ምዕራፍ 7 · 16 ደቂቃ ንባብ · 20 ደቂቃ ማዳመጥ
ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር መፈተኛዎች
እግዚአብሔርን ከሚወዱት ወገን መሆናችንን ያለ አድልዎ ራሳችንን እንፈትን። ይህን ለመለየት፣ ፍቅራችን ከፍሬዎቹ በተሻለ ሁኔታ የሚታይ ስለ ሆነ፣ ለእግዚአብሔር ያለ ፍቅር አሥራ አራት ምልክቶችን ወይም ፍሬዎችን አቀርባለሁ፤ ከእነዚህም ፍሬዎች አንዳቸው እንኳ በአትክልት ስፍራችን ውስጥ ይበቅሉ እንደ ሆነ አጥብቀን መመርመር ይገባናል።
1. የፍቅር የመጀመሪያው ፍሬ አእምሮ በእግዚአብሔር ላይ ማሰላሰሉ ነው። በፍቅር ያለ ሰው አሳቡ ሁልጊዜ በሚወድደው ላይ ነው። እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው እግዚአብሔርን በማሰላሰል ይመሰጣል፤ በደስታም ይነጠቃል። «ብነቃም ገና ከአንተ ጋር ነኝ» (መዝሙር 139:18)። አሳቦች በአእምሮ ውስጥ እንደሚመላለሱ መንገደኞች ናቸው። የዳዊት አሳቦች የሰማይን መንገድ ይዘው ይጓዙ ነበር፦ ገና ከአንተ ጋር ነኝ። እግዚአብሔር መዝገብ ነው፤ መዝገብ ባለበትም ልብ በዚያ ይሆናል። ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር በዚህ ልንፈትን እንችላለን። አሳባችን ይበልጥ የሚያርፈው በምን ላይ ነው? ስለ እግዚአብሔር ስናስብ በደስታ እንመሰጣለን ማለት እንችላለንን? አሳቦቻችን ክንፍ አውጥተዋልን? ወደ ላይ በርረዋልን? ክርስቶስንና ክብርን እናሰላስላለንን? ወይ! ስለ እግዚአብሔር እምብዛም የማያስቡ ሰዎች እግዚአብሔርን ከመውደድ ምንኛ የራቁ ናቸው! «እግዚአብሔር በአሳቡ ሁሉ የለም» (መዝሙር 10:4)። ኃጢአተኛ እግዚአብሔርን ከአሳቡ ገፍቶ ያስወጣዋል። እስረኛ ዳኛውን እንደሚያስበው በድንጋጤ ካልሆነ በቀር ፈጽሞ ስለ እግዚአብሔር አያስብም።
2. የፍቅር ቀጣዩ ፍሬ የኅብረት ናፍቆት ነው። ፍቅር መቀራረብንና መነጋገርን ይሻል። «ልቤና ሥጋዬ ወደ ሕያው አምላክ ይጮኻሉ» (መዝሙር 84:2)። ንጉሥ ዳዊት የመገኘቱ የሚታይ ምልክት የሆነው ድንኳን ካለበት ከእግዚአብሔር ቤት በተከለከለ ጊዜ፣ እግዚአብሔርን ተናፈቀ፤ በቅዱስ የናፍቆት ስሜትም ወደ ሕያው አምላክ ጮኸ። የሚዋደዱ ሰዎች አብረው መነጋገርን ይወዳሉ። እግዚአብሔርን የምንወድ ከሆንን የጸጋ መንገዶቹን ከፍ አድርገን እንመለከታለን፤ በዚያ ከእግዚአብሔር ጋር እንገናኛለንና። እርሱ በቃሉ ይናገረናል፤ እኛም በጸሎት እንናገረዋለን። ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር በዚህ እንመርምር። ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ኅብረት እንናፍቃለንን? የሚዋደዱ ሰዎች ለረጅም ጊዜ ተለያይተው መቆየት አይችሉም። እግዚአብሔርን የሚወዱ ቅዱስ የልብ ዝንባሌ አላቸው፤ ከእርሱ ተለይተው እንዴት እንደሚኖሩ አያውቁም። ከእግዚአብሔር መገኘት በቀር የማንኛውንም ነገር መጓደል ሊታገሡ ይችላሉ። ያለ ጤናና ያለ ወዳጆች መኖር ይችላሉ፤ ማዕዳቸው ባይሞላም ደስተኞች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ያለ እግዚአብሔር ግን ደስተኞች ሊሆኑ አይችሉም። «ወደ መቃብር እንደሚወርዱት እንዳልሆን ፊትህን ከእኔ አትሰውር» (መዝሙር 143:7)። የሚዋደዱ ሰዎች ራሳቸውን የሚስቱበት ጊዜ አለ። ዳዊት እግዚአብሔርን ማየት ባጣ ጊዜ ዝሎ ሊሞት ደርሶ ነበር። እግዚአብሔርን የሚወዱ በጸጋ መንገዶች ውስጥ እግዚአብሔርን ካላገኙ የጸጋ መንገዶች ስላሏቸው ብቻ አይረኩም፤ ይህ ማሩን ሳይሆን ብርጭቆውን እንደ መላስ ይሆናልና።
በዕድሜ ዘመናቸው ሁሉ ያለ እግዚአብሔር መኖር ስለሚችሉ ሰዎች ምን እንላለን? እግዚአብሔር ቢቀርባቸው ምንም እንደማይጎድልባቸው ያስባሉ፤ ጤናና ንግድ እንደ ጎደላቸው ያማርራሉ፤ እግዚአብሔር እንደ ጎደላቸው ግን አያማርሩም! ክፉዎች ሰዎች እግዚአብሔርን አያውቁትም፤ የማያውቁትንስ እንዴት ሊወዱ ይችላሉ! ከዚህም የከፋው፣ እርሱን ለማወቅ እንኳ አይፈልጉም። «እግዚአብሔርን፦ ከእኛ ራቅ፥ መንገድህንም ማወቅ አንወድድም ይሉታል» (ኢዮብ 21:14)። ኃጢአተኞች ከእግዚአብሔር ጋር መተዋወቅን ይሸሻሉ፤ መገኘቱንም እንደ ሸክም ይቆጥሩታል፤ እነዚህ እግዚአብሔርን የሚወዱ ናቸውን? ባሏ ባለበት መሆንን የማትታገሥ ሴት ባሏን ትወዳለችን?
