ነገር ሁሉ ለበጎ
እግዚአብሔርን እንድንወድ የቀረበ ምክር

ምዕራፍ 8 · 19 ደቂቃ ንባብ · 24 ደቂቃ ማዳመጥ

እግዚአብሔርን እንድንወድ የቀረበ ምክር

1. ምክር። የክርስቲያንን ስም የተሸከሙ ሁሉ እግዚአብሔርን የሚወዱ እንዲሆኑ አጥብቄ ላሳስባቸው እወዳለሁ። «እናንተ ቅዱሳኑ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ውደዱት» (መዝሙር 31:23)። እግዚአብሔርን የሚወዱ ጥቂቶች ብቻ ናቸው፤ ብዙዎች የግብዝነት መሳም ይስሙታል፤ የሚወዱት ግን ጥቂቶች ናቸው። ብዙዎች እንደሚያስቡት እግዚአብሔርን መውደድ ቀላል አይደለም። የፍቅር ስሜት በተፈጥሮ ያለ ነው፤ የፍቅር ጸጋ ግን በተፈጥሮ አይገኝም። ሰዎች በተፈጥሮአቸው አምላክን የሚጠሉ ናቸው (ሮሜ 1:30)። ክፉዎች ቢችሉ ከእግዚአብሔር ይሸሹ ነበር፤ ከሥርዓቱ በታች መሆንንም ሆነ እጁ በሚደርስበት መገኘትን አይሹም። እግዚአብሔርን ይፈሩታል እንጂ አይወዱትም። የሰዎችም ሆነ የመላእክት ኃይል ሁሉ ልብን እግዚአብሔርን እንዲወድ ሊያደርገው አይችልም። የጸጋ መንገዶች በራሳቸው ይህን አያደርጉም፤ ፍርዶችም አያደርጉትም፤ ፍቅርን በነፍስ ውስጥ ሊያሳድር የሚችለው ሁሉን የሚችለውና የማይሸነፈው የእግዚአብሔር መንፈስ ኃይል ብቻ ነው። ይህ እንዲህ ያለ ከባድ ሥራ በመሆኑ፣ ለዚህ መልአካዊ የፍቅር ጸጋ ይበልጥ አጥብቀን እንድንጸልይና እንድንተጋ ይጠራናል። ለእርሱ ያለንን ናፍቆት ለማነሣሣትና ለማቀጣጠል እግዚአብሔርን እንድንወድ የሚያነሣሡ ሃያ ምክንያቶችን አቀርባለሁ።

(1). ያለ ፍቅር ሃይማኖታችን ሁሉ ከንቱ ነው። እግዚአብሔር የሚመለከተው መንፈሳዊ ተግባርን ሳይሆን ለመንፈሳዊ ተግባር ያለንን ፍቅር ነው። ዋናው ነገር ምን ያህል እንደምንሠራ ሳይሆን ምን ያህል እንደምንወድ ነው። አገልጋይ ሥራውን በፈቃደኝነትና በፍቅር ካልሠራው ተቀባይነት የለውም። ፍቅር ያልተቀላቀለባቸው መንፈሳዊ ተግባሮች ለእኛ ሸክም እንደ ሆኑ ለእግዚአብሔርም ሸክም ናቸው። ስለዚህ ዳዊት ልጁን ሰሎሞንን እግዚአብሔርን በፈቃደኛ ነፍስ እንዲያገለግለው መከረው (1ኛ ዜና መዋዕል 28:9)። ያለ ፍቅር መንፈሳዊ ተግባርን መፈጸም መሥዋዕት ሳይሆን የቅጣት ድካም ነው።

(2). ፍቅር እጅግ የከበረና እጅግ የላቀ ጸጋ ነው። ከሰማይ የተቀጣጠለ ንጹሕ ነበልባል ነው፤ በእርሱ ፍቅር የሆነውን እግዚአብሔርን እንመስላለን። ማመንና መታዘዝ እግዚአብሔርን እንድንመስል አያደርጉንም፤ በፍቅር ግን እርሱን እየመሰልን እናድጋለን (1ኛ ዮሐንስ 4:16)። ፍቅር በእግዚአብሔር እጅግ ደስ የሚሰኝ፣ ለእርሱም እጅግ ደስ የሚያሰኝ ጸጋ ነው። ከደቀ መዛሙርቱ ፍቅር እጅግ የሞላበት ያ ደቀ መዝሙር በክርስቶስ እቅፍ ተጠግቶ ተቀመጠ። ፍቅር በጸጋዎች ሁሉ ላይ ልምላሜንና ድምቀትን ያለብሳቸዋል፤ ፍቅር በውስጣቸው ካላበራና ካላንጸባረቀ ጸጋዎቹ የጨለሙ ይመስላሉ። እምነት በፍቅር ካልሠራ እውነተኛ አይደለም። የንስሐ ውኃዎች ከፍቅር ምንጭ ካልፈለቁ ንጹሐን አይደሉም። ፍቅር አገልግሎታችንን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መዓዛ ያለውና ተቀባይነት ያለው የሚያደርግ ዕጣን ነው።

(3). እግዚአብሔር የሚጠይቀው ነገር ምክንያታዊ ያልሆነ ነውን? የሚጠይቀው ፍቅራችንን ብቻ ነው። ንብረታችንን ወይም የአብራካችንን ፍሬ ቢጠይቀን እምቢ ልንለው እንችል ነበርን? እርሱ ግን የሚጠይቀው ፍቅራችንን ብቻ ነው፤ ሊቀጥፍ የሚወደው ይህችን አበባ ብቻ ነው። ይህ ከባድ ልመና ነውን? እንደዚህ በቀላሉ የሚከፈል ዕዳ ከቶ ነበረን? ይህን ዕዳ በመክፈላችን በምንም አንደኸይም። ፍቅር ሸክም አይደለም። ሙሽራ ባሏን መውደዷ ድካም ይሆንባታልን? ፍቅር ደስ የሚያሰኝ ነው።

(4). እግዚአብሔር ለፍቅራችን እጅግ የሚገባና ፍጹም የሆነ ዓላማ ነው። በፍጥረታት ውስጥ ተበታትነው የሚገኙት መልካምነቶች ሁሉ በእርሱ ውስጥ በአንድነት ተሰብስበዋል። እርሱ ጥበብ፣ ውበት፣ ፍቅር ነው፤ አዎን፣ የቸርነት ራሱ ዋና ባሕርይ ነው። በእግዚአብሔር ውስጥ የሚያስጠላ ምንም ነገር የለም፤ ፍጥረት ከማርካቱ በፊት ያስጠግባል፣ ያስመርራልም፤ በእግዚአብሔር ውስጥ ግን አዳዲስ ውበቶች ዘወትር ያበራሉ። ከእርሱ ይበልጥ ባገኘን መጠን ይበልጥ በደስታ እንመሰጣለን።

