ምዕራፍ 15 · 11 ደቂቃ ንባብ · 14 ደቂቃ ማዳመጥ
በ1826 በኦበርን የሆነው መነቃቃት
በኦበርን የመጀመሪያው የፕሪስባይቴሪያን ቤተ ክርስቲያን እረኛ የነበሩት ዶ/ር ላንሲንግ በዚያ የነበረውን መነቃቃት ለማየት ወደ ዩቲካ መጡ፤ እኔም ወደዚያ ወጥቼ ለጥቂት ጊዜ ከእርሳቸው ጋር እንድሠራ አጥብቀው ለመኑኝ። በ1826 የበጋ ወራት ልመናቸውን ተቀብዬ ወደዚያ ሄድሁና ለተወሰነ ጊዜ ከእርሳቸው ጋር ሠራሁ። ወደ ኦበርን ከሄድሁ ብዙም ሳይቆይ፥ በዚያ ስፍራ በሚገኘው የሥነ መለኮት ትምህርት ቤት ውስጥ ያሉ አንዳንድ መምህራን በመነቃቃቱ ላይ የጠላትነት አቋም እየያዙ መሆናቸውን ተገነዘብሁ። ከዩቲካ በስተ ምሥራቅ የሚገኙ አገልጋዮች፥ ቍጥራቸውም ጥቂት ያልሆኑት፥ እነዚህን መነቃቃቶች በሚመለከት እርስ በርሳቸው ደብዳቤ እየተጻጻፉ በእነርሱ ላይ የጠላትነት አቋም እየያዙ እንደ ነበር ቀደም ብዬ አውቄ ነበር።
ይሁን እንጂ ኦበርን እስክደርስ ድረስ ከአገልጋዮች ዘንድ ሊገጥመኝ የተዘጋጀልኝ ተቃውሞ ምን ያህል ብዛት እንዳለው ሙሉ በሙሉ አላወቅሁም ነበር፤ ተቃውሞውም የመጣው በሠራሁበት አካባቢ ካሉ አገልጋዮች አልነበረም፤ ነገር ግን ካልሠራሁባቸው ስፍራዎች፥ እኔን በግል ምንም ከማያውቁኝ፥ ይልቁንም በሰሙት የሐሰት ወሬ ከተነዱ አገልጋዮች ነበር። ኦበርን ከደረስሁ ብዙም ሳይቆይ ግን፥ አገልጋዮችና አብያተ ክርስቲያናት በሰፊው ተባብረው በዙሪያዬ አጥር እንዲያበጁብኝና ከአገልግሎቴ ጋር የተያያዙት መነቃቃቶች እንዳይስፋፉ እንዲከለክሉ የሚያደርስ፥ ደግሞም ለዚያው የታለመ የስለላ ሥርዓት እየተካሄደ መሆኑን ከልዩ ልዩ ምንጮች ተረዳሁ።
በዚህ ጊዜ አካባቢ አቶ ኔትልተን ከዚህ ወዲያ ወደ ምሥራቅ ልዘልቅ እንደማልችል፥ በተለይም የኒው ኢንግላንድ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በእኔ ላይ እንደ ተዘጉ እንደ ተናገሩ ተነገረኝ። አቶ ኔትልተን መጥተው በአልባኒ ጸንተው ቆሙ፤ ደግሞም ከዶ/ር ቢቸር የተጻፈ አንድ ደብዳቤ በእጄ ገባ፤ በዚያም አቶ ኔትልተንን በእኔና በማዕከላዊ ኒው ዮርክ በነበሩት መነቃቃቶች ላይ በወንድነት ጸንተው እንዲቆሙ መከሯቸው፤ እርሳቸው እንደ ጠሯቸውም የኒው ኢንግላንድ «የፍርድ ጉባኤዎች» በተሰበሰቡ ጊዜ ሁሉም በግልጽ እንደሚናገሩና በተቃውሟቸው እንደሚደግፏቸው ቃል ገቡላቸው።
ለአሁን ግን በኦበርን ወደ ሆነው ነገር መመለስ አለብኝ። ወደዚያ ከሄድሁ ብዙም ሳይቆይ፥ ቀደም ብዬ የተናገርሁለት የስለላ ሥርዓት በሰፊው እየሠራ መሆኑ አእምሮዬን እጅግ ያዘው። የዋይትስቦሮው አቶ ፍሮስት ስለ ሁኔታው በከፍተኛ መጠን አውቀው ነበርና ነገሩኝ። እኔ ግን ስለ ጉዳዩ በአደባባይ፥ እንደማስታውሰውም በግል ለማንም ምንም አልተናገርሁም፤ ራሴን ለጸሎት ሰጠሁ እንጂ። እንዲመራኝ ከቀን ወደ ቀን በታላቅ ትጋት ወደ እግዚአብሔር ተመለከትሁ፤ የሥራዬን መንገድ እንዲያሳየኝና ማዕበሉን በሰላም አልፌ እንድወጣ ጸጋ እንዲሰጠኝ ለመንሁት።