3. ሌላው የፍቅር ፍሬ ኀዘን ነው። ለእግዚአብሔር ፍቅር ባለበት በእርሱ ላይ ስለ ፈጸምነው የውለታ ቢስነት ኃጢአት ኀዘን አለ። አባቱን የሚወድ ልጅ አባቱን በማስቀየሙ ከማልቀስ አይመለስም። በፍቅር የሚነድድ ልብ በእንባ ይቀልጣል። ወዮ! የዚህን ያህል የተወደደውን የአዳኝን ፍቅር እንዴት አቃልላለሁ! ጌታዬ በመስቀል ላይ የተቀበለው መከራ አይበቃምን፣ እኔም ተጨማሪ መከራ ላስቀበለው ይገባልን? ተጨማሪ ሐሞትና ሆምጣጤ ላጠጣውን? ምንኛ ታማኝነት የጐደለኝና ቅንነት የሌለኝ ሆኛለሁ! መንፈሱን ምንኛ አሳዝኛለሁ፤ ንጉሣዊ ትእዛዛቱን ረግጫለሁ፤ ደሙንም አቃልያለሁ! ይህ እግዚአብሔርን የሚያሰኝ የኀዘን ምንጭ ይከፍታል፤ ልብንም እንደ ገና ያደማል። ጴጥሮስም «ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ልቅሶ አለቀሰ» (ማቴዎስ 26:75)። ጴጥሮስ ክርስቶስ ምን ያህል አጥብቆ እንደ ወደደው፣ ክርስቶስ የሰማይን ክብር በራእይ ወዳሳየበት ወደ ተለወጠበት ተራራ እንዴት እንደ ተወሰደ፣ ከእርሱም ይህን የመሰለ ልዩ ፍቅር ከተቀበለ በኋላ ክርስቶስን መካዱን ባሰበ ጊዜ፣ ይህ ልቡን በኀዘን ሰበረው፤ ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ልቅሶ አለቀሰ።
ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር በዚህ እንፈትን። እግዚአብሔርን የሚያሰኝ የኀዘን እንባ እናፈስሳለንን? በእግዚአብሔር ላይ ስለ ፈጸምነው የውለታ ቢስነት፣ ምሕረቱን ስላቃለልን፣ መክሊቶቻችንንም ስላላተረፍንባቸው እናዝናለንን? ዕለት ዕለት ኃጢአት እየሠሩ ልባቸው ፈጽሞ የማይወቅሳቸው ሰዎች እግዚአብሔርን ከመውደድ ምንኛ የራቁ ናቸው! የኃጢአት ባሕር አላቸው፤ የኀዘን ጠብታ ግን የላቸውም። ከመታወክ እጅግ ርቀው በኃጢአታቸው ይፈነጥዛሉ። «ክፉ ስታደርጊ ያን ጊዜ ደስ ይልሻል» (ኤርምያስ 11:15)። አንተ ጐስቋላ! ክርስቶስ ስለ ኃጢአት ደሙን አፈሰሰ፤ አንተስ ትስቅበታለህን? እነዚህ እግዚአብሔርን ከመውደድ የራቁ ናቸው። ወዳጁን መበደል የሚወድ ሰው ወዳጁን ይወዳልን?
4. ሌላው የፍቅር ፍሬ የልብ ጀግንነት ነው። ፍቅር ደፋር ነው፤ ፍርሃትን ወደ ድፍረት ይለውጣል። ፍቅር ሰውን ታላላቅ ችግሮችንና አደጋዎችን እንዲጋፈጥ ያደርገዋል። ፈሪዋ ዶሮ ጫጩቶቿን ለመከላከል በውሻ ወይም በእባብ ላይ ትወረወራለች። ፍቅር በክርስቲያን ውስጥ የጀግንነትንና የጽናትን መንፈስ ያሳድራል። እግዚአብሔርን የሚወድ ስለ ጉዳዩ ይቆማል፤ ጠበቃም ይሆንለታል። «ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም» (የሐዋርያት ሥራ 4:20)። ክርስቶስን በግልጥ ለመመስከር የሚፈራ ሰው ለእርሱ ያለው ፍቅር ጥቂት ነው። ኒቆዲሞስ በሌሊት ተደብቆ ወደ ክርስቶስ መጣ (ዮሐንስ 3:2)። በቀን ከእርሱ ጋር መታየትን ፈርቶ ነበር። ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል። ፀሐይ ጭጋግንና እንፋሎትን እንደምታስወግድ፣ መለኮታዊ ፍቅርም ሥጋዊ ፍርሃትን በብዙ መጠን ያስወግዳል። የተባረኩ እውነቶቹ ሲሰደቡ እየሰማ ዝም የሚል እግዚአብሔርን ይወዳልን? ወዳጁን የሚወድ ሰው ወዳጁ በተነቀፈ ጊዜ ይቆምለታል፤ ይከራከርለታልም። ክርስቶስ በሰማይ ስለ እኛ ይታያል፤ እኛስ በምድር ስለ እርሱ ለመታየት እንፈራለንን? ፍቅር ክርስቲያንን ያበረታዋል፤ ልቡን በቅናት ያቀጣጥለዋል፤ በድፍረትም ያጸናዋል።
5. አምስተኛው የፍቅር ፍሬ ለእግዚአብሔር ክብር መቈርቈር ነው። እግዚአብሔርን የምንወድ ከሆንን ክፉዎች ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ በሚያደርሱት ውርደት ልባችን ይታመማል። የሃይማኖት ብቻ ሳይሆን የግብረ ገብነትም ዳርቻዎች ፈርሰው የክፋት ጐርፍ ሲገባ ማየት፤ የእግዚአብሔር ሰንበቶች ሲረከሱ፣ በስሙ የተማለው መሐላ ሲፈርስ፣ ስሙም ሲዋረድ ማየት፤ በእኛ ውስጥ ለእግዚአብሔር ጥቂት ፍቅር እንኳ ቢኖር እነዚህን ነገሮች በልባችን እናኖራቸዋለን። የሎጥ ጻድቅ ነፍስ «በዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ ተጨንቃ» ነበር (2ኛ ጴጥሮስ 2:7)። የሰዶም ኃጢአቶች ነፍሱን እንደሚወጉ ብዙ ጦሮች ነበሩ። በእግዚአብሔር ውርደት ፈጽሞ የማይነኩ ሰዎች እግዚአብሔርን ከመውደድ ምንኛ የራቁ ናቸው? ሰላምና ንግድ ብቻ ካላቸው ምንም ነገር ልባቸውን አይነካውም። ጥንብዝ ብሎ የሰከረ ሰው ሌላው ሰው በአጠገቡ ደሙ እየፈሰሰ ቢሞትም አያስተውልም፤ አይነካውምም፤ እንዲሁ ብዙዎች በብልጽግና ወይን ሰክረው የእግዚአብሔር ክብር ሲቈስልና እውነቶቹ ደም እያፈሰሱ ሲወድቁ አይነኩም። ሰዎች እግዚአብሔርን ቢወዱ ኖሮ ክብሩ ሲጎዳና ሃይማኖት ራሱ ሰማዕት ሲሆን በማየታቸው ባዘኑ ነበር።
6. ስድስተኛው የፍቅር ፍሬ ኃጢአትን መጥላት ነው። እሳት ከማዕድኑ ዝቃጩን ያጠራል። የፍቅር እሳትም ኃጢአትን አጥርቶ ያስወግዳል። «ኤፍሬም፦ ከእንግዲህ ወዲህ ከጣዖታት ጋር ምን አለኝ? ይላል» (ሆሴዕ 14:8)። እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ሊዋጋው ካልሆነ በቀር ከኃጢአት ጋር ምንም ግንኙነት አይኖረውም። ኃጢአት የሚመታው የእግዚአብሔርን ክብር ብቻ ሳይሆን ህልውናውንም ጭምር ነው። የዘውዱን ከሃዲ የሚያስጠጋ ሰው ንጉሡን ይወዳልን? እግዚአብሔር የሚጠላውን የሚወድ ሰው የእግዚአብሔር ወዳጅ ነውን? የእግዚአብሔር ፍቅርና የኃጢአት ፍቅር በአንድነት ሊኖሩ አይችሉም። የልብ ዝንባሌዎች በአንድ ጊዜ ወደ ሁለት ተቃራኒ ነገሮች ሊሄዱ አይችሉም። ሰው ጤናንም መርዝንም በአንድነት ሊወድ እንደማይችል፣ እንዲሁ እግዚአብሔርንም ኃጢአትንም በአንድነት ሊወድ አይችልም። በልቡ ውስጥ የተፈቀደ ስውር ኃጢአት ያለው ሰው ሰማይና ምድር እርስ በርሳቸው እንደሚራራቁ እግዚአብሔርን ከመውደድ የራቀ ነው።
7. ሌላው የፍቅር ፍሬ ለዓለም መሰቀል ነው። እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ለዓለም የሞተ ነው። «እኔ ለዓለም ተሰቅያለሁ» (ገላትያ 6:14)። ለዓለም ክብርና ተድላ ሞቻለሁ። እግዚአብሔርን አጥብቆ የሚወድ ሰው ሌላ ነገርን እምብዛም አይወድም። የእግዚአብሔር ፍቅርና የዓለም የጋለ ፍቅር አብረው አይሄዱም። «ማንም ዓለምን ቢወድ የአብ ፍቅር በእርሱ የለም» (1ኛ ዮሐንስ 2:15)። የሙሴ በትር የግብፃውያንን በትሮች እንደ ዋጠች፣ ለእግዚአብሔር ያለ ፍቅር ሌላውን ፍቅር ሁሉ ይውጣል። ሰው በፀሐይ ውስጥ መኖር ቢችል ኖሮ ምድር ሁሉ ምንኛ ትንሽ ነጥብ በሆነችበት ነበር፤ እንዲሁ የሰው ልብ እግዚአብሔርን በማድነቅና በመውደድ ከዓለም በላይ ከፍ ሲል እነዚህ በታች ያሉ ነገሮች ምንኛ ደሃና ኢምንት ይሆናሉ! በዓይኑ እንደ ምንም ይታዩታል። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን እንደ ወደዱ የሚያሳይ ምልክት ነበር፤ ንብረታቸው ከልባቸው ጋር አልተጣበቀም ነበርና፤ ነገር ግን ገንዘባቸውን «በሐዋርያትም እግር አጠገብ ያኖሩ ነበር» (የሐዋርያት ሥራ 4:35)።
ለእግዚአብሔር ያለህን ፍቅር በዚህ ፈትን። ከዓለም ፈጽሞ ስለማይጠግቡ ሰዎች ምን እናስባለን? ባለጠግነትን ያለ ጥጋብ እየተጠሙ በመጎምጀት የውኃ ጥም በሽታ ተይዘዋል፤ «የምድርን ትቢያ የሚናፍቁ» ናቸው (አሞጽ 2:7)። አግናጥዮስ እንዲህ ይላል፦ ዓለምን ዋጋዋ እጅግ ከበዛው ዕንቁ ስታስበልጥ ለክርስቶስ ስላለህ ፍቅር ፈጽሞ አትናገር፤ ከእግዚአብሔር ይልቅ ወርቃቸውን የሚያከብሩ እንደዚህ ያሉ ብዙዎች የሉምን? የደቡብ ምድር ካላቸው ለሕይወት ውኃ ግድ የላቸውም። ክርስቶስንና በጎ ሕሊናን ለገንዘብ ይሸጣሉ። የሚያብረቀርቅ ትቢያን ከክቡር አምላክ አስበልጠው በዚህ ያህል ዝቅ አድርገው ለሚያቃልሉት እግዚአብሔር መንግሥተ ሰማያትን ይሰጣቸዋልን? ልባችንን በዚህ ያህል እንድናኖርበት በምድር ላይ ምን አለ? በማጉያ መነጽር እንድንመለከታት የሚያደርገን ዲያብሎስ ብቻ ነው። ዓለም እውነተኛ የራሷ ዋጋ የላትም፤ ቀለምና ማታለያ ብቻ ናት።
8. ቀጣዩ የፍቅር ፍሬ ፍርሃት ነው። እግዚአብሔርን በሚፈሩ ሰዎች ዘንድ ፍቅርና ፍርሃት ይሳሳማሉ። ከፍቅር የሚመነጭ ሁለት ዓይነት ፍርሃት አለ።
