በጠባቧ በር አጠገብ
በማመን መንገድ ላይ ያለ ችግር

ምዕራፍ 6 · 5 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ

በማመን መንገድ ላይ ያለ ችግር

ምናልባት አንባቢው ለማመን ችግር ይሰማው ይሆናል። እንግዲያስ ያስብበት። በቅጽበታዊ ድርጊት ልናምን አንችልም። ማመን ብለን የምንገልጸው የአእምሮ ሁኔታ ቀደም ሲል በነበሩ የአእምሮ ሁኔታዎች ላይ ተከትሎ የሚመጣ ውጤት ነው። ወደ እምነት የምንደርሰው ቀስ በቀስ ነው። በመጀመሪያ እይታ የሚመጣ እምነት የሚባል ነገር ሊኖር ይችላል፤ ብዙውን ጊዜ ግን ወደ እምነት የምንደርሰው በደረጃ ነው፤ ፍላጎት ያድርብናል፣ እናስባለን፣ ማስረጃ እንሰማለን፣ እንረዳለን፣ እንዲሁም ወደ ማመን እንመራለን። እንግዲህ ማመን ብፈልግ፣ ነገር ግን በሆነ ምክንያት ወደ እምነት ልደርስ እንዳልቻልሁ ባገኝ፣ ምን ላድርግ? አዲስ በር እንደምታፈጥ ላም ቆሜ ልቅር፣ ወይስ እንደ አስተዋይ ፍጡር ተገቢውን መንገድ ልጠቀም? አንድን ነገር ለማመን ብፈልግ ምን አደርጋለሁ? በጤናማ አስተሳሰብ ሕግጋት መሠረት እንመልሳለን።

የዛንዚባር ሡልጣን መልካም ሰው እንደ ሆነ ቢነገረኝና ጉዳዩ የሚያገባኝ ቢሆን፣ ለማመን ምንም ችግር የሚሰማኝ አይመስለኝም። ነገር ግን በሆነ ምክንያት በነገሩ ብጠራጠርና ቢሆንም ወሬውን ለማመን ብፈልግ፣ እንዴት አደርጋለሁ? ስለ ግርማዊነታቸው በእጄ ሊገኝ የሚችለውን መረጃ ሁሉ አፈላልጌ፣ ጋዜጦችንና ሌሎች ሰነዶችን በማጥናት ወደ እውነቱ ለመድረስ አልሞክርምን? ከዚህም የተሻለ፣ እርሱ በዚህች አገር ቢገኝና ሊያየኝ ቢፈቅድ፣ ከቤተ መንግሥቱ ሰዎችና ከአገሩ ዜጎችም ጋር ብነጋገር፣ እነዚህን የመረጃ ምንጮች በመጠቀም ወደ ውሳኔ ለመድረስ እጅግ እረዳ ነበር። የተመዘነ ማስረጃና የተገኘ እውቀት ወደ እምነት ያደርሳሉ። በኢየሱስ ማመን የእግዚአብሔር ስጦታ እንደ ሆነ እውነት ነው፤ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ የሚሰጠው በአእምሮ ሕግጋት መሠረት ነው፤ ስለዚህም «እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው» ተብለናል። በኢየሱስ ማመን ብትፈልግ ስለ እርሱ ስማ፣ ስለ እርሱ አንብብ፣ ስለ እርሱ አስብ፣ ስለ እርሱ እወቅ፤ እንዲህም ሲሆን በተዘራው ዘር ላይ በሚሠሩት እርጥበትና ሙቀት አማካይነት እንደሚበቅል ስንዴ እምነት በልብህ ውስጥ ሲበቅል ታገኘዋለህ። በአንድ ሐኪም ላይ እምነት እንዲኖረኝ ብፈልግ፣ ስለ ፈወሳቸው ሰዎች ምስክርነት እጠይቃለሁ፤ የሙያ እውቀቱን የሚያረጋግጡትን ዲፕሎማዎች ማየት እፈልጋለሁ፤ ደግሞም ስለ አንዳንድ ውስብስብ ሕመሞች የሚለውን መስማት እወዳለሁ። በአጭሩ፣ አምን ዘንድ ለማወቅ መንገድ እፈልጋለሁ።

ስለ ኢየሱስ በመስማት ብዙ ትጋ። ኢየሱስን በግልጽና ያለ ማቋረጥ በሚያቀርብ አገልግሎት ሥር ነፍሳት በመቶዎች ወደ እምነት ይመጣሉ። ታላቅ ርእሱ የተሰቀለው ክርስቶስ በሆነ ሰባኪ ሥር ሳያምኑ የሚቀሩ ጥቂቶች ናቸው። ከዚህ ሌላ ዓይነት አገልጋይ አትስማ። እንደዚህ ያሉ አሉና። በመድረኩ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ ቃል የተጻፈበት ወረቀት ስላገኘ አንድ አገልጋይ ሰምቻለሁ፦ «ጌታ ሆይ፥ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን»። ኢየሱስን ለማየት ወደ አምልኮ ስፍራ ሂድ፤ ስሙ ሲጠራ እንኳ መስማት ካልቻልህ፣ እርሱ ወደሚታሰብበትና ስለዚህም የመገኘቱ ዕድል ወደሚበዛበት ወደ ሌላ ስፍራ ሂድ።

