የቄስ ቻርልስ ጂ. ፊኒ ማስታወሻዎች
በሮም የሆነው መነቃቃት

ምዕራፍ 13 · 19 ደቂቃ ንባብ · 24 ደቂቃ ማዳመጥ

በሮም የሆነው መነቃቃት

በዚህ ጊዜ በሮም የሚገኘው የኮንግሪጌሽናል ቤተ ክርስቲያን እረኛ ቄስ ሞዝስ ጊሌት ጌታ በዌስተርን ያደርግ የነበረውን ሰምተው፥ ከቤተ ክርስቲያናቸው ታዋቂ አባላት አንዷ ከሆነችው ከወይዘሪት ኤች—— ጋር እየተካሄደ ያለውን ሥራ ለማየት መጡ። ሁለቱም በእግዚአብሔር ሥራ እጅግ ተነኩ። የእግዚአብሔር መንፈስ እስከ አእምሮአቸው ጥልቅ መሠረት ድረስ እያነቃቃቸው እንደ ነበረ አየሁ። ከጥቂት ቀናት በኋላ አቶ ጊሌትና ወይዘሪት ኤች—— እንደ ገና መጡ። ወይዘሪት ኤች—— እጅግ ቀናተኛና ትጉ ክርስቲያን ልጃገረድ ነበረች። ለሁለተኛ ጊዜ በመጡ ጊዜ አቶ ጊሌት እንዲህ አሉኝ፦ «ወንድም ፊኒ፥ አዲስ መጽሐፍ ቅዱስ ያገኘሁ ይመስለኛል። ተስፋዎቹን አሁን እንደምረዳቸው ከዚህ በፊት ፈጽሞ ተረድቻቸው አላውቅም፤ ከዚህ በፊት ፈጽሞ አልጨበጥኋቸውም ነበር፤ ማረፍ አልችልም፤ አእምሮዬ በዚህ ጉዳይ ተሞልቷል፤ ተስፋዎቹም ለእኔ አዲስ ሆነውብኛል።» ለተወሰነ ጊዜ የዘለቀው ይህ ንግግር፥ ጌታ በራሳቸው ጉባኤ ውስጥ ለሚሠራው ታላቅ ሥራ እያዘጋጃቸው እንደ ነበረ እንድረዳ አደረገኝ።

ከዚህ ብዙም ሳይቆይ፥ መነቃቃቱ በዌስተርን በሙሉ ኃይሉ ላይ በነበረበት ጊዜ፥ አቶ ጊሌት ለአንድ ቀን የስብከት ቦታ እንድንለዋወጥ አግባቡኝ። ሳልወድ ተስማማሁ።

ቦታ የምንለዋወጥበት ቀን በፊት ባለው ቅዳሜ ወደ ሮም በመሄድ ላይ ሳለሁ ለመለዋወጡ በመስማማቴ እጅግ ተጸጸትሁ። አቶ ጊሌት ከአሮጌ ስብከቶቻቸው አንዳንዶቹን ይሰብካሉ፤ እነዚያም ለነበረው ሁኔታ ሊስማሙ እንደማይችሉ በሚገባ አውቅ ነበርና ይህ በዌስተርን ያለውን ሥራ እጅግ የሚያበላሽ መሰለኝ። ይሁን እንጂ ሕዝቡ ይጸልዩ ነበር፤ ሥራውንም ሊያዘገየው ይችል እንደ ሆነ እንጂ አያቆመውም ነበር። ወደ ሮም ሄጄ በሰንበት ሦስት ጊዜ ሰበክሁ። ቃሉ ታላቅ ውጤት እንዳመጣ ለእኔ ፍጹም ግልጽ ነበር። በዕለቱ ብዙ ራሶች ተደፍተው እንደ ነበሩ፥ እጅግ ብዙዎቹም በጥልቅ የኃጢአት ወቀሳ እንደ ተዋረዱ አየሁ። ጠዋት «ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና» በሚለው ጥቅስ ላይ ሰበክሁ፤ ከሰዓት በኋላና ማታም በዚያው አቅጣጫ የሚሄድ ነገር በማከል ቀጠልሁበት። ሰኞ ጠዋት አቶ ጊሌት ከዌስተርን እስኪመለሱ ድረስ ጠበቅሁ። ስለ ሕዝቡ ሁኔታ የተሰማኝን ነገርኋቸው። እኔ እንደ ገመትሁት ሥራው በዚያ ያህል ኃይል መጀመሩን የተረዱ አይመስሉም ነበር። ነገር ግን በጉባኤው ውስጥ ጠያቂዎች ካሉ ሊጠሯቸው ፈለጉ፤ እኔም በስብሰባው ላይ እንድገኝ ተመኙ። ከዚህ በፊት እንደ ተናገርሁት፥ እስከዚያ ጊዜ ድረስ መነቃቃትን ለማስፋፋት ስጠቀምባቸው የነበሩት መንገዶች ብዙ ጸሎት (በስውርም በኅብረትም)፥ የሕዝብ ስብከት፥ የግል ንግግርና ከቤት ወደ ቤት መጐብኘት ነበሩ፤ ጠያቂዎች ሲበዙም ስብሰባዎችን እወስንላቸውና የሚጠይቁትን ለፍላጎታቸው የሚስማማ ትምህርት እንዲቀበሉ እንዲሰበሰቡ እጋብዛቸው ነበር። የነፍሳትን መለወጥ ለማረጋገጥ በመሞከር እስከዚያ ጊዜ ድረስ የተጠቀምሁባቸው መንገዶች እነዚህና እነዚህ ብቻ ነበሩ። አቶ ጊሌት በታቀደው የጠያቂዎች ስብሰባ ላይ እንድገኝ ጠየቁኝ። እንደምገኝ ነገርኋቸው፤ ሰኞ ምሽት የጠያቂዎች ስብሰባ እንደሚኖር በመንደሩ ውስጥ ወሬውን ማሰራጨት እንደሚችሉም ነገርኋቸው። እኔ ወደ ዌስተርን ሄጄ ልክ ምሽት ላይ እመለሳለሁ፤ እኔ እንድገኝ እንደሚጠብቁ ለሕዝቡ እንዳያሳውቁ ተስማማን። ስብሰባው የተጠራው ከዲያቆኖቻቸው በአንዱ ቤት ነበር። በደረስን ጊዜ ሰፊው የእንግዳ ማረፊያ ክፍል እስከ መጨረሻው አቅሙ ድረስ ተጨናንቆ አገኘነው። አቶ ጊሌት በመገረምና በግልጽ በሚታይ መረበሽ ዙሪያቸውን ተመለከቱ፤ ስብሰባው ከጉባኤያቸው እጅግ አስተዋዮችና ተሰሚነት ካላቸው አባላት ብዙዎቹን የያዘ መሆኑን፥ በተለይም በአብዛኛው በከተማው ውስጥ የታወቁ ወጣቶችን ያቀፈ መሆኑን አዩ። ከእነርሱ ጋር ለመነጋገር በመሞከር ጥቂት ጊዜ አሳለፍን፤ ስሜቱም እጅግ ጥልቅ ከመሆኑ የተነሣ ለመቆጣጠር የማይቻል የሚያህል የስሜት ፍንዳታ ሊከሰት የሚችልበት አደጋ እንዳለ ብዙም ሳይቆይ አየሁ። ስለዚህ አቶ ጊሌትን እንዲህ አልኋቸው፦ «ስብሰባውን በዚህ መልክ መቀጠል አይሆንም። የሚያስፈልጋቸውን ያህል ጥቂት ቃል እናገርና አሰናብታቸዋለሁ።»

