የቄስ ቻርልስ ጂ. ፊኒ ማስታወሻዎች
በሮቼስተር የተካሄደው መነቃቃት፥ 1830

ምዕራፍ 21 · 21 ደቂቃ ንባብ · 27 ደቂቃ ማዳመጥ

በሮቼስተር የተካሄደው መነቃቃት፥ 1830

ከኒው ዮርክ ከወጣሁ በኋላ በዋይትስታውን ጥቂት ሳምንታት ቆየሁ፤ እንደ ወትሮውም ወደ ብዙ አቅጣጫዎች እንድሄድ ስለ ተጨነቅሁ፥ ተግባሬ ምን እንደ ሆነ ለማወቅ እጅግ ግራ ተጋባሁ። ከሌሎቹም መካከል፥ አቶ ፓርከር እረኛ ሆነው ያገለገሉበት በሮቼስተር የሚገኘው ሦስተኛው የፕሪስባይቴሪያን ቤተ ክርስቲያን ወደዚያ መጥቼ ለተወሰነ ጊዜ እንዳገለግላቸው አጥብቆ ጋበዘኝ።

ስለ ሁኔታው ጠየቅሁ፤ በብዙ ምክንያቶችም ተስፋ የማይሰጥ የሥራ መስክ ሆኖ አገኘሁት። በሮቼስተር የነበሩት የፕሪስባይቴሪያን አብያተ ክርስቲያናት ሦስት ብቻ ነበሩ። ግብዣውን ያቀረበው ሦስተኛው ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ አልነበረውም፤ ሃይማኖትም በዚያ ዝቅ ያለ ሁኔታ ላይ ነበረ። ሁለተኛው ቤተ ክርስቲያን፥ ማለትም ይጠራበት እንደ ነበረው «የጡብ ቤተ ክርስቲያን»፥ እረኛ ነበረው፤ እርሳቸውም እጅግ መልካም ሰው ነበሩ፤ ነገር ግን ስለ ስብከታቸው በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ከፍተኛ መከፋፈል ነበረ፤ እርሳቸውም ተረብሸው ለመልቀቅ ተዘጋጅተው ነበር። በሦስተኛው ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌና በመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን እረኛ መካከል በፕሪስባይተሪው ፊት ሊታይ የተቃረበ ክርክር ነበረ። ይህና ሌሎች ጉዳዮች በሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በተወሰነ መጠን ክርስቲያናዊ ያልሆነ ስሜት ቀስቅሰው ነበር፤ በአጠቃላይም በዚያን ጊዜ የሚያስፈራ የሥራ መስክ መስሎ ታየ። በሮቼስተር የነበሩት ወዳጆች፥ ማለቴ የሦስተኛው ቤተ ክርስቲያን አባላት፥ ወደዚያ እንድሄድ እጅግ ጓጉተው ነበር። ያለ እረኛ በመቅረታቸው፥ በመካከላቸው ሃይማኖትን የሚያነቃቃ አንድ ነገር ካልተደረገ በቀር ይበተናሉ፥ ምናልባትም እንደ ቤተ ክርስቲያን ፈጽመው ይጠፋሉ የሚል ታላቅ ፍርሃት ተሰምቷቸው ነበር።

እነዚህ አጥብቀው የቀረቡ ግብዣዎች በፊቴ ሳሉ፥ ብዙ ጊዜ እንደ ሆነብኝ፥ እጅግ ግራ ተጋባሁ። በአማቴ ቤት ቆይቼ ጉዳዩን አሰላሰልሁ፤ በመጨረሻም አንድ ቦታ ሥራ መያዝና መሥራት እንዳለብኝ ተሰማኝ። ስለዚህ ሣጥኖቻችንን ሸክፈን ሰባት ማይል ያህል ርቃ ወደምትገኘው ወደ ዩቲካ ወረድን፤ በዚያም ብዙ የሚጸልዩ ወዳጆች ነበሩኝ። ከሰዓት በኋላ ደረስን፤ በምሽቱም በጸሎታቸውና በጥበባቸው እጅግ የምተማመንባቸው ቁጥራቸው ብዙ የሆነ ዋና ዋና ወንድሞች፥ በጠየቅኋቸው መሠረት፥ ስለሚቀጥለው የሥራ መስኬ ለመመካከርና ለመጸለይ ተሰበሰቡ። ስለ ሮቼስተር ያለውን እውነታ ሁሉ በፊታቸው አቀረብሁ፤ እንዲሁም በዚያን ጊዜ ስለ ተጋበዝሁባቸው ሌሎች የሥራ መስኮች በማውቀው መጠን ዋና ዋና እውነታዎቹን ገለጽሁላቸው። ከሁሉም ይበልጥ የማይስበው ሮቼስተር መሰለ።

ጉዳዩን ሁሉ ተነጋግረን፥ በውይይት መካከል ብዙ ጊዜ ከጸለይን በኋላ፥ ወንድሞች ባደርገው ጥበብ ነው ብለው ስላሰቡት ነገር አንዱ ከሌላው ቀጥሎ አስተያየታቸውን ሰጡ። ሮቼስተር ከኒው ዮርክ ወይም ከፊላዴልፊያ፥ በዚያን ጊዜም ከተጋበዝሁባቸው ከሌሎች አንዳንድ የሥራ መስኮች ጋር ጨርሶ ሊወዳደር የማይችል እጅግ የማይስብ የሥራ መስክ ነው በሚለው አስተያየት በአንድ ድምፅ ተስማሙ። ከዩቲካ ወደ ምዕራብ ሳይሆን ወደ ምሥራቅ መሄድ አለብኝ የሚል ጽኑ እምነት ነበራቸው። በዚያን ጊዜ ይህ የእኔም ስሜትና እምነት ነበር፤ ወደ ሮቼስተር ሳይሆን ወደ ኒው ዮርክ ወይም ወደ ፊላዴልፊያ ለመሄድ የቈረጥሁ መስሎኝ ከስብሰባው ወጣሁ። ይህ የባቡር ሐዲዶች ከመኖራቸው በፊት ነበር፤ በዚያም ምሽት ስንለያይ፥ ለቤተሰብ ጉዞ ከሁሉ ይበልጥ አመቺ የነበረውን የቦይ ጀልባ ይዤ በማለዳ ወደ ኒው ዮርክ ለመነሣት አስቤ ነበር።

ነገር ግን ወደ ማረፊያዬ ከገባሁ በኋላ ጥያቄው በተለየ መልክ ወደ አእምሮዬ መጣ። አንድ ነገር እንዲህ ብሎ የሚጠይቀኝ መሰለ፦ «ወደ ሮቼስተር ከመሄድ የሚከለክሉህ ምክንያቶች ምንድር ናቸው?» በቀላሉ ልዘረዝራቸው እችል ነበር፤ ነገር ግን ጥያቄው እንደ ገና እንዲህ ብሎ ተመለሰ፦ «አሃ! ግን እነዚህ መልካም ምክንያቶች ናቸውን? በእርግጥ በእነዚህ ችግሮች ምክንያት በሮቼስተር ይበልጥ ትፈለጋለህ። መታረም የሚያስፈልጋቸው ብዙ ነገሮች ስላሉ፥ ስሕተቱም ብዙ ስለ ሆነ ነውን ከዚያ የሥራ መስክ የምትሸሸው? ሁሉ የተስተካከለ ቢሆን ኖሮ ግን አንተ ባላስፈለግህ ነበር።» ብዙም ሳልቆይ ሁላችንም ተሳስተን እንደ ነበርን፥ ወደ ሮቼስተር እንዳልሄድ የወሰንንባቸው ምክንያቶችም እንድሄድ የሚያስገድዱ እጅግ ጠንካራ ምክንያቶች እንደ ሆኑ ደመደምሁ። ከችግሮቹ የተነሣ ሥራውን ከመያዝ ወደ ኋላ ማለቴ አሳፈረኝ፤ ጌታም ከእኔ ጋር እንደሚሆን፥ ያም የሥራ መስኬ እንደ ሆነ በብርቱ ተሰማኝ። ለማረፍ ከመተኛቴ በፊት ጌታ እንድሄድበት የሚፈልገው ስፍራ ሮቼስተር እንደ ሆነ አእምሮዬ ፈጽሞ ወሰነ። ውሳኔዬን ለባለቤቴ ነገርኋት፤ በዚሁ መሠረትም በማለዳ፥ የከተማው ሰዎች በአብዛኛው ገና ሳይንቀሳቀሱ፥ የመንገደኞች ጀልባ መጣ፤ ተሳፍረንም ወደ ምሥራቅ ፈንታ ወደ ምዕራብ ሄድን።

