የቄስ ቻርልስ ጂ. ፊኒ ማስታወሻዎች
በኦበርን፥ በባፋሎ፥ በፕሮቪደንስና በቦስተን የተካሄዱ መነቃቃቶች

ምዕራፍ 22 · 21 ደቂቃ ንባብ · 27 ደቂቃ ማዳመጥ

በኦበርን፥ በባፋሎ፥ በፕሮቪደንስና በቦስተን የተካሄዱ መነቃቃቶች

በሮቼስተር በቆየሁበት ጊዜ የመጨረሻ ክፍል ጤንነቴ ደካማ ነበር። ከአቅሜ በላይ ደክሜ ነበር፤ አንዳንድ ታዋቂ ሐኪሞችም ከእንግዲህ ወዲያ ፈጽሞ እንደማልሰብክ ወስነው እንደ ነበር ሰማሁ። በዚያን ጊዜ በሮቼስተር የነበረኝ አገልግሎት ለስድስት ወር ቀጥሎ ነበር፤ ወደ መገባደጃውም አካባቢ የኢታካው ቄስ ዶ/ር ዊዝነር ወርደው ሥራውን እየተመለከቱና እያገዙ ጥቂት ጊዜ አሳለፉ። በዚያው መካከል ወደ ብዙ የአገልግሎት መስኮች ተጋበዝሁ፤ ከእነዚህም መካከል በስኬኔክታዲ የሚገኘው የዩኒየን ኮሌጅ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኖት መጥቼ ከእርሳቸው ጋር እንዳገለግልና ቢቻል የብዙ ተማሪዎቻቸውን መለወጥ እንዳስገኝ አጥብቀው ለመኑኝ። ልመናቸውንም ለመቀበል ቈረጥሁ።

በ1831 የጸደይ ወራት፥ መንገዱ እጅግ መጥፎ በነበረበት ጊዜ፥ ከዶ/ር ዊዝነርና ከጆሳያ ቢሰል ጋር በመንገደኞች ሠረገላ ተነሣሁ። መንገዱ ለእነርሱ እጅግ አደገኛ፥ ጒዞውም እጅግ አድካሚ ስለ ነበረ ሚስቴንና ልጆቼን ለጊዜው በሮቼስተር ተውኋቸው። ጄኒቫ በደረስን ጊዜ ዶ/ር ዊዝነር ጥቂት እንዳርፍ ከእርሳቸው ጋር ወደ ቤታቸው እንድሄድ አጥብቀው ጠየቁኝ። እኔ ግን እምቢ አልሁ፤ ሥራዬን መቀጠል እንዳለብኝም ነገርኋቸው። እንድሄድ እጅግ አድርገው ገፋፉኝ፤ በመጨረሻም የሮቼስተር ሐኪሞች ልሞት ስለ ሆነ ከእርሳቸው ጋር ወደ ቤታቸው ይዘውኝ እንዲሄዱ እንደ ነገሯቸው ነገሩኝ፤ የሳንባ ነቀርሳ ስላለብኝና ጥቂት ጊዜ ብቻ ልኖር ስለምችል ከእንግዲህ በመነቃቃቶች ፈጽሞ እንደማላገለግል ነግረዋቸው ነበር። እኔም ይህ ከዚህ በፊት እንደ ተነገረኝ፥ ነገር ግን ስሕተት እንደ ሆነ መለስሁላቸው፤ ሐኪሞቹ ሁኔታዬን እንዳልተረዱት፥ እኔ የደከምሁ ብቻ እንደ ሆንሁና ጥቂት ዕረፍት እንደምታበረታኝ ነገርኋቸው።

ዶ/ር ዊዝነርም በመጨረሻ ውትወታቸውን ተዉ፤ እኔም በሠረገላው ወደ ኦበርን አለፍሁ። መንገዱ እጅግ መጥፎ ከመሆኑ የተነሣ አንዳንድ ጊዜ በሰዓት ከሁለት ማይል በላይ መጓዝ አንችልም ነበር፤ ከሮቼስተር ወደ ኦበርን ለመድረስም ሁለት ሦስት ቀን ፈጅቶብን ነበር። በኦበርን ብዙ የምወዳቸው ወዳጆች ስለ ነበሩኝና እጅግ ደክሜ ስለ ነበር፥ በዚያ ቆይቼ እስከሚቀጥለው ሠረገላ ድረስ ለማረፍ ወሰንሁ። እስከ ስኬኔክታዲ ድረስ ሙሉውን ዋጋ ከፍዬ ነበር፤ ሆኖም ብፈልግ ለአንድ ወይም ለብዙ ቀናት መቆየት እችል ነበር። የዋና ዳኛ ኤስ—— ልጅ በሆኑት በአቶ ቲ—— ኤስ—— ቤት ዐረፍሁ። እርሳቸው ቅን ክርስቲያን፥ ደግሞም እጅግ የምወዳቸው ወዳጄ ነበሩ፤ ስለዚህ በሆቴል ከማረፍ ይልቅ ወደ ቤታቸው ሄጄ እስከሚቀጥለው ሠረገላ ድረስ በዚያ ለማረፍ ወሰንሁ።

በአቶ ኤስ—— ቤት በሰላም ካደርሁ በኋላ በማለዳ ተነሥቼ በቀኑ መጀመሪያ ክፍል ይደርስ የነበረውን ሠረገላ ለመሳፈር እየተዘጋጀሁ ሳለ፥ አንድ ሰው እንድቆይ የሚጠይቅ ልመና ይዞ ገባ፤ ልመናው በጽሑፍ የቀረበ ነበር፤ ቀደም ብዬ እንደ ተናገርሁት በ1826 በዚያ ስፍራ የነበረውን መነቃቃት በተቃወሙት በዚያ ብዙ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች ስብስብ የተፈረመ ነበር። እነዚህ ሰዎች በቀደመው ጊዜ መነቃቃቱን ተቃውመው ነበር፤ ተቃውሟቸውንም ከዶ/ር ላንሲንግ ጉባኤ ተለይተው አዲስ ጉባኤ እስከ ማቋቋም ድረስ አድርሰውት ነበር። በዚያው መካከል ዶ/ር ላንሲንግ ወደ ሌላ የአገልግሎት መስክ ተጠርተው ነበር፤ የቨርሞንቱ ቄስ ጆሳያ ሆፕኪንስም የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን እረኛ ሆነው ተሹመው ነበር። የጠቀስሁት ወረቀት ቆሜ ስለ መዳናቸው እንዳገለግል የሚማጸን ልባዊ ልመና የያዘ ነበር፤ የፈረሙትም ረጅም ዝርዝር ያልተለወጡ ሰዎች ነበሩ፤ አብዛኞቻቸውም በከተማዪቱ ካሉት እጅግ ታዋቂ ነዋሪዎች መካከል ነበሩ። ይህ እጅግ አስደነቀኝ። በዚህ ወረቀት በአገልግሎቴ ላይ ቀድሞ ያደረጉትን ተቃውሞ ጠቅሰው፥ ያን ቸል ብዬ እንድቆይና ወንጌልን እንድሰብክላቸው ለመኑኝ።