አንድ ቀን በዶ/ር ላንሲንግ ቤት በክፍሌ ውስጥ ያለፍሁበትን ሁኔታ ፈጽሞ አልረሳውም። ጌታ ከፊቴ ያለውን ነገር በራእይ እንደሚመስል አሳየኝ። በጸሎት ተጠምጄ ሳለሁ እጅግ ወደ እኔ ቀረበና ሥጋዬ በእውነት በአጥንቶቼ ላይ ተንቀጠቀጠ። የእግዚአብሔርን መገኘት በሙላት ተሰምቶኝ ከራሴ እስከ እግሬ ተንቀጠቀጥሁ። በመጀመሪያም ሆነ ለተወሰነ ጊዜ፥ በክርስቶስ መስቀል ፊት ከመሆን ይልቅ፥ ነጐድጓዱ ሁሉ በሚያስገመግምበት በሲና ተራራ ጫፍ ላይ የመሆን ያህል መሰለኝ።
እንደማስታውሰው በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንደዚያን ጊዜ ፍርሃትና ትሕትና ተሞልቼ አላውቅም። ይሁን እንጂ የመሸሽ ስሜት ከማድረብ ይልቅ ወደ እግዚአብሔር ይበልጥ እየቀረብሁ የምሳብ መሰለኝ፤ ሊነገር በማይቻል ፍርሃትና መንቀጥቀጥ ወደ ሞላኝ ወደዚያ መገኘት ይበልጥ እየተጠጋሁ የምሄድ መሰለኝ። በፊቱ ታላቅ ውርደትና ራስን ዝቅ የማድረግ ጊዜ ካለፈ በኋላ፥ ታላቅ ከፍ መደረግ መጣ። እግዚአብሔር ከእኔ ጋር እንደሚሆንና እንደሚደግፈኝ፥ ምንም ተቃውሞ እንደማያሸንፈኝ፥ በዚህ ጉዳይ ሁሉ ሥራዬን ከመሥራትና የእግዚአብሔርን ማዳን ከመጠበቅ በቀር ሌላ የማደርገው ነገር እንደሌለ አረጋገጠልኝ።
የእግዚአብሔርን መገኘት ስሜትና በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔርና በነፍሴ መካከል ያለፈውን ነገር ሁሉ ፈጽሞ ልገልጸው አልችልም። ፍጹም እንድታመን፥ ፍጹም እንድረጋጋ፥ ተሳስተው በእኔ ላይ ለተሰለፉት ወንድሞች ሁሉ ከፍጹም ደግነት በቀር ሌላ ስሜት እንዳይኖረኝ አደረገኝ። ሁሉ ነገር መልካም ሆኖ እንደሚፈጸም፥ ትክክለኛው መንገዴም ሁሉን ለእግዚአብሔር ትቼ ሥራዬን መሥራት እንደ ሆነ ተረጋገጠልኝ፤ ማዕበሉ እየተሰበሰበና ተቃውሞው እየጨመረ በሄደ ጊዜም ፍጻሜው ምን እንደሚሆን ለአንድ አፍታ እንኳ አልተጠራጠርሁም። ፈጽሞ አልታወክሁበትም፤ ስለ እርሱ በማሰብ ነቅቼ አንድ ሰዓት እንኳ አላሳለፍሁም፤ ይህም በውጭ ለሚታየው ሁሉ፥ ከሠራሁባቸው ስፍራዎች በቀር የአገሪቱ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ከመድረኮቻቸው ሊያወጡኝ የሚተባበሩ በሚመስልበት ጊዜ ነበር። እኔ እንደ ተረዳሁት፥ ተቃውሞውን የመሩት ሰዎች በግልጽ የወሰኑትም ይህንኑ ነበር። እጅግ ከመታለላቸው የተነሣ ከመተባበርና እነርሱ እንደ ተናገሩት «እርሱን ከማስቆም» በቀር ውጤታማ መንገድ እንደሌለ አሰቡ። እግዚአብሔር ግን ሊያስቆሙኝ እንደማይችሉ አረጋገጠልኝ።
