የጸሎት መልሶች
አዲሶቹ የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤቶች፣ አሽሊ ዳውን

ምዕራፍ 2 · 12 ደቂቃ ንባብ · 16 ደቂቃ ማዳመጥ

አዲሶቹ የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤቶች፣ አሽሊ ዳውን


በኦክቶበር 1845 አንድ ጨዋ ሰው፣ የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤቶቹ በዊልሰን ጎዳና መኖራቸው አንዳንድ የጎዳናውን ነዋሪዎች እንዳስቸገራቸው ቅሬታ አቀረበ። ሙለርም በዚህና በሌሎች ምክንያቶች፣ ብዙ በጸሎት ካሰላሰለ በኋላ፣ በመጨረሻ 300 ልጆችን የሚያስተናግድ የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤት በሌላ ስፍራ ለመሥራት ወሰነ፤ ይህንንም ለማድረግ የሚያስችለውን ገንዘብ ከጌታ መለመን ጀመረ፦

«ጃንዋሪ 31 ቀን [1846] — ስለ አንድ የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤት ግንባታ በየዕለቱ እግዚአብሔርን መጠባበቅ ከጀመርሁ ዛሬ 89 ቀን ሆነኝ። ጌታ አንድ ቁራሽ መሬት የሚሰጠን ጊዜ አሁን የቀረበ ይመስለኛል፤ ይህንንም ዛሬ ማታ፣ በወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤቶች ዘወትር ቅዳሜ ማታ ከምናደርገው የጸሎት ስብሰባ በኋላ፣ ለወንድሞችና ለእኅቶች ነገርኋቸው።

«ፌብሩዋሪ 1 ቀን — አንዲት ድሀ መበለት ዛሬ 10 ሽልንግ ላከች።

«ፌብሩዋሪ 2 ቀን — ዛሬ በአሽሊ ዳውን ተስማሚና ርካሽ መሬት እንዳለ ሰማሁ።

«ፌብሩዋሪ 3 ቀን — መሬቱን አየሁት። እስካሁን ካየኋቸው ሁሉ እጅግ የሚመረጠው እርሱ ነው። — ስሙን ያልገለጸ አንድ ሰው በቤቴ ባለው የወላጅ አልባ ሕፃናት የመዋጮ ሣጥን ውስጥ በወረቀት የተጠቀለለ አንድ ሶቨሪን (የአንድ ፓውንድ የወርቅ ሳንቲም) አስገባ፤ በወረቀቱም ላይ ‹አዲሱ የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤት› ተብሎ ተጽፎ ነበር።

«ፌብሩዋሪ 4 ቀን — በ2ኛው ቀን ስለ ሰማሁት በአሽሊ ዳውን ስላለው መሬት ባለቤቱን ለማግኘት ዛሬ ማታ ወደ ቤቱ ሄድሁ፤ እርሱ ግን ቤት አልነበረም። ይሁን እንጂ በሥራ ቦታው እንደማገኘው ተነግሮኝ ስለ ነበር ወደዚያ ሄድሁ፤ ነገር ግን እዚያም አላገኘሁትም፤ ምክንያቱም እርሱ ልክ ጥቂት ቀደም ብሎ ወጥቶ ነበር። ከአገልጋዮቹ አንዱ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ በእርግጥ ቤት እንደሚገኝ ስለ ነገረኝ፣ ቆየት ብዬ እንደ ገና ወደ መኖሪያ ቤቱ ልሄድ እችል ነበር፤ ነገር ግን እርሱን በሁለቱም ስፍራ አለማግኘቴ የእግዚአብሔር እጅ እንዳለበት ስለ ገመትሁ እንዲህ አላደረግሁም፤ ስለዚህም ነገሩን አለማስገደድ፣ ይልቁንም ‹ትዕግሥትም … ሥራውን ይፈጽም› የሚለውን መከተል የተሻለ እንደ ሆነ ወሰንሁ።

«ፌብሩዋሪ 5 ቀን — ዛሬ ጠዋት የመሬቱን ባለቤት አገኘሁት። እርሱም ዛሬ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ እንደ ነቃና እስከ ንጋቱ አሥራ አንድ ሰዓት ድረስ እንደ ገና መተኛት እንዳልቻለ ነገረኝ። እንዲህ ነቅቶ ተጋድሞ ሳለ፣ በእኔ ጥያቄ የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤት ለመሥራት ስለ ተጠየቀበት ስለዚያ ቁራሽ መሬት ሐሳቡ ሁልጊዜ ተይዞ ነበር፤ እኔ ብጠይቀውም መሬቱን ሊሰጠኝ ብቻ ሳይሆን፣ ቀደም ብሎ ይጠይቅበት በነበረው በአንድ ኤከር 200 ፓውንድ ፋንታ በአንድ ኤከር 120 ፓውንድ ሊሸጥልኝ ቈረጠ። ጌታ እንዴት ቸር ነው! ስምምነቱ ዛሬ ጠዋት ተደረገ፤ እኔም ሰባት ኤከር የሚጠጋ አንድ ሜዳ በአንድ ኤከር 120 ፓውንድ ገዛሁ።