ይህ ልመና የመጣው ከእረኛው ወይም ከቤተ ክርስቲያኑ ሳይሆን ቀድሞ ሥራውን በመቃወም ግንባር ቀደም ከነበሩት ሰዎች ነበር። ነገር ግን እረኛውና የቤተ ክርስቲያኑ አባላት እንድቆይና እንድሰብክ፥ የእነዚህንም ሰዎች ልመና እንድቀበል በሙሉ ተጽዕኖአቸው ገፋፉኝ። በእነዚያ ሰዎች አቋም ለውጥ እኔ እንደ ተደነቅሁ እነርሱም እንዲሁ የተደነቁ ይመስሉ ነበር። ወደ ክፍሌ ሄጄ ጉዳዩን በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋሁት፤ ምን ማድረግ እንዳለብኝም ብዙም ሳልቆይ ወሰንሁ። ለእረኛውና ለሽማግሌዎቹ እጅግ እንደ ደከምሁና ልዝል ጥቂት እንደ ቀረኝ፥ ነገር ግን በተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎች እንደምቆይ ነገርኋቸው። በሰንበት ሁለት ጊዜ፥ በሳምንቱ ውስጥም ሁለት ምሽቶች እሰብካለሁ፤ ነገር ግን የቀረውን ሥራ ሁሉ እነርሱ ራሳቸው በእጃቸው መውሰድ አለባቸው፤ ከምሰብክባቸው ስብሰባዎች በቀር በሌላ ስብሰባ እገኛለሁ ብለው መጠበቅ የለባቸውም፤ ጠያቂዎችን የማስተማሩንና የጸሎቱንና የሌሎቹን ስብሰባዎች የመምራቱን ሥራ በራሳቸው ላይ መውሰድ አለባቸው። ከኃጢአተኞች ጋር እንዴት መሥራት እንዳለባቸው እንደሚያውቁ ስለማውቅ ያን የሥራውን ክፍል እንዲፈጽሙ በሚገባ ልተማመንባቸው እችል ነበር። ከዚህም በላይ እነርሱም ሆኑ ሕዝባቸው ከአስከፊ ሁኔታ በቀር በማረፊያዬ እንዳይጎበኙኝ ቅድመ ሁኔታ አደረግሁ፤ ምክንያቱም ዕረፍት እንዳገኝ ከእሑዶች በቀር ቀኖቼ፥ ደግሞም ከምሰብክባቸው ምሽቶች በቀር ምሽቶቼ ለእኔ መተው ነበረባቸው። በሰንበት ሦስት የስብከት አገልግሎቶች ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱን አቶ ሆፕኪንስ ይሰብኩበት ነበር። እኔ በየሰንበቱ ጠዋትና ማታ፥ እርሳቸው ደግሞ ከቀትር በኋላ ይሰብኩ ነበር ብዬ አስባለሁ።

ቃሉ ወዲያውኑ ሠራ። በሰበክሁበት በመጀመሪያው ወይም በሁለተኛው የሰንበት ምሽት ቃሉ እጅግ በኃይል ልባቸውን እየያዘ መሆኑን አየሁ፤ ስለዚህ በመጨረሻ ውሳኔ ያደረጉ ሰዎች ወደ ፊት ወጥተው በአደባባይ ኃጢአታቸውን እንዲክዱና ራሳቸውን ለክርስቶስ እንዲሰጡ ጠራሁ። እኔን እጅግ ያስደነቀኝ፥ እረኛውንና ብዙዎቹን የቤተ ክርስቲያን አባላት ደግሞ ከዚያ በላይ ያስደነቃቸው፥ ወደ ፊት ሲወጣና መንገዱን ሲመራ ያየሁት የመጀመሪያው ሰው ቀድሞ የነበረውን መነቃቃት በመቃወም ግንባር ቀደም የነበረውና ከማንም ሰው ይበልጥ ተጽዕኖ ያሳደረው ሰው መሆኑ ነበር። እርሱም ሳያመነታ ወደ ፊት ወጣ፤ ያን ወረቀት ከፈረሙት ሰዎችም ብዙዎቹ ተከተሉት፤ በዚያም ምሽት በከተማዪቱ ሁሉ አጠቃላይ መነሣሣትን እስኪያስከትል ድረስ ታላቅ መገለጥ ሆነ።

ስለ አቶ ክሌሪ፥ በሮቼስተር ስለ ነበረው ስለዚያ ጸሎተኛ ሰው፥ ቀደም ብዬ ተናግሬአለሁ። እርሱ በኦበርን የሚኖር ሐኪም ወንድም ነበረው። በዚህ ጊዜ በኦበርን በነበርሁበት በሁለተኛው ሰንበት ይመስለኛል፥ በጉባኤው መካከል የዚህን የአቶ ክሌሪን ጭምት ፊት አየሁ። በጸሎት ጭንቅ የተዋጠ ይመስል ነበር። በሚገባ ስለማውቀውና በእርሱ ላይ ያደረውን ታላቁን የእግዚአብሔር ስጦታ፥ የጸሎትን መንፈስ፥ ስለማውቅ በዚያ በማየቴ እጅግ ደስ አለኝ። እርሱም ከወንድሙ ከዶክተሩ ጋር በአንድ ወንበር ተቀምጦ ነበር፤ ዶክተሩም እምነቱን የሚመሰክር ክርስቲያን ነበር፤ ነገር ግን ወንድሙ አቤል በእግዚአብሔር ዘንድ ስለ ነበረው ታላቅ ኃይል በልምድ ምንም አያውቅም ነበር ብዬ እገምታለሁ።

በእረፍቱ ጊዜ ከመስበኪያ መድረኩ እንደ ወረድሁ አቶ ክሌሪ ከወንድሙ ጋር በመድረኩ ደረጃ ላይ አገኙኝ፤ ዶክተሩም የእረፍቱን ጊዜ በቤቱ እንዳሳልፍና ጥቂት እንድመገብ ወደ ቤቱ ጋበዘኝ። እንዲሁም አደረግሁ።

ቤቱ ከደረስን በኋላ ብዙም ሳንቆይ ወደ ምሳ ማዕድ ተጠራን። በማዕዱ ዙሪያ ተሰበሰብን፤ ዶ/ር ክሌሪም ወደ ወንድሙ ዞሮ፥ «ወንድም አቤል፥ እባክህ ምግቡን ትባርክልናለህን?» አለው። ወንድም አቤልም ራሱን ዝቅ አድርጎ ምግቡን በሚሰማ ድምፅ መባረክ ጀመረ። አንድ ወይም ሁለት ዓረፍተ ነገር ብቻ እንደ ተናገረ ድንገት ተሰበረ፤ ፈጥኖ ከማዕዱ ወደ ኋላ ተመልሶ ወደ መኝታ ክፍሉ ሸሸ። ዶክተሩም ድንገት የታመመ መስሎት ተነሥቶ ተከተለው። ከጥቂት ጊዜ በኋላም ወርዶ፥ «አቶ ፊኒ፥ ወንድሜ አቤል ሊያይህ ይፈልጋል» አለ። እኔም፥ «ምን ሆኖ ነው?» አልሁት። እርሱም፥ «አላውቅም፤ እርሱ ግን አንተ ታውቃለህ ይላል። በታላቅ ጭንቅ ውስጥ ያለ ይመስላል፤ ነገር ግን የአእምሮው ሁኔታ ይመስለኛል» አለኝ። እኔም ወዲያውኑ ተረዳሁ፤ ወደ ክፍሉም ሄድሁ። በአልጋው ላይ ተኝቶ ያቃስት ነበር፤ መንፈስ ስለ እርሱና በእርሱ ውስጥ በማይነገር መቃተት ይማልድ ነበር። ገና ወደ ክፍሉ እንደ ገባሁ፥ «ወንድም ፊኒ፥ ጸልይ» ለማለት ቻለ። ተንበርክኬም ነፍሱን ስለ ኃጢአተኞች መለወጥ በጸሎት በመምራት በጸሎቱ አገዝሁት። ጭንቁ እስኪያልፍ ድረስ መጸለዬን ቀጠልሁ፤ ከዚያም ወደ ምሳ ማዕዱ ተመለስሁ።

ይህ የእግዚአብሔር ድምፅ እንደ ሆነ ተረዳሁ። የጸሎት መንፈስ በእርሱ ላይ እንዳለ አየሁ፤ ተጽዕኖውም በራሴ ላይ ተሰማኝ፤ ሥራውም በኃይል እንደሚቀጥል እርግጠኛ ሆንሁ። እንዲሁም ሆነ። ረጅም የስሞች ዝርዝር ሆነው ያን ወረቀት ከፈረሙት ሰዎች እያንዳንዳቸው በዚያ መነቃቃት ወቅት እንደ ተለወጡ አምናለሁ፤ ነገር ግን ፈጽሞ እርግጠኛ አይደለሁም።

ከጥቂት ዓመታት በፊት የኦበርኑ ዶ/ር ኤስ—— ያን ወረቀት ጠብቄ እንደ ሆነ ለማወቅ ጻፉልኝ፤ እንደ ተናገሩትም የፈረሙት ሰዎች ሁሉ በዚያን ጊዜ ተለውጠው እንደ ሆነ ለማረጋገጥ ፈልገው ነበር። ወረቀቱ የት እንደ ተቀመጠ ጠፍቶብኛል፤ ምናልባት ከብዙ ወረቀቶቼና ደብዳቤዎቼ መካከል ሊኖርና አንድ ቀን ሊገኝ ቢችልም፥ በዚያን ጊዜ ግን ለጥያቄአቸው መልስ መስጠት አልቻልሁም።