በኤርምያስ ሃያኛው ምዕራፍ ያለ አንድ ክፍል በታላቅ ኃይል ደጋግሞ በልቤ ታተመ። እንዲህ ይላል፦ «አቤቱ፥ አታለልኸኝ፥ እኔም ተታለልሁ።» በዳር ማስታወሻው ላይ «አባበልኸኝ» ይላል። «ከእኔ ይልቅ በርትተሃል፥ አሸንፈኸኛልም። ቀኑን ሁሉ መሳለቂያ ሆንሁ፥ ሁሉም ያፌዝብኛል። በተናገርሁ ጊዜ ሁሉ እጮኻለሁና፥ ግፍና ቅሚያ ብዬ እጮኻለሁ፤ የእግዚአብሔር ቃል ቀኑን ሁሉ ስድብና መሳለቂያ ሆኖብኛልና። እኔም፦ አላነሣውም፥ ደግሞም በስሙ ከእንግዲህ አልናገርም አልሁ። ቃሉ ግን በአጥንቶቼ ውስጥ እንደ ተዘጋ እንደሚነድድ እሳት በልቤ ውስጥ ሆነ፤ መታገሥም ደከመኝ፥ ልችልም አልቻልሁም። የብዙዎችን ሐሜት ሰምቻለሁና፥ በዙሪያዬም ሽብር አለ። ‹ተናገሩ፥ እኛም እንናገርበታለን› ይላሉ። ወዳጆቼ ሁሉ መሰናከሌን ይጠባበቃሉ፦ ‹ምናልባት ይታለል ይሆናል፥ እኛም እናሸንፈዋለን፥ በእርሱም ላይ በቀላችንን እንወስዳለን› ይላሉ። እግዚአብሔር ግን እንደ ኃያልና እንደ አስፈሪ ከእኔ ጋር ነው፤ ስለዚህ አሳዳጆቼ ይሰናከላሉ፥ አያሸንፉምም። አይከናወንላቸውምና እጅግ ያፍራሉ፤ የዘላለም እፍረታቸውም ከቶ አይረሳም። ነገር ግን ጻድቁን የምትፈትን፥ ኵላሊትንና ልብን የምታይ የሠራዊት ጌታ አቤቱ፥ ክርክሬን ለአንተ ገልጬአለሁና በእነርሱ ላይ የምትበቀለውን በቀል ልይ።» (ኤርምያስ 20:7-12)።
ይህ ክፍል የእኔን ሁኔታ ቃል በቃል ይገልጻል ወይም ስሜቴን ይናገራል ማለቴ አይደለም፤ ነገር ግን በሁኔታው ብዙ መመሳሰል ስለ ነበረ ይህ ክፍል ብዙ ጊዜ ለነፍሴ ድጋፍ ሆነልኝ። ጌታ ተቃውሞውን በልቤ እንዳኖረው አልፈቀደልኝም፤ ደግሞም እስከማስታውሰው ድረስ፥ ተቃውሟቸው በቆየበት ዘመን ሁሉ በአቶ ኔትልተንም ሆነ በዶ/ር ቢቸር፥ ወይም በሥራው ላይ በተነሣ በማናቸውም ዋና ተቃዋሚ ላይ ክፉ ስሜት ኖሮኝ እንደማያውቅ በእውነት መናገር እችላለሁ።
ቀደም ብዬ በጠቀስሁት በዊልያም አር. ዊክስ የታተመውን በራሪ ጽሑፍና የወሰዱትን አካሄድ በሚመለከት ልዩ የሆነ የመሸበር ስሜት እንደ ነበረኝ አስታውሳለሁ። የአቶ ዊክስን ታሪክ የሚያውቁ ሰዎች፥ ከዚህ ብዙም ሳይቆይ «የመንገደኛው ጉዞ በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን» ብለው የጠሩትን መጽሐፍ መጻፍ እንደ ጀመሩ ያስታውሳሉ። ይህም በክፍል በክፍል ታትሞ በመጨረሻ በአንድ ጥራዝ ተጠረዘ፤ ከዚህ ትረካ አንባቢዎች ብዙዎቹ ያውቁት ይሆናል። እርሳቸው ብዙ ችሎታ የነበራቸው ሰው ነበሩ፤ ደግ ሰው እንደ ነበሩም ተስፋ ማድረግ አለብኝ፤ ነገር ግን እኔ እንደማስበው በፍልስፍናቸው እጅግ የተታለሉ፥ በሥነ መለኮታቸውም ከመንገድ እጅግ የወጡ ነበሩ። እርሳቸውንም ሆነ መጽሐፋቸውን የጠቀስሁት ስለ እነርሱ ክፉ ለመናገር ስለ ፈለግሁ አይደለም፤ ነገር ግን እኔ እስከማውቀው ድረስ የእርሳቸውን ልዩ አመለካከት በማይደግፉ መነቃቃቶች ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ብዙም ይሁን ጥቂት ተቃውሞ ማቅረባቸውን ፈጽሞ እንዳላቋረጡ ለመናገር ብቻ ነው። አቶ ኔትልተን በእነዚያ መነቃቃቶች ላይ በተነሣው ተቃውሞ ራስ ሆነው የወሰዱትን አካሄድ፥ ስማቸውን ሳይጠሩ ለመከላከል ብዙ ደከሙ። እግዚአብሔር ግን ያንን ተጽዕኖ ሁሉ አስወግዶታል። አሁን ለብዙ ዓመታት ስለ እርሱ ምንም አልሰማሁም።
በኦበርን የነበሩ አንዳንድ መምህራን በውጭ ካሉ ከብዙ አገልጋዮች ጋር ተባብረው የያዙት አቋም ቢኖርም፥ ጌታ ብዙም ሳይቆይ በኦበርን ሥራውን አነቃቃ። አቶ ላንሲንግ ትልቅና እጅግ አስተዋይ ጉባኤ ነበራቸው። መነቃቃቱ ብዙም ሳይቆይ በሕዝቡ መካከል ሥር ሰደደ፤ ኃይለኛም ሆነ።
በዚያን ጊዜ ነበር እስከ ዛሬ በዚያ የሚኖሩት የኦበርኑ ዶ/ር ኤስ—— በነፍሳቸው እጅግ ተባርከው ፍጹም ሌላ ሰው የሆኑት። እኔ እዚያ በደረስሁ ጊዜ ዶ/ር ኤስ—— በፕሪስባይቴሪያን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሽማግሌ ነበሩ። እጅግ ዓይናፋርና ተጠራጣሪ ዓይነት ክርስቲያን ነበሩ፤ እምነታቸው ጥቂት ስለ ነበረ በክርስቲያናዊ ውጤታማነታቸውም ጥቂት ነበሩ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ጥልቅ የኃጢአት ወቀሳ ያዛቸው፤ ወደ ውርደትና ጭንቀት ጥልቀት ወረዱ፤ ተስፋ ወደ መቍረጥም ሊደርሱ ጥቂት ቀራቸው። በዚህ ሁኔታ ለሳምንታት ቆዩ፤ እስከ አንድ ሌሊትም ድረስ በአንድ የጸሎት ስብሰባ ላይ በስሜታቸው ፈጽመው ተሸንፈው አቅም አጥተው መሬት ላይ ወደቁ። በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር በክርስቶስ ያለውን የመዳናቸውን እውነተኛነት እንዲያዩ ዓይናቸውን ከፈተ። ይህ የሆነው እኔ ኦበርንን ትቼ ለመሥራት ወደ ትሮይ፥ ኒው ዮርክ ከሄድሁ በኋላ ወዲያውኑ ነበር። ዶ/ር ኤስ—— ብዙም ሳይቆዩ ተከትለውኝ ወደ ትሮይ መጡ፤ በዚያም ለመጀመሪያ ጊዜ ባየኋቸው ጊዜ ለእርሳቸው ብቻ በሆነ አጽንዖት፦ «ወንድም ፊኒ፥ አዳኙን ቀብረውት ነበር፤ ክርስቶስ ግን ተነሥቷል» ብለው ጮኹ። እጅግ ድንቅ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ስለ ተቀበሉ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ደስታና መደነቂያ ሆነው ኖረዋል።
ብዙ አገልጋዮች በሥራዬ ላይ ተቃውሞ እንዳላቸው በመታወቁ በከፊል፥ በኦበርን ብዙ ተቃውሞ ተነሣ፤ በዚያም ትልቅ መንደር ከነበሩት ዋና ዋና ሰዎች ብዙዎቹ በሥራው ላይ ጽኑ አቋም ያዙ። የጌታ መንፈስ ግን በታላቅ ኃይል በሕዝቡ መካከል ነበረ።
