ምዕራፍ 4 · 23 ደቂቃ ንባብ · 30 ደቂቃ ማዳመጥ
የማርች ወር
ማርች 1
ለተጣሉት ደስታ
«በቃሉ የምትንቀጠቀጡ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የሚጠሉአችሁ ስለ ስሜም የሚያወጡአችሁ ወንድሞቻችሁ። እግዚአብሔር ይክበር ብለዋል፤ እርሱ ግን ለደስታችሁ ይገለጣል፥ እነርሱም ያፍራሉ» ኢሳይያስ 66:5
ይህ ቃል ምናልባት ይህን ትንሽ የተስፋዎች መጽሐፍ ከሚያነቡ ከሺህ አንዱን እንኳ ላይመለከት ይችላል፤ ጌታ ግን ያን አንዱን በእንደዚህ ያሉ ቃላት ያጽናናዋል። ከሚወዱት ማኅበር ያለ አግባብ ለተጣሉት ሁሉ እንጸልይ። ጌታ ለደስታቸው ይገለጥላቸው!
ቃሉ የሚመለከተው በጌታ ቃል ለሚንቀጠቀጡ በእውነት ጸጋን ለተቀበሉ ሰዎች ነው። እነዚህ በወንድሞቻቸው ተጠሉ፤ በመጨረሻም ስለ ታማኝነታቸውና ስለ ቅድስናቸው ተጣሉ። ይህ እጅግ መራራ ሆኖባቸው መሆን አለበት፤ መጣላቸው በሃይማኖት ስም፥ ደግሞም እግዚአብሔርን ለማክበር ነው ተብሎ መፈጸሙ ይበልጥ መራራ አደረገው። በእግዚአብሔር ስም ለዲያብሎስ የሚሠራው ሥራ እንዴት ብዙ ነው! የጥንቱ እባብ በንክሻው ላይ መርዝ ለመጨመር የእግዚአብሔርን ስም መጠቀሙ የተንኰሉ አንድ ምሳሌ ነው።
ጌታ ስለ እነርሱ መገለጡ የተሰደዱት ሕዝቡ ተስፋ ነው። እርሱ ለመረጣቸው ጠበቃና ተከላካይ ሆኖ ይገለጣል፤ እንዲህ ሲያደርግም እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ግልጥ መዳን፥ ለአስጨናቂዎቻቸውም እፍረት ይሆናል። አቤቱ ጌታ ሆይ፥ ሰዎች ለሚያላግጡባቸው ይህን ቃል ፈጽምላቸው!
ማርች 2
ሹክ ሳይሉ መስጠት
«አንተ ግን ምጽዋት ስታደርግ ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ቀኝህ የምታደርገውን ግራህ አትወቅ፤ በስውር የሚያይ አባትህም ራሱ በግልጥ ይከፍልሃል» ማቴዎስ 6:3,4
ሰዎች እንዲያዩአቸው ለድሆች ለሚሰጡ ምንም ተስፋ አልተሰጠም። ዋጋቸውን ወዲያው ተቀብለዋል፤ ሁለት ጊዜ ይከፈለናል ብለው መጠበቅ አይችሉም።
ልግስናችንን እንሰውር፤ — አዎን፥ ከራሳችንም እንኳ እንሰውረው። ምግብህን በየጊዜው መብላትህን ከምታስተውለው በላይ ድሆችን መርዳትህን እንዳታስተውል፥ እንደ ተራ ነገር አዘውትረህ አብዝተህም ስጥ። «እንዴት ለጋስ ነኝ!» ብለህ ለራስህ እንኳ ሹክ ሳትል ምጽዋትህን አድርግ። በዚህ መንገድ ራስህን ለመሸለም አትሞክር። ነገሩን ማየትን፥ መመዝገብንና ዋጋ መክፈልን ፈጽሞ ለማይዘነጋው ለእግዚአብሔር ተወው። በስውር በቸርነቱ የሚተጋ ሰው ብፁዕ ነው፤ በማይታወቀው ደግነቱ ልዩ ደስታ ያገኛል። ይህ በስውር ሲበላ ከነገሥታት ግብዣ ይልቅ የሚጣፍጥ እንጀራ ነው። ዛሬ በዚህ በሚያስደስት ቅንጦት ራሴን እንዴት ላስደስት እችላለሁ? እውነተኛ የርኅራኄ ግብዣና የነፍስ ፍሰት ይኑረኝ።
በዚህም ሆነ በሚመጣው ዓለም ጌታ ራሱ በስውር ምጽዋት የሚሰጠውን ሰው ዋጋ በግሉ ይከፍለዋል። ይህም በራሱ መንገድና ጊዜ ይሆናል፤ እጅግ የተሻለውንም ይመርጣል። ይህ ተስፋ ምን ያህል ትርጉም እንዳለው ለመግለጥ ዘላለም ያስፈልጋል።
ማርች 3
ለጥፋት አይተወንም
«ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም» መዝሙር 16:10
ይህ ቃል ትክክለኛ ፍጻሜውን በጌታ ኢየሱስ አግኝቷል፤ ነገር ግን በመጠኑ ልዩነት በእርሱ ላሉት ሁሉ ደግሞ ይሠራል። ነፍሳችን በተለየው ሁኔታ አትቀርም፤ ሥጋችንም መበስበስን ቢያይ እንኳ እንደገና ይነሣል። በዚህ ጊዜ የአንባቢዎቻችንን አሳብ ልንስብበት የምንወደው ግን ከተለየው አተገባበር ይልቅ አጠቃላዩን ትርጉም ነው።
በመንፈስ እጅግ ዝቅ ብለን ወደ ሲኦል ጥልቅ የተጣልን እስኪመስለን ድረስ እንወርድ ይሆናል፤ ነገር ግን በዚያ አንተውም። በልብ፥ በነፍስና በአእምሮ በሞት ደጅ ያለን ልንመስል እንችላለን፤ ነገር ግን በዚያ መቆየት አንችልም። በደስታና በተስፋ በኩል ያለው ውስጣዊ ሞታችን እጅግ ሊራመድ ይችላል፤ ነገር ግን የጨለማ ተስፋ መቍረጥ ወደሆነው ፍጹም መበስበስ እስኪደርስ ድረስ ወደ ሙሉ ውጤቱ ሊሄድ አይችልም። እጅግ ዝቅ ልንል እንችላለን፥ ጌታ ከሚፈቅደው በታች ግን አይደለም፤ በጥርጥር የታችኛው እስር ቤት ለጊዜው ልንቆይ እንችላለን፥ በዚያ ግን አንጠፋም። ሌሊቱ እጅግ በጨለመ ጊዜ እንኳ የተስፋ ኮከብ ገና በሰማይ አለ። ጌታ አይረሳንም፥ ለጠላትም አሳልፎ አይሰጠንም። በተስፋ እናርፍ። የምንገናኘው ምሕረቱ ለዘላለም ከሆነው ጋር ነው። በእርግጥ ከሞት፥ ከጨለማና ከተስፋ መቍረጥ ወደ ሕይወት፥ ወደ ብርሃንና ወደ ነጻነት ገና እንነሣለን።
ማርች 4
እግዚአብሔርን አክብር
«የሚያከብሩኝን አከብራለሁ» 1ኛ ሳሙኤል 2:30
የእግዚአብሔርን ክብር የሕይወቴ ታላቅ ዓላማና የአካሄዴ መመሪያ አደርገዋለሁን? እንዲህ ከሆነ እርሱ ያከብረኛል። ለጊዜው ከሰው ምንም ክብር ላልቀበል እችላለሁ፤ እግዚአብሔር ግን ራሱ እጅግ በሚሠራ መንገድ ክብርን ያጐናጽፈኛል። በመጨረሻ ስለ ኅሊና ብሎ ለመዋረድ ፈቃደኛ መሆን ወደ ክብር የሚያደርስ እጅግ የተረጋገጠ መንገድ መሆኑ ይታወቃል።
ዔሊ ቤተ ሰቡን በመልካም በመምራት ጌታን አላከበረም፥ ልጆቹም ለተቀደሰው ሹመታቸው በሚገባ ጠባይ ጌታን አላከበሩም፤ ስለዚህ ጌታ አላከበራቸውም፥ ነገር ግን ሊቀ ክህነትን ከቤተ ሰባቸው ወሰደ፥ ከዘራቸውም በማንም ፋንታ ብላቴናውን ሳሙኤልን በምድሪቱ ላይ ገዥ አደረገው። ቤተ ሰቤ እንዲከበር ብወድ፥ ጌታን በነገር ሁሉ ማክበር አለብኝ። እግዚአብሔር ክፉዎች ዓለማዊ ክብርን እንዲያገኙ ሊፈቅድ ይችላል፤ ራሱ የሚሰጠውን ማዕረግ ግን፥ ይኸውም ክብርን፥ ምስጋናንና የማይጠፋነትን፥ በቅዱስ መታዘዝ እርሱን ለማክበር ለሚጠነቀቁ ያስቀምጣል።