(ሀ) እርሱን ማስቀየምን መፍራት። ሙሽራይቱ ባሏን ትወዳለች፤ ስለዚህ እርሱን ከምታስቀይም ይልቅ ራሷን መካድ ትመርጣለች። እግዚአብሔርን ይበልጥ በወደድን መጠን መንፈሱን ከማሳዘን ይበልጥ እንፈራለን። «እንግዲህ እኔ ይህን ታላቅ ክፋት አደርግ ዘንድ በእግዚአብሔርስ ፊት ኃጢአትን እሠራ ዘንድ እንዴት እችላለሁ?» (ዘፍጥረት 39:9)። እቴጌ ኤውዶክስያ ዮሐንስ አፈወርቅን (ክሪሶስቶም) ልታሰድደው በዛተች ጊዜ፣ እርሱ፦ ከኃጢአት በቀር ምንም እንደማልፈራ ንገሯት አለ። ክርስቲያንን በቅናት ትኩሳት የሚያግለው፣ በፍርሃትም ብርድ የሚያንቀጠቅጠው፣ እንዲርድና እንዲንቀጠቀጥ፣ እግዚአብሔርንም ወዶ ሊያስቀይም እንዳይደፍር የሚያደርገው ፍቅር የተባረከ ፍቅር ነው።
(ለ) ከቅናት ጋር የተቀላቀለ ፍርሃት። «የዔሊ ልብ ስለ ታቦቱ ተንቀጠቀጠ» (1ኛ ሳሙኤል 4:13)። ልቡ ስለ ሁለቱ ልጆቹ ስለ ሆፍኒና ስለ ፊንሐስ ተንቀጠቀጠ አልተባለም፤ ነገር ግን ታቦቱ ቢወሰድ ክብሩ ይለያልና ልቡ ስለ ታቦቱ ተንቀጠቀጠ። እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው በቤተ ክርስቲያን ላይ ክፉ እንዳይደርስ በፍርሃት የተሞላ ነው። እግዚአብሔርን አለመፍራት (እርሱም የለምጽ መቅሠፍት ነው) እንዳይበዛ፣ ጳጳሳዊነት ሥር እንዳይሰድ፣ እግዚአብሔርም ከሕዝቡ እንዳይለይ ይፈራል። የእግዚአብሔር መገኘት በጸጋ መንገዶቹ ውስጥ የአንድ ሕዝብ ውበትና ብርታት ነው። የእግዚአብሔር መገኘት ከአንድ ሕዝብ ጋር እስካለ ድረስ ያ ሕዝብ ደኅና ነው፤ ለእግዚአብሔር ባለ ፍቅር የምትነድድ ነፍስ ግን የእግዚአብሔር መገኘት የሚታዩ ምልክቶች እንዳይወሰዱ ትፈራለች።
በዚህ የወርቅ መፈተኛ ድንጋይ ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር እንፈትን። ብዙዎች ሰላምና ንግድ እንዳይሄድባቸው ይፈራሉ፤ እግዚአብሔርና ወንጌሉ እንዳይሄዱ ግን አይፈሩም። እነዚህ እግዚአብሔርን የሚወዱ ናቸውን? እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ከምድራዊ በረከቶች ይልቅ መንፈሳዊ በረከቶችን ማጣት ይበልጥ ይፈራል። የጽድቅ ፀሐይ ከአድማሳችን ቢለይ ከጨለማ በቀር ምን ይከተላል? ወንጌል ከሄደ የሙዚቃ መሣሪያ ወይም የመዘምራን ዜማ ምን መጽናናት ሊሰጥ ይችላል? በቀብር ላይ እንደሚነፋ መለከት ወይም በአንድነት እንደሚተኮስ ጥይት ድምፅ አይደለምን?
9. እግዚአብሔርን የምንወድ ከሆንን እግዚአብሔር የሚወደውን እንወዳለን።
(ሀ) የእግዚአብሔርን ቃል እንወዳለን። ዳዊት ቃሉን ስለ ጣፋጭነቱ ከማር አብልጦ (መዝሙር 119:103)፣ ስለ ዋጋውም ከወርቅ አብልጦ አከበረው (መዝሙር 119:72)። የመጽሐፍ ቅዱስ መስመሮች ከወርቅ ማዕድናት ይበልጥ ባለጠጎች ናቸው። ቃሉን ብንወድ ተገቢ ነው፤ ወደ ሰማይ የሚመራን መሪ ኮከብ ነው፤ ዕንቁው የተሰወረበትም እርሻ ነው። ቃሉን የማይወድ፣ ነገር ግን እጅግ ጥብቅ ነው ብሎ የሚያስብና (አንድ አመንዝራ ሰባተኛው ትእዛዝ እንዲቀደድ እንደ ተመኘ) ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ክፍል ተቀድዶ ቢወጣ የሚመኝ ሰው በልቡ ውስጥ ጥቂቷ የፍቅር ብልጭታ እንኳ የለችውም።
(ለ) የእግዚአብሔርን ቀን እንወዳለን። ሰንበትን የምንጠብቅ ብቻ ሳይሆን ሰንበትን እንወዳለን። «ሰንበትንም ደስታ ብትለው» (ኢሳይያስ 58:13)። ሰንበት በመካከላችን የሃይማኖትን ገጽታ የሚያስጠብቀው ነው፤ ይህ ቀን ለጌታ የከበረ ሆኖ መቀደስ አለበት። የእግዚአብሔር ቤት የታላቁ ንጉሥ ቤተ መንግሥት ነው፤ በሰንበት እግዚአብሔር በዚያ በዐይነ ርግብ በኩል ራሱን ይገልጣል። እግዚአብሔርን የምንወድ ከሆንን ቀኑን ከሌሎች ቀኖች ሁሉ አብልጠን እናከብራለን። ይህ ቀን ባይኖር ሳምንቱ ሁሉ ጨለማ በሆነ ነበር፤ በዚህ ቀን መና እጥፍ ሆኖ ይወርዳል። የሰማይ ደጅ የሚከፈትበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው፤ እግዚአብሔርም እንደ ወርቅ ዝናብ ይወርዳል። በዚህ በተባረከ ቀን የጽድቅ ፀሐይ በነፍስ ላይ ትወጣለች። በጸጋ የተሞላ ልብ በእግዚአብሔር ደስ እንዲሰኝበት ተብሎ የተሠራውን ያንን ቀን ምንኛ ያከብራል!