በእግዚአብሔር ውስጥ የልብ ዝንባሌዎቻችንን የሚያደነዝዝ ወይም ፍቅራችንን የሚያጠፋ ምንም ነገር የለም፤ ብዙውን ጊዜ ፍቅርን የሚያደክሙና የሚያቀዘቅዙ ድካምም ሆነ ጕድለት በእርሱ የለም። በእግዚአብሔር ውስጥ ፍቅራችንን የሚጋብዝ ብቻ ሳይሆን የሚያዝዝም የላቀ መልካምነት አለ። በሰማይ ካሉት የሚበልጡ መላእክት ቢኖሩ፣ እነዚያም የከበሩ ሱራፌል ሁሉ ለዘላለም በደረታቸው ውስጥ የሚነድ ወሰን የሌለው የፍቅር ነበልባል ቢኖራቸው፣ በእርሱ ውስጥ ካለው ወሰን የሌለው ፍጽምናና ከሁሉ የላቀ ቸርነት ጋር የሚመጣጠን ፍቅር እግዚአብሔርን ሊወዱት አይችሉም ነበር። እንግዲያስ እግዚአብሔርን እንድንወድ የሚያነሣሣ በቂ ነገር በዚህ እንዳለ የተረጋገጠ ነው — ፍቅራችንን ከዚህ በሚሻል ዓላማ ላይ ልናውለው አንችልም።

(5). ፍቅር ሃይማኖትን ቀላል ያደርጋል። የልብ ዝንባሌዎችን መንኰራኵሮች ዘይት ይቀባቸዋል፤ በእግዚአብሔር አገልግሎትም ይበልጥ ሕያዋንና ደስተኞች ያደርጋቸዋል። ፍቅር የመንፈሳዊ ተግባርን አሰልቺነት ያስወግዳል። ያዕቆብ ለራሔል ከነበረው ፍቅር የተነሣ ሰባቱን ዓመት እንደ ጥቂት ቈጠረው። ፍቅር መንፈሳዊ ተግባርን ደስታ ያደርገዋል። መላእክት በእግዚአብሔር አገልግሎት እንደዚህ ፈጣኖችና ክንፍ ያላቸው የሆኑት ስለ ምንድር ነው? ስለሚወዱት ነው። ፍቅር ፈጽሞ አይታክትም። እግዚአብሔርን የሚወድ ይህን ከመናገር ፈጽሞ አይታክትም። እግዚአብሔርን የሚወድ እርሱን ከማገልገል ፈጽሞ አይታክትም።

(6). እግዚአብሔር ፍቅራችንን ይሻል። ውበታችንን አጥተናል፤ ደማችንንም አርክሰናል፤ ቢሆንም የሰማይ ንጉሥ እኛን ለማጨት ይለምነናል። እግዚአብሔር እንዲፈልገው በፍቅራችን ውስጥ ምን አለ? በፍቅራችንስ እግዚአብሔር ምን ይጠቀማል? አያስፈልገውም፤ በራሱ ወሰን በሌለው ሁኔታ ብፁዕ ነው። ፍቅራችንን ብንከለክለው፣ በደስታ የፍቅርን ግብር የሚከፍሉለት ከእኛ የላቁ ፍጥረታት አሉት። እግዚአብሔር ፍቅራችን አያስፈልገውም፤ ቢሆንም ይፈልገዋል።

(7). እግዚአብሔር ፍቅራችን ይገባዋል፤ እርሱ እንዴት ወደደን! የልብ ዝንባሌዎቻችን በእግዚአብሔር ፍቅር እሳት ሊቀጣጠሉ ይገባቸዋል። በእኛ ውስጥ የሚወደድ ምንም ነገር ሳይኖር እግዚአብሔር መውደዱ እንዴት ያለ የፍቅር ተአምር ነው! «በደምሽ ውስጥ ሳለሽ፦ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ» (ሕዝቅኤል 16:6)። የተጸየፍንበት ጊዜ እግዚአብሔር የወደደበት ጊዜ ነበር። ቍጣን የሚያነሣሣ ነገር እንጂ ፍቅርን የሚቀሰቅስ ምንም ነገር በእኛ ውስጥ አልነበረም። ክርስቶስን ለእኛ መስጠቱ እንዴት ያለ ከመረዳት ሁሉ የሚያልፍ ፍቅር ነው! ክርስቶስ ስለ ኃጢአተኞች መሞቱ! እግዚአብሔር በሰማይ ያሉትን መላእክት ሁሉ በዚህ ፍቅር እንዲደነቁ አድርጓቸዋል። አውግስጢኖስ እንዲህ ይላል፦ «መስቀል መስበኪያ መድረክ ነው፤ ክርስቶስ በእርሱ ላይ ሆኖ የሰበከው ትምህርትም ፍቅር ነው።» የሚሞተው አዳኝ ሕያው ፍቅር እንዴት ያለ ነው! ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሁለንተናው እየደማ የማየው ይመስለኛል! እንዲህ ሲለን የምሰማው ይመስለኛል፦ «እጆቻችሁን ወደዚህ አምጡ። በጎኖቼ ውስጥ አግቧቸው። የሚደማውን ልቤን ዳስሱ። እንደምወዳችሁ ወይም እንደማልወዳችሁ እዩ። እናንተስ ፍቅራችሁን አትሰጡኝምን? ከእኔ ይልቅ ዓለምን ትወዳላችሁን? ዓለም ስለ እናንተ የእግዚአብሔርን ቍጣ አበረደን? ይህን ሁሉ ያደረግሁ እኔ አይደለሁምን? እናንተስ አትወዱኝምን?» ወደሚወደን መውደድ ተፈጥሯዊ ነው። ክርስቶስ የፍቅርን ናሙና ጽፎ፣ በደሙም ጽፎ ስለ ሰጠን፣ እንደዚያ ያለውን ውብ ናሙና ተከትለን ለመጻፍ፣ በፍቅርም እርሱን ለመምሰል እንትጋ።

(8). እግዚአብሔርን መውደድ ከሁሉ የተሻለው ራስን መውደድ ነው። ነፍስን ማዳን ራስን መውደድ ነው፤ እግዚአብሔርን በመውደዳችን የራሳችንን መዳን እናፋጥናለን። «በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል» (1ኛ ዮሐንስ 4:16)። እግዚአብሔር በልቡ የሚኖርበት ሰው በሰማይ ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚኖር እርግጠኛ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔርን መውደድ እጅግ እውነተኛው ራስን መውደድ ነው፤ እግዚአብሔርን የማይወድ ራሱንም አይወድም።

(9). እግዚአብሔርን መውደድ ቅንነትን ያሳያል። «ቅኖች ይወዱሃል» (መኃልየ መኃልይ 1:4)። ብዙ የእግዚአብሔር ልጆች ግብዝ እንዳይሆኑ ይፈራሉ። አንተ እግዚአብሔርን ትወደዋለህን? ጴጥሮስ በኃጢአቱ ስሜት በተሰበረ ጊዜ፣ ክርስቶስ ዳግመኛ ሊመለከተው ወይም በሐዋርያነቱ ሥራ ሊጠቀምበት እንደማይገባው አሰበ፤ ክርስቶስ እርሱን ለማጽናናት እንዴት እንደሚጣጣር ተመልከት። «ጴጥሮስ ሆይ፥ ትወደኛለህን?» (ዮሐንስ 21:15)። ክርስቶስ እንዲህ ያለ ይመስላል፦ «ምንም እንኳ በፍርሃት ብትክደኝ፣ ከልብህ እንደምትወደኝ ልትናገር ከቻልህ ቅንና ትክክለኛ ነህ።» እግዚአብሔርን መውደድ እርሱን ከመፍራት ይልቅ የተሻለ የቅንነት ምልክት ነው። እስራኤላውያን የእግዚአብሔርን ፍትሕ ፈሩ። «በገደላቸው ጊዜ ፈለጉት፥ ተመልሰውም ወደ እግዚአብሔር ማለዱ» (መዝሙር 78:34)። ይህ ሁሉ ግን ወደ ምን አደረሰ? «ነገር ግን በአፋቸው ሸነገሉት፥ በአንደበታቸውም ዋሹበት፤ ልባቸው ከእርሱ ጋር የቀና አልነበረምና» (ቍጥር 36, 37)። ከእግዚአብሔር ፍርዶች ፍርሃት ብቻ የሚነሣና ፍቅር ያልተቀላቀለበት ንስሐ ከሽንገላ አይሻልም። እግዚአብሔርን መውደድ ልብ የእግዚአብሔር መሆኑን ያሳያል፤ ልብ የእርሱ ከሆነ ደግሞ የቀረውን ሁሉ ያዝዛል።