በዚህ ጊዜ በኦበርን ስድስት ሰንበታት ቆየሁ፤ እንደ ተናገርሁትም በሰንበት ሁለት ጊዜ፥ በሳምንቱ ውስጥም ሁለት ጊዜ እሰብክ ነበር፤ የቀረውን ሥራ ሁሉ ለእረኛውና ለቤተ ክርስቲያኑ አባላት ተውሁ። እዚህም እንደ ሮቼስተር በዚህ ጊዜ በግልጽ የሚታይ ተቃውሞ ጥቂት ነበር ወይም ምንም አልነበረም። አገልጋዮችና ክርስቲያኖች ሥራውን በእጃቸው ያዙ፤ ለመሥራት ልብ የነበረው ሁሉ የሚሠራው በቂ ሥራ፥ በድካሙም መልካም ፍሬ አገኘ።

እረኛው በኋላ እንደ ነገረኝ፥ እኔ በዚያ በነበርሁባቸው ስድስት ሳምንታት አምስት መቶ ነፍሳት እንደ ተለወጡ ተረድቶ ነበር። የተጠቀምንባቸው መንገዶች በሮቼስተር የተጠቀምንባቸው ያው መንገዶች ነበሩ። ይህ መነቃቃት ከሮቼስተር ማዕከል ተነሥቶ ኦበርን የደረሰ የመለኮታዊ ኃይል ማዕበል ብቻ ይመስል ነበር፤ ከዚያ ማዕከል በምድሪቱ ርዝመትና ስፋት ሁሉ እንዲህ ያለ ብርቱ ተጽዕኖ ወጥቶ ነበርና።

እዚህ የነበረኝ አገልግሎት ሊያበቃ ሲቃረብ፥ ያን ከተማ እንድጎበኝ ልባዊ ልመና የያዘ መልእክተኛ ከባፋሎ መጣ። በሮቼስተር የነበረው መነቃቃት በዙሪያው እንዳሉት ስፍራዎች ሁሉ በኦበርንም መንገድ አዘጋጅቶ ነበር፤ በባፋሎም መንገድ አዘጋጅቶ ነበር። መልእክተኛው እንደ ነገረኝ በባፋሎ ሥራው ተጀምሮ ነበር፤ ጥቂት ነፍሳትም ተስፋ በሚሰጥ ሁኔታ ተለውጠው ነበር፤ ነገር ግን ሌሎች መንገዶች ሥራ ላይ መዋል እንዳለባቸው ተሰምቷቸው ነበር፤ እጅግም አድርገው ስለ ለመኑኝ ከኦበርን በሮቼስተር በኩል ወደ ኋላ ተመልሼ ወደ ባፋሎ ሄድሁ። በባፋሎ ያሳለፍሁት አንድ ወር ገደማ ብቻ ይመስለኛል፤ በዚያም ጊዜ ብዙ ሰዎች ተስፋ በሚሰጥ ሁኔታ ተለወጡ።

በባፋሎ የነበረው ሥራ እንደ ኦበርንና እንደ ሮቼስተር በአብዛኛው ይበልጥ ተሰሚነት ባላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሠራ። በዚያን ጊዜ ጠበቃ የነበሩት ቄስ ዶ/ር ሎርድ በዚያን ጊዜ የተለወጡ ይመስለኛል፤ ደግሞም የባፋሎው የቄስ ዶ/ር ኤች—— አባት አቶ ኤች——። ከእርሳቸው መለወጥ ጋር የተያያዙ ፈጽሞ ያልረሳኋቸው ብዙ ሁኔታዎች ነበሩ። እርሳቸው በባፋሎ ከነበሩት እጅግ ሀብታምና ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች አንዱ ነበሩ፤ በውጭ ሲታዩ መልካም ሥነ ምግባር፥ ንጹሕ ስምና እንደ ዜጋ ከፍ ያለ ማዕረግ ያላቸው ሰው ነበሩ፤ ነገር ግን ንስሐ ያልገቡ ኃጢአተኛ ነበሩ። ሚስታቸው ክርስቲያን ሴት ነበሩ፤ ለረጅም ጊዜም ስለ እርሳቸው ሲጸልዩና እንደሚለወጡ ተስፋ ሲያደርጉ ነበር። ነገር ግን እኔ በዚያ መስበክ በጀመርሁና የኃጢአተኛው «አልችልም» ማለት «አልፈልግም» ማለት እንደ ሆነ፥ መወገድ ያለበት ችግር የኃጢአተኞች በፈቃድ የሚሠሩት ክፋት እንደ ሆነ፥ ክርስቲያን ለመሆንም ፈጽሞ ፈቃደኞች እንዳልሆኑ አጥብቄ በተናገርሁ ጊዜ፥ አቶ ኤች—— እንዲህ ያለውን ትምህርት በቈራጥነት ተቃወሙ። ክርስቲያን ለመሆን ፈቃደኛ መሆናቸውንና ለረጅም ጊዜም ፈቃደኛ እንደ ነበሩ በልባቸው ያውቁ ስለ ነበር፥ ትምህርቱ በእርሳቸው ረገድ ሐሰት እንደ ሆነ አጥብቀው ተከራከሩ።

ሚስታቸው የነበሩበትን አቋም ስለ ነገሩኝ አልራራሁላቸውም፤ ነገር ግን ከቀን ወደ ቀን ከመሸሸጊያዎቻቸው አሳደድኋቸው፤ ተቃውሞአቸውን ሁሉ መለስሁ፤ ምክንያቶቻቸውንም ሁሉ ተጋፈጥሁ። እርሳቸውም ይበልጥ እየተቈጡ ሄዱ። ብርቱ ፈቃድ የነበራቸው ሰው ነበሩ፤ እንዲህ ያለውን ትምህርት እንደማያምኑና እንደማያምኑበትም አወጁ። ትምህርቱን በመቃወም እጅግ ብዙ ከመናገራቸው የተነሣ፥ ሥራውን ከመቃወማቸው በቀር ምንም ዓይነት ኅብረት ያልነበራቸውን አንዳንድ ሰዎች በዙሪያቸው ሳቡ። እኔ ግን በእያንዳንዱ ስብከቴ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ክርስቲያን ለመሆን ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ይዤ ከመጫን ወደ ኋላ አላልሁም።

ከተለወጡ በኋላ አንዳንድ ዘባቾች ከእርሳቸው ጀርባ ተሸሽገው እንደ ነበር ባወቁ ጊዜ እንደ ደነገጡና እንዳፈሩ ነገሩኝ። አንድ ምሽት፥ አሉ፥ ከአንድ የታወቀ ዘባች ጋር በመተላለፊያው ትይዩ ተቀምጠው ነበር። በሌሎች ጉዳዮች ምንም ኅብረት ያልነበራቸው ይህ ሰው እኔ እየሰበክሁ ሳለ ደጋግሞ ወደ እርሳቸው እየተመለከተ ፈገግ ይል እንደ ነበር፥ አቶ ኤች—— መነቃቃቱን ከመቃወማቸው ጋር መተባበሩን በግልጽ ያሳይ እንደ ነበር ነገሩኝ። ይህንም ባስተዋሉ ጊዜ ልባቸው በቍጣ እንደ ተነሣ፥ በልባቸውም፥ «ከዚህ ዓይነት ሰዎች ጋር አልተባበርም፤ ከእነርሱ ጋር ምንም ግንኙነት አይኖረኝም» እንዳሉ ነገሩኝ።

ሆኖም በዚያው ሌሊት በስብከቴ መጨረሻ የኃጢአተኞችን ሕሊና እጅግ አጥብቄ ስለ ጫንሁና በፈቃዳቸው የሚያደርጉትን ተቃውሞ ትተው ወደ ክርስቶስ እንዲመጡ እጅግ ብርቱ ጥሪ ስላቀረብሁ፥ ራሳቸውን መቈጣጠር አቃታቸው። ስብሰባው እንዳበቃ፥ ከልማዳቸው ፈጽሞ በተቃራኒ፥ ገና ከቤቱ ሳይወጡ መቃወምና በተነገረው ላይ መናገር ጀመሩ። መተላለፊያዎቹ ሞልተው ነበር፤ ሰዎችም በዙሪያቸው በየአቅጣጫው ተጨናንቀው ነበር። እንዲያውም ሚስታቸው እንደ ነገሩኝ፥ አንድ የስድብ ቃል ተናገሩ፤ ይህም ሚስታቸውን እጅግ አወካቸው፤ በተቃውሞአቸው የእግዚአብሔርን መንፈስ አሳዝነው ሊያርቁትና ነፍሳቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ ተሰምቷቸው ነበርና።