(ሐ) የእግዚአብሔርን ሕግጋት እንወዳለን። በጸጋ የተሞላች ነፍስ የኃጢአት ልቅነቷን ስለሚገታላት በሕጉ ደስ ይላታል። በእግዚአብሔር ሕግ አንዳንድ የተባረኩ ልጓሞች ባይደረጉበት ኖሮ ልብ በኃጢአት ውስጥ ልቅ ሆኖ ለመሮጥ የተዘጋጀ በሆነ ነበር። እግዚአብሔርን የሚወድ ሕጉን ይወዳል — የንስሐን ሕግ፣ ራስን የመካድን ሕግ። ብዙዎች እግዚአብሔርን እንወዳለን ይላሉ፤ ሕግጋቱን ግን ይጠላሉ። «ማሰሪያቸውን እንበጥስ፥ ገመዳቸውንም ከእኛ እንጣል» (መዝሙር 2:3)። የእግዚአብሔር ትእዛዛት ከገመድ ጋር ተመስለዋል፤ ሰዎችን በመልካም ጠባይ ያስራሉ፤ ክፉዎች ግን እነዚህ ገመዶች እጅግ ጥብቅ እንደ ሆኑ ያስባሉ፤ ስለዚህ፦ እንበጥሳቸው ይላሉ። ክርስቶስን እንደ አዳኝ የሚወዱት መስለው ይታያሉ፤ እንደ ንጉሥ ግን ይጠሉታል። ክርስቶስ ስለ ቀንበሩ ይነግረናል (ማቴዎስ 11:29)። ኃጢአተኞች ክርስቶስ በራሳቸው ላይ አክሊል እንዲያኖር ይፈልጋሉ፤ በአንገታቸው ላይ ቀንበር እንዲጭን ግን አይፈልጉም። ያለ ሕግ የሚገዛ ንጉሥ እንግዳ ንጉሥ በሆነ ነበር።
(መ) የእግዚአብሔርን ሥዕል እንወዳለን፤ በቅዱሳን ላይ የሚያበራውን መልኩን እንወዳለን። «ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል» (1ኛ ዮሐንስ 5:1)። ቅዱስን መውደድ ይቻላል፤ ቢሆንም ቅዱስ በመሆኑ ላይወዱት ይቻላል፤ በሌላ ነገር ምክንያት ልንወደው እንችላለን፤ ስለ ብልሃቱ፣ ወይም ተግባቢና ለጋስ ስለ ሆነ። እንስሳ ሰውን ይወዳል፤ ሰው ስለ ሆነ ሳይሆን ስለሚመግበውና መኖ ስለሚሰጠው ነው። ቅዱስን ቅዱስ በመሆኑ መውደድ ግን ለእግዚአብሔር የፍቅር ምልክት ነው። ቅዱስን ስለ ቅድስናው፣ ማለትም ከእግዚአብሔር የሆነ ነገር በእርሱ ውስጥ ስላለ፣ የምንወደው ከሆነ በእነዚህ አራት ሁኔታዎች እንወደዋለን።
(፩) ቅዱስን ደሃ ቢሆንም እንወደዋለን። ወርቅን የሚወድ ሰው በጨርቅ ውስጥ ቢሆንም የወርቅ ቍራጭን ይወዳል፤ እንዲሁ ቅዱስ በቡትቶ ቢሆንም፣ የክርስቶስ የሆነ ነገር በእርሱ ውስጥ ስላለ እንወደዋለን።
(፪) ቅዱስን ብዙ የግል ድካሞች ቢኖሩበትም እንወደዋለን። በዚህ ዓለም ፍጽምና የለም። በአንዳንዶች ችኩል ቍጣ ያይላል፤ በአንዳንዶች ወላዋይነት፤ በአንዳንዶች ደግሞ ከመጠን ያለፈ የዓለም ፍቅር። በዚህ ሕይወት ያለ ቅዱስ በማዕድን ውስጥ እንዳለ ወርቅ ነው፤ የድካም ብዙ ዝቃጭ ተጣብቆበታል፤ ቢሆንም በእርሱ ውስጥ ስላለው ጸጋ እንወደዋለን። ቅዱስ ጠባሳ እንዳለበት ውብ ፊት ነው፤ ጠባሳ ቢኖርበትም የቅድስናን ውብ ፊት እንወዳለን። እጅግ ምርጡ መረግድ እንከን አለበት፤ እጅግ ብሩሃን ከዋክብትም ብልጭ ድርግም ይላሉ፤ ከቅዱሳንም እጅግ ምርጦቹ ድካሞች አሏቸው። አንተ ሌላውን ስለ ድካሙ መውደድ የማትችል፣ እግዚአብሔር አንተን እንዴት እንዲወድህ ትሻለህ?