በስብሰባው ውስጥ ምንም ዓይነት ስሜት ለመቀስቀስ የተባለም ሆነ የተደረገም ነገር አልነበረም። ስሜቱ ሁሉ በራሱ የመጣ ነበር። ሥራው በዚያ ያህል ኃይል ነበርና ጥቂት የንግግር ቃላት እንኳ በጣም ጠንካራ የሆኑትን ሰዎች ሰይፍ ወደ ልባቸው እንደ ተሰካ ያህል በተቀመጡበት እንዲንፈራገጡ ያደርጋቸው ነበር። እንደዚህ ያለውን ትዕይንት ፈጽሞ አይቶ የማያውቅ ሰው፥ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሥር እውነት አንዳንድ ጊዜ ምን ያህል ኃይል እንዳለው መረዳት ምናልባት አይቻለውም። በእርግጥም ሰይፍ፥ ያውም ሁለት አፍ ያለው ሰይፍ ነበር። በጥቂት የንግግር ቃላት ጠልቆ በሚመረምር መንገድ በቀረበ ጊዜ ያስከተለው ሕመም ሊታገሡት የማይቻል የሚመስል ጭንቀት ይፈጥር ነበር።

አቶ ጊሌት እጅግ ተረበሹ። ፊታቸው ገረጣ፤ በብዙ መደናገጥም «ምን እናድርግ? ምን እናድርግ?» አሉ። እጄን በትከሻቸው ላይ አድርጌ በሹክሹክታ «ተረጋጉ፥ ተረጋጉ፥ ወንድም ጊሌት» አልኋቸው። ከዚያም በተቻለኝ መጠን በለዘብተኛ ነገር ግን ግልጽ በሆነ መንገድ ተናገርኋቸው፤ ወዲያውኑ ትኩረታቸውን ወደ ብቸኛው መፍትሔአቸው ሳብሁ፤ ያም አሁኑኑ የሚገኝና ለሁሉ የሚበቃ መፍትሔ መሆኑን አረጋገጥሁላቸው። የዓለም አዳኝ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ አመለከትኋቸው፤ ሊታገሡት እስከቻሉ ድረስ በዚሁ መንገድ ቀጠልሁ፤ ይህም በእርግጥ ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ነበር።

አቶ ጊሌት እጅግ ከመረበሻቸው የተነሣ ወደ እርሳቸው ቀርቤ ክንዳቸውን ይዤ «እንጸልይ» አልኋቸው። ቆመንበት በነበረው በክፍሉ መካከል ተንበረከክን። በዝግታና ስሜትን በማያንጸባርቅ ድምፅ በጸሎት መራሁ፤ ነገር ግን አዳኙ በዚያኑ ጊዜና በዚያኑ ስፍራ ደሙን ጣልቃ እንዲያስገባ፥ እነዚህንም ኃጢአተኞች ሁሉ እርሱ ያቀረበላቸውን መዳን እንዲቀበሉና ነፍሳቸውን ለማዳን እንዲያምኑ እንዲመራቸው ማለድሁት። መረበሹ በየደቂቃው እየጠለቀ ሄደ፤ ልቅሶአቸውንና ትካዜአቸውን ስሰማም ጸሎቴን ዘግቼ ከተንበረከክሁበት ድንገት ተነሣሁ። ሁሉም ተነሡ፤ እኔም እንዲህ አልሁ፦ «አሁን እባካችሁ አንዳችሁ ለሌላው አንዲት ቃል ሳትናገሩ ወደ ቤታችሁ ሂዱ። ዝም ለማለት ሞክሩ፤ ስሜታችሁንም በጩኸት አትግለጹ፤ ነገር ግን አንዲት ቃል ሳትናገሩ ወደ ክፍሎቻችሁ ሂዱ።»

በዚህ ቅጽበት በአቶ ኤች—— መደብር ጸሐፊ የነበረና በስፍራው ካሉት ቀዳሚ ወጣቶች አንዱ የሆነ ደብሊው—— የተባለ ወጣት ሊዝል ምንም አልቀረውም ነበርና አጠገቡ በቆሙት በአንዳንድ ወጣቶች ላይ ወደቀ፤ እነርሱም ሁሉ በከፊል ራሳቸውን ስተው አብረው ወደቁ። ይህ ኃይለኛ ጩኸት ሊያስነሣ ጥቂት ቀርቶት ነበር፤ እኔ ግን ጸጥ አሰኘኋቸውና ወጣቶቹን «እባካችሁ ያንን በር ወለል አድርጋችሁ ክፈቱትና ውጡ፤ ሁሉም በጸጥታ ይሂዱ» አልኋቸው። እንደ ጠየቅኋቸውም አደረጉ። አልጮኹም፤ ነገር ግን እያለቀሱና እየተከዙ ወጡ፤ ልቅሶአቸውና ትካዜአቸውም ወደ መንገድ እስኪወጡ ድረስ ይሰማ ነበር።

ይህ የጠቀስሁት አቶ ደብሊው—— ወደሚኖርበት ቤት በር እስኪገባ ድረስ ዝም አለ፤ ከዚያ በኋላ ግን ራሱን መቆጣጠር አልቻለም። በሩን ዘግቶ መሬት ላይ ወደቀ፤ የነበረበትን አስፈሪ ሁኔታ እያየም በታላቅ ድምፅ ዋይታ አሰማ። ይህ ቤተሰቡን በዙሪያው አሰባሰበ፤ በሁሉም ላይ የኃጢአት ወቀሳን አዛመተ።

ተመሳሳይ ትዕይንቶች በሌሎች ቤተሰቦች ውስጥም እንደ ተከሰቱ በኋላ ሰማሁ። በኋላ እንደ ተረጋገጠው፥ በስብሰባው ላይ አያሌዎች ተለውጠው ነበር፤ ራሳቸውን መቆጣጠር እስኪያቅታቸውም ድረስ በደስታ ተሞልተው ወደ ቤታቸው ሄዱ።

በማግሥቱ ጠዋት ገና በደንብ እንደ ነጋ፥ በከባድ የኃጢአት ወቀሳ ውስጥ እንዳሉ የገለጹአቸውን የቤተሰቦቻቸውን አባላት ሄደን እንድንጐበኝ ለመጠየቅ ሰዎች ወደ አቶ ጊሌት ቤት መምጣት ጀመሩ። በችኮላ ቁርስ በልተን ወጣን። ወደ መንገድ እንደ ወጣን ሰዎች ከብዙ ቤቶች እየሮጡ ወጥተው ወደ ቤቶቻቸው እንድንገባ ለመኑን። በአንድ ጊዜ አንድ ስፍራ ብቻ መጐብኘት እንችል ስለ ነበረ፥ ወደ አንድ ቤት ስንገባ ጎረቤቶች እየተጣደፉ ገብተው ትልቁን ክፍል ይሞሉት ነበር። ለአጭር ጊዜ ቆይተን ትምህርት እንሰጣቸውና ወደ ሌላ ቤት እንሄድ ነበር፤ ሰዎቹም ይከተሉን ነበር።