አንድ የሰንበት ጠዋት እየሰበክሁ ሳለሁ፥ አንዳንድ ሰዎች ቤተሰቦቻቸውን እንዴት እንደሚቃወሙና ቢቻላቸውም እንዳይለወጡ እንዴት እንደሚከለክሉ እየገለጽሁ እንደ ነበረ አስታውሳለሁ። የዚህን ዓይነት ሁኔታ እጅግ ሕያው አድርጌ ስለ ገለጽሁ፦ «ምናልባት እናንተን ባውቃችሁ ኖሮ ቤተሰቦቻችሁን በዚህ መንገድ የምትይዙትን አንዳንዶቻችሁን በስማችሁ ልጠራችሁ እችል ነበር» አልሁ። በዚያችው ቅጽበት አንድ ሰው በጉባኤው መካከል፦ «ስሜን ጥራ!» ብሎ ጮኸ፤ ከዚያም ራሱን ከፊቱ ባለው መቀመጫ ላይ ወደ ፊት ጣለ፤ በታላቅ ስሜትም እንደሚንቀጠቀጥ ግልጽ ነበር። ቤተሰቡን በዚህ መንገድ ይይዝ እንደ ነበረና በዚያው ጠዋት እኔ የጠቀስኋቸውን ነገሮች እንዳደረገ ታወቀ። «ስሜን ጥራ!» ብሎ መጮኹ በድንገት የመጣና ሊቋቋመው የማይችል ስለ ነበረ ራሱን ሊገታ እንዳልቻለ ተናገረ። ነገር ግን ወደ ክርስቶስ ፈጽሞ ያልተለወጠ ይመስለኛል ብዬ እፈራለሁ።
በዚያን ጊዜ በኦበርን ኤች—— የሚባል አንድ ባርኔጣ ሰፊ ይኖር ነበር። ሚስቱ ክርስቲያን ሴት ነበረች፤ እርሱ ግን ዩኒቨርሳሊስትና የመነቃቃቱ ተቃዋሚ ነበር። ተቃውሞውን እስከዚያ ድረስ አስፋፍቶ ሚስቱ ወደ ስብሰባዎቻችን እንዳትሄድ ከለከላት፤ እርሷም ለተከታታይ ብዙ ምሽቶች በቤት ቀረች። አንድ ሌሊት፥ ጉባኤው ከመሰብሰቡ ግማሽ ሰዓት በፊት የስብሰባው ማስታወቂያ ደወል በተደወለ ጊዜ፥ ወይዘሮ ኤች—— ስለ ባሏ በአእምሮዋ እጅግ ተጨንቃ ስለ ነበረ ለጸሎት ገለል አለች፤ ያንንም ግማሽ ሰዓት ነፍሷን በእግዚአብሔር ፊት በማፍሰስ አሳለፈች። ባሏ እንዴት እንደሚያደርግና ወደ ስብሰባ እንድትሄድ እንደማይፈቅድላት ነገረችው፤ ወደ እግዚአብሔርም እጅግ ቀረበች።
እኔ እንደ ሰማሁት፥ ሕዝቡ እንዲሰበሰብ ደወሉ እየተደወለ ሳለ ከእልፍኟ ወጣች፤ ባሏም ከሱቁ ወደ ቤት ገብቶ አገኘችው፤ እርሷም ወደ መቀመጫ ክፍሉ ስትገባ ወደ ስብሰባ አትሄጂም ወይ ብሎ ጠየቃት፤ ብትሄድም አብሯት እንደሚሄድ ነገራት። በኋላም በዚያች ሌሊት ወደ ስብሰባው ለመሄድ የወሰነው፥ በሚስቱ ላይ ያለውን ተቃውሞ የሚያጸድቅለት አንድ ነገር ያገኝ እንደ ሆነ፥ ወይም ቢያንስ የሚስቅበትንና ሥራውን ሁሉ በማላገጡ የሚደግፈውን አንድ ነገር ለማግኘት እንደ ነበረ ነገረኝ። ከሚስቱ ጋር ለመሄድ ባቀረበ ጊዜ እርሷ እጅግ ተደነቀች፤ ነገር ግን ተዘጋጀች፤ ወደ ስብሰባውም መጡ።
በዚያን ጊዜ ስለዚህ ሁሉ በእርግጥ ምንም አላውቅም ነበር። ቀኑን ሙሉ ጠያቂዎችን እየጐበኘሁና ከእነርሱ ጋር እየሠራሁ ነበርና ሐሳቤን ለማደራጀት፥ ወይም ጥቅስ እንኳ ለመምረጥ ምንም ጊዜ አላገኘሁም ነበር። በመግቢያው አገልግሎት ጊዜ አንድ ጥቅስ ወደ አእምሮዬ መጣ። ይህም ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው፦ «ተዉን» ብሎ የጮኸው ቃል ነበር። እነዚያን ቃላት ይዤ መስበክ ቀጠልሁ፤ እንዲተዉ የሚፈልጉትን፥ ከክርስቶስ ጋር