«የመሬቱን ባለቤት ትናንት ማታ በቤቱ ባለማግኘቴ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን እጅ ተመልከት! ጌታ፣ እኔ እርሱን ሳላየው በፊት፣ እንቅልፍ ባጣበት ሌሊት ስለዚህ ጉዳይ በመጀመሪያ ለባሪያው ሊናገረውና ሙሉ በሙሉ እንዲወስን ሊመራው አስቦ ነበር።»


«ስለ ንዝነዛው»

«ኖቬምበር 19 ቀን [1846] — ግንባታውን መጀመር እንድችል የሚያስፈልገውን ገንዘብ እንዲልክልኝ ጌታን ይበልጥ እየደጋገምሁ እንድለምነው አሁን ይበልጥና ይበልጥ እየተመራሁ ነው። ምክንያቱም (1) አንዳንድ የዊልሰን ጎዳና ነዋሪዎች የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤቶች በዚያ ጎዳና በመኖራቸው መቸገራቸው ያለ ምክንያት እንዳልሆነ እንደምቀበል ለተወሰነ ጊዜ በሕትመት በይፋ ሲገለጽ ቆይቷል፤ ስለዚህም ወላጅ አልባ ሕፃናቱን በተቻለ ፍጥነት ከዚያ ለማዛወር እናፍቃለሁ። (2) አዲሱ የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤት ሲሠራ ልጆቹ እንዲኖሩበት በታሰበው ዓይነት ስፍራ መሆናቸው፣ በእግዚአብሔር በረከት፣ በአካልም በሥነ ምግባርም እጅግ እንደሚጠቅማቸው ይበልጥና ይበልጥ እየተረዳሁ ነው። (3) ደግሞም ለመግባት የሚጠባበቁት እጅግ ድሆችና ረዳት የሌላቸው ወላጅ አልባ ሕፃናት ቍጥር እጅግ ብዙ ስለ ሆነ፣ አዳዲስ ማመልከቻዎችም ያለማቋረጥ ስለሚቀርቡ ነው። እንግዲህ በእግዚአብሔር ጸጋ ግንባታው ፈቃዱ ከሆነበት ቀን አንዲት ቀን እንኳ ቀድሞ እንዲጀመር ባልመኝም፣ በራሱም ጊዜ የሚያስፈልገኝን እያንዳንዷን ሽልንግ እንደሚሰጠኝ አጥብቄ ባምንም፣ እርሱ አጥብቆ መለመንን እንደሚወድድ፣ በጸሎት መጽናትንና እርሱን መነዝነዝን ደስ እንደሚለው ደግሞ አውቃለሁ፤ ይህም ከመበለቲቱና ከዓመፀኛው ዳኛ ምሳሌ (ሉቃስ 18:1-8) በግልጽ ይታያል። ስለዚህ ጌታ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲልክ ትናንት ማታ እንደ ገና በተለየ ሁኔታ ራሴን ለጸሎት ሰጠሁ፤ ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች በተጨማሪ ይህን ለማድረግ በተለይ የተመራሁት፣ ካለፈው ወር 29ኛ ቀን ወዲህ የገባው ገንዘብ በንጽጽር ጥቂት ስለ ነበረ ነው። ዛሬ ጠዋት ከንጋቱ አሥራ አንድና አሥራ ሁለት ሰዓት መካከል፣ ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ስለ ሕንፃ ፈንዱ እንደ ገና ጸለይሁ፤ ከዚያም የእግዚአብሔርን ቃል ለማንበብ ረጅም ጊዜ ወሰድሁ። እያነበብሁም ማርቆስ 11:24 ላይ ደረስሁ፦ ‹…የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል።› በዚህ ክፍል ውስጥ ያለው እውነት ምን ያህል አስፈላጊ እንደ ሆነ ብዙ ጊዜ ተሰምቶኛል፣ ስለ እርሱም ተናግሬአለሁ፤ ዛሬ ጠዋት ግን እንደ ገና በተለየ ሁኔታ ተሰማኝ፤ ቃሉንም በአዲሱ የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤት ላይ በማዋል ጌታን እንዲህ አልሁት፦ ‹ጌታ ሆይ፣ ለዚህ ሥራ የሚያስፈልገኝን ሁሉ እንደምትሰጠኝ አምናለሁ። ለጸሎቴ መልስ እንደ ተቀበልሁ ስለማምን ሁሉን እንደማገኝ እርግጠኛ ነኝ።› እንዲህም ስለዚህ ሥራ ልቤ በሰላም ተሞልቶ የምዕራፉን ቀሪ ክፍልና ቀጣዩን ምዕራፍ ማንበብ ቀጠልሁ። ከቤተሰብ ጸሎት በኋላ ስለ ሥራው ብዙ ክፍሎችና ስለ ልዩ ልዩ ፍላጎቶቹ ሁሉ እንደ ልማዴ እንደ ገና የጸሎት ጊዜ ወሰድሁ፤ አብረውኝ ለሚሠሩትም፣ ለመጽሐፍ ቅዱሶችና ለበራሪ ጽሑፎች ስርጭት፣ በአዋቂዎች ትምህርት ቤት፣ በሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ በስድስቱ የዕለት ትምህርት ቤቶችና በአራቱ የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ላሉት ውድ ነፍሳትም በረከትን ለመንሁ። ከእነዚህ ሁሉ ብዙ ጉዳዮች መካከልም ስለ ሕንፃው ገንዘብ እንደ ገና ልመናዬን አቀረብሁ። እንግዲህ ተመልከት፦ ከተንበረከክሁበት ተነሥቼ አምስት ደቂቃ ያህል እንደ ቆየሁ፣ 300 ፓውንድ ቼክ የያዘ አንድ በሪኮማንዴ የተላከ ደብዳቤ ተሰጠኝ፤ ከዚህም 280 ፓውንድ ለሕንፃ ፈንዱ፣ 10 ፓውንድ ለራሴ የግል ወጪ፣ 10 ፓውንድ ደግሞ ለወንድም ክሬክ ነው። ለዚህ ውድ ማበረታቻ የጌታ ቅዱስ ስም ይመስገን፤ በዚህም የሕንፃ ፈንዱ አሁን ከስድስት ሺህ ፓውንድ በላይ ደርሷል።»


