የእምነት ባንክ የቼክ ደብተር
የሴፕቴምበር ወር

ምዕራፍ 10 · 23 ደቂቃ ንባብ · 30 ደቂቃ ማዳመጥ

የሴፕቴምበር ወር

ሴፕቴምበር 1

በመታዘዝ፥ በፍቅር መኖር

«ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ» ዮሐንስ 15:10

እነዚህ ነገሮች ሊለያዩ አይችሉም፤ በመታዘዝ መኖርና በኢየሱስ ፍቅር መኖር። የጌታችን ደስታ መሆናችንን ሊያረጋግጥ የሚችለው በክርስቶስ አገዛዝ ሥር ያለ ሕይወት ብቻ ነው። በፍቅሩ ልንሞቅ ብንወድ የጌታችንን ትእዛዝ መጠበቅ አለብን። በኃጢአት ብንኖር በክርስቶስ ፍቅር ልንኖር አንችልም። እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ቅድስና ከሌለን ኢየሱስን ደስ ልናሰኝ አንችልም። ስለ ቅድስና ግድ የሌለው ሰው ስለ ኢየሱስ ፍቅር አንዳች አያውቅም።

የጌታችንን ፍቅር እያወቁ መደሰት እጅግ ስስ ነገር ነው። ሜርኩሪ ለቅዝቃዜና ለሙቀት ከሚሰማው እጅግ በበለጠ ለኃጢአትና ለቅድስና ይሰማዋል። ልባችን ርኅሩኅ ሲሆን፥ ጌታችንን ኢየሱስን ለማክበር በሐሳብ፥ በከንፈርና በሕይወት ስንጠነቀቅ፥ ያን ጊዜ ቍጥር የሌለው የፍቅሩን ምልክት እንቀበላለን። ይህ ደስታ እንዲቀጥልልን ብንወድ ቅድስናን ማስቀጠል አለብን። ጌታ ኢየሱስ ፊታችንን ከእርሱ ካልሰወርን በቀር ፊቱን ከእኛ አይሰውርም። ፀሐያችንን የሚያጨልመውን ደመና የሚሠራው ኃጢአት ነው፤ በንቃት ብንታዘዝና ፈጽመን ብንቀደስ ግን፥ እግዚአብሔር በብርሃን እንዳለ በብርሃን እንመላለሳለን፤ ኢየሱስም በአብ ፍቅር እንደሚኖር እንዲሁ እኛም በኢየሱስ ፍቅር በእርግጥ እንኖራለን። እነሆ፥ የሚያስፈራ «ብትጠብቁ» የሚል ቃል ያለበት ጣፋጭ ተስፋ። ጌታ ሆይ፥ ይህን «ብትጠብቁ» በእጄ እንድይዝ አድርገኝ፤ እንደ መክፈቻ ይህን ሣጥን ይከፍታልና።

ሴፕቴምበር 2

ለማወቅ ተከተል

«እግዚአብሔርንም ለማወቅ ብንከተል እናውቃለን» ሆሴዕ 6:3

ቅዱስ እውቀትን የምናገኘው በአንድ ጊዜ ሳይሆን በጥቂት በጥቂቱ ነው፤ ሥራችንም መጽናትና ቀስ በቀስ መማር ነው። ዕድገታችን ቢዘገይም ተስፋ መቍረጥ አያስፈልገንም፤ ገና እናውቃለንና። አስተማሪያችን የሆነው ጌታ ምንም ያህል ለማስተዋል የዘገየን ብንሆን አይተወንም፤ የሰው ሞኝነት በምንም መጠን ጥበቡን ቢያሸንፍ ለክብሩ አይሆንምና። ጌታ አላዋቂዎችን ጠቢባን ማድረግ ደስ ያሰኘዋል።

ተግባራችን በዋናው ጉዳያችን ላይ መጽናትና ማወቅን መከተል ነው፤ ይህን ወይም ያን ልዩ ትምህርት ሳይሆን ይሖዋን ራሱን ለማወቅ። አብን፥ ወልድንና መንፈስን፥ ሥላሴ አምላክን ማወቅ የዘላለም ሕይወት ይህ ነው፤ በዚህ እንጽና፤ በዚህ መንገድ ፍጹም ትምህርት እናገኛለንና። ጌታን ለማወቅ በመከተል ከተቀደድን በኋላ መፈወስን፥ ከተመታን በኋላ መታሰርን፥ ከሞትም በኋላ ሕይወትን እንማራለን። ልብ ሁሉን የሚችለውን ጌታ ዱካ ሲከተል ልምድ ፍጹም ሥራውን ይሠራል።

ነፍሴ ሆይ፥ ከኢየሱስ ጋር ተጣበቂ፤ እግዚአብሔርን በኢየሱስ ለማወቅ ተከተዪ፤ እንዲሁም ከሳይንሶች ሁሉ እጅግ የሚበልጠውን የክርስቶስን እውቀት ታገኛለሽ። መንፈስ ቅዱስ ወደ እውነት ሁሉ ይመራሻል። ይህ የጸጋው ሥራ አይደለምን? እንዲፈጽመው በእርሱ ተደገፊ።

ሴፕቴምበር 3

ከመንፈሳዊ ሞት መውጣት

«ሕዝቤ ሆይ፥ መቃብራችሁን በከፈትሁ ጊዜ ከመቃብራችሁም ባወጣኋችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ» ሕዝቅኤል 37:13

በእርግጥ እንዲህ መሆን አለበት፤ ከሙታን ሕይወትን የተቀበሉ በእንዲህ ያለ ትንሣኤ የጌታን እጅ በእርግጥ ያውቃሉ። ሰው ሊያገኘው ከሚችለው ለውጥ ሁሉ ይህ የሚበልጥና እጅግ የሚደነቅ ነው፤ ከመንፈሳዊ ሞት መቃብር ወጥቶ በመንፈሳዊ ሕይወት ብርሃንና ነጻነት ደስ እንዲለው መደረግ። ይህን ሊሠራ የሚችል ከሕያው እግዚአብሔር፥ ከሕይወት ጌታና ሰጪ በቀር ማንም የለም።

ወዮልኝ! ደረቅ አጥንቶች በሞሉበት ሸለቆ ውስጥ እንደ ማንኛቸውም ደርቄ ተኝቼ የነበርሁበትን ጊዜ እንዴት አስታውሰዋለሁ! ነጻና ሉዓላዊ ጸጋ የእግዚአብሔርን ሰው በእኔ ላይ ትንቢት እንዲናገር የላከበት ቀን የተባረከ ነበር! ያ የእምነት ቃል በደረቁ አጥንቶች መካከል ስላስነሣው መናወጥ ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን። ከዚህም ይልቅ ሕያው ያደረገኝ ከአራቱ ነፋሳት የመጣው ያ ሰማያዊ እስትንፋስ የተባረከ ነው! አሁን የዘላለም ሕያው የይሖዋን ሕይወት ሰጪ መንፈስ አውቃለሁ። በእውነት ይሖዋ ሕያው አምላክ ነው፤ ሕያው አድርጎኛልና። አዲሱ ሕይወቴ በመጠውለጉና በኀዘኑ እንኳ ጌታ እንደሚገድልና ሕያው እንደሚያደርግ ግልጥ ማስረጃ ይሆነኛል። እርሱ ብቻ አምላክ ነው። ታላቅ፥ ቸርና ክቡር የሆነ ሁሉ እርሱ ነው፤ ሕያው የሆነችው ነፍሴም እንደ ታላቁ «እኔ ነኝ» ታመልከዋለች። ክብር ሁሉ ለቅዱስ ስሙ ይሁን! በሕይወት እስካለሁ ድረስ አመሰግነዋለሁ።

ሴፕቴምበር 4

ያለ ሰልፍ ድል

«ለይሁዳ ቤት ግን እራራለሁ፥ በአምላካቸውም በእግዚአብሔር አድናቸዋለሁ፤ በቀስትም በሰይፍም በሰልፍም በፈረሶችም በፈረሰኞችም አላድናቸውም» ሆሴዕ 1:7

የከበረ ቃል! ይሖዋ ራሱ በምሕረቱ ብዛት ሕዝቡን ያድናል፤ በተለመደው መንገድ ግን አያደርገውም። ሰዎች ለስሙ የሚገባውን ክብር ለእግዚአብሔር ለመስጠት ይዘገያሉ። በሰይፍና በቀስት ወደ ሰልፍ ወጥተው ድል ቢያደርጉ አምላካቸውን ማመስገን ይገባቸዋል፤ እነርሱ ግን አያደርጉትም፤ ይልቁንም የራሳቸውን ቀኝ ክንድ ማግነንና በፈረሶቻቸውና በፈረሰኞቻቸው መመካት ይጀምራሉ። ስለዚህ ይሖዋችን ክብሩ ሁሉ ለእርሱ ብቻ እንዲሆን ብዙ ጊዜ ሕዝቡን ያለ ሁለተኛ መሣሪያ ሊያድን ይወስናል።