(፫) ቅዱሳንን በአንዳንድ ታናናሽ ነገሮች ከእኛ ቢለዩም እንወዳቸዋለን። ምናልባት ሌላው ክርስቲያን እንደ አንተ ያህል ብርሃን የለው ይሆናል፤ ይህም በአንዳንድ ነገሮች እንዲሳሳት ያደርገው ይሆናል፤ ወደ ብርሃንህ መድረስ ስላልቻለ ወዲያውኑ ቅዱስነቱን ትገፍፈዋለህን? በመሠረታዊ እውነቶች አንድነት ባለበት በልብ ዝንባሌዎችም አንድነት ሊኖር ይገባል።
(፬) ቅዱሳንን ቢሰደዱም እንወዳቸዋለን። ክቡር ማዕድንን በእቶን ውስጥ ቢሆንም እንወደዋለን። ቅዱስ ጳውሎስ የጌታ የኢየሱስን ማኅተም በሥጋው ተሸከመ (ገላትያ 6:17)። እነዚያ ምልክቶች እንደ ወታደር ጠባሳ የክብር ምልክቶች ነበሩ። ቅዱስን በቀይ ልብስ ሳለ እንደምንወደው በሰንሰለትም ሳለ ልንወደው ይገባል። ክርስቶስን የምንወድ ከሆንን የተሰደዱትን ብልቶቹን እንወዳለን።
እንግዲህ በቅዱሳን ላይ የሚያንጸባርቀውን መልኩን ስንወድ ይህ ለእግዚአብሔር ያለ ፍቅር ከሆነ፣ ወይ! እግዚአብሔርን የሚወዱ ምንኛ ጥቂቶች ይገኛሉ! እግዚአብሔርን የሚመስሉትን የሚጠሉ እግዚአብሔርን ይወዳሉን? በሕዝቡ ላይ የበቀል መንፈስ የሞላባቸው ክርስቶስን ራሱን ይወዳሉን? የባሏን ሥዕል የምትቀድድ ሚስት ባሏን ትወዳለች እንዴት ሊባል ይችላል? በእርግጥ ይሁዳና ዩልያኖስ ገና አልሞቱም፤ መንፈሳቸው አሁንም በዓለም ይኖራል። ዲያብሎስ ከታላቁ የዳኞች ሸንጎ አንዱ ቢሆን ከንጹሐን በቀር በደለኛ ማን ይገኛል! ከቅድስና የሚበልጥ ምን ወንጀል ይኖራል! ክፉዎች ሰዎች ላረፉ ቅዱሳን ታላቅ አክብሮት ያላቸው ይመስላሉ፤ የሞቱትን ቅዱሳን በቅድስና ስም ያከብራሉ፤ ሕያዋኑን ግን ያሳድዳሉ። ሰዎች የሃይማኖት መግለጫው በሚነበብበት ጊዜ ቆመው በእግዚአብሔር እንደሚያምኑ ለዓለም መናገራቸው ከንቱ ነው፤ ከመግለጫው አንቀጾች አንዱን፣ ማለትም የቅዱሳንን ኅብረት ይጸየፋሉና። በእርግጥ ሰው ለሲኦል መብሰሉን የሚያሳይ ከዚህ የሚበልጥ ምልክት የለም፤ ጸጋ ማጣት ብቻ ሳይሆን ጸጋን መጥላት።
10. ሌላው የተባረከ የፍቅር ምልክት ስለ እግዚአብሔር መልካም አሳብ ማሰብ ነው። ወዳጁን የሚወድ ሰው ወዳጁ የሚያደርገውን በበጎ ይተረጒማል። «ፍቅር… በደልን አይቆጥርም» (1ኛ ቆሮንቶስ 13:5)። ክፋት ሁሉን በክፉ ይተረጒማል፤ ፍቅር ሁሉን በበጎ ይተረጒማል። ፍቅር ለመግቦት እጅግ ግሩም ተርጓሚ ነው፤ ክፉ አያስብም። እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ስለ እግዚአብሔር መልካም አስተያየት አለው፤ እግዚአብሔር አጥብቆ ቢያስጨንቀውም ነፍሱ ሁሉን በበጎ ትቀበላለች። በጸጋ የተሞላ መንፈስ ቋንቋ ይህ ነው፦ «አምላኬ ልቤ ምንኛ ደንዳና እንደ ሆነ ያያል፤ ስለዚህ ልቤን ለመስበር አንዱን የመከራ ሽብልቅ ከሌላው በኋላ ያስገባል። ምንኛ በክፉ የሰውነት ፈሳሾች እንደ ተሞላሁ፣ በጎን ውጋት ምን ያህል እንደ ታመምሁ ያውቃል፤ ስለዚህ ሕይወቴን ለማዳን ደሜን ያፈስሳል። ይህ ጽኑ አያያዝ አንዱን ርኵሰት ለመግደል ወይም አንዱን ጸጋ ለማለማመድ ነው። ነፍሴን ለማዳን ሥጋዬን የሚመታ፣ በኃጢአቴም ውስጥ ዝም ብሎ የማይተወኝ እግዚአብሔር ምንኛ ቸር ነው!» እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው እንዲሁ ሁሉን በበጎ ይቀበላል። ፍቅር የእግዚአብሔርን ሥራዎች ሁሉ በቅን ልቡና ይተረጒማል። አንተ እግዚአብሔር ክፉ እንዳደረገብህ በእርሱ ላይ ለማጉረምረም የምትቸኩል፣ ስለዚህ ራስህን ዝቅ አድርግ፤ ለራስህም እንዲህ በል፦ «እግዚአብሔርን ይበልጥ ብወደው ኖሮ ስለ እግዚአብሔር የተሻለ አሳብ ባሰብሁ ነበር።» ስለ ራሳችን መልካም፣ ስለ እግዚአብሔር ግን ክፉ አሳብ እንድናስብ የሚያደርገን ሰይጣን ነው። ፍቅር ሁሉን እጅግ በተሻለው ትርጒም ይቀበላል፤ በደልን አይቆጥርም።
11. ሌላው የፍቅር ፍሬ መታዘዝ ነው። «ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው» (ዮሐንስ 14:21)። ትእዛዛቱን እያቃለልን ክርስቶስን ራሱን እንወዳለን ማለት ከንቱ ነገር ነው። አባቱን ለመታዘዝ እምቢ የሚል ልጅ አባቱን ይወዳልን? እግዚአብሔርን የምንወድ ከሆንን ሥጋንና ደምን በሚቃረኑ ነገሮች እንታዘዘዋለን፤ (ሀ) በአስቸጋሪ ነገሮች፣ እና (ለ) በአደገኛ ነገሮች።
