ምዕራፍ 3 · 28 ደቂቃ ንባብ · 36 ደቂቃ ማዳመጥ
ስለ ወደቁት
ማብራሪያ።—ደራሲያችን ስለ ቤተ ክርስቲያን ያልተጠበቀ ሰላም፥ ስለ እምነት ምስክሮችና በእምነት ጸንተው ስለ ቆሙት ሰዎች ጽናት በሰፊው ከተናገረ በኋላ፥ ቀጥሎም በታላቅ ኀዘን የወደቁትን ውድቀት አመልክቶ የአለፈውን ስደት ምክንያቶች፥ ማለትም የሥርዓትን ቸልተኝነትና የምእመናንን ኃጢአት ከገለጠ በኋላ፥ የወደቁትን አጥብቆ ይወቅሳቸዋል፤ ጠላት ሲያስፈራራቸው በመጀመሪያዎቹ ቃላት ለጣዖታት ሠዉ እንጂ እንደ ክርስቶስ ምክር ፈቀቅ አላሉምና። በመጨረሻም አንባቢዎቹን ከኖቫጥያኖሳውያን እንዲርቁ ያስጠነቅቃል፤ ኑፋቄያቸውንም በብዙ መጻሕፍት ይረታል።
1. እነሆ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞች፥ ለቤተ ክርስቲያን ሰላም ተመለሰላት፤ ምንም እንኳ ይህ ቀድሞ ለማያምኑ ሰዎች አስቸጋሪ፥ ለከሐዲዎችም የማይቻል መስሎ ቢታይ፥ ደኅንነታችን በመለኮታዊ ርዳታና ብድራት እንደ ገና ጸንቶአል። ልቡናችን እንደ ገና ወደ ደስታ ይመለሳል፤ የመከራው ዘመንና ደመናው ተበትኖ ጸጥታና ብሩህነት ዳግመኛ አበሩ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ሊሰጥ ይገባል፤ ቸርነቱና ስጦታዎቹም በምስጋና ሊከበሩ ይገባል፤ ምንም እንኳ በስደት ዘመን እንኳ ቢሆን ድምፃችን ማመስገንን ፈጽሞ ባያቋርጥም። ጌታን በፍጹም ልባችን፥ በፍጹም ነፍሳችንና በፍጹም ኃይላችን የምንወድደውን እኛን በረከቱንና ምስጋናውን ሁልጊዜና በየስፍራው በክብር ከመናገር ይከለክለን ዘንድ ጠላት እንኳ ይህን ያህል ኃይል የለውምና። በሁሉም ሰው ጸሎት አጥብቆ የተናፈቀው ያ ቀን እነሆ ደረሰ፤ ከረጅም ሌሊት አስፈሪና አስጸያፊ ጨለማም በኋላ ዓለም በጌታ ብርሃን ተበርቶ እንደ ገና አበራ።
2. በመልካም ስም ክብር ያጌጡትን፥ በበጎነትና በእምነትም ምስጋና የከበሩትን የእምነት ምስክሮች በደስተኛ ፊት እንመለከታቸዋለን፤ በቅዱስ አምኃ ተጣብቀን ለረጅም ጊዜ የናፈቅናቸውን በማይጠግብ ጉጉት እናቅፋቸዋለን። ለወህኒ መከራ ተዘጋጅተው ሞትንም ለመታገሥ ታጥቀው፥ በብርቱ ጦርነት የአስጨናቂውን ስደት አስፈሪ ሁከት የሰበሩ፥ ነጭ የለበሱ የክርስቶስ ወታደሮች ሠራዊት እነሆ በዚህ አሉ። እናንተ ዓለምን በጀግንነት ተቃወማችሁ፤ በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ትዕይንት ሆናችሁ፤ ከኋላችሁ ለሚከተሏችሁ ወንድሞቻችሁ ምሳሌ ሆናችሁ። ያ ሃይማኖተኛ ድምፅ አንድ ጊዜ እንዳመነበት የመሰከረለትን የክርስቶስን ስም ጠራ፤ ለመለኮታዊ ሥራ ብቻ የለመዱት እነዚያ የከበሩ እጆች የረከሰውን መሥዋዕት ተቃወሙ፤ ከጌታ ሥጋና ደም በኋላ በሰማያዊ ምግብ የተቀደሱት እነዚያ ከንፈሮች የረከሰውን መነካካትና የጣዖታትን ትራፊ እምቢ አሉ። የሠዉት ሰዎች ምርኮኛ ራሶች በዚያ ከተሸፈኑበት ከኃጢአተኛውና ከክፉው መሸፈኛ ራሳችሁ ነጻ ሆኖ ቀረ፤ በእግዚአብሔር ምልክት ንጹሕ የሆነው ግንባራችሁ የዲያብሎስን አክሊል ሊሸከም አልቻለም፥ ለጌታ አክሊል ግን ራሱን ጠበቀ። እናታችሁ ቤተ ክርስቲያን ከጦርነት ስትመለሱ በምን ያህል ደስታ በእቅፍዋ ትቀበላችኋለች! በአንድነት ተሰልፋችሁ ከወደቀው ጠላት የተገኘውን ዋንጫ ተሸክማችሁ ትገቡ ዘንድ በምን ያህል ሐሴትና ደስታ ደጆችዋን ትከፍታለች! ከድል አድራጊዎቹ ወንዶች ጋር ከዓለም ጋር ሲታገሉ ጾታቸውንም ያሸነፉ ሴቶች ደግሞ ይመጣሉ፤ የጦርነታቸውን እጥፍ ክብር ይዘው ደናግልም ይመጣሉ፥ በበጎነታቸውም ዕድሜያቸውን የሚያልፉ ብላቴኖችም ይመጣሉ። ደግሞም የቀሩት በጽናት የቆሙት ብዙ ሕዝብ ክብራችሁን ይከተላሉ፤ ከእናንተ ጋር እጅግ በቀረበና በተጣመረ በሚመስል የምስጋና ምልክትም ፍለጋችሁን ይሸኛሉ። በእነርሱ ዘንድም ደግሞ ያው የልብ ቅንነት፥ ያው የጸናች እምነት ጤንነት አለ። በማይናወጡት በሰማያዊ ትእዛዛት ሥሮች ላይ ተደግፈው በወንጌላዊ ትውፊትም በርትተው ስለ ነበር፥ የታዘዘው ግዞት፥ የተዘጋጀው ሥቃይ፥ የንብረት መጥፋትና የሥጋ ቅጣት አላስፈራቸውም። እምነታቸውን የሚፈትኑበት ቀኖች አስቀድመው ተወስነው ነበር፤ ነገር ግን ዓለምን መካዱን የሚያስብ የዓለምን ቀጠሮ ቀን አያውቅም፥ ከእግዚአብሔርም ዘላለማዊነትን ተስፋ የሚያደርግ ከእንግዲህ የምድርን ዘመናት አይቈጥርም።
3. የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፥ ማንም ይህን ክብር አያሳንስ፤ ማንም በክፉ ነቀፋ የቆሙትን ሰዎች ያልረከሰ ጽናት አያጕድል። ለመካድ የተወሰነው ቀን ባለፈ ጊዜ፥ በዚያ ጊዜ ውስጥ ክርስቲያን አይደለሁም ብሎ ያልተናገረ ሁሉ ክርስቲያን መሆኑን መሰከረ። በአሕዛብ እጅ ግፍ ሥር ጌታን መመስከር የድል የመጀመሪያው ማዕረግ ነው። በጥንቃቄ ፈቀቅ ብሎ መሸሸግና ለጌታ መጠበቅ ወደ ክብር የሚያደርስ ሁለተኛው ደረጃ ነው። የመጀመሪያው በሕዝብ ፊት በግልጥ የሚደረግ፥ ሁለተኛው ግን በስውር የሚደረግ ምስክርነት ነው። የመጀመሪያው የዚህን ዓለም ዳኛ ያሸንፋል፤ ሁለተኛው እግዚአብሔር ዳኛው በመሆኑ ረክቶ በልብ ቅንነት ንጹሕ ሕሊናን ይጠብቃል። በመጀመሪያው የፈጠነ ብርታት አለ፤ በሁለተኛው ጥንቃቄው ይበልጥ የተጠበቀ ነው። የመጀመሪያው ሰዓቱ በቀረበ ጊዜ የበሰለ ሆኖ ተገኘ፤ ሁለተኛው ግን ምናልባት ገና ዘገየ ይሆናል፤ እርሱ ርስቱን ትቶ ለጊዜው ፈቀቅ አለ፥ ሊክድ ስላልፈለገ፥ እርሱም ቢያዝ ኖሮ በእርግጥ ይመሰክር ነበርና።
4. እነዚህን የሰማዕታት ሰማያዊ አክሊሎች፥ እነዚህን የከበሩ መንፈሳዊ ምስክርነቶች፥ እነዚህን የቆሙትን ወንድሞች እጅግ ታላላቅና የከበሩ በጎነቶች አንድ የኀዘን ምክንያት ያጨልማቸዋል፤ ይኸውም የጠላት ግፍ ከገዛ አንጀታችን ከፍሎ ቀድዶ በራሱ ጭካኔ ጥፋት ውስጥ መጣሉ ነው። የተወደዳችሁ ወንድሞች፥ በዚህ ነገር እኔ ምን ላድርግ? በልዩ ልዩ የስሜት ማዕበል እየተወዛወዝሁ ምን ወይም እንዴት ልናገር? የሥጋችን ቍስል የሚለቀስበትን፥ በአንድ ወቅት ብዙ የነበረው ሕዝብ ልዩ ልዩ ጥፋት የሚያዝንበትን ኀዘን ለመግለጥ ከቃላት ይልቅ እንባ ያስፈልገኛል። በወዳጆቹ ልዩ ልዩ ፍርስራሽ መካከል፥ በውርደትም ሁሉ በተበላሸው በሚያሳዝነው ቅሪት መካከል ቆሞ ዓይኑን ደረቅ አድርጎ ሊጠብቅ የሚችል፥ የኀዘኑም ፍንዳታ ሲመጣ ልቅሶውን ከቃላት ይልቅ በእንባ የማይገልጥ፥ ልቡ እንደዚህ የደነደነ ወይም ጨካኝ፥ የወንድማማችን ፍቅር እንደዚህ የሚረሳ ማን ነው? ወንድሞች ሆይ፥ አዝናለሁ፥ ከእናንተ ጋር አዝናለሁ፤ የራሴ ቅንነትና የግሌ ጤንነት ኀዘኔን ለማስታገሥ አያታልለኝም፤ በመንጋው ቍስል ይበልጥ የሚቈስለው እረኛው ነውና። ደረቴን ከእያንዳንዱ ጋር አጣምራለሁ፥ በከባዱም የኀዘንና የልቅሶ ሸክም እካፈላለሁ። ከሚያለቅሱት ሁሉ ጋር አለቅሳለሁ፥ ከሚያነቡት ጋር አነባለሁ፥ ከወደቁትም ጋር እንደ ወደቅሁ እቈጥራለሁ። ብልቶቼ በዚያው በሚቈጣው ጠላት ፍላጻ ተመትተዋል፤ ጨካኝ ሰይፎቻቸው አንጀቴን ወጉ፤ በወደቁት ወንድሞቼ መካከል ልቡናዬ ከስደት ወረራ ሳይነካና ነጻ ሆኖ ሊቀር አልቻለም፤ የወንድማማች ርኅራኄ እኔንም ደግሞ ከእነርሱ ጋር ጣለኝ።
5. ነገር ግን፥ የተወደዳችሁ ወንድሞች፥ የእውነት ጉዳይ ሊታሰብ ይገባል፤ የአስፈሪው ስደት ድቅድቅ ጨለማ መለኮታዊ ትእዛዛት የሚታዩበት ብርሃንና ማብራት እስከማይቀር ድረስ ልቡናንና ስሜትን ሊያሳውር አይገባም። የመከራው ምክንያት በግልጥ ከታወቀ ለቍስሉ የሚሆን መድኃኒት ወዲያው ይገኛል። ጌታ የገዛ ቤተ ሰቡ ይፈተን ዘንድ ወደደ፤ ረጅም ሰላምም በመለኮት የተሰጠንን ሥርዓት አበላሽቶ ስለ ነበረ፥ ሰማያዊው ተግሣጽ እየደከመች የነበረችውን፥ ተኝታ ነበር ለማለት የቀረበችውን እምነታችንን አነቃት፤ ስለ ኃጢአታችንም ከዚህ እጅግ የበለጠ ቅጣት የሚገባን ቢሆንም፥ እጅግ መሐሪ የሆነው ጌታ የሆነው ሁሉ ከስደት ይልቅ ፈተና መስሎ እንዲታይ ሁሉን ነገር እንዲሁ አለዘበ።