እንግዲህ ልቤ ሆይ፥ ወደ ሰው ሳይሆን ወደ ጌታ ብቻ ተመልከት። የምትመለከተው ሌላ ሰው በሌለ ጊዜ እግዚአብሔርን አብልጠህ በግልጥ ለማየት ተጠባበቅ። ወዳጅ፥ መካሪ፥ ከኋላዬም የሚቆም ሰው ባይኖረኝ፥ ጌታ ራሱ ከጎኔ እንደ ሆነ ከተሰማኝ ትምክህቴ አይቀንስ፤ እንዲያውም ጥቅሱ እንደሚያመለክት ያለ ሰልፍ ድል ቢሰጠኝ ደስ ይበለኝ። ይሖዋ ራሱ ቢምረኝና ክንዱን ለመከላከያዬ ቢያነሣ ፈረሶችንና ፈረሰኞችን ለምን እለምናለሁ? እግዚአብሔር የሚያድን ከሆነ ቀስት ወይም ሰይፍ ለምን ያስፈልገኛል? ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ልታመን እንጂ አልፍራ። አሜን።

ሴፕቴምበር 5

በሄድሁበት ሁሉ ከእኔ ጋር

«እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሆናል» 2ኛ ዜና መዋዕል 20:17

ይህ ለኢዮሣፍጥ ታላቅ ምሕረት ነበር፤ ብዙ ሕዝብ ሊወጋው መጥቶ ነበርና፤ ለእኔም ታላቅ ምሕረት ይሆናል፤ ታላቅ ችግር አለብኝ፥ ኃይልም ጥበብም የለኝምና። ጌታ ከእኔ ጋር ቢሆን ማን ቢተወኝ ግድ የለኝም። ጌታ ከእኔ ጋር ቢሆን በሕይወት ሰልፍ ድል አደርጋለሁ፤ ፈተናዬ በበዛ መጠን ድሌ ይበልጥ ክቡር ይሆናል። ጌታ ከእኔ ጋር እንደ ሆነ እንዴት ልረዳ እችላለሁ?

እኔ ከእርሱ ጋር ብሆን እርሱ በእርግጥ ከእኔ ጋር ነው። በታማኝነቱ ብታመን፥ ቃሉን ባምን፥ ትእዛዙንም ብታዘዝ፥ እርሱ በእርግጥ ከእኔ ጋር ነው። በሰይጣን ወገን ብሆን እግዚአብሔር ይቃወመኛል፤ ሌላ ሊሆንም አይችልም፤ እግዚአብሔርን ለማክበር ብኖር ግን እርሱ እንደሚያከብረኝ እርግጠኛ ልሆን እችላለሁ።

ኢየሱስ ብቸኛና አንድ አዳኜ ከሆነ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር እንደ ሆነ ፈጽሞ እርግጠኛ ነኝ። ነፍሴን በእግዚአብሔር አንድያ ልጅ እጅ ካኖርኋት፥ ልጁ እንዳይዋረድ አብ እኔን ለመጠበቅ ኃይሉን ሁሉ እንደሚገልጥ እርግጠኛ ልሆን እችላለሁ።

ለዛሬ የተሰጠውን አጭር ግን ጣፋጭ ጥቅስ የሚይዝ እምነት ምነው ቢኖረኝ! አቤቱ ጌታ ሆይ፥ ይህን ቃል ለባሪያህ ፈጽም! በቤት፥ በመንገድ፥ በእርሻ፥ በሱቅ፥ በሰዎች መካከልና ብቻዬንም ስሆን ከእኔ ጋር ሁን። ከሕዝብህም ሁሉ ጋር ደግሞ ሁን።

ሴፕቴምበር 6

የጸና ልብ

«እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ አይዞህ፥ ልብህንም ያጸናል፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ እላለሁ» መዝሙር 27:14

ጠብቅ! ጠብቅ! መጠበቅህ ጌታን ይሁን! መጠበቅ የሚገባው እርሱ ነው። የምትጠብቀውን ነፍስ ፈጽሞ አያሳፍራትም።

እየጠበቅህ መንፈስህን አበርታ። ታላቅ ማዳንን ተጠባበቅ፤ ስለ እርሱም እግዚአብሔርን ለማመስገን ተዘጋጅ።

ሊያበረታታህ የሚገባው ተስፋ በጥቅሱ መካከል ይገኛል፤ «ልብህንም ያጸናል።» ይህ ርዳታ ወደሚያስፈልግህ ስፍራ ወዲያው ይደርሳል። ልብ ጤነኛ ከሆነ የቀረው ሰውነት ሁሉ በመልካም ይሠራል። ልብ ጸጥታና መጽናናት ይፈልጋል፤ ሁለቱም ልብ ከጸና ይመጣሉ። ብርቱ ልብ ያርፋል፥ ደስም ይለዋል፥ በሰውነቱ ሁሉም ኃይልን ይረጫል።

ያንን የተሰወረ የሕይወት ዕቃ፥ ልብን፥ ብርታት ሊያፈስስበት ደርሶ የሚችል ሌላ ማንም የለም። የሠራው እርሱ ብቻ ሊያበረታው ይችላል። እግዚአብሔር በኃይል የተሞላ ነው፤ ስለዚህም ለሚያስፈልጋቸው ሊሰጥ ይችላል። እንግዲህ አይዞህ፤ ጌታ ብርታቱን ይሰጥሃልና፤ በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ጸጥ ትላለህ፥ በኀዘንም ውስጥ ደስ ይልሃል።

እነዚህን መስመሮች የጻፈው ሰው ዳዊት እንደ ጻፈው ሊጽፍ ይችላል፤ «እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ እላለሁ።» በእርግጥ እላለሁ። ጌታን መጠበቅ ለእኔ መልካም እንደ ሆነ በረጅምና በጥልቅ ልምድ አውቃለሁ።

ሴፕቴምበር 7

ሁሉን የሚችል ጸጋ የሚደርስበት

«እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም በተባለበት ስፍራ በዚያ የሕያው እግዚአብሔር ልጆች ናችሁ ይባላቸዋል» ሆሴዕ 1:10

ሉዓላዊ ጸጋ እንግዶችን ልጆች ሊያደርግ ይችላል፤ ጌታም በዚህ ዓመፀኞችን እንዲሁ ሊያደርጋቸውና ያደረገውንም እንዲያውቁ ሊያደርጋቸው ዓላማው እንደ ሆነ ይናገራል። የተወደድህ አንባቢ ሆይ፥ ጌታ ይህን በእኔ ላይ አድርጓል፤ ለአንተስ እንዲሁ አድርጎልሃልን? እንግዲያስ የሚሰገድለትን ስሙን ለማመስገን እጅና ልብ እናገናኝ።

አንዳንዶቻችን እጅግ ኃጢአተኞች ስለ ነበርን የጌታ ቃል ለኅሊናችንና ለልባችን «ሕዝቤ አይደላችሁም» ብሎ በእውነት ተናግሯል። በእግዚአብሔር ቤትም በራሳችን ቤትም መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ በነፍሳችን ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ ድምፅ «ሕዝቤ አይደላችሁም» የሚል ነበር። በእውነት የሚያሳዝን የፍርድ ድምፅ ነበር። አሁን ግን በዚያው ስፍራ፥ ከዚያው አገልግሎትና መጽሐፍ፥ «የሕያው እግዚአብሔር ልጆች ናችሁ» የሚል ድምፅ እንሰማለን። ስለዚህ በበቂ ልናመሰግን እንችላለንን? ድንቅ አይደለምን? ለሌሎችስ ተስፋ አይሰጠንምን? ሁሉን የሚችል ጸጋ ከማይደርስበት ማን ነው? ጌታ በእኛ ላይ እንዲህ ያለ ድንቅ ለውጥ ካደረገ በማንም ላይ እንዴት ተስፋ እንቈርጣለን?

ይህን አንድ ታላቅ ተስፋ የጠበቀ ሌላውን ሁሉ ይጠብቃል፤ ስለዚህ በአምልኮና በትምክህት መዝሙር ወደ ፊት እንሂድ።

ሴፕቴምበር 8

የተቀጠቀጠና የሚጤስ

«የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ አይሰብርም፥ የሚጤሰውንም የጧፍ ክር አያጠፋም» ኢሳይያስ 42:3

እንግዲያስ ከጌታዬ ርኅራኄን እጠብቃለሁ። በእርግጥ ራሴን ብዙ ቢባል እንደ ሸምበቆ ደካማ፥ ተጣማሚና ዋጋ ቢስ አድርጌ እቈጥራለሁ። አንድ ሰው «አንተን እንደ ቄጤማ እንኳ አልቈጥርህም» አለ፤ ንግግሩም ጨካኝ ቢሆን ሐሰት አልነበረም። ወዮ! በወንዝ አጠገብ ከሚበቅል ሸምበቆ ይልቅ የከፋሁ ነኝ፤ እርሱ ቢያንስ ራሱን ቀና ማድረግ ይችላልና። ተቀጥቅጫለሁ፤ ክፉኛና በኀዘን ተቀጥቅጫለሁ። አሁን በእኔ ውስጥ ዜማ የለም፤ ዜማውን ሁሉ የሚያፈስስ ስንጥቅ አለብኝ። ወዮልኝ! ኢየሱስ ግን አይሰብረኝም፤ እርሱ ካልሰበረኝ ሌሎች ሊያደርጉ የሚሞክሩት ብዙም አያሳስበኝም። ጣፋጭና ሩኅሩኅ ጌታ ሆይ፥ በጥበቃህ ሥር እሸሸጋለሁ፥ መቀጥቀጤንም እረሳለሁ!