ምንም ግንኙነት እንዲኖራቸው የማይፈልጉትን የእነዚያን ኃጢአተኞች አካሄድ ግልጥ አድርጌ ለማሳየት ጣርሁ። ጌታ እንዲህ ያሉ ሰዎች የሚከተሉትን መንገድ እጅግ ሕያው አድርጌ እንድገልጽ ኃይል ሰጠኝ። በስብከቴ መካከል በሰፊው መተላለፊያ አጠገብ አንድ ሰው ከመቀመጫው ሲወድቅ አየሁ፤ እርሱም እጅግ በሚያስፈራ ሁኔታ ጮኸ። ጉባኤው እጅግ ደነገጠ፤ የሰውዬውም ጩኸት እጅግ ታላቅ ስለ ነበረ መስበኬን አቁሜ ዝም ብዬ ቆምሁ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ እኔ ወርጄ ከሰውዬው ጋር እስክነጋገር ድረስ ጉባኤው ዝም ብሎ እንዲቀመጥ ለመንሁ። ሰውዬው ስለ እርሱ ስናገር የነበርሁት ይኸው አቶ ኤች—— ሆኖ አገኘሁት። የጌታ መንፈስ በመቀመጫው ላይ መቀመጥ እስኪያቅተው ድረስ በኃይል ወቅሶት ነበር። እርሱ ዘንድ በደረስሁ ጊዜ ራሱን በሚስቱ ጭን ላይ አድርጎ በጉልበቱ ለመንበርከክ የሚያስችል ጉልበት አግኝቶ ነበር። እንደ ሕፃን ልጅ ጮክ ብሎ እያለቀሰ ኃጢአቱን ይናዘዝ፥ ራሱንም በሚያስፈራ ሁኔታ ይከስ ነበር። ጥቂት ቃላት ነገርሁት፤ እርሱ ግን ለእነርሱ ብዙም ትኵረት የሰጠ አይመስልም ነበር። የእግዚአብሔር መንፈስ ትኵረቱን ፈጽሞ ይዞት ስለ ነበረ፥ የምለውን እንዲያዳምጥ ለማድረግ የማደርገውን ጥረት ሁሉ ብዙም ሳይቆይ ተውሁት። ማን እንደ ሆነ ለጉባኤው በነገርኋቸው ጊዜ ሁሉም እርሱንና ጠባዩን ያውቁ ነበር፤ ይህም በቤቱ ክፍል ሁሉ እንባና ልቅሶ አስከተለ። ስብከቴን ለመቀጠል የሚያስችል ያህል ጸጥ ይል እንደ ሆነ ለማየት ለጥቂት ጊዜ ቆምሁ፤ ነገር ግን ጮክ ብሎ ማልቀሱ ይህን የማይቻል አደረገው። ሚስቱ ፊቱን በእጆቿ ይዛ በጭኗ ላይ አድርጋ ተቀምጣ ሳለች የነበራትን መልክ ፈጽሞ ልረሳው አልችልም። በፊቷ ላይ ቃላት ሊገልጹት የማይችሉ ቅዱስ ደስታና የድል ስሜት ይታይ ነበር።
ብዙ ጸሎቶች ካደረግን በኋላ ስብሰባውን አሰናበትሁ፤ አንዳንድ ሰዎችም አቶ ኤች——ን ወደ ቤቱ እንዲደርስ ረዱት። ወዲያውኑ በዚያ ስፍራ በጌታ ሥራ ላይ አብረውት ሲያላግጡ የነበሩትን አንዳንድ ጓደኞቹን እንዲጠሩለት ፈለገ። ብዙዎቹን አስጠርቶ እስኪናዘዝላቸው ድረስ ማረፍ አልቻለም፤ ይህንንም እጅግ በተሰበረ ልብ አደረገው።
እጅግ ተሸንፎ ስለ ነበረ ለሁለት ወይም ለሦስት ቀናት በከተማ ውስጥ መዘዋወር አልቻለም፤ ሊናዘዝላቸውና ከሚመጣው ቍጣ እንዲሸሹ ሊያስጠነቅቃቸው ያሰባቸውን ሰዎች ማስጠራቱን ቀጠለ። መዘዋወር እንደ ቻለ ወዲያውኑ በፍጹም ትሕትናና በጠባይ ቅንነት፥ ነገር ግን በታላቅ ትጋት ሥራውን ያዘ። ብዙም ሳይቆይ ሽማግሌ ወይም ዲያቆን ሆኖ ተሾመ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም እጅግ አርአያ የሚሆንና ጠቃሚ ክርስቲያን ሆኖ ኖሯል። መለወጡ እጅግ ጉልህና ኃይለኛ ስለ ነበረ፥ ውጤቶቹም እጅግ ግልጽ ስለ ነበሩ ተቃውሞን ጸጥ በማሰኘት ረገድ እጅግ ብዙ አደረገ።