6. እያንዳንዱ ሰው የገዛ ንብረቱን ለማብዛት ይመኝ ነበር፤ አማኞች በሐዋርያት ዘመን አስቀድመው ያደረጉትን ወይም ሁልጊዜ ሊያደርጉ የሚገባቸውን ረስተው፥ በማይጠግብ የስስት ግለት ራሳቸውን ለሀብታቸው ብዛት ሰጡ። በካህናት ዘንድ የሃይማኖት ትጋት አልነበረም፤ በአገልጋዮች ዘንድ ጤናማ እምነት አልነበረም፤ በሥራቸው ምሕረት አልነበረም፤ በጠባያቸውም ሥርዓት አልነበረም። በወንዶች ዘንድ ጢማቸው ተበላሸ፤ በሴቶች ዘንድ የፊታቸው መልክ በቀለም ተቀባ፤ ዓይኖች የእግዚአብሔር እጅ ከሠራቸው ተለውጠው ተኳሉ፤ ጠጕራቸውም በሐሰት ቀለም ተነከረ። የየዋሃንን ልብ ለማታለል ተንኰለኛ ሸንገላ፥ ወንድሞችን ለማጥመድ ረቂቅ ዘዴ ይጠቀሙ ነበር። ከማያምኑ ጋር በጋብቻ ማሰሪያ ተጣመሩ፤ የክርስቶስን ብልቶች ለአሕዛብ አመነዘሩ። በችኮላ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ይልቅ በሐሰት ይምሉ ነበር፤ በላያቸው የተሾሙትን በትዕቢት ተነፍተው ይንቁ ነበር፤ በመርዘኛ አንደበት እርስ በርሳቸው ይሳደቡ ነበር፤ በግትር ጥላቻም እርስ በርሳቸው ይጣሉ ነበር። ለሌሎች ምክርንና ምሳሌን ሊሰጡ የሚገባቸው ብዙ ጳጳሳት መለኮታዊ አደራቸውን ንቀው የዓለም ንግድ ወኪሎች ሆኑ፤ መንበራቸውን ተዉ፥ ሕዝባቸውን ጣሉ፥ በባዕድ አውራጃዎች ተንከራተቱ፥ ትርፍ የሚያስገኝ ሸቀጥ ለማግኘት ገበያዎችን አሰሱ፤ በዚያው ጊዜ ወንድሞች ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይራቡ ነበር። ገንዘብን በክምር ሊያከማቹ ፈለጉ፤ በተንኰል ማታለል ርስቶችን ቀሙ፤ አራጣን በማብዛት ትርፋቸውን አበዙ። መለኮታዊው ተግሣጽ አስቀድሞ። «ሕጌን ቢተዉ በፍርዴም ባይሄዱ፥ ሥርዓቴን ቢያረክሱ ትእዛዜንም ባይጠብቁ፥ በደላቸውን በበትር ኃጢአታቸውንም በመቅሠፍት እጐበኛለሁ» ብሎ ያስጠነቀቀን ሲሆን፥ እንደ እኛ ያሉ ስለ እንዲህ ያለ ኃጢአት የማይገባቸው መከራ ምንድር ነው?
7. እነዚህ ነገሮች አስቀድመው ተነግረውን በትንቢትም ተነግረውልን ነበር። እኛ ግን ከእኛ የሚፈለገውን ሕግና መታዘዝ ረስተን፥ የጌታን ትእዛዛት ስንንቅ ለኃጢአታችን መታረምና ለእምነታችን መፈተን ወደ ከበደ ወደ መራራ መድኃኒት እስክንደርስ ድረስ በኃጢአታችን እንዲህ አደረግን። ይህን እርማታችንንና መለኮታዊ ፈተናችንን በትዕግሥትና በጀግንነት እንቀበል ዘንድ በመጨረሻ እንኳ ወደ ጌታ ፍርሃት አልተመለስንም። ወዲያው በሚያስፈራራው ጠላት የመጀመሪያ ቃላት እጅግ ብዙዎቹ ወንድሞች እምነታቸውን አሳልፈው ሰጡ፤ በስደት ጥቃት ሳይሆን በፈቃዳቸው ውድቀት ራሳቸውን ጣሉ። እባካችሁ፥ ያልታወቀና ያልተጠበቀ ነገር እንደ ተከሰተ ያህል የክርስቶስ ቃል ኪዳን በግድየለሽ ችኮላ ይፈታ ዘንድ ምን ያልተሰማ ነገር፥ ምን አዲስ ነገር ተደረገ? ቀድሞ ነቢያት፥ ከዚያም በኋላ ደግሞ ሐዋርያት ስለ እነዚህ ነገሮች አልተናገሩምን? እነርሱ መንፈስ ቅዱስ ሞልቶባቸው የጻድቃንን መከራ የአሕዛብንም ግፍ ሁልጊዜ አስቀድመው አልተናገሩምን? እምነታችንን ሁልጊዜ የሚያስታጥቅ የእግዚአብሔርንም ባሪያዎች ከሰማይ በሆነ ድምፅ የሚያበረታ ቅዱሱ መጽሐፍ። «ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ» አይልምን? ደግሞም። «ጣቶቻቸው ለሠሩት ሰገዱ፤ ታናሹ ሰው አጐነበሰ፥ ታላቁም ሰው ራሱን አዋረደ፤ ይቅርም አልላቸውም» ሲል የመለኮታዊውን ቍጣ መዓት አያሳይምን? የቅጣትንስ ፍርሃት አስቀድሞ አያስጠነቅቅምን? ደግሞም እግዚአብሔር ይናገራል እንዲህም ይላል። «ከእግዚአብሔር ብቻ በቀር ለአማልክት የሚሠዋ ፈጽሞ ይጥፋ።» ከዚያም በኋላ በወንጌል ደግሞ በቃሉ የሚያስተምር በሥራውም የሚፈጽም ጌታ፥ ሊደረግ የሚገባውን እያስተማረ ያስተማረውንም ሁሉ እያደረገ፥ አሁን የሚደረገውንና ወደ ፊት የሚደረገውን ሁሉ አስቀድሞ አላስጠነቀቀንምን? ለሚክዱት የዘላለም ቅጣትን፥ ለሚመሰክሩለትም የመዳን ዋጋን አስቀድሞ አልወሰነምን?