በእውነት ብርሃኑ ጠፍቶ ጢሱ ብቻ ከቀረው «ከሚጤሰው የጧፍ ክር» ጋር ልመሰል ይገባኛል። ከጥቅም ይልቅ ሸክም እንደ ሆንሁ እፈራለሁ። ፍርሃቴ ዲያብሎስ ብርሃኔን አጥፍቶ የሚያስጠላ ጢስ እንደ ተወልኝ፥ ጌታዬም በቅርቡ ማጥፊያ እንደሚጭንብኝ ይነግረኛል። ነገር ግን በሕጉ ሥር የፋና መቍረጫዎች ቢኖሩም ማጥፊያዎች እንዳልነበሩ አስተውላለሁ፤ ኢየሱስም አያጠፋኝም፤ ስለዚህ ተስፋ አለኝ። ጌታ ሆይ፥ እንደ ገና አቀጣጥለኝ፤ ለክብርህና ርኅራኄህን ከፍ ለማድረግ እንዳበራ አድርገኝ።

ሴፕቴምበር 9

ፍርሃትም ስፍራ አለው

«ሁልጊዜ የሚፈራ ሰው ምስጉን ነው» ምሳሌ 28:14

እግዚአብሔርን መፍራት የእውነተኛ ሃይማኖት ሁሉ መጀመሪያና መሠረት ነው። ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ግርማ ፍርሃትና አክብሮት ከሌለ ለሚያበሩት በጎነቶች መቆሚያ የለም። ነፍሱ የማታመልክ ሰው በቅድስና ፈጽሞ አይኖርም።

ክፉ ከማድረግ በቅናት የሚፈራ ሰው ደስተኛ ነው። ቅዱስ ፍርሃት ከመዝለሉ በፊት ብቻ ሳይሆን ከመንቀሳቀሱም በፊት ይመለከታል። ስሕተትን ይፈራል፥ ተግባርን መተውን ይፈራል፥ ኃጢአት መሥራትን ይፈራል። ክፉ ባልንጀርነትን፥ ልቅ ንግግርንና አጠራጣሪ አካሄድን ይፈራል። ይህ ሰውን ጐስቋላ አያደርገውም፤ ደስታን ያመጣለታል እንጂ። በዘብ ጥበቃው ላይ ከሚተኛ ወታደር ይልቅ ነቅቶ የሚጠብቅ ዘብ ደስተኛ ነው። ክፉውን አይቶ የሚያመልጥ ሳይጠነቀቅ ሄዶ ከሚጠፋ ይልቅ ደስተኛ ነው።

እግዚአብሔርን መፍራት ሰውን በተመረጠ መንገድ የሚመራ ጸጥ ያለ ጸጋ ነው፤ ስለዚያም መንገድ «አንበሳ አይገኝበትም፥ ነጣቂ አውሬም አይወጣበትም» ተብሎ ተጽፏል። የክፉውን መልክ እንኳ መፍራት ሰው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ልብሱን ከዓለም እድፍ ሳያረክስ እንዲጠብቅ የሚያስችል የሚያነጻ መርሕ ነው። በሁለቱም ትርጕም «ሁልጊዜ የሚፈራ» ደስተኛ ይሆናል። ሰሎሞን ዓለማዊነትንም ቅዱስ ፍርሃትንም ሞክሮ ነበር፤ በአንዱ ከንቱነትን፥ በሌላው ደስታን አገኘ። ሙከራውን አንድገመው፤ ፍርዱን እንጠብቅ እንጂ።

ሴፕቴምበር 10

መግባትና መውጣት

«በመግባትህ ቡሩክ ትሆናለህ፥ በመውጣትህም ቡሩክ ትሆናለህ» ዘዳግም 28:6

የሕጉ በረከቶች አልተሻሩም። ኢየሱስ ቅጣቱን በተሸከመ ጊዜ ተስፋውን አጸና። የጌታዬን ትእዛዝ ብጠብቅ ይህን ተስፋ ያለ ጥርጥር የራሴ ላደርገው እችላለሁ።

ዛሬ ክፉ ወሬ ሳልፈራ ወደ ቤቴ እገባለሁ፤ ከጌታዬም የምሥራች ለመስማት እየጠበቅሁ ወደ እልፍኜ እገባለሁ። ራሴን በመመርመር ወደ ራሴ ለመግባት፥ ሥራዬንም በትጋት በማየት ወደ ጉዳዮቼ ለመግባት አልፈራም። በቤት ውስጥ፥ በራሴ ነፍስ ውስጥ፥ የምሠራው ብዙ ሥራ አለኝ፤ በዚያ ሁሉ ላይ በረከት ምነው ቢሆን፤ ከእኔ ጋር ሊኖር የተስፋ ቃል የሰጠው የጌታ ኢየሱስ በረከት።

ደግሞም መውጣት አለብኝ። ፍርሃት በቤት ውስጥ ብቻ እንድቀመጥና ዳግመኛ ወደ ኃጢአተኛው ዓለም እንዳልወጣ ያስመኘኛል። ነገር ግን በጥሪዬ መውጣት አለብኝ፤ ወንድሞቼን ለመርዳትና ለኃጢአተኞችም ለመጥቀም መውጣት አለብኝ። የእምነት ተከላካይና የክፋት አጥቂ መሆን አለብኝ። ዛሬ በመውጣቴ ላይ በረከት ምነው ቢሆን! ጌታ ሆይ፥ አንተ ወደምትመራኝ፥ በመልእክትህ፥ በትእዛዝህ ሥርና በመንፈስህ ኃይል እንድሄድ አድርገኝ።

ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ከእኔ ጋር ግባ እንግዳዬም ሁን፤ ከዚያም ከእኔ ጋር ውጣ፤ በመንገድ ስትናገረኝም ልቤ እንዲቃጠል አድርግ።

ሴፕቴምበር 11

መከራ የተቀበሉ ብርቱ አማኞች ይሆናሉ

«ለሰው በታናሽነቱ ቀንበርን ቢሸከም መልካም ነው» ሰቆቃው ኤርምያስ 3:27

ይህ እንደ ተስፋ ቃል ያህል መልካም ነው። ቀንበርን መሸከም ለእኔ መልካም ሆኖአል፥ አሁንም መልካም ነው፥ ወደ ፊትም መልካም ይሆናል።

ገና በሕይወቴ መጀመሪያ የኃጢአትን ወቀሳ ክብደት ሊሰማኝ ግድ ሆነ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ነፍስን የሚያበለጽግ ሸክም ሆኖ ተገኝቷል። በጸጋ የሆነውን የመዳን አስፈላጊነት በጥልቅ ልምድ ባልማር ኖሮ ወንጌልን እንዲህ እወድደው ነበርን? እናቱ በኀዘን ስለ ወለደችው ያቤጽ ከወንድሞቹ ይልቅ የከበረ ነበረ፤ ለእግዚአብሔር ሲወለዱ ብዙ መከራ የሚቀበሉም በሉዓላዊ ጸጋ የሚያምኑ ብርቱ አማኞች ይሆናሉ።

የነቀፋ ቀንበር የሚያሰለች ነው፤ ነገር ግን ሰውን ለሚመጣው ክብር ያዘጋጀዋል። በንቀት መካከል ያላለፈ ሰው መሪ ለመሆን አይበቃም። ውርደት ካልቀደመው ምስጋና ያሰክራል። ያለ ትግል ወደ ከፍታ የሚወጡ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ወደ ውርደት ይወድቃሉ።

የመከራ፥ የተስፋ መቍረጥና የከባድ ድካም ቀንበር ፈጽሞ የሚፈለግ አይደለም፤ ጌታ ግን በወጣትነታችን ሲጭንብን እግዚአብሔርን የሚያከብርና ቤተ ክርስቲያንን የሚባርክ ጠባይ ብዙ ጊዜ ያሳድጋል።

ነፍሴ ሆይ፥ ነዪ፤ አንገትሽን አጎንብሺ፤ መስቀልሽን አንሺ። በወጣትነትሽ መልካም ሆኖልሻል፤ አሁንም አይጎዳሽም። ስለ ኢየሱስ ብለሽ በደስታ በትከሻሽ ተሸከሚው።

ሴፕቴምበር 12

ቤተ ሰቤስ?

«በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ» የሐዋርያት ሥራ 16:31

ሰይፍ በጕሮሮው ላይ ለነበረ ሰው የተነገረው ይህ ወንጌል ለእኔም ወንጌል ነው። ብሞት ይህ ይበቃኛል፤ በሕይወት ሳለሁም የሚያስፈልገኝ ይህ ብቻ ነው። ከራሴ፥ ከኃጢአትና ከግል ብቃት ሐሳብ ሁሉ ዞር ብዬ እግዚአብሔር የሰጠውን አዳኝ ጌታ ኢየሱስን እታመናለሁ። በእርሱ አምናለሁ፥ በእርሱ ላይ አርፋለሁ፥ ሁሉ በሁሉ እንዲሆንልኝ እቀበለዋለሁ። ጌታ ሆይ፥ በኢየሱስ አምናለሁና ድኛለሁ፥ ለዘላለምም እድናለሁ። ስለዚህ ስምህ የተባረከ ይሁን። ከራስ ወዳድነት፥ ከዓለማዊነትና ከክፋት ዓይነት ሁሉ እንደ ዳንሁ በሕይወቴ በየዕለቱ ላረጋግጥ።

ስለ «ቤተ ሰዎችህ» የሚናገሩት እነዚያ የመጨረሻ ቃላት ግን፥ ጌታ ሆይ፥ አንተ ሙሉ ተስፋ ስትሰጠኝ እኔ ግማሹን ይዤ ልሸሽ አልወድም። ቤተ ሰቤን ሁሉ እንድታድን እለምንሃለሁ። የቅርብና የተወደዱትን አድን። ልጆችን፥ የልጅ ልጆችም ካሉኝ መልሳቸው። ለአገልጋዮቼ፥ በጣራዬ ሥር ለሚኖሩና ለሚሠሩልኝም ሁሉ ቸር ሁን። በጌታ በኢየሱስ ባምን ይህን ተስፋ ለእኔ በግሌ ትሰጠኛለህ፤ እንዳልህ እንድታደርግ እለምንሃለሁ።

የወንድሞቼንና የእኅቶቼን፥ የወላጆቼን፥ የልጆቼን፥ የወዳጆቼን፥ የዘመዶቼንና የአገልጋዮቼን ስም ሁሉ በየዕለቱ በጸሎቴ እዘረዝራለሁ፤ «አንተና ቤተ ሰዎችህ» የሚለውም ቃል እስኪፈጸም ዕረፍት አልሰጥህም።

ሴፕቴምበር 13

የሰማይ ጠል

«ሰማዮቹም ጠልን ያንጠባጥባሉ» ዘዳግም 33:28

በምሥራቅ ጠል ለተፈጥሮ ዓለም እንደ ሆነ፥ በጸጋ ግዛትም የመንፈስ ሥራ እንዲሁ ነው። እንዴት አብዝቶ ያስፈልገኛል! ያለ እግዚአብሔር መንፈስ ደረቅና የጠወለግሁ ነገር ነኝ። እጠወልጋለሁ፥ እደበዝዛለሁ፥ እሞታለሁ። ይህ ጠል እንዴት ጣፋጭ ሆኖ ያድሰኛል! አንድ ጊዜ ሲሰጠኝ ደስተኛ፥ ሕያው፥ ብርቱና ከፍ ያልሁ ይሰማኛል። ከዚህ በላይ ምንም አልፈልግም። መንፈስ ቅዱስ ሕይወትን፥ ሕይወትም የሚፈልገውን ሁሉ ያመጣልኛል። ያለ መንፈስ ጠል ሌላው ሁሉ ለእኔ ከምንም ያነሰ ነው፤ እሰማለሁ፥ አነባለሁ፥ እጸልያለሁ፥ እዘምራለሁ፥ ወደ ቅዱስ ቍርባን ገበታም እሄዳለሁ፤ መንፈስ ቅዱስ እስኪጎበኘኝ ድረስ ግን በዚያ በረከት አላገኝም። እርሱ በጠል ሲያረሰርሰኝ ግን የጸጋ መንገድ ሁሉ ጣፋጭና ጠቃሚ ይሆናል።

ይህ ለእኔ እንዴት ያለ ተስፋ ነው! «ሰማዮቹም ጠልን ያንጠባጥባሉ።» በጸጋ እጎበኛለሁ። ለተፈጥሮ ድርቅነቴ፥ ለዓለም የሚያቃጥል ሙቀት ወይም ለሰይጣናዊ ፈተና ሞቃት ነፋስ አልተውም። ምነው በዚህች ሰዓት የጌታን ለስላሳ፥ ጸጥ ያለና የሚያረሰርስ ጠል ቢሰማኝ! ለምን አይሰማኝም? ሣር በመስክ እንደሚኖር እንድኖር ያደረገኝ፥ ሣሩን እንደሚያደርገው እኔንም ያደርገኛል፤ ከላይ ያድሰኛል። ሣር እኔ እንደምለምን ጠልን ሊለምን አይችልም። በእርግጥ የማይጸልየውን ተክል የሚጎበኝ ጌታ ለሚማጸነው ልጁ ይመልሳል።

ሴፕቴምበር 14

የመለኮታዊ ተቀባይነት ምልክት

«በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና» ያዕቆብ 1:12

አዎን፥ ፈተናውን እየታገሠ ሳለ የተባረከ ነው። በሰማያዊ ኵል እስኪኳል ድረስ ይህን ማየት የሚችል ዓይን የለም። ነገር ግን መታገሥ አለበት፤ በእግዚአብሔር ላይ ማመፅም ሆነ ከቅንነቱ ፈቀቅ ማለት የለበትም። በእሳት ውስጥ አልፎ እንደ ሐሰተኛ ገንዘብ ያልጠፋ የተባረከ ነው።

ፈተናው ሲያልቅ የመለኮታዊ ተቀባይነት ማኅተም ይመጣል፤ «የሕይወትን አክሊል።» ጌታ፥ «በሕይወት ይኑር፤ በሚዛን ተመዝኗል፥ ቀልሎም አልተገኘም» ያለ ያህል ነው። ዋጋው ሕይወት ነው፤ ተራ መኖር ሳይሆን ቅዱስ፥ ደስተኛና እውነተኛ ኑሮ፥ እግዚአብሔር ስለ እኛ ያለው ዓላማ መፈጸም ነው። በእምነትና በፍቅር እጅግ የከበዱትን ፈተናዎች በሰላም ያለፉትን ከፍ ያለ መንፈሳዊ ሕይወትና ደስታ አሁንም ያቀዳጃቸዋል።

ጌታ የሕይወትን አክሊል ለሚወዱት ተስፋ ሰጥቷል። በፈተና ሰዓት የሚጸኑት ጌታን የሚወዱ ብቻ ናቸው፤ ሌሎቹ ወይ ይሰምጣሉ ወይ ያኮርፋሉ፥ ወይም ሾልከው ወደ ዓለም ይመለሳሉ። ልቤ ሆይ፥ ና፤ ጌታህን ትወደዋለህን? በእውነት? በጥልቅ? በሙሉ? እንግዲያስ ያ ፍቅር ይፈተናል፤ ብዙ ውኃ ግን አያጠፋውም፥ ፈሳሾችም አያሰጥሙትም። ጌታ ሆይ፥ ፍቅርህ ፍቅሬን እስከ መጨረሻ ይመግበው።

ሴፕቴምበር 15

እጅግ አስተማማኝ መጠጊያ

«ሰውም ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ፥ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ ይሆናል።» ኢሳይያስ 32:2

ይህ ሰው ማን እንደ ሆነ ሁላችንም እናውቃለን። ከሁለተኛው ሰው፥ ከሰማይ ከመጣው ጌታ፥ ከሕማም ሰው፥ ከሰው ልጅ በቀር ማን ሊሆን ይችላል? ለሕዝቡ እንዴት ያለ መሸሸጊያ ሆኖላቸዋል! የነፋሱን ኃይል ሁሉ ራሱ ይሸከማል፤ በዚህም በእርሱ የሚሸሸጉትን ይጋርዳል። በዚህ መንገድ ከእግዚአብሔር ቍጣ አምልጠናል፤ እንዲሁም ከሰዎች ቍጣ፥ ከዚህ ሕይወት ጭንቀትና ከሞት ፍርሃት እናመልጣለን። ከጌታችን በስተ ኋላ በመሸሸግ በቀላሉና በእርግጥ ከነፋሱ ልንወጣ ስንችል ለምን በነፋስ ውስጥ እንቆማለን? ዛሬ ወደ እርሱ እንሩጥ፥ በሰላምም እንኑር።

ብዙ ጊዜ የተለመደው የመከራ ነፋስ በኃይሉ ተነሥቶ ዐውሎ ይሆናል፥ ሁሉንም ጠራርጎ ይወስዳል። ጽኑና የማይናወጡ የመሰሉ ነገሮች በነፋሱ ይንገዳገዳሉ፤ በሥጋዊ መታመኛዎቻችንም መካከል የሚደርሰው ውድቀት ብዙና ታላቅ ነው። ጌታችን ኢየሱስ፥ ክቡሩ ሰው፥ ፈጽሞ የማይገረሰስ መጠጊያ ነው። በእርሱ ውስጥ ሆነን ዐውሎው ሲያልፍ እናያለን፤ እኛ ራሳችን ግን ደስ በሚያሰኝ ጸጥታ እናርፋለን።

ዛሬ በመሸሸጊያችን ውስጥ ራሳችንን እንሰውር፤ በመጠጊያችንም ጥበቃ ሥር ተቀምጠን እንዘምር። የተባረክህ ኢየሱስ! የተባረክህ ኢየሱስ! እንዴት እንወድሃለን! ልንወድህም ይገባናል፤ በማዕበል ጊዜ መጠጊያችን ነህና።