የሙለር የመጀመሪያው የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤት

«ጃንዋሪ 25 ቀን [1847] — ግንባታ ሊጀመር የሚችልበት የዓመቱ ወቅት አሁን እየቀረበ ነው። ስለዚህ ጌታ ስለ እኛ ይገለጥ ዘንድ፣ የሚያስፈልገውንም ቀሪ ገንዘብ በፍጥነት ይልክ ዘንድ እየለመንሁት በበለጠ ትጋት ራሴን ለጸሎት ሰጥቻለሁ፤ ደግሞም ጌታ ግንባታውን ለመጀመር የሚያስፈልገውን ሁሉ የሚሰጠኝ ጊዜ እየቀረበ እንደ ሆነ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይበልጥ ተሰምቶኛል። ብዙ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ያቀረብኋቸውን ልዩ ልዩ ምክንያቶች ሁሉ ዛሬ ጠዋትም እንደ ገና በፊቱ አቀረብኋቸው። ስለዚህ ሥራ ልመናዬን በየዕለቱ ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ ከጀመርሁ እነሆ 14 ወር ከ3 ሳምንት ሆነኝ። ዛሬ ጠዋት ከተንበረከክሁበት የተነሣሁት እግዚአብሔር ገንዘቡን ሊልክ እንደሚችል ብቻ ሳይሆን እንደሚልክም፣ ያውም በቅርቡ እንደሚልክ ሙሉ በሙሉ ተማምኜ ነው። በእነዚህ 14 ወር ከ3 ሳምንት ውስጥ የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደማገኝ ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ አድሮብኝ አያውቅም። — እንግዲህ ውድ አማኝ አንባቢ ሆይ፣ ከእኔ ጋር ደስ ይበልህ፣ አመስግንም። እንዲህ ከጸለይሁ ከአንድ ሰዓት ያህል በኋላ ለሕንፃ ፈንዱ የሚሆን ሁለት ሺህ ፓውንድ ተሰጠኝ። በዚህም ለዚህ ሥራ በአጠቃላይ 9,285 ፓውንድ 3 ሽልንግ 9½ ፔንስ ተቀብያለሁ። — ይህን ስጦታ በተቀበልሁ ጊዜ በእግዚአብሔር ያገኘሁትን ደስታ ልገልጸው አልችልም። ሊሰማ የሚችለው በተሞክሮ ሲታወቅ ብቻ ነው። ገንዘቡ ከላይ የተጠቀሰው መጠን ከመድረሱ በፊት 447 ቀን በየዕለቱ እግዚአብሔርን መጠባበቅ ነበረብኝ። ነፍስ በእግዚአብሔር በመታመንና በትዕግሥት በመጠባበቅ የምታገኘው በረከት እንዴት ታላቅ ነው! የእግዚአብሔርን ሥራ በዚህ መንገድ መሥራት፣ ገንዘብን ስለ ማግኘት እንኳ ቢሆን፣ ምን ያህል ውድ እንደ ሆነ ግልጽ አይደለምን?»