8. ከአንዳንዶች ዘንድ—ወዮ መከራ!—እነዚህ ሁሉ ወድቀዋል ከትዝታም አልፈዋል። ወደ ላይ ከመውጣታቸው በፊት ሊያዙ፥ ከመካዳቸውም በፊት ሊጠየቁ እንኳ አልጠበቁም። ብዙዎች ገና ከጦርነቱ በፊት ተሸነፉ፥ ከጥቃቱም በፊት ተጣሉ። ለጣዖታት ሳይወዱ የሠዉ መስለው ታዩ ተብሎ እንዲነገርላቸው እንኳ አላስቀሩም። በገዛ ፈቃዳቸው ወደ አደባባዩ ሮጡ፤ ቀድሞ የተመኙት ይመስል፥ ሁልጊዜም የፈለጉትን አሁን የተሰጠ አጋጣሚ የሚያቅፉ ይመስል በነጻ ወደ ሞት ቸኮሉ። በዚያን ጊዜ ምሽት እየገፋ ሲሄድ ስንቶቹ በሹማምንቱ ቀጠሮ ተሰጣቸው! ስንቶቹስ ደግሞ ጥፋታቸው እንዳይዘገይ እንኳ አጥብቀው ለመኑ! እንዲህ ያለው ሰው ታዲያ ምን ዓይነት ግፍ ለምክንያት ሊያቀርብ ይችላል? የገዛ ጥፋቱን ለማምጣት ይልቁንም ኃይል የተጠቀመው ራሱ ሲሆን ወንጀሉን እንዴት ሊያነጻ ይችላል? በፈቃዳቸው ወደ ካፒቶል በመጡ ጊዜ፥—ለአስፈሪው ክፋት ለመታዘዝ በነጻ በቀረቡ ጊዜ፥—እርምጃቸው አልተንገዳገደምን? ዓይናቸው አልጨለመምን፥ ልባቸው አልተንቀጠቀጠምን፥ ክንዳቸውስ ያለ ኃይል አልወደቀምን? ስሜታቸው አልደከመምን፥ ምላሳቸው በአፋቸው አልተጣበቀምን፥ ንግግራቸውስ አልላላምን? የእግዚአብሔር ባሪያ ዲያብሎስንና ዓለምን ከዚህ አስቀድሞ ክዶ ሳለ በዚያ ቆሞ ተናግሮ ክርስቶስን ሊክድ ይችላልን? ሊጠፋ የቀረበበት ያ መሠዊያ ለእርሱ የሬሳ ማቃጠያ እሳት አልሆነበትምን? የሕይወቱ ቀብርና መቃብር ይመስል ሲጤስና የከፋ ግማት ሲሸት ያየውን የዲያብሎስን መሠዊያ ሊፈራውና ሊሸሸው አይገባውምን? አንተ ጐስቋላ ሰው፥ ለምን መሥዋዕት ታመጣለህ? ለምንስ እንስሳ ትሠዋለህ? አንተ ራስህ መባ ሆነህ ወደ መሠዊያው መጥተሃል፤ አንተ ራስህ የሚሠዋ መሥዋዕት ሆነህ መጥተሃል፤ በዚያ መዳንህን፥ ተስፋህን ሠዋህ፤ በዚያም እምነትህን በእነዚያ ገዳይ እሳቶች ውስጥ አቃጠልህ።
9. ለብዙዎች ግን የገዛ ራሳቸው ጥፋት ብቻ አልበቃቸውም። እርስ በርስ በመመካከር ሰዎች ወደ ጥፋታቸው ተገፋፉ፤ ሞትም በገዳዩ ጽዋ ውስጥ ተራ በተራ እየተሰጠ ተጠጣ። ወንጀሉን የሚያከብድ ምንም እንዳይጐድል፥ ሕፃናት ደግሞ በወላጆቻቸው ክንድ ተሸክመው ወይም ተመርተው፥ ገና ታናናሾች ሳሉ በልደታቸው የመጀመሪያ ጅማሬ ያገኙትን አጡ። የፍርድ ቀን ሲመጣ እነርሱ። «እኛ ምንም ነገር አላደረግንም፤ ወደ ረከሰ መነካካት በነጻ ለመቸኮል የጌታን እንጀራና ጽዋ አልተውንም፤ የሌሎች አለማመን አጠፋን። ወላጆቻችንን ገዳዮቻችን ሆነው አገኘናቸው፤ ቤተ ክርስቲያንን እናት እንድትሆነን ከለከሉን፤ እግዚአብሔርን አባት እንዲሆነን ከለከሉን፤ ስለዚህም ታናናሾችና አስቀድመን የማናይ እንዲህ ያለውንም ወንጀል የማናውቅ ሳለን በሌሎች ወደ ክፋት ተካፋይነት ተቀላቀልን፥ በሌሎችም ተንኰል ተጠመድን» አይሉምን?
10. ወዮ፥ እንዲህ ያለውን ወንጀል የሚያስተባብል ቅንና ክብደት ያለው ምክንያት የለም። የገዛ አገራቸውን ሊተዉ ግድ ሆነባቸው፥ የርስታቸውንም መጥፋት ሊታገሡ ግድ ሆነባቸው ይባላል። ነገር ግን ለተወለደና ለሚሞት ሰው አንድ ጊዜ አገሩን የሚተውበትና የርስቱን መጥፋት የሚታገሥበት ግድ የለበትምን? ነገር ግን የመዳንና የዘላለም ቤት መጥፋት ሊፈራ እንዲገባ ሆኖ ክርስቶስ ፈጽሞ አይተው። እነሆ፥ መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ እንዲህ ብሎ ይጮኻል። «የእግዚአብሔርን ዕቃ የምትሸከሙ ሆይ፥ ሂዱ፥ ሂዱ፥ ከዚያ ውጡ፥ ርኩስን ነገር አትንኩ፤ ከመካከልዋ ውጡ፥ ተለዩም።» ነገር ግን የጌታ ዕቃና የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሆኑት ርኩሱን ነገር እንዲነኩ፥ በገዳይ ምግብም እንዲረክሱና እንዲበላሹ እንዳይገደዱ ከመካከልዋ አይወጡም፥ ከዚያም አይሄዱም። በሌላ ስፍራ ደግሞ ለእግዚአብሔር ባሪያዎች ሊያደርጉት የሚገባውን አስቀድሞ የሚያስጠነቅቅ ድምፅ ከሰማይ እንዲህ ሲል ይሰማል። «ሕዝቤ ሆይ፥ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ።» የሚወጣና የሚሄድ የበደሉ ተካፋይ አይሆንም፤ በወንጀሉ ባልንጀራ ሆኖ የተገኘ ግን በመቅሠፍቱ ይቈስላል። ስለዚህም ጌታ በስደት ጊዜ እንድንሄድና እንድንሸሽ አዘዘን፤ ይህ እንዲደረግ አስተማረ፥ ራሱም አደረገው። አክሊል በእግዚአብሔር ቸርነት ስለሚሰጥ፥ የሚቀበልበትም ሰዓት ሳይደርስ ሊቀበል ስለማይቻል፥ በክርስቶስ እየኖረ ለጊዜው የሚሄድ ሁሉ እምነቱን አይክድም፥ ጊዜውን ግን ይጠብቃል፤ ለመሄድ እምቢ ብሎ የወደቀ ግን ሊክደው በዚያ ቀረ።