በዚያች ሌሊት እንቅልፍ አልወሰዳቸውም። አእምሮአቸው እጅግ ከመታወኩ የተነሣ ገና ብርሃን እንደ ታየ ተነሥተው ከቤታቸው ወጡ፤ በዚያን ጊዜ ጥሻ ወደ ነበረበት፥ «ሃይድሮሊክሱ» ብለው የሚጠሩት የውኃ መሣሪያ ወደ ነበራቸው ስፍራ አጠገብ፥ ራቅ ያለ ቦታ ሄዱ። በዚያም በጥሻው ውስጥ ለመጸለይ ተንበረከኩ። በኃጢአታቸው ስሜትና ወዲያውኑ ከእግዚአብሔር ጋር የመታረቅ አስፈላጊነት ከመጠን በላይ ስለ ተጨነቁ፥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው መናገርና ድምፃቸውንና ልባቸውን ማፍሰስ እንዲችሉ ብቻቸውን ራቅ ብለው መሄድ እንዳለባቸው በሌሊቱ ተሰምቷቸው እንደ ነበር ነገሩኝ። ነገር ግን ተንበርክከው ለመጸለይ በሞከሩ ጊዜ፥ የሚያስደንቅና የሚያሳፍር ሆኖ፥ ልባቸው እንደማይጸልይ አገኙት። ቃል አልነበራቸውም፤ በቃል ሊገልጡት የሚችሉት ምንም ምኞት አልነበራቸውም። ልባቸው እንደ እብነ በረድ የደነደነ፥ በጉዳዩም ላይ ትንሽ ስሜት እንኳ የሌላቸው መስሎ እንደ ታያቸው ነገሩኝ። ተስፋ ቈርጠውና ግራ ተጋብተው በጕልበታቸው ቆሙ፤ ለመጸለይ አፋቸውን ቢከፍቱም፥ በቅንነት ሊናገሩት የሚችሉት የጸሎት ዓይነት ምንም እንደሌላቸው አገኙ።

በዚህ ሁኔታ ሳሉ የጌታን ጸሎት ሊጸልዩ እንደሚችሉ ታሰባቸው። ስለዚህ፥ «በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ» ብለው ጀመሩ። ቃሉን እንደ ተናገሩ፥ እግዚአብሔርን አባቴ ብለው በመጥራታቸው ግብዝነታቸው እንደ ወቀሳቸው ነገሩኝ። «ስምህ ይቀደስ» የሚለውን ልመና ሲጨምሩ ሊያስደነግጣቸው ምንም እንዳልቀረ ነገሩኝ። ቅኖች እንዳልሆኑ፥ ቃላቸውም የአእምሮአቸውን ሁኔታ ፈጽሞ እንደማይገልጥ አዩ። የእግዚአብሔር ስም እንዲቀደስ ግድ አልነበራቸውም። ከዚያም የሚቀጥለውን ልመና፥ «መንግሥትህ ትምጣ» የሚለውን ተናገሩ። በዚህ ጊዜ፥ አሉ፥ ሊታነቁ ምንም አልቀራቸውም። የእግዚአብሔር መንግሥት እንድትመጣ እንደማይፈልጉ፥ ይህን ማለታቸው ግብዝነት እንደ ሆነ፥ የልባቸውን ቅን ምኞት በእውነት እንደሚገልጥ አድርገውም ሊሉት እንደማይችሉ አዩ። ከዚያም «ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን» የሚለው ልመና መጣ። ልባቸው በዚያ ላይ እንደ ተነሣና ሊሉት እንዳልቻሉ ነገሩኝ። እዚህ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ፊት ለፊት ተገናኙ። ይህን ፈቃድ እንደሚቃወሙ፥ ሊቀበሉትም ፈቃደኞች እንዳልሆኑ፥ ለመለወጣቸው በመንገድ ላይ ያለው ብቸኛ እንቅፋት በፈቃዳቸው በእግዚአብሔር፥ በሕጉና በፈቃዱ ላይ የሚያደርጉት ተቃውሞ እንደ ሆነ ከቀን ወደ ቀን ተነግሯቸው ነበር። ይህን ሐሳብ ተቃውመውት፥ ተስፋ በቈረጠ ብርታትም ታግለውት ነበር። አሁን ግን እዚህ በጕልበታቸው ሆነው፥ የጌታ ጸሎት በአፋቸው ሳለ፥ ከዚያ ጥያቄ ጋር ፊት ለፊት ተገናኙ፤ የተነገራቸው እውነት እንደ ሆነ ፈጽሞ በግልጽ አዩ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሆን ፈቃደኞች እንዳልሆኑ፥ እነርሱ ራሳቸውም ያን የማያደርጉት ስላልፈለጉ እንደ ሆነ ነው።

እዚህ የዓመፃቸው ጉዳይ በሙሉ በባሕርዩና በስፋቱ እጅግ አጥብቆ በፊታቸው ስለ ቀረበ፥ ያን በፈቃዳቸው በእግዚአብሔር ላይ የሚያደርጉትን ተቃውሞ ለመተው ብርቱ ትግል እንደሚያስከፍላቸው አዩ። ከዚያም፥ አሉ፥ የፈቃዳቸውን ብርታት ሁሉ ሰብስበው፥ «ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን» ብለው ጮኹ። ፈቃዳቸው ከቃላቸው ጋር አብሮ እንደ ሄደ፥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ፥ ደግሞም የእግዚአብሔርን ፈቃድ በሙሉ እንደ ተቀበሉ፥ ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ እንደ ተገዙና ክርስቶስን በወንጌል እንደ ቀረበው እንደ ተቀበሉት ፍጹም አድርገው እንዳወቁ ነገሩኝ። ኃጢአታቸውን ተዉ፤ የእግዚአብሔርንም ፈቃድ የሕይወታቸው ሁሉን አቀፍ ሥርዓት አድርገው ተቀበሉ። የልባቸውም ቋንቋ፥ «ጌታ ሆይ፥ በፊትህ መልካም የሆነውን አድርግብኝ። ፈቃድህ በእኔ ላይ፥ በምድርም ባሉ ፍጥረታት ሁሉ ላይ በሰማይ እንደ ሆነች ትሁን» የሚል ነበር። ፈቃዳቸው እንደ ተገዛ ወዲያውኑ በነፃነት እንደ ጸለዩ፥ ልባቸውም እንደ ጎርፍ እንደ ፈሰሰ ነገሩኝ። ዓመፃቸው ሁሉ አለፈ፤ ስሜታቸውም ወደ ታላቅ ጸጥታ ረጋ፤ ጣፋጭ ሰላምም ነፍሳቸውን ሁሉ የሞላ መሰለ።

ከጕልበታቸው ተነሥተው ወደ ቤታቸው ሄዱ፤ ስለ እርሳቸው እጅግ አጥብቀው ሲጸልዩ ለነበሩት ለተጨነቁት ሚስታቸውም ጌታ ለነፍሳቸው ያደረገውን ነገሯቸው፤ በተቃውሞአቸው ፈጽመው ተሳስተው እንደ ነበር፥ ክርስቲያን ለመሆን ስላላቸው ፈቃደኝነትም ፈጽመው ተታልለው እንደ ነበር ተናዘዙ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሔርን ሥራ ለማስፋፋት ትጉ ሠራተኛ ሆኑ።

ከዚያ በኋላ የኖሩት ሕይወት የለውጡን እውነተኛነት መሰከረ፤ ጠቃሚ ክርስቲያን ሰው ሆነው ኖሩ፤ ሞቱም። ከባፋሎ በጁን ይመስለኛል፥ በዋይትስታውን ወደሚገኘው ወደ አማቴ ቤት ሄድሁ። የበጋውን ከፊል ለመዝናናትና ጤንነቴንና ብርታቴን መልሼ ለማግኘት በመጓዝ አሳለፍሁ።