ለሕንፃ ፈንዱ የገባው ጠቅላላ ገንዘብ 15,784 ፓውንድ 18 ሽልንግ 10 ፔንስ ነበር።


ቁጥር 2 እና 3 የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤቶች

«ማርች 12 ቀን 1862 — የወላጅ አልባ ሕፃናቱን ሥራ ከ300 ወላጅ አልባ ሕፃናት ወደ 1000፣ ከዚያም ወደ 1150 ስለ ማስፋት ሐሳቤ መያዝ የጀመረው በኖቬምበር 1850 ነበር፤ ይህ ዓላማዬም በይፋ የታወቀው በጁን 1851 ነበር፤ ከሰባት ወር ለሚበልጥ ጊዜ በየዕለቱ ስለ እርሱ እየጸለይሁ በምስጢር ይዤው ቆይቼ ነበር። ከኖቬምበር 1850 መጨረሻ ጀምሮ እስከ ዛሬ፣ ማርች 12 ቀን 1862 ድረስ፣ ይህ የታሰበው መስፋፋት በጸሎት በእግዚአብሔር ፊት ሳይቀርብ — አብዛኛውን ጊዜም በቀን ከአንድ ጊዜ በላይ — ያለፈች አንዲት ቀን እንኳ የለችም። ነገር ግን አዲሱ ቁጥር 3 የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤት ሊከፈት እስኪችል ድረስ የደረሰው አሁን፣ ዛሬ ብቻ ነው። እንግዲህ የተከበርህ አንባቢ ሆይ፣ በመጀመሪያ ይህን ተመልከት፦ ለጸሎታችን — በሺዎችና በአሥር ሺዎች ለሚቆጠሩ ጸሎቶች እንኳ — ሙሉ መልስ ከመሰጠቱ በፊት ምን ያህል ረጅም ጊዜ ሊወስድ ይችላል፤ አዎን፣ እነዚያ ጸሎቶች የእምነት ጸሎቶች፣ የትጋት ጸሎቶችና በጌታ ኢየሱስ ስም የቀረቡ ቢሆኑም፣ እኛም መልሱን የምንፈልገው ለጌታችን ክብር ብቻ ቢሆንም እንኳ፤ እኔ በእግዚአብሔር ጸጋ ያለ አንዳች ጥርጣሬና ማወላወል ሙሉውን መልስ ከአሥራ አንድ ዓመት በላይ ተጠባብቄአለሁና፤ * * * በዚህ ጉዳይም የፈለግሁት የእግዚአብሔርን ክብር ብቻ ነበር።»


ለረዳቶች በቀን ሦስት ጊዜ መጸለይ

«በቁጥር 2 እንደ ሆነው፣ እንዲሁ በአዲሱ ቁጥር 3 የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤትም ለተለያዩት ክፍሎች ለሚያስፈልጉት ረዳቶችና አጋዦች በየዕለቱ ጸልዬ ነበር። ገና አንድ ድንጋይ ሳይጣል ስለዚህ መጸለይ ጀመርሁ፤ ግንባታው እየገፋ ሲሄድም፣ ሥራው ሁሉ ለእርሱ ክብርና ምስጋና የታሰበ ስለ ሆነ፣ እንደ ሌላው ነገር ሁሉ በዚህ ልዩ ጉዳይም ስለ እኛ ተገልጦ ሊረዳን በቸርነቱ እንደሚወድድ ተማምኜ፣ ይህን ጉዳይ በየዕለቱ በእግዚአብሔር ፊት ማቅረቤን ቀጠልሁ።