በዩቲካ የነበሩት ወንድሞች መድረሻችን እንደ ተለወጠ ሲሰሙ እጅግ ተደነቁ፤ ውጤቱንም በብዙ ስጋት ተጠባበቁ።

በማለዳ ሮቼስተር ደረስን፤ የሦስተኛው ቤተ ክርስቲያን ዋና ሽማግሌ፥ ዶ/ር ፔኒንም በፕሪስባይተሪው ፊት የከሰሱት ሰው፥ አቶ ጆሳያ ቢሰል ለጊዜው በቤታቸው እንድናርፍ ጋበዙን። እንደ ደረስሁ የአጎቴን ልጅ አቶ ኤስ——ን በመንገድ ላይ አገኘሁት፤ እርሱም ወደ ቤቱ ጋበዘኝ። እርሱ የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ነበር፤ ወደ ሮቼስተር እንደምመጣ ይጠበቅ እንደ ነበር ሰምቶ፥ እረኛው ዶ/ር ፔኒ ከእኔ ጋር ተገናኝተው እንዲነጋገሩና በሥራዬ ከእኔ ጋር ለመተባበር እንዲዘጋጁ እጅግ ጓጉቶ ነበር። የአቶ ቢሰል እንግዳ እንደምሆን ነግሬው መልካም ግብዣውን አልተቀበልሁም። ነገር ግን ከቁርስ በኋላ እንደ ገና ወደ እኔ መጥቶ በቤቱ በእኔና በዶ/ር ፔኒ መካከል ስብሰባ እንዳዘጋጀ ነገረኝ። ዶክተሩን ለማግኘት ፈጥኜ ሄድሁ፤ የሚያበረታታ ክርስቲያናዊ ውይይትም አደረግን። ሥራዬን በጀመርሁ ጊዜ ዶ/ር ፔኒ ስብሰባዎቻችንን ተካፈሉ፤ ብዙም ሳይቆዩ ወደ መስበኪያ መድረካቸው ጋበዙኝ። አቶ ኤስ—— በእረኞቹና በአብያተ ክርስቲያናቱ መካከል መልካም መግባባት እንዲፈጠር ጥረት አደረገ፤ ብዙም ሳይቆይ በአብያተ ክርስቲያናቱ አቋምና መንፈሳዊ ሁኔታ ላይ ታላቅ ለውጥ ታየ።

ብዙም ሳይቆይ በጣም ጐልተው የሚታዩ አንዳንድ መለወጦች ሆኑ። ከመጀመሪያዎቹ አማኞች አንዷ በዚያች ከተማ የታወቀ የአንድ ጠበቃ ሚስት ነበረች። እርሷ ከፍ ያለ ማዕረግ የነበራት፥ የተማረችና ሰፊ ተጽዕኖ የነበራት ወይዘሮ ነበረች። መለወጧ እጅግ ጐልቶ የሚታይ ነበር። መጀመሪያ ያየኋት አንዲት ወዳጇ ከእርሷ ጋር ወደ ክፍሌ መጥታ ስታስተዋውቀኝ ነበር። ያስተዋወቀቻት ሴት ክርስቲያን ነበረች፤ እርሷም ወዳጇ በአእምሮዋ እጅግ እንደ ተጨነቀች ተረድታ መጥታ እንድታየኝ አግባብታት ነበር።

ወይዘሮ ኤም—— ተድላ የምትወድ፥ ዓለማዊና ማኅበራዊ ግንኙነትን እጅግ የምትወድ ሴት ነበረች። በኋላ እንደ ነገረችኝ፥ መጀመሪያ ወደዚያ በመጣሁ ጊዜ እጅግ አዝና ነበር፤ መነቃቃት ይሆናል ብላ ፈርታ ነበር፤ መነቃቃት ደግሞ በዚያ ክረምት ለራሷ ያቀደቻቸውን ደስታዎችና መዝናኛዎች እጅግ ያደናቅፍባት ነበር። ከእርሷ ጋር ስነጋገር የጌታ መንፈስ በእርግጥ ሳይራራ ከእርሷ ጋር እየሠራ እንደ ነበረ ተረዳሁ። በታላቅ የኃጢአት ወቀሳ ተደፍታ ነበር። ከእርሷ ጋር ብዙ ከተነጋገርሁ በኋላ ኃጢአትን፥ ዓለምንና ራሷን፥ ሁሉንም ነገር ለክርስቶስ ብላ እንድትተው አጥብቄ መከርኋት። እጅግ ትዕቢተኛ ሴት እንደ ሆነች አየሁ፤ ይህም ከባሕርይዋ ሁሉ ይበልጥ ጐልቶ የሚታየው ገጽታ መሆኑ ታየኝ። ንግግራችንን ስንጨርስ ለመጸለይ ተንበረከክን፤ አእምሮዬም በግልጥ በታየው በልቧ ትዕቢት ጉዳይ ተሞልቶ ስለ ነበር፥ ብዙም ሳልቆይ ይህን ጥቅስ አነሣሁ፦ «ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም።» ይህን ጉዳይ በጸሎት አገላብጬ አቀረብሁት፤ ወዲያውም ወይዘሮ ኤም—— ከጎኔ ተንበርክካ ሳለች ያን ጥቅስ ስትደግም ሰማሁ፦ «ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ — እንደ ሕፃናት — ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ።» አእምሮዋ በዚያ እንደ ተያዘ፥ የእግዚአብሔርም መንፈስ በልቧ ላይ እያስጨነቀው እንደ ነበረ አስተዋልሁ። ስለዚህ ያን ጉዳይ በአእምሮዋ ፊት እያቀረብሁ፥ እርሷንም ያን ነገር ራሱን፥ ማለትም መለወጥንና እንደ ሕፃን መሆንን የምትፈልግ አድርጌ በእግዚአብሔር ፊት እያቀረብኋት መጸለዬን ቀጠልሁ።

ጌታ ጸሎትን እየመለሰ እንደ ነበረ ተሰማኝ። እንዲያደርገው የለመንሁትን ሥራ ራሱን እየሠራ እንደ ነበረ እርግጠኛ ሆንሁ። ልቧ ተሰበረ፤ ስሜቷ ፈሰሰ፤ ከተንበረከክንበትም ከመነሣታችን በፊት በእርግጥ ሕፃን ሆነች። መጸለዬን አቁሜ ዓይኖቼን ገልጬ ስመለከታት፥ ፊቷ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ እንባዋ ይፈስስ ነበር፤ ሕፃን እንድትሆን እየጸለየች ያለች ትመስል ነበር። ተነሣች፤ ሰላም አገኘች፤ በደስታ በተሞላ እምነት ጸንታ ሄደች። ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ስለ ሃይማኖታዊ እምነቷ በግልጥ የምትናገር፥ ለወዳጆቿም መለወጥ የምትቀና ሆነች። መለወጧም፥ እንደሚጠበቀው፥ እርሷ በምትገኝበት የኅብረተሰብ ክፍል መካከል ብዙ መነቃቃትን ፈጠረ።

ወደ ሮቼስተር እስከ ሄድሁበት ጊዜ ድረስ፥ አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር፥ ከጊዜ በኋላ «የተጨነቁ ሰዎች መቀመጫ» ተብሎ የተጠራውን መነቃቃትን ለማስፋፋት እንደ መንገድ ፈጽሞ ተጠቅሜበት አላውቅም ብዬ አምናለሁ። አንዳንድ ጊዜ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሰዎች እንዲቆሙ እጠይቅ ነበር፤ ይህን ግን ብዙ ጊዜ አላደረግሁትም። ይሁን እንጂ ጉዳዩን ሳጠና፥ ኃጢአተኞችን ቆም ብለው እንዲወስኑ የሚያደርግ አንድ ዘዴ እንደሚያስፈልግ ብዙ ጊዜ ይሰማኝ ነበር። ከራሴ ልምድና ምልከታ እንደ ተረዳሁት፥ በተለይ በከፍተኛዎቹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ማሸነፍ የሚያስፈልገው ትልቁ መሰናክል፥ ስለ ነፍሳቸው የተጨነቁ ጠያቂዎች መሆናቸው እንዳይታወቅ የነበራቸው ፍርሃት ነበር። ስለ ነፍሳቸው መጨነቃቸውን ለሌሎች የሚገልጥ ማናቸውንም አቋም ለመያዝ እጅግ ይኰሩ ነበር።