በ1831 የበልግ ወራት መጀመሪያ ላይ፥ በዚያን ጊዜ «ተከታታይ ስብሰባ» ይባል የነበረውን፥ ማለትም የስብሰባዎች ቅደም ተከተልን፥ በፕሮቪደንስ እንዳካሂድ የቀረበልኝን ግብዣ ተቀበልሁ። ባብዛኛው የሠራሁት በዚያን ጊዜ ዶ/ር ዊልሰን እረኛ በነበሩበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነበር። በየምሽቱ ስብሰባ እያደረግሁና በሰንበት ሦስት ጊዜ እየሰበክሁ በዚያ ሦስት ሳምንት ያህል የቆየሁ ይመስለኛል። ጌታ መንፈሱን ወዲያውኑ በሕዝቡ ላይ አፈሰሰ፤ የጸጋውም ሥራ እጅግ በሚያስደስት ሁኔታ ተጀምሮ ወደ ፊት ገፋ። ይሁን እንጂ፥ ቆይታዬ በዚያ ስፍራ እንደዚያ ያለ ሰፊ የጸጋ ሥራ ለማስገኘት በጣም አጭር ነበር፤ እንደዚያ ያለው ሰፊ ሥራ የተከሰተው ኋላ በ1842 ሁለት ወር ያህል በዚያ ባሳለፍሁ ጊዜ ነበር፤ ዝርዝሩን በተገቢው ስፍራ እተርከዋለሁ።

በዚያን ጊዜ ብዙ አስደሳች የመለወጥ ታሪኮች ነበሩ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በዚያች ከተማ ግንባር ቀደም ክርስቲያናዊ ተጽዕኖ የነበራቸው በርካታ ሰዎችም ተለወጡ። ይህ በሴቶችም ዘንድ እውነት ነበር፤ በመካከላቸውም እጅግ አስደሳች የሆኑ ብዙ የመለወጥ ታሪኮች ተከሰቱ። የአንዲት ወጣት ሴት መለወጥ በግልጽ ትዝ ይለኛል፤ እርሱንም በአጭሩ እተርካለሁ። በሰንበት ዕለት በጉባኤው መካከል፥ በኋላ ወንድሟ እንደ ሆነ ካወቅሁት አንድ ወጣት ጋር በአንድ ወንበር ተቀምጣ የነበረች እጅግ ውብ የሆነች አንዲት ወጣት ሴት አስተውዬ ነበር። እጅግ አስተዋይና እጅግ ልባዊ ገጽታ ነበራት፤ የምናገረውንም ቃል ሁሉ በከፍተኛ ትኩረትና በጽሞና የምታዳምጥ ትመስል ነበር።

እንግዳ ሆኜ ያረፍሁት በአቶ ጆስያ ቻፒን ቤት ነበር፤ ከእርሳቸው ጋር ከቤተ ክርስቲያን ወደ ቤታቸው ስንሄድ፥ እነዚህ ወጣት ወንድምና እኅት በዚያው መንገድ ሲሄዱ አየኋቸው። ለአቶ ቻፒን አመለከትኋቸውና እነማን እንደ ሆኑ ጠየቅኋቸው። እነርሱም አቶ ኤ—— እና ወይዘሪት ኤ—— የተባሉ ወንድምና እኅት እንደ ሆኑ ነገሩኝ፤ እርሷም በፕሮቪደንስ ካሉት ልጃገረዶች ሁሉ እጅግ ውቢቱ ተደርጋ እንደምትቆጠር አከሉ። እምነቷን የምትመሰክር ክርስቲያን እንደ ሆነች ጠየቅኋቸው፤ እርሳቸውም፦ «አይደለችም» አሉ። በጥልቅ የተነካች መስላ እንደ ታየችኝ ነገርኋቸውና ሄጄ ባያት መልካም ይሆን እንደ ሆነ ጠየቅኋቸው። እርሳቸው ግን በዚህ ረገድ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ተናገሩ፤ ጊዜ ማባከን እንደሚሆን፥ ምናልባትም በደስታ ላልቀበል እንደምችል አሰቡ። እጅግ የተሞላቀቀችና የተወደሰች ልጃገረድ ስለ ሆነች፥ ዙሪያዋም እንደዚያ ያለ ስለ ነበረ፥ ስለ ነፍሷ መዳን ምናልባት ጥቂት ቁም ነገር ያለው ሐሳብ ብቻ ታስብ ይሆናል ብለው አሰቡ። ነገር ግን ተሳስተው ነበር፤ እኔ ግን የጌታ መንፈስ ከእርሷ ጋር እየታገለ ነው ብዬ ማሰቤ ትክክል ነበር።

ሄጄ አላየኋትም፤ ነገር ግን ከዚህ በኋላ ጥቂት ቀናት ቆይታ እርሷ ራሷ ልታየኝ መጣች። ወዲያውኑ ዐወቅኋት፤ ስለ ነፍሷም ሁኔታ ጠየቅኋት። እጅግ በጥልቅ ነቅታ ነበር፤ ነገር ግን እውነተኛው የኃጢአት ወቀሳዋ ገና ላይ ልደርስበት የፈለግሁትና የክርስቶስን ጽድቅ በማስተዋል በእውነት ከመቀበሏ በፊት አስፈላጊ ነው ብዬ ወዳሰብሁት ደረጃ አልበሰለም ነበር። ስለዚህ የልቧን ብልሹነት ላሳያት በመሞከር አንድ ወይም ሁለት ሰዓት አሳለፍሁ — ጉብኝቷ በእጅጉ ረዝሞ ነበርና። መጀመሪያ ላይ ከሚመረምሩት ጥያቄዎቼ ሸሸች። ነገር ግን ከእርሷ ጋር ስነጋገር የኃጢአት ወቀሳዋ እየበሰለ የሄደ ይመስል ነበር፤ እርሷም እየበለጠ በጥልቅ ቁም ነገረኛ እየሆነች ሄደች።

በእግዚአብሔር መንፈስ ተጽዕኖ ሥር የበሰለና የተሟላ የኃጢአት ወቀሳ ለማስገኘት አስፈላጊ ነው ብዬ ያሰብሁትን ከነገርኋት በኋላ፥ ቅሬታ እንደ ተሰማት በግልጽ እየታየ ተነሥታ ትታኝ ሄደች። የእግዚአብሔር መንፈስ ጉዳዮዋን እጅግ አጥብቆ ስለ ያዘው፥ የነገርኋት ነገር ከላይዋ ተራግፎ እንደማይቀር፥ ይልቁንም ላስገኘው የፈለግሁትን የኃጢአት ወቀሳ እንደሚያመጣ ተማምኜ ነበር።

ከሁለት ወይም ከሦስት ቀን በኋላ እንደ ገና ልታየኝ መጣች። በመንፈሷ እጅግ ዝቅ ብላ እንደ ነበረች ወዲያውኑ አየሁ። እንደ ገባችም ተቀመጠችና ልቧን ገልጣ አሳየችኝ። በፍጹም ግልጽነት እንዲህ አለችኝ፦ «አቶ ፊኒ፥ ከዚህ በፊት እዚህ በነበርሁ ጊዜ ጥያቄዎችዎና ያደረጉብኝ አያያዝ በጣም ጠንካራ ነበሩ ብዬ አስቤ ነበር። ነገር ግን» አለች፥ «አሁን እርስዎ እንደ ገለጹኝ ሁሉ መሆኔን አያለሁ። በእርግጥም» አለች፥ «ኩራቴና ለስሜ ያለኝ ጥንቃቄ ባይኖር ኖሮ በፕሮቪደንስ እንዳለች እንደ ማንኛዋም ክፉ ልጃገረድ ክፉ በሆንሁ ነበር። ሕይወቴ የተገታው በኩራትና ለስሜ በነበረኝ ጥንቃቄ እንጂ ለእግዚአብሔር ወይም ለሕጉ ወይም ለወንጌሉ በነበረኝ ማናቸውም አክብሮት እንዳልሆነ» አለች፥ «በግልጽ አያለሁ። እግዚአብሔር ከአሳፋሪ በደሎች ሊገታኝ ኩራቴንና ምኞቴን እንደ ተጠቀመበት አያለሁ። ተሞላቅቄና ተወድሼ ኖሬአለሁ፤ በክብሬም ላይ ቆሜአለሁ፤ ስሜንም የጠበቅሁት ፍጹም ከራስ ወዳድነት በመነጨ ምክንያት ነው።» በራሷ ፈቃድ ቀጠለች፤ ሁሉን አምና ተናዘዘች፤ የኃጢአት ወቀሳዋም የተሟላና ጸንቶ የሚኖር መሆኑን አሳየች። በተናገረችው ነገር ሁሉ በስሜት የተቀሰቀሰች ሳትሆን የተረጋጋችና እጅግ ማስተዋል የተሞላች ትመስል ነበር። ቢሆንም፥ ትኩስ ባሕርይ፥ ጠንካራ ፈቃድ፥ እንዲሁም ባልተለመደ ሁኔታ ሚዛኑን የጠበቀና የሠለጠነ አእምሮ እንደ ነበራት ግልጽ ነበር።