እጅግ ያልተለመደ ሁኔታ አገኘን። የኃጢአት ወቀሳዎቹ እጅግ ጥልቅና በሁሉ ዘንድ የተስፋፉ ከመሆናቸው የተነሣ አንዳንድ ጊዜ ወደ አንድ ቤት ስንገባ አንዳንዶቹን ተንበርክከው፥ አንዳንዶቹን ደግሞ መሬት ላይ በግንባራቸው ተደፍተው እናገኛቸው ነበር። እኩለ ቀን ድረስ በዚህ መንገድ ከቤት ወደ ቤት እየጐበኘን፥ እየተነጋገርንና እየጸለይን ቆየን። ከዚያም አቶ ጊሌትን እንዲህ አልኋቸው፦ «ይህ ፈጽሞ አይሆንም፤ የጠያቂዎች ስብሰባ ሊኖረን ይገባል። ከቤት ወደ ቤት መሄድ አንችልም፤ የሕዝቡንም ፍላጎት ፈጽሞ እያሟላን አይደለንም።» እርሳቸውም በዚህ ተስማሙ፤ ነገር ግን ስብሰባውን የት እናድርግ የሚል ጥያቄ ተነሣ።

በዚያ ጊዜ ሃይማኖተኛ የሆነ አንድ አቶ ኤፍ—— የሚባል ሰው በከተማው መሀል ባለው ማዕዘን ላይ ሆቴል ነበረው። ትልቅ የመመገቢያ ክፍልም ነበረው፤ አቶ ጊሌትም «ጎራ ብዬ የጠያቂዎችን ስብሰባ በመመገቢያ ክፍሉ ውስጥ እንድናደርግ ይፈቀድልን እንደ ሆነ ልይ» አሉ። ያለ ችግር ፈቃድ አገኙ፤ ወዲያውኑም ወደ ሕዝብ ትምህርት ቤቶች ሄደው ከቀትር በኋላ በሰባት ሰዓት በአቶ ኤፍ—— የመመገቢያ ክፍል የጠያቂዎች ስብሰባ እንደሚኖር አሳወቁ። ወደ ቤት ሄደን ምሳችንን በላንና ወደ ስብሰባው ተነሣን። ሰዎች ሲጣደፉ፥ አንዳንዶቹም በእውነት እየሮጡ ወደ ስብሰባው ሲሄዱ አየን። ከየአቅጣጫው ይመጡ ነበር። እኛ በደረስንበት ጊዜ ክፍሉ ትልቅ ቢሆንም እስከ መጨረሻው አቅሙ ድረስ ታጭቆ ነበር። ወንዶች፥ ሴቶችና ልጆች ክፍሉን አጨናንቀውት ነበር።

ይህ ስብሰባ ባለፈው ምሽት ካደረግነው ስብሰባ ጋር እጅግ ይመሳሰል ነበር። ስሜቱ እጅግ ከአቅም በላይ ነበር። እጅግ ጠንካራ ነርቭ የነበራቸው አንዳንድ ሰዎች በተሰጡት ማሳሰቢያዎች እጅግ ከመሰበራቸው የተነሣ ራሳቸውን መርዳት አቅቷቸው ወዳጆቻቸው ወደ ቤታቸው ሊወስዷቸው ግድ ሆነ። ይህ ስብሰባ እስከ ምሽት ገደማ ድረስ ዘለቀ። በውጤቱም እጅግ ብዙ ተስፋ ሰጪ መለወጦች ሆኑ፤ ሥራውንም በየአቅጣጫው እጅግ ለማስፋፋት መንገድ ሆነ።

በዚያ ምሽት ሰበክሁ፤ አቶ ጊሌትም በማግሥቱ ጠዋት በፍርድ ቤቱ አዳራሽ የጠያቂዎች ስብሰባ እንዲሆን ወሰኑ።

ይህ ከመመገቢያው አዳራሽ እጅግ የሚበልጥ ክፍል ነበር፤ ምንም እንኳ እንደ እርሱ በመሀል የሚገኝ ባይሆንም። ይሁን እንጂ በሰዓቱ የፍርድ ቤቱ አዳራሽ ተጨናንቆ ነበር፤ የቀኑን ብዙ ክፍል ትምህርት በመስጠት አሳለፍን፤ ሥራውም በሚያስደንቅ ኃይል ቀጠለ። ማታ እንደ ገና ሰበክሁ፤ አቶ ጊሌትም በማግሥቱ ጠዋት በቤተ ክርስቲያኑ የጠያቂዎች ስብሰባ እንዲሆን ወሰኑ፤ በዚያ ጊዜ በመንደሩ ውስጥ ጠያቂዎቹን ለመያዝ የሚበቃ ሌላ ክፍል አልነበረምና።

የነገሮቹን ቅደም ተከተል በትክክል የማስታውስ ከሆነ፥ ምሽት ላይ በአንድ ትልቅ የትምህርት ቤት ሕንፃ ውስጥ የጸሎትና የምክክር ስብሰባ ለማድረግ ተነሣን። ነገር ግን ስብሰባው ገና እንደ ተጀመረ ስሜቱ እጅግ ስለ ጠለቀ፥ የማይፈለግ ከአቅም በላይ የሆነ የስሜት ፍንዳታ እንዳይከሰት፥ ስብሰባውን አሰናብተን ሕዝቡ በጸጥታ እንዲሄዱ፥ ክርስቲያኖችም እንደሚሻላቸው መስሎ በታያቸው መጠን ምሽቱን በስውር ጸሎት ወይም በቤተሰብ ጸሎት እንዲያሳልፉ እንድንጠይቅ ለአቶ ጊሌት ሐሳብ አቀረብሁ። ኃጢአተኞችን ደግሞ ልባቸውን ለእግዚአብሔር እስኪሰጡ ድረስ እንዳይተኙ መከርናቸው። ከዚህ በኋላ ሥራው እጅግ ከመስፋፋቱ የተነሣ፥ እንደማስበው ለሃያ ተከታታይ ምሽቶች በየምሽቱ፥ በሰንበትም ሁለት ጊዜ ሰበክሁ። በዚህ ጊዜ የጸሎት ስብሰባዎቻችን በቀን በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ይደረጉ ነበር። የጸሎቱ ስብሰባ በቀኑ አንድ ክፍል፥ የጠያቂዎች ስብሰባ ደግሞ በሌላው ክፍል ይደረግ ነበር። በትክክል የማስታውስ ከሆነ፥ ሥራው በዚህ መልክ ከጀመረ በኋላ በየቀኑ የጸሎት ስብሰባና የጠያቂዎች ስብሰባ እናደርግ ነበር፤ ማታ ደግሞ ስብከት ነበር። በስፍራው ሁሉ፥ እግዚአብሔር በዚያ እንዳለ ሰውን ሁሉ እንዲሰማው የሚያደርግ ግርማና ፍርሃት ሰፍኖ ነበር።

ከአጎራባች ከተሞች አገልጋዮች መጥተው ባዩትና በሰሙት ነገር እጅግ መደነቃቸውን ገለጹ፤ ቢደነቁም አይፈረድባቸውም ነበር። መለወጦቹ በፍጥነት እጅግ ከመብዛታቸው የተነሣ እነማን እንደ ተለወጡ የምናውቅበት መንገድ አልነበረንም። ስለዚህ በየምሽቱ በስብከቴ መጨረሻ ላይ በዚያ ቀን የተለወጡ ሁሉ ጥቂት እንድናነጋግራቸው ወደ ፊት ወጥተው በመድረኩ ፊት ራሳቸውን እንዲያሳውቁ ጠየቅሁ። በየምሽቱ ወደ ፊት በሚወጡት ሰዎች ብዛትና ማንነት እንደነቅ ነበር።