ደግሞም ልባቸውን ወዲያውኑ እንዲሰጡ እንደሚጠበቅባቸው በእነርሱ ላይ ስሜት የሚያሳድር አንድ ነገር እንደሚያስፈልግ ተረድቼ ነበር፤ በኃጢአታቸው እንደ ነበሩት በዓለም ፊት በግልጥ እንዲሠሩና እንዲወስኑ የሚጠራቸው፥ በሕዝብ ፊትም ለክርስቶስ አገልግሎት ራሳቸውን የሚያስገዛቸው አንድ ነገር። በሕዝብ ጉባኤ ውስጥ እንዲቆሙ ብቻ በጠራኋቸው ጊዜ ይህ እጅግ መልካም ውጤት እንደ ነበረው አገኘሁ፤ በሄደበትም መጠን የታሰበለትን ዓላማ አሟላ። ይሁን እንጂ ከብዙዎቹ ኃጥኣን መካከል ለይቶ አውጥቶ የኃጢአት መንገዳቸውን በይፋ እንዲክዱና ራሳቸውን በይፋ ለእግዚአብሔር እንዲሰጡ ለማድረግ ከዚህ የበለጠ ነገር እንደሚያስፈልግ ለተወሰነ ጊዜ ተሰምቶኝ ነበር።

በትክክል የማስታውስ ከሆነ፥ ይህን ዘዴ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቅሁት በሮቼስተር ነበር። ይህም «አዳዲስ ዘዴዎች» የሚለው ጩኸት ከተነሣ ከብዙ ዓመታት በኋላ ነበር። ወይዘሮ ኤም—— ከተለወጠች ከጥቂት ቀናት በኋላ፥ ለመጀመሪያ ጊዜ ይመስለኛል፥ የኃጢአት ወቀሳቸው በስሎ ኃጢአታቸውን ለመተውና ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ለመስጠት ፈቃደኞች የሆኑትን ሰዎች ሁሉ፥ ባዶ እንዲደረጉ ወደ ጠየቅኋቸው ወደ አንዳንድ መቀመጫዎች ወደ ፊት እንዲመጡና፥ እኛ ስለ እነርሱ ስንጸልይ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር እንዲያቀርቡ ጠራኋቸው። ከጠበቅሁት እጅግ የሚበልጥ ቁጥር ወደ ፊት መጣ፤ ከእነርሱም መካከል ሌላ አንዲት የታወቀች ወይዘሮ ነበረች፤ እርሷን የሚያውቁና ከዚያው የኅብረተሰብ ክበብ የሆኑ ሌሎች ብዙዎችም ወደ ፊት መጡ። ይህም በዚያ የኅብረተሰብ ክፍል ዘንድ ያለውን ትኩረት ጨመረ፤ ጌታም ከፍተኛዎቹን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመለወጥ እያለመ እንደ ነበረ ብዙም ሳይቆይ ታየ። ብዙም ሳይቆይ ስብሰባዎቼ በዚያ ክፍል ሰዎች ተጨናነቁ። ጠበቆች፥ ሐኪሞች፥ ነጋዴዎች፥ በእርግጥም ከሁሉ ይበልጥ የተማሩት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ እየተሳቡ፥ ይበልጥም በቀላሉ እየተነኩ ሄዱ።

ብዙም ሳይቆይ ሥራው በዚያች ከተማ በነበሩት ጠበቆች መካከል በሰፊው ውጤት አሳየ። ከግዛቱ ዋና ዋና ጠበቆች ብዙዎቹ ሁልጊዜ የሚኖሩት በሮቼስተር ነበር። ሥራው ብዙም ሳይቆይ ከእነርሱ ብዙዎቹን ያዘ። እጅግ ተጨነቁ፤ ወደ ጠያቂዎች ስብሰባዎቻችንም በነጻነት መጡ፤ ከእነርሱም ብዙዎቹ ከጊዜ በኋላ እንደ ተጠራው ወደ ተጨነቁ ሰዎች መቀመጫ ወደ ፊት መጥተው ልባቸውን በይፋ ለእግዚአብሔር ሰጡ። አንድ ምሽት ከስብከት በኋላ ሦስቱ ተከትለውኝ ወደ ክፍሌ እንደ መጡ አስታውሳለሁ፤ ሁሉም በኃጢአት ወቀሳ በጥልቅ ተይዘው ነበር፤ ሁሉም፥ እንደማምነው፥ በተጨነቁ ሰዎች መቀመጫ ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነገር ግን በአእምሮአቸው ግልጽ አልነበሩም፤ ከእግዚአብሔር ጋር ሰላማቸው እንደ ተደረገ እስኪረጋገጥላቸውም ድረስ ወደ ቤታቸው መሄድ እንደማይችሉ ተሰማቸው። ከእነርሱ ጋር ተነጋገርሁ፤ ከእነርሱም ጋር ጸለይሁ፤ ከመሄዳቸውም በፊት ሁሉም በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ሰላም እንዳገኙ አምናለሁ።

ሥራው ከተጀመረ ብዙም ሳይቆይ በአቶ ቢሰልና በዶ/ር ፔኒ መካከል የነበሩት ችግሮች እንደ ተፈወሱ መናገር ነበረብኝ፤ በዚያ የነበሩት መከፋፈሎችና ግጭቶች ሁሉ ተስተካከሉ፤ ስለዚህም የሁሉን አቀፍ ደግነትና የኅብረት መንፈስ አብያተ ክርስቲያናትን ሁሉ ሞላ።

በአንድ ወቅት በመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን የስብከት ቀጠሮ ነበረኝ። በዚያ ቀን በከተማው ውስጥ ወታደራዊ ሰልፍ ነበረ። ሚሊሻዎቹ ተጠርተው ነበር፤ የሰልፉ ግርግርም የሕዝቡን ትኩረት ይስብና የጌታን ሥራ ያበላሻል ብዬ ፈርቼ ነበር። ቤቱ በየስፍራው ሁሉ ሞልቶ ነበር። ዶ/ር ፔኒ የአምልኮውን ሥርዓት ከፍተው የመጀመሪያውን ጸሎት እየጸለዩ ሳሉ፥ የጠመንጃ ተኩስ ድምፅ የመሰለኝን ነገርና መስኮት እንደ ተሰበረ ያህል የመስተዋት ኳኳታ ሰማሁ። ከውጭ ካለው ወታደራዊ ሰልፍ አንድ ግድ የለሽ ሰው ወደ መስኮቱ እጅግ ቀርቦ ተኩሶ የመስኮቱን መስተዋት የሰበረ መሰለኝ። ነገር ግን እንደ ገና ለማሰብ ጊዜ ሳላገኝ፥ ዶ/ር ፔኒ በላዬ ላይ ሊዘሉ ምንም ያልቀራቸው ያህል ከመስበኪያ መድረኩ ዘለው ወረዱ፤ እኔ ከኋላቸው ባለው ሶፋ አጠገብ ተንበርክኬ ነበርና። መስበኪያ መድረኩ በቤተ ክርስቲያኑ ፊት ለፊት በሁለቱ በሮች መካከል ነበረ። የቤተ ክርስቲያኑ የኋላ ግንብ በቦዩ ዳር ላይ ቆሞ ነበር። ጉባኤው በቅጽበት ፍጹም ድንጋጤ ውስጥ ገባ፤ ሁሉም አእምሮአቸውን እንደ ሳቱ ወደ በሮቹና ወደ መስኮቶቹ ተሯሯጡ። አንዲት አረጋዊት ሴት በቤተ ክርስቲያኑ ጀርባ ያለውን መስኮት ከፍ አድርጋ ያዘች፤ በዚያም፥ እንደ ተነገረኝ፥ ብዙዎች ዘለው ወደ ቦዩ ገቡ። ግፊያው እጅግ የሚያስፈራ ነበር። አንዳንዶች ከሰገነቶቹ ላይ ወደ ታች ወዳሉት መተላለፊያዎች ዘለሉ፤ በመተላለፊያዎቹም ውስጥ እርስ በርሳቸው ተረጋገጡ።

