ምዕራፍ 9 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ
ጥያቄ ስለ ማንሣት
በዚህ ዘመን ቀላልና እንደ ሕፃን ያለ እምነት እጅግ ብርቅ ነው፤ የተለመደው ነገር ምንም አለማመንና ሁሉን መጠራጠር ነው። ጥርጣሬዎች እንደ ጥቍር እንጆሪ በዝተዋል፤ እጆችና ከንፈሮችም ሁሉ በእነርሱ ተበክለዋል። ሰዎች ስለ ገዛ መዳናቸው ችግሮችን እየፈለጉ ማውጣታቸው ለእኔ እጅግ እንግዳ ነገር ሆኖ ይታየኛል። ሞት ተፈርዶብኝ ሳለ የምሕረት ፍንጭ ቢደርሰኝ፣ ይቅርታ የማላገኝበትን ምክንያት ለማግኘት አእምሮዬን እንደማላደክም እርግጠኛ ነኝ። ያን ሥራ ለጠላቶቼ ልተወው እችላለሁ፤ እኔ ግን ፈጽሞ ወደ ሌላ አቅጣጫ እመለከት ነበር። በውኃ እየሰጠምሁ ብሆን የሕይወት ማዳኛ ቀለበትን ከእኔ ከመግፋት ይልቅ ገለባን እንኳ ለመያዝ እሞክር ነበር። በገዛ ሕይወት ላይ መከራከር ከሰካራም በቀር ማንም የማይፈጽመው የራስን ሕይወት የማጥፋት ዓይነት ነው። በብቸኛው ተስፋህ ላይ መከራከር በዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ተቀምጦ ራሱን ለመጣል ቅርንጫፉን የሚቈርጥ ሞኝ ሰውን ይመስላል። ከሞኝ በቀር ይህን ማን ያደርጋል? ሆኖም ብዙዎች ለገዛ ጥፋታቸው የቆሙ ልዩ ጠበቆች ይመስላሉ። የሚያስፈራሩ ጥቅሶችን ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ያስሳሉ፤ ከዚያ ሲጨርሱም በገዛ ፊታቸው በሩን ለመዝጋት ወደ አእምሮ ምርምር፣ ወደ ፍልስፍናና ወደ ጥርጣሬ ይመለሳሉ። በእርግጥ ይህ ለአስተዋይ ሰው የማይገባ ከንቱ ሥራ ነው።
ዛሬ ከሃይማኖታዊ ሐሳብ ፈጽመው መራቅ የማይችሉ ብዙዎች በታላላቆቹ የመገለጥ እውነቶች ላይ በመነታረክ የሕሊናን አስቸጋሪ ግፊት ከራሳቸው ማራቅ ይችላሉ። በእግዚአብሔር መጽሐፍ ውስጥ ታላላቅ ምሥጢራት መኖራቸው የግድ ነው፤ ወሰን የሌለው እግዚአብሔር ሐሳቡ ሁሉ ወሰን ባለው ሰው እንዲጨበጥ አድርጎ እንዴት ሊናገር ይችላል? ነገር ግን በእነዚህ ጥልቅ ነገሮች ላይ ክርክር ጀምሮ ግልጥና ነፍስን የሚያድኑ እውነቶችን ወደ ጎን መተው የሞኝነት ጫፍ ነው። ይህ ስለ ምግብ እየተከራከሩ ከማዕዱ ባዶ ሆደው የሄዱትን ሁለት ፈላስፎች ያስታውሰናል፤ በማዕዘን የተቀመጠው ተራው ገበሬ ግን ምንም ጥያቄ ሳያነሣ ቢላውንና ሹካውን በትጋት ተጠቅሞ ደስ ብሎት መንገዱን ሄደ። ወንጌልን እንደ ትንንሽ ልጆች በመቀበላቸው ሺዎች ዛሬ በጌታ ደስተኞች ናቸው፤ ዘወትር ችግሮችን የሚያዩ ወይም የሚፈጥሩ ሌሎች ግን አሁንም ከሚያጽናና የመዳን ተስፋ እንደ ቀድሞው ሩቅ ናቸው። የምርጫ ትምህርት ከወንጌል ነጻ ግብዣዎች ጋር እንዴት እንደሚስማማ እስኪገባቸው ድረስ ወደ ክርስቶስ ላለመምጣት የወሰኑ የሚመስሉ ብዙ ጨዋ ሰዎችን አውቃለሁ። ይህ ደግሞ እግዚአብሔር እንዴት በሕይወት እንደሚያኖረኝና ሆኖም ለመኖር መብላት እንዳለብኝ እስኪብራራልኝ ድረስ አንዲት ቍራሽ እንጀራ ላለመብላት ከመወሰን አይለይም። እውነቱ ግን ከእኛ የሚበዙቱ አሁንም ቢሆን በቂ እናውቃለን፤ የሚጎድለን በአእምሮአችን ውስጥ ያለ ብርሃን ሳይሆን በልባችን ውስጥ ያለ እውነት ነው፤ በችግሮች ላይ የሚያሻግረን እርዳታ ሳይሆን ኃጢአትን እንድንጠላና መታረቅን እንድንፈልግ የሚያደርገን ጸጋ ነው።