«በመጨረሻም ቤቱ ሊከፈት የሚችልበት ጊዜ ቀረበ፤ ስለዚህም የተለያዩትን የሥራ መደቦች ለመሙላት ከሁለት ዓመት በላይ ቀደም ብለው በጽሑፍ የቀረቡት ማመልከቻዎች የሚታዩበት ጊዜ ቀረበ። ነገር ግን ለተለያዩት መደቦች 50 ያህል ማመልከቻዎች የቀረቡ ቢሆንም፣ ያመለከቱት ሰዎች ያገቡ ስለ ነበሩ ወይም ሲመረመሩ ብቁ ሆነው ስላልተገኙ፣ አንዳንድ መደቦች ሊሞሉ እንዳልቻሉ አሁን ታወቀ። ይህ ቀላል የእምነት ፈተና አልነበረም፤ ምክንያቱም በአዲሱ ቁጥር 2 የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤት እንዳደረገልኝ፣ በዚህም ጉዳይ እንዲረዳኝ ለዓመታት በየዕለቱ እግዚአብሔርን ለምኜው ነበር፤ ደግሞም እርዳታን ጠብቄ ነበር፣ በሙሉ ልብ እርዳታን ጠብቄ ነበር፤ ሆኖም አሁን እርዳታ የሚያስፈልግ በሚመስልበት ጊዜ እርዳታው ጠፋ። ውድ አንባቢ ሆይ፣ እንግዲህ አሁን ምን መደረግ ነበረበት? እግዚአብሔርን ታማኝ አይደለህም ብሎ መክሰስ ትክክል ይሆን ነበርን? እርሱን አለማመን ትክክል ይሆን ነበርን? መጸለይ ዋጋ የለውም ማለት ትክክል ይሆን ነበርን? ፈጽሞ አይደለም። ይልቁንም ያደረግሁት ይህ ነው፦ ከመስፋፋቱ ሥራ ሁሉ ጋር በተያያዘ ስለ ሰጠኝ እርዳታ ሁሉ እግዚአብሔርን አመሰገንሁት፤ እጅግ ብዙና እጅግ ታላላቅ ችግሮችን እንዳሸንፍ ስላስቻለኝ አመሰገንሁት፤ ለቁጥር 2 ስለ ሰጠኝ ረዳቶች አመሰገንሁት፤ ለቁጥር 3 አስቀድሞ ስለ ሰጠኝ ረዳቶችም ደግሞ አመሰገንሁት፤ እግዚአብሔርንም ከመጠራጠር ይልቅ፣ ይህን የጸሎቱን ሙሉ መልስ መዘግየት የእምነት ፈተና ብቻ አድርጌ ተመለከትሁት፤ ስለዚህም ለዓመታት በየዕለቱ ስናደርገው እንደ ነበረው ስለዚህ ጉዳይ ከውድ ሚስቴ ጋር በቀን አንድ ጊዜ ከመጸለይ ይልቅ፣ ይህን በእግዚአብሔር ፊት ለማቅረብ ከአሁን ጀምሮ በየዕለቱ ሦስት ጊዜ እንድንገናኝ ወሰንሁ። ጉዳዩንም በሥራው ላሉት ረዳቶቼ ሁሉ አቅርቤ ጸሎታቸውን ጠየቅሁ። በዚህ ዓይነት ስለዚህ ፍላጎት በቀን ሦስት ጊዜ እግዚአብሔርን እየጠራሁ ለአራት ወር ያህል ተጨማሪ ጊዜ በጸሎት ቀጠልሁ፤ ውጤቱም ይህ ነው፦ እርዳታው እጅግ ዘግይቶ ሳይመጣ፣ ሥራውም ሳይታወክ፣ የልጆቹም መግባት ሳይስተጓጐል አንዱ ረዳት ከሌላው ቀጥሎ ተሰጥቶአል፤ ገና የሚያስፈልጉት ጥቂቶችም በእውነት በሚያስፈልጉበት ጊዜ እንደሚገኙ ሙሉ በሙሉ ተረድቻለሁ።»


ከጸሎትና ከትዕግሥት በኋላ የተወገዱ ችግሮች

ሙለር ለሕንፃ ፈንዱ አምስት ሺህ ፓውንድ ከተቀበለ በኋላ፣ ለአራተኛውና ለአምስተኛው የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤቶች የሚሆነውን መሬት ከመግዛቱ ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን ሁኔታዎች ይተርካል፦

«ከሜይ 26 ቀን 1864 ጀምሮ የገባውን ሁሉ፣ ይህንንም በመጨረሻ የተጠቀሰውን ስጦታ ጨምሮ፣ አሁን በእጄ ከሃያ ሰባት ሺህ ፓውንድ በላይ ነበረኝ። የእግዚአብሔርን ጊዜ በትዕግሥት ተጠባብቄ ነበር። ለሁለቱ ቤቶች ከሚያስፈልገው ገንዘብ ሙሉውን ግማሽ እስካገኝ ድረስ ምንም ላለማድረግ ወስኜ ነበር። አሁን ግን ከግማሹ በላይ ከሁለት ሺህ ፓውንድ የሚበልጥ ስለ ነበረኝ፣ እንደ ገና ከእግዚአብሔር ምክር ከፈለግሁ በኋላ፣ መሬት ለመግዛት እርምጃ በመውሰዴ እጅግ ደስ ተሰኘሁ።

