ምዕራፍ 2 · 5 ደቂቃ ንባብ · 7 ደቂቃ ማዳመጥ
ኢየሱስ ብቻ
ለምትፈልገው ነፍስ የመዳን ብቸኛ ተስፋዋ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንደ ሆነ ብዙ ጊዜም ሆነ ግልጽ አድርገን ብንነግራት አይበዛም። ተስፋዋ ሙሉ በሙሉ፣ በእርሱ ብቻ፣ በእርሱም ብቻውን ነው። ከኃጢአት በደልም ሆነ ከኃጢአት ኃይል ለማዳን ኢየሱስ ሁሉን የሚበቃ ነው። ስሙ ኢየሱስ የተባለው «እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል» ተብሎ ስለ ተነገረ ነው። ደግሞም «ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን እንዳለው» ተጽፎአል። እርሱ «ንስሐን የኃጢአትንም ስርየት ይሰጥ ዘንድ» ከፍ ከፍ ብሎአል። ሙሉ በሙሉ በአንድያ ልጁ ውስጥ የተጠቃለለ የማዳን መንገድ ማዘጋጀት ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው። ጌታ ኢየሱስ ይህን መዳን ለመፈጸም ሰው ሆነ፤ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ፣ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። ሌላ የመዳኛ መንገድ ቢቻል ኖሮ የመራራው ጽዋ ከእርሱ ባለፈ ነበር። በጥቂት ዋጋ ልንድን ብንችል ኖሮ የሰማይ ውድ ተወዳጅ እኛን ለማዳን እንደማይሞት ግልጽ ነው። ወሰን የሌለው ጸጋ ታላቁን መሥዋዕት አዘጋጀ፤ ወሰን የሌለው ፍቅር ስለ እኛ ለሞት ተገዛ። እግዚአብሔር በዚህ ያህል ዋጋ ካዘጋጀውና በቅዱሳት መጻሕፍት እንዲህ ቀላል አድርጎና አጥብቆ ካቀረበው መንገድ ሌላ መንገድ ሊኖር ይችላል ብለን እንዴት እናልማለን? በእርግጥ «መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና» የሚለው ቃል እውነት ነው።
ጌታ ኢየሱስ ሰዎችን በግማሽ ብቻ እንዳዳናቸውና ሥራውን ለመፈጸም የእነርሱ የሆነ አንዳች ሥራ ወይም ስሜት እንደሚያስፈልግ ማሰብ ክፋት ነው። በደሙና በጽድቁ ላይ ሊጨመር የሚችል የእኛ የሆነ ምን ነገር አለ? «ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው።» እነዚህ እጅግ ውድ በሆነው በመለኮታዊ ጽድቁ ልብስ ላይ ሊጣፉ ይችላሉን? ቡትቶና ነጭ ቀጭን በፍታ! የእኛ ዝቃጭና የእርሱ ንጹሕ ወርቅ! እንዲህ ያለውን ነገር ማለም አዳኙን መስደብ ነው። ይህን በሌሎቹ በደሎቻችን ሁሉ ላይ ሳንጨምር እንኳ የበደልነው በቂ ነው።
የምንመካበት አንዳች ጽድቅ ቢኖረን እንኳ፣ የበለስ ቅጠሎቻችን ከወትሮው ይልቅ ሰፋ ያሉ ቢሆኑና እንዲህ ፈጽመው የሚጠወልጉ ባይሆኑ እንኳ፣ እነርሱን አስወግደን ከራሳችን ከማናቸውም ነገር ይልቅ እግዚአብሔርን እጅግ ደስ የሚያሰኘውን ያን ጽድቅ መቀበል ጥበብ ይሆን ነበር። ጌታ ከእኛ መካከል ከሚሻለው ይልቅ በልጁ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ነገር አብልጦ ማየቱ አይቀርም። ከእኛ መካከል የሚሻለው! ቃሉ እንዲህ ታስቦ ባይነገርም የፌዝ ይመስላል። በማናችንም ዘንድ ምን የሚሻል ነገር አለ? «ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም።» እነዚህን መስመሮች የምጽፈው እኔ የራሴ የሆነ የበጎነት ክር እንኳ እንደሌለኝ በፍጹም ነጻነት እመሰክራለሁ። አንድ ቡትቶ ወይም የቡትቶ ቍራጭ እንኳ ማዘጋጀት አልችልም። ፈጽሞ ባዶ ነኝ። ነገር ግን ትዕቢት እንኳ ሊያስበው የሚችል እጅግ ያማረ የመልካም ሥራ ልብስ ቢኖረኝ፣ ጌታ ኢየሱስ ከራሱ ብቃት ሰማያዊ የልብስ ማስቀመጫ በነጻ ከሚሰጠው ከመዳን ልብስ በቀር ሌላ ምንም እንዳልለብስ ያን ልብስ እቀድደው ነበር።