ከጠዋት የጸሎት ስብሰባዎቻችን በአንዱ የቤተ ክርስቲያኑ የታችኛው ክፍል ሞልቶ ነበር። ተነሥቼ ለሕዝቡ ጥቂት ማሳሰቢያዎች እየሰጠሁ ሳለ ያልተለወጠ አንድ ሰው፥ ነጋዴ፥ ወደ ስብሰባው ገባ። በፊቴ፥ ቆሜ እናገርበት ከነበረው ስፍራ አጠገብ መቀመጫ እስኪያገኝ ድረስ መጣ። ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ እንደ ተቀመጠ በጥይት እንደ ተመታ ያህል ከመቀመጫው ወደቀ። በሚያስፈራ ሁኔታ ተንፈራገጠ፤ አቃሰተም። ወደ መቀመጫው በር ቀረብ ብዬ ስመለከት ሙሉ በሙሉ የአእምሮ ሥቃይ እንደ ሆነ አየሁ።

ተጠራጣሪ የሆነ አንድ ሐኪም አጠገቡ ተቀምጦ ነበር። ከመቀመጫው ወጥቶ መጣና በዚህ ሁኔታ የተጨነቀውን ሰው መረመረው። ትርታውን ዳሰሰ፤ ሁኔታውንም ለጥቂት ደቂቃዎች መረመረ። ምንም አልተናገረም፤ ነገር ግን ዘወር ብሎ ሰገነቱን ደግፎ በያዘው ምሰሶ ላይ ራሱን አስደገፈ፤ ታላቅ መረበሽም አሳየ።

በኋላ እንደ ተናገረው፥ የአእምሮ ጭንቀት መሆኑን ወዲያውኑ አየ፤ ይህም ጥርጣሬውን ፈጽሞ አስወገደለት። ብዙም ሳይቆይ እርሱ ራሱ ተስፋ በሚሰጥ ሁኔታ ተለወጠ። በመቀመጫው ውስጥ ለወደቀው ሰው በጸሎት ተጋን፤ ከቤቱም ከመውጣቱ በፊት፥ እንደማምነው፥ ሥቃዩ አለፈለትና በክርስቶስ ደስ አለው።

በጣም ተወዳጅ ሰው የሆነ ነገር ግን ተጠራጣሪ የነበረ ሌላ ሐኪም ትንሽ ሴት ልጅና የምትጸልይ ሚስት ነበረችው። ምናልባት ስምንት ወይም ዘጠኝ ዓመት የሚሆናት ትንሿ ኤች—— በኃጢአት ጽኑ ወቀሳ ውስጥ ገባች፤ እናቷም ስለ ልጅቷ የአእምሮ ሁኔታ እጅግ ተጨነቀች። አባቷ ግን በመጀመሪያ እጅግ ተቆጣ። ሚስቱንም እንዲህ አላት፦ «የሃይማኖት ጉዳይ ለእኔ ከአቅሜ በላይ ነው። ፈጽሞ ልረዳው አልቻልሁም። ታዲያ ያቺ ትንሽ ልጅ በማስተዋል በኃጢአት እስክትወቀስ ድረስ ትረዳዋለች ትዪኛለሽ? አላምንም። ከዚህ የተሻለ አውቃለሁ። ልታገሠው አልችልም። አክራሪነት ነው፤ እብደት ነው።» የልጅቷ እናት ግን በጸሎት አጥብቃ ያዘች። ሐኪሙ እነዚህን ቃላት የተናገረው፥ እንደ ሰማሁት፥ በብዙ ቁጣ ነበር። ወዲያውኑም ፈረሱን ይዞ አንድን ታማሚ ለማየት ብዙ ማይሎች ሄደ። በመንገዱ ላይ ሳለ፥ በኋላ እንደ ተናገረው፥ ያ ጉዳይ አእምሮውን እንዲህ ያዘው፤ ሁሉም ለማስተዋሉ ተከፈተለት፤ በክርስቶስ የሆነው የመዳን ዕቅድ ሁሉ ለእርሱ እጅግ ግልጽ ሆኖለት አንድ ልጅ ሊረዳው እንደሚችል አየ። ቀድሞ እንዴት እንደዚያ የተሰወረ ሆኖ ይታየው እንደ ነበረ ተደነቀ። ስለ ትንሿ ኤች—— ለሚስቱ በተናገረው ነገር እጅግ ተጸጸተ፤ ቃሉን መልሶ ለመውሰድ ወደ ቤቱ ለመድረስ ቸኮለ። ብዙም ሳይቆይ ሌላ ሰው ሆኖ ወደ ቤቱ መጣ፤ በአእምሮው ውስጥ የሆነውን ለሚስቱ ነገራት፤ ውዲቱን ትንሿን ኤች—— ወደ ክርስቶስ እንድትመጣ አበረታታት፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም አባትና ልጅ ሁለቱም ትጉ ክርስቲያኖች ሆነው ብዙ ዘመን ኖረዋል፤ ብዙ መልካም ነገርም አድርገዋል።

ነገር ግን በዚህ መነቃቃት፥ እኔ እንዳወቅኋቸው እንደ ሌሎቹ ሁሉ፥ እግዚአብሔር በጽድቅ አንዳንድ የሚያስፈሩ ነገሮችን አደረገ። እዚያ በነበርሁበት ጊዜ በአንድ ሰንበት ከመድረኩ ወርደን ከቤተ ክርስቲያኑ ልንወጣ ስንል አንድ ሰው በችኮላ ወደ አቶ ጊሌትና ወደ እኔ መጥቶ አንድ ሰው በዚያ ሞቶ ስለ ወደቀ ወደ አንድ ስፍራ እንድንሄድ ጠየቀን። እኔ ከአንድ ሰው ጋር በመነጋገር ላይ ነበርሁና አቶ ጊሌት ብቻቸውን ሄዱ። ንግግሬን ስጨርስ ወደ አቶ ጊሌት ቤት ሄድሁ፤ እርሳቸውም ብዙም ሳይቆዩ ተመልሰው ይህን ሁኔታ ነገሩኝ። ሥራውን ሲቃወሙ የነበሩ ሦስት ሰዎች በዚያ የሰንበት ቀን ተገናኝተው ቀኑን ሲጠጡና በሥራው ሲሳለቁ አሳለፉት። ከእነርሱ አንዱ ድንገት ሞቶ እስኪወድቅ ድረስ በዚሁ ሁኔታ ቀጠሉ። አቶ ጊሌት ቤቱ ደርሰው ሁኔታው በተነገራቸው ጊዜ፥ «እነሆ! ያ ሰው በእግዚአብሔር እንደ ተመታና ወደ ሲኦል እንደ ተላከ ምንም ጥርጥር የለውም» አሉ። ጓደኞቹ የሚናገሩት አጡ። ምንም ሊሉ አልቻሉም፤ ይህን አስፈሪ የመለኮታዊ ቁጣ ምት በእርሱ ላይ ያመጣው የእነርሱ ምግባር እንደ ሆነ ለእነርሱ ግልጽ ነበርና።