ሴፕቴምበር 16

ዋጋው የተረጋገጠ ነው

«ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም» ማቴዎስ 10:42

እንግዲህ ይህንንስ ያህል ማድረግ እችላለሁ። ለጌታ አገልጋይ የደግነት ሥራ ማድረግ እችላለሁ። ሁሉንም እንደምወዳቸው፥ እግራቸውንም ማጠብ እንደ ክብር እንደምቈጥረው ጌታ ያውቃል። ስለ ጌታቸው ብዬ ደቀ መዛሙርቱን እወዳለሁ።

ጌታ እንዲህ ያለውን ጥቃቅን ሥራ መጥቀሱ እንዴት ያለ ቸርነት ነው፤ «ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ የሚያጠጣ»! ይህን ምንም ድሀ ብሆን ላደርገው እችላለሁ፤ ምንም ዝቅተኛ ብሆን ላደርገው እችላለሁ፤ ይህን በደስታ አደርገዋለሁ። ይህን እጅግ ትንሽ የሚመስለውን ጌታ ያስተውለዋል፤ ከተከታዮቹ ለታናሹ ሲደረግ ያስተውለዋል። የሚመለከተው ዋጋውን፥ ችሎታውን ወይም ብዛቱን ሳይሆን ዓላማውን እንደ ሆነ ግልጥ ነው፤ ለደቀ መዝሙር ደቀ መዝሙር ስለ ሆነ የምናደርገውን ጌታው ያያል፥ ብድራቱንም ይመልሳል። የሚከፍለን እንደ ሥራችን ብቃት ሳይሆን እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት ነው።

እኔ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ እሰጣለሁ፤ እርሱ የሕይወትን ውኃ ያጠጣኛል። ከታናናሾቹ ለአንዱ እሰጣለሁ፤ እርሱም እንደ አንዱ ያደርገኛል። ኢየሱስ ጸጋው እንዳደርግ ባነሣሣኝ ነገር ለለጋስነቱ ምክንያት ያገኛል፤ «ዋጋው አይጠፋበትም» ይላል።

ሴፕቴምበር 17

እንደ ዘንባባና እንደ ዝግባ

«ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል፤ በሊባኖስ እንዳለ ዝግባ ያድጋል» መዝሙር 92:12

እነዚህ ዛፎች በሰው አይኰተኰቱም አይገረዙም፤ ዘንባባና ዝግባ «የእግዚአብሔር ዛፎች» ናቸው፤ የሚለመልሙትም በእርሱ ጥበቃ ነው፤ የጌታ ቅዱሳንም እንዲሁ ናቸው፤ የእርሱ የራሱ ጥበቃ ናቸው። እነዚህ ዛፎች ሁልጊዜ አረንጓዴ ናቸው፤ በዓመቱ ወቅቶች ሁሉ ውብ ናቸው። አማኞች አንዳንድ ጊዜ ቅዱሳን አንዳንድ ጊዜ ኃጢአተኞች አይደሉም፤ በአየሩ ሁሉ በጌታ ውበት ይቆማሉ። እነዚህ ዛፎች በየትም ስፍራ የሚታዩ ናቸው፤ ዘንባባ ወይም ዝግባ ያለበትን ምድር የሚመለከት ሁሉ ዓይኑ በእነዚህ ንጉሣዊ ዕፅዋት ላይ ማረፉ አይቀርም። የኢየሱስ ተከታዮች በሁሉ ዘንድ የሚታዩ ናቸው፤ በተራራ ላይ እንዳለች ከተማ ሊሰወሩ አይችሉም።

የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ዘንባባ ይለመልማል፤ ዘንባባ አንድም ቅርንጫፍ ሳይኖረው ኃይሉን ሁሉ በአንድ ቀጥ ያለ ዓምድ ወደ ላይ ይገፋል። ክቡር ጕልላት ያለው ዓምድ ነው። ወደ ቀኝም ወደ ግራም አያድግም፤ ኃይሉን ሁሉ ወደ ሰማይ ይልካል፥ ፍሬውንም በተቻለ መጠን ወደ ሰማይ ቀርቦ ያፈራል። ጌታ ሆይ፥ ይህን ምሳሌ በእኔ ፈጽም።

ዝግባ ዐውሎን ሁሉ ይቋቋማል፤ በዘላለማዊ በረዶ አጠገብ ያድጋል፤ ጌታ ራሱ ልቡን የሚያሞቅና ቅርንጫፎቹን የሚያጸና ሕይወት ይሞላበታል። ጌታ ሆይ፥ ከእኔም ጋር እንዲሁ ይሁን፤ እለምንሃለሁ። አሜን።

ሴፕቴምበር 18

ፍጹም ደኅንነት

«ስለ ብንያምም እንዲህ አለ፤ የእግዚአብሔር ወዳጅ በእርሱ ዘንድ ተዘልሎ ይኖራል፤ እግዚአብሔርም ቀኑን ሁሉ ይጋርደዋል፤ በትከሻዎቹም መካከል ያድራል» ዘዳግም 33:12

አዎን፥ ወደ እግዚአብሔር ቀርቦ ከመኖር እንደሚገኘው ያለ ደኅንነት የለም። ጌታ ለሚወደው ከዚህ የበለጠ የተረጋገጠና አስተማማኝ ስፍራ አያገኝም። ጌታ ሆይ፥ ሁልጊዜ በጥላህ ሥር፥ ከቈሰለው ጎንህ አጠገብ እንድኖር አድርገኝ። ጌታዬ ሆይ፥ ወደ አንተ ይበልጥ ይበልጥ መቅረብ እወዳለሁ፤ አንድ ጊዜም በተለየ ሁኔታ ወደ አንተ ከቀረብሁ በዚያ ለዘላለም መኖር እወዳለሁ።

ጌታ ለመረጣቸው የሚሰጠው መጋረጃ እንዴት ያለ ነው! የሚጋርደው ያማረ ጣራ ወይም ቦምብ የማይበሳው ምሽግ ወይም የመልአክ ክንፍ እንኳ አይደለም፤ ይሖዋ ራሱ ነው እንጂ። እንዲህ ተጋርደን ሳለ ምንም ሊደርስብን አይችልም። ቀኑ ምንም ያህል ቢረዝም ጌታ ይህን መጋረጃ ቀኑን ሁሉ ይሰጠናል። ጌታ ሆይ፥ ዛሬ በዚህ የፍቅር ጥላ፥ በዚህ የሉዓላዊ ኃይል ድንኳን ሥር እያወቅሁ እንድኖር አድርገኝ።

ሦስተኛው ሐረግ ጌታ በመቅደሱ በብንያም ተራሮች መካከል ያድራል ማለት ነውን? ወይስ የብንያም ሸክም በሚቀመጥበት ጌታ ይሆናል ማለት ነው? ወይስ በዘላለማዊው አምላክ ትከሻ ላይ እንደምንሸከም ያሳያል? በማንኛውም መንገድ ጌታ የቅዱሳኑ ድጋፍና ብርታት ነው። ጌታ ሆይ፥ ርዳታህን ሁልጊዜ እንድደሰትበት አድርገኝ፤ ያን ጊዜ ክንዶቼ ይበቁኛል።

ሴፕቴምበር 19

የመዘመር ምክንያት

«አምላክህ እግዚአብሔር በመካከልህ ያለ ኃያል ነው፤ ያድናል፤ በአንተ ደስ ይለዋል፥ በፍቅሩ ያርፋል፥ በእልልታም በአንተ ደስ ይለዋል» ሶፎንያስ 3:17

ይህ እንዴት ያለ ቃል ነው! ይሖዋ አምላክ በኃይሉ ግርማ ሁሉ በሕዝቡ መካከል! ይህ መገኘቱ ብቻ ሰላምንና ተስፋን ሊሞላን ይበቃል። ወሰን የሌለው የኃይል ሀብት በይሖዋችን ውስጥ ተከማችቷል፤ እርሱም በቤተ ክርስቲያኑ ይኖራል፤ ስለዚህ ሕዝቡ በደስታ እልል ይበሉ።

መገኘቱ ብቻ ሳይሆን የመረጠውን የማዳን ሥራውን ይሠራል። «ያድናል።» ሁልጊዜ ያድናል፤ ኢየሱስ የሚለውን ስሙን የወሰደው ከዚሁ ነው። ለማዳን ኃያል ነውና ማንኛውንም አደጋ አንፍራ።

ይህ ብቻም አይደለም። ለዘላለም ያው ሆኖ ይኖራል፤ ይወዳል፥ በመውደድ ዕረፍትን ያገኛል፥ መውደድንም አያቋርጥም። ፍቅሩ ደስታን ይሰጠዋል። በሚወዳቸውም ዘንድ የመዝሙር ምክንያት ያገኛል። ይህ እጅግ የሚያስደንቅ ነው። እግዚአብሔር ፍጥረትን በሠራ ጊዜ አልዘመረም፤ «እጅግ መልካም ነው» ብቻ አለ እንጂ፤ ወደ ቤዛነት በመጣ ጊዜ ግን ቅድስት ሥላሴ በመዝሙር የሚገለጥ ደስታ ተሰማው። ይህን አስብ፥ ተደነቅም! ይሖዋ ኢየሱስ በመረጣት ሙሽራው ላይ የሰርግ መዝሙር ይዘምራል። እርስዋ ለእርሱ ፍቅሩ፥ ደስታው፥ ዕረፍቱና መዝሙሩ ናት። ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ለእኛ ባለህ ልክ በሌለው ፍቅርህ አንተን እንድንወድ፥ በአንተ ደስ እንዲለን፥ የሕይወታችንንም መዝሙር ለአንተ እንድንዘምር አስተምረን።