11. ወንድሞች ሆይ፥ እውነቱ ሊሸፈን አይገባም፤ የቍስላችንም ጉዳይና ምክንያት ሊሰወር አይገባም። የገዛ ንብረትን የሚወድ ዕውር ፍቅር ብዙ ሰዎችን አታለለ፤ ሀብታቸው እንደ ሰንሰለት ሲያስራቸው ለመሄድ ሊዘጋጁ ወይም ሊቀልላቸው አልቻለም። ለቀሩት ሰንሰለቶቹ እነዚያ ነበሩ—በጎነት የዘገየባቸው፥ እምነት የከበደባቸው፥ መንፈስ የታሰረባቸው፥ ነፍስም የተከለከለባቸው ማሰሪያዎች እነዚያ ነበሩ፤ ስለዚህም በምድራዊ ነገር የተጠላለፉት እንደ እግዚአብሔር ፍርድ ምድርን ለሚበላው እባብ ምርኮና ምግብ ሆኑ። ስለዚህም የመልካም ነገር አስተማሪ የሆነው ጌታ ስለሚመጣው ዘመን አስቀድሞ እያስጠነቀቀ እንዲህ ይላል። «ፍጹም ልትሆን ብትወድ፥ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፥ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ።» ባለ ጠጎች ይህን ቢያደርጉ በሀብታቸው ባልጠፉ ነበር፤ መዝገብን በሰማይ ቢያከማቹ አሁን የቤት ውስጥ ጠላትና አጥቂ ባልኖራቸው ነበር። መዝገቡ በሰማይ ቢሆን ልብና አእምሮ ስሜትም ሁሉ በሰማይ በሆኑ ነበር፤ በዓለም የሚሸነፍበት ምንም ነገር በዓለም የሌለው በዓለም ሊሸነፍ አይችልም። እንደ ሐዋርያት፥ በሐዋርያትም ዘመን እንደ ነበሩት ብዙዎች፥ ገንዘባቸውንና ዘመዶቻቸውን ትተው ባልተከፋፈለ ማሰሪያ ከክርስቶስ ጋር እንደ ተጣበቁ ብዙዎች፥ እርሱም ተፈትቶና ነጻ ሆኖ ጌታን በተከተለ ነበር።
12. ነገር ግን በሀብታቸው ሰንሰለት ወደ ኋላ የተያዙ ክርስቶስን እንዴት ሊከተሉ ይችላሉ? ወይስ በምድራዊ ምኞት የከበዱ ሰማይን እንዴት ሊሹ፥ ወደ ከፍተኛና ልዕልና ወዳለው ከፍታ እንዴት ሊወጡ ይችላሉ? ይልቁንም እነርሱ ራሳቸው እየተያዙ ሳሉ ገንዘብን የያዙ ይመስላቸዋል፤ የትርፋቸው ባሪያዎች ናቸው እንጂ የገንዘባቸው ጌቶች አይደሉም፥ ይልቁንም የገንዘባቸው ባሪያዎች ናቸው። ሐዋርያው እነዚህን ዘመናትና እነዚህን ሰዎች እንዲህ ሲል ያመለክታል። «ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።» ነገር ግን ጌታ የዓለምን ሀብት እንድንንቅ በምን ዋጋ ይጋብዘናል? የዚህን የአሁኑን ዘመን ጥቃቅንና ኢምንት ጥፋቶች በምን ብድራት ይክሳል? «ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ቤትን ወይም ወላጆችን ወይም ወንድሞችን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን የተወ፥» ይላል፥ «በዚህ ዘመን ብዙ እጥፍ በሚመጣውም ዓለም የዘላለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።» ይህን ብናውቅ፥ ከተስፋ ሰጪው ጌታ እውነትም ብንረዳው፥ እንዲህ ያለው ጥፋት ሊፈራ አይገባም ብቻ ሳይሆን እንዲያውም ሊመኝ ይገባዋል፤ ጌታ ራሱ ደግሞ እንዲህ ብሎ እንደሚያውጅና እንደሚያስጠነቅቀን። «ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ ሲለዩአችሁም ሲነቅፉአችሁም ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ፥ ብፁዓን ናችሁ። እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ ዝለሉም።»
13. ነገር ግን (ይላሉ) ከዚያ በኋላ ሥቃዮች መጡ፥ ብርቱ መከራዎችም የተቃወሙትን ያስፈራሩ ነበር። በሥቃይ የተሸነፈ ስለ ሥቃይ ሊያማርር ይችላል፤ በመከራ የተሸነፈ የመከራን ምክንያት ሊያቀርብ ይችላል። እንዲህ ያለው ሰው እንዲህ ብሎ ሊለምን ይችላል፦ «በእርግጥ በጽናት ልጋደል ወደድሁ፤ መሐላዬንም አስቤ የአምልኮንና የእምነትን የጦር ዕቃ በእጄ አነሣሁ፤ ነገር ግን በፍልሚያው ስታገል ልዩ ልዩ ሥቃዮችና ለብዙ ጊዜ የቆዩ መከራዎች አሸነፉኝ። አእምሮዬ ጸንቶ ቆመ፥ እምነቴም ጠንካራ ነበረ፥ ነፍሴም በሚያሠቃዩ ሕማማት ሳትናወጥ ብዙ ጊዜ ታገለች፤ ነገር ግን ከሁሉ ጨካኝ የሆነው ዳኛ ጭካኔውን ባደሰ ጊዜ፥ እኔ ደክሜ ሳለሁ፥ ጅራፎቹ ይቀድዱኝ፥ ዱላዎቹ ያደቅቁኝ፥ መወጠሪያው ይዘረጋኝ፥ መንጠቆው ይቆፍረኝ፥ እሳቱም ይጠብሰኝ ነበር፤ ሥጋዬ በትግሉ ውስጥ ከዳኝ፥ የሰውነቴ ደካማነት እጅ ሰጠ፤ በመከራው የተሸነፈው አእምሮዬ ሳይሆን ሰውነቴ ነው።» እንዲህ ያለው ልመና በቀላሉ ለይቅርታ ሊጠቅም ይችላል፤ እንዲህ ያለው ምክንያት ርኅራኄን ሊያነሣሣ ይችላል። ጌታ በአንድ ወቅት ካስጦስንና አሚልዮስን እንዲሁ ይቅር አላቸው፤ እንዲሁም በመጀመሪያው ፍልሚያ ተሸንፈው በሁለተኛው ውጊያ አሸናፊዎች ሆኑ። ስለዚህ ቀድሞ ለእሳት እጅ የሰጡት ከእሳት ይልቅ በረቱ፥ በተሸነፉበትም ነገር አሸናፊዎች ሆኑ። ርኅራኄን የለመኑት በእንባቸው ሳይሆን በቍስላቸው ነው፤ በሚያሳዝን ድምፅ ብቻም ሳይሆን በሰውነት መቈራረጥና መከራ ነው። በልቅሶ ፈንታ ደም ፈሰሰ፤ በእንባም ፈንታ በግማሽ ከተቃጠለው አንጀታቸው ደም ወረደ።