ጌታን ለማክበር ዛሬ ምን ማድረግ እችላለሁ? በአፌ ምስክርነትና በተግባራዊ መታዘዜ ክብሩን አስፋፋለሁ። ደግሞም በሀብቴና አንዳች ልዩ አገልግሎት በማቅረብ አከብረዋለሁ። እርሱ ያከብረኛልና እንዴት እንደማከብረው ተቀምጬ ላስብ።
ማርች 5
የቤት በረከት
«የጻድቃንን ቤት ይባርካል» ምሳሌ 3:33
ጻድቁ ጌታን ይፈራል፤ ስለዚህ እርሱንና ቤተ ሰቡን የሚሸፍነው ጣራ እንኳ ሳይቀር በመለኮታዊ ጥበቃ ሥር ይሆናል። ቤቱ የፍቅር መኖሪያ፥ የቅዱስ ሥልጠና ትምህርት ቤትና የሰማያዊ ብርሃን ስፍራ ነው። በውስጡ የጌታ ስም ዕለት ዕለት በአክብሮት የሚጠራበት የቤተ ሰብ መሠዊያ አለ። ስለዚህ ጌታ መኖሪያውን ይባርካል። ትሑት ጎጆ ወይም ታላቅ ቤተ መንግሥት ሊሆን ይችላል፤ የጌታ በረከት የሚመጣው ግን ስለ ነዋሪው ጠባይ እንጂ ስለ ቤቱ ስፋት አይደለም።
ጌታውና እመቤቲቱ እግዚአብሔርን የሚፈሩ የሆኑበት ቤት እጅግ የተባረከ ነው፤ ነገር ግን ወንድ ወይም ሴት ልጅ፥ አገልጋይም እንኳ በቤተ ሰቡ ሁሉ ላይ በረከትን ሊያመጣ ይችላል። ጌታ ብዙ ጊዜ በእርሱ ዘንድ ጻድቃን ሆነው ስለሚቆጠሩ፥ ጸጋውም ጻድቃን ስላደረጋቸው በውስጡ ስላሉ አንድ ወይም ሁለት ሰዎች ብሎ ቤተ ሰብን ይጠብቃል፥ ያበለጽጋል፥ ይመግባልም። ወዳጆች ሆይ፥ የቢታንያ እኅቶች እንዳደረጉት ኢየሱስን ዘወትር እንግዳችን እናድርገው፤ ያን ጊዜም በእውነት እንባረካለን።
በነገር ሁሉ ጻድቃን እንድንሆን እንጠንቀቅ — በንግዳችን፥ በሌሎች ላይ በምንሰጠው ፍርድ፥ ለጎረቤቶቻችን በምናደርገው አያያዝና በግል ጠባያችን። ጻድቅ አምላክ ዓመፀኛ ሥራን ሊባርክ አይችልም።
ማርች 6
የድሀ አደጎች ጠባቂ
«ድሀ አደጉ በአንተ ምሕረትን ያገኛልና» ሆሴዕ 14:3
ይህ ሌላውን መታመኛ ሁሉ ጥሎ በጌታ ብቻ ለመደገፍ እጅግ መልካም ምክንያት ነው። ልጅ ያለ ተፈጥሮአዊ ጠባቂው ሲቀር አምላካችን ገብቶ ጠባቂው ይሆናል፤ እንዲሁም ሰው የሚደገፍበትን ሁሉ ሲያጣ ራሱን በሕያው እግዚአብሔር ላይ ሊጥልና የሚያስፈልገውን ሁሉ በእርሱ ሊያገኝ ይችላል። ድሀ አደጎች በእግዚአብሔር አባትነት ላይ ይጣላሉ፥ እርሱም ያዘጋጅላቸዋል። የእነዚህ ገጾች ጸሐፊ በእግዚአብሔር ባዶ ክንድ ላይ መንጠልጠል ምን እንደ ሆነ ያውቃል፤ በማይታየው ነገር ግን ዘወትር ሕያው በሆነው አምላክ እንደ መታመን በእውነታ የተደገፈ ወይም በውጤቱ ዋጋው የሚከፈል መታመን እንደሌለ በፈቃዱ ይመሰክራል።
አባት ያላቸው አንዳንድ ልጆች በአባታቸው ምክንያት እምብዛም አልተጠቀሙም፤ ከእግዚአብሔር ጋር ያሉ ድሀ አደጎች ግን ባለጠጎች ናቸው። በምድር ያሉ ደጋፊዎች ሁሉ ኖረውህ እግዚአብሔር ከሚጠፋህ ይልቅ እግዚአብሔር ኖሮህ ሌላ ወዳጅ ባይኖርህ ይሻላል። ፍጡርን ማጣት ያማል፤ ነገር ግን ጌታ ለእኛ የምሕረት ምንጭ ሆኖ እስካለ ድረስ በእውነት ድሀ አደጎች አይደለንም። አባት የሌላቸው ልጆች ይህን የዛሬ ጠዋት የጸጋ ቃል ይዘው ይማልዱ፤ የሚታየውን ድጋፍ ያጡ ሁሉ ደግሞ እንዲሁ ያድርጉ። ጌታ ሆይ፥ በአንተ ምሕረትን ላግኝ! ይበልጥ ችግረኛና ረዳት የሌለኝ በሆንሁ መጠን፥ ይበልጥ በመተማመን ወደ አፍቃሪ ልብህ እማልዳለሁ።
ማርች 7
ከሰንሰለት ነጻ
«እግዚአብሔር የታሰሩትን ይፈታል» መዝሙር 146:7
እርሱ አድርጎታል። ዮሴፍን፥ በግብፅ የነበረውን እስራኤልን፥ ምናሴን፥ ኤርምያስን፥ ጴጥሮስንና ሌሎችን ብዙዎች አስቡ። አሁንም ሊያደርገው ይችላል። የናሱን መወርወሪያ በቃል ይሰብራል፥ የብረቱንም እግር ብረት በአንድ እይታ ይቈርጣል። አሁንም እያደረገው ነው። በሺህ ስፍራዎች የተጨነቁ ወደ ብርሃንና ወደ ሰፊ ስፍራ እየወጡ ነው። ኢየሱስ ለታሰሩት መፈታትን ዛሬም ያውጃል። በዚህች ሰዓት በሮች እየተከፈቱ፥ እግር ብረቶችም ወደ መሬት እየወደቁ ነው።
ውድ ወዳጄ ሆይ፥ በዚህ ጊዜ በኀዘን፥ በጥርጥርና በፍርሃት ምክንያት የምታለቅስ ከሆንህ፥ ነጻ ሊያወጣህ ደስ ይለዋል። ነጻነትን ሊሰጥህ ለኢየሱስ ደስታ ይሆንለታል። አንተ መፈታትህ እንደሚያስደስትህ፥ እርሱም አንተን መፍታቱ እንዲሁ ታላቅ ደስታ ይሰጠዋል። አይደለም፥ የብረቱን ማሰሪያ መበጠስ ያለብህ አንተ አይደለህም፤ ጌታ ራሱ ያደርገዋል። ብቻ ታመነው፥ እርሱም ነጻ አውጪህ ይሆናል። የድንጋይ ቅጥርና የብረት ሰንሰለት ቢኖርም በእርሱ እመን። አሁን በጌታ ኢየሱስ፥ በጸጋውም ነጻነት፥ ለማዳንም ባለው በኃይሉ ሙላት ብታምን፥ ሰይጣን ሊይዝህ አይችልም፥ ኃጢአት በሰንሰለት ሊያስርህ አይችልም፥ ተስፋ መቍረጥ እንኳ ሊያስርህ አይችልም።
ጠላትን ተገዳደር፤ አሁን በፊትህ ያለው ቃልም የመዳን መዝሙርህ ይሁን፤ «እግዚአብሔር የታሰሩትን ይፈታል።»
ማርች 8
የተባረከ ሀብታችን
«እንቅብህና ቡሃቃህ የተባረኩ ይሆናሉ» ዘዳግም 28:5
መታዘዝ ትጋታችን በሚያስገኝልን ስንቅ ሁሉ ላይ በረከትን ያመጣል። ወዲያው ለመብላት በእንቅብ እንዳለ ፍሬ ወዲያው የሚገባውና የሚወጣው ይባረካል፤ ለረዘመ ጊዜ በእኛ ዘንድ የሚቀመጠውም እንዲሁ በረከትን ይቀበላል። ምናልባት የእኛ ድርሻ በእጅ የሚያዝ እንቅብ ያህል ነው። ጠዋት ሥራችንን ልንሠራ ስንወጣ ለቁርስ ጥቂት፥ ለምሳም በእንቅብ ትንሽ ቍራሽ አለን። ይህ መልካም ነው፥ የእግዚአብሔር በረከት ለእንቅቡ ተሰጥቶአልና። ከእጅ ወደ አፍ የምንኖር፥ የዕለቱን ስንቅ በዕለቱ የምናገኝ ብንሆን፥ እንደ እስራኤል ደኅና ነን፤ ጌታ የተወደደውን ሕዝቡን ሲመግብ በአንድ ጊዜ የአንድ ቀን መና ብቻ ይሰጣቸው ነበርና። ከዚህ በላይ ምን ያስፈልጋቸው ነበር? ከዚህ በላይስ ምን ያስፈልገናል?