በከተማው ውስጥ በዶ/ር ላንሲንግና በእኔ፥ እንዲሁም በዚያ መነቃቃት በሠሩት ሰዎች ላይ የተቀየሙ ብዙ ሀብታም ሰዎች ነበሩ፤ እኔም ከሄድሁ በኋላ ተሰብስበው አዲስ ጉባኤ አቋቋሙ። ከእነዚህ አብዛኞቹ በዚያን ጊዜ ያልተለወጡ ሰዎች ነበሩ። አንባቢው ይህን በልቡ ይያዝ፤ ምክንያቱም በተገቢው ስፍራ የዚህን ተቃውሞ ውጤቶችና የአዲሱን ጉባኤ መቋቋም፥ ከዚያም በኋላ የእነዚያ ተቃዋሚዎች ከሞላ ጎደል ሁሉም መለወጣቸውን የምጠቅስበት አጋጣሚ ይኖረኛል።
በኦበርን ሳለሁ በዙሪያው ባሉ አጎራባች አብያተ ክርስቲያናት ብዙም ይሁን ጥቂት ሰበክሁ፤ መነቃቃቱም ወደ ልዩ ልዩ አቅጣጫዎች፥ ወደ ካዩጋና ወደ ስካኒያትለስ ተስፋፋ። ይህም የሆነው በ1826 በበጋና በበልግ ወራት ነበር።
ኦበርን ከደረስሁ ብዙም ሳይቆይ እጅግ የሚያስደንቅ አንድ ሁኔታ ስለ ተከሰተ በአጭሩ ልተርከው ይገባኛል። እኔና ባለቤቴ የቤተ ክርስቲያኒቱ እረኛ የዶ/ር ላንሲንግ እንግዶች ነበርን። ቤተ ክርስቲያኒቱ ከዓለም ጋር እጅግ ተመሳስላ ነበር፤ ያልተለወጡ ሰዎችም በአለባበስ፥ በፋሽንና በዓለማዊነት ቀዳሚዎች ናቸው ብለው ይከሷቸው ነበር። እንደ ልማዴ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትታደስና ወደ መነቃቃት ሁኔታ እንድትገባ ስብከቴን ወደዚያ አቀናሁ። አንድ ሰንበት በዓለም ፊት ስለ ያዙት አቋም በተቻለኝ መጠን ልብን በሚመረምር ሁኔታ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሰበክሁ። ቃሉ ሕዝቡን አጥብቆ ያዘ።
ንግግሬን በጨረስሁ ጊዜ እንደ ልማዴ እረኛውን እንዲጸልዩ ጠየቅኋቸው። እርሳቸው በስብከቱ እጅግ ተነክተው ስለ ነበረ ወዲያውኑ ወደ ጸሎት ከመግባት ይልቅ፥ እኔ የነገርኋቸውን የሚያጸና አጭር ነገር ግን እጅግ ልባዊ ንግግር ለቤተ ክርስቲያኒቱ አደረጉ። በዚህ ቅጽበት አንድ ሰው በላይኛው ሰገነት ላይ ተነሥቶ እጅግ በተረጋጋና ግልጽ በሆነ ሁኔታ፦ «አቶ ላንሲንግ፥ እርስዎ የተጣጠፈ ጌጥ ያለው ሸሚዝና የወርቅ ቀለበት እያደረጉ፥ ባለቤትዎና የቤተሰብዎ ሴቶችም እንደሚያደርጉት በዘመኑ ፋሽን ቀዳሚዎች ሆነው ለብሰው በጉባኤው ፊት እየተቀመጡ፥ እንዲህ ያለው ንግግር ከእርስዎ ሲወጣ ምንም መልካም ነገር ሊያደርግ ይችላል ብዬ አላምንም» አለ። ይህ ዶ/ር ላንሲንግን ፈጽሞ የሚገድላቸው መሰለ። ምንም መልስ አልሰጡም፤ ነገር ግን ራሳቸውን በመድረኩ ጎን ላይ ጣሉና እንደ ሕፃን አለቀሱ። ጉባኤውም እንደ እርሳቸው ያህል ደነገጠ፤ ልቡም ተነካ። ከሞላ ጎደል ሁሉም ራሳቸውን ከፊታቸው ባለው መቀመጫ ላይ ደፉ፤ ብዙዎቹም በየአቅጣጫው አለቀሱ። ከልቅሶውና ከትካዜው በቀር ቤቱ ፈጽሞ ጸጥ ብሎ ነበር። ለጥቂት ጊዜ ጠበቅሁ፤ ዶ/ር ላንሲንግ ስላልተንቀሳቀሱም ተነሥቼ አጭር ጸሎት አቀረብሁና ጉባኤውን አሰናበትሁ።