ለተወሰነ ጊዜ ከእርሷ ጋር ከተነጋገርሁና የቻልሁትን ያህል የተሟላ ትምህርት ከሰጠኋት በኋላ፥ በጌታ ፊት ለጸሎት ተንበረከክን፤ እርሷም ሰው ሊያየው በሚችለው ሁሉ ራሷን ያለ አንዳች ገደብ ለክርስቶስ ሰጠች። በዚያን ጊዜ የነበረችበት የአእምሮ ሁኔታ ዓለምን መካድ ቀላል እንዲሆንላት ያደረገ ይመስል ነበር። ዘወትር እጅግ የምትማርክ ክርስቲያን ሆና ኖራለች። ከተለወጠች ብዙ ዓመታት ሳይቆዩ በኒው ዮርክ ከተማ ለሚኖር አንድ ባለጠጋ ሰው ተዳረች። ለበርካታ ዓመታት ከእርሷ ጋር በቀጥታ አልተጻጻፍንም። ባሏ እኔ የተለየ ትውውቅ ወደሌለኝ የማኅበረሰብ ክበብ ወሰዳት፤ እርሱም እስኪሞት ድረስ ከእርሷ ጋር የነበረኝን ትውውቅ አላደስሁም። ከዚያ ወዲህ ግን ከእርሷ ጋር ብዙ ክርስቲያናዊ ደብዳቤ ተጻጽፌአለሁ፤ ለሃይማኖታዊ ሕይወቷም ታላቅ ትኩረት መስጠቴን ፈጽሞ አላቋረጥሁም። ይህን ታሪክ የጠቀስሁት የእግዚአብሔር ጸጋ በዓለም መማረኪያዎች ላይ ያገኘው አስደናቂ ድል እንደ ሆነ ሁልጊዜ ስለ ቈጠርሁት ነው። የዓለም መማረኪያ ሁሉ በከበባት እንደዚህ ባለ ሁኔታ እንኳ የእግዚአብሔር ጸጋ ከዓለም ይልቅ በረታ።

በፕሮቪደንስ ሳለሁ፥ ወደ ቦስተን የመሄዴ ጉዳይ በዚያች ከተማ በሚገኙት የተለያዩ የኮንግሪጌሽናል አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮችና ዲያቆናት መካከል ይነሣ ነበር። እኔ ራሴ በዚያ የሚያደርጉትን አላወቅሁም ነበር፤ ነገር ግን በዚያን ጊዜ የኦልድ ሳውዝ ቤተ ክርስቲያን እረኛ የነበሩት ዶ/ር ዊዝነር ወደ ፕሮቪደንስ መጥተው ስብሰባዎቻችንን ተካፈሉ። በኋላ እንደ ተረዳሁት፥ «ምድሪቱን ሰልለው ወሬ እንዲያመጡ» በአገልጋዮቹ የተላኩ ነበሩ። ከእርሳቸው ጋር ብዙ ጊዜ ተነጋገርሁ፤ በፕሮቪደንስ ባዩትና በሰሙትም ነገር ወደ ቅንዓት የተቃረበ ፍላጎት አሳዩ። እርሳቸው በዚያ በነበሩበት ጊዜ አካባቢ እጅግ አስገራሚ የሆኑ አንዳንድ የመለወጥ ታሪኮች ተከሰቱ።

በፕሮቪደንስ የነበረው ሥራ እምነታቸውን የሚመሰክሩ ክርስቲያኖችን በሚመለከት ረገድ ለየት ያለ የመመርመር ባሕርይ ነበረው። የቆዩ ተስፋዎች እጅግ ተናወጡ፤ በተለያዩት አብያተ ክርስቲያናትም በደረቁ አጥንቶች መካከል ታላቅ መናወጥ ሆነ። ከአብያተ ክርስቲያናቱ የአንዱ ዲያቆን በአንድ አጋጣሚ እጅግ ከመመርመሩ የተነሣ፥ ከመስበኪያ መድረኩ ስወርድ እንዲህ አለኝ፦ «አቶ ፊኒ፥ በፕሮቪደንስ አሥር እውነተኛ ክርስቲያኖች ያሉ አይመስለኝም። ሁላችንም ተሳስተናል» አለ፤ «ተታለናል።» ዶ/ር ዊዝነር ሥራው እውነተኛ እንደ ሆነ፥ ለጊዜውም ሰፊ እንደ ነበረ፥ የሚያሳዝኑ ተጽዕኖዎች ወይም ውጤቶች እንዳሉ የሚያመለክት አንዳችም ነገር እንዳልነበረ ፈጽመው ያመኑ ይመስለኛል።

ዶ/ር ዊዝነር ወደ ቦስተን ከተመለሱ በኋላ፥ ወደዚያች ከተማ መጥቼ እንዳገለግል ከኮንግሪጌሽናል አገልጋዮችና አብያተ ክርስቲያናት ብዙም ሳይቆይ ጥያቄ ደረሰኝ። በዚያን ጊዜ ዶ/ር ላይማን ቢቸር የቦውዶይን ስትሪት ቤተ ክርስቲያን እረኛ ነበሩ፤ ልጃቸው ኤድዋርድ ቢቸር በፓርክ ስትሪት እረኛ ወይም ቋሚ ተተኪ አገልጋይ ነበሩ፤ አቶ ግሪን የተባሉ ሰው የኤሴክስ ስትሪት ቤተ ክርስቲያን እረኛ ነበሩ፤ ነገር ግን ለጤንነታቸው ሲሉ ወደ አውሮፓ ሄደው ስለ ነበር፥ ያ ቤተ ክርስቲያን በዚያን ጊዜ ምንም ቋሚ ተተኪ አገልጋይ አልነበረውም። ዶ/ር ፌይ በቻርልስታውን የሚገኘው የኮንግሪጌሽናል ቤተ ክርስቲያን እረኛ ነበሩ፤ ዶ/ር ጄንክስም በግሪን ስትሪት የሚገኘው የኮንግሪጌሽናል ቤተ ክርስቲያን እረኛ ነበሩ። በዚያን ጊዜ የሌሎቹ አብያተ ክርስቲያናት እረኞች እነማን እንደ ነበሩ ትዝ አይለኝም።

ሥራዬን የጀመርሁት በሰንበት በተለያዩት አብያተ ክርስቲያናት እየተዘዋወርሁ በመስበክ ነበር፤ በሳምንቱ ምሽቶች ደግሞ በፓርክ ስትሪት እሰብክ ነበር። የእግዚአብሔር ቃል ሥራውን እየሠራ እንደ ሆነና ትኩረቱም ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ እንደ ሄደ ብዙም ሳይቆይ አየሁ። ነገር ግን እምነታቸውን በሚመሰክሩ ክርስቲያኖች መካከል ታላቅ መመርመር እንደሚያስፈልግ ደግሞ ተረዳሁ። በምዕራቡና በኒው ዮርክ ከተማ በነበሩት መነቃቃቶች ውስጥ ሰፍኖ የነበረውን የሚመስል የጸሎት መንፈስ በመካከላቸው እንዳለ ማወቅ አልቻልሁም። በዚያ፥ በኒው ዮርክ ማየት የለመድሁትን የእምነት ነጻነትና ብርታት የማያሳይ ለየት ያለ የሃይማኖት ዓይነት ያለ ይመስል ነበር።