በመስበኪያ መድረኩ ላይ ቆምሁ፤ የሆነውንም ሳላውቅ እጆቼን አንሥቼ በሙሉ ድምፄ «ጸጥ በሉ! ጸጥ በሉ!» ብዬ ጮኽሁ። ወዲያውም ሁለት ሴቶች ወደ መስበኪያ መድረኩ እየተሯሯጡ ወጥተው፥ አንዷ በአንድ ወገን ሌላዋም በሌላው ወገን ሆነው፥ ተሸብረው ያዙኝ። ዶ/ር ፔኒ ወደ መንገድ ሮጠው ወጡ፤ ሰዎቹም በሚችሉት ፍጥነት በየአቅጣጫው እየወጡ ነበር። አንዳች አደጋ እንዳለ ስላላወቅሁ ሁኔታው እጅግ አስቂኝ ሆኖ ታየኝ፤ ከመሳቅ ራሴን መግታት እስኪያቅተኝ ድረስ። በመተላለፊያዎቹ ውስጥ እርስ በርሳቸው ይረጋገጡ ስለ ነበር፥ በብዙ አጋጣሚዎች ተጨፍልቀው የወደቁ ሰዎች ሲነሡና በላያቸው ላይ የተረባረቡትን ሌሎች ሲያስወግዱ አስተዋልሁ። በመጨረሻ ሁሉም ወጡ። ብዙዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተጎዱ፤ ነገር ግን የሞተ አልነበረም። ሆኖም ቤቱ በልዩ ልዩ የሴቶች አልባሳት ተሞልቶ ነበር። የሴቶች ባርኔጣዎች፥ ሻሾች፥ ጓንቶች፥ መሐረቦችና የቀሚስ ቁርጥራጮች በየአቅጣጫው ተበትነው ነበር። ወንዶቹ በአብዛኛው ባርኔጣቸውን ሳይዙ የወጡ ይመስለኛል፤ በዚያ አስፈሪ ግፊያም ብዙ ሰዎች ክፉኛ ተቀጥቅጠው ነበር።

የቤተ ክርስቲያኑ ግንቦች ለተወሰነ ጊዜ ወደ ታች ሲሰምጡ እንደ ነበሩ በኋላ ተረዳሁ፤ ምክንያቱም መሬቱ ለቦዩ ቅርብ በመሆኑ እጅግ ርጥብ ነበር። ይህ ጉዳይ አጥጋቢ ሁኔታ ላይ እንዳልሆነ በጉባኤው ውስጥ ይነገር ነበር፤ አንዳንዶችም ማማው ወይም ጣሪያው ይወድቃል፥ ወይም የሕንጻው ግንቦች ይፈርሳሉ ብለው ፈርተው ነበር። እኔ ራሴ ስለዚህ ምንም አልሰማሁም ነበር። የመጀመሪያው ድንጋጤ የተፈጠረው ከጣሪያው አንድ ግንድ ጫፉን ወደ ታች አድርጎ ወድቆ፥ ከኦርጋኑ ፊት ለፊት ካለው መብራት በላይ ያለውን ኮርኒስ ሰብሮ በመግባቱ ነበር።

ቤቱ ሲመረመር ግንቦቹ በእርግጥ ጣሪያው ሊደረመስ የሚችልበት አደጋ እስኪኖር ድረስ ተለጥጠው እንደ ነበሩ ታወቀ። በዚያ ምሽት በሰገነቱ ላይ የነበረው ግፊት በየጎኑ ያሉትን ግንቦች እውነተኛ አደጋ እስኪኖር ድረስ ወደ ውጭ ገፍቷቸው ነበር። ይህ በሆነ ጊዜ፥ ሌሎችም እንደ ፈሩ እገምታለሁ፥ የሕዝቡ ትኩረት ይሳባል፥ ሥራውም እጅግ ይደናቀፋል ብዬ እጅግ ፈራሁ። ነገር ግን የጌታ መንፈስ ሥራውን በእውነት ይዞት ስለ ነበር፥ ምንም ነገር ሊያቆመው የቻለ አይመስልም ነበር።

የጡብ ቤተ ክርስቲያን ተከፈተልን፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም ስብሰባዎቻችን በሁለተኛውና በሦስተኛው ቤተ ክርስቲያን እየተፈራረቁ ይደረጉ ነበር፤ የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያንና ጉባኤ ሰዎችም ወደ ቤቱ መግባት በቻሉት መጠን ይካፈሉ ነበር። ሦስቱ አብያተ ክርስቲያናት፥ በእርግጥም በአጠቃላይ የሁሉም ቤተ እምነቶች ክርስቲያኖች፥ በአንድ ዓላማ የተባበሩ መሰሉ፤ ኃጢአተኞችንም ከእሳት ለመንጠቅ በሙሉ ፈቃደኝነት ወደ ሥራ ገቡ። ስብሰባዎችን ያለማቋረጥ ለማድረግ ተገደድን። በየምሽቱ ማለት ይቻላል እሰብክ ነበር፤ በሰንበትም ሦስት ጊዜ እሰብክ ነበር። ሥራው እንዲህ ያለ ብርቱ መልክ ከያዘ በኋላ የጠያቂዎች ስብሰባዎቻችንን አብዛኛውን ጊዜ በጠዋት እናደርግ ነበር።

አንድ ቀን ጠዋት የጠያቂዎች ስብሰባ እያደረግን እንደ ነበር አስታውሳለሁ፤ በዚያም አንድ ሰው ተገኝቶ ተለወጠ፤ እርሱም የሦስተኛው ቤተ ክርስቲያን አባል የሆነች እጅግ የምትጸልይ፥ እግዚአብሔርን የምትፈራ የአንዲት ሴት አማች ነበር። እርሷ ስለ እርሱ እጅግ ተጨንቃ ነበር፤ ስለ እርሱም በመጸለይ ብዙ ጊዜ ታሳልፍ ነበር። ከጠያቂዎች ስብሰባ በተመለሰ ጊዜ በደስታና በሰላም በተስፋም ተሞልቶ ነበር። እርሷ እግዚአብሔር በዚያ ስብሰባ እንዲለውጠው አጥብቃ በመጸለይ ጊዜውን አሳልፋ ነበር። እንዳገኘችውና መለወጡን እንደ ነገራት፥ ከፊቱም በእውነት እንደ ሆነ ባየች ጊዜ፥ ስሜቱ አሸነፋት፤ ራሷን ስታ ወደቀች፤ ሞተችም።

በዚያን ጊዜ በሮቼስተር አንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበረ፤ ርእሰ መምህሩም በዚያን ጊዜ በሮቼስተር አቅራቢያ በምትገኘው በብራይተን የቤተ ክርስቲያን እረኛ የነበሩት የኤ—— ቢ—— ልጅ አቶ ቢ—— የተባለ ሰው ነበር። አቶ ቢ—— ተጠራጣሪ ነበር፤ ነገር ግን እጅግ ትልቅና የበለጸገ ትምህርት ቤት ይመራ ነበር። ትምህርት ቤቱ የሁለቱም ፆታዎች ተማሪዎች ስለ ነበሩበት፥ በዚያን ጊዜ ወይዘሪት ኤ—— የተባለች ረዳቱና የሥራ ባልደረባው ነበረች። ወይዘሪት ኤ—— ክርስቲያን ሴት ነበረች። ተማሪዎቹ በሃይማኖታዊ አገልግሎቶቹ ተካፈሉ፤ ከእነርሱም ብዙዎቹ ብዙም ሳይቆዩ ስለ ነፍሳቸው በጥልቅ ተጨነቁ። አንድ ቀን ጠዋት አቶ ቢ—— ክፍሎቹ ትምህርታቸውን ማቅረብ እንዳልቻሉ ተረዳ። በፊቱ ባቀረባቸው ጊዜ ስለ ነፍሳቸው እጅግ ተጨንቀው ያለቅሱ ነበር፤ እርሱም እጅግ ግራ እስኪጋባ ድረስ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን አየ። የሥራ ባልደረባውን ወይዘሪት ኤ——ን ጠርቶ፥ ወጣቶቹ ስለ ነፍሳቸው እጅግ ከመጨነቃቸው የተነሣ ትምህርታቸውን ማቅረብ እንዳልቻሉ ነገራት፤ ትምህርት እንዲሰጣቸው አቶ ፊኒን ቢያስጠሩ አይሻልም ወይ ብሎ ጠየቃት። እርሷ ይህን በኋላ ነገረችኝ፤ ይህን ጥያቄ በማቅረቡ እጅግ እንደ ተደሰተች፥ እኔንም እንዲያስጠራኝ በሙሉ ልቧ እንደ መከረችው ነገረችኝ። እንዲሁ አደረገ፤ መነቃቃቱም ያን ትምህርት ቤት በብርቱ ያዘው። አቶ ቢ—— ራሱ ብዙም ሳይቆይ ተስፋ በሚሰጥ ሁኔታ ተለወጠ፤ በትምህርት ቤቱ ውስጥ የነበሩትም ሰዎች ሁሉ ማለት ይቻላል ተለወጡ። ከጥቂት ዓመታት በፊት ወይዘሪት ኤ—— በዚያን ጊዜ በዚያ ትምህርት ቤት ከተለወጡት መካከል ከአርባ የሚበልጡ ሰዎች አገልጋዮች እንደ ሆኑ ነገረችኝ። ይህ ከዚያ በፊት የማላውቀው እውነታ ነበር። በዚያን ጊዜ ከእነርሱ ብዙዎቹን በስማቸው ጠራችልኝ። ከእነርሱም ብዙዎቹ በውጭ አገር ሚስዮናውያን ሆነው ነበር።