(ሀ) በአስቸጋሪ ነገሮች። ለምሳሌ ኃጢአትን በመግደል። እንደ ልብስ ለእኛ ቅርብ ብቻ ሳይሆኑ እንደ ዓይን ለእኛ ውድ የሆኑ አንዳንድ ኃጢአቶች አሉ። እግዚአብሔርን የምንወድ ከሆንን በአሳብም በተግባርም በእነዚህ ላይ እንነሣለን። ደግሞም ጠላቶቻችንን ይቅር በማለት። እግዚአብሔር ይቅር እንድንል በሞት ቅጣት ያዝዘናል። «ይቅር ተባባሉ» (ኤፌሶን 4:32)። ይህ ከባድ ነው፤ ወንዙን ተቃርኖ እንደ መዋኘት ነው። ቸርነትን ለመርሳት፣ በደልን ግን ለማስታወስ የፈጠንን ነን፤ እግዚአብሔርን የምንወድ ከሆንን ግን በደልን እናልፋለን። እግዚአብሔር ስንት መክሊት ይቅር እንዳለን፣ ከእጃችን ስንት ስድብና ማስቈጣት እንደ ታገሠ በቍም ነገር ስናስብ፣ ይህ የእርሱን አርአያ እንድንከተልና በደልን ከመበቀል ይልቅ ለመቅበር እንድንጥር ያደርገናል።
(ለ) በአደገኛ ነገሮች። እግዚአብሔር ስለ እርሱ መከራ እንድንቀበል ሲጠራን እንታዘዛለን። ፍቅር ክርስቶስን ስለ እኛ መከራ እንዲቀበል አደረገው፤ ፍቅር በመስቀል ላይ ያሰረው ሰንሰለት ነበር፤ እንዲሁ እግዚአብሔርን የምንወድ ከሆንን ስለ እርሱ መከራ ለመቀበል ፈቃደኞች እንሆናለን። ፍቅር እንግዳ ባሕርይ አለው፤ እጅግ የማይታገሥ ጸጋ ነው፤ ደግሞም እጅግ ታጋሽ ጸጋ ነው። በአንድ በኩል እጅግ የማይታገሥ ጸጋ ነው፤ የታወቀ ኃጢአት ንስሐ ሳይገባበት በነፍስ ውስጥ እንዲኖር አይታገሥም፤ በእግዚአብሔር ላይ የሚደርሰውን ስድብና ውርደት አይታገሥም፤ በዚህ መንገድ እጅግ የማይታገሥ ጸጋ ነው። ቢሆንም እጅግ ታጋሽ ጸጋ ነው፤ ስለ ክርስቶስ ብሎ ነቀፋን፣ እስራትንና ወኅኒን ይታገሣል። «ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ተሰናድቼአለሁ እንጂ ለእስራት ብቻ አይደለም» (የሐዋርያት ሥራ 21:13)። እያንዳንዱ ክርስቲያን ሰማዕት አለመሆኑ እውነት ነው፤ ነገር ግን የሰማዕትነት መንፈስ በውስጡ አለ። እንደ ጳውሎስ፦ «ለእስራት ተሰናድቼአለሁ» ይላል፤ እግዚአብሔር ቢጠራው መከራን ለመቀበል የተዘጋጀ ልቡና አለው። ፍቅር ሰዎችን ከራሳቸው ኃይል በላይ ያወጣቸዋል። ተርቱሊያን አሕዛብ ለአገራቸው ካላቸው ፍቅር የተነሣ ምን ያህል መከራ እንደ ተቀበሉ ያስተውላል። የተፈጥሮ ምንጭ ይህን ያህል ከፍ ብሎ ከፈለቀ፣ በእርግጥ ጸጋ ከዚህ ይበልጥ ከፍ ይላል። ለአገር ያለ ፍቅር ሰዎችን መከራ እንዲቀበሉ ካደረገ፣ ለክርስቶስ ያለ ፍቅርማ ይልቁን እንዴት! «ፍቅር… በሁሉ ይጸናል» (1ኛ ቆሮንቶስ 13:7)። ባስልዮስ በእሳት እንድትቃጠል ስለ ተፈረደባት አንዲት ድንግል ይናገራል፤ ለጣዖቱ ብትሰግድ ሕይወቷና ንብረቷ እንደሚመለስላት ቢነገራትም እርሷ፦ «ሕይወትም ገንዘብም ይሂዱ፤ ክርስቶስ ሆይ፥ እንኳን ደህና መጣህ» ብላ መለሰች። አግናጥዮስ፦ «የእግዚአብሔር ንጹሕ ስንዴ እሆን ዘንድ በአራዊት ጥርስ ልፈጭ» ማለቱ ታላቅና በቅናት የተሞላ ንግግር ነበር። መለኮታዊ ፍቅር የጥንቶቹን ቅዱሳን ከሕይወት ፍቅርና ከሞት ፍርሃት በላይ እንዴት ከፍ አደረጋቸው! ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወገረ፤ ቅዱስ ሉቃስ በወይራ ዛፍ ላይ ተሰቀለ፤ ቅዱስ ጴጥሮስ ራሱ ወደ ታች ሆኖ በኢየሩሳሌም ተሰቀለ። እነዚህ መለኮታዊ ጀግኖች በፍርሃታቸው የእግዚአብሔርን ስም ከማስነቀፍ ይልቅ ራሳቸው መከራ ለመቀበል ፈቃደኞች ነበሩ። ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ የለበሰውን ሰንሰለት ምንኛ ከፍ አድርጎ ተመለከተው! ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚለው፣ በጌጣጌጦቿ እንደምትኰራ ሴት በእርሱ ተመካ። ቅዱሱ አግናጥዮስም እግር ብረቱን እንደ አልማዝ አምባር ለበሰው። «መዳንን ሳይቀበሉ» (ዕብራውያን 11:35)። በኃጢአት ውል ከወኅኒ ለመውጣት እምቢ አሉ፤ ንጽሕናቸውን ከነጻነታቸው አስበለጡ።
ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር በዚህ እንፈትን። የሰማዕትነት መንፈስ አለንን? ብዙዎች እግዚአብሔርን እንወዳለን ይላሉ፤ ነገር ግን ይህ በምን ይታያል? ስለ እርሱ ብለው ትንሿን ምቾት እንኳ አይተዉም፤ ትንሹንም መስቀል አይሸከሙም። ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «በጣም እወዳችኋለሁ፤ ለእኔ ውዶች ናችሁ፤ ነገር ግን መከራ መቀበል አልችልም፤ ሕይወቴን ስለ እናንተ አሳልፌ መስጠት አልችልም» ብሎ ቢለን ኖሮ፣ ፍቅሩን እጅግ በተጠራጠርን ነበር፤ እኛስ እንወደዋለን እያልን ስለ እርሱ ምንም የማንታገሥ ስንሆን ክርስቶስ ቢጠረጥረን አይገባውምን?
12. እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው በሌሎች ዓይን የከበረ ሆኖ እንዲታይ ይጥራል። በፍቅር ያሉ ሰዎች የሚወዷቸውን ሰዎች መወደድ ያወድሳሉ፤ ይገልጣሉም። እግዚአብሔርን የምንወድ ከሆንን ዝናውና ክብሩ ከፍ እንዲል፣ ሌሎችም እርሱን እንዲወዱ ለማነሣሣት ታላቅነቱን እናወራለን። ፍቅር ዝም ማለት አይችልም፤ የእግዚአብሔርን ጸጋ በነጻ መሰጠት፣ የፍቅሩን ልዕልና፣ የመንግሥቱንም ክብር የምናውጅ እንደ ብዙ መለከቶች እንሆናለን። ፍቅር እንደ እሳት ነው፤ በልብ ውስጥ በሚነድድበት ጊዜ በከንፈር በኩል ገንፍሎ ይወጣል። የእግዚአብሔርን ምስጋና በመግለጥ አንደበተ ርቱዕ ይሆናል፤ ፍቅር መውጫ ሊያገኝ ይገባዋል።
13. ሌላው የፍቅር ፍሬ የክርስቶስን መገለጥ መናፈቅ ነው። «ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም» (2ኛ ጢሞቴዎስ 4:8)። ፍቅር አንድነትን ይሻል፤ አርስጣጣሊስ ምክንያቱን ሲሰጥ ደስታ ከአንድነት ስለሚፈስ ነው ይላል። ከክርስቶስ ጋር ያለን አንድነት በክብር ፍጹም በሚሆንበት ጊዜ ደስታችን ሙሉ ይሆናል። ክርስቶስን የሚወድ መገለጡን ይወዳል። የክርስቶስ መገለጥ ለቅዱሳን አስደሳች መገለጥ ይሆናል። አሁን እንደ ጠበቃ ስለ እኛ በሚታይበት ጊዜ (ዕብራውያን 9:24) መገለጡ እጅግ የሚያጽናና ነው። ያኛው መገለጥ ግን እንደ ሙሽራችን ስለ እኛ በሚገለጥበት ጊዜ ወሰን በሌለው መጠን ይበልጥ የሚያጽናና ይሆናል። በዚያ ቀን ሁለት ዕንቁዎችን ይሰጠናል። ፍቅሩን፤ ከመነገሩ ይልቅ ቢሰማ የሚሻል እጅግ ታላቅና አስደናቂ ፍቅር። መልኩንም። «ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን» (1ኛ ዮሐንስ 3:2)። ከእነዚህ ከሁለቱ፣ ከፍቅርና ከመልክ፣ ወሰን የሌለው ደስታ ወደ ነፍስ ይፈስሳል። እንግዲያስ ክርስቶስን የሚወድ መገለጡን ቢናፍቅ አያስደንቅም። «መንፈሱና ሙሽራይቱም። ና ይላሉ… አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና» (ራእይ 22:17, 20)። ለክርስቶስ ያለንን ፍቅር በዚህ እንፈትን። በራሱ ላይ የፈረደ ክፉ ሰው የክርስቶስን መገለጥ ይፈራል፤ ፈጽሞ እንዳይገለጥም ይመኛል፤ ክርስቶስን የሚወዱ ግን በደመና ስለ መምጣቱ ሲያስቡ ደስ ይላቸዋል። ያን ጊዜ ከኃጢአታቸውና ከፍርሃታቸው ሁሉ ይድናሉ፤ በሰዎችና በመላእክት ፊት ነጻ ይወጣሉ፤ ለዘላለምም ወደ እግዚአብሔር ገነት ይፈልሳሉ።
14. ፍቅር እጅግ ዝቅተኛ ወደ ሆኑ አገልግሎቶች ዝቅ እንድንል ያደርገናል። ፍቅር ትሑት ጸጋ ነው፤ በክብር ተንጐራዶ አይሄድም፤ በእጆቹ ይዳኻል፤ ለክርስቶስ የሚጠቅምበትን ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ዝቅ ይላል፤ ይገዛልም። ይህንም በአርማትያሱ ዮሴፍና በኒቆዲሞስ እናያለን፤ ሁለቱም የተከበሩ ሰዎች ነበሩ፤ ቢሆንም አንዱ የክርስቶስን ሥጋ በገዛ እጆቹ አወረደ፤ ሌላውም በጣፋጭ ሽቱ አዘጋጀው። እንደ እነርሱ ያለ ማዕረግ ላላቸው ሰዎች በዚያ አገልግሎት መሠማራት ብዙ ሊመስል ይችል ነበር፤ ፍቅር ግን እንዲያደርጉት አደረጋቸው። እግዚአብሔርን የምንወድ ከሆንን ለክርስቶስ ብልቶች የምንረዳበትን ማንኛውንም ሥራ ለእኛ እጅግ ዝቅተኛ ነው ብለን አናስብም። ፍቅር ተጸያፊ አይደለም፤ የታመሙትን ይጐበኛል፤ ድሆችን ይረዳል፤ የቅዱሳንን ቍስል ያጥባል። ልጇን የምትወድ እናት አትጠየፍም፤ አትቀናጣምም፤ ሌሎች ለማድረግ የሚንቁትን ነገር ለልጇ ታደርጋለች። እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ለክርስቶስና ለብልቶቹ እጅግ ዝቅተኛ የሆነውን የፍቅር አገልግሎት ለማድረግ ራሱን ዝቅ ያደርጋል።
ለእግዚአብሔር ያለ ፍቅር ፍሬዎች እነዚህ ናቸው። ለተፈጥሮአቸው እንግዳ የሆኑት እነዚህ ፍሬዎች በነፍሳቸው ውስጥ ሲያድጉ የሚያገኙ ብፁዓን ናቸው።
ምዕራፍ 7 ተጠናቋል
ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር መፈተኛዎች