ነገር ግን ቡሃቃ ካለን፥ ጌታ እንዲባርከው እንዴት እጅግ ያስፈልገናል! የማግኘት ጭንቀት፥ የመጠበቅ ጭንቀት፥ የማስተዳደር ጭንቀት፥ የመጠቀም ጭንቀት አለና፤ ጌታም ካልባረከው፥ ንብረታችን ጣዖታችን እስኪሆን፥ ጭንቀታችንም ነቀርሳ እስኪሆን ድረስ እነዚህ ጭንቀቶች ልባችንን ይበሉታል።
ጌታ ሆይ፥ ሀብታችንን ባርክ። ለክብርህ እንድንጠቀምበት አስችለን። ዓለማዊ ነገሮችን በተገቢ ስፍራቸው እንድናኖር እርዳን፤ ያጠራቀምነውም የነፍሳችንን መዳን ፈጽሞ አያስጊው።
ማርች 9
ለሰላም ጸሎት
«እንድትማረኩ ወዳደረግኋችሁ ከተማ ሰላምን ፈልጉ፥ ስለ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ፤ በእርስዋ ሰላም ሰላም ይሆንላችኋልና» ኤርምያስ 29:7
በዚህ ቃል ውስጥ ያለው መርሕ የጌታ እንግዶችና መጻተኞች ለሆንን ለሁላችን በመካከላቸው የምንኖርባቸውን ሕዝብ ሰላምና ብልጽግና ለማስፋፋት መሻት እንዳለብን ያመለክታል። በተለይም ሕዝባችንና ከተማችን በማያቋርጥ ምልጃችን ሊባረኩ ይገባል። ለአገርህና ለሌሎች አገሮች የሚቀርብ የልብ ጸሎት ለእያንዳንዱ አማኝ አፍ የሚገባ ነው።
በአገር ውስጥም በውጭም ለታላቁ የሰላም ስጦታ በትጋት እንጸልይ። ጠብ በመንገዶቻችን ደም ቢያፈስስ፥ ወይም የውጭ ጦርነት ጀግኖች ወታደሮቻችንን ቢገድል፥ ሁላችንም ስለ መከራው እናለቅሳለን፤ ስለዚህ ለሰላም እንጸልይ፥ በአገር ውስጥ ያሉት ወገኖችና በውጭ ያሉት ሕዝቦች በወዳጅነት ማሰሪያ የሚተሳሰሩባቸውንም መርሖች በትጋት እናስፋፋ።
እኛ ራሳችን ከሕዝቡ ሰላም ጋር ተያይዞ ጸጥታ ተሰጥቶናል፤ ይህም እጅግ የሚወደድ ነው፤ በዚህ ልጆቻችንን በጌታ ፍርሃት ማሳደግ፥ ወንጌልንም ያለ እንቅፋትና ያለ ክልከላ መስበክ እንችላለንና። ዛሬ ብሔራዊ ኃጢአትን እየተናዘዝን፥ ስለ ኢየሱስም ብሔራዊ ይቅርታንና በረከትን እየለመንን ስለ አገራችን አብዝተን እንጸልይ።
ማርች 10
በብርሃን ተመላለሱ
«በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ» ዮሐንስ 12:46
ይህ ዓለም እንደ እኩለ ሌሊት ጨለማ ነው፤ ኢየሱስ የመጣው በእምነት ብርሃን እንዲኖረን፥ የቀረውንም የሰው ልጅ ሁሉ በሚሸፍነው ጨለማ ውስጥ ከእንግዲህ እንዳንቀመጥ ነው።
«ሁሉ» እጅግ ሰፊ ቃል ነው፤ አንተንና እኔን ማለት ነው። በኢየሱስ ብንታመን ከእንግዲህ በሞት ጥላ ጨለማ ውስጥ አንቀመጥም፥ ነገር ግን ፍጻሜ ወደሌለው ቀን ሞቅ ያለ ብርሃን እንገባለን። ስለ ምን ወዲያው ወደ ብርሃን አንወጣም?
አንዳንድ ጊዜ ደመና በላያችን ሊያንዣብብ ይችላል፤ በኢየሱስ ካመንን ግን በጨለማ አንኖርም። እርሱ ሙሉ የቀን ብርሃን ሊሰጠን መጥቷል። በከንቱ ይመጣልን? እምነት ካለን የፀሐይ ብርሃን መብት አለን፤ እንደሰትበት። ከተፈጥሮአዊ ርኵሰት፥ ከድንቁርና፥ ከጥርጥር፥ ከተስፋ መቍረጥ፥ ከኃጢአት፥ ከፍርሃትም ሌሊት ነጻ ሊያወጣን ኢየሱስ መጥቷል፤ አማኞችም ሁሉ ፀሐይ ወጥታ ሙቀቷንና ብርሃኗን ሳትበትን እንደማትቀር፥ እርሱም በከንቱ እንደማይመጣ ያውቃሉ።
ውድ ወንድሜ ሆይ፥ ጭንቀትህን አራግፍ። በጨለማ አትኑር፥ በብርሃን ግን ኑር። ተስፋህ፥ ደስታህ፥ ሰማይህም በኢየሱስ ነው። ወደ እርሱ፥ ወደ እርሱ ብቻ ተመልከት፤ ወፎች በፀሐይ መውጫ ደስ እንደሚላቸው፥ መላእክትም በዙፋኑ ፊት ደስ እንደሚላቸው አንተም ደስ ይልሃል።
ማርች 11
የማን ሰልፍ?
«ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነውና፥ እርሱም በእጃችን አሳልፎ ይሰጣችኋልና እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር እንዳያድን ይህ ጉባኤ ሁሉ ያውቃል» 1ኛ ሳሙኤል 17:47
ሰልፉ የጌታ ነው የሚለው ነገር ይጽና፤ ያን ጊዜ ስለ ድሉ፥ ደግሞም የእግዚአብሔርን ኃይል ከሁሉ በተሻለ በሚገልጥ መንገድ ስለሚሆነው ድል ፈጽሞ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ጌታ በሰዎች ሁሉ፥ አዎን፥ በእስራኤል ጉባኤዎች እንኳ እጅግ ተረስቷል፤ ታላቁ የመጀመሪያ ምክንያት ያለ ሰው ኃይል ዓላማውን ሊፈጽም እንደሚችል ሰዎች እንዲያዩ የሚያደርግ ዕድል ሲገኝ፥ ይህ በሚገባ ሊሠራበት የሚገባ ዋጋ የማይገኝለት አጋጣሚ ነው። እስራኤል እንኳ ወደ ሰይፍና ወደ ጦር እጅግ ይመለከታል። በዳዊት እጅ ሰይፍ አለመኖሩ፥ ሆኖም ዳዊት አምላኩ የባዕዳንን ሠራዊት ሁሉ እንደሚገለብጥ ማወቁ ታላቅ ነገር ነው።
በእውነት ስለ እውነትና ስለ ጽድቅ የምንታገል ከሆንን፥ ችሎታ ወይም ሀብት ወይም ሌላ ዓይነት የሚታይ ኃይል በእጃችን እስኪገኝ ድረስ አንዘግይ፤ ነገር ግን በወንዙ ውስጥ ባገኘናቸው ድንጋዮችና በተለመደው ወንጭፋችን ጠላትን ለመግጠም እንሩጥ። ጦርነቱ የራሳችን ቢሆን ኖሮ ላንተማመን እንችል ነበር፤ ለኢየሱስ የቆምን፥ በእርሱም ኃይል ብቻ የምንዋጋ ከሆንን ግን ማን ሊቋቋመን ይችላል? ያለ አንዳች ማመንታት ፍልስጥኤማውያንን እንግጠም፤ የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነውና፥ ማንስ ሊቃወመን ይችላል?