(10). ለእግዚአብሔር ካለን ፍቅር እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር ልንረዳ እንችላለን። «እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን» (1ኛ ዮሐንስ 4:19)። ነፍስ እንዲህ ትላለች፦ «ወይ፣ እግዚአብሔር እንደሚወደኝ ባውቅ ኖሮ ደስ ባለኝ ነበር!» አንተ እግዚአብሔርን ትወደዋለህን? እንግዲያስ እግዚአብሔር እንደሚወድህ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። በሚያቃጥሉ መነጽሮች እንደሚሆነው ነው፤ መነጽሩ ቢያቃጥል ፀሐይ አስቀድማ በእርሱ ላይ ስላበራች ነው፤ አለዚያ ሊያቃጥል አይችልም ነበር፤ እንዲሁ ልባችን ለእግዚአብሔር ባለ ፍቅር ቢነድድ የእግዚአብሔር ፍቅር አስቀድሞ በእኛ ላይ ስላበራ ነው፤ አለዚያ በፍቅር ልንነድድ አንችልም ነበር። ፍቅራችን የእግዚአብሔር ፍቅር ነጸብራቅ እንጂ ሌላ አይደለም።

(11). እግዚአብሔርን ካልወደድህ ሌላ ነገርን ትወዳለህ፤ ዓለምን ወይም ኃጢአትን፤ እነዚህስ ለፍቅርህ የሚገባቸው ናቸውን? ከእነዚህ ይልቅ እግዚአብሔርን መውደድ አይሻልምን? በሚከተሉት ነጥቦች እንደሚታየው ከዓለም ይልቅ እግዚአብሔርን መውደድ ይሻላል።

ፍቅርህን በዓለማዊ ነገሮች ላይ ብታደርግ አያረኩህም። ነፍስህን በምድር ከምታጠግብ ሥጋህን በአየር ብታጠግብ ይቀላል። «በጥጋቡ ሙላት ይጨነቃል» (ኢዮብ 20:22)። ብዛትም የራሱ ድህነት አለው። የዓለም ክበብ ሁሉ የአንተ ቢሆን ነፍስህን አይሞላትም። ታዲያ ፈጽሞ እርካታ በማይሰጥህ ነገር ላይ ፍቅርህን ታደርጋለህን? እግዚአብሔርን መውደድ አይሻልምን? እርሱ የሚያረካህን ይሰጥሃል። «በነቃሁ ጊዜ በመልክህ እጠግባለሁ» (መዝሙር 17:15)። ከሞት እንቅልፍ በነቃሁ ጊዜ፣ ከእግዚአብሔርም ክብር ጨረሮችና ብርሃናት ጥቂቱ በላዬ በተደረገ ጊዜ፣ ያን ጊዜ በመልኩ እጠግባለሁ።

ዓለማዊ ነገሮችን ብትወድ የአእምሮን ጭንቀት ሊያስወግዱ አይችሉም። በሕሊና ውስጥ እሾህ ቢኖር ዓለም ሁሉ ሊነቅለው አይችልም። ንጉሥ ሳኦል በአእምሮው በተጨነቀ ጊዜ የዘውዱ ዕንቍዎች ሁሉ ሊያጽናኑት አልቻሉም (1ኛ ሳሙኤል 28:15)። እግዚአብሔርን ብትወድ ግን ሌላ ምንም ነገር ሊሰጥህ በማይችልበት ጊዜ እርሱ ሰላምን ሊሰጥህ ይችላል፤ « የሞትን ጥላ ወደ ንጋት» ሊለውጥ ይችላል (አሞጽ 5:8)። ነፍስህን ለማደስ የክርስቶስን ደም ሊያደርግልህ ይችላል፤ በመንፈሱ ፍቅሩን በሹክሹክታ ሊነግርህ፣ በአንድ ፈገግታም ፍርሃቶችህንና ጭንቀቶችህን ሁሉ ሊበትን ይችላል።

ዓለምን ብትወድ ከሰማይ ሊያስቀርህ የሚችለውን ትወዳለህ። ዓለማዊ ምቾቶች በሠራዊት ውስጥ ካሉ የስንቅ ሠረገላዎች ጋር ሊነጻጸሩ ይችላሉ፤ ወታደሮች በሠረገላዎቹ ዘንድ ስንቃቸውን ሲሰበስቡ ጦርነቱን ተሸንፈዋል። «ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል!» (ማርቆስ 10:23)። ብልጽግና ለብዙዎች ጀልባን ፈጥኖ እንደሚገለብጥ ሸራ ነው፤ ስለዚህ ዓለምን በመውደድህ አደጋ ላይ የሚጥልህን ትወዳለህ። እግዚአብሔርን ብትወድ ግን ሰማይን የማጣት ፍርሃት የለም። ሊሰውርህ እንጂ ሊጎዳህ ያልሆነ ዓለት ይሆንልሃል። እርሱን በመውደድ እርሱን ወደ መደሰት እንደርሳለን።

ዓለማዊ ነገሮችን ልትወድ ትችላለህ፤ እነርሱ ግን በምላሹ ሊወዱህ አይችሉም። ወርቅንና ብርን ትወዳለህ፤ ወርቅህ ግን በምላሹ ሊወድህ አይችልም። ሥዕልን ትወዳለህ፤ ሥዕሉ ግን በምላሹ ሊወድህ አይችልም። ፍቅርህን ለፍጥረት ትሰጣለህ፤ ምንም ፍቅር ግን አትቀበልም። እግዚአብሔርን ብትወድ ግን እርሱ በምላሹ ይወድሃል። «የሚወደኝ ቢኖር … አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን» (ዮሐንስ 14:23)። እግዚአብሔር እኛን በመውደድ ወደ ኋላ አይቀርም፤ ስለ ጠብታችን ውቅያኖስን እንቀበላለን።

ዓለምን ስትወድ ከእናንተ የሚያንሰውን ትወዳላችሁ። የደማስቆው ዮሐንስ እንደሚለው፣ ነፍስ የሰማያዊ ብርሃን ፍንጣሪ ናት፤ የእግዚአብሔርን አምሳያና መልክ በውስጧ ትሸከማለች። ዓለምን በምትወዱበት ጊዜ ከነፍሳችሁ ክብር እጅግ በታች የሆነውን ትወዳላችሁ። በማቅ ላይ ገንዘቡን የሚያፈስስ ማን ነው? ፍቅራችሁን በዓለም ላይ በምታውሉበት ጊዜ ዕንቍን በእሪያ ላይ ታንጠለጥላላችሁ፤ ከራሳችሁ የሚያንሰውን ትወዳላችሁ። ክርስቶስ በሌላ ትርጕም ስለ ሰማይ ወፎች፦ «እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?» (ማቴዎስ 6:26) እንዳለ፣ እኔም ስለ ዓለማዊ ነገሮች፦ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? እላለሁ። ያማረ ቤትን፣ ውብ ሥዕልን ትወዳላችሁ፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? እግዚአብሔርን ብትወዱ ግን ፍቅራችሁን እጅግ በከበረውና በላቀው ዓላማ ላይ ታደርጋላችሁ፤ ከራሳችሁ የሚበልጠውን ትወዳላችሁ። እግዚአብሔር ከነፍስ ይበልጣል፤ ከመላእክት ይበልጣል፤ ከሰማይም ይበልጣል።

