ምዕራፍ 5 · 4 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ
አባሪ ሐ
ደስ የሚያሰኘውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈትኖ ማወቅ
ሙለር 300 ብቻ ሳይሆን 1000 ወላጅ አልባ ሕፃናትን ለማኖር የወላጅ አልባ ሕፃናቱን ሥራ ስለ ማስፋት በልቡ በተጨነቀ ጊዜ፣ ደስ የሚያሰኘውን የጌታን ፈቃድ እንዴት ፈትኖ እንዳወቀ ማየት እጅግ አስተማሪና ጠቃሚ ነው።
«ዲሴምበር 11 ቀን 1850 — ስለዚህ የጸሎቴ ዋና ሸክም እግዚአብሔር ፈቃዱን ሊያስተምረኝ እንዲወድድ ነው። አእምሮዬም በተለይ ስለዚህ ጉዳይ ፈቃዱን በሚያረካ ሁኔታ እንዴት ማወቅ እንደምችል ሲያሰላስል ቆይቷል። እንደምማር እርግጠኛ ነኝ። ስለዚህ ስለዚህ ነጥብ በመንገዴ ላይ ሊያበራ የሚወድድበትን የጌታን ጊዜ በትዕግሥት ልጠባበቅ እሻለሁ።
«ዲሴምበር 26 ቀን — የቀደመውን አንቀጽ ከጻፍሁ ወዲህ አሥራ አምስት ቀን አለፈ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በየቀኑ ስለዚህ ጉዳይ መጸለዬን ቀጥያለሁ፤ ያውም በእግዚአብሔር እርዳታ በብዙ ትጋት ነው። በእነዚህ ቀናት ውስጥ፣ ነቅቼ ሳለሁ፣ ይህ ጉዳይ ብዙም ይሁን ጥቂት በፊቴ ያልነበረበት አንድ ሰዓት እንኳ አላለፈም ማለት ይቻላል። ነገር ግን ይህ ሁሉ የስሜት መነሣሣት ጥላ እንኳ ሳይኖርበት ነው። ስለ ጉዳዩ ከማንም ጋር አልነጋገርም። እስካሁን ከውዲቱ ባለቤቴ ጋር እንኳ አልተነጋገርሁበትም። ይህን ከማድረግ አሁንም እቈጠባለሁ፤ የውጭ ተጽዕኖም ሆነ የውጭ የስሜት መነሣሣት ፈቃዱን በግልጽ ከማወቅ እንዳይከለክለኝ ስለ ጉዳዩ ከእግዚአብሔር ብቻ ጋር እነጋገራለሁ። ፈቃዱን በግልጽ እንደሚያሳየኝ ሙሉና እጅግ ሰላማዊ እርግጠኝነት አለኝ። ዛሬ ማታ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ በመፈለግ እንደ ገና የተለየና የተቀደሰ የጸሎት ጊዜ ነበረኝ። ነገር ግን በዚህ ጉዳይ እንድታለል እንዳይፈቅድ ጌታን መለመኔንና መማጠኔን ብቀጥልም፣ ውጤቱ ምን እንደሚሆን፣ ማለትም በዚህ ጉዳይ ወደ ፊት እንድገፋ እንደ ሆነ፣ በአእምሮዬ ውስጥ የቀረ ጥርጣሬ የለም ለማለት እችላለሁ።
«ይሁን እንጂ ይህ እስካሁን ከወሰድኋቸው እርምጃዎች ሁሉ እጅግ ታላቅ ክብደት ካላቸው አንዱ ስለ ሆነ፣ በዚህ ጉዳይ ምንም ያህል ብጠነቀቅ፣ ብጸልይና ባሰላስል ከልክ በላይ ሊሆን እንደማይችል እገምታለሁ። በዚህ ነገር አልቸኩልም። የእርሱ ፈቃድ ቢሆን፣ በእግዚአብሔር ጸጋ፣ ወደዚህ ነገር አንዲት እርምጃ እንኳ ከመውሰዴ ወይም ስለ ጉዳዩ ለማንም ከመናገሬ በፊት ለዓመታት ልጠብቅ እችል ነበር፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጌታ እንዳደርግ ቢያዝዘኝ ነገ ሥራውን እጀምር ነበር። ይህ የአእምሮ እርጋታ፣ በጉዳዩ የራሴ ፈቃድ አለመኖሩ፣ በእርሱ የሰማዩን አባቴን ብቻ ደስ ማሰኘትን መመኘቴ፣ በእርሱም የእኔን ሳይሆን የእርሱን ክብር ብቻ መፈለጌ፤ ይህ የልብ ሁኔታ፣ እላለሁ፣ ልቤ በሥጋዊ የስሜት መነሣሣት ሥር እንዳልሆነ፣ እንዲሁም ወደ ፊት እንዲህ እንድቀጥል ብረዳ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሙሉ በሙሉ እንደማውቅ ከሁሉ የላቀ ማረጋገጫ ይሆንልኛል። ነገር ግን ይህን እየጻፍሁ ሳለ፣ በጌታ ይበልጥና ይበልጥ ጥቅም ላይ የመዋልን ክብርና የከበረ ዕድል በእርግጥ እንደምናፍቅ በዚያው ጊዜ ከመጨመር አልቈጠብም። በወጣትነቴ ዓመታት ሰይጣንን ብዙ አገልግያለሁ፤ አሁን ደግሞ በምድራዊ ጕዞዬ በቀሩት ቀናት እግዚአብሔርን በሙሉ ኃይሌ ለማገልገል እሻለሁ። ዕድሜዬ አርባ አምስት ዓመት ከሦስት ወር ነው። በምድር ላይ የምቆይባቸው ቀናት ቍጥር በየቀኑ ይቀንሳል። ስለዚህ በሙሉ ኃይሌ ልሠራ እሻለሁ። ሊረዱ የሚገባቸው እጅግ ብዙ ወላጅ አልባ ሕፃናት አሉ። * * *