«ዓይኖቼ ለዓመታት ያረፉት፣ አዲሱ ቁጥር 3 የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤት ከተሠራበት ቦታ የሚለየው የክፍያ መንገዱ ብቻ በሆነ አንድ ውብ መሬት ላይ ነበር። መሬቱ 18 ኤከር ያህል ሲሆን በአንድ ዳርቻው ላይ አንድ ትንሽ ቤትና ተቀጽላ ቤቶች ተሠርተውበታል። ባለፉት ዓመታት እግዚአብሔር ስለ ኢየሱስ ብሎ በዚህ መሬት ላይ ሁለት ተጨማሪ የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤቶችን እንድሠራ እንዲፈቀድልኝ የተገባሁ አድርጎ እንዲቈጥረኝ በመቶ የሚቆጠሩ ጊዜያት ጸልዬ ነበር፤ በመቶ የሚቆጠሩ ጊዜያትም ይህን መሬት በጸሎት ዓይን ተመልክቼዋለሁ፤ አዎን፣ በጸሎቴ ያራስሁት ያህል ነበር። ከዓመታት በፊት ልገዛው እችል ነበር፤ ነገር ግን ይህ ከጌታ መቅደም ይሆን ነበር። ከዓመታት በፊት ዋጋውን ለመክፈል የሚበቃ ገንዘብ በእጄ ነበረኝ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን የራሱን ጊዜ በትዕግሥትና በመገዛት ልጠብቅ፣ እርሱም ጊዜው እንደ ደረሰና እርምጃውን የወሰድሁት እንደ ፈቃዱ መሆኑን በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ እንዲያሳይ ፈለግሁ፤ ሥራው የጌታ ሳይሆን የእኔ ቢሆን ኖሮ፣ በውጫዊ ሁኔታ ምንም ያህል ብፈጽም፣ ምንም በረከት ልጠብቅ አልችልም ነበርና። አሁን ግን የጌታ ሐሳብ በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ ተገለጠ። መሬቱን ለመግዛትና አንድ ቤት ለመሥራት የሚበቃ ገንዘብ በእጄ ነበረኝ፤ ስለዚህ ጌታን አሁንም ምሪት ከጠየቅሁና ንቁ እርምጃ እንድወስድ ፈቃዱ እንደ ሆነ ከተረዳሁ በኋላ ወደ ፊት ገፋሁ። በመጀመሪያ ያደረግሁት የመሬቱን ባለቤት ወክሎ የሚሠራውን ወኪል አግኝቼ መሬቱ ለሽያጭ የቀረበ እንደ ሆነ መጠየቅ ነበር። እርሱም ለሽያጭ እንደ ሆነ፣ ነገር ግን እስከ ማርች 25 ቀን 1867 ድረስ እንደ ተከራየ መለሰልኝ። ዋጋውንም ጽፎ እንደሚጠይቅ ነገረኝ። እዚህ ላይ አንድ ታላቅ ችግር ወዲያውኑ ተደቀነ፤ ይኸውም መሬቱ ለተጨማሪ ሁለት ዓመት ከአራት ወር ተከራይቶ ነበር፤ እኔ ግን በስድስት ወር ገደማ ውስጥ፣ ማለትም የባለቤትነት ማስተላለፊያ ሰነዱ እንደ ተዘጋጀ፣ የአዲሱ ቁጥር 4 የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤት ንድፎች እንደ ተዘጋጁና ከተቋራጮች ጋር ስምምነት እንደ ተደረገ፣ መሬቱን መረከብ መቻሌ ተፈላጊ መስሎ ታየ። ነገር ግን በዚህ ችግር ተስፋ አልቈረጥሁም፤ ምክንያቱም ተከራዩ ጊዜው ከማለቁ በፊት ስለሚለቅ ተገቢ ካሳ ልሰጠው ፈቃደኛ ስለ ነበርሁ፣ በጸሎት አማካይነት ከእርሱ ጋር ደስ የሚያሰኝና አጥጋቢ ስምምነት እንደማደርግ ጠብቄ ነበር። ነገር ግን ይህን ለማየት ጊዜ ሳላገኝ ሌሎች ሁለት ታላላቅ ችግሮች ተደቀኑ፤ አንደኛው፣ ባለቤቱ ለመሬቱ 7,000 ፓውንድ መጠየቁ ነበር፤ ይህም ከዋጋው እጅግ የበለጠ እንደ ሆነ ገመትሁ፤ ሁለተኛውም፣ የብሪስቶል የውሃ ሥራዎች ኩባንያ በዚሁ መሬት ላይ ለውሃው ተጨማሪ ማጠራቀሚያ ለመሥራትና ለዚሁ ዓላማ የፓርላማ ሕግ ለማስወጣት እንዳሰበ መስማቴ ነበር።