ሥራው እየቀጠለ ሲሄድ የሕዝቡን ሁሉ ማለት ይቻላል ሰበሰበ። ከጠበቆች፥ ከነጋዴዎችና ከሐኪሞች እያንዳንዳቸው ማለት ይቻላል፥ ዋና ዋና ሰዎችም ከሞላ ጎደል ሁሉም፥ በእርግጥም የመንደሩ አዋቂ ሕዝብ ከሞላ ጎደል በሙሉ፥ በተለይም የአቶ ጊሌት ጉባኤ አባላት የነበሩት፥ ገቡ። ከመሄዴ በፊት እንዲህ አሉኝ፦ «ጉባኤዬን በተመለከተ ሺው ዓመት አሁኑኑ መጥቷል። ሕዝቤ ሁሉ ተለውጠዋል። ካለፈው ድካሜ ሁሉ ለጉባኤዬ ጨርሶ የሚስማማ አንድም ስብከት የለኝም፤ ሁሉም ክርስቲያኖች ናቸውና።» አቶ ጊሌት በኋላ እንደ ተናገሩት፥ በሮም ባሳለፍኋቸው ሃያ ቀናት ውስጥ በዚያች ከተማ አምስት መቶ ሰዎች ተለውጠዋል።

ይህ ሥራ እየገፋ በሄደበት ወቅት በዩቲካ ብዙ መነጋገር ተቀሰቀሰ፤ በዚያም የነበሩ አንዳንዶች በሮም የነበረውን ሥራ ለማሾፍ ያዘነበሉ ነበሩ። በሮም ይኖሩ የነበሩት አቶ ኤች—— እጅግ ታዋቂ ዜጋ ነበሩ፤ በሀብትም በዕውቀትም በዚያ ማኅበረሰብ ራስ ላይ የቆሙ ሆነው ይታዩ ነበር። ነገር ግን ተጠራጣሪ ነበሩ፤ ወይም የዩኒቴሪያንን አመለካከት ይዘው ነበር ብል ይሻል ይሆናል። እጅግ ግብረ ገባዊና የተከበሩ ሰው ነበሩ፤ ልዩ አመለካከታቸውንም ለማንም ብዙም ሳይናገሩ በጸጥታ ይዘው ነበር። በዚያ በሰበክሁበት የመጀመሪያው ሰንበት አቶ ኤች—— ተገኝተው ነበር፤ በኋላም እንደ ነገሩኝ በስብከቴ እጅግ ከመደነቃቸው የተነሣ ዳግመኛ ላለመሄድ ወሰኑ። ወደ ቤታቸው ሄደው ለቤተሰባቸው «ያ ሰው አብዷል፤ ከተማይቱን በእሳት ቢያቃጥላት እንኳ አይገርመኝም» አሉ። ለሁለት ሳምንት ያህል ከስብሰባው ቀሩ። በዚህ መካከል ሥራው ጥርጣሬያቸውን እስኪያደናግር ድረስ እጅግ ታላቅ ሆነ፤ እርሳቸውም በብርቱ ግራ መጋባት ውስጥ ገቡ።

በዩቲካ የአንድ ባንክ ፕሬዚዳንት ነበሩ፤ በየሳምንቱ የሚደረገውን የዳይሬክተሮች ስብሰባ ለመካፈልም ወደዚያ ይወርዱ ነበር። ከእነዚህ አጋጣሚዎች በአንዱ ከዳይሬክተሮቹ አንዱ በዚያ ያሉት ሁሉ የሚያብዱ ይመስል በሮም ስላለው ሁኔታ ይቀልድባቸው ጀመር። አቶ ኤች—— እንዲህ አሉ፦ «ክቡራን፥ የፈለጋችሁትን በሉ፤ በሮም ባለው ሁኔታ ውስጥ እጅግ አስደናቂ የሆነ አንድ ነገር አለ። በዚያ የምናየውን በእርግጥ ምንም ዓይነት የሰው ኃይል ወይም የንግግር ችሎታ አላስገኘውም። ልረዳው አልችልም። በቅርቡ ይበርዳል ትላላችሁ። አሁን በሮም ያለው የስሜት ብርታት በቅርቡ መብረዱ አይቀርም፤ አለዚያ ሕዝቡ ያብዳል። ነገር ግን ክቡራን፥» አሉ፥ «በውስጡ መለኮታዊ የሆነ ነገር ከሌለ በቀር ያንን የስሜት ሁኔታ በማናቸውም ፍልስፍና ማብራራት አይቻልም።»

አቶ ኤች—— ለሁለት ሳምንት ያህል ከስብሰባው ከቀሩ በኋላ፥ ጥቂቶቻችን አንድ ከሰዓት በኋላ እርሳቸውን የጸሎታችን ልዩ ርእስ ለማድረግ ተሰበሰብን። ጌታ ስለ እርሳቸው ስንጸልይ ብርቱ እምነት ሰጠን፤ ጌታም በነፍሳቸው ውስጥ እየሠራ እንደ ሆነ በልባችን ተረዳን። በዚያው ምሽት ወደ ስብሰባ መጡ። ወደ ቤቱ ሲገቡ፥ አቶ ጊሌት በመድረኩ ላይ ተቀምጠን ሳለን በሹክሹክታ «ወንድም ፊኒ፥ አቶ ኤች—— መጥተዋል። የሚያስቀይማቸውን ምንም ነገር እንደማትናገር ተስፋ አደርጋለሁ» አሉኝ። እኔም «አይ፥ ነገር ግን አልምራቸውም» አልሁ። በዚያ ዘመን ፈጽሞ ያለ ቅድመ ዝግጅት ለመስበክ እገደድ ነበር፤ ሐሳቤን አስቀድሜ ለማደራጀት የምወስደው አንድ ሰዓት እንኳ በሳምንት ውስጥ አልነበረኝምና።

ርእሴን መርጬ ሰበክሁ። ቃሉ በኃይል ያዘ፤ እኔም ተስፋ እንዳደረግሁትና እንዳሰብሁት አቶ ኤች——ንም ራሳቸውን በኃይል ያዛቸው። በስብሰባው መጨረሻ በዚያ ቀንና ምሽት የተለወጡ ሁሉ ወደ ፊት ወጥተው ራሳቸውን እንዲያሳውቁ የጠየቅሁት በዚያው ሌሊት ይመስለኛል፤ አቶ ኤች—— በእርጋታና በታላቅ አክብሮት ወደ ፊት ወጥተው ልባቸውን ለእግዚአብሔር እንደ ሰጡ ካሳወቁት አንዱ ነበሩ። ትሑትና ንስሐ የገቡ መሰሉ፤ እኔም በእውነት ወደ ክርስቶስ እንደ ተለወጡ ሁልጊዜ አምን ነበር።

