ዘወትር ተዘጋጅተው እንዴት እንደሚቆሙ እናስብ። መጽሐፍ እንዲህ ይላልና፦ «አእላፋት ጊዜ አእላፋት በዙሪያው ቆመው ነበር፥ ሺህ ጊዜ ሺህም ያገለግሉት ነበር፤ እንዲህም ብለው ጮኹ፦ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ [ነው] ጌታ ፀባዖት፤ ፍጥረት ሁሉ ክብሩን ሞልቶአል።» እንግዲህ እኛም በሕሊናችን በስምምነት በአንድነት ተሰብስበን፣ የታላቁንና የክቡሩን የተስፋ ቃሉን ተካፋዮች እንድንሆን እንደ አንድ አፍ ሆነን አጥብቀን ወደ እርሱ እንጩኽ። [መጽሐፍ] እንዲህ ይላልና፦ «ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው፥ እርሱ ለሚጠብቁት ያዘጋጀው ነው።»
ምዕራፍ 34 ተጠናቋል
በእግዚአብሔር ዘንድ የመልካም ሥራ ዋጋ ታላቅ ነው