ስለ ጌታ ኢየሱስ በማንበብ ብዙ ትጋ። የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት እርሱ የሚሰማራባቸው አበቦች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ጌታችንን የምናይበት መስኮት ነው። የመከራውንና የሞቱን ታሪክ በአምልኮ መንፈስና በጥንቃቄ ደጋግመህ አንብብ፤ ብዙም ሳይቆይ ጌታ እምነት በስውር ወደ ነፍስህ እንዲገባ ያደርጋል። የክርስቶስ መስቀል እምነትን የሚሸልም ብቻ ሳይሆን እምነትን የሚወልድም ነው። ብዙ አማኞች እንዲህ ማለት ይችላሉ፦

«ቈስለህ፣ አዝነህ፣ ትንፋሽ አጥተህ በተረገመው እንጨት ላይ ሳይህ፣ ስለ እኔ እንዲህ መከራ እንደ ተቀበልህ ልቤ ወዲያው ሲያምን ይሰማኛል።»

መስማትና ማንበብ ካልበቁ ደግሞ ሆን ብለህ ጉዳዩን በጥልቅ ለመመርመር አእምሮህን አሠራ፤ እስከ መጨረሻውም ድረስ ተከራከርበት። ወይ እመን፣ ወይም የማታምንበትን ምክንያት እወቅ። ጉዳዩን በችሎታህ መጠን እስከ መጨረሻው መርምር፤ ጥልቅ ምርመራ እንድታደርግና ወደ አንዱ ወይም ወደ ሌላው ቅን ውሳኔ እንድትደርስ እግዚአብሔር እንዲረዳህ ጸልይ። ኢየሱስ ማን እንደ ነበረ አስብ፤ የአካሉ ማንነት መታመንን የሚያሰጠው እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ አስብ። ያደረገውን አስብ፤ ይህም ደግሞ ለመታመን መልካም መሠረት መሆን እንዳለበት ወይም እንደሌለበት አስብ። ሲሞት፣ ከሙታን ሲነሣ፣ ሲያርግ፣ ስለ ዓመፀኞችም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ሲኖር አስበው፤ ይህም አንተ እንድትደገፍበት የሚያበቃው እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ እይ። ከዚያም ወደ እርሱ ጩኽ፤ ይሰማህ እንደ ሆነም እይ። ኡሸር ራዘርፎርድ እንደሚባለው በእርግጥ ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ ሊያውቅ በፈለገ ጊዜ፣ እንደ ለማኝ ሆኖ ወደ ቤቱ ሄደ፤ ማደሪያም አገኘ፤ በሌሊትም ያ የእግዚአብሔር ሰው ልቡን በጌታ ፊት ሲያፈስስ ሰማ። ኢየሱስን ማወቅ ብትፈልግ ባሕርዩን በማጥናትና ወደ ፍቅሩ በመማጸን በተቻለህ መጠን ወደ እርሱ ቅረብ።

በአንድ ወቅት በጌታ በኢየሱስ እንዳምን ማስረጃ ያስፈልገኝ ይሆናል፤ አሁን ግን በመሞከር እጅግ ስለማውቀው እንድጠራጠረው እጅግ ብዙ ማስረጃ ያስፈልገኛል። አሁን ካለማመን ይልቅ መታመን ይቀልልኛል፤ ይህ አዲሱ ባሕርይ ድል ማድረጉ ነው፤ በመጀመሪያ ግን እንዲህ አልነበረም። የእምነት አዲስነት በመጀመሪያ የድካም ምንጭ ነው፤ ነገር ግን የመታመን ድርጊት በመታመን ድርጊት ላይ እየተደራረበ እምነትን ልማድ ያደርገዋል። ልምድ ለእምነት ብርቱ ማረጋገጫ ያመጣል።

