አንድነትና ኅብረት
መቅድም

ምዕራፍ 1 · 1 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ

መቅድም

ይህ ትንሽ መጽሐፍ ዓላማው ቀናተኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ወደ መልካሙ እረኛ ለምለም መስክ፣ ከዚያም ወደ ንጉሡ የግብዣ ቤት፣ ከዚያም ወደ ወይኑ ቦታ አገልግሎት መምራት ነው፤ ሃድሰን ቴለር ለቤተ ክርስቲያን ትቶአቸው ካለፋቸው ጸንተው የሚኖሩ ቅርሶች አንዱ ነው። ከቅዱሱ ዘንድ በግልጥ በተሰጠው ቅባት ኃይል፣ በምሳሌና በሥዕላዊ አነጋገር የመኃልየ መኃልይ ርእሰ ጉዳይ የሆነውን፣ አማኙ ከጌታ ጋር ያለውን የግል አንድነት ጥልቅ እውነት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እጅግ ቀላል በሆነ ቋንቋ ለመግለጥ ተችሎታል። ይህንም በማድረጉ፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት መካከል በአብዛኛው ቸል ለሚባለውና በተሳሳተ መንገድ ለሚረዳው ለአንዱ የማይሳሳት መመሪያ አበርክቶአል። ትርጉሙን በአንድ ጊዜ የሚሰውሩትና የሚገልጡት የቋንቋው ብልጽግናና የምሳሌዎቹ ብዛት ግራ አጋብቶአቸው፦ «የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?» ያሉ ስንቶች ናቸው! እነዚህ ገጾች እንደነዚህ ያሉትን ሁሉ ከመርዳትና ከመባረክ እንደማይቀሩ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

ለሚያውቁት ሰዎች፣ የሃድሰን ቴለር ሕይወት ራሱ የዚህን ትንሽ መጽሐፍ ዋጋ የሚያጐላ ነበር። በዚህ ያብራራውን በሕይወቱም አሳይቶአልና። ቃሎቹ ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆን እንደሚቻልና ብፁዕ እንደ ሆነ የሚያመለክቱ ከሆነ፣ ሕይወቱ በሙሉ ይህንኑ በእውነተኛ ተሞክሮ አውጆአል። «ለሌላው፥ ከሙታን ለተነሣው፥ ለእርሱ» እንደ ሆነ ሰው ኖረ፤ ከዚያም አንድነት የተነሣ «ለእግዚአብሔር ፍሬ» አፈራ። እርሱ ማንነቱ በዚህ ለተናገረው ነገር ከቶ ሊጋነን የማይችል ትርጉምና ማረጋገጫ ሰጥቶታል። ከማይታየው ጌታ ጋር ካለው የኅብረት ቅርበት ጋር በቀጥታ የተያያዘውን ይህን ነገር አንብበው ምሥጢራዊና ለተግባር የማይሆን ብለው የሚጥሉት ሰዎች መኖራቸው አይቀርም። እንደነዚህ ያሉትን ግን የእነዚህ ገጾች ጸሐፊ የቻይና የውስጥ ሚስዮንን የመሠረተ ሰው መሆኑን ላሳስባቸው እደፍራለሁ! እርሱ ስለ ውዱ ያየውን ራእይ ዕድሜ ልኩን በትጋት ወደ ተሞላ አገልግሎት ለወጠው፤ በዚህም በዘመናችን አቻ በሌለው ሕይወቱ ዓመታት ሁሉ ያ ራእይ ሳይደበዝዝ እንዲኖር አደረገ።

የሚከተሉት አጫጭር ምዕራፎች በእውነት የሚመሰገኑበት ይህ ነው። ከተሞክሮ ተጣርቶ የወጣውን የምሥራች ያውጃሉ፤ በዚህ በታጠረው የእግዚአብሔር ቃል ክፍል ውስጥ ቢያንስ አንድ መንገድ ያበጃሉ፤ ይህም መንገድ በእርሱ የሚሄዱትን ብዙዎች ወደ አማኑኤል ምድር ደስታ ያደርሳቸዋል።

ጄ. ስቱዋርት ሆልደን

የቅዱስ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን፣

ፖርትማን አደባባይ፣ ምዕራብ ለንደን።

ጁን 1 ቀን 1914።

ምዕራፍ 1 ተጠናቋል

መቅድም

ገጽ 1 / 1 · 1 ደቂቃ በምዕራፉ ቀርቷል
ቀጣይ