ዓለምን ልትወዱ ትችላላችሁ፤ ስለ ፍቅራችሁም ጥላቻን ትቀበላላችሁ። «ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል» (ዮሐንስ 15:19)። እህልን ወይም ወይንን ከማፍራት ይልቅ ሳማ ብቻ በሚያበቅል መሬት ላይ ገንዘቡን ማውጣት ሰውን አያበሳጭምን? ከጨረቃ በታች ያሉ ነገሮች ሁሉ እንዲሁ ናቸው፤ እንወዳቸዋለን፤ እነርሱም የሚያቃጥሉ ሳማዎች ይሆኑብናል። ከተስፋ መቍረጥ በቀር ምንም አናገኝም። «ከእሾሁ ቍጥቋጦ እሳት ይውጣ፥ የሊባኖስንም ዝግባ ይብላ» (መሳፍንት 9:15)። ፍጥረትን በምንወድበት ጊዜ ከዚህ የእሾህ ቍጥቋጦ እኛን የሚበላ እሳት ይወጣል፤ እግዚአብሔርን ብንወድ ግን ስለ ፍቅር ጥላቻን አይመልስልንም። «የሚወድዱኝን እወድዳቸዋለሁ» (ምሳሌ 8:17)። እግዚአብሔር ሊገሥጽ ይችላል፤ ሊጠላ ግን አይችልም። አማኝ ሁሉ የክርስቶስ ክፍል ነው፤ እግዚአብሔር አማኝን ከሚጠላ ክርስቶስን ቢጠላ ይቀላል።

ፍጥረትን ከመጠን በላይ ልትወዱ ትችላላችሁ። የወይን ጠጅን ከመጠን በላይ፣ ብርንም ከመጠን በላይ ልትወዱ ትችላላችሁ፤ እግዚአብሔርን ግን ከመጠን በላይ ልትወዱት አትችሉም። ማለፍ ቢቻል ኖሮ በዚህ ረገድ ከመጠን ማለፍ በጎነት በሆነ ነበር፤ ኃጢአታችን ግን እግዚአብሔርን በበቂ መውደድ አለመቻላችን ነው። «ልብሽ እንዴት ደካማ ነው!» (ሕዝቅኤል 16:30)። እንዲሁ ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር እንዴት ደካማ ነው! ሊባል ይችላል። ኃይሉ እጅግ ያነሰውን ከማንጠሪያው በመጨረሻ የሚወጣውን ውኃ ይመስላል። እግዚአብሔርን አሁን ከምንወደው እጅግ አብልጠን ብንወደው እንኳ ለክብሩ የሚመጣጠን አይሆንም ነበር፤ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ባለን ፍቅር ከመጠን የማለፍ አደጋ የለም።

ዓለማዊ ነገሮችን ልትወዱ ትችላላችሁ፤ እነርሱም ይሞታሉ፣ ትተዋችሁም ይሄዳሉ። ባለጠግነት ክንፍ ያወጣል፤ ዘመዶች ይረግፋሉ። በዚህ የሚኖር ምንም ነገር የለም፤ ፍጥረት በአፉ ጥቂት ማር አለው፤ ነገር ግን ክንፍ አለው፤ ፈጥኖ ይበርራል። እግዚአብሔርን ብትወዱ ግን እርሱ « ለዘላለም ዕድል ፈንታ» ነው (መዝሙር 73:26)። ስለ መጽናናት ፀሐይ እንደ ተባለ እንዲሁ ስለ ዘላለማዊነት ዓለት ተብሏል፤ ለዘላለም ይኖራል። እንግዲህ ከዓለም ይልቅ እግዚአብሔርን መውደድ እንደሚሻል እናያለን።

ከዓለም ይልቅ እግዚአብሔርን መውደድ የሚሻል ከሆነ፣ በእርግጥ ከኃጢአትም ይልቅ እግዚአብሔርን መውደድ ይሻላል። ማንም ይወደው ዘንድ በኃጢአት ውስጥ ምን አለ? ኃጢአት ዕዳ ነው። «በደላችንን ይቅር በለን» (ማቴዎስ 6:12)። ለእግዚአብሔር ቍጣ የሚያስይዝ ዕዳ ነው፤ ታዲያ ኃጢአትን ለምን እንወዳለን? ዕዳ ውስጥ መግባትን የሚወድ ሰው አለን? ኃጢአት በሽታ ነው። «ራስ ሁሉ ታሞአል» (ኢሳይያስ 1:5)። ታዲያ ኃጢአትን ትወዳለህን? በሽታን የሚያቅፍ ሰው አለን? የመቅሠፍት ቍስሎቹን ይወዳልን? ኃጢአት ርኵሰት ነው። ሐዋርያው «ርኵሰት» ብሎ ይጠራዋል (ያዕቆብ 1:21)። ከለምጽና ከእባብ መርዝ ጋር ተነጻጽሯል። የእግዚአብሔር ልብ በኃጢአተኞች ላይ ይነሣል። «ነፍሴ ተጸየፈቻቸው» (ዘካርያስ 11:8)። ኃጢአት መልኩ የተበላሸ ጭራቅ ነው፤ ምኞት ሰውን እንስሳ ያደርገዋል፤ ክፋት ሰይጣን ያደርገዋል። በኃጢአት ውስጥ የሚወደድ ምን አለ? የተበላሸን መልክ እንወዳለንን? ኃጢአት ጠላት ነው። ከ«እባብ» ጋር ተነጻጽሯል (ምሳሌ 23:32)። አራት መውጊያዎች አሉት — ኀፍረት፣ በደለኛነት፣ ሽብርና ሞት። ሰው ሞቱን የሚሻውን ይወዳልን? እንግዲያስ በእርግጥ ከኃጢአት ይልቅ እግዚአብሔርን መውደድ ይሻላል። እግዚአብሔር ያድንሃል፤ ኃጢአት ግን ያስኰንንሃል፤ ኵነኔን የሚወድ ሰነፍ አልሆነምን?