ሴፕቴምበር 20

ፍጹም ፈቃደኝነት

«ሕዝብህ በኃይልህ ቀን በፈቃዳቸው ይሆናሉ» መዝሙር 110:3

ይህ እንዲህ ስለ ሆነ የጸጋ አምላክ የተባረከ ይሁን! የተለየ ርስቱ እንዲሆኑ ከጥንት የመረጣቸው ሕዝብ አለው። እነዚህ በተፈጥሮአቸው እንደ ሌሎቹ የአዳም ጠማማ ልጆች ሁሉ እልከኛ ፈቃድ አላቸው፤ የኃይሉ ቀን ሲመጣና ጸጋ ሁሉን የሚችል ኃይሉን ሲገልጥ ግን ንስሐ ለመግባትና በኢየሱስ ለማመን ፈቃደኞች ይሆናሉ። ሳይፈቅድ የሚድን ማንም የለም፤ ፈቃድ ግን በጣፋጭነት እንዲገዛ ይደረጋል። ፈቃድን ፈጽሞ ሳይጥስ የሚገዛው ይህ እንዴት ያለ ድንቅ ኃይል ነው! እግዚአብሔር ቁልፉን አይሰብረውም፤ እርሱ ብቻ ሊይዘው በሚችለው ዋና መክፈቻ ይከፍተዋል እንጂ።

አሁን ጌታ እንደ ፈቀደ ለመሆን፥ ለማድረግ ወይም መከራ ለመቀበል ፈቃደኞች ነን። በማንኛውም ጊዜ ብናምፅ በኃይል ወደ እኛ መምጣት ብቻ ይበቃዋል፤ ወዲያውም በፍጹም ልባችን በትእዛዙ መንገድ እንሮጣለን። ይህ ቀን ለእግዚአብሔር ክብርና ለባልንጀሮቼ መልካም ለሚሆን ለአንድ ክቡር ጥረት የኃይል ቀን ይሁንልኝ! ጌታ ሆይ፥ ፈቃደኛ ነኝ፤ ይህ የኃይልህ ቀን እንደ ሆነ ተስፋ አላደርግምን? ፈጽሞ በአንተ እጅ ነኝ፤ ለቅዱስ ዓላማህ በአንተ ልጠቀም ፈቃደኛ፥ እንዲያውም ጓጕቻለሁ። አቤቱ ጌታ ሆይ፥ «ፈቃድ አለኝና፥ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም» ብዬ እንድጮኽ አትተወኝ፤ ፈቃድን እንደምትሰጠኝ ኃይልንም ስጠኝ እንጂ።

ሴፕቴምበር 21

መከራዎች ይባርኩ

«መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ እናውቃለን» ሮሜ 5:3

ይህ በቅርጹ ባይሆን በባሕርዩ ተስፋ ነው። ትዕግሥት ያስፈልገናል፤ እዚህም እርሱን የምናገኝበትን መንገድ እናያለን። ሰዎች በመዋኘት መዋኘትን እንደሚማሩ፥ እኛም መታገሥን የምንማረው በመታገሥ ብቻ ነው። ያን ጥበብ በደረቅ መሬት ላይ ልትማረው አትችልም፤ ትዕግሥትንም ያለ መከራ ልትማር አትችልም። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሁሉ በጸጥታ የሚቀበለውን ያን ውብ የአእምሮ እርጋታ ለማግኘት ስንል መከራን መቀበል የሚገባ አይደለምን?

ነገር ግን ጥቅሳችን እንደ ተፈጥሮ ያልሆነ፥ ይልቁንም ከተፈጥሮ በላይ የሆነ አንድ ልዩ እውነት ያቀርባል። መከራ በራሱ ቍጣን፥ አለማመንንና ዓመፅን ያደርጋል። በእኛ ውስጥ ትዕግሥትን እንዲያደርግ የሚደረገው በጸጋ ቅዱስ ብልሃት ብቻ ነው። አቧራን ለማስተኛት ብለን ስንዴን አንወቃም፤ የመከራ መውቂያ ግን በእግዚአብሔር አውድማ ላይ ይህን ያደርጋል። ሰውን ዕረፍት ለመስጠት ብለን ወዲያና ወዲህ አናንገላታውም፤ ጌታ ግን ከልጆቹ ጋር እንዲሁ ያደርጋል። በእውነት ይህ የሰው መንገድ አይደለም፤ ይልቁንም ሁሉን ለሚያውቀው አምላካችን ታላቅ ክብር ይሆናል።

መከራዎቼ እንዲባርኩኝ የሚያስችል ጸጋ ምነው ባገኘሁ! የምሕረት ሥራቸውን ለማስቆም ለምን እመኛለሁ? ጌታ ሆይ፥ መከራዬን እንድታስወግድልኝ እለምንሃለሁ፤ ትዕግሥት ማጣቴን እንድታስወግድልኝ ግን አሥር እጥፍ አጥብቄ እማልድሃለሁ። ውድ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ በመስቀልህ የትዕግሥትህን መልክ በልቤ ላይ ቅረጽ።

ሴፕቴምበር 22

መቅዘፊያ መርከብ የሌለባቸው ሰፋፊ ወንዞች

«በዚያ ግን ክቡር እግዚአብሔር ሰፋፊ ወንዞችና ፈሳሾች ያሉበት ስፍራ ይሆንልናል፤ በዚያም መቅዘፊያ ያለው መርከብ አይሄድበትም፥ ታላቅም መርከብ አያልፍበትም» ኢሳይያስ 33:21

ምድራዊ በሆኑ ምርጥ ነገሮች ላይ የግድ የሚከተሉ የሚመስሉ ጉድለቶች ሳይኖሩበት ጌታ ለእኛ ታላቅ መልካም ነገር ይሆንልናል። አንዲት ከተማ ሰፋፊ ወንዞች ቢሰጧት፥ መቅዘፊያ ባላቸው መርከቦችና በሌሎች የጦር መርከቦች ልትጠቃ ትችላለች። ጌታ ግን የቸርነቱን ብዛት በዚህ ምሳሌ ሲገልጥ፥ ምሳሌው ሊያመጣ የሚችለውን ፍርሃት ሆን ብሎ ይዘጋዋል። ፍጹም ፍቅሩ የተባረከ ይሁን!

ጌታ ሆይ፥ እንደ ሰፋፊ ወንዞች ባለጠግነትን ብትልክልኝ፥ መቅዘፊያ ያለው መርከብ በዓለማዊነት ወይም በትዕቢት መልክ እንዲመጣ አትፍቀድ። የተትረፈረፈ ጤናና ደስተኛ መንፈስ ብትሰጠኝ፥ የሥጋ ምቾት «ታላቅ መርከብ» በሚፈሰው ጎርፍ ላይ እየቀዘፈ እንዲመጣ አትፍቀድ። በቅዱስ አገልግሎት እንደ ጀርመኑ ራይን ወንዝ ሰፊ የሆነ ስኬት ቢኖረኝ፥ የራስን ከፍ የማድረግና በራስ የመታመን መርከብ በጥቅሜ ማዕበል ላይ ሲንሳፈፍ ፈጽሞ እንዳላገኘው አድርግ። የፊትህን ብርሃን ከዓመት ወደ ዓመት እስካገኝ ድረስ እጅግ ደስተኛ ብሆን እንኳ፥ ደካሞች ቅዱሳንህን ፈጽሞ እንዳልንቅ፥ ስለ ራሴም ፍጽምና ያለው ከንቱ አሳብ በሙሉ እርግጠኛነቴ ሰፋፊ ወንዞች ላይ እንዲቀዝፍ እንዳልፈቅድ አድርግ። ጌታ ሆይ፥ ባለጠጋ የምታደርገውን፥ ኀዘንንም ኃጢአትንም የማትጨምረውን በረከት ስጠኝ።

ሴፕቴምበር 23

ከአቧራና ከገለባ መዳን

«እነሆ፥ እኔ አዝዛለሁ፥ እህልም በወንፊት እንደሚነፋ የእስራኤልን ቤት በአሕዛብ ሁሉ መካከል እነፋለሁ፤ ነገር ግን ከፍሬው ትንሽ እንኳ በምድር ላይ አይወድቅም!» አሞጽ 9:9

የማበጠሩ ሥራ ዛሬም ይቀጥላል። በሄድንበት ሁሉ አሁንም እየተነፋንና እየተበጠርን ነው። በአገሮች ሁሉ የእግዚአብሔር ሕዝብ «እህል በወንፊት እንደሚነፋ» እየተፈተኑ ነው። አንዳንድ ጊዜ ዲያብሎስ ወንፊቱን ይዞ ለዘላለም ሊያስወግደን አጥብቆ በመሻት በታላቅ ፍጥነት ወደ ላይና ወደ ታች ያንገላታናል። አለማመንም በዕረፍት የለሽ ፍርሃቱ ልባችንንና አእምሮአችንን ለማናወጥ አይዘገይም። ዓለምም በዚሁ ሥራ በፈቃደኝነት እጁን ያበድራል፤ በታላቅ ብርታትም ወደ ቀኝና ወደ ግራ ያናውጠናል። ከሁሉ የሚከፋው ደግሞ እጅግ የካደችው ቤተ ክርስቲያን ገብታ ለማበጠሩ ሥራ ይበልጥ የከረረ ኃይል ትሰጣለች።