ማርች 12
በደስታ መውጣት
«ስለ ዛብሎንም እንዲህ አለ። ዛብሎን ሆይ፥ በመውጣትህ ደስ ይበልህ» ዘዳግም 33:18
የነገዶቹ በረከቶች የእኛ ናቸው፤ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክና በሥጋ የማንታመን እውነተኛው እስራኤል እኛ ነንና። እግዚአብሔር «መውጣቱን» ስለሚባርክ ዛብሎን ደስ ሊለው ይገባል፤ እኛም በዚህ ቡራኬ ውስጥ ለራሳችን የተሰወረ ተስፋ እናያለን። ስንወጣ የደስታን አጋጣሚ እንፈልጋለን።
ለመጓዝ እንወጣለን፥ የእግዚአብሔርም መግቦት አጃቢያችን ነው። ወደ ሌላ አገር ለመሰደድ እንወጣለን፥ ጌታም በየብስም በባሕርም ከእኛ ጋር ነው። እንደ ሚስዮናውያን እንወጣለን፥ ኢየሱስም «እነሆም፥ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ» ይላል። ዕለት ዕለት ወደ ሥራችን እንወጣለን፥ ይህንም በደስታ ልናደርግ እንችላለን፤ እግዚአብሔር ከጥዋት እስከ ማታ ከእኛ ጋር ይሆናልና።
ስንነሣ ምን እንደሚገጥመን ስለማናውቅ አንዳንድ ጊዜ ፍርሃት ሾልኮ ይገባብናል፤ ይህ በረከት ግን እንደ ማጽናኛ ቃል በሚገባ ሊጠቅመን ይችላል። ለመጓዝ ስንሸከፍ ይህን ቃል በጉዞ ሻንጣችን ውስጥ እናኑረው፤ በልባችን እንጣለው፥ በዚያም እንጠብቀው፤ አዎን፥ እንድንዘምር በምላሳችን ላይ እናኑረው። መልሕቅን በመዝሙር እናንሣ፥ ወይም በመዝሙር ወደ ሠረገላው እንዝለል። የሚደሰተው ነገድ አባላት እንሁን፥ በእንቅስቃሴያችንም ሁሉ ጌታን በደስተኛ ልብ እናመስግን።
ማርች 13
ወጣትነትህን አትናቅ
«እኔም። ወዮ፥ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ እነሆ፥ ሕፃን ነኝና መናገር አላውቅም አልሁ። እግዚአብሔር ግን። ሕፃን ነኝ አትበል፤ ወደምልክህ ሁሉ ዘንድ ትሄዳለህና፥ የማዝዝህንም ሁሉ ትናገራለህና አለኝ» ኤርምያስ 1:6, 7
ኤርምያስ ወጣት ነበር፤ ጌታ በታላቅ መልእክት ሲልከው በተፈጥሮው ወደ ኋላ አለ፤ የላከው ግን «ሕፃን ነኝ» እንዲል አልፈቀደለትም። እርሱ በራሱ ምን እንደ ነበረ መጠቀስ አልነበረበትም፤ ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር ለመናገር መመረጡን በማሰብ ሊረሳ ይገባው ነበር። መልእክትን አስቦ መፍጠር ወይም አድማጮችን መምረጥ አልነበረበትም፤ እግዚአብሔር ያዘዘውን መናገር፥ እግዚአብሔር በላከውም ስፍራ መናገር ነበረበት፤ ይህንም ከራሱ ባልሆነ ኃይል ለማድረግ ይችል ነበር።
እነዚህን መስመሮች ለሚያነብ ወጣት ሰባኪ ወይም አስተማሪ እንዲሁ አይደለምን? እግዚአብሔር ምን ያህል ወጣት እንደ ሆንህ፥ እውቀትህና ልምድህ ምን ያህል ጥቂት እንደ ሆኑ ያውቃል፤ ሊልክህ ከመረጠ ግን ከሰማያዊው ጥሪ ወደ ኋላ ማለት የአንተ ድርሻ አይደለም። እግዚአብሔር በድካምህ ራሱን ያገንናል። እንደ ማቱሳላ ያረጀህ ብትሆን፥ ዕድሜህ ምን ያህል ይረዳህ ነበር? እንደ ሰሎሞን ጥበበኛ ብትሆን፥ እንደ እርሱ እልከኛ ልትሆን ትችል ነበር። መልእክትህን አጥብቀህ ያዝ፥ እርሱም ጥበብህ ይሆናል፤ የሰልፍ ትእዛዝህን ተከተል፥ እርሱም ማስተዋልህ ይሆናል።
ማርች 14
ርኅሩኅ መጽናናት
«እናቱ እንደምታጽናናው ሰው፥ እንዲሁ አጽናናችኋለሁ» ኢሳይያስ 66:13
የእናት መጽናናት! አቤት፥ ይህ ርኅራኄ ራሱ ነው። እንዴት የልጅዋን ኀዘን ትካፈላለች! እንዴት ወደ ደረቷ ታቅፈዋለች፥ ኀዘኑንም ሁሉ ወደ ራስዋ ልብ ለመውሰድ ትሞክራለች! እርሱ ሁሉን ሊነግራት ይችላል፥ እርስዋም ማንም እንደማይችል ትራራለታለች። ከአጽናኞች ሁሉ ልጁ ከሁሉ አብልጦ እናቱን ይወዳል፤ ያደጉ ሰዎችም እንኳ እንዲሁ ሆኖ አግኝተውታል።
እግዚአብሔር የእናትን ድርሻ ለመፈጸም ራሱን ዝቅ ያደርጋልን? ይህ በእውነት ቸርነት ነው። እንዴት አባት እንደ ሆነ በቀላሉ እንረዳለን፤ ነገር ግን እንደ እናትም ይሆናልን? ይህ ወደ ቅዱስ መቀራረብ፥ ወደ ያልተገደበ መተማመንና ወደ ቅዱስ ዕረፍት አይጋብዘንምን? እግዚአብሔር ራሱ «አጽናኝ» ሲሆን ምንም ጭንቀት ለረጅም ጊዜ ሊቆይ አይችልም። ልቅሶና ትካዜ በቀላሉ የሚወጡ ቃላቶቻችን ቢሆኑ እንኳ መከራችንን እንንገረው። ስለ እንባችን አይንቀንም፤ እናታችን አልናቀችንም። እርስዋ እንዳደረገችው ድካማችንን ያስባል፥ ጥፋታችንንም ያስወግዳል፥ ብቻ እናታችን ከምትችለው ይልቅ በተረጋገጠና በተጠበቀ መንገድ። ኀዘናችንን ብቻችንን ለመሸከም አንሞክርም፤ ይህ እጅግ ገርና ደግ ለሆነው ደግነት የጐደለው ይሆናል። ቀኑን ከአፍቃሪው አምላካችን ጋር እንጀምር፤ እናቶች በልጆቻቸው አይታክቱምና ስለ ምን በዚያው ኅብረት አንፈጽመውም?
ማርች 15
እግዚአብሔር መቅደስ ነው
«ስለዚህ እንዲህ በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በአሕዛብ መካከል ባርቃቸውም፥ በአገሮችም ውስጥ ብበትናቸውም፥ በሚመጡባቸው አገሮች ለእነርሱ ጥቂት መቅደስ እሆንላቸዋለሁ» ሕዝቅኤል 11:16
ከሕዝባዊው የጸጋ መንገዶች ብንለይም ከመንገዶቹ ጸጋ አልተለየንም። ሕዝቡን እንደ ስደተኞች በሚሰማቸው ስፍራ የሚያኖራቸው ጌታ ራሱ ከእነርሱ ጋር ይሆናል፤ በቤታቸው፥ በተቀደሰው ጉባኤአቸው ስፍራ ሊኖራቸው የሚችለውን ሁሉ ይሆንላቸዋል። እናንተ እንድትንከራተቱ የተጠራችሁ ሆይ፥ ይህን ለራሳችሁ ውሰዱ!
እግዚአብሔር ለሕዝቡ መጠጊያ ስፍራ ነው። ከጠላት ሁሉ በእርሱ ዘንድ መሸሸጊያ ያገኛሉ። የአምልኮ ስፍራቸውም እርሱ ነው። ያዕቆብ በሜዳ በተኛ ጊዜ ከእርሱ ጋር እንደ ነበረ ከእነርሱ ጋር ነው፤ ያዕቆብም ተነሥቶ «በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ነበረ» አለ። ለእነርሱም የዘላለማዊው ጸጥ ያለ ማደሪያ እንደ ነበረው እንደ ቅድስተ ቅዱሳን የጸጥታ መቅደስ ይሆንላቸዋል። ክፉን ከመፍራት ጸጥ ይላሉ።
እግዚአብሔር ራሱ በክርስቶስ ኢየሱስ የምሕረት መቅደስ ነው። የኪዳኑ ታቦት ጌታ ኢየሱስ ነው፤ የአሮን በትር፥ የመናው መሶብ፥ የሕጉ ጽላቶች ሁሉ መቅደሳችን በሆነው በክርስቶስ ውስጥ ናቸው። በእግዚአብሔር የቅድስናንና የኅብረትን መቅደስ እናገኛለን። ከዚህ በላይ ምን ያስፈልገናል? ጌታ ሆይ፥ ይህን ተስፋ ፈጽም፥ ሁልጊዜም ጥቂት መቅደስ ሁንልን!
ማርች 16
ለሌሎች «ምሳሌ»
«ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል» ፊልጵስዩስ 4:9
ሰው ጳውሎስ ሊሆን እንደሚችለው በዝርዝር ሲከተሉት የሚጠቅም ሲሆን መልካም ነው። ዛሬና ዕለት ዕለት እርሱን ለመምሰል ጸጋ ቢኖረን!
