ምዕራፍ 38 · 3 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ
የማርታ ፔይን የሕይወት ተሞክሮ
ለወይዘሮ አማንዳ ስሚዝ የተጻፈ ደብዳቤ።
ሞንሮቪያ፣ ጁን 19 ቀን 1883።የምወድሽ እኅቴ ሆይ፦ ባቀረብሽልኝ ጥያቄ መሠረት እነሆ የመንፈሳዊ ሕይወቴን ተሞክሮ ልጽፍልሽ ወሰንሁ። የተለወጥሁት በአሥራ አምስት ዓመቴ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ በጨለማ ውስጥ ነበርሁ፤ ምክንያቱም የመንፈስ ዕለታዊ ምስክር አልነበረኝም። አንድ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የሚያረጋግጥ ዕለታዊ ምስክር ሊኖረው ይገባል ብዬ አምን ነበር። በልቤ ውስጥ የእግዚአብሔር ፍርሃት ተሰውሮ ነበር፤ ነገር ግን የሚዘልቅ ደስታ አልነበረኝም፤ ይህም እጅግ ያሳስበኝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ መለወጤን እጠራጠር ነበር። ታማኝና ጽኑ ለመሆን ደጋግሜ ቍርጥ ውሳኔ አደርግ ነበር፤ ነገር ግን ፈጽሞ ረዳት የሌለኝ መሆኔን ተረዳሁ።
ቍጣዬ ብዙ ያስቸግረኝ ነበር፤ ብዙ ጊዜም ጸሎቴን እንድተው ያደርገኝ ነበር። ከዚያም በጥርጣሬና በ
ፍርሃት እሞላና ዘወትር ወዲያና ወዲህ እዋልል ነበር። የቤተሰቡ ኀላፊነት እየጨመረ ሲሄድ ጸንቼ እቆም ዘንድ መቀደስን ፈለግሁ። ነገር ግን አላገኘሁትም፤ እጅግም ጨለመብኝ። በእግዚአብሔር ፍርሃት ብቻ እኖር ነበር። ከዚያም ከኃጢአት ነጻ ለመውጣት ትዕግሥት አጥቼ እረፍት የሚነሣ ጭንቀት ያዘኝ። ጸጋንና እምነትን እንዲሰጠኝ ስጸልይ የልቤ የተሰወሩ ክፋቶች ተገለጡልኝ። ከዚያም ወደ ክርስቶስ ለመመልከት ቈረጥሁ፤ «ተግተው የሚፈልጉ ያገኛሉ» የሚለውን የተስፋ ቃል መጽናኛዬ አድርጌ በጸጋ አደግሁ። መጽሐፍ ቅዱሴን ዘወትር አነብ ነበር፤ ሸክሜንም በጌታ ላይ ለመጣል እሞክር ነበር፤ በችግሮች ውስጥ በእርሱ መታመንን ተምሬ ነበርና። መንፈስ ሳበኝ፤ እኔም ጌታን ለማወቅ ተከትዬ ገፋሁ።
የአፕሀምን «ውስጣዊ ሕይወት» አንብቤ ነበር። እጅግ ተበረታታሁ፤ በሁሉም ነገር ለመገዛትም ጣርሁ። ከዚያም ከባድ ፈተና ደረሰብኝ፤ ልቤም እጅግ ከበደ። በእኩለ ሌሊት ተነሥቼ ሁሉን ለእግዚአብሔር አስገዛሁ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጸንቼ ተጠበቅሁ፤ የክርስቶስ ተከታይ መሆኔንም ለመመስከር ከቀድሞው ሁሉ ይልቅ ፈቃደኛ ሆንሁ። ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ ወይዘሮ አማንዳ ስሚዝ ወደ ሞንሮቪያ መጥታ ስለ ቅድስና ሰበከች። በዚህ ጉዳይ ላይ ብርሃን ለማግኘት እጓጓ ነበር። የተነገረውን ሁሉ በጥንቃቄ አዳመጥሁ። ከሁለተኛው ስብከቷ በኋላ መቀደስን የሚፈልጉ ሰዎች ወደ ፊት እንዲወጡ ጠራች። እኔም ልቀደስ ፈለግሁ፤ ወደዚያ የተባረከ ተሞክሮ ለማደግ በጸጥታ ልፈልግና ስለ ጉዳዩ ለማንም ምንም ላልናገር ለራሴ ቃል ገባሁ፤ በረከቱ ካልተገኘ ጨለማው ታላቅ እንደሚሆን ተምሬ ነበርና። ከጥቂት ወራት በኋላ ወይዘሮ ስሚዝ ሥራዋን እንደ ገና ጀመረች። ሕመም ስላደከማት እንደ ፈለገችው መሥራት አልቻለችም። በዲሴምበር ወር በየቀኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጀመረች። ለትምህርቷ ሙሉ ትኩረቴን ሰጠሁ፤ ቤቴ ቤቷ ሆኖ ሳለ እንኳ በረከቱን እንደምፈልግ እንድታውቅ አላደረግሁም። በትምህርቷም ወደ እግዚአብሔር የምናቀርበው ልመና ግልጽና የተወሰነ መሆን እንዳለበት አሳወቀችን። እኔ ግን «መቀደስ» የሚለውን ቃል እጠላው ስለ ነበር በዙሪያው እየዞርሁ እጸልይ ነበር። በመጨረሻ የጥሉ የመለያያ ግድግዳ ፈረሰ፤ «ጌታ ሆይ፥ ቀድሰኝ» የሚሉትንም ቃላት ለመናገር ፈቃደኛ ሆንሁ። ሁሉን አሳልፌ ሰጠሁ፤ ለሦስት ቀንም የነፍስ ጸጥታ ተከተለ። ብርሃን እስኪሰጠኝ ድረስ ጸንቼ ለመቆም ቈርጬ ነበር። ያ ጸጥታ የተሰበረው ለሌሊት ከመተኛቴ በፊት በእርጋታ ስፈልግ በዚህ ቃል ነበር፦ «የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።» ይህ ቃል በዚህ ያህል ኀይል ተረጋገጠልኝ፤ ስለዚህም ድምፄን አሰምቼ፦ «አዎን፣ እንዲሁ ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላልና። ከቃሉ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ያልፋሉ» ብዬ ተቀበልሁ። ልቤም እንዲህ ብሎ መለሰ፦ «አዎን፣ ቃሉ
እንዲህ ይላልና፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ‹ተፈጸመ› ባለ ጊዜ ሙሉ መዳን ተጠናቀቀ።» ከዚያም በነፍሴ ሙሉ ትጋት፦ «ጌታ ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ፤ አሁን መንፈስ ከደሙ ጋር ይመስክር፤ ደሙንም በልቤ ላይ ያሳርፈው» አልሁ። በዚያን ጊዜ የመስመጥ የሚመስል ስሜት በውስጤ ሲያልፍ ተሰማኝ። ለመጸለይ በጉልበቴ ተንበረከክሁ፤ ነገር ግን ጸሎቴ ለኢየሱስ ወደሚቀርብ ውዳሴና ምስጋና ተለወጠ። ነፍሴ በትሕትና፣ ዓይኖቼም በእንባ ተሞሉ። እምነቴ በክርስቶስ ጸና፤ ነፍሴ ለአዲስ ሕይወት ሕያው ሆነች፤ «ከእናንተ ጋር እኖራለሁ» ከሚለው የተስፋ ቃል ጋር ኢየሱስ ክርስቶስን ከቀድሞው ፈጽሞ በተለየ ሁኔታ በእምነት ተመለከትሁት። ነፍሴ ከኃጢአት መንጻቷን በግልጥ እንደ መሰከርሁም ወዲያውኑ መላ ሰውነቴ እንደ ገና አዲስ ሆኖ የተለወጠ መሰለኝ። ክብር ለኢየሱስ ይሁን! ድኛለሁ! ከዲሴምበር ወር አሥራ ሁለተኛው ቀን ጀምሮ ምስክሩ በውስጤ አለ፤ ወደ ፊት በገፋሁ መጠንም መንገዱ ይበልጥ እየጠራ ይሄዳል።
በኢየሱስ ክርስቶስ እኅትሽ፣
ማርታ ፔይን።