(12). ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ዝምድና ፍቅርን ይጠይቃል። የቅርብ ዝምድና አለ። «ፈጣሪሽ ባልሽ ነው» (ኢሳይያስ 54:5)። ታዲያ ሚስት ባሏን አትወድምን? እርሱ ርኅራኄ የሞላበት ነው፤ ሙሽራይቱ ለእርሱ እንደ ዓይኑ ብሌን ናት። ሙሽራ በሙሽራይቱ ደስ እንደሚለው እርሱ በእርሷ ደስ ይለዋል (ኢሳይያስ 62:5)። ክርስቶስን እንደሚወድ አማኙን ይወዳል (ዮሐንስ 17:26)። በመጠን እኩል ባይሆንም በዓይነቱ ያው ፍቅር ነው። እግዚአብሔርን መውደድ አለብን፤ አለዚያ ገና ከእርሱ ጋር ያልተባበርን መሆናችንን የሚያስጠረጥር ምክንያት እንሰጣለን።

(13). ፍቅር እጅግ ጸንቶ የሚኖር ጸጋ ነው። ሌሎች ጸጋዎች ተሰናብተው በሚሄዱበት ጊዜ ይህ ከእኛ ጋር ይኖራል። በሰማይ ኃጢአት ስለማይኖርብን ንስሐ አያስፈልገንም። በሰማይ መከራ ስለማይኖር ትዕግሥት አያስፈልገንም። በሰማይ እምነት አያስፈልገንም፤ እምነት የማይታዩትን ነገሮች ይመለከታልና (ዕብራውያን 11:1)። ያን ጊዜ ግን እግዚአብሔርን ፊት ለፊት እናያለን፤ ማየት ባለበት ስፍራ ደግሞ እምነት አያስፈልግም።

ሌሎቹ ጸጋዎች ጊዜያቸው ባለፈ ጊዜ ግን ፍቅር ይቀጥላል፤ በዚህም ትርጕም ሐዋርያው ፍቅር ከእምነት እንደሚበልጥ ይናገራል፤ ከሁሉ አብልጦ ጸንቶ ይኖራልና። «ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም» (1ኛ ቆሮንቶስ 13:8)። እምነት በዚህ ሕይወት የምንመረኰዝበት በትር ነው። «በእምነት እንመላለሳለን» (2ኛ ቆሮንቶስ 5:7)። ይህን በትር ግን በሰማይ ደጅ እንተወዋለን፤ የሚገባው ፍቅር ብቻ ነው። በዚህ ፍቅር ከሌሎቹ ጸጋዎች ሁሉ አክሊሉን ይወስዳል። ፍቅር ከጸጋዎች ሁሉ ረጅም ዕድሜ ያለው ነው፤ የዘላለም ፍሬ አበባ ነው። በሰማይ ከእኛ ጋር ብቻውን በሚኖረውና ወደ በጉ የሰርግ እራት በሚያጅበን በዚህ ጸጋ ልንበልጥ እንዴት ልንተጋ ይገባናል!

(14). ለእግዚአብሔር ያለ ፍቅር ኃጢአት በልብ ውስጥ እንዲለመልም ፈጽሞ አይፈቅድም። አንዳንድ ተክሎች ተቀራርበው ሲተከሉ አይለመልሙም፤ የእግዚአብሔር ፍቅር ኃጢአትን ያጠወልጋል። አሮጌው ሰው ቢኖርም እንደ ታመመ ሰው ደካማ ነው፤ ትንፋሹም አጭር ነው። የፍቅር አበባ የኃጢአትን አረም ይገድላል፤ ኃጢአት ፈጽሞ ባይሞትም ዕለት ዕለት ይሞታል። ኃጢአትን ለማጥፋት ብቸኛው የሚያቃጥል መድኃኒት ለሆነው ለዚያ ጸጋ እንዴት ልንደክም ይገባናል!

(15). ለእግዚአብሔር ያለ ፍቅር በጸጋ ለማደግ እጅግ ጥሩ መንገድ ነው። «ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ» (2ኛ ጴጥሮስ 3:18)። በጸጋ ማደግ እግዚአብሔርን እጅግ ደስ ያሰኘዋል። ክርስቶስ የጸጋን እውነተኛነት ይቀበላል፤ የጸጋን መጠን ደግሞ ያመሰግናል፤ ጸጋን ለእግዚአብሔር ካለ ፍቅር ይበልጥ የሚያሳድገውና የሚያበዛው ምን አለ? ፍቅር ዛፉን የሚያሳድገውን ሥሩን ማጠጣት ይመስላል። ስለዚህ ሐዋርያው በጸሎቱ ይህን አገላለጽ ይጠቀማል፦ «ጌታም ወደ እግዚአብሔር ፍቅር … ልባችንን ያቅናው» (2ኛ ተሰሎንቄ 3:5)። ይህ የፍቅር ጸጋ ጸጋዎችን ሁሉ እንደሚያጠባና እንደሚንከባከብ ያውቅ ነበር።

(16). እግዚአብሔርን ብንወድ የሚገኝልን ታላቅ ጥቅም። «ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው» (1ኛ ቆሮንቶስ 2:9)። ዓይን ብርቅ ትዕይንቶችን አይቷል፤ ጆሮ ጣፋጭ ዜማን ሰምቷል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀውን ዓይን አላየችውም፤ ጆሮም አልሰማውም፤ የሰውም ልብ ሊያስበው አይችልም! አውግስጢኖስ እንደሚለው፣ እምነት ራሱ ሊረዳው የማይችል እንደዚህ ያለ የከበረ ዋጋ ተዘጋጅቷል። እግዚአብሔር ለሚወዱት የሕይወትን አክሊል ተስፋ ሰጥቷል (ያዕቆብ 1:12)። ይህ አክሊል ብፅዕናን ሁሉ — ባለጠግነትን፣ ክብርንና ደስታን — በውስጡ ያቅፋል፤ የማይጠወልግ አክሊልም ነው (1ኛ ጴጥሮስ 5:4)። እንዲህ እግዚአብሔር በሽልማት ወደ እርሱ ሊስበን ይወዳል።

(17). ለእግዚአብሔር ያለ ፍቅር ከስሕተት የሚጠብቅ የተፈተነ ጦር ዕቃ ነው። ልባቸው በፍቅር ስላልተሞላ የሰዎች ራስ በስሕተት ይሞላል፤ ርኩስ አስተሳሰቦች የሚመጡት ቅዱስ የልብ ዝንባሌዎች በመጥፋታቸው ነው። ሰዎች ለብርቱ ማታለል አልፈው የሚሰጡት ስለ ምንድር ነው? «የእውነትን ፍቅር ስላልተቀበሉ» ነው (2ኛ ተሰሎንቄ 2:10, 11)። እግዚአብሔርን ይበልጥ በወደድን መጠን ከእግዚአብሔር አርቀው ወደ ልቅነት ሊስቡን የሚሹትን ከትክክለኛ አስተምህሮ ያፈነገጡ አስተሳሰቦች ይበልጥ እንጠላለን።

(18). እግዚአብሔርን ብንወድ ነፋሳት ሁሉ ለእኛ ይነፍሳሉ፤ በዓለም ያለ ነገር ሁሉ ለበጎአችን ይተባበራል። ምን ዓይነት የእሳት ፈተናዎች እንደሚገጥሙን አናውቅም፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን ለሚወዱት ነገር ሁሉ ለበጎ ይደረግላቸዋል። የሚቃወሟቸው ነገሮች ለእነርሱ ይሠራሉ፤ መስቀላቸው ለአክሊል መንገድ ያዘጋጃል፤ ነፋስ ሁሉ ወደ ሰማያዊው ወደብ ይነፍሳቸዋል።

(19). ለእግዚአብሔር ፍቅር ማጣት የክህደት መሠረት ነው። በምሳሌው ውስጥ ሥር ያልነበረው ዘር ወደቀ። የእግዚአብሔር ፍቅር በልቡ ውስጥ ሥር ያልሰደደበት በፈተና ጊዜ ይወድቃል። እግዚአብሔርን የሚወድ ሩት ከኑኃሚን ጋር እንደ ተጣበቀች ከእርሱ ጋር ይጣበቃል። «ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ፤ በምትሞቺበትም እሞታለሁ» (ሩት 1:16, 17)። ለእግዚአብሔር ፍቅር የጐደለው ግን ዖርፋ ለአማቷ እንዳደረገችው ያደርጋል፤ ሳመቻት፤ ተሰናብታትም ሄደች። ለአዛዡ ፍቅር የሌለው ወታደር አጋጣሚ ባገኘ ጊዜ ትቶት ወደ ጠላት ወገን ይሸሻል። በልቡ ውስጥ ለእግዚአብሔር ፍቅር የሌለውን ከሃዲ ብለህ ልትመዘግበው ትችላለህ።