በመለኮታዊ ጸጋ የጳውሎስን ትምህርት በተግባር ብንፈጽም፥ አሁን በፊታችን የተከፈተውን ተስፋ ልንጠይቅ እንችላለን፤ እንዴትስ ያለ ተስፋ ነው! ሰላምን የሚወድ፥ ሰላምን የሚያደርግ፥ ሰላምንም የሚተነፍስ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሆናል። «ሰላም ለእናንተ ይሁን» ጣፋጭ ቡራኬ ነው፤ የሰላም አምላክ ከእኛ ጋር መሆኑ ግን እጅግ ይበልጣል። በዚህ ጅረቶቹን ብቻ ሳይሆን ምንጩን፥ ጨረሩን ብቻ ሳይሆን ፀሐዩን እናገኛለን። የሰላም አምላክ ከእኛ ጋር ከሆነ፥ የውጭ ሁኔታዎች ሊያውኩ ቢያስፈራሩም እንኳ አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔርን ሰላም እንደሰታለን። ሰዎች ቢጣሉ፥ የሰላም ፈጣሪ ከእኛ ጋር ከሆነ፥ እኛ በእርግጥ የሚያስታርቁ እንሆናለን።
እውነተኛ ሰላም የሚገኘው በእውነት መንገድ ነው። ሰላምን እናስፋፋለን ብለን እምነትን ብንተው ወይም የጽድቅን መንገድ ብንለቅ፥ እጅግ እንሳሳታለን። በመጀመሪያ ንጽሕና፥ ከዚያም ሰላም፤ ይህ የጥበብና የእውነታ ሥርዓት ነው። የጳውሎስን መስመር እንያዝ፤ ከሐዋርያው ጋር እንደ ነበረ የሰላም አምላክ ከእኛ ጋር ይሆናል።
ማርች 17
ፍርሃትን ፍራ
«ከፊታቸው አትፍራ፤ አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና፥ ይላል እግዚአብሔር» ኤርምያስ 1:8
ፍርሃት በገባና ባንገዳገደን ቁጥር በኃጢአት የመውደቅ አደጋ ላይ ነን። ትዕቢት የሚያስፈራ ነው፥ ፍርሃትም እንዲሁ። «ዳንኤል ለመሆን ድፈር።» ታላቁ አለቃችን በጀግኖች ወታደሮች ሊገለገል ይገባዋል።
ለጀግንነት እንዴት ያለ ምክንያት ይኸውና! እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ካሉት ጋር ነው። የትግሉ ሰዓት ሲመጣ እግዚአብሔር ፈጽሞ አይርቅም። ያስፈራሩሃልን? የሚሞተውን ሰው ትፈራ ዘንድ አንተ ማን ነህ? ሥራህን ታጣለህን? የምታገለግለው አምላክህ ለባሪያዎቹ እንጀራና ውኃ ያገኝላቸዋል። ልትታመነው አትችልምን? ያፌዙብሃልን? ይህ አጥንትህን ወይም ልብህን ይሰብራልን? ስለ ክርስቶስ ብለህ ታገሠው፥ በዚህም ምክንያት እንኳ ደስ ይበልህ።
እግዚአብሔር ሊያድናቸው ከእውነተኞች፥ ከጻድቃንና ከቅዱሳን ጋር ነው፤ አንተንም ያድንሃል። ዳንኤል ከአንበሶች ጕድጓድ፥ ሦስቱ ቅዱሳን ብላቴኖችም ከእቶን እንዴት እንደ ወጡ አስብ። የአንተ ጉዳይ እንደ እነርሱ ያለ ተስፋ ቢስ አይደለም፤ ቢሆን እንኳ ጌታ ያሻግርሃል፥ ከአሸናፊም ይልቅ ያደርግሃል። ፍርሃትን ፍራ። መፍራትን ፍራ። ከጠላቶችህ ሁሉ የከፋው በገዛ ደረትህ ውስጥ ነው። ተንበርክከህ ለእርዳታ ጩኽ፤ ከዚያም «እታመናለሁ አልፈራምም» እያልህ ተነሥ።
ማርች 18
ቅን ሆነህ ጽና
«የቅኖች ጸሎት ግን ደስ ያሰኘዋል» ምሳሌ 15:8
ይህ እንደ ተስፋ ያህል መልካም ነው፤ በዘመናት ሁሉ ያው የሚሆነውን የአሁኑን እውነታ ያውጃልና። እግዚአብሔር በቅኖች ሰዎች ጸሎት እጅግ ደስ ይለዋል፤ ደስታውም ብሎ ይጠራቸዋል። የመጀመሪያው ጉዳያችን ቅኖች መሆን ነው። ወደዚህም ወደዚያም ሳትጐበጥ ቅን ሆነህ ጽና፤ በተንኰል ሳትጣመም፥ ለክፋትም በመገዛት ሳትወድቅ፥ በጽኑ ታማኝነትና በቀጥተኝነት ቅን ሁን። ማመካኘትና መሽሎክሎክ ብንጀምር ራሳችንን እንድንችል እንተዋለን። ጠማማ መንገድን ብንሞክር መጸለይ እንደማንችል እናገኛለን፤ የምንጸልይ መስለን ብንቀርብም ጸሎታችን ከሰማይ ተዘግቶ እናገኘዋለን።
በቀጥተኛ መስመር እየሠራን የጌታን የተገለጠ ፈቃድ እንከተላለንን? እንግዲያስ አብዝተን በእምነትም እንጸልይ። ጸሎታችን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ከሆነ፥ ደስ በሚያሰኘው ነገር አናሳንሰው። ሰዋስዉን፥ ፍልስፍናውን፥ የንግግር ውበቱንም አይመለከትም፤ በእነዚህ ሁሉ ሰዎች ሊንቁት ይችላሉ። እርሱ እንደ አባት በገዛ ሕፃናቱ መንተባተብ፥ አዲስ በተወለዱት ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ መንተባተብ ደስ ይለዋል። ጌታ በጸሎት ደስ የሚለው ከሆነ እኛስ በጸሎት ደስ ሊለን አይገባምን? ወደ ዙፋኑ ጕዳይ ይዘን እንሂድ። ጌታ ለጸሎት በቂ ምክንያቶችን ያገኝልናል፤ እንዲህ በመሆኑም ልናመሰግነው ይገባናል።
ማርች 19
ለክብር የተገባ መሆን
«እግዚአብሔር ጸጋንና ክብርን ይሰጣል» መዝሙር 84:11
አሁን የሚያስፈልገን ጸጋ ነው፤ በነጻም ይገኛል። ከስጦታ የበለጠ ነጻ ምን አለ? ዛሬ የሚደግፍ፥ የሚያበረታ፥ የሚቀድስና የሚያጠግብ ጸጋ እንቀበላለን። እስከ አሁን ዕለት ዕለት ጸጋን ሰጥቶአል፤ ስለሚመጣውም ያ ጸጋ አሁንም ይበቃል። ጸጋችን ጥቂት ቢሆን ጥፋቱ በእኛ ላይ መሆን አለበት፤ ጌታ አልተወሰነምና፥ በብዛት ለመስጠትም አይዘገይም። የፈለግነውን ያህል ልንለምን እንችላለን፤ እምቢታንም ፈጽሞ አንፈራም። ሳይነቅፍ በልግስና ይሰጣል።
ጌታ ወርቅን ላይሰጥ ይችላል፥ ጸጋን ግን ይሰጣል፤ ትርፍን ላይሰጥ ይችላል፥ ጸጋን ግን ይሰጣል። በእርግጥ ፈተናን ይልክብናል፥ ነገር ግን በዚያ መጠን ጸጋን ይሰጣል። ለድካምና ለመከራ ልንጠራ እንችላለን፤ ከጥሪው ጋር ግን የሚያስፈልገው ጸጋ ሁሉ ይመጣል።
በቃሉ ውስጥ ያለው ያ «እና» እንዴት ያለ ነው — «ክብርንም»! ገና ክብር አያስፈልገንም፥ ገናም አልተገባንለትም፤ ነገር ግን በተገቢው ሥርዓት እናገኘዋለን። የጸጋን እንጀራ ከበላን በኋላ የክብርን ወይን እንጠጣለን። በቅድስቱ በኩል —ይኸውም ጸጋ ነው— ወደ ቅድስተ ቅዱሳን — ይኸውም ክብር ነው — ማለፍ አለብን። «ክብርንም» የሚሉት እነዚህ ቃላት ሰውን በደስታ ለማስዘለል ይበቃሉ። ጥቂት ጊዜ — ጥቂት ጊዜ፥ ከዚያም ለዘላለም ክብር!