ጆዛያ ቢሰል ቤት ጥቂት ሳምንታት ከቆየን በኋላ፥ ይበልጥ መሃል ከተማ በሆነ ስፍራ፥ በከተማዪቱ ጠበቃ በአቶ ቢ—— ቤት ማረፊያ ያዝን፤ እርሳቸውም ክርስቲያን ነኝ የሚሉ ሰው ነበሩ። የሚስታቸው እህት አብራቸው ትኖር ነበር፤ እርሷም ንስሐ ያልገባች ልጃገረድ ነበረች። መልከ መልካም፥ እጅግ ጥሩ ዘማሪና የተማረች ሴት ነበረች፤ ብዙም ሳይቆይ እንደ ተረዳነውም፥ በዚያን ጊዜ የግዛቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ከነበረ ሰው ጋር ለጋብቻ ታጭታ ነበር። እርሱ እጅግ ትዕቢተኛ ሰው ነበር፤ የተጨነቁ ሰዎች መቀመጫን ተቃወመ፥ በእርሱም ላይ ይናገር ነበር። ችሎት ለማስቻል ብዙ ጊዜ ከከተማዪቱ ይርቅ ነበር፤ በዚያም ክረምት አልተለወጠም። ይሁን እንጂ ከጠበቆቹ ብዙዎቹ ተለወጡ፤ ለእርሱ የታጨችው ወጣት ሴትም ተለወጠች። ይህን የምጠቅሰው ዳኛው በኋላ ስላገባት ነው፤ ይህም ከአሥር ዓመት ገደማ በኋላ በተከሰተ መነቃቃት ለራሱ መለወጥ ምክንያት እንደ ሆነ ጥርጥር የለውም፤ የዚያንም መነቃቃት ዋና ዋና ዝርዝሮች በሌላ የትረካዬ ክፍል እጠቅሳለሁ።

ይህ መነቃቃት በሮቼስተር የሥነ ምግባር ሁኔታና በቀጣዩ ታሪኳ ታላቅ ለውጥ አመጣ። በከተማዪቱ ከነበሩት ታዋቂ ወንዶችና ሴቶች እጅግ አብዛኞቹ ተለወጡ። በቶሎ የማልረሳቸው እጅግ ብዙ አስገራሚ ድርጊቶች ተፈጸሙ። አንድ ቀን፥ መጀመሪያ የጐበኘችኝና መለወጥዋን የጠቀስሁት ሴት እንዳነጋግራት ከፈለገችው አንዲት ወዳጅዋ ጋር ልታየኝ መጣች። አነጋገርኋት፤ ነገር ግን በመልክ ሁሉ እጅግ የደነደነችና በጉዳዩ ላይ ለመቀለድ ያዘነበለች ሆና አገኘኋት። ባልዋ ነጋዴ ነበር፤ በማኅበረሰቡም ዘንድ ከፍ ያለ ቦታ የነበራቸው ሰዎች ነበሩ። ለጉዳዩ ትኩረት እንድትሰጥ ባጣደፍኋት ጊዜ፥ ባልዋ ትኩረት ስለማይሰጠው እርሷም እንደማትሰጥ፥ እርሱንም ትታ እንደማትሄድ ነገረችኝ። ባልዋ ትኩረት ስላልሰጠው ብቻ ለመጥፋት ፈቃደኛ እንደ ሆነች፥ እርሱ የራሱን ነፍስ ቸል ስላለ የእርሷን ነፍስ ቸል ማለቷስ ሞኝነት እንዳልሆነ ጠየቅኋት። እርሷም ወዲያውኑ «እርሱ ወደ ሲኦል ቢሄድ እኔም መሄድ እፈልጋለሁ። እርሱ ወደሚሄድበት መሄድ እፈልጋለሁ። በምንም ዓይነት ከእርሱ መለየት አልፈልግም» ብላ መለሰች። በእርሷ ላይ ያሳደርሁት ተጽዕኖ ቢኖርም እንኳ እጅግ ጥቂት እንደ ሆነ መሰለኝ። ነገር ግን ከምሽት ወደ ምሽት ለጉባኤው ልመና አቀርብ፥ ልባቸውን ለእግዚአብሔር ለመስጠት የተዘጋጁትንም ወደ ፊት እንዲወጡ እጠራ ነበር፤ በየምሽቱም እጅግ ብዙ ሰዎች ይለወጡ ነበር።

በኋላ እንደ ሰማሁት፥ ይህች ሴት ወደ ቤት በሄደች ጊዜ ባልዋ «ውዴ ሆይ፥ ዛሬ ማታ ወደ ፊት ወጥቼ ልቤን ለእግዚአብሔር ልሰጥ አስቤአለሁ» አላት። እርሷም «ምን!» አለች፤ «እኔ ዛሬ ክርስቲያን እንደማልሆን፥ ከዚህም ነገር ጋር ምንም ግንኙነት እንደማይኖረኝ ለአቶ ፊኒ ነግሬአቸዋለሁ፤ አንተ ክርስቲያን እንዳልሆንህ፥ እኔም እንደማልሆን፥ አንተም ወደ ሲኦል ብትሄድ ከአንተ ጋር እንደምሄድ ነግሬአቸዋለሁ።» እርሱም «እንግዲህ፥ እኔ ወደ ሲኦል የመሄድ ሐሳብ የለኝም። ዛሬ ማታ ወደ ፊት ወጥቼ ልቤን ለክርስቶስ ለመስጠት ቁርጥ ውሳኔ አድርጌአለሁ» አለ። እርሷም «እንግዲያውስ እኔ ወደ ስብሰባው አልሄድም፤ ያን ማየት አልፈልግም። ከዚህ ሁሉ በኋላ ክርስቲያን ለመሆን ከፈለግህ ትችላለህ፤ እኔ ግን አልሆንም» አለች። ጊዜው በደረሰ ጊዜ እርሱ ብቻውን ወደ ስብሰባው ሄደ። መስበኪያ መድረኩ በቤተ ክርስቲያኑ ፊት ለፊት፥ በሁለቱ በሮች መካከል ነበር። ቤቱ እጅግ ተጨናንቆ ነበር፤ እርሱ ግን በመጨረሻ በቤተ ክርስቲያኑ እጅግ የኋለኛ ክፍል፥ ከመተላለፊያዎቹ በአንዱ አጠገብ መቀመጫ አገኘ። በስብሰባው መጨረሻ፥ በሌላ ጊዜ እንዳደረግሁት፥ የተጨነቁና ውሳኔ ያደረጉ ሰዎች ወደ ፊት መጥተው የተወሰኑ መቀመጫዎችን እንዲይዙና በመስበኪያ መድረኩ ዙሪያ ያለውን የተወሰነ ስፍራ እንዲይዙ፥ በዚያም በጸሎት ለእግዚአብሔር አደራ እንድንሰጣቸው ጠራሁ። ሚስቱ ራሷ ወደ ስብሰባው መጥታ በሌላው መተላለፊያ ገብታ፥ በቤቱ ጽንፍ ክፍል ከእርሱ ትይዩ በሚባል ስፍራ እንደ ተቀመጠች በኋላ ታወቀ። ጥሪውን ባቀረብሁ ጊዜ እርሱ ወዲያውኑ ተነሣ። እርሷ ትከታተል ነበር፤ እርሱ ቆሞ በተጨናነቀው መተላለፊያ ሲያልፍ እንዳየችው እርሷም በሌላው መተላለፊያ ወረደች፤ በመስበኪያ መድረኩ ፊትም ተገናኙ፥ የጸሎት ተቀባዮች ሆነውም አብረው ተንበረከኩ።