14. አሁን ግን የተሸነፉት ምን ቍስል ሊያሳዩ ይችላሉ? በፍልሚያው የወደቀው እምነት ሳይሆን ከትግሉ አስቀድሞ የቀደመው አለማመን በሆነበት ጊዜ፥ የተከፈተ አንጀት ምን ቍስል፥ የብልቶችስ ምን ሥቃይ ሊያሳዩ ይችላሉ? ወንጀሉ በፈቃድ በተሠራበት ስፍራ የወንጀሉ ግዴታ የተገደደውን ሰው አያጸድቀውም። ይህንንም የምለው የወንድሞችን ጉዳይ ለማክበድ ብዬ አይደለም፤ ይልቁንም ወንድሞችን ወደ ማስተስረያ ጸሎት ለማነሣሣት ነው። «ብፁዓን የሚሉአችሁ ያስቱአችኋል፥ የእግራችሁንም መንገድ ያጠፋሉ» ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኃጢአተኛውን በሚያቈላምጥ ሽንገላ የሚያባብል ለኃጢአት መነሣሣትን ይሰጣል፤ ክፋትን ያሳድጋል እንጂ አይገታም። በጠንካራ ምክር ግን ወንድሙን እያስተማረ የሚገሥጽ ወደ መዳን ይገፋዋል። ጌታ «እኔ የምወዳቸውን ሁሉ» ይላል፥ «እገሥጻቸዋለሁ እቀጣቸውማለሁ።» ስለዚህም የጌታ ካህን በሚያታልል ልል ፈቃድ ሊያስት አይገባውም፤ ይልቁንም በሚያድን መድኃኒት ሊያክም ይገባዋል። የቍስልን ያበጡ ጠርዞች በለስላሳ እጅ ብቻ የሚዳስስ፥ በሰውነትም ጥልቅ ስፍራ የተዘጋውን መርዝ ይዞ የሚያበዛው አላዋቂ ሐኪም ነው። ቍስሉ ሊከፈት፥ ሊቈረጥም፥ የበሰበሱትንም ክፍሎች ቈርጦ በሚያወጣ በጠንካራ መድኃኒት ሊፈወስ ይገባዋል። ታማሚው ሕመሙን መታገሥ አቅቶት ይጮኽ፥ ይጣራ፥ ያማርርም ይሆናል፤ ነገር ግን እንደ ተፈወሰ ባወቀ ጊዜ በኋላ ያመሰግናል።
15. ደግሞም የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፥ አዲስ ዓይነት ጥፋት ተገልጧል፤ የስደቱም ማዕበል ጥቂት እንደ ተናወጠ ሆኖ፥ በምሕረት ስም አታላይ ክፋትና ያማረ የሚመስል መቅሠፍት በላዩ ተጨመረ። ከወንጌል ብርታት በተቃራኒ፥ ከጌታና ከአምላክ ሕግም በተቃራኒ፥ በአንዳንዶች ድፍረት ኅብረት ለግድየለሾች ተለቀቀ፤ ይህም ለሚሰጡት አደገኛ፥ ለሚቀበሉትም አንዳች የማይጠቅም ከንቱና ሐሰተኛ ሰላም ነው። ለጤና የሚያስፈልገውን ትዕግሥትና ከማስተስረያ የሚገኘውን እውነተኛ መድኃኒት አይሹም። ንስሐ ከልባቸው ተባርሯል፥ የእጅግ ከባድና የመጨረሻ ኃጢአታቸውም መታሰቢያ ተወስዷል። የሚሞቱት ሰዎች ቍስል ተሸፍኗል፤ በጥልቁና በስውሩ አንጀት የተተከለውም ገዳይ ምት በሐሰት በተሸፈነ ሕመም ተሰውሯል። ከዲያብሎስ መሠዊያዎች ተመልሰው በረከሰና የሚያስጸይፍ ሽታ በሚያወጣ እጅ ወደ ጌታ ቅዱስ ስፍራ ይቀርባሉ፤ መቅሠፍት የሚያመጣውን የጣዖት መሥዋዕት ሥጋ ገና ይተነፍሳሉ ማለት ይቻላል፤ መንጋጋቸው ገና ወንጀላቸውን እያወጣ፥ በገዳዩም ንክኪ እየሸተተ ሳለ ወደ ጌታ ሥጋ ይጋፋሉ፤ ቅዱስ መጽሐፍ ግን በመንገዳቸው ቆሞ እንዲህ እያለ ይጮኻል፦ «ንጹሕ የሆነ ሁሉ ከሥጋው ይበላል፤ ርኵሰቱም በላዩ ሳለ ለእግዚአብሔር ከሆነው ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ የሚበላ ነፍስ፥ ያ ነፍስ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።» ሐዋርያውም ደግሞ እንዲህ ብሎ ይመሰክራል፦ «የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም።» ደግሞም እልከኞችንና ጠማሞችን ያስፈራራል፥ እንዲህም ብሎ ያወግዛቸዋል፦ «ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት።»
16. እነዚህ ሁሉ ማስጠንቀቂያዎች ተንቀውና ተዋርደው፥ ኃጢአታቸው ሳይሰረይ፥ ስለ ወንጀላቸው ኑዛዜ ሳይደረግ፥ ሕሊናቸው በመሥዋዕትና በካህኑ እጅ ሳይነጻ፥ የተቈጣውና የሚያስፈራራው ጌታ ሳይታረቅ፥ በሥጋውና በደሙ ላይ ግፍ ይፈጸማል፤ ጌታቸውንም ከካዱበት ጊዜ ይልቅ አሁን በእጃቸውና በአፋቸው በጌታቸው ላይ አብልጠው ይበድላሉ። አንዳንዶች በአታላይ ቃል የሚያውጁትን ሰላም ነው ብለው ያስባሉ፤ ያ ሰላም አይደለም፥ ጦርነት ነው እንጂ፤ ከወንጌልም የተለየ ከቤተ ክርስቲያን ጋር አልተጣመረም። ጉዳትን ስለ ምን ቸርነት ብለው ይጠሩታል? ኃጢአተኛነትን ስለ ምን በአምልኮ ስም ይጠሩታል? ዘወትር ሊያለቅሱና ጌታቸውን ሊለምኑ የሚገባቸውን ከንስሐ ኀዘን ስለ ምን ይከለክሏቸዋል፥ ወደ ኅብረትም እንደሚቀበሏቸው