መልካም ነገርን ሁሉ ከእርሱ ብቻ መጠባበቃችን ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እጅግ ያከብረዋል። ይህ እርሱ ሊስተናገድ በሚገባው መንገድ እርሱን ማስተናገድ ነው፤ እርሱ አምላክ ነውና፥ ከእርሱም በቀር ሌላ የለምና፥ ወደ እርሱ ተመልክተን ልንድን ይገባናል።
ይህም እርሱ ሊስተናገድ በሚወድደው መንገድ እርሱን ማስተናገድ ነው፤ ደካሞችንና ሸክማቸው የከበደውን ሁሉ ወደ እርሱ እንዲመጡ ይጠራቸዋልና፤ እርሱም ያሳርፋቸዋል። ፈጽሞ ሊያድን አይችልም ብሎ ማሰብ የእስራኤልን ቅዱስ መወሰንና በኃይሉ ላይ ነቀፋ መጣል ነው፤ አለዚያም የኃጢአተኞችን ወዳጅ አፍቃሪ ልብ ማማትና በፍቅሩ ላይ ጥርጣሬ መጣል ነው። በሁለቱም ሁኔታ፣ እጅግ ስሱ በሆኑት በክብሩ ገጽታዎች፣ ማለትም በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ሁሉ ለማዳን ባለው ችሎታውና ፈቃደኝነቱ ላይ ጨካኝና ግድ የለሽ ኃጢአት በሠራን ነበር።
በእሳት አደጋ ውስጥ ያለችው ሕፃን የእሳት አደጋ ሠራተኛውን አጥብቃ ትይዛለች፤ በእርሱ ብቻም ትታመናለች። ሊሸከማት ስለሚችለው የክንዶቹ ብርታት ወይም ሊያድናት ስላለው የልቡ ቅንዓት አንዳች ጥያቄ አታነሣም፤ ዝም ብላ ትጣበቃለች እንጂ። ሙቀቱ አስፈሪ ነው፤ ጢሱ ያሳውራል፤ እርሷ ግን ትጣበቃለች፤ የሚታደጋትም ሰው ፈጥኖ ወደ ደኅና ስፍራ ይሸከማታል። አንተም በዚያው ዓይነት የሕፃን መታመን ከኃጢአት ነበልባል አደጋ ሊያወጣህ በሚችለውና በሚያወጣህ በኢየሱስ ላይ ተጣበቅ።
የጌታ ኢየሱስ ባሕርይ ፍጹም የሆነ መታመንን ሊያሳድርብን ይገባል። አምላክ እንደ መሆኑ ለማዳን ሁሉን ቻይ ነው፤ ሰው እንደ መሆኑ ለመባረክ በሙላት ሁሉ የተሞላ ነው፤ በአንድ ግርማዊ አካል አምላክም ሰውም እንደ መሆኑ፣ ሰውን በፍጥረትነቱ፣ እግዚአብሔርንም በቅድስናው ይገናኛል። መሰላሉ በምድር ላይ ከተደፋው ከያዕቆብ አንሥቶ በሰማይ እስከሚነግሠው እስከ ይሖዋ ድረስ ለመድረስ በቂ ርዝመት አለው። ሌላ መሰላል ማምጣት እርሱ ርቀቱን ማገናኘት እንዳቃተው መገመት ይሆናል፤ ይህም እርሱን እጅግ ማዋረድ ይሆናል። በቃሉ ላይ መጨመር እንኳ በራሳችን ላይ መርገምን መጥራት ከሆነ፣ በእርሱ በራሱ ላይ ለመጨመር መሞከርማ ምን ይሆን? እርሱ ራሱ መንገድ እንደ ሆነ አስታውስ፤ በመለኮታዊው መንገድ ላይ በሆነ መንገድ መጨመር አለብን ብሎ ማሰብ በእርሱ ላይ ለመጨመር እስከ ማሰብ ድረስ መታበይ ነው። እንዲህ ያለው ሐሳብ ይወገድ! ስድብን እንደምትጸየፍ ተጸየፈው፤ በመሠረቱ በፍቅር ጌታ ላይ ከሚነገር ስድብ ሁሉ የከፋ ነውና።
የምናመጣው አንዳች ዋጋ ቢኖረን እንኳ፣ በእጃችን ዋጋ ይዘን ወደ ኢየሱስ መምጣት የማይታገሡት ትዕቢት ይሆናል። እርሱ ከእኛ ምን ያስፈልገዋል? ቢያስፈልገውስ ምን ልናመጣለት እንችላለን? የቤዛነቱን በዋጋ የማይተመኑ በረከቶች ይሸጣልን? በልቡ ደም የፈጸመውን በእንባችንና በስእለታችን፣ ወይም በሥርዓተ አምልኮ ልማዶቻችን፣ በስሜታችንና በሥራችን ይለውጠናልን? ራሱን ለገበያ እስኪያቀርብ ድረስ አልደኸየም፤ ለንጉሣዊ ፍቅሩ እንደሚገባ በነጻ ይሰጣል፤ ዋጋ የሚያቀርብለት ግን ከማን ጋር እንደሚደራደር፣ ነጻውን መንፈሱንም ምን ያህል እንደሚያሳዝን አያውቅም። ባዶ እጃቸውን የሚመጡ ኃጢአተኞች የፈለጉትን ሊያገኙ ይችላሉ። ሊያስፈልጋቸው የሚችለው ሁሉ በኢየሱስ ዘንድ አለ፤ ለሚለምነውም ይሰጠዋል፤ ነገር ግን እርሱ ሁሉ በሁሉ እንደ ሆነ ማመን አለብን፤ እርሱ የፈጸመውን ስለ ማሟላት ወይም ለማይገባን ኃጢአተኞች ለሚሰጠን ነገር ራሳችንን ብቁ ስለ ማድረግ አንዲት ቃል እንኳ ለመተንፈስ መድፈር የለብንም።