ብዙ ሰዎች በዚያው ስፍራ ተስፋ አገኙ፤ ይህ ባልና ሚስት ግን አላገኙም። ስላደረጉት ነገር እርስ በርሳቸው ብዙ ለመነጋገር እጅግ ኮርተው ወደ ቤታቸው ሄዱ፤ እጅግ የተረበሸ ሌሊትም አሳለፉ። በማግሥቱ ረፋድ በአራት ሰዓት ገደማ እርሱ ሊያየኝ መጣ፤ ወደ ክፍሌም እንዲገባ ተደረገ። ሚስቴ በሁለተኛው ፎቅ የፊት ለፊቱን ክፍል ይዛ ነበር፤ እኔም በዚያው ፎቅ የኋለኛውን ክፍል ይዤ ነበር። ከእርሱ ጋር እየተነጋገርሁ ሳለሁ፥ አንዲት ሴት ልታየኝ በወይዘሮ ፊኒ ክፍል እየጠበቀች እንደ ሆነ አገልጋዩ ነገረኝ። ለጥቂት ደቂቃዎች ይቅርታ ጠይቄ፥ እርሷን ለማየት ስሄድ እንዲጠብቀኝ ለመንሁት። ሄጄ ሳያት፥ ልክ በትላንትናው ዕለት እንዲያ እልከኛ የነበረችው ሴት፥ በዚያን ጊዜ በክፍሌ የነበረው ሰው ሚስት ሆና አገኘኋት። አንዳቸውም ሌላው ሊያየኝ እንደ መጣ አያውቁም ነበር። አነጋገርኋት፤ ለክርስቶስ ለመገዛት አፋፍ ላይ እንዳለችም ተረዳሁ። እርሱም በመልክ ሁሉ በዚያው ሁኔታ ላይ እንዳለ ተገንዝቤ ነበር። ከዚያም ወደ እርሱ ተመልሼ «በወይዘሮ ፊኒ ክፍል ከአንዲት ሴት ጋር ልጸልይ ነው፤ ፈቃድህ ከሆነ ወደዚያ እንሄድና ሁላችንም በአንድነት በጸሎት እንተባበራለን» አልሁት። ተከተለኝ፥ የገዛ ሚስቱንም አገኘ። በመገረም እርስ በርሳቸው ተያዩ፤ ነገር ግን እያንዳንዳቸው ሌላውን በዚያ በማግኘታቸው ሁለቱም እጅግ ተነኩ። ለመጸለይ ተንበረከክን። በጸሎቴ ብዙም ሳልገፋ እርሷ ማልቀስና ስለ ባልዋ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ መጸለይ ጀመረች። ቆም ብዬ አዳመጥሁ፤ ስለ ራሷ የነበራትን ጭንቀት ሁሉ ትታ ስለ እርሱ መለወጥ በጸሎት ጭንቅ እየታገለች እንደ ነበረች ተረዳሁ። የእርሱ ልብ የተሰበረና እጅ የሰጠ መሰለ፤ ልክ በዚህ ጊዜ የምሳ ደወል ተደወለ። ብቻቸውን አብረው ብተዋቸው መልካም እንደሚሆን አሰብሁ። ስለዚህ ሚስቴን ነካ አደረግኋት፤ በጸጥታም ተነሥተን በጸሎት ላይ እንዳሉ ትተናቸው ለምሳ ወረድን። በችኮላ ምሳ በልተን ስንመለስ፥ ሊመኙት በሚቻለው መጠን ልባቸው የለሰለሰ፥ ትሑታንና አፍቃሪዎች ሆነው አገኘናቸው።

በዚህ መነቃቃት ውስጥ ሰፍኖ ስለ ነበረው የጸሎት መንፈስ እስካሁን ብዙ አልተናገርሁም፤ ይህን ግን ሳልጠቅስ ማለፍ የለብኝም። ወደ ሮቼስተር በመጓዝ ላይ ሳለሁ፥ ከሮቼስተር በስተ ምሥራቅ ሠላሳ ማይል ገደማ ርቃ በምትገኝ አንዲት መንደር ስናልፍ፥ የማውቀው አንድ ወንድም አገልጋይ በቦዩ ጀልባ ላይ አይቶኝ፥ ጥቂት ርቀት ብቻ አብሮ ተጉዞ ለመመለስ አስቦ ከእኔ ጋር ጥቂት ለመነጋገር ዘሎ ጀልባዋ ላይ ወጣ። ነገር ግን በጨዋታው ተመሰጠ፤ ወዴት እንደምሄድም ባወቀ ጊዜ መንገዱን ቀጥሎ ከእኔ ጋር ወደ ሮቼስተር ለመሄድ ወሰነ። በዚያ ጥቂት ቀናት ብቻ እንደ ቆየን ይህ አገልጋይ በኃጢአት ወቀሳ እጅግ ከመያዙ የተነሣ፥ አንድ ጊዜ በመንገድ ሲያልፍ ጮኾ ከማልቀስ ራሱን መግታት አቃተው። ጌታ ብርቱ የጸሎት መንፈስ ሰጠው፤ ልቡም ተሰበረ። እርሱና እኔ አብረን ብዙ ስንጸልይ፥ ጌታ በዚያ ሊያደርገው ስላለው ነገር የነበረው እምነት አስደነቀኝ። «ጌታ ሆይ፥ እንዴት እንደ ሆነ አላውቅም፤ ነገር ግን በዚህች ከተማ ታላቅ ሥራ ልትሠራ እንዳለህ የማውቅ ይመስለኛል» ይል እንደ ነበር አስታውሳለሁ። የጸሎት መንፈስ በብርቱ ፈሰሰ፤ እስከዚህም ድረስ አንዳንድ ሰዎች በስብከት ጊዜ ስሜታቸውን መግታት ስለማይችሉ ለመጸለይ ብለው ከሕዝባዊ አገልግሎቶች ይቀሩ ነበር።

እዚህ ላይ በተደጋጋሚ የምጠቅሰውን የአንድ ሰው ስም፥ የአቶ ኤቤል ክለሪን ስም ማስተዋወቅ አለብኝ። እርሱ የአንድ እጅግ መልካም ሰው ልጅ ነበር፤ እርሳቸውም እኔ በተለወጥሁባት ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ነበሩ። እርሱ እኔ በተለወጥሁበት በዚያው መነቃቃት ተለወጠ። ለመስበክ ፈቃድ ተሰጥቶት ነበር፤ ነገር ግን የጸሎት መንፈሱ እንዲህ ያለ ስለ ነበረ፥ ስለ ሰዎች ነፍሳትም እጅግ ሸክም ስለ ነበረበት፥ ጊዜውና ኃይሉ ሁሉ ለጸሎት ተሰጥቶ ብዙ መስበክ አልቻለም። የነፍሱ ሸክም ብዙ ጊዜ እጅግ ታላቅ ከመሆኑ የተነሣ መቆም ያቅተዋል፤ በጭንቅም ይንፈራፈርና ያቃስት ነበር። በሚገባ አውቀው ነበር፤ በእርሱም ላይ ስለ ነበረው አስደናቂ የጸሎት መንፈስ ጥቂት አውቅ ነበር።

ያን ብርቱ የጸሎት መንፈስ ያላቸው ሁሉ ማለት ይቻላል እንደሚሆኑት፥ እርሱም እጅግ ዝምተኛ ሰው ነበር።

በሮቼስተር መኖሩን መጀመሪያ ያወቅሁት፥ ከከተማዪቱ በስተ ምዕራብ አንድ ማይል ገደማ ርቀው የሚኖሩ አንድ ሰው አንድ ቀን ሊያዩኝ መጥተው፥ አቶ ኤቤል ክለሪ የተባለ አገልጋይ አውቅ እንደ ሆነ በጠየቁኝ ጊዜ ነው። በሚገባ እንደማውቀው ነገርኋቸው። እርሳቸውም «እንግዲያውስ እርሱ በቤቴ አለ፤ ለተወሰነ ጊዜም በዚያ ቆይቷል፤ ስለ እርሱ ምን እንደማስብ አላውቅም» አሉ። እኔም «በአንዳቸውም ስብሰባዎቻችን ላይ አላየሁትም» አልሁ። እርሳቸውም «አይ፥ አላዩትም፤ እርሱ ራሱ እንደሚለው ወደ ስብሰባ መሄድ አይችልም። ቀንና ሌሊት ሁልጊዜ ማለት ይቻላል ይጸልያል፤ ደግሞም ምን እንደማደርገው እስከማላውቅ ድረስ በእንዲህ ያለ የአእምሮ ጭንቅ ውስጥ ሆኖ ነው። አንዳንድ ጊዜ በጉልበቱ እንኳ መቆም አይችልም፤ ይልቁንም በመሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ እኔን እጅግ በሚያስገርመኝ ሁኔታ ያቃስታል፥ ይጸልያልም» ብለው መለሱ። ወንድሙንም «ይገባኛል፤ እባክዎ ዝም ይበሉ። ሁሉም በመልካም ይፈጸማል፤ እርሱ በእርግጥ ያሸንፋል» አልኋቸው።