መልካም፥ መልካም! ይቀጥል። ገለባው ከስንዴው የሚለየው እንዲህ ነው። ስንዴው ከአቧራና ከገለባ የሚድነው እንዲህ ነው። በጥቅሱም ውስጥ ወደ እኛ የሚመጣው ምሕረት እንዴት ታላቅ ነው፤ «ነገር ግን ከፍሬው ትንሽ እንኳ በምድር ላይ አይወድቅም»! መልካም፥ እውነትና ጸጋ ያለበት ሁሉ ይጠበቃል። ከአማኞች ታናሽ የሆነ አንድ እንኳ አይጠፋም፤ ማንኛውም አማኝ ጥፋት ሊባል የሚገባውን አንዳች አያጣም። በማበጠሩ ውስጥ እንዲህ ተጠብቀን ስለምንኖር በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል እውነተኛ ትርፍ ይሆንልናል።

ሴፕቴምበር 24

ሕይወት ሰጪው ወንዝ

«እንዲህም ይሆናል፤ ወንዙ በሚደርስበት ስፍራ ሁሉ የሚኖርና የሚንቀሳቀስ ሕይወት ያለው ሁሉ በሕይወት ይኖራል» ሕዝቅኤል 47:9

በነቢዩ ራእይ ሕያው ውኃ ወደ ሙት ባሕር ፈሰሰ፤ ወደዚያ ወደ ረጋው ሐይቅ እንኳ ሕይወትን ተሸክሞ ሄደ። ጸጋ በሄደበት ሁሉ መንፈሳዊ ሕይወት ፈጣንና ዘላለማዊ ውጤቱ ነው። ወንዝ በጠመዝማዛ መንገዱ ሁሉ የራሱን ጣፋጭ ፈቃድ እንደሚከተል፥ ጸጋም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሉዓላዊነት ይሄዳል፤ በደረሰበትም ሁሉ ሕይወት ወደ እርሱ እስኪመጣ አይጠብቅም፥ ነገር ግን በራሱ ሕይወት ሰጪ ፍሰት ሕይወትን ይፈጥራል። ምነው በመንገዶቻችን ቢፈስስ፥ ደሀ መንደሮቻችንንም ቢያጥለቀልቅ! ምነው አሁን ወደ ቤቴ ቢገባ፥ ክፍሉ ሁሉ በእርሱ እስኪዋኝ ድረስ ከፍ ከፍ ቢል! ጌታ ሆይ፥ ሕያው ውኃ ወደ ቤተ ሰቤና ወደ ወዳጆቼ ይፍሰስ፤ እኔንም አያልፈኝ። ከእርሱ አስቀድሜ እንደ ጠጣሁ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ነገር ግን በእርሱ ልታጠብ፥ አዎን፥ በእርሱ ልዋኝ እመኛለሁ። አዳኜ ሆይ፥ የበለጠ የተትረፈረፈ ሕይወት ያስፈልገኛል። እለምንሃለሁ፥ የባሕርዬ ክፍል ሁሉ ሕያውና እጅግ ትጉ እስኪሆን ድረስ ወደ እኔ ና። ሕያው አምላክ ሆይ፥ እለምንሃለሁ፥ በራስህ ሕይወት ሙላኝ። እኔ ምስኪን ደረቅ በትር ነኝ፤ ና፥ እንደ አሮን በትር ለክብርህ እንዳቈጠቍጥ፥ እንዳብብና ፍሬ እንዳፈራ አድርገህ ሕያው አድርገኝ። ስለ ጌታዬ ስለ ኢየሱስ ብለህ ሕያው አድርገኝ። አሜን።

ሴፕቴምበር 25

መሥዋዕቱ ተቀባይነት አግኝቷል

«እግዚአብሔር ሊገድለን ቢወድድ ኖሮ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ከእጃችን ባልተቀበለ ነበር፥ ይህንም ሁሉ ባላሳየን ነበር» መሣፍንት 13:23

ይህ በአመክንዮ የተገኘ የተስፋ ዓይነት ነው። ከተረጋገጡ እውነቶች በትክክል የተወሰደ መደምደሚያ ነው። ጌታ ለማኑሄና ለሚስቱ ወንድ ልጅ እንደሚወለድላቸው ገልጦላቸው ሳለ፥ በልቡ ሊያጠፋቸው አስቦ ይሆናል ማለት የማይመስል ነገር ነበር። ሚስቲቱ መልካም አድርጋ አመዛዘነች፤ እኛም የእርስዋን የአመክንዮ መንገድ ብንከተል መልካም እናደርጋለን።

አብ ታላቁን የቀራንዮ መሥዋዕት ተቀብሎአል፤ በእርሱም ደስ እንደ ተሰኘ ተናግሮአል፤ እንግዲህ አሁን እኛን ሊገድለን እንዴት ይወድዳል? ኃጢአተኛው ገና የሚጠፋ ከሆነ ምትክ ለምን አስፈለገ? ተቀባይነት ያገኘው የኢየሱስ መሥዋዕት ፍርሃትን ያስወግዳል።

ጌታ መመረጣችንን፥ ልጅነታችንን፥ ከክርስቶስ ጋር አንድነታችንን፥ ከተወደደው ጋር ጋብቻችንን አሳይቶናል፤ እንግዲህ አሁን እንዴት ሊያጠፋን ይችላል? ተስፋዎቹ ለዘላለም ሕይወት እንድንጠበቅ የግድ በሚያደርጉ በረከቶች ተሞልተዋል። ጌታ እኛን ጥሎ ኪዳኑን ሊፈጽም አይቻለውም። ያለፈው ያረጋግጥልናል፤ የሚመጣውም ደግሞ ያጸናልናል። ኢየሱስን አይተናልና፥ በእርሱም በመንፈስ ቅዱስ ብርሃን አብን አይተናልና አንሞትም፥ በሕይወት እንኖራለን እንጂ። ከዚህ ሕይወት ሰጪ እይታ የተነሣ ለዘላለም በሕይወት መኖር አለብን።

ሴፕቴምበር 26

ከተዋጁት መካከል

«እነሆ፥ ይህ ሕዝብ ብቻውን ይኖራል፥ ከአሕዛብም ጋር አይቈጠርም» ዘኍልቍ 23:9

በአሕዛብ መካከል መኖርንና ከእነርሱ ጋር መቈጠርን ማን ይመኛል? እንዲያውም ክርስቲያን ነኝ የምትለው ቤተ ክርስቲያን እንኳ በድንበሯ ውስጥ ጌታን ፈጽሞ መከተል እጅግ አስቸጋሪ የሚሆንባት ናት። እንዲህ ያለ መደባለቅና መቀላቀል ስላለ አንድ ሰው ብዙ ጊዜ «በሰፊ ምድረ በዳ ውስጥ ያለች ጎጆ» ይናፍቃል።

ጌታ ሕዝቡ ከዓለም ተለይተው የተለየ መንገድ እንዲከተሉ፥ በቍርጥና በግልጥ ከእርሱ እንዲወጡ እንደሚወድ የተረጋገጠ ነው። በመለኮታዊ ውሳኔ፥ በመዋጀትና በመጠራት ተለይተናል፤ የውስጥ ልምዳችንም ከዓለም ሰዎች እጅግ እንድንለይ አድርጎናል፤ ስለዚህ ስፍራችን በከንቱነት ገበያቸው ወይም በጥፋት ከተማቸው ውስጥ አይደለም፤ እውነተኛ መንገደኞች ሁሉ ጌታቸውን ሊከተሉበት በሚገባው በጠባቡ መንገድ ነው እንጂ።

ይህ ከዓለም ቀዝቃዛ ፊትና ፌዝ ጋር እንድንታረቅ ብቻ ሳይሆን፥ የኪዳን ድርሻችን ክፍል እንደ መሆናቸው በደስታ እንድንቀበላቸው እንኳ ያደርገናል። ስሞቻችን በአንድ መጽሐፍ ውስጥ አይደሉም፤ ከአንድ ዘር አይደለንም፤ ወደ አንድ ስፍራ አንሄድም፤ በአንድ መሪም አንታመንም፤ ስለዚህ ከእነርሱ ቍጥር አለመሆናችን መልካም ነው። ብቻ በተዋጁት ቍጥር ውስጥ እንገኝ፤ እስከ መጨረሻው ድረስ እንግዳና ብቸኞች መሆን ይበቃናል።

ሴፕቴምበር 27

በጨለማ ውስጥ ያለው መለኮታዊ ብርሃን

«አንተ መብራቴን ታበራለህና» መዝሙር 18:28

ምናልባት ነፍሴ በጨለማ ተቀምጣ ይሆናል፤ ይህም መንፈሳዊ ዓይነት ቢሆን ማንም ሰብዓዊ ኃይል ብርሃን ሊያመጣልኝ አይችልም። እግዚአብሔር ይባረክ! ጨለማዬን ሊያበራ፥ መብራቴንም ወዲያው ሊያበራ ይችላል። «የሚዳሰስ ጨለማ» ቢከብበኝ እንኳ እርሱ ጭጋጉን ሰብሮ በዙሪያዬ ወዲያው ብሩህ ሊያደርገው ይችላል።