(20). ለእግዚአብሔር ልንመልስለት የምንችለው ብቸኛው ነገር ፍቅር ነው። እግዚአብሔር ቢቈጣን እኛ መልሰን ልንቈጣው አይገባም፤ ቢገሥጸን መልሰን ልንገሥጸው አይገባም፤ እግዚአብሔር ቢወደን ግን መልሰን ልንወደው ይገባናል። ከፍቅር በቀር ለእግዚአብሔር መልሰን የምንሰጠው ምንም ነገር የለም። ለቃል ቃል ልንመልስለት አይገባም፤ ለፍቅር ግን ፍቅርን ልንመልስለት ይገባናል።

ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር የሚያነሣሡና የሚያቀጣጥሉ ሃያ ምክንያቶችን እንዲህ አይተናል።

ጥያቄ፦ እግዚአብሔርን ለመውደድ ምን እናድርግ?

መልስ፦ እግዚአብሔርን አጥና። እርሱን ይበልጥ ብናጠና ኖሮ ይበልጥ በወደድነው ነበር። ከሁሉ የላቁትን መልካምነቶቹን፣ ቅድስናውን፣ ሊመረመር የማይችለውን ቸርነቱን ተመልከት። መላእክት እግዚአብሔርን ከእኛ በተሻለ ያውቁታል፤ የግርማውንም ድምቀት በግልጥ ያያሉ፤ ስለዚህ በእርሱ ፍቅር እጅግ የተማረኩ ናቸው።

በእግዚአብሔር ድርሻ እንዲኖርህ ትጋ። «አቤቱ፥ አንተ አምላኬ ነህ» (መዝሙር 63:1)። ያ «አምላኬ» የሚለው «የእኔ» ወደ ፍቅር የሚስብ ጣፋጭ ማግኔት ነው፤ ሰው የራሱ የሆነውን ይወዳል። ይበልጥ ባመንን መጠን ይበልጥ እንወዳለን፤ እምነት ሥር ነው፤ ፍቅርም በእርሱ ላይ የሚያብብ አበባ ነው። «በፍቅር የሚሠራ እምነት» (ገላትያ 5:6)።

እርሱን የሚወድ ልብ እንዲሰጥህ ወደ እግዚአብሔር አጥብቀህ ልመና አቅርብ። ይህ ተቀባይነት ያለው ልመና ነው፤ በእርግጥ እግዚአብሔር እምቢ አይለውም። ንጉሥ ሰሎሞን ከእግዚአብሔር ጥበብን በለመነ ጊዜ፦ «ለባሪያህ አስተዋይ ልብ ስጠው» (1ኛ ነገሥት 3:9)፣ «ይህም ነገር ጌታን ደስ አሰኘው» (ቍጥር 10)። እንዲሁ አንተ ወደ እግዚአብሔር፦ «ጌታ ሆይ፥ አንተን የሚወድ ልብ ስጠኝ። ከዚህ በላይ ልወድህ አለመቻሌ ኀዘኔ ነው። ወይ፣ ይህን ከሰማይ የሆነ እሳት በልቤ መሠዊያ ላይ አቀጣጥለው!» ብለህ ስትጮኽ፣ በእርግጥ ይህ ጸሎት ጌታን ደስ ያሰኘዋል፤ ወርቃማ ዘይቱ የፍቅርህን መብራት አብርቶ የሚያነድደውን መንፈሱንም በአንተ ላይ ያፈስሳል።

2. ለእግዚአብሔር ያላችሁን ፍቅር እንድትጠብቁ የቀረበ ምክር።

ለእግዚአብሔር ፍቅር ያላችሁ እናንተ ልትጠብቁት ትጉ፤ ይህ ፍቅር እንዲሞትና እንዲጠፋ አትፍቀዱ።

የእግዚአብሔር ፍቅር በእናንተ ላይ እንዲቀጥል እንደምትፈልጉ ሁሉ ፍቅራችሁም በእርሱ ላይ ይቀጥል። ፍቅር እንደ እሳት ለመጥፋት የተጋ ነው። «የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃል» (ራእይ 2:4)። ሰይጣን ይህን ነበልባል ለማጥፋት ይደክማል፤ እኛም መንፈሳዊ ተግባርን በመዘንጋታችን እናጣዋለን። ስስ ሰውነት ልብሱን ባወለቀ ጊዜ ለብርድ እንደሚጋለጥ፣ እንዲሁ መንፈሳዊ ተግባርን በተውን ጊዜ ለእግዚአብሔር ባለን ፍቅር ቀስ በቀስ እንቀዘቅዛለን። ከጸጋዎች ሁሉ ለመድከም እጅግ የተጋ ፍቅር ነው፤ ስለዚህ ልንጠብቀው ይበልጥ መጠንቀቅ ያስፈልገናል። ሰው ዕንቍ ቢኖረው ይጠብቀዋል፤ የርስት መሬት ቢኖረው ይጠብቀዋል፤ እንግዲያስ ይህን የፍቅር ጸጋ ለመጠበቅ ምን ያህል ልንጠነቀቅ ይገባናል! ክርስትናን የሚናገሩ ሰዎች ለእግዚአብሔር ባላቸው ፍቅር ሲቀንሱ ማየት ያሳዝናል፤ ብዙዎች በመንፈሳዊ የመመንመን በሽታ ተይዘዋል፤ ፍቅራቸው እየደከመ ነው።

ክርስቲያኖች ፍቅራቸው በመመንመን በሽታ መያዙን የሚያውቁባቸው አራት ምልክቶች አሉ።

(1). ጣዕም ማጣታቸው። በጽኑ የመመንመን በሽታ የተያዘ ሰው ጣዕም የለውም፤ በምግቡ ውስጥ እንደ ቀድሞው ያለ ጣፋጭ ጣዕም አያገኝም። እንዲሁ ክርስቲያኖች ጣዕማቸውን ባጡ ጊዜ፣ በተስፋ ቃል ውስጥም ምንም ጣፋጭነት ባላገኙ ጊዜ፣ የመንፈሳዊ የመመንመን በሽታ ምልክት ነው። «ጌታ ቸር እንደ ሆነ ቀምሳችሁ እንደ ሆነ» (1ኛ ጴጥሮስ 2:3)። ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ መጽናናትን ያገኙበት ጊዜ ነበር። ቃሉ እንደሚንጠባጠብ ማር ለነፍሳቸው ምላስ እጅግ ጣፋጭ ነበር፤ አሁን ግን እንደዚያ አይደለም። በመንፈሳዊ ነገሮች ውስጥ «በእንቍላል ነጭ» ውስጥ ካለው የበለጠ ጣፋጭነት ሊቀምሱ አይችሉም (ኢዮብ 6:6)። ይህ በመመንመን በሽታ መያዛቸውን የሚያሳይ ምልክት ነው፤ ጣዕምን ማጣት የቀደመውን ፍቅር ማጣት ያመለክታል።