ማርች 20
መለኮታዊ ስንቅ
«እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት?» ማቴዎስ 6:30
ልብስ ውድ ነው፤ ድሆች አማኞችም የሚቀጥለው ልብሳቸው ከየት እንደሚመጣ ሊጨነቁ ይችላሉ። የጫማው ሶል ስስ ነው፤ አዲስ ጫማ እንዴት እናገኛለን? አሳቢው ጌታችን ይህን ጭንቀት እንዴት አስቀድሞ እንዳሰበበት እዩ። የሰማዩ አባታችን የሜዳን ሣር ሰሎሞን ሊተካከለው በማይችል ግርማ ያለብሰዋል፤ የገዛ ልጆቹንስ አያለብስምን? እንደሚያለብስ እርግጠኞች ነን። ብዙ መጣፍና መስፋት ሊኖር ይችላል፥ ልብስ ግን ይኖረናል።
አንድ ድሀ አገልጋይ ልብሱ ሊያልቅ ተቃርቦ፥ እስከማይያያዝም ድረስ አርጅቶ አገኘው፤ ነገር ግን የጌታ አገልጋይ እንደ መሆኑ ጌታው የአገልግሎት ልብሱን እንዲያገኝለት ይጠብቅ ነበር። ይህን የጻፈው ሰው አንድ ወዳጁን ሊጠይቅ በሄደ ጊዜ የዚያን መልካም ሰው መስበኪያ ለጊዜው ተዋሰ፤ ለእርሱም መዋጮ የመሰብሰብ አሳብ በልቡ መጣ፤ ልብሱም በዚያ ተገኘ። ጌታን ያገለገሉ ሰዎች ለልብሳቸው እንደሚያስብ ያገኙባቸውን ሌሎች ብዙ ታሪኮች አይተናል። ሰውን ኃጢአት በሠራ ጊዜ ልብስ እንዲያስፈልገው አድርጎ የፈጠረው እርሱ በምሕረቱ ልብስን ደግሞ ሰጠው፤ ጌታ ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የሰጣቸው ልብሶችም ለራሳቸው ካዘጋጁት እጅግ የተሻሉ ነበሩ።
ማርች 21
ያን መንሸራተት ተጠንቀቅ
«የዚያን ጊዜ መንገድህን ተማምነህ ትሄዳለህ፥ እግርህም አይሰናከልም» ምሳሌ 3:23
ይህም ማለት የጥበብንና የቅድስናን መንገድ ብንከተል በእነርሱ እንጠበቃለን። በቀን ብርሃን በአውራ ጎዳና የሚጓዝ ሰው በመጠኑ ጥበቃ ሥር ነው። ለእያንዳንዱ ሰው መንገድ አለው፤ ይኸውም በሕይወቱ የራሱ የሆነ ጥሪው ነው፤ በእግዚአብሔርም ፍርሃት በዚያ በትጋት ብንመላለስ እርሱ እኛን ከክፉ ይጠብቀናል። በቅንጦት ላንጓዝ እንችላለን፥ በሰላም ግን እንሄዳለን። እንደ ጐበዛዝት መሮጥ ላንችል እንችላለን፥ እንደ ደጋግ ሰዎች ግን መሄድ እንችላለን።
ታላቁ አደጋችን በራሳችን ውስጥ ነው፤ ደካማ እግራችን ለመሰናከል እጅግ የተጋ ነው። የመንሸራተት ዝንባሌያችን እንዲሸነፍ ተጨማሪ የሞራል ብርታት እንለምን። አንዳንዶች በመንገድ ያለውን ድንጋይ ስለማያዩ ይሰናከላሉ፤ መለኮታዊ ጸጋ ግን ኃጢአትን እንድናይና እንድንርቀው ያስችለናል። ይህን ተስፋ ይዘን እንማልድ፥ የመረጣቸውን በሚደግፍ በእርሱም እንታመን።
ወዮ! ከሁሉ የከፋው አደጋችን የራሳችን ቸልተኝነት ነው፤ ጌታ ኢየሱስ ግን «ትጉና ጸልዩ» ብሎ ከዚህ እንድንጠነቀቅ አስጠንቅቆናል።
ዛሬን አንድ ጊዜ እንኳ ሳንሰናከል እንድንመላለስ ጸጋ ቢሰጠን! በእርግጥ አለመውደቃችን ብቻ አይበቃም፤ ጩኸታችን እግሮቻችን ትንሺቱን እንኳ እንዳይንሸራተቱ፥ በመጨረሻም «ሳትሰናከሉ እንዲጠብቃችሁ ለሚችለው» ለእርሱ እንድንሰግድ ይሁን።
ማርች 22
ለትሑታን የሚሰጥ ጸጋ
«ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል» ያዕቆብ 4:6
ትሑታን ልቦች ጸጋን ይሻሉ፤ ስለዚህም ያገኙታል። ትሑታን ልቦች ለጸጋ ጣፋጭ ተጽዕኖ ይገዛሉ፤ ስለዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ አብልጦ ይሰጣቸዋል። ትሑታን ልቦች የጸጋ ወንዞች በሚፈሱባቸው ሸለቆዎች ውስጥ ይተኛሉ፤ ስለዚህም ከእነርሱ ይጠጣሉ። ትሑታን ልቦች ስለ ጸጋ አመስጋኞች ናቸው፥ ክብሩንም ለጌታ ይሰጣሉ፤ ስለዚህም ጸጋን ለእነርሱ መስጠቱ ከክብሩ ጋር የሚስማማ ነው።
ውድ አንባቢ ሆይ፥ ና፥ ዝቅተኛውን ስፍራ ያዝ። ጌታ ከፍ ያደርግህ ዘንድ በራስህ ዓይን ታናሽ ሁን። ምናልባት «ትሑት አይደለሁም ብዬ እፈራለሁ» የሚል ትካዜ ይወጣ ይሆናል። ይህ የእውነተኛ ትሕትና ቋንቋ ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች በትሑትነታቸው ይኮራሉ፤ ይህም ከትዕቢት ዓይነቶች ሁሉ እጅግ የከፋው ነው። እኛ ችግረኞች፥ ረዳት የሌለን፥ ምንም የማይገባን፥ ሲኦል የሚገባን ፍጥረቶች ነን፤ ትሑታን ካልሆንን ልንሆን ይገባናል። በትሕትና ላይ ስለ ሠራነው ኃጢአት ራሳችንን እናዋርድ፤ ያን ጊዜም ጌታ ሞገሱን እንድንቀምስ ያደርገናል። ትሑታን የሚያደርገን ጸጋ ነው፤ በዚህም ትሕትና አብልጦ ጸጋን ለማፍሰስ ዕድል የሚያገኘውም ጸጋ ነው። እንነሣ ዘንድ እንውረድ። እግዚአብሔር ባለ ጠጎች ያደርገን ዘንድ በመንፈስ ድሆች እንሁን። መዋረድ እንዳያስፈልገን፥ ይልቁንም በእግዚአብሔር ጸጋ ከፍ እንድንል ትሑታን እንሁን።
ማርች 23
እርግጠኛ መሪ
«ዕውሮችንም በማያውቋት መንገድ እመራቸዋለሁ» ኢሳይያስ 42:16
ወሰን የሌለው ክቡር እግዚአብሔር ለዕውሮች መሪ ሆኖ ሲሠራ አስቡ! ይህ እንዴት ያለ ወሰን የሌለው ዝቅ ማለት ነው! ዕውር ሰው የማያውቀውን መንገድ ሊያገኝ አይችልም። መንገዱን ቢያውቀው እንኳ በእርሱ መሄድ ይከብደዋል፤ የማያውቀው መንገድ ግን መሪ ለሌላቸው እግሮቹ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው። እንግዲህ እኛ በተፈጥሮ ስለ መዳን መንገድ ዕውሮች ነን፤ ጌታ ግን ወደ እርሱ ይመራናል፥ ወደ ራሱም ያመጣናል፥ ከዚያም ዓይኖቻችንን ይከፍታል። ስለሚመጣው ዘመን ሁላችንም ዕውሮች ነን፤ አንዲትን ሰዓት እንኳ ወደ ፊት ማየት አንችልም፤ ጌታ ኢየሱስ ግን እስከ ጉዞአችን ፍጻሜ ይመራናል። ስሙ የተባረከ ይሁን!
መዳን በምን መንገድ ሊመጣልን እንደሚችል መገመት አንችልም፤ ጌታ ግን ያውቃል፤ ከአደጋም ሁሉ እስክናመልጥ ድረስ ይመራናል። እጃቸውን በታላቁ መሪ እጅ ውስጥ የሚያኖሩ፥ መንገዳቸውንና ራሳቸውንም ፈጽመው ለእርሱ የሚተዉ ብፁዓን ናቸው። መንገዱን ሁሉ ይመራቸዋል፤ ወደ ክብር ቤታቸው ባደረሳቸውና የመራቸውን መንገድ ያዩ ዘንድ ዓይኖቻቸውን በከፈተ ጊዜ፥ ለታላቁ ባለውለታቸው እንዴት ያለ የምስጋና መዝሙር ይዘምራሉ! ጌታ ሆይ፥ መንገዴን አላውቅምና ምስኪኑን ዕውር ልጅህን ዛሬ ምራው!