በዚያን ጊዜ በዚሁ መንገድ የተያዙ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ሰዎችን አውቅ ነበር። በኦናይዳ ካውንቲ የካምደኑ ዲያቆን ፒ——፥ በጀፈርሰን ካውንቲ የሮድማኑ ዲያቆን ቲ——፥ በዚያው ካውንቲ የአዳምሱ ዲያቆን ቢ——፥ ይህ አቶ ክለሪና ከወንዶቹ መካከል ሌሎች ብዙዎች፥ ደግሞም ብዙ ሴቶች የዚያው መንፈስ ተካፋዮች ነበሩ፤ ከጊዜያቸውም ታላቁን ክፍል በጸሎት ያሳልፉ ነበር። አባ ናሽ ብለን የምንጠራቸው፥ በብዙ የአገልግሎት መስኮቼ ወደ እኔ መጥተው የረዱኝ ሰው፥ እንዲህ ያለ ብርቱ የሚያሸንፍ የጸሎት መንፈስ ከነበራቸው ሰዎች አንዱ ነበሩ። ይህ አቶ ክለሪ እኔ እስከ ቆየሁበት ጊዜ ድረስ በሮቼስተር ቆየ፤ እኔ ከሄድሁም በኋላ እንጂ ከዚያ አልወጣም። እኔ ማወቅ እስከ ቻልሁት ድረስ በሕዝብ ፊት ፈጽሞ አልታየም፤ ራሱን ሙሉ በሙሉ ለጸሎት ሰጠ እንጂ።

የነገሮች የሥነ ምግባር ገጽታ በዚህ መነቃቃት እጅግ እንደ ተለወጠ ተናግሬአለሁ። ከተማዪቱ በብልጽግናና በትጋት የተሞላች፥ በኃጢአትም የተሞላች ወጣት ከተማ ነበረች። ነዋሪዎቿ በከፍተኛ ደረጃ አስተዋዮችና ትጉሃን ነበሩ፤ ነገር ግን መነቃቃቱ ከተማዪቱን አዳርሶ ከወንዶችም ከሴቶችም ተሰሚነት ያላቸውን ሰዎች አብዛኞቹን ሲለውጥ፥ በከተማዪቱ ሥርዓት፥ ጨዋነትና ሥነ ምግባር ላይ የመጣው ለውጥ አስደናቂ ነበር።

በኋላ፥ በስፍራው በምጠቅሰው ጊዜ፥ በዚህ በምናገርለት መነቃቃት ከተለወጠና ብዙም ሳይቆይ የከተማዪቱ የአውራጃ ዐቃቤ ሕግ ሆኖ ከተሾመ አንድ ጠበቃ ጋር እየተነጋገርሁ ነበር። ሥራው ወንጀለኞችን የመክሰስን ሂደት መቆጣጠር ነበር። ከሥልጣኑ የተነሣ በዚያች ከተማ የወንጀልን ታሪክ በሚገባ አውቆ ነበር። ስለ ተለወጠበት መነቃቃት ሲናገር፥ ከብዙ ዓመታት በኋላ እንዲህ አለኝ፦ «የወንጀል ፍርድ ቤቶችን መዛግብት ስመረምር ቆይቻለሁ፤ ይህንንም አስገራሚ እውነታ አገኘሁ፦ ከተማችን ከዚያ መነቃቃት ወዲህ በሦስት እጥፍ ብታድግም፥ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ከነበረው የወንጀል ክስ አንድ ሦስተኛው እንኳ የለም። ይህ» አለ፥ «ያ መነቃቃት በማኅበረሰቡ ላይ ያሳደረው አስደናቂ ተጽዕኖ ነው።» በእርግጥም በዚያ መነቃቃት ኃይል የሕዝብ አስተያየት ተቀርጿል። የከተማዪቱ ሕዝባዊ ጉዳዮች በብዙ መጠን በክርስቲያን ሰዎች እጅ ቆይተዋል፤ በማኅበረሰቡም ውስጥ የሚገዙት ተጽዕኖዎች በክርስቶስ ወገን ሆነዋል።

ከሌሎች መለወጦች መካከል፥ በዚያ ስፍራ ታዋቂ ዜጋና መጻሕፍት ሻጭ የነበሩትን የአቶ ፒ——ን መለወጥ መጥቀስ መርሳት የለብኝም። አቶ ፒ—— ከሐዲ ነበሩ፤ አምላክ የለም ባይ ሳይሆኑ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ ሥልጣን የማያምኑ ነበሩ። አንባቢና አሳቢ፥ የሰላ ብልህ አእምሮ፥ ጠንካራ ፈቃድና እጅግ ቆራጥ ጠባይ የነበራቸው ሰው ነበሩ። እንደማምነው በውጫዊ ሥነ ምግባር መልካም የሆኑ፥ እጅግም የተከበሩ ጨዋ ሰው ነበሩ። አንድ ቀን ማለዳ ወደ ክፍሌ መጥተው «አቶ ፊኒ፥ እዚህ በሃይማኖት ጉዳይ ታላቅ እንቅስቃሴ አለ፤ እኔ ግን ተጠራጣሪ ነኝ፤ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት መሆኑን እንዲያረጋግጡልኝ እፈልጋለሁ» አሉኝ። ጌታ ከእርሳቸው ጋር የምከተለውን መንገድ ለመወሰን እስኪያስችለኝ ድረስ የአእምሮአቸውን ሁኔታ ወዲያውኑ እንድለይ አስቻለኝ። እኔም «በእግዚአብሔር መኖር ያምናሉን?» አልኋቸው። «አዎን!» አሉ፤ «እኔ አምላክ የለም ባይ አይደለሁም።» «እንግዲያውስ እግዚአብሔርን ሊይዙት በሚገባ መንገድ እንደ ያዙት ያምናሉን? ሥልጣኑን አክብረዋልን?

ወደዱትን? ደስ ያሰኘዋል ብለው ያሰቡትን፥ ደስ ለማሰኘትም አስበው አድርገዋልን? ባለዎት በተሻለው ብርሃን መሠረት ሊወዱት፥ ሊያመልኩትና ሊታዘዙት እንደሚገባዎ አይቀበሉምን?» «አዎን!» አሉ፤ «ይህን ሁሉ እቀበላለሁ።» «ታዲያ እንዲህ አድርገዋልን?» ብዬ ጠየቅሁ። «እንግዲህ፥ አላደረግሁም፤ አድርጌአለሁ ማለት አልችልም» ብለው መለሱ። እኔም «እንግዲያውስ ግዴታዎን ካልተወጡና ቀድሞ ያለዎትን ብርሃን ካልታዘዙ፥ ለምን ተጨማሪ መረጃና ተጨማሪ ብርሃን እሰጥዎታለሁ? አሁን» አልኋቸው፥ «እንደ ኅሊናዎ ወቀሳ ለመኖር፥ ባለዎት በተሻለው ብርሃን መሠረት እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ ሲያደርጉ፥ እስካሁን ቸል ስላሉት ንስሐ ለመግባትና በቀረው ዕድሜዎ በሚያውቁት በተሻለው መንገድ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ሲወስኑ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር መሆኑን ላሳይዎ እሞክራለሁ። እስከዚያ ድረስ ግን እንዲህ ያለ ነገር ማድረጌ ምንም ጥቅም የለውም።» እኔ አልተቀመጥሁም፤ እርሳቸውንም እንዲቀመጡ ያልጋበዝኋቸው ይመስለኛል። እርሳቸውም «ይህ ፍትሐዊ ሳይሆን አይቀርም» ብለው ሄዱ።