ከተጐዱት ከውዱ እረኛ ጋር ወደ ቤት ሄድሁ፤ ቤተሰቡም ሁሉ ከቤተ ክርስቲያን ከተመለሱ በኋላ ቀለበቱን ከጣታቸው አወለቁ፤ ይህም ዓይን ሊስብ የማይችል ቀጭን የወርቅ ቀለበት ነበር፤ የመጀመሪያዋ ሚስታቸው በሞት አልጋ ላይ ሳለች ከጣቷ አውልቃ በእርሳቸው ጣት ላይ እንዳደረገችውና ስለ እርሷ ብለው እንዲያደርጉት እንደ ለመነቻቸው ነገሩን። ይህ ማሰናከያ ይሆናል ብለው ሳያስቡ እንዲሁ አድርገው ነበር። ስለ ሸሚዛቸው ጌጦችም ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲለብሷቸው እንደ ኖሩና ተገቢ ያልሆነ ነገር አድርገው እንዳላሰቧቸው ተናገሩ። በእርግጥም መቼ መልበስ እንደ ጀመሩ ሊያስታውሱ አልቻሉም፤ ስለዚህም በእርግጥ ስለ እነርሱ ምንም አላሰቡም ነበር። «ነገር ግን» አሉ፥ «እነዚህ ነገሮች ለማንም የመሰናከል ምክንያት ከሆኑ አላደርጋቸውም።» እርሳቸው ክቡር ክርስቲያን ሰውና እጅግ ጥሩ እረኛ ነበሩ።
ከዚህ በኋላ ወዲያውኑ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከእግዚአብሔር መራቋንና ክርስቲያናዊ መንፈስ እንደ ጐደላት በዓለም ፊት በይፋ ለመናዘዝ ፈቃደኛ ሆነች። በዚህም መሠረት ጉዳዩን ሁሉ የሚሸፍን የኑዛዜ ቃል ተዘጋጀ። ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድታጸድቀው ቀረበላት፤ ከዚያም በጉባኤው ፊት ተነበበ። ኑዛዜው ሲነበብ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተነሥታ ቆመች፤ ብዙዎቹም ያለቅሱ ነበር። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሥራው እጅግ በጨመረ ኃይል ወደ ፊት ገፋ።
ኑዛዜው ከልብ የመነጨ ሥራ እንጂ ማስመሰል እንዳልነበረ ግልጽ ነበር፤ እግዚአብሔርም በታላቅ ቸርነትና በግልጽ ተቀበለው፤ የተቃዋሚዎችም አፍ ተዘጋ። እውነቱ በከፍተኛ መጠን አብያተ ክርስቲያናትና አገልጋዮች በዝቅተኛ የጸጋ ሁኔታ ላይ ነበሩ፤ እነዚያ ኃይለኛ መነቃቃቶችም ድንገት ደረሱባቸው። እነዚያ ድንቅ የእግዚአብሔር ሥራዎች በመነቃቃት ሁኔታ ውስጥ ባልነበሩት ሰዎች ዘንድ በሚገባ ያልተረዱና ያልተቀበሉ መሆናቸው በዚያን ጊዜም ሆነ ከዚያ ወዲህ ብዙም አላስደነቀኝም።
በኦበርንና በአካባቢዋ፥ ደግሞም ሥራው በየአቅጣጫው ሲስፋፋ በዚያ የክፍለ ሀገሩ ክፍል ባሉ አጎራባች ከተሞች ሁሉ ብዙ የሚያስደስቱ መለወጦች ነበሩ። በ1831 የጸደይ ወራት እንደ ገና በኦበርን ነበርሁ፤ በዚያም ሌላ ኃይለኛ መነቃቃት አየሁ። ሁኔታዎቹ ልዩና እጅግ የሚያስደስቱ ነበሩ፤ በዚህ ትረካ ውስጥም በተገቢው ስፍራቸው ይተረካሉ።