በመንደሪቱና በዙሪያዋ ባለው አካባቢ የነበረው ሁኔታ፥ ማንም ሰው እግዚአብሔር በልዩና በአስደናቂ ሁኔታ በዚያ እንዳለ በሚሰማው ስሜት በፍርሃት ሳይዋጥ ወደ መንደሪቱ መግባት የማይችልበት ነበር። ለዚህ ምሳሌ እንዲሆን አንድ ገጠመኝ እተርካለሁ። የአውራጃው ሸሪፍ የሚኖረው በዩቲካ ነበር። በአውራጃው ውስጥ ሁለት የፍርድ ቤት ሕንፃዎች ነበሩ፤ አንዱ በሮም፥ ሌላውም በዩቲካ፤ ስለዚህ ቢ—— የሚባለው ሸሪፍ በሮም ብዙ ጉዳይ ነበረው። በሮም ስላለው ሁኔታ እንደ ሰማ፥ እርሱና ሌሎችም በሚኖርበት ሆቴል ስለ ሰሙት ነገር ብዙ ይስቁ እንደ ነበር በኋላ ነገረኝ።

ነገር ግን አንድ ቀን ወደ ሮም መሄድ አስፈላጊ ሆነበት። በዚያ ጉዳይ በማግኘቱ ደስ እንዳለው ተናገረ፤ ሰዎች ይህን ያህል የሚያወሩለት ነገር ምን እንደ ሆነና በሮም ያለው ሁኔታ በእውነት ምን እንደሚመስል በዓይኑ ለማየት ይፈልግ ነበርና። እንደ ነገረኝ፥ አሮጌው ቦይ ተብሎ የሚጠራውን፥ ከከተማዪቱ አንድ ማይል ያህል የሚርቀውን ስፍራ እስኪሻገር ድረስ፥ በአእምሮው ላይ ምንም የተለየ ስሜት ሳይኖር በአንድ ፈረስ በሚጎተት የበረዶ ተንሸራታች ጋሪው እየነዳ ሄደ። አሮጌውን ቦይ እንደ ተሻገረ ወዲያውኑ አንድ እንግዳ ስሜት፥ ሊያራግፈው የማይችለው ጥልቅ ፍርሃት እንደ ወረደበት ተናገረ። እግዚአብሔር አየሩን ሁሉ እንደ ሞላው ተሰማው። ይህም ወደ መንደሪቱ እስኪደርስ ድረስ በመንገዱ ሁሉ እየጨመረ እንደ ሄደ ተናገረ። በአቶ ኤፍ—— ሆቴል ቆመ፤ የፈረስ ጠባቂውም ወጥቶ ፈረሱን ተቀበለው። የፈረስ ጠባቂው ልክ እርሱ ራሱ እንደ ተሰማው ለመናገር የፈራ መስሎ እንደ ታየው አስተዋለ አለ። ወደ ቤቱ ገብቶ ጉዳይ የነበረውን ሰው በዚያ አገኘው። ሁሉም በግልጽ እጅግ ተነክተው ስለ ነበር ጉዳያቸውን መከታተል እንኳ እንደ ተሳናቸው ተናገረ። በዚያ በቆየበት በአጭሩ ጊዜ ውስጥ እንዳያለቅስ ብዙ ጊዜ ከጠረጴዛው በድንገት ተነሥቶ ወደ መስኮቱ በመሄድ ወደ ውጭ ማየትና ትኩረቱን ለማዞር መሞከር እንደ ነበረበት ተናገረ። ሌላውም ሰው ሁሉ ልክ እንደ እርሱ የተሰማው መስሎ እንደ ታየው አስተዋለ አለ። እንዲህ ያለ ፍርሃት፥ እንዲህ ያለ ግርማ፥ እንዲህ ያለ ሁኔታ ከዚያ በፊት ፈጽሞ አስቦት አያውቅም ነበር። ጉዳዩን በችኮላ ጨርሶ ወደ ዩቲካ ተመለሰ፤ ነገር ግን እርሱ ራሱ እንዳለው፥ ከዚያ በኋላ በሮም ስለ ነበረው ሥራ በቀላሉ ዳግመኛ ላይናገር ነው። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በዩቲካ ተስፋ በሚሰጥ ሁኔታ ተለወጠ፤ ሁኔታውንም በተገቢው ስፍራ እተርካለሁ።

ከሮም በስተ ሰሜን ምሥራቅ ሁለት ወይም ሦስት ማይል ያህል ርቃ ስለምትገኘው ራይትስ ሰትልመንት ስለምትባል መንደር ቀደም ብዬ ተናግሬአለሁ። መነቃቃቱ በዚያም በኃይል ሠራ፤ አብዛኞቹን ነዋሪዎችም ለወጠ።

በሮም ጥቅም ላይ የዋሉት ዘዴዎች ቀደም ብዬ የተጠቀምሁባቸው ናቸው እንጂ ሌላ አልነበሩም፤ ስብከት፥ የሕዝብ፥ የኅብረትና የግል ጸሎት፥ ምክርና የግል ውይይት። በሮም እንደ ታየው ያለ ይህን ያህል ጥልቅና ሁሉን አቀፍ የሆነ ሃይማኖታዊ ስሜት፥ አንድም የሥርዓት መጓደል ወይም ሁከት ወይም አክራሪነት ወይም ተቃውሞ የሚያስነሣ ምንም ነገር ሳይኖርበት ማሰብ አስቸጋሪ ነው። ከዚያ መነቃቃት የተለወጡ ብዙዎች በአገሪቱ ሁሉ ተበትነው እስከ ዛሬ በሕይወት አሉ፤ በእነዚያም ስብሰባዎች ፍጹም ሥርዓትና ግርማ እንደ ሰፈነ፥ የሚያሳዝን ነገር ሁሉ እንዳይከሰትም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደ ተደረገ ሊመሰክሩ ይችላሉ።

የመንፈሱ ሥራ እጅግ ድንገተኛ፥ እጅግ ኃያልና እጅግ የሚያጥለቀልቅ ስለ ነበር፥ የሕዝቡን የመሰማት ችሎታ በቶሎ ሊያደክምና የኋሊት መመለስን ሊያስከትል የሚችል የማይፈለግ የስሜት ፍንዳታ እንዳይከሰት፥ ስብሰባዎቹን ሁሉ በመምራት ረገድ ታላቅ ጥንቃቄና ጥበብ መጠቀም አስፈላጊ ሆነ። ነገር ግን እውነታውን የሚያውቅ ሁሉ እንደሚያውቀው፥ ምንም ዓይነት የኋሊት መመለስ አልተከተለም። ለብዙ ወራት፥ እንዲያውም ከዚያ በኋላ ከአንድ ዓመት በላይ እንደ ሆነ አምናለሁ፥ በዓመቱ ወቅቶች ሁሉ የፀሐይ መውጫ የጸሎት ስብሰባ ያካሂዱ ነበር፤ ይህም በብዙ ሰዎች የሚሞላና አንድ የጸሎት ስብሰባ ሊኖረው በሚችለው መጠን እጅግ የሚማርክ ነበር። የሕዝቡ የሥነ ምግባር ሁኔታ እጅግ ከመለወጡ የተነሣ አቶ ጊሌት ያው ስፍራ አይመስልም እያሉ ብዙ ጊዜ ይናገሩ ነበር። የቀረው ኃጢአት ሁሉ ራሱን ለመደበቅ ተገደደ። በዚያ ምንም ዓይነት ግልጽ ብልግና ለአፍታ እንኳ ሊታገሥ አይችልም ነበር። በሮም የሆነውን በጣም ደካማ ንድፍ ብቻ ነው የሰጠሁት። በዚያ መነቃቃት ውስጥ የተጨናነቁትን ልብ የሚነኩ ገጠመኞች ሁሉ በታማኝነት መግለጽ በራሱ አንድ ጥራዝ መጽሐፍ ይሆናል።