ስለዚህ ለክርስቲያኖች አንዳንድ የሚመረምሩ ስብከቶችን መስበክ ጀመርሁ። እንዲያውም በሳምንቱ በተወሰኑ ምሽቶች በፓርክ ስትሪት ለክርስቲያኖች ተከታታይ ስብከቶችን እንደምሰብክ በሰንበት አስታወቅሁ። ነገር ግን እነዚህ ስብከቶች ለቦስተን ክርስቲያኖች ፈጽሞ የማይጣፍጡ መሆናቸውን ብዙም ሳይቆይ ተረዳሁ። ፈጽሞ ያልለመዱት ነገር ነበር፤ በፓርክ ስትሪት የሚገኙት ሰዎች ቍጥርም እየቀነሰ ሄደ፤ በተለይም እምነታቸውን ለሚመሰክሩ ክርስቲያኖች በሰበክሁባቸው ምሽቶች። ይህ ለእኔ አዲስ ነገር ነበር። እምነታቸውን የሚመሰክሩ ክርስቲያኖች በዚያን ጊዜ በቦስተን እንዳደረጉት ከሚመረምሩ ስብከቶች ወደ ኋላ ሲያፈገፍጉ ከዚያ በፊት አይቼ አላውቅም ነበር። ነገር ግን እንደዚህ ያሉ ንግግሮችን ደጋግሜ እሰማ ነበር፦ «ይህ ነገር በእኛ በኦርቶዶክሶቹ ላይ እውነት ከሆነ ዩኒቴሪያኖቹ ምን ይላሉ?» «አቶ ፊኒ በዚህ መንገድ የሚሰብኩልን ከሆነ ዩኒቴሪያኖቹ በእኛ ላይ ድል ይነሣሉ፤ ቢያንስ ኦርቶዶክሶቹ ከዩኒቴሪያኖቹ የተሻሉ ክርስቲያኖች አይደሉም ይላሉ።» ግልጽ አቀራረቤን በመጠኑ እንዳልወደዱት፥ የሚመረምሩት ስብከቶቼም ከእነርሱ እጅግ ብዙዎቹን እንዳስደነቁ፥ እንዲያውም እንዳስቀየሙ ግልጽ ነበር። ይሁን እንጂ ሥራው ወደ ፊት ሲገፋ ይህ ሁኔታ እጅግ ተለወጠ፤ ከጥቂት ሳምንታትም በኋላ የሚመረምር ስብከትን ያዳምጡ ጀመር፤ ሊያደንቁትም በቁ።

በሌሎች ስፍራዎች ሁሉ እንዳገኘሁት በቦስተንም ከሚጠይቁ ኃጢአተኞች ጋር የሚደረግ፥ እጅግ የሚያስጨንቀኝ አያያዝ እንዳለ አገኘሁ። አንዳንድ ጊዜ ከዶ/ር ቢቸር ጋር በቤተ ክርስቲያናቸው ምድር ቤት ውስጥ የጠያቂዎች ስብሰባ እናደርግ ነበር። አንድ ምሽት ብዙ ሰው በተገኘበትና በጠያቂዎቹ መካከል ታላቅ የመመርመርና የጽሞና ስሜት በነበረበት ጊዜ፥ እንደ ልማዴ በመጨረሻ ላይ ጌታ ከእነርሱ የሚፈልገውን በትክክል ላሳያቸው የሞከርሁበትን ንግግር አደረግሁ። ዓላማዬ ራሳቸውንና ያላቸውን ሁሉ እንዲክዱ፥ ራሳቸውንና ያላቸውን ሁሉ ለክርስቶስ እንዲሰጡ ማድረግ ነበር። የራሳቸው እንዳልሆኑ፥ ነገር ግን በዋጋ እንደ ተገዙ ላሳያቸው ሞከርሁ፤ ያላቸውን ሁሉ እንዲተዉና ሁሉን የእርሱ እንደ ሆነ አድርገው ለክርስቶስ እንዲያስረክቡ የሚጠበቅባቸው በምን ስሜት እንደ ሆነም አመለከትኋቸው።

ይህን ነጥብ በተቻለኝ መጠን ግልጽ አደረግሁት፤ በጠያቂዎቹም ላይ ያሳደረው ስሜት እጅግ ጥልቅ እንደ ሆነ አየሁ። በጸሎት ለእግዚአብሔር ስናቀርባቸው እንዲንበረከኩ ልጠይቃቸው ስል፥ ዶ/ር ቢቸር ተነሥተው እንዲህ አሏቸው፦ «ሁሉን ለክርስቶስ ለመስጠት፥ ንብረታችሁንም ሁሉ፥ አትፍሩ፤ እርሱ መልሶ ይሰጣችኋልና።» ንብረታቸውን የሚተዉት በምን ስሜት እንደ ሆነና ጌታ እንዲይዙት የሚፈቅድላቸው በምን ስሜት እንደ ሆነ አንዳችም ትክክለኛ ልዩነት ሳያደርጉ፥ ጌታ መልሶ ስለሚሰጣቸው እንዲያደርጉ እንደ ተገፋፉት ሁሉን ለመተው እንዳይፈሩ በቀላሉ መከሯቸው። የተሳሳተ ስሜት እያሳደሩ እንደ ሆነ አየሁ፤ እኔም በጭንቅ ውስጥ ሆንሁ። ቃላቸው ከእውነት ፍጹም ተቃራኒ የሆነ ስሜት የሚያሳድር እንደ ሆነ አየሁ።

ንግግራቸውን ከጨረሱ በኋላ፥ በተቻለኝ መጠን በጥበብና በጥንቃቄ፥ እግዚአብሔር ንብረታቸውን እንዲተዉ በሚፈልግበት ስሜት ፈጽሞ መልሶ እንደማይሰጣቸው፥ እነርሱም እንደዚህ ያለ ሐሳብ ሊያስተናግዱ እንደማይገባቸው እንዲያስተውሉ መራኋቸው። ያልሁትን ዶ/ር ቢቸርን የምቃወም በማይመስል መንገድ ለመናገር፥ ነገር ግን እርሳቸው ያሳደሩትን ስሜት ፈጽሞ ለማረም ሞከርሁ። ጌታ ንብረታቸውን ሁሉ እንዲተዉ፥ ሥራቸውንና ቤቶቻቸውንና ንብረቶቻቸውን እንዲለቁና ዳግመኛም እንዳይዟቸው እንደማይፈልግ ነገርኋቸው፤ ነገር ግን የባለቤትነት መብታቸውን እንዲክዱ፥ እነዚህ ነገሮች የጌታ እንጂ የእነርሱ እንዳልሆኑ እንዲያስተውሉና እንዲገነዘቡ እንደሚፈልግ፤ የእርሱ ይገባኛል ጥያቄ ፍጹም እንደ ሆነ፥ በእነርሱና በሌላው ነገር ሁሉ ላይ ያለው ባለቤትነትም በጽንፈ ዓለም ካለ ከማንኛውም ፍጡር መብት እጅግ በላይ እንደ ሆነ፥ ስለዚህም ከእነርሱ የሚፈልገው ራሳቸውንና ሌላውን ነገር ሁሉ የእርሱ እንደ ሆነ አድርገው እንዲጠቀሙበት እንደ ሆነ፤ ጊዜያቸውን፥ ኃይላቸውን፥ ሀብታቸውን፥ ተጽዕኖአቸውን፥ ወይም ያላቸውን ሌላ ማንኛውንም ነገር የጌታ ሳይሆን የራሳቸው እንደ ሆነ አድርገው የመጠቀም መብት እንዳላቸው ፈጽሞ እንዳያስቡ ነገርኋቸው።

እኔ እስከማውቀው ድረስ ዶ/ር ቢቸር በዚያን ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ በምንም ጊዜ በተናገርሁት ነገር ላይ ተቃውሞ አላነሡም፤ በተናገሩትም ነገር ከዚህ ጋር የሚጋጭ ነገር ማለታቸው አይመስልም። ቢሆንም ቃላቸው፥ ንብረታቸውን በተዉበትና ለእርሱ በሰጡበት ስሜት እግዚአብሔር መልሶ እንደሚሰጣቸው የሚያስመስል ስሜት የሚያሳድር ነበር።