(2). ክርስቲያኖች የምግብ ፍላጎታቸውን ማጣታቸው። በጽኑ የመመንመን በሽታ የተያዘ ሰው እንደ ቀድሞው ምግቡን አይፈልግም። ክርስቲያኖች «ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ» የነበሩበት ጊዜ ነበር (ማቴዎስ 5:6)። ሰማያዊ መልክ ያላቸውን ነገሮች — የመንፈስን ጸጋ፣ የመስቀሉን ደም፣ የእግዚአብሔርን ፊት ብርሃን — ያስቡ ነበር። የጸጋ መንገዶችን ይናፍቁ ነበር፤ የተራበ ሰው ወደ ግብዣ እንደሚመጣ ወደ እነርሱ ይመጡ ነበር። አሁን ግን ሁኔታው ተለውጧል። የምግብ ፍላጎት የላቸውም፤ ክርስቶስን እንደዚያ ከፍ አድርገው አይመለከቱትም፤ ለቃሉ እንደዚያ ያለ ብርቱ የልብ ዝንባሌ የላቸውም፤ ልባቸው በውስጣቸው አይቃጠልባቸውም፤ ይህ በመመንመን በሽታ መያዛቸውን፣ ፍቅራቸውም እየደከመ መሆኑን የሚያሳይ አሳዛኝ ምልክት ነው። ልብስ ቢያለብሱትም ሙቀት ባላገኘ ጊዜ የዳዊት የተፈጥሮ ብርታት እንደ ደከመ የሚያሳይ ምልክት ነበር (1ኛ ነገሥት 1:1)። እንዲሁ ሰዎች በሞቀ ልብስ (የጸጋ መንገዶችን ማለቴ ነው) ቢለበሱም የልብ ዝንባሌ ሙቀት ከሌላቸው፣ ይልቁንም ለመገነዝ የተዘጋጁ ይመስል ቀዝቃዛዎችና የደረቁ ከሆኑ፣ ይህ የቀደመ ፍቅራቸው እንደ ቀነሰ፣ በጽኑ የመመንመን በሽታም እንደ ተያዙ የሚያሳይ ምልክት ነው።

(3). ክርስቲያኖች ዓለምን ይበልጥ እየወደዱ ሲሄዱ፣ ይህ የመንፈሳዊ ፍቅር መቀነስን ያመለክታል። በአንድ ወቅት ከፍ ያለና ሰማያዊ ጠባይ ነበራቸው፤ የከነዓንን ቋንቋ ይናገሩ ነበር፤ አሁን ግን በወንጌል ውስጥ እንዳለው በአፉ ገንዘብ እንደ ነበረው ዓሣ ናቸው (ማቴዎስ 17:27)። ሦስት ቃላት መናገር አይችሉም፤ አንዱ ስለ ገንዘብ (ማሞና) ካልሆነ። አሳባቸውና የልብ ዝንባሌዎቻቸው እንደ ሰይጣን ዘወትር ምድርን ይዞራሉ፤ ይህ ኮረብታውን በፍጥነት እየወረዱ መሆናቸውን፣ ለእግዚአብሔር ያላቸውም ፍቅር በመመንመን በሽታ መያዙን የሚያሳይ ምልክት ነው። ተፈጥሮ ሲደክምና ሲዝል ሰዎች ይበልጥ እየጐበጡ እንደሚሄዱ እናስተውላለን፤ በእውነትም ልብ ወደ ምድር ይበልጥ ሲጐብጥ፣ ወደ ሰማያዊ አሳብ ራሱን ቀና ማድረግ እስኪሳነው ድረስ ሲጐነበስ፣ አሁን በቀደመ ፍቅሩ በአሳዛኝ ሁኔታ እየቀነሰ ነው። ዝገት ከብረት ጋር ሲጣበቅ የብረቱን ድምቀት የሚያጠፋ ብቻ ሳይሆን ይበላዋል፣ ያጠፋዋልም፤ እንዲሁ ምድር ከሰዎች ነፍስ ጋር ስትጣበቅ የጸጋዎቻቸውን ብሩህ ድምቀት የምትከለክል ብቻ ሳይሆን ቀስ በቀስ ትበላቸዋለች።

(4). ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን አምልኮ በጥቂቱ ሲቈጥሩት። የሃይማኖት ተግባሮች በሙት፣ ለይስሙላ በሆነ ሁኔታ ይፈጸማሉ፤ ሳይፈጸሙ ባይቀሩ እንኳ በክፉ ይፈጸማሉ። ይህ የመንፈሳዊ የመመንመን በሽታ አሳዛኝ ምልክት ነው፤ በመንፈሳዊ ተግባር መላላት በቀደመው ፍቅራችን መድከምን ያሳያል። የመሰንቆ አውታሮች ሲላሉ መሰንቆው ፈጽሞ መልካም ዜማ ሊያሰማ አይችልም፤ ሰዎች በመንፈሳዊ ተግባር ሲላሉ እንዳልጸለዩ ሆነው ይጸልያሉ፤ ይህ በእግዚአብሔር ጆሮ ፈጽሞ የሚስማማ ድምፅ ሊያሰማ አይችልም። መንፈሳዊው እንቅስቃሴ ዘገምተኛና ከባድ ሲሆን፣ የነፍስም ትርታ ዝቅ ብሎ ሲመታ፣ ክርስቲያኖች የቀደመ ፍቅራቸውን እንደ ተዉ የሚያሳይ ምልክት ነው።

ከዚህ መንፈሳዊ የመመንመን በሽታ እንጠንቀቅ፤ በፍቅራችን መቀነስ አደገኛ ነው። ፍቅር ያለ እርሱ እንዴት መኖር እንደምንችል የማናውቀው ጸጋ ነው። ክርስቲያን ያለ ፍቅር ከሚኖር ወታደር ያለ ጦር መሣሪያው፣ ሠዓሊ ያለ ብሩሹ፣ ሙዚቀኛ ያለ መሣሪያው ቢኖር ይቀላል። ሰውነት የተፈጥሮ ሙቀቱን ሊያጣ አይችልም። የተፈጥሮ ሙቀት ለሰውነት እንደ ሆነ ፍቅር ለነፍስ እንዲሁ ነው፤ ያለ እርሱ መኖር የለም። ፍቅር በጸጋዎች ላይ ኃይሉን ያሳድራል፤ የልብ ዝንባሌዎችን ያነሣሣል፤ ስለ ኃጢአት እንድናዝን ያደርገናል፤ በእግዚአብሔር ደስተኞች ያደርገናል፤ ለመንኰራኵሮች እንደ ዘይት ነው፤ በእግዚአብሔር አገልግሎት ሕያዋን ያደርገናል። እንግዲያስ ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር ሕያው አድርገን ለመጠበቅ ምን ያህል ልንጠነቀቅ ይገባናል!

ጥያቄ፦ ፍቅራችን እንዳይጠፋ እንዴት ልንጠብቀው እንችላለን?