በዚህ ጊዜ በሮም ስለ ሰፈነው የጸሎት መንፈስ ጥቂት ቃላት ልናገር ይገባኛል። ከአቶ ጊሌት ጋር መድረክ ለመለዋወጥ ከዌስተርን የወረድሁት ቅዳሜ ዕለት ይመስለኛል፤ ከሰዓት በኋላ ቤተ ክርስቲያኒቱን በአምልኮ ቤታቸው በጸሎት ስብሰባ አገኘኋቸው። እግዚአብሔር ጸሎትን ለመመለስ ተስፋ የሰጠባቸውን ሁኔታዎች ከፈጸሙ፥ በተለይም ልመናቸውን እንደሚመልስ በመጠበቅ ትርጉም ካመኑ፥ ጸሎትን ወዲያውኑ እንደሚመልስ እንዲገነዘቡ ለማድረግ ጣርሁ። ቤተ ክርስቲያኒቱ በንግግሬ እጅግ እንደ ተሳበች፥ ፊታቸውም ለጸሎታቸው መልስ ለማየት ብርቱ ናፍቆት እንዳላቸው እንደሚያሳይ አስተዋልሁ። በስብሰባው መገባደጃ ላይ እንዲህ ማለቴን አስታውሳለሁ፦ «በዚህ ከሰዓት በኋላ መንፈሱን ወዲያውኑ እንዲያፈስ በእምነት ጸሎት ወደ እግዚአብሔር በአንድነት ብትጸልዩ፥ ሊላክ በሚችለው በፈጣኑ መልእክተኛ ከአልባኒ መልእክት ከምታገኙ ይልቅ ከሰማይ መልስ ቶሎ እንደምትቀበሉ በእውነት አምናለሁ።»

ይህን በታላቅ አጽንኦት ተናገርሁት፤ ተሰምቶኛልም፤ ሕዝቡም ለጸሎት የሚሰጠውን አፋጣኝ መልስ በተመለከተ በገለጽሁት ቁም ነገረኛነትና እምነት እንደ ደነገጡ አስተዋልሁ። እውነቱ፥ ይህን ውጤት ለጸሎት መልስ ሆኖ ብዙ ጊዜ አይቼው ስለ ነበር ያንን ንግግር ያለ አንዳች ጥርጣሬ ተናገርሁት። በዚያን ጊዜ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ማንም ምንም አልተናገረም፤ ነገር ግን ሥራው ከጀመረ በኋላ ሦስት ወይም አራት የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ወደ አቶ ጊሌት የጥናት ክፍል ጎራ እንዳሉ፥ ስለ ጸሎት ፈጣን መልስ በተነገረው ነገር እጅግ ተነክተው እግዚአብሔርን በቃሉ ለመያዝና ገና እየተናገሩ ሳሉ ይመልስ እንደ ሆነ ለማየት እንደ ወሰኑ ሰማሁ። ከእነርሱ አንዱ፥ አፋጣኝ መልስ እንዲሰጣቸው ለመጸለይ በእግዚአብሔር መንፈስ አስደናቂ እምነት እንደ ተሰጣቸው በኋላ ነገረኝ፤ ደግሞም «መልሱ፥ ልንልከው በምንችለው በፈጣኑ መልእክተኛ ከአልባኒ መልስ ልናገኝ ከምንችለው ይልቅ በእርግጥ ቶሎ መጣ» ብሎ አከለ።

በእርግጥ ከተማይቱ በጸሎት ተሞልታ ነበር። ወደ የትም ብትሄድ የጸሎት ድምፅ ትሰማ ነበር። በመንገድ ላይ ብታልፍ፥ ሁለት ወይም ሦስት ክርስቲያኖች በአጋጣሚ አብረው ቢገኙ ይጸልዩ ነበር። በተገናኙበት ሁሉ ይጸልዩ ነበር። ያልተለወጠ ኃጢአተኛ ባለበት ሁሉ፥ በተለይም ተቃውሞ የሚያሳይ ከሆነ፥ እርሱን የጸሎታቸው ልዩ ርእስ ለማድረግ የተስማሙ ሁለት ወይም ሦስት ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ታገኝ ነበር።

በሮም የምትኖር የአሜሪካ ጦር ሠራዊት መኰንን ሚስት የሆነች፥ የዚያም ስፍራ ታዋቂ ዜጋ ልጅ የሆነች አንዲት ሴት ነበረች። ይህች ሴት በሥራው ላይ ብዙ ተቃውሞ አሳየች፤ እንደ ተወራውም በሥራው ላይ አንዳንድ ብርቱ ነገሮችን ተናገረች፤ ይህም የጸሎት ልዩ ርእስ እንድትሆን ምክንያት ሆነ። ልተርከው ያለሁት ነገር ከመፈጸሙ ጥቂት ቀደም ብሎ ብቻ ነበር ይህ ወደ ጆሮዬ የደረሰው። በዚህ ጉዳይ፥ በስፍራው ታዋቂ ተጽዕኖ ያላት ሰው በመሆኗ፥ አንዳንድ ዋና ዋና ሴቶች ይህችን ሴት የጸሎታቸው ልዩ ርእስ እንዳደረጓት አምናለሁ። የተማረች፥ ብርቱ ባሕርይና ጠንካራ ፈቃድ ያላት ሴት ነበረች፤ ስለዚህ ተቃውሞዋ መሰማቱ የታወቀ ነው። ነገር ግን ይህ እንደ ታወቀና በተለይ ለእርሷ የጸሎት መንፈስ እንደ ተሰጠ ወዲያውኑ ማለት ይቻላል፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ጉዳይዋን በእጁ ያዘ። ስለ እርሷ ከሰማሁ በኋላ ወዲያውኑ ማለት ይቻላል፥ ምናልባትም ነገሩ ወደ ጆሮዬ በደረሰበት በዚያው ቀን ምሽት፥ ስብሰባው ተበትኖ ሕዝቡ ከሄደ በኋላ፥ አቶ ጊሌትና እኔ በኃጢአት ወቀሳ እጅግ ከተዋረዱ አንዳንድ ሰዎች ጋር እየተነጋገርን እስከ መጨረሻው ቀረን። እነርሱ ሲሄዱና እኛም ልንሄድ ስንል፥ ስንወጣ የቤተ ክርስቲያኑ ጠባቂ በችኮላ ወደ እኛ መጥቶ «በዚያ ወንበር ውስጥ መውጣት የማትችል አንዲት ሴት አለች፤ ምንም ማድረግ አትችልም። መጥታችሁ አታዩአትምን?» አለ። ተመለስን፤ እነሆም፥ ስለ እርሷ የተናገርሁላት ይህች ሴት በኃጢአት ወቀሳ ፈጽሞ ተውጣ በወንበሩ ውስጥ ወድቃ ነበር። ወንበሩ ሞልቶ ነበር፤ እርሷም ከወጡት ሌሎች ጋር ለመውጣት ሞክራ ነበር፤ ነገር ግን የመጨረሻዋ ወጪ ስለ ነበረች መቆም እንዳቃታት አገኘች፤ ወደ ወለሉም ወደቀች፤ ይህንም ከእርሷ ቀድመው የወጡት ሳያስተውሉ ሆነ። ከእርሷ ጋር ጥቂት ተነጋገርን፤ ጌታም በማይነገር የኃጢአት ወቀሳ እንደ መታት አገኘን። ከእርሷ ጋር ከጸለይሁና ልቧን ወዲያውኑ ለክርስቶስ እንድትሰጥ በብርቱ ካሳሰብኋት በኋላ ትቻት ሄድሁ፤ አቶ ጊሌትም ወደ ቤቷ እንደ ረዷት አምናለሁ። ቤቷ ጥቂት እርምጃዎች ብቻ ነበር የሚርቀው። በኋላ እንደ ሰማነው፥ ቤቷ እንደ ደረሰች ብቻዋን ወደ አንድ ክፍል ገብታ ሌሊቱን አሳለፈች። ብርድ የነበረበት የክረምት ሌሊት ነበር። በሩን ቈልፋ ሌሊቱን ብቻዋን አሳለፈች።