«በዚህም ሁኔታ፣ በጸሎት መልስ ብቻ ለ700 ወላጅ አልባ ሕፃናት የሚሆን ቤትና እነርሱን የምመግብበትን ገንዘብ ሊሰጠኝ ራሱን ዝቅ ባደረገ ጊዜ፣ እግዚአብሔር አሁንም ጸሎትን የሚሰማና የሚመልስ እንደ ሆነ፣ ቀድሞም እንደ ነበረና ለዘላለምም እንደሚሆን ሁሉ ዛሬም ሕያው አምላክ እንደ ሆነ ይበልጥ በብዛት እንዲገለጥ እሻለሁ። ይህ የመጨረሻው አሳብ በአእምሮዬ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጥ ነጥብ ነው። በዚህ ጉዳይ ሁሉ ዋናው ነገር ለእኔ የጌታ ክብር ነው፤ ይህም ስለ ሆነ፣ በዚህ ነገር ወደ ፊት ባለመግፋቴ እርሱ ይበልጥ የሚከብር ቢሆን፣ በጸጋው ስለ ሌላ የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤት ያለኝን አሳብ ሁሉ በመተው ፍጹም እረካለሁ። በመንፈስ ቅዱስ በተገኘ እንዲህ ባለ የአእምሮ ሁኔታ ውስጥ ሳለሁ፣ አንተ የሰማዩ አባቴ ሆይ፣ ልጅህ እንዲሳሳት፣ ይልቁንም እንዲታለል በእርግጥ አትተወውም! በእግዚአብሔር እርዳታ፣ እንድሠራ እስኪያዝዘኝ ድረስ ስለዚህ ነገር ቀን በቀን በጸሎት እርሱን መጠባበቄን እቀጥላለሁ።
«ጃንዋሪ 2 ቀን 1851 — የቀደመውን አንቀጽ ከጻፍሁ አንድ ሳምንት ሆነ። በዚህ ሳምንት ውስጥ ስለ ሌላ የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤት የጌታን አመራር እንድፈልግ ቀን በቀን፣ በየቀኑም ከአንድ ጊዜ በላይ፣ አሁንም እርዳታ አግኝቻለሁ። የጸሎቴ ሸክም አሁንም ቢሆን እርሱ በታላቅ ምሕረቱ ከመሳሳት እንዲጠብቀኝ ነበር። ባለፈው ሳምንት መጽሐፍ ቅዱስን በማነብበት ቅደም ተከተል የምሳሌ መጽሐፍ ደረሰ፤ ልቤም ስለዚህ ጉዳይ በሚከተሉት ክፍሎች ታደሰ፦ ‹በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል› (ምሳሌ 3:5-6)። በእግዚአብሔር ጸጋ ጌታን በመንገዴ ሁሉ፣ በተለይም በዚህ ነገር አውቀዋለሁ፤ ስለዚህ በዚህ የአገልግሎቴ ክፍል ላይ እሰማራ እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ጎዳናዬን እንደሚያቀና የሚያጽናና እርግጠኝነት አለኝ። ደግሞም፦ ‹የቅኖች ቅንነት ትጠብቃቸዋለች፤ የሰነፎች ጠማምነት ግን ታጠፋቸዋለች› (ምሳሌ 11:3)። በእግዚአብሔር ጸጋ በዚህ ጉዳይ ቅን ነኝ። ቅን ዓላማዬ ለእግዚአብሔር ክብርን ማምጣት ነው። ስለዚህ በትክክል እንድመራ እጠብቃለሁ። ደግሞም፦ ‹ሥራህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፥ አሳብህም ይጸናልሃል› (ምሳሌ 16:3)። ሥራዬን ለጌታ አደራ እሰጣለሁ፤ ስለዚህም አሳቤ እንደሚጸና እጠብቃለሁ። — ጌታ በወላጅ አልባ ሕፃናቱ ሥራ ከዚህም በላይ ሊጠቀምብኝ ራሱን ዝቅ እንደሚያደርግ ልቤ ይበልጥና ይበልጥ ወደ ረጋ፣ ጸጥ ወዳለና ወደ ጸና እርግጠኝነት እየመጣ ነው። ጌታ ሆይ፣ ባሪያህ እነሆ!»