«የተከበርህ አንባቢ ሆይ፣ እዚህ ላይ ለጥቂት ጊዜ ቆም በል። ከገንዘብ አቅርቦት አንጻር ጌታ ወደ ፊት ለመሄድ እንደ ተፈቀደልኝ እስኪሰማኝ ድረስ እንዴት እንዳደረሰኝ አይተሃል፤ ደግሞም ወደዚህ ደረጃ የደረስሁት ስለዚህ ዓላማ በሺዎች ጊዜ የመጸለዬ ውጤት እንደ ሆነ፣ ለመግባት የሚጠባበቁ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ልጆችም እንደ ነበሩ ልጨምር እችላለሁ፤ ሆኖም ጌታ ራሱ በ5,000 ፓውንዱ ስጦታ ስለ እኛ እንዲህ በግልጽ ከተገለጠ በኋላ፣ ሁሉን የሚገድል የሚመስል ይህ ምት በጠቅላላው ሥራ ላይ እንዲመጣ ፈቀደ። ነገር ግን ጌታን ካወቅሁበት ጊዜ ጀምሮ በመቶ በሚቆጠሩ ጊዜያት እንዲሁ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እርሱ እንዲነሡ የሚፈቅዳቸው ችግሮች፣ በእንደዚህ ያሉ ሁኔታዎች፣ የሚፈቀዱት እምነታችንና ትዕግሥታችን እንዲለማመዱ ብቻ ነው፤ ተጨማሪ ጸሎት፣ ተጨማሪ ትዕግሥትና እምነትን መለማመድም ችግሮቹን ያስወግዳሉ። እንግዲህ ጌታን ስለማውቀው እነዚህ ችግሮች ለእኔ የማይሻገሩ ችግሮች አልነበሩም፤ ‹እግዚአብሔርም ለተገፉት መጠጊያ ይሆናል፥ በመከራም ጊዜ መጠጊያ ይሆናል። ስምህንም የሚያውቁ በአንተ ይታመናሉ፤ አቤቱ፥ የሚፈልጉህን አልተውሃቸውምና› (መዝሙር 9:9-10) በሚለው ቃል መሠረት በእርሱ ታምኛለሁና። ስለዚህ ስለ መሬቱ ስለ ተነሡት ስለ እነዚህ ሦስት ልዩ ችግሮች ሁሉ ራሴን አጥብቄ ለጸሎት ሰጠሁ። ስለ ጉዳዩ በቀን ብዙ ጊዜ ጸለይሁ፤ የሚከተሉትንም መንገዶች ተጠቀምሁ፦ 1. ልገዛው ባሰብሁት መሬት ላይ ስለታሰበው የውሃ ማጠራቀሚያቸው የብሪስቶል የውሃ ሥራዎች ኩባንያ ዳይሬክተሮችን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አግኝቼ፣ ስለ ዕቅዳቸው በሕትመት ያየሁትን ነገርኋቸው። እነርሱም የሚያስፈልጋቸው ከመሬቱ ትንሽ ክፍል ብቻ እንደ ሆነ፣ ይህም ዓላማዬን የሚያደናቅፍ እንዳልሆነ፣ ቢቻልም ይህች ትንሽ ክፍል እንኳ እንደማትወሰድ በትሕትና ነገሩኝ። 2. ይህ ከተስተካከለ በኋላ፣ ከብዙ ጸሎት በኋላ ተከራዩን አገኘሁት፤ ምክንያቱም ይህ መሬት የሚገዛ ከሆነ፣ ከእርሱ ጋር በተያያዘ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲሆን እንደ ክርስቲያን ፈልጌ ነበር። በመጀመሪያው ግንኙነታችን ዓላማዬን ገለጽሁለት፤ በዚያው ጊዜም ጉዳዩ ለእርሱ በሚያስደስት መንገድ እንዲፈጸም ያለኝን ምኞት ገለጽሁ። እርሱም ጉዳዩን እንደሚያስብበት ተናገረ፤ ለዚህም ጥቂት ቀናት ጠየቀ። ከአንድ ሳምንት በኋላ እንደ ገና አገኘሁት፤ እርሱም መሬቱ ለእንዲህ ያለ ዓላማ የሚፈለግ ስለ ሆነ እንቅፋት እንደማይሆን፣ ነገር ግን በቤቱና በመሬቱ ላይ ብዙ ገንዘብ ስላወጣ ጊዜው ሳያልቅ ለቅቆ በመውጣቱ ካሳ እንደሚጠብቅ በደግነት ነገረኝ። እኔም እንደ እርግጥ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ ካሳ ለመስጠት ፈጽሞ ፈቃደኛ ስለ ነበርሁ፣ ይህን እጅግ ውድ የጸሎት መልስ አድርጌ ቈጠርሁት። 3. አሁን ወደ ሦስተኛው ችግር፣ ወደ መሬቱ ዋጋ ገባሁ። መሬቱ ለወላጅ አልባ ሕፃናቱ ተቋም ምን ያህል እንደሚጠቅም በሚገባ አውቅ ነበር፤ ነገር ግን ለተቋሙ ያለው ዋጋ የገበያ ዋጋው አልነበረም። ስለዚህ ጌታ ባለቤቱን ከጠየቀው እጅግ ያነሰ ገንዘብ እንዲቀበል እንዲያስገድደው በየዕለቱ ራሴን ለጸሎት ሰጠሁ፤ የጠየቀውን ያህል የማያወጣበትንም ምክንያት አስረዳሁት። በመጨረሻም በ7,000 ፓውንድ ፋንታ 5,500 ፓውንድ ለመቀበል ተስማማ፤ እኔም ጥያቄውን ተቀበልሁ፤ ምክንያቱም መሬቱ ደልዳላ በመሆኑ ለሁለቱ ቤቶች ብዙ ገንዘብ እንደምንቆጥብ፣ ደግሞም ከጥቂት ወራት በፊት ብቻ ተሠርቶ የተጠናቀቀው፣ ከሜዳው አጠገብ ከክፍያ መንገዱ በታች የሚያልፈው አዲሱ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ እጅግ እንደሚጠቅመን አውቅ ነበር። ከእነዚህ ሁለት ነጥቦች በተጨማሪ፣ ሥራ በጀመሩት በሦስቱ ቤቶች እንደሚደረገው ከብሪስቶል ጋዝ ልናገኝ እንደምንችል ከግምት ማስገባት ነበረብኝ። በመጨረሻም፣ ከሁሉ የሚበልጠው ነጥብ፣ ሁሉም በአንድ አመራርና ቍጥጥር ሥር በቀላሉ ሊሆኑ እንዲችሉ ይህ መሬት ለሌሎቹ ሦስት ቤቶች ቅርብ መሆኑ ነበር። በእርግጥም ጌታ እንዲህ እጅግ በደግነት ከሰጠን ከዚህ ስፍራ በላይ ቅርብም ሆነ ሩቅ ሌላ ምንም መሬት ይህን ያህል ጥቅም ሊሰጠን አይችልም ነበር። ሁሉ ከተስተካከለ በኋላ፣ መሬቱ ለአዲሶቹ ቁጥር 1፣ ቁጥር 2 እና ቁጥር 3 የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤቶች ባለአደራ ለነበሩት ለእነዚያው ባለአደራዎች እንዲተላለፍ አደረግሁ። — አንባቢው ችግሮች ምንም ያህል ታላላቅ፣ ብዙና ልዩ ልዩ ቢሆኑ ተስፋ እንዳይቈርጥ፣ ይልቁንም ጌታ እንዲረዳው እየታመነ፣ አዎን፣ በራሱ ጊዜና መንገድ በእርግጥ የሚሰጠውን እርዳታ እየጠበቀ ራሱን ለጸሎት እንዲሰጥ ለማበረታታት፣ በእነዚህ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ እንዲህ በዝርዝር ቆይቻለሁ።»