በጌታ ኢየሱስ በማመን የኃጢአት ይቅርታንና የዘላለም ሕይወትን ተስፋ ልናደርግ የምንችለው እግዚአብሔር እንዲሁ ስለ ወሰነ ነው። በጌታ ኢየሱስ በእውነት የሚታመኑትን ሁሉ ለማዳን በወንጌል ራሱን በቃል አስሮአል፤ ከተስፋውም ከቶ ወደ ኋላ አይልም። በአንድያ ልጁ እጅግ ደስ ስለሚሰኝ፣ ልጁን ብቸኛ ተስፋቸው አድርገው በሚይዙት ሁሉ ደስ ይሰኛል። ልጁን የያዘውን ታላቁ እግዚአብሔር ራሱ ይዞታል። ያን መዳን አንድ ጊዜ ከታረደው ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ መዳንን ያደርጋል። ለልጁ ክብር ሲል በእርሱ የሚታመነውን ሰው እንዲያፍር አይተወውም። «በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው»፤ ለዘላለም ሕያው የሆነው እግዚአብሔር ወደ ራሱ ወስዶታልና፤ የሕይወቱም ተካፋይ እንዲሆን ሰጥቶታልና። መታመኛህ ኢየሱስ ብቻ ቢሆን፣ አሁንም በሚገለጥበትም ቀን በእርግጥ ትድናለህ፤ በዚህ አትፍራ።
ሰው ሲታመን በእርሱና በእግዚአብሔር መካከል የአንድነት ነጥብ ይኖራል፤ ያ አንድነትም በረከትን ያረጋግጣል። እምነት የሚያድነን በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ እንድንጣበቅ ስለሚያደርገን ነው፤ እርሱም ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ነው፤ በዚህም ከእግዚአብሔር ጋር ያገናኘናል። ከብዙ ዓመታት በፊት ከናያጋራ ፏፏቴ በላይ አንዲት ጀልባ እንደ ተገለበጠች፣ ሁለት ሰዎችም በወንዙ ፍሰት እየተወሰዱ ሳሉ በዳርቻው ላይ የነበሩ ሰዎች ገመድ አንሳፈው ወደ እነርሱ እንዳደረሱ፣ ሁለቱም ገመዱን እንደ ያዙ ተነግሮኛል። ከእነርሱ አንዱ ገመዱን አጥብቆ ያዘ፤ በደኅናም ወደ ዳርቻው ተጎተተ፤ ሌላው ግን አንድ ትልቅ ግንድ ተንሳፎ ሲያልፍ አይቶ ባለማስተዋል ገመዱን ለቀቀና ያን ትልቅ ግንድ ተጠመጠመበት፤ ከሁለቱ የሚበልጠው እርሱ ነበርና፤ ለመያዝም የተሻለ ይመስል ነበር። ወዮ! ግንዱ ከነሰውዬው በቀጥታ ወደ ሰፊው ጥልቅ ገደል ወረደ፤ በእንጨቱና በዳርቻው መካከል ምንም ግንኙነት አልነበረምና። የግንዱ ትልቅነት ለያዘው ሰው ምንም አልጠቀመውም፤ ደኅንነትን ለማስገኘት ከዳርቻው ጋር ግንኙነት ያስፈልገው ነበር። እንዲሁም ሰው በሥራው ወይም በጸሎቱ ወይም በምጽዋቱ ወይም በምሥጢራት ወይም በዚያ ዓይነት በማናቸውም ነገር ሲታመን አይድንም፤ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል በእርሱና በእግዚአብሔር መካከል ምንም መገናኛ የለምና፤ እምነት ግን ቀጭን ገመድ ቢመስልም በዳርቻው በኩል በታላቁ እግዚአብሔር እጅ ነው፤ ወሰን የሌለው ኃይል የሚያገናኘውን ገመድ ይስባል፤ በዚህም ሰውን ከጥፋት ያወጣዋል። እግዚአብሔር በሾመው አዳኝ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ስለሚያደርገን የእምነት ብፅዕና እንዴት ታላቅ ነው! አንባቢ ሆይ፥ በዚህ ጉዳይ ውስጥ ቀላል ማስተዋል የለምን? አስብበት፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለህ እምነት በአንተና በእግዚአብሔር መካከል የአንድነት ማሰሪያ ፈጥኖ ይኑር!
ምዕራፍ 2 ተጠናቋል
ኢየሱስ ብቻ