ማርች 24
የጸኑና የተጠበቁ
«ነገር ግን የሚያጸናችሁ ከክፉውም የሚጠብቃችሁ ጌታ የታመነ ነው» 2ኛ ተሰሎንቄ 3:3
ሰዎች ብዙ ጊዜ እምነት እንደሌላቸው ሁሉ ማስተዋልም የላቸውም። «ዓመፀኞችና ክፉዎች ሰዎች» አሁንም በመካከላችን አሉ። ከእነርሱ ጋር መከራከር ወይም ከእነርሱ ጋር በሰላም ለመኖር መሞከር ጥቅም የለውም፤ በልባቸው ሐሰተኞች፥ በንግግራቸውም አታላዮች ናቸው። ታዲያ ይህ ምን ይሁን? በእነርሱ ምክንያት ራሳችንን እናስጨንቅን? አይደለም፤ እርሱ የታመነ ነውና ወደ ጌታ እንመለስ። ከቃሉ የትኛውም ተስፋ ከቶ አይታጠፍም። እርሱ በእኛ ላይ በሚጠይቀው ነገር ማስተዋል የጎደለው፥ ወይም እኛ በእርሱ ላይ ላለን መብት የማይታመን አይደለም። የታመነ አምላክ አለን። ይህ ደስታችን ይሁን።
ክፉ ሰዎች እንዳይጥሉን ያጸናናል፤ አሁን ከሚያጠቁን ክፋቶች አንዳቸውም በእውነት እንዳይጎዱን ይጠብቀናል። ከሰዎች ጋር መታገል ሳያስፈልገን፥ ከእኛ ጋር በእውነተኛ ርኅራኄ ባለው በጌታ ኢየሱስ እንድንጠለል መፈቀዱ እንዴት ያለ በረከት ነው! አንድ እውነተኛ ልብ፥ አንድ የታመነ አሳብ፥ ከቶ የማይለወጥ አንድ ፍቅር አለ፤ በዚያ እንረፍ። ጌታ ለእኛ ለባሪያዎቹ የጸጋውን አሳብ ይፈጽማል፤ የፍርሃትም ጥላ በመንፈሳችን ላይ እንዲያርፍ መፍቀድ አያስፈልገንም። ሰዎችም ሆኑ አጋንንት የሚያደርጉት ሁሉ መለኮታዊውን ጥበቃና ስንቅ ሊከለክሉን አይችሉም። ዛሬ ጌታ እንዲያጸናንና እንዲጠብቀን እንጸልይ።
ማርች 25
የሚያድስ እንቅልፍ
«በተኛህ ጊዜ አትፈራም፤ አዎን፥ ትተኛለህ፥ እንቅልፍህም ጣፋጭ ይሆናል» ምሳሌ 3:24
አንባቢው በሕመም ምክንያት ለጥቂት ጊዜ በአልጋ ላይ ሊውል ይሆን? ይህን ተስፋ በልቡ ይዞ ያለ ጭንቀት ወደ መኝታው ይውጣ — «በተኛህ ጊዜ አትፈራም።»
ሌሊት ወደ አልጋ ስንሄድ ይህ ቃል ትራሳችንን ያለስልስልን። በእንቅልፍ ራሳችንን መጠበቅ አንችልም፤ ጌታ ግን ሌሊቱን ሁሉ ይጠብቀናል። በጌታ ጥበቃ ሥር የሚተኙ በቤተ መንግሥታቸው እንዳሉ ነገሥታትና ንግሥቶች ደኅና ናቸው፤ እንዲያውም ከእነርሱ እጅግ ይበልጣሉ። ስንተኛ ጭንቀትንና ምኞትን ሁሉ ብናኖር፥ የተጨነቁና ስግብግቦች በአልጋቸው ከቶ የማያገኙትን እረፍት ከአልጋችን እናገኛለን። ክፉ ሕልሞች ይባረራሉ፤ ቢመጡም እንኳ ሕልሞች ብቻ መሆናቸውን አውቀን ስሜታቸውን እናጠፋለን።
እንዲህ ብንተኛ መልካም እናደርጋለን። ጴጥሮስ የመልአኩ ብርሃን እንኳ ሳይቀሰቅሰው፥ ሊነቃም ጎኑን በኃይል መጎሸም ሲያስፈልገው እንዴት ጣፋጭ ተኛ! ደግሞም በማግሥቱ እንዲሞት ተፈርዶበት ነበር። ሰማዕታትም ከመቃጠላቸው በፊት እንዲሁ ተኝተዋል። «ለወዳጆቹ እንዲሁ እንቅልፍን ይሰጣል።»
ጣፋጭ እንቅልፍ እንዲኖረን ጣፋጭ ሕይወት፥ ጣፋጭ ጠባይ፥ ጣፋጭ ማሰላሰልና ጣፋጭ ፍቅር ሊኖረን ይገባል።
ማርች 26
ለድሆች የሚደረግ ጥንቃቄ
«እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ላይ ያበረታዋል» መዝሙር 41:3
ይህ ለድሆች ለሚያስብ ሰው የተሰጠ ተስፋ መሆኑን አስታውስ። አንተ ከእነዚህ አንዱ ነህን? እንግዲያስ ጥቅሱን ወደ ቤትህ ውሰድ።
በሕመም ሰዓት የድሆች አምላክ ለድሆች የሚያስበውን ሰው እንዴት እንደሚባርክ እዩ! የወዳጅ እጆችና ለስላሳ ትራሶች የታማሚውን ሥጋ እንደሚደግፉ፥ የዘላለም ክንዶች ነፍሱን ይደግፋሉ። ይህ ምሳሌ እንዴት ርኅሩኅና አዛኝ ነው፤ አምላካችንን ወደ ድካማችንና ወደ ሕመማችን እንዴት ያቀርበዋል! ስለ ጥንቱ የአሕዛብ አምላክ ጁፒተር፥ ወይም ስለ ሕንድ ወይም ስለ ቻይና አማልክት ይህን ማን ሰምቶ ያውቃል? ይህ ለእስራኤል አምላክ ብቻ የተለየ ቋንቋ ነው፤ ለመልካም ሰዎች አስታማሚና አገልጋይ ለመሆን ራሱን ዝቅ የሚያደርግ እርሱ ነው። በአንድ እጁ ቢመታ በሌላው ይደግፋል። ኦ፥ አንድ ሰው በጌታ በራሱ እቅፍ ላይ ወድቆ በዚያ ሲሸከም መዛል የተባረከ ነው! ጸጋ ከፈውስ መድኃኒቶች ሁሉ የሚበልጥ ነው፤ መለኮታዊ ፍቅር ለደከመ ታማሚ ከሁሉ የሚያስተማምን ብርታት ሰጪ ነው፤ አጥንቶች ቆዳን ሰንጥቀው ሊወጡ ሲደርሱ እንኳ ነፍስን እንደ ኃያል ብርቱ ያደርጋታል። እንደ ጌታ ያለ ሐኪም፥ እንደ ተስፋውም ያለ ብርታት ሰጪ፥ እንደ ፍቅሩም ያለ የወይን ጠጅ የለም።
አንባቢው ለድሆች ያለበትን ግዴታ ሳይፈጽም ቀርቶ ከሆነ የሚያጣውን ይመልከት፥ ወዲያውኑም ወዳጃቸውና ረዳታቸው ይሁን።
ማርች 27
ወደ እግዚአብሔር መቅረብ
«ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል» ያዕቆብ 4:8
ወደ እግዚአብሔር ይበልጥ በቀረብን መጠን እርሱም ራሱን በበለጠ ቸርነት ይገልጥልናል። አባካኙ ልጅ ወደ አባቱ ሲመጣ አባቱ ሊቀበለው ይሮጣል። የተቅበዘበዘችው ርግብ ወደ መርከቡ ስትመለስ ኖኅ ወደ ራሱ ሊያስገባት እጁን ይዘረጋል። ርኅሩኅ ሚስት የባልዋን አብሮነት ስትፈልግ እርሱ በፍቅር ክንፍ ወደ እርሷ ይመጣል። እንግዲያስ ውድ ወዳጄ ሆይ፥ በቸርነት ወደሚጠብቀን፥ አዎን ሊቀበለን ወደሚመጣው ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ።
በኢሳይያስ 58:9 ያለውን ክፍል አስተውለህ ታውቃለህን? በዚያ ጌታ ለሕዝቡ «እነሆኝ» እያለ ራሱን በእጃቸው ያኖረ ይመስላል። ይህም እንዲህ እንደ ማለት ነው — «ምን ልትሉኝ ትወዳላችሁ? ምን ላድርግላችሁ? ልባርካችሁ እጠብቃለሁ።» ታዲያ ለመቅረብ እንዴት እናመነታለን? እግዚአብሔር ይቅር ለማለት፥ ለመባረክ፥ ለማጽናናት፥ ለመርዳት፥ ሕያው ለማድረግ፥ ለማዳን ቅርብ ነው። ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ዋናው ጉዳያችን ይሁን። ይህ ከተደረገ ሁሉ ተደርጓል። ወደ ሌሎች ብንቀርብ ብዙ ሳይቆዩ ሊሰለቹንና ሊተዉን ይችላሉ፤ ጌታን ብቻ ብንፈልግ ግን በአሳቡ ምንም ለውጥ አይመጣም፤ ይልቁንም በበለጠ ሙላትና በበለጠ ደስታ ባለው ኅብረት ወደ እኛ ይበልጥ እየቀረበ ይመጣል።
ማርች 28
ቀድሞ መምራት
«እግዚአብሔርም ራስ ያደርግሃል እንጂ ጅራት አያደርግህም» ዘዳግም 28:13
ጌታን ብንታዘዝ በረከቱ በእኛ ላይ ማረፉን ጠላቶቻችን እንዲያዩ ያስገድዳቸዋል። ይህ የሕግ ተስፋ ቢሆንም ለእግዚአብሔር ሕዝብ አሁንም ይጸናል፤ ኢየሱስ እርግማኑን አስወግዷልና፥ በረከቱን ግን አጽንቷል።
በቅዱስ ተጽዕኖ በሰዎች መካከል ቀድሞ መምራት የቅዱሳን ድርሻ ነው፤ በሌሎች ወዲያና ወዲህ የሚጎተቱ ጅራት ሊሆኑ አይገባቸውም። ለዘመኑ መንፈስ መገዛት የለብንም፤ ይልቁንም ዘመኑ ለክርስቶስ እንዲሰግድ ማስገደድ አለብን። ጌታ ከእኛ ጋር ቢሆን ለሃይማኖት መቻቻልን አንለምንም፤ ይልቁንም በማኅበረሰቡ ዙፋን ላይ ልናስቀምጠው እንሻለን። ጌታ ኢየሱስ ሕዝቡን ካህናት አላደረገምን? በእርግጥ ሊያስተምሩ ይገባቸዋል፤ ከማያምኑ ሰዎች ፍልስፍና የሚማሩ ሊሆኑ አይገባቸውም። በክርስቶስ በምድር ላይ እንድንነግሥ ነገሥታት አልተደረግንምን? እንግዲህ የልማድ አገልጋዮች፥ የሰው አስተያየት ባሪያዎች እንዴት እንሆናለን?