ስለ ምን ያስመስላሉ? ይህ ለወደቁት በረዶ ለመከር፥ ማዕበላዊ ኮከብ ለዛፎች፥ የቸነፈር ጥፋት ለመንጎች፥ የሚያናውጥ ዐውሎ ነፋስ ለመርከቦች እንደ ሆነ ያለ ነገር ነው። የዘላለምን ተስፋ መጽናናት ይወስዳሉ፤ ዛፉን ከሥሩ ይገለብጣሉ፤ በመርዘኛ ቃላቸው ወደ ገዳይ ተላላፊ ደዌ ሹልክ ብለው ይገባሉ፤ መርከቡ ወደ ወደቡ እንዳይደርስ በዓለት ላይ ያላትሙታል። እንዲህ ያለው ቅለት ሰላምን ይወስዳል እንጂ አይሰጥም፤ ኅብረትንም አይሰጥም፥ ከመዳን ይከለክላል እንጂ። ይህ ተንኰለኛው ጠላት የወደቁትን ይበልጥ የሚያጠቃበት ሌላ ስደትና ሌላ ፈተና ነው፤ ልቅሶአቸው ጸጥ እንዲል፥ ኀዘናቸው ዝም እንዲል፥ የኃጢአታቸው መታሰቢያ እንዲያልፍ፥ የልባቸው መቃተት እንዲገታ፥ የዓይናቸውም እንባ እንዲደርቅ በስውር ርኵሰት ያጠቃቸዋል፤ ረጅምና ሙሉ ንስሐም እጅግ የተበደለውን ጌታ እንዳይለምን ያደርጋል፤ ምንም እንኳ «ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ» ተብሎ የተጻፈ ቢሆንም።
17. ማንም ራሱን አያታልል፥ ማንም ራሱን አያስት። ምሕረት ማድረግ የሚችል ጌታ ብቻ ነው። በእርሱ ላይ ለተሠሩ ኃጢአቶች ይቅርታን መስጠት የሚችል ኃጢአታችንን የተሸከመ፥ ስለ እኛ ያዘነ፥ እግዚአብሔርም ስለ ኃጢአታችን አሳልፎ የሰጠው እርሱ ብቻ ነው። ሰው ከእግዚአብሔር በምንም ሊበልጥ አይችልም፤ ባሪያም በጌታ ላይ በከፋ ወንጀል የተሠራውን በቸርነቱ ሊምር ወይም ሊተው አይችልም፤ ይህም ለወደቀው ሰው «በሰው የሚታመን ሰው ርጉም ነው» ተብሎ እንደ ተነገረ ባያውቅ በኃጢአቱ ላይ ሌላ እንዳይጨመርበት ነው። ጌታ ሊለመን ይገባዋል። የሚክደውን እንደሚክደው የተናገረው፥ ፍርድንም ሁሉ ከአባቱ ብቻውን የተቀበለው ጌታ በእኛ ማስተስረያ ሊታረቅ ይገባዋል። በእርግጥ የሰማዕታት ትሩፋትና የጻድቃን ሥራ በዳኛው ዘንድ እጅግ እንደሚጠቅም እናምናለን፤ ነገር ግን ይህ የሚሆነው የፍርድ ቀን በመጣ ጊዜ፥ ይህ ሕይወትና ዓለም ካለፉ በኋላ ሕዝቡ በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት በቆሙ ጊዜ ነው።
18. ነገር ግን ማንም ከልክ ባለፈ ችኰላ ለሁሉ የኃጢአት ስርየትን መስጠት እንደሚችል በድፍረት ቢያስብ፥ ወይም የጌታን ትእዛዛት ሊሽር ቢደፍር፥ ለወደቁት በምንም አይጠቅማቸውም፤ ይጐዳቸዋል እንጂ። ፍርዱን አለመጠበቅ ቍጣውን ማነሣሣት ነው፤ የእግዚአብሔርም ምሕረት አስቀድሞ ሊለመን አይገባውም ብሎ ማሰብ፥ ጌታንም ንቆ በሥልጣኑ መመካት ነው። በእግዚአብሔር መሠዊያ በታች የታረዱት የሰማዕታት ነፍሳት በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያሉ ይጮኻሉ፦ «ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?» እንዲያርፉም ገናም እንዲታገሡ ታዘዙ። ታዲያ ማንም ሰው ዳኛውን ተቃውሞ ለአጠቃላይ የኃጢአት ስርየትና ይቅርታ ሊጠቅም እንደሚችል፥ ወይም እርሱ ራሱ ሳይጸድቅ ሌሎችን ሊከልል እንደሚችል ያስባልን? ሰማዕታት አንድ ነገር እንዲደረግ ያዝዛሉ፤ ነገር ግን ይህ ነገር ቅንና የተፈቀደ ከሆነ፥ በእግዚአብሔር ካህን ጌታን ራሱን ሳይቃወም ሊደረግ ከቻለ፥ የሚታዘዘውም ወገን ፈቃድ ቀላልና ለስላሳ ከሆነ፥ የሚለምነውም ወገን ልከኝነት በአምልኮ የተሞላ ከሆነ ብቻ ነው። ሰማዕታት አንድ ነገር እንዲደረግ ያዝዛሉ፤ ነገር ግን ያዘዙት በጌታ ሕግ ያልተጻፈ ከሆነ፥ አስቀድመን የለመኑትን ከእግዚአብሔር እንዳገኙ ማወቅ አለብን፥ ከዚያም ያዘዙትን እናደርጋለን። በሰው ተስፋ የተሰጠው ሁሉ በመለኮታዊው ግርማ ወዲያውኑ የተፈቀደ ሆኖ ሁልጊዜ አይገኝምና።
19. ሙሴም ደግሞ ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ለመነ፤ ነገር ግን ለእነዚህ ኃጢአተኞች ይቅርታን በለመነ ጊዜ አላገኘም። «እለምንሃለሁ» አለ፥ «አቤቱ፥ ይህ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአትን ሠርቷል፥ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክትን አድርገዋል። አሁንም ኃጢአታቸውን ይቅር ብትል ይቅር በል፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍ ደምስሰኝ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ የበደለኝን እርሱን ከመጽሐፌ እደመስሰዋለሁ አለው።» እርሱ ሙሴ የእግዚአብሔር ወዳጅ የነበረው፥ ብዙ ጊዜ ከጌታ ጋር ፊት ለፊት የተነጋገረው፥ የለመነውን ማግኘት አልቻለም፥ የተቈጣውን አምላክ ቍጣም በልመናው ማብረድ አልቻለም። እግዚአብሔር ኤርምያስን ያመሰግነዋል፥ እንዲህም ብሎ ያውጃል፦ «በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፤ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀደስሁህ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌ ሾምሁህ።» ለዚያው ሰው ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ብዙ ጊዜ በለመነና በጸለየ ጊዜ እንዲህ ይለዋል፦ «አንተ ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፥ ስለ እነርሱም ጩኸትንና ጸሎትን አታንሣ፤ በሚጠሩኝ ጊዜ፥ በመከራቸው ጊዜ አልሰማቸውምና።» ነገር ግን ምድር በኃጢአት በተሞላች ጊዜ በምድር ላይ ብቻውን ጻድቅ ሆኖ ከተገኘው ከኖኅ ይልቅ ጻድቅ ማን ነበረ? ከዳንኤል ይልቅ የከበረ ማን ነው? በእምነት ጽናት ሰማዕትነትን ለመቀበል ከእርሱ ይልቅ የበረታ፥ በእግዚአብሔር ቸርነት ከእርሱ ይልቅ የተባረከ፥ ብዙ ጊዜ ሲጋደል ያሸነፈ፥ ካሸነፈም በኋላ በሕይወት የኖረ ማን ነው? በበጎ ሥራ ከኢዮብ ይልቅ የተዘጋጀ፥ በፈተና የበረታ፥ በመከራ የታገሠ፥ በፍርሃቱ የተዋረደ፥ በእምነቱ የታመነ ማን ነበረ? ነገር ግን እግዚአብሔር ቢለምኑ እንኳ እንደማይሰጣቸው ተናገረ። ነቢዩ ሕዝቅኤል ስለ ሕዝቡ ኃጢአት በለመነ ጊዜ፥ «ማናቸውም ምድር» አለ፥ «እጅግ በመበደል በእኔ ላይ ብትበድል፥ እጄን እዘረጋባታለሁ፥ የእንጀራዋንም በትር እሰብራለሁ፥ ራብንም እሰድድባታለሁ፥ ሰውንና እንስሳንም ከእርስዋ አጠፋለሁ። እነዚህ ሦስቱ ሰዎች ኖኅ፥ ዳንኤልና ኢዮብ በውስጧ ቢኖሩ ወንዶችንም ሴቶችንም ልጆች አያድኑም፤ እነርሱ ብቻ ራሳቸው ይድናሉ።» እንዲሁም የሚለመነው ሁሉ በለማኙ ቅድመ ፍርድ ሳይሆን በሰጪው ነጻ ፈቃድ ነው፤ መለኮታዊው ፈቃድ ካልተቀበለው በቀር የሰው ፍርድ አንዳችን ለራሱ ሊወስድ ወይም ሊነጥቅ አይችልም።
20. በወንጌል ጌታ ይናገራል፥ እንዲህም ይላል፦ «በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ።» የሚክደውን ካልካደ፥ የሚመሰክረውንም አይመሰክርለትም፤ ወንጌል በአንድ ክፍል ጤናማ በሌላውም የሚናወጥ ሊሆን አይችልም። ወይ ሁለቱም ጸንተው ይቆማሉ፥ ወይ ሁለቱም የእውነትን ኃይል ያጣሉ። የሚክዱት በወንጀል የማይጠየቁ ከሆነ፥ የሚመሰክሩትም የበጎነትን ዋጋ አይቀበሉም። ደግሞም ያሸነፈው እምነት ዘውድ የሚቀዳጅ ከሆነ፥ የተሸነፈው አለማመን ሊቀጣ ግድ ነው። ስለዚህ ወንጌል ሊሻር የሚችል ከሆነ ሰማዕታት ምንም ሊያደርጉ አይችሉም፤ ወንጌል ሊሻር የማይችል ከሆነ ደግሞ ስለ ወንጌል ሰማዕታት ስለሚሆኑ በወንጌል ላይ ምንም ሊያደርጉ አይችሉም። የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፥ ማንም፥ ማንም የሰማዕታትን ክብር አያቃልል፥ ማንም ክብራቸውንና ዘውዳቸውን አያዋርድ። ያልረከሰው እምነታቸው ብርታት ጤናማ ሆኖ ይኖራል፤ ተስፋውም፥ እምነቱም፥ በጎነቱም፥ ክብሩም ሁሉ በክርስቶስ የሆነ ሰው በክርስቶስ ላይ ምንም ሊናገርም ሊያደርግም አይችልም፤ እነርሱ ራሳቸው የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ያደረጉ ሰዎች ጳጳሳት በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ አንዳች እንዲያደርጉ ሥልጣን ሊሆኑ አይችሉም። ታዲያ እግዚአብሔር እንዲደረግ የፈቀደውን እንዳልተደረገ ሊመኝ፥ ወይም እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያኑን ለመጠበቅ ጥቂት ኃይል ብቻ እንዳለው አድርጎ በእርሱ እርዳታ ልንጠበቅ እንደምንችል ሊያስብ ከእግዚአብሔር የሚበልጥ፥ ወይም ከእግዚአብሔር ቸርነት ይልቅ መሐሪ የሆነ ማን ነው?
21. ምናልባት እነዚህ ነገሮች ያለ እግዚአብሔር እውቀት ተደርገው፥ ወይም እነዚህ ሁሉ ያለ ፈቃዱ ደርሰው ካልሆነ በቀር፤ ነገር ግን ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ብሎ በሚናገርበት ስፍራ የማይማሩትን ያስተምራል፥ የሚዘነጉትንም ይመክራል፦ «ያዕቆብን ለብዝበዛ፥ እስራኤልንም ለበዝባዦች አሳልፎ የሰጠ ማን ነው? የበደሉት፥ በመንገዱም ሊሄዱ ያልወደዱት፥ ለሕጉም ያልታዘዙለት እግዚአብሔር አይደለምን? የቍጣውንም መዓት በላያቸው አፈሰሰ።