ምዕራፍ 37 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ
ከሴራሊዮን የአፍሪካ ሜቶዲስት ኤጲስ ቆጶሳዊ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን የተላከ መልእክት
ውድ እመቤት፦ እኛ ከዚህ በታች የፈረምን አባላት፣ ከላይ በተጠቀሰችው ቤተ ክርስቲያንና በሚሲዮናችን ጉዳይ በሚያስቡ ክርስቲያን ሕዝብ ሁሉ ስም፣ ይህን መልእክት እጅግ በታላቅ አክብሮት እንልክልሻለን፤ ይህም በጉብኝትሽ ደስ ካለውና አንቺም በሴራሊዮን በቆየሽበት በዚህ አጭር ጊዜ ሳትታክቺ በብርቱ ቅንዓት ባገለገልሽበት፣ እጅግ ካመሰገነ ማኅበር የተሰጠ እርግጠኛ የምስክርነት ቃል ነው።
የምንፈልገውን ያህል ሐሳባችንን ሙሉ በሙሉ መግለጽ አንችልም። ስሜታችንን ስንገልጽ የምንሸነግልሽ እንዳይመስልሽ ተስፋ እናደርጋለን፤ ይህን የምንናገረው በቅንነት ነውና፤ ሽንገላን ከሚመስል ከማንኛውም አነጋገርም በጥንቃቄ እንደምንርቅ እንተማመናለን። ቄስ ጄ. አር. ፍሬድሪክ አንቺ ከመምጣትሽ ጥቂት ቀደም ብሎ፣ በመካከላችን ልታገለግዪ መምጣትን በቸርነት እንደ ተቀበልሽ ባስታወቀን ጊዜ፣ ስለ ቅንዓትሽ፣ ስለ ድካምሽና በብዙ ስፍራዎች ስላደረግሽው ጕዞ እጅግ ብዙ ነገር ነግሮን ነበር። ዓይኖቻችን እስካዩትና ጆሮዎቻችን እስከ ሰሙት ድረስ፣ በእኛ አስተያየት ስለ አንቺ «እኩሌታው እንኳ አልተነገረም» ማለት እንችላለን። በሁሉም ረገድ የተነገረን ወሬ እውነት ነው።
ሁሉም በስብከቶችሽ እጅግ እንደ ረኩ ልንነግርሽ አያስፈልገንም። ወደ አገልግሎቶችሽ ይመጣ የነበረው እጅግ ብዙ ሕዝብ፣ በውጫዊ ስኬት በኩል ቢታይ፣ በሥራሽ በምንም መንገድ እንዳልወደቅሽ ያረጋግጥልሻል። እግዚአብሔር ጸሎትሽን በዚያ መንገድ እንደ መለሰልሽ እናምናለን፤ ክርስቶስ ባዘዘው በታንኳይቱ ወገን መረብሽን ስትጥዪ ነበር፤ ዓሣዎችንም ሰብስበሻል።
ኃጢአታቸውን ለመተው ፈቃደኞች የሆኑት፣ አንቺም ለመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ለተወሰነ ጊዜ ስለ እነርሱ በጸሎት ስትታገዪላቸው የነበሩት ሰዎች ብዛት ደግሞ የድካምሽን ፍሬያማነት ያሳምንሻል። ከእነዚህ ዳርቻዎች ከሄድሽ ብዙ ዘመን በኋላ እንኳ የጉብኝትሽ ውጤት ገና ይሰማል።
«በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ
ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ» ወዘተ፣ ወዘተ የሚለው የኢዩኤል ትንቢት ሲፈጸም ለማየት ዕድል ስለ ተሰጠን ሁሉን ቻዩን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን።
በአቅራቢያ ባሉት ወንዞች አጠገብ ስለሚኖሩት ምስኪን አሕዛብ ስላሳየሽው ትኩረትም እናመሰግንሻለን፤ በዚያም በብዙ ችግሮች መካከል ሆነሽ ስታገለግዪ ነበር። ድካምሽ በከንቱ እንዳልቀረ ስለ መሰከርሽም እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፤ ጌታ ሊምራቸው የወደዳቸውን ምሯቸዋል።
በዘመኑ የተስፋፉትን ኃጢአቶች ማለትም፦ አጉል እምነትን፣ ምንዝርን፣ ስካርን፣ ሐሜትን፣ ትዕቢትን፣ ለወላጆች አለመታዘዝን፣ በሃይማኖት ግብዝነትን፣ በኃጢአት መቀማጠልን፣ ወዘተ፣ ወዘተ ስለ ገሠጽሽም እናመሰግናለን። ለአገልግሎትሽ ስጦታ እንዲሆን ከትርፋቸው ወደ መዝገብ የሚጥሉ ባለጠጎች ስላልሆንን እጅግ እናዝናለን፤ ነገር ግን ከድህነታችን ከእኛና ከቸሩ ሕዝብ የተገኘው ጥቂት ገንዘብ፣ ክርስቶስ የመበለቲቱን ሁለት ሳንቲሞች እንደ ተቀበለ፣ በአንቺ ዘንድ ተቀባይነት እንደሚያገኝ እንተማመናለን።
«ደኅና ሁኚ» ልንልሽ እጅግ ያሳዝነናል፤ ነገር ግን ሕይወት እንዲህ ናት። እዚህ የምንገናኘው ዳግመኛ ለመለያየት ቢሆንም፣ በሰማይ ግን ዳግመኛ ላንለያይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን፤ እንተማመናለንም። እግዚአብሔር ሙሴ ከመሞቱ በፊት ኢያሱን እንዳስነሣ፣ በመንገድ ላይ የተውሻቸውን ነፍሳት ወደ ከነዓን የሚያደርስ ተተኪ እንዲያስነሣልሽ፣ የመንፈስሽም እጥፍ ድርሻ በእርሷ ላይ እንዲያርፍ እንጸልያለን።
ሁሉን ቻዩ እግዚአብሔር ብዙ የደስታ ዘመናትን ይስጥሽ፤ ሰማያዊ እጁ ብዙ ልዩና ያልተለመዱ ጸጋዎችን እንዳበለጸገሽ፣ በእነዚህ በኋለኞቹ ቀናት በደስታና በእውነተኛ ብፅዕና የዓለም አስደናቂ እንድትሆኚ፤ ከመቃብርም ማዶ ነፍስሽ ከክርስቶስ ጋር ወደ ገነት እንድትገባ የዘላለም ደጆች እንዲከፈቱላት፣ ይህ የሚከተሉት ሰዎች ጸሎት ነው፦
በክርስቶስ ወንድሞችሽና እኅቶችሽ።
[በፓስተሩና በቤተ ክርስቲያኒቱና በሰንበት ትምህርት ቤቱ አባላት በሙሉ የተፈረመ ሲሆን፣ ከመቶ ዶላር በላይ የሚሆን የምስክርነት ስጦታም አብሮት ተሰጥቷል።]