ውድ ወዳጄ ሆይ፥ ለኢየሱስ ትክክለኛ ስፍራህን ይዘሃልን? ብዙዎች ፈሪዎች ባይሆኑም እንኳ ዓይናፋሮች ስለ ሆኑ ዝም ይላሉ። የጌታ የኢየሱስ ስም ከኋላ ተሸሽጎ እንዲቀመጥ እንፍቀድን? ሃይማኖታችን እንደ ጅራት እየተጎተተ ይሂድን? ይልቁንም ቀድሞ ሊመራና በራሳችንም በሌሎችም ላይ የሚገዛ ኃይል ሊሆን አይገባውምን?
ማርች 29
የማይደነግጥ እምነት
«እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ ማንም ሊጎዳህ አይነሣብህም» ሐዋርያት ሥራ 18:10
ጌታ ጳውሎስ በቆሮንቶስ የሚሠራው ሥራ እስካለው ድረስ የሕዝቡ ቍጣ ተገትቶ ነበር። አይሁድ ተቃወሙ ተሳደቡም፤ ነገር ግን የወንጌልን ስብከትም ሆነ የሰሚዎችን መለወጥ ማስቆም አልቻሉም። እግዚአብሔር እጅግ ኃይለኛ በሆኑ አእምሮዎች ላይ ሥልጣን አለው። የሰው ቍጣ በገነፈለ ጊዜ እንዲያመሰግነው ያደርገዋል፤ ሲገታውም ግን ቸርነቱን አብልጦ ይገልጣል፤ ሊገታውም ይችላል። «አቤቱ፥ ሕዝብህ እስኪያልፍ ድረስ በክንድህ ታላቅነት እንደ ድንጋይ ጸጥ ይላሉ።»
ስለዚህ ግዴታህን እየፈጸምህ መሆንህን ስታውቅ ሰውን ከቶ አትፍራ። ኢየሱስ ያደርግ እንደ ነበረ በቀጥታ ወደ ፊት ሂድ፤ የሚቃወሙህም እንደ ተቀጠቀጠ ሸምበቆና እንደሚጤስ የጥዋፍ ክር ይሆናሉ። ብዙ ጊዜ ሰዎች ራሳቸው ስለ ፈሩ የሚያስፈራ ምክንያት አጋጥሟቸዋል፤ በእግዚአብሔር ያለ የማይደነግጥ እምነት ግን በኃያል ሰው መንገድ ላይ እንዳለ የሸረሪት ድር ፍርሃትን ጠርጎ ያስወግዳል። ጌታ ካልፈቀደ በቀር ማንም ሊጎዳን አይችልም። ዲያብሎስን ራሱን በአንድ ቃል የሚያባርረው እርሱ የዲያብሎስን ወኪሎች በእርግጥ ሊቆጣጠር ይችላል። ምናልባት አንተ ከምትፈራቸው ይልቅ እነርሱ አንተን ይበልጥ ፈርተው ይሆናል። ስለዚህ ወደ ፊት ሂድ፤ ጠላቶችን አገኛለሁ ብለህ በተጠባበቅህበት ስፍራ ወዳጆችን ታገኛለህ።
ማርች 30
ጸሎት፥ ምስጋና፥ ውዳሴ
«በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል» ፊልጵስዩስ 4:6,7
ጭንቀት አይሁን፥ ሁሉም ጸሎት ይሁን። ስጋት አይሁን፥ ከእግዚአብሔር ጋር ብዙ የደስታ ኅብረት ይሁን። ምኞቶችህን ወደ ሕይወትህ ጌታ፥ ወደ ነፍስህ ጠባቂ ውሰድ። ሁለት እጅ ጸሎትና አንድ እጅ መዓዛ ያለው ውዳሴ ይዘህ ወደ እርሱ ሂድ። በምስጋና እንጂ በጥርጣሬ አትጸልይ። የለመንኸውን እንዳገኘህ አስብ፤ ስለዚህ ስለ ጸጋው እግዚአብሔርን አመስግን። ጸጋን እየሰጠህ ነው፤ አንተም ምስጋናን ስጠው። ምንም አትሰውር። አንዳችም ጉድለት በብብትህ ውስጥ እንዲቈጠቍጥህ አትተው፤ «ልመናችሁን አስታውቁ።» ወደ ሰው አትሩጥ። በእርሱ ወደሚወድህ ወደ ኢየሱስ አባት ወደ አምላክህ ብቻ ሂድ።
ይህ የእግዚአብሔርን የራሱን ሰላም ያመጣልሃል። የምትደሰትበትን ሰላም ልትረዳው አትችልም። ወሰን በሌለው እቅፉ ይጠቀልልሃል። ልብና አሳብ በክርስቶስ ኢየሱስ በዕረፍት ባሕር ውስጥ ይዘፈቃሉ። ሕይወት ወይም ሞት፥ ድህነት፥ ሕመም፥ ስም ማጥፋት ቢመጣ፥ ከሚያናውጥ ነፋስና ከሚያጨልም ደመና ሁሉ በላይ በኢየሱስ ትኖራለህ። ይህን ውድ ትእዛዝ አትታዘዝምን?
አዎን ጌታ ሆይ፥ አምንሃለሁ፤ ነገር ግን አለማመኔን እርዳ ብዬ እለምንሃለሁ።
ማርች 31
የአእምሮ መረጋጋት
«ድንገት ከሚመጣ ፍርሃት፥ ከኃጥአንም ጥፋት በመጣ ጊዜ አትፍራ። እግዚአብሔር መታመኛህ ይሆናልና፥ እግርህንም ከወጥመድ ይጠብቃል» ምሳሌ 3: 25,26
እግዚአብሔር በፍርድ በወጣ ጊዜ ሕዝቡ እንዲደነግጡ አይወድም። የወጣው ጻድቃንን ሊጠብቅ እንጂ ሊጎዳ አይደለም።
ድፍረትን እንዲያሳዩ ይወዳል። የእግዚአብሔርን ሀልዎት የምናጣጥም እኛ የአእምሮ መረጋጋትን ልናሳይ ይገባናል። ጌታ ራሱ በድንገት ሊመጣ ስለሚችል በማንኛውም ድንገተኛ ነገር ልንደነቅ አይገባንም። ባልተጠበቁ ክፉ ነገሮች ግርግርና ጩኸት መካከል መረጋጋት የመለኮታዊ ፍቅር ውድ ስጦታ ነው።
ጌታ የመረጣቸው የኃጥአን ጥፋት ለዓለም እውነተኛ መቅሠፍት አለመሆኑን እንዲያዩ ማስተዋልን እንዲያሳዩ ይወዳል። ክፉ ኃጢአት ብቻ ነው፤ ከእርሱ በኋላ የሚመጣው ቅጣት ማኅበረሰቡን ከመበስበስ እንደሚጠብቅ ጨው ነው። ከኃጢአት ከሚመጣው ሲኦል ይልቅ ሲኦልን በሚያስገባው ኃጢአት እጅግ ልንደነግጥ ይገባናል።
እንዲሁም የጌታ ሕዝብ ታላቅ የመንፈስ ጸጥታ ሊያሳዩ ይገባቸዋል። ሰይጣንና የእባቡ ዘር በተንኰል ሁሉ የተሞሉ ናቸው፤ ከእግዚአብሔር ጋር የሚሄዱ ግን በአታላይ ወጥመዳቸው አይያዙም። በኢየሱስ የምታምን ሆይ፥ ወደ ፊት ሂድ፤ ጌታም መታመኛህ ይሁን።