ሙለር ለሰባት መቶ ወላጅ አልባ ሕፃናት የሚሆን ሌላ የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤት ማቋቋምን የሚቃወሙ ስምንት ምክንያቶችንና የሚደግፉ ስምንት ምክንያቶችን ጻፈ።
እንዲህ ለማድረግ ያቀረበው የመጨረሻው ምክንያት የሚከተለው ነው፦
«ቀደም ሲል ሥራውን ማስፋት በሚያስፈልገኝ ጊዜያት እንደ ነበረው ሁሉ፣ አሁንም ሥራውን የማስፋት ተስፋ በፊቴ ሲሆን በመንፈስ ሰላምና ደስታ አለኝ። ወደ ፊት ለመግፋት ምክንያት በመሆኑ ይህ በተለይ ከብዶ ይታየኛል። ለስምንት ሳምንታት ያህል ጉዳዩን በእርጋታ፣ በጸጥታና በጸሎት ካሰብሁበት በኋላ፣ የሥራውን መስክ ለማስፋት ባለኝ ዓላማ በመንፈስ ሰላምና ደስታ አለኝ። ይህን ሁሉ ልቤን ከመመርመሬ፣ በዚህ ነገር ከመታለልና ከመሳሳት እንድጠበቅ በየቀኑ ከመጸለዬና ወደ እግዚአብሔር ቃል ከመጠጋቴ በኋላ፣ ጌታ በዚህ አገልግሎት ከምንጊዜውም በላይ ሊጠቀምብኝ ራሱን ዝቅ ለማድረግ ባያስብ ኖሮ ይህ ሁኔታ እንዲህ ባልሆነ ነበር ብዬ እገምታለሁ።
«ስለዚህ መልስ በተሰጣቸው ተቃውሞዎችና ሥራውን ለማስፋት በሚደግፉት በእነዚህ ስምንት ምክንያቶች ላይ ተመሥርቼ፣ ድሀውና እጅግ የማይገባው ባሪያው በዚህ ሥራ ከቀድሞው ይበልጥ በስፋት እንዲያገለግለው የቡሩክ እግዚአብሔር ፈቃድ እንደ ሆነ እደመድማለሁ፤ እርሱም ይህን ለማድረግ ፈጽሞ ፈቃደኛ ነው።»
«ሜይ 24 ቀን — የአእምሮዬን ትግል በዲሴምበር 5 ቀን 1850 መጻፍ ከጀመርሁበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ዘጠና ሁለት ተጨማሪ ወላጅ አልባ ሕፃናት እንዲገቡ ማመልከቻ ቀርቦላቸዋል፤ ከዚያ በፊትም ሰባ ስምንት ወላጅ አልባ ሕፃናት ለመግባት እየተጠባበቁ ነበር። ሥራው ይበልጥና ይበልጥ እየታወቀ ሲሄድ ግን ይህ ቍጥር በፍጥነት ይጨምራል።
«ከላይ በተመዘገበው ላይ ተመሥርቼ በዚህ አገልግሎት ወደ ፊት ለመግፋትና ለሕያው እግዚአብሔር ምስጋናና ክብር ሰባት መቶ ወላጅ አልባ ሕፃናትን ለማኖር የሚበቃ ሌላ የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤት ለመሥራት ለመሞከር አስቤአለሁ።»
ምዕራፍ 5 ተጠናቋል
አባሪ ሐ