እዚህ ላይ የእግዚአብሔርን ቃል ከመነካካት እንድትጠበቅ ማስጠንቀቂያ ልጨምር። ከዚህ የበለጠ ነፍስን የሚያጠፋ ልማድ የለም። ቍጭ ብሎ ፈጣሪህን ማረም ቀዝቃዛና ንቀት የሞላበት ድፍረት ነው፤ ልብንም ከወፍጮው የታችኛው ድንጋይ ይልቅ ያደነድነዋል። በመጽሐፍ ቅዱሱ ላይ የኪስ ቢላ የተጠቀመ አንድ ሰው እናስታውሳለን፤ ብዙም ሳይቆይ የቀድሞ እምነቶቹን ሁሉ ትቶ ነበር። የአክብሮት መንፈስ ጤናማ ነው፤ በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን ቃል የመተቸት ድፍረት ግን በእግዚአብሔር ፊት ሊኖር የሚገባውን ትክክለኛ ስሜት ሁሉ ያጠፋል።
አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በትዕቢትና በትችት መንፈስ ከያዘ በኋላ አዳኝ እንደሚያስፈልገው ቢሰማው፣ ሕሊናው በቅዱሱ ቃል ላይ የፈጸመውን በደል እያሳሰበው እንቅፋት ሆኖ እንዳይጽናና ሊከለክለው እጅግ ቅርብ ነው። በቸልታ የያዛቸውን፣ ወይም የሚታሰቡ እንዳልሆኑ አድርጎ ፈጽሞ ወደ ጎን የገፋቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከእነርሱ መጽናናትን መቅዳት ይከብደዋል። በጭንቀቱ ጊዜ ቅዱሳት ጥቅሶች በመከራው የሚስቁ ይመስሉታል። የችግር ጊዜ በመጣ ጊዜ በድንጋይ የደፈናቸው ጕድጓዶች ለጥሙ ውኃ አይሰጡትም። አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ስትንቅ በጭንቀት ሰዓት ሊረዳህ የሚችለውን ብቸኛ ወዳጅ እንዳትጥል ተጠንቀቅ።
አንድ የጀርመን መስፍን በየማለዳው አገልጋዩ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ምዕራፍ እንዲያነብለት የማዘዝ ልማድ ነበረው። አንድ ነገር ከአስተያየቱ ጋር ሳይስማማ ሲቀር፦ «ሃንስ፣ ያንን ሰርዘው» ብሎ በቍጣ ይጮኽ ነበር። በመጨረሻም ሃንስ ማንበብ ለመጀመር ብዙ ጊዜ ወሰደ። መምህሩ፦ «ሃንስ፣ ለምን አታነብም?» ብሎ እስኪጠራው ድረስ መጽሐፉን ይገላልጥ ነበር። ሃንስም፦ «ጌታዬ፣ የቀረ ነገር የለም ማለት ይቻላል። ሁሉም ተሰርዟል!» ብሎ መለሰ። አንድ ቀን የጌታው ተቃውሞ ወደ አንድ አቅጣጫ፣ በሌላ ቀን ደግሞ ወደ ሌላ አቅጣጫ ይሄድ ነበር፤ ሌላ የጥቅስ ስብስብም ይሰረዝ ነበር፤ በመጨረሻም የሚያስተምረው ወይም የሚያጽናናው ምንም አልቀረም። በነቃፊ ትችት የገዛ ምሕረቶቻችንን አናጥፋ። አላስፈላጊ የሚመስሉንን የተስፋ ቃሎች ገና ልንፈልጋቸው እንችላለን፤ ተጠራጣሪዎች እጅግ የተቃወሟቸው የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎችም ለሕይወታችን ራሱ አስፈላጊ ሆነው ሊገኙ ይችላሉ፤ ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስን የከበረ መዝገብ እንጠብቅ፤ ከእርሱም አንዲትን መስመር እንኳ አሳልፈን ላለመስጠት እንወስን።