የማምነው እውነት በእኔ ላይ ተአምር ስለ ሠራ በጥርጣሬ አልታወክም። በእርሱ አማካይነት በአንድ ወቅት እንግዳ የነበርሁበትን አዲስ ሕይወት ተቀብያለሁ፤ አሁንም ይዤዋለሁ፤ ይህም እጅግ ብርቱ የሆነ ማረጋገጫ ነው። ለዓመታት የመብራት ማማ ይጠብቁ እንደ ነበሩት ደግ ሰውና ሚስቱ ነኝ። የመብራት ማማውን ሊያይ የመጣ አንድ ጎብኚ በመስኮቱ ሰፊውን ባሕር እየተመለከተ ደጊቱን ሴት እንዲህ ብሎ ጠየቃት፦ «ማዕበል ሲነሣና ታላላቅ ሞገዶች በመብራቱ ላይ ሲገማሸሩ በሌሊት አትፈሪም? የመብራት ማማውና በውስጡ ያለው ሁሉ ተጠራርጎ እንዳይወሰድ አትሰጊም? እኔ ብሆን በታላላቅ ሞገዶች መካከል ባለ ቀጭን ግንብ ውስጥ ራሴን ለማኖር እንደምፈራ እርግጠኛ ነኝ።» ሴቲቱም ይህ አሳብ አሁን ፈጽሞ ወደ አእምሮዋ እንደማይመጣ ተናገረች። በዚያ እጅግ ለረጅም ጊዜ ስለ ኖረች በየብስ ላይ ትኖር በነበረ ጊዜ እንደሚሰማት ሁሉ በብቸኛው ዓለት ላይም ደኅንነት ይሰማት ነበር። ባልዋም ነፋሱ እንደ ዐውሎ ሲነፍስ አይጨነቅም እንደ ሆነ በተጠየቀ ጊዜ፦ «አዎን፤ ማንኛውም መርከብ እንዳይሰበር መብራቶቹ በሚገባ ተስተካክለው እንዲያበሩ እጨነቃለሁ» ብሎ መለሰ። ስለ መብራት ማማው ደኅንነት ወይም በውስጡ ስላለው የራሱ ደኅንነት ያለውን ጭንቀት ግን ከረጅም ጊዜ በፊት አልፎታል። በሙላት ያደገ አማኝም እንዲሁ ነው። በትሕትና፦ «ያመንሁትን አውቃለሁና፥ የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ሊጠብቅ እንዲችል ተረድቼአለሁ» ማለት ይችላል። ከእንግዲህ ወዲህ ማንም በጥርጣሬና በጥያቄ አያስቸግረኝ፤ የመንፈስን እውነትና ኃይል ማስረጃዎች በነፍሴ ተሸክሜአለሁ፤ ብልጣ ብልጥ ክርክሮቻችሁንም አልቀበልም። ወንጌል ለእኔ እውነት ነው፤ እውነት ካልሆነ ልጠፋ ፈቃደኛ ነኝ። የነፍሴን ዘላለማዊ ዕጣ በወንጌል እውነት ላይ አደራ እሰጣለሁ፤ በዚህም ምንም አደጋ እንደሌለ አውቃለሁ። የእኔ ብቸኛ ጉዳይ በዚህ ሌሎችን እጠቅም ዘንድ መብራቶቹ እንዲያበሩ መጠበቅ ነው። ጌታ መብራቴን የሚመግብ በቂ ዘይት ብቻ ይስጠኝ፤ በጨለማውና በአታላዩ የሕይወት ባሕር ላይ ብርሃን እንድፈነጥቅ፤ እኔም ፍጹም እረካለሁ።

እንግዲህ አንተ የምትጨነቅ ፈላጊ ሆይ፣ አገልጋይህና የምትታመንባቸው ሌሎች ብዙዎች በወንጌል ፍጹም ሰላምና ዕረፍት ካገኙ፣ አንተ ለምን አታገኝም? የእግዚአብሔር መንፈስ ትዕግሥቱ አጭር ነውን? ቃሉ በቅንነት ለሚሄዱ መልካም አያደርግምን? አንተስ የሚያድነውን ኃይሉን አትሞክረውምን?

ወንጌል እጅግ እውነተኛ ነው፤ ደራሲው እግዚአብሔር ነውና። እመነው። አዳኙ እጅግ ብርቱ ነው፤ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነውና። ታመነው። ክቡር ደሙ እጅግ ኃያል ነው። ለይቅርታ ወደ እርሱ ተመልከት። ቸሩ ልቡ እጅግ አፍቃሪ ነው። አሁኑኑ ወደ እርሱ ሩጥ።

አንባቢው እምነትን እንዲፈልግ እንዲህ አድርጌ አሳስበዋለሁ፤ ፈቃደኛ ካልሆነ ግን ከዚህ በላይ ምን ማድረግ እችላለሁ? ፈረሱን ወደ ውኃው አምጥቼዋለሁ፤ ነገር ግን እንዲጠጣ ማስገደድ አልችልም። ይህን ግን አስታውሱ—ማስረጃ በሰው መንገድ ላይ ተቀምጦለት በጥንቃቄ ሊመረምረው እምቢ ሲል አለማመኑ ሆን ተብሎ የሚደረግ ነው። እውነትን ለማወቅና ለመቀበል የማይፈልግ በቀኝ እጁ ውሸት ይዞ ቢሞት ራሱን ብቻ ይውቀስ። «ያመነ የተጠመቀም ይድናል» የሚለው እውነት ነው፤ «ያላመነ ግን ይፈረድበታል» የሚለውም እኩል እውነት ነው።


ምዕራፍ 6 ተጠናቋል

በማመን መንገድ ላይ ያለ ችግር

ገጽ 1 / 1 · 5 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