ምሕረቱ ይህ ነው፤ እርሱ መብራቱን ካበራ ማንም ሊያጠፋው አይችልም፤ በመቀጣጠያ እጦትም አይጠፋም፤ በሰዓታት ማለፍም በራሱ ተቃጥሎ አያልቅም። ጌታ በመጀመሪያ ያበራቸው ብርሃናት ዛሬም ያበራሉ። የጌታ መብራቶች መከርከም ያስፈልጋቸው ይሆናል፤ እርሱ ግን አያጠፋቸውም።

እንግዲህ እንደ ናይቲንጌል ወፍ በጨለማ ልዘምር። መጠባበቅ ዜማ ይሰጠኛል፤ ተስፋም ቅኝቱን ያወጣል። ብዙም ሳይቆይ እግዚአብሔር ባበራው መብራት ደስ ይለኛል። አሁን ደክሜአለሁ፤ አዝኛለሁም። ምናልባት የአየሩ ሁኔታ፥ ወይም የሰውነት ድካም፥ ወይም የድንገተኛ መከራ መደነቅ ይሆናል፤ ጨለማውን ያመጣው ምንም ይሁን ምን ብርሃኑን የሚያመጣ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ዓይኖቼ ወደ እርሱ ብቻ ናቸው። ብዙም ሳይቆይ የጌታ መብራቶች በዙሪያዬ ያበራሉ፤ ከዚያም በኋላ በራሱ መልካም ጊዜ መብራትም የፀሐይም ብርሃን በማያስፈልጋቸው ስፍራ እሆናለሁ። ሃሌ ሉያ!

ሴፕቴምበር 28

ሥራው ተፈጽሟል፤ በእርሱ ዕረፍ

«እንግዲያስ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል» ዕብራውያን 4:9

እግዚአብሔር ሰንበትን አዘጋጅቷል፤ አንዳንዶችም ወደ እርሱ መግባት አለባቸው። አስቀድሞ የተሰበከላቸው ባለማመናቸው ምክንያት አልገቡም፤ ስለዚህ ያ ሰንበት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶአል። ዳዊት ስለ እርሱ ዘመረ፤ እስራኤል የእግዚአብሔርን ዕረፍት ስላልተቀበሉ ግን የኀዘን ቃና ማሰማት ነበረበት። ኢያሱ ሊሰጠው አልቻለም፥ ከነዓንም ልታስገኘው አልቻለችም፤ ለአማኞች ቀርቶአል።

እንግዲህ ኑ፥ ወደዚህ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ። የኃጢአትንና የራስን አድካሚ ድካም እንተው። «እጅግ መልካም ነው» ሊባልላቸው በሚችሉ ሥራዎች እንኳ መታመንን ሁሉ እንተው። እንደዚህ ያለ ሥራ አለን? ቢሆንም እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ እኛም ከሥራችን እናርፍ። አሁን በጌታችን በኢየሱስ በተፈጸመው ሥራ መጽናናትን እናግኝ። ሁሉ ፈጽሞ ተሠርቷል፤ ፍትሕ ከዚህ በላይ አይጠይቅም። በክርስቶስ ኢየሱስ ታላቅ ሰላም ድርሻችን ነው።

የመግቦትን ጉዳዮች፥ በነፍስ ውስጥ ያለውን የጸጋ ሥራ፥ በሌሎችም ነፍሳት ውስጥ ያለውን የጌታ ሥራ በተመለከተ፥ እነዚህን ሸክሞች በጌታ ላይ እንጣል፤ በእርሱም እንረፍ። ጌታ የምንሸከመው ቀንበር ሲሰጠን፥ በመሸከማችን ዕረፍት እንድናገኝ ብሎ ነው። በእምነት ወደ እግዚአብሔር ዕረፍት ለመግባት እንተጋለን፤ ራስን በማርካትና በስንፍና ያለውን ዕረፍት ሁሉ እንክዳለን። ኢየሱስ ራሱ ፍጹም ዕረፍት ነው፤ እኛም በእርሱ እስከ አፋፍ ተሞልተናል።

ሴፕቴምበር 29

ክርስቶስ ኢየሱስን ለማክበር

«እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና።» ዮሐንስ 16:14

መንፈስ ቅዱስ ራሱ የክርስቶስን የራሱን ነገሮች ከማሳየት የበለጠ ጌታ ኢየሱስን ሊያከብረው አይችልም። ኢየሱስ ራሱ የራሱ ምርጥ ምስክር ነው። በራሱ ወርቅ ካልሆነ በቀር እርሱን ማስጌጥ አይቻልም።

አጽናኙ ከጌታችን ከኢየሱስ የተቀበለውን ያሳየናል። እርሱ እስኪገልጠው ድረስ አንድንም ነገር በትክክል አናይም። አእምሮአችንን የሚከፍትበት፥ መጻሕፍትንም የሚከፍትበት መንገድ አለው፤ በዚህ በሁለት እጥፍ ሥራም ጌታችንን በፊታችን ያቀርባል። አንድን ነገር በማቅረብ ብዙ ጥበብ አለ፤ ያም ጥበብ በከፍተኛ ደረጃ የእውነት መንፈስ ነው። እርሱ ነገሮቹን ራሳቸውን ያሳየናል። ያን የተቀደሰ ራእይ ያገኙ እንደሚያውቁት ይህ ታላቅ መብት ነው።

የመንፈስን ብርሃን እንፈልግ፤ የማወቅ ጕጕታችንን ለማርካት ወይም የግል መጽናናትን እንኳ ለማግኘት ሳይሆን ይልቁንም ጌታ ኢየሱስን ለማክበር። ስለ እርሱ የሚገባ አሳብ ምነው ቢኖረን! ዝቅተኛ አሳቦች ውድ ጌታችንን ያዋርዳሉ። በልብና በነፍስ ለምስጋናው እንድንጮኽ ስለ ማንነቱ፥ ስለ ሥራውና ስለ ክብሩ እንዲህ ያለ ሕያው ስሜት ምነው ቢኖረን! በመንፈስ ቅዱስ ትምህርት የበለጸገ ልብ ባለበት ከሚነገረው በላይ የከበረ አዳኝ ይኖራል። መንፈስ ቅዱስ ሆይ፥ ሰማያዊ ብርሃን ሆይ፥ ና፤ ጌታችንን ኢየሱስን አሳየን!

ሴፕቴምበር 30

አፋችንን መክፈት ያስፈልገናል

«አፍህን አስፋ፥ እሞላዋለሁም» መዝሙር 81:10

ለጸሎት እንዴት ያለ ማበረታቻ ነው! የሚገባን እጅግ ትንሽ ስለ ሆነ ሰብዓዊ አሳባችን ትንንሽ ነገሮችን እንድንለምን ይመራን ነበር፤ ጌታ ግን ታላላቅ በረከቶችን እንድንጠይቅ ይወድዳል። ጸሎት እንደ አፍ መክፈት ቀላል ነገር መሆን አለበት፤ ተፈጥሮአዊና ያልተገደደ ንግግር መሆን አለበት። ሰው በትጋት ሲሆን አፉን ያሰፋል፤ ጥቅሳችንም በልመናችን ትጉዎች እንድንሆን ያሳስበናል።

ደግሞም በእግዚአብሔር ፊት ድፍረት እንድናገኝና ብዙና ታላላቅ በረከቶችን ከእጁ እንድንለምን መፈቀዱን ያመለክታል። ቍጥሩን በሙሉ አንብብ፥ ክርክሩንም ተመልከት፤ «ከግብፅ ምድር ያወጣሁህ እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ፤ አፍህን አስፋ፥ እሞላዋለሁም።» ጌታ ብዙ ስለ ሰጠን የበለጠ እንድንለምን፥ አዎን፥ የበለጠ እንድንጠብቅ ይጋብዘናል።

ትንንሾቹ ወፎች እናታቸው ልትመግባቸው ስትመጣ በጎጆአቸው ውስጥ ሁለንተናቸው አፍ ብቻ እንደሚመስሉ ተመልከት። ከእኛም ጋር እንዲሁ ይሁን። ጸጋን በበሩ ሁሉ እንቀበል። ሰፍነግ የተኛበትን ውኃ እንደሚመጥ እንጠጣው። እኛ ለመሞላት ብቻ ዝግጁ ብንሆን እግዚአብሔር ሊሞላን ዝግጁ ነው። ፍላጎቶቻችን አፋችንን እንድንከፍት ያድርጉን፤ ድካማችን አፋችንን ከፍተን እንድናለከልክ ያድርገን፤ አዎን፥ ድንጋጤአችን እንደ ሕፃን ልቅሶ አፋችንን እንድንከፍት ያድርገን። የተከፈተው አፍ በጌታ ራሱ ይሞላል። ጌታ ሆይ፥ ዛሬ እንዲሁ ይሁንልን።

ቀዳሚ ቀጣይ