ቁጥር 4 እና 5 የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤቶች

«ማርች 5 ቀን 1874 — ቁጥር 4 እና ቁጥር 5 ሁለቱም ቤቶች አሁን ለዓመታት ሥራ ላይ ቆይተዋል፤ ቁጥር 4 ከኖቬምበር 1868 ጀምሮ፣ ቁጥር 5 ደግሞ ከ1870 መጀመሪያ ጀምሮ፤ ከ1,200 በላይ ወላጅ አልባ ሕፃናትም አስቀድመው ተቀብለዋል፤ ወላጅ አልባ ሕፃናቱ እንደ ሙያ ተለማማጆች ወይም እንደ ሠራተኞች ተልከው ከዚያ ሲወጡም በየወሩ ተጨማሪዎች ይቀበላሉ። ከዚህም በላይ ቤቶቹን ከመሥራት፣ ከማደራጀትና የቤት ዕቃ ከማሟላት ጋር የተያያዙ ወጪዎች ሁሉ ፍላጎቱ በተነሣ ቍጥር ሙሉ በሙሉ ተሸፈኑ፤ ሁሉ ከተከፈለ በኋላም ብዙ ሺህ ፓውንድ ቀሪ ገንዘብ ተረፈ፤ ይህም ቤቶቹን ለመጠገን እየዋለ ነው። የተከበርህ አንባቢ ሆይ፣ እግዚአብሔር ጸሎታችንን እንዴት አትረፍርፎ እንደ መለሰ፣ ፈቃዱን በትዕግሥትና በጸሎት ለማወቅ ከፈለግን በኋላም እንዳልተሳሳትን ምን ያህል ግልጽ እንደ ሆነ ተመልከት። ስለዚህ በሕያው እግዚአብሔር ይበልጥና ይበልጥ እንድትታመን ተበረታታ።»


ምዕራፍ 2 ተጠናቋል

አዲሶቹ የወላጅ አልባ ሕፃናት መኖሪያ ቤቶች፣ አሽሊ ዳውን

ገጽ 1 / 1 · 12 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