በማግሥቱ በክርስቶስ ተስፋ እንዳገኘች ተናገረች፤ እኔ እስከማውቀውም ድረስ በእውነት እንደ ተለወጠች አሳየች።

በዚህ መነቃቃት ወቅት የወይዘሮ ጊሌትን መለወጥም መጥቀስ ያለብኝ ይመስለኛል። የአሜሪካ ቦርድ እንዲቋቋም ምክንያት ከሆኑት ቅንዓታቸው ከታወቀ ወጣቶች አንዱ የነበረው የሚስዮናዊው ሚልስ እኅት ነበረች። ከባሏ በብዙ ዓመት የምታንስ ውብ ሴት ነበረች፤ የእርሱም ሁለተኛ ሚስት ነበረች። አቶ ጊሌት ከማግባታቸው በፊት ለብዙ ሳምንታት በኃጢአት ወቀሳ ሥር ቆይታ፥ ልታብድ ተቃርባ ነበር። በትክክል የማስታውስ ከሆነ፥ ከተመረጡት አንዷ እንዳልሆነችና ለእርሷ መዳን እንደሌለ ይሰማት ነበር። በሮም መነቃቃቱ ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ በጌታ መንፈስ እንደ ገና በኃይል ተወቀሰች።

የተራቀቀችና አለባበስ የምትወድ ሴት ነበረች፤ በጣም የተለመደ እንደ ሆነውም በራሷና በሰውነቷ ላይ አንዳንድ ጥቃቅን ጌጣጌጦችን ታደርግ ነበር፤ ይሁን እንጂ በመንገዷ ላይ እንቅፋት ይሆናል ብዬ ላስበው የምችለው ምንም ነገር አልነበረም። እንግዳዋ በመሆኔ ወቀሳዋ እየጨመረ ሲሄድ ደጋግሜ አነጋገርኋት፤ ነገር ግን አለባበስ መውደዷ ወደ እግዚአብሔር እንዳትለወጥ ሊያግዳት ይችላል የሚል ሐሳብ ፈጽሞ ወደ አእምሮዬ አልመጣም። ነገር ግን ሥራው እጅግ ኃያል እየሆነ ሲሄድ ጭንቀቷ አስደንጋጭ ሆነ፤ አቶ ጊሌትም ቀደም ሲል በእርሷ ላይ የሆነውን ስለሚያውቁ፥ ከዓመታት በፊት ወደ ነበረችበት ወደዚያ የተስፋ መቍረጥ ሁኔታ እንዳትገባ እጅግ ሰጉ። እርሷም ለምክር ራሷን በእኔ ላይ ጣለች። ወደ ቤቱ በገባሁ ቍጥር ማለት ይቻላል ወደ እኔ መጥታ እንድጸልይላት ትለምነኝና ጭንቀቷ ልትሸከመው ከምትችለው በላይ እንደ ሆነ ትነግረኝ ነበር። በግልጽ በፍጥነት ወደ ተስፋ መቍረጥ እየሄደች ነበር፤ ነገር ግን በእኔ ላይ ከመጠን በላይ እንደምትደገፍ አየሁ፤ ስለዚህ ከእርሷ ለመራቅ ሞከርሁ።

ይህ እንዲህ ቀጠለ፤ አንድ ቀንም ወደ ቤቱ ገብቼ ወደ ጥናት ክፍሉ ዞርሁ። እንደ ልማዷ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ፊቴ ቆማ እንድጸልይላት ትለምነኝና ለእርሷ መዳን እንደሌለ ታማርር ጀመር። እኔም በድንገት ተነሥቼ ከእርሷ ጋር ሳልጸልይ ትቻት ሄድሁ፤ በጸሎቴ ላይ ስለምትደገፍ ስለ እርሷ መጸለዬ ምንም ጥቅም እንደሌለው ነገርኋት። ይህን ባደረግሁ ጊዜ የምትዝል መስላ ወደቀች። ቢሆንም ብቻዋን ትቻት ከጥናት ክፍሉ በድንገት ወደ እንግዳ መቀበያው ክፍል ሄድሁ። በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ፊቷ ሁሉ እያበራ መተላለፊያውን አቋርጣ እየሮጠች ወደ እንግዳ መቀበያው ክፍል መጥታ እንዲህ ብላ ጮኸች፦ «ወይ አቶ ፊኒ! አዳኙን አገኘሁት! አዳኙን አገኘሁት! እንዳልለወጥ መንገዴን የዘጋው በፀጉሬ ላይ ያሉት ጌጣጌጦች አይመስሉህምን? ስጸልይ እነርሱ ወደ ፊቴ እንደሚመጡ አገኘሁ፤ እኔም እንደ መሰለኝ እንድተዋቸው እፈተን ነበር። ነገር ግን» አለች፥ «ጥቃቅን ነገሮች እንደ ሆኑና እግዚአብሔር ስለ እንደዚህ ያሉ ጥቃቅን ነገሮች ግድ እንደማይለው አሰብሁ። ይህ የሰይጣን ፈተና ነበር። ነገር ግን ልቤን ለእግዚአብሔር ለመስጠት በሞከርሁ ቍጥር ያደረግኋቸው ጌጣጌጦች ያለማቋረጥ ወደ አእምሮዬ ይመጡ ነበር። በድንገት ትተኸኝ ስትሄድ» አለች፥ «ተስፋ ወደ መቍረጥ ተገፋሁ። ራሴን ወደ ታች ጣልሁ፤ እነሆም፥ እነዚህ ጌጣጌጦች እንደ ገና ወደ ፊቴ መጡ፤ እኔም፦ ‹እነዚህ ነገሮች ዳግመኛ እንዲመጡ አልፈቅድም፤ ለዘላለም ከእኔ አስወግዳቸዋለሁ› አልሁ።» ደግሞም አለች፦ «ተውኋቸው፤ በመዳኔ መንገድ ላይ እንደ ቆሙ ነገሮችም ጠላኋቸው። እነርሱን ለመተው ቃል እንደ ገባሁ ወዲያውኑ ጌታ ራሱን ለነፍሴ ገለጠ፤ ወይ!» አለች፥ «ይህን ከዚህ በፊት ፈጽሞ ያልተረዳሁት ለምን እንደ ሆነ ይገርመኛል። ቀደም ሲል በወቀሳ ሥር ሳለሁ በእውነት ዋናው ችግሬ ይኸው ነበር፤ አለባበስ መውደዴ፤ እኔም አላወቅሁትም ነበር።»

ቀዳሚ ቀጣይ