ነፍሳችን በአደጋ ላይ ሳለች ከተሰወሩ ጥያቄዎች ጋር ምን ጉዳይ አለን? ከኃጢአት የምናመልጥበት መንገድ በቂ ግልጥ ነው። መንገደኛ ሰው ሰነፍ ቢሆን እንኳ አይስትበትም። እግዚአብሔር ልንረዳው በማንችለው መዳን አላፌዘብንም። እመንና በሕይወት ኑር የሚለው ሕፃን እንኳ ሊረዳውና ሊታዘዘው የሚችል ትእዛዝ ነው።
ከእንግዲህ አትጠራጠር፣ አሁን እመን፤ አትጠይቅ፣ እንዲሁ ተቀበል። ተንኰለኛ ጥርጣሬና ክርክር ሁሉ ከኢየሱስ ጋር በእንጨት ላይ ይቸንከሩ።በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመራ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከመነታረክ ይልቅ ወዲያውኑ ጌታ ኢየሱስን አጥብቆ ይይዛል። ሺዎች ጨዋና አስተዋይ ሰዎች—ደግሞም መልካም ስም ያላቸው ሰዎች—ያላቸውን ሁሉ ለኢየሱስ አደራ ሰጥተው እንደሚታመኑበት ሲያይ፣ እርሱም እንዲሁ ያደርጋል፤ ከተጨማሪ መዘግየትም ይገላገላል። ያን ጊዜ ሊኖሩት የሚገባ ሕይወት ጀምሯል፤ ከፍርሃትም ሊገላገል ይችላል። ከአዳኙ ከኢየሱስ ፍቅር ወደሚበቅለው ወደዚያ ከፍ ያለና የተሻለ የኑሮ መንገድ ወዲያውኑ ሊገሠግሥ ይችላል። አንባቢውስ ለምን ወዲያውኑ እንዲሁ አያደርግም? ምነው ባደረገ!
በኒውአርክ፣ ኒው ጀርሲ፣ የሚኖር አንድ ሥጋ ሻጭ በጀርመን ካለው የቀድሞ አገሩ ደብዳቤ ደረሰው፤ ደብዳቤውም አንድ ዘመዱ በመሞቱ ብዙ ገንዘብ እንደ ወረሰ የሚያስታውቅ ነበር። በዚያን ጊዜ አሳማ እየቈራረጠ ነበር። ደብዳቤውን ካነበበ በኋላ የቆሸሸውን ሽርጡን በችኮላ ቀድዶ አወለቀ፤ ሥጋው ለቋሊማ እስኪቈረጥ ድረስ አልጠበቀም፤ ነገር ግን ወደ ጀርመን አገሩ ለመሄድ ዝግጅት ሊያደርግ ሱቁን ትቶ ወጣ። ትወቅሰዋለህን? ወይስ ከመክተፊያውና ከሜንጫው ጋር በኒውአርክ እንዲቀር ትፈልግ ነበር?
እዚህ የእምነትን አሠራር ተመልከት። ሥጋ ሻጩ የተነገረውን አመነ፤ ወዲያውኑም በእርሱ መሠረት አደረገ። ደግሞም አስተዋይ ሰው ነው!
እግዚአብሔር የመዳንን የምሥራች የሚነግሩ መልእክቶቹን ወደ ሰው ልኳል። ሰው የምሥራቹን እውነት እንደ ሆነ ሲያምን የተነገረለትን በረከት ይቀበላል፤ ሊይዘውም ይቸኩላል። በእውነት ካመነ ክርስቶስን ከሚሰጠው ሁሉ ጋር ወዲያውኑ ይቀበላል፤ ከአሁኑ ክፉ መንገዱ ይመለሳል፤ ሙሉው በረከት ወደሚገኝባት ወደ ሰማያዊቱ ከተማም ጉዞ ይጀምራል። በጣም ቶሎ ቅዱስ ሊሆን ወይም የኃጢአትን መንገድ በጣም ቀድሞ ሊተው አይችልም። ሰው ኃጢአት ምን እንደ ሆነ በእውነት ማየት ቢችል ከገዳይ እባብ እንደሚሸሽ ከእርሱ ይሸሽ ነበር፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ከእርሱ በመፈታቱም ደስ ይለው ነበር።
ምዕራፍ 9 ተጠናቋል
ጥያቄ ስለ ማንሣት