መልስ፦ ልባችሁን በየዕለቱ ጠብቁ። በጸጋ የመጀመሪያውን መቀነስ ልብ በሉ። መደንዘዝና መታከት በጀመራችሁ ጊዜ ራሳችሁን አስተውሉ፤ ለመነቃቃትም መንገዶችን ሁሉ ተጠቀሙ። በጸሎት፣ በማሰላሰልና በቅዱስ ውይይት አብዝታችሁ ትጉ። እሳት ሊጠፋ ሲል ማገዶ ትጨምራላችሁ፤ እንዲሁ የፍቅራችሁ ነበልባል ሊጠፋ ሲል የፍቅራችሁ እሳት እየነደደ እንዲቀጥል የጸጋ መንገዶችንና የወንጌልን የተስፋ ቃሎች እንደ ማገዶ ተጠቀሙባቸው።

3. ለእግዚአብሔር ያላችሁን ፍቅር እንድታበዙ የቀረበ ምክር። ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ያላችሁን ፍቅር እንድታበዙ ልምከራችሁ። ፍቅራችሁ ወደ ላይ ከፍ ይበል። «ፍቅራችሁ ከፊት ይልቅ እጅግ እየበዛ እንዲሄድ ይህን እጸልያለሁ» (ፊልጵስዩስ 1:9)። ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር እንደ ማለዳ ብርሃን ሊሆን ይገባዋል፤ መጀመሪያ ጎሕ ይቀዳል፤ ከዚያም እስከ ቀትር ሙላት ድረስ እየደመቀ ያበራል። ጥቂት የፍቅር ፍንጣሪዎች ያሏቸው እነዚያን መለኮታዊ ፍንጣሪዎች አርግበው ነበልባል ሊያደርጓቸው ይገባል። ክርስቲያን ጸጋ አለኝ ወይስ የለኝም ብሎ እስኪጠራጠር ድረስ በምታደርገው በዚህ ያህል ትንሽ የጸጋ ቅንጣት ሊረካ አይገባውም፤ ይልቁንም ሀብቱን ዘወትር ሊያበዛ ይገባዋል። ጥቂት ወርቅ ያለው ይበልጥ እንዲኖረው ይፈልጋል፤ እግዚአብሔርን በጥቂቱ የምትወዱ እናንተ ይበልጥ ልትወዱት ትጉ። እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው በዓለም ነገር እጅግ ጥቂት ቢሆንም ይረካል፤ ቢሆንም ፈጽሞ አይጠግብም፤ ይልቁንም የመንፈስን ሥራ ይበልጥ ይሻል፤ በአንዱ የፍቅር ደረጃ ላይ ሌላውን ለመጨመርም ይደክማል። ክርስቲያኖች በመብራታቸው ላይ ዘይት እንዲጨምሩና የፍቅራቸውን ነበልባል እንዲያበዙ ለማሳመን እነዚህን አራት መለኮታዊ ማነሣሻዎች ላቅርብ።

(1). የፍቅር ማደግ እውነተኛነቱን ያረጋግጣል። የለውዝ ዛፍ ሲያቈጠቍጥና ሲያብብ ባይ በሥሩ ሕይወት እንዳለ አውቃለሁ። ቀለም አያድግም፤ ሥዕል ብቻ የሆነ ግብዝ አያድግም። ለእግዚአብሔር ያለ ፍቅር እንደ ኤልያስ ደመና እየጨመረና እየሰፋ ሲሄድ በምናይበት ስፍራ ግን እውነተኛና ትክክለኛ መሆኑን ልንደመድም እንችላለን።

(2). በፍቅር በማደግ በመጽሐፍ ቅዱስ ያሉትን ቅዱሳን እንመስላለን። ለእግዚአብሔር የነበራቸው ፍቅር እንደ መቅደሱ ውኃዎች ወደ ላይ ከፍ እያለ ሄደ። ደቀ መዛሙርት ለክርስቶስ የነበራቸው ፍቅር በመጀመሪያ ደካማ ነበር፤ ከክርስቶስ ሸሹ፤ ከክርስቶስ ሞት በኋላ ግን ይበልጥ በረታ፤ በግልጥም መሰከሩለት። የጴጥሮስ ፍቅር በመጀመሪያ ይበልጥ ደካማና ዝል ነበር፤ ክርስቶስን ካደ፤ በኋላ ግን እርሱን በምን ያህል ድፍረት ሰበከው! ክርስቶስ ፍቅሩን በፈተነው ጊዜ፦ «የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን?» (ዮሐንስ 21:16)፣ ጴጥሮስ በትሕትና ቢሆንም በመተማመን ወደ ክርስቶስ፦ «ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ።» ብሎ ሊማጸን ቻለ። እንዲህ ቀድሞ በፈተና ነፋስ የተገረሰሰው ያ ለጋ ተክል አሁን የሲኦል ኃይላት ሁሉ ሊያናውጡት የማይችሉት ዝግባ ሆኖ አደገ።

(3). የፍቅር ማደግ ሽልማትን ያሰፋል። በፍቅር ይበልጥ በነደድን መጠን በክብር ይበልጥ እናበራለን፤ ፍቅራችን በበለጠ ከፍታ መጠን አክሊላችን ይበልጥ ይደምቃል።

(4). እግዚአብሔርን ይበልጥ በወደድን መጠን ከእርሱ ይበልጥ ፍቅር እናገኛለን። እግዚአብሔር የፍቅሩን ጣፋጭ ምሥጢሮች ለእኛ እንዲገልጥልን እንወዳለንን? የፊቱን ፈገግታ እንሻለንን? ወይ፣ እንግዲያስ ወደ ከፍተኛ የፍቅር ደረጃዎች ለመድረስ እንጣጣር። ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ወርቅንና ዕንቍን እንደ ጕድፍ ቈጠረ (ፊልጵስዩስ 3:8)። አዎን፣ ለእግዚአብሔር ባለው ፍቅር እጅግ ተቀጣጥሎ ስለ ነበር፣ ስለ ወንድሞቹ ስለ አይሁድ ከክርስቶስ ተለይቶ ራሱ የተረገመ እንዲሆን እስኪመኝ ደርሶ ነበር (ሮሜ 9:3)። ከክርስቶስ ተለይቶ ሊረገም ይችል ነበር ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ክብር የነበረው የጋለ ፍቅርና የቅድስና ቅናት እጅግ ታላቅ ስለ ነበር፣ እግዚአብሔር ይበልጥ ክብር የሚያገኝ ቢሆን ኖሮ ለመናገር እንኳ ከሚገባው በላይ መከራን ለመቀበል ፈቃደኛ በሆነ ነበር።

በዚህ ፍቅር ሟች ሰው ሊደርስበት ወደሚቻለው ከፍተኛ ጫፍ ድረስ ተወጥሮ ነበር፤ እነሆም፣ እርሱ ለእግዚአብሔር ልብ ምን ያህል ቅርብ ነበር! ጌታ ለጊዜው ወደ ሰማይ ወሰደው፤ በእቅፉም አስተኛው፤ በዚያም እግዚአብሔርን እጅግ በከበረ ሁኔታ አየ፤ «ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል» ሰማ (2ኛ ቆሮንቶስ 12:4)። ለእግዚአብሔር ባለው ፍቅር የከሰረ ሰው ከቶ የለም።

ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር ካልጨመረ ፈጥኖ ይቀንሳል። እሳት ካልተራገበ ፈጥኖ ይጠፋል። ስለዚህ ክርስቲያኖች ከምንም በላይ ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር ለመንከባከብና ለማነሣሣት ሊተጉ ይገባቸዋል። ወደ ሰማይ በደረስን ጊዜ ይህ ምክር ጊዜው ያልፍበታል፤ ያን ጊዜ ብርሃናችን ጥርት ያለ፣ ፍቅራችንም ፍጹም ይሆናልና፤ አሁን ግን ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር ከፊት ይልቅ እጅግ እየበዛ እንዲሄድ መምከር ጊዜው ነው።

ምዕራፍ 8 ተጠናቋል

እግዚአብሔርን እንድንወድ የቀረበ ምክር

ገጽ 1 / 1 · 19 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀዳሚ ቀጣይ