በዚያን ጊዜ የቦስተን የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት አባላት በአጠቃላይ የትምህርት አመለካከቶቼን ያለ ጥያቄ የተቀበሉ ይመስለኛል። ዶ/ር ቢቸር እንደ ተቀበሉ አውቃለሁ፤ ከእኔ ጋር እንደሚስማሙት የሥነ መለኮት አመለካከቱ ፈጽመው የሚስማሙበትን ሰው አይተው እንደማያውቁ ነግረውኛልና። ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ ብዙዎቹ የተቃወሙት የኦርቶዶክሳዊነቴ አንድ ነጥብ ነበር። በዚያን ጊዜ በቦስተን አንድ ወቅታዊ መጽሔት ያሳትሙ የነበሩ ይመስለኛል፥ አቶ ራንድ የተባሉ አንድ ሰው በዳግመኛ መወለድ ውስጥ ስላለው መለኮታዊ ተግባር በነበረኝ አመለካከት ላይ ጠንካራ ጽሑፍ ጻፉ። እኔ የሰበክሁት መለኮታዊው ተግባር የማስተማርና የማሳመን ተግባር እንደ ሆነ፥ ተጽዕኖውም ምግባራዊ እንጂ ግዑዛዊ እንዳልሆነ ነበር። ፕሬዚዳንት ኤድዋርድስ የዚህ ተቃራኒ የሆነውን አመለካከት ይዘው ነበር፤ አቶ ራንድም ከፕሬዚዳንት ኤድዋርድስ ጋር በመስማማት በዳግመኛ መወለድ የሚፈጸመው መለኮታዊ ተግባር ግዑዛዊ እንደ ሆነ፥ በነፍስ የፈቃድ አቋምና ምርጫ ላይ ለውጥ ከማምጣት ይልቅ የባሕርይ ለውጥን እንደሚያስገኝ ያምኑ ነበር። አቶ ራንድ በዚህ ጉዳይ ላይ የነበረኝን አመለካከት ፈጽሞ ከመንገድ የወጣ አድርገው ቈጠሩት። በትችት መንፈስ ያተኮሩባቸው ሌሎች አንዳንድ የትምህርት ነጥቦችም ነበሩ፤ ለምሳሌም ምግባራዊ ብልሹነት በፈቃድ ላይ የተመሠረተ ባሕርይ እንዳለው፥ ኃጢአተኛውም በዳግመኛ መወለድ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንደ ሆነ የነበሩኝ አመለካከቶች።

ዶ/ር ዊዝነር መልስ ጻፉ፤ ስለ መንፈስ ቅዱስ የማሳመን ወይም ምግባራዊ ተጽዕኖ ከያዝኋቸው አመለካከቶች በቀር አመለካከቶቼን ደገፉ። የመንፈስ ተግባር ግዑዛዊ ሳይሆን ምግባራዊ ብቻ ነው የሚለውን አቋም፥ ፕሬዚዳንት ኤድዋርድስንና የኒው ኢንግላንድን አጠቃላይ የኦርቶዶክስ አመለካከት በመቃወም ለመያዝ በዚያን ጊዜ ገና ዝግጁ አልነበሩም። የአንዶቨሩ ዶ/ር ውድስም በአንዱ ወቅታዊ መጽሔት፥ በአንዶቨር በሚታተመው ይመስለኛል፥ «መንፈስ ቅዱስ የዳግመኛ መወለድ ደራሲ ነው» በሚል ርዕስ አንድ ጽሑፍ አሳተሙ። ርዕሱ ይህ ነበር ብዬ አስባለሁ፤ ያም ሆነ ይህ ዓላማው ዳግመኛ መወለድ የእግዚአብሔር ሥራ መሆኑን ማረጋገጥ ነበር። እርሳቸውም እንደሚጠበቀው ልብን በመለወጥ ሥራ ውስጥ ያለውን መለኮታዊ ተግባር የሚያረጋግጡትን የመጽሐፍ ክፍሎች ጠቀሱ።

ለዚህ በጽሑፍ ምንም መልስ አልሰጠሁም፤ ነገር ግን በስብከቴ ያ የእውነት ግማሽ ብቻ እንደ ሆነ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ዳግመኛ መወለድ የሰው ሥራ እንደ ሆነም እንዲሁ በግልጽ እንደሚያረጋግጥ ተናገርሁ፤ ይህንንም የሚያረጋግጡትን ክፍሎች ጠቀስሁ። ጳውሎስ ለአንዲቱ ቤተ ክርስቲያን እንደ ወለዳቸው፥ ማለትም ዳግመኛ እንደ ወለዳቸው ተናግሯል፤ ዳግመኛ መወለድ ለእግዚአብሔር በተሰጠባቸው በሌሎች ክፍሎች የተጠቀሰው ያው ቃል ነውና። ስለዚህ እግዚአብሔር በዳግመኛ መወለድ ውስጥ ተግባር እንዳለው፥ ተግባሩም የማስተማር ወይም የማሳመን እንደ ሆነ ማሳየት ቀላል ነው። ዳግመኛ የሚወለደው ሰውም ተግባር እንዳለው፥ የንስሐ፥ የእምነትና የፍቅር ድርጊቶች የራሱ እንደ ሆኑ፥ መንፈስም እውነትን በፊቱ በማቅረብ እነዚህን ድርጊቶች እንዲፈጽም እንደሚያሳምነው ማሳየት ቀላል ነው። እውነት መሣሪያው እንደ መሆኑ መጠን መንፈስ ቅዱስ ከፈጻሚዎቹ አንዱ መሆን አለበት፤ ሰባኪ ወይም ሌላ አስተዋይ ሰብዓዊ ፈጻሚም በአብዛኛው በሥራው ውስጥ ይተባበራል። እኔ እስከማስታውሰው ድረስ በዚያን ጊዜ ባደረግናቸው ውይይቶች በአንዳቸውም ውስጥ ክርስቲያናዊ ያልሆነ አንዳችም ነገር አልነበረም፤ መንፈስን ያሳዘነ ወይም በወንድሞች መካከል ደግነት የጎደለው ስሜት የፈጠረ ነገር አልነበረም።

በተለያዩት ጉባኤዎች እየተዘዋወርሁ በመስበክ አንዳንድ ሳምንታት ካሳለፍሁ በኋላ፥ በኤሴክስ ስትሪት የሚገኘውን የአቶ ግሪንን ቤተ ክርስቲያን ለተወሰነ ጊዜ በቋሚነት ለማገልገል ተስማማሁ። ስለዚህ ጥረቴን በዚያ የሥራ መስክ ላይ አተኮርሁ። የተባረከ የጸጋ ሥራ ሆነ፤ በከተማዪቱ የተለያዩ ክፍሎችም ብዙ ሰዎች ተለወጡ።

በዚያ ዘመን ሁሉ ከጥቂት ቀናት ወይም ሳምንታት በላይ ዕረፍት ሳይኖረኝ ለአሥር ዓመት ያህል በወንጌላዊነት ሠርቼ ስለ ነበር ደክሞኝ ነበር። የአገልግሎት ወንድሞቹ እውነተኛ ሰዎች ነበሩ፤ በሚያውቁት መጠን ሥራውን አጥብቀው ይዘውት ነበር፤ መልካም ውጤቶችንም ለማስገኘት በታማኝነትና በብቃት ሠርተዋል።

በዚህ ጊዜ በኒው ዮርክ ከተማ ሁለተኛ ነጻ ቤተ ክርስቲያን ተመሥርቶ ነበር። የመጀመሪያው ነጻ ቤተ ክርስቲያን የሆነው የአቶ ጆኤል ፓርከር ቤተ ክርስቲያን እጅግ ከማደጉ የተነሣ አንድ ቡድን ተለይቶ ወጥቶ ሁለተኛ ቤተ ክርስቲያን መሥርቶ ነበር፤ በቅርብ ዓመታት በአንዶቨር ፕሮፌሰር የሆኑት ቄስ ባሮውስም ለዚህ ቤተ ክርስቲያን ይሰብኩ ነበር። አንዳንድ ቀናተኛ ወንድሞች እኔ ወደዚያ መጥቼ እንድሰብክ ቅድመ ሁኔታ አድርገው፥ አንድ ቲያትር ቤት ተከራይተው ለቤተ ክርስቲያን እንዲሆን ለማዘጋጀት ሐሳብ በማቅረብ ከኒው ዮርክ ጻፉልኝ። በኒው ዮርክ እጅግ ሃይማኖተ ቢስ የሆነው ሕዝብ በሚኖርበት አካባቢ እምብርት ላይ የሚገኘውን «የቻታም ስትሪት ቲያትር» ይባል የነበረውን ለማግኘት ሐሳብ አቀረቡ። ባለቤቶቹም ወደ ቤተ ክርስቲያን ቢለወጥ በእጅጉ የሚፈቅዱ ሰዎች ነበሩ። በዚህ ጊዜ ሦስት ልጆች ነበሩን፤ በወንጌላዊነት እየሠራሁ ቤተሰቤን ይዤ መሄድ በቀላሉ አልቻልሁም። ኃይሌም በእጅጉ ተሟጦ ነበር፤ ስለ ጉዳዩ ከጸለይሁና ካጤንሁት በኋላ ከሁለተኛው ነጻ ቤተ ክርስቲያን የቀረበልኝን ጥሪ ተቀብዬ ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ በኒው ዮርክ ለመሥራት ወሰንሁ።

ጨርሰዋል፦ በኦበርን፥ በባፋሎ፥ በፕሮቪደንስና በቦስተን የተካሄዱ መነቃቃቶች

ቀዳሚ ቀጣይ