እስከ ማግሥቱ ጠዋት ድረስ ስለ እርሳቸው ምንም አልሰማሁም። ከተነሣሁ ብዙም ሳይቆይ እንደገና ወደ ክፍሌ መጡ፤ እንደ ገቡም እጃቸውን እያጨበጨቡ «አቶ ፊኒ፥ እግዚአብሔር ተአምር አደረገ!» አሉ። ቀጥለውም «ከክፍልዎ ከወጣሁ በኋላ የነገሩኝን እያሰብሁ ወደ ሱቁ ወረድሁ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ባለኝ ግንኙነት ስሕተት መሆኑን ከማውቀው ነገር ንስሐ ለመግባትና ከዚህ በኋላ ባለኝ በተሻለው ብርሃን መሠረት ለመኖር ወሰንሁ። ይህንንም በወሰንሁ ጊዜ» አሉ፥ «ስሜቴ እጅግ አሸንፎኝ ወደቅሁ፤ በሱቁ ውስጥ ከእኔ ጋር የነበሩት አቶ —— ባይኖሩ ኖሮ ሞቼ ሊሆን ይችል ነበር።» ከዚያ ጊዜ ጀምሮ፥ የሚያውቋቸው ሁሉ እንደሚያውቁት፥ የሚጸልዩ ትጉ ክርስቲያን ሆነዋል። ለብዙ ዓመታት ከኦበርሊን ኮሌጅ ባለ አደራዎች አንዱ ሆነው፥ በፈተናዎቻችን ሁሉ ከጎናችን ቆመዋል፤ በገንዘባቸውና በሙሉ ተጽዕኖአቸውም ረድተውናል።

በዚህ ታላቅ መነቃቃት ወቅት ሰዎች ከሮቼስተር በሌላ ስፍራ ላሉ ወዳጆቻቸው ስለ ሥራው የሚተርኩ ደብዳቤዎችን ጻፉ፤ እነዚህም በብዙ ግዛቶች በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ተነበቡ፥ ታላላቅ የሃይማኖት መነቃቃቶችን ለማስገኘትም መሣሪያ ሆኑ። ብዙ ሰዎች ታላቁን የእግዚአብሔር ሥራ ለማየት ከሌላ ስፍራ መጥተው ተለወጡ። አንድ ሐኪም ስለ ሥራው በሰማው ነገር እጅግ ተስቦ፥ ጌታ የሚያደርገውን ለማየት ከኒው ጀርሲ ግዛት ከኒውአርክ ወደ ሮቼስተር እንደ መጣና ራሱም በዚያ እንደ ተለወጠ አስታውሳለሁ። ተሰጥኦና ከፍተኛ ትምህርት የነበረው ሰው ነበር፤ ለዓመታትም ለማይሞቱ ነፍሳት የሚተጋ ቀናተኛ ክርስቲያን ሠራተኛ ሆኖ ቆይቷል።

አንድ ምሽት፥ የተጨነቁት ወደ ፊት መጥተው እንዲገዙ ጥሪ ባቀረብሁ ጊዜ፥ በአጎራባች ከተማ የሚኖር አንድ ተሰሚነት ያለው ሰው ራሱና ከቤተሰቡ አባላት በርካቶቹ ወደ ፊት መጥተው ራሳቸውን ለእግዚአብሔር እንደ ሰጡ አስታውሳለሁ። በእርግጥም ሥራው እንደ ማዕበል በየአቅጣጫው ተሰራጨ። ዋናው ድካሜ በሮቼስተር ሆኖ ሳለ፥ ጊዜዬና ኃይሌ በፈቀደልኝ መጠን በዙሪያው ባሉ ብዙ ስፍራዎች ሰበክሁ። ወደ ካናንዴጓ ሄጄ ብዙ ጊዜ ሰበክሁ። በዚያም ቃሉ ሠራ፤ ብዙዎችም ተለወጡ። እረኛው ቄስ አንሰል ኤዲ በሙሉ ልብ ወደ ሥራው ገቡ። በትውልድ እንግሊዛዊ የሆኑ አንድ አረጋዊ የቀድሞ እረኛም ሥራውን ወደ ፊት ለማራመድ የቻሉትን አደረጉ። በሄድሁበት ሁሉ የእግዚአብሔር ቃል ወዲያውኑ ሠራ፤ የሰዎችን መለወጥ ለማስገኘት በሚያስችል ግንኙነትና መጠን የእግዚአብሔርን ሕግና ክርስቶስ በሰዎች ላይ ያለውን መብት ማቅረብ ብቻ የሚያስፈልግ ይመስል ነበር፤ ሰዎችም በብዙ ቍጥር ይለወጡ ነበር።

በዚያን ጊዜ በሮቼስተር የነበረው ሥራ ታላቅነት በመላው የኒው ዮርክ ግዛት፥ በመላው ኒው ኢንግላንድና በብዙ የዩናይትድ ስቴትስ ክፍሎች የሚገኙ አገልጋዮችንና ክርስቲያኖችን ትኩረት እጅግ ከመሳቡ የተነሣ፥ የዝናው ብዛት ራሱ፥ ይህች አገር እስከዚያ ጊዜ ድረስ አይታው የማታውቀውን ታላቁን የሃይማኖት መነቃቃት በምድሪቱ ሁሉ ለማስፋፋት በእግዚአብሔር መንፈስ እጅ ውጤታማ መሣሪያ ሆነ። ከዚህ ከዓመታት በኋላ ስለዚህ ብርቱ መነቃቃትና ስለ ውጤቶቹ ከዶ/ር ቢቸር ጋር ስነጋገር እንዲህ አሉ፦ «ያ በዚህ ያህል አጭር ጊዜ ዓለም አይቶት የማያውቀው ታላቁ የእግዚአብሔር ሥራና ታላቁ የሃይማኖት መነቃቃት ነበር። ከዚያ ታላቅ መነቃቃት የተነሣ» አሉ፥ «አንድ መቶ ሺህ ሰዎች ከአብያተ ክርስቲያናት ጋር እንደ ተቀላቀሉ ተዘግቧል። ይህ» አሉ፥ «በቤተ ክርስቲያን ታሪክና በሃይማኖት እድገት ታሪክ አቻ የሌለው ነው።» ይህ በአንድ ዓመት ውስጥ እንደ ተደረገ ተናገሩ፤ በክርስትና ዘመን ውስጥ በየትኛውም ዓመት እንዲህ ያለ ታላቅ የሃይማኖት መነቃቃት የሚገልጽ ዘገባ እንደሌለንም አሉ።

ቀደም ብዬ ከጠቀስሁት ከኒው ሌባኖን ጉባኤ ጊዜ ጀምሮ፥ በሃይማኖት መነቃቃቶች ላይ የነበረው ግልጽና ሕዝባዊ ተቃውሞ እየቀነሰ ሄደ፤ በተለይም ቀደም ሲል ከገጠመኝ እጅግ ያነሰ የግል ተቃውሞ ገጠመኝ። ተቃውሞው ቀስ በቀስ ነገር ግን በእጅጉ በረደ። በሮቼስተር ምንም አልተሰማኝም። በእርግጥም የመዳን ውኃዎች እጅግ ከፍ ብለው ነበር፤ መነቃቃቶች እጅግ ብርቱና ሰፊ ሆነው ነበር፤ ሰዎችም መነቃቃቶቹንና ውጤቶቻቸውን በበቂ መጠን ለማወቅ ጊዜ አግኝተው ስለ ነበር፥ ሰዎች ቀድሞ ያደርጉት እንደ ነበረው እነርሱን ለመቃወም ፈሩ። አገልጋዮች ይበልጥ ተረድተዋቸው ነበር፤ እጅግ እግዚአብሔርን የማይፈሩ ኃጢአተኞችም እነርሱ በእርግጥ የእግዚአብሔር ሥራ መሆናቸውን አምነው ነበር። የመለወጦቹ አብዛኞቹ በግልጥ ጤናማ ስለ ነበሩ፥ የተለወጡትም በእውነት ዳግመኛ የተወለዱና አዲስ ፍጥረት የሆኑ ስለ ነበሩ፥ ግለሰቦችና መላ ማኅበረሰቦች በሚገባ ስለ ታደሱ፥ ውጤቶቹም ዘላቂና የማያጠራጥሩ ስለ ነበሩ፥ እነርሱ የእግዚአብሔር ሥራ ናቸው የሚለው እምነት ሁሉን አቀፍ ለማለት የሚያስደፍር ሆነ።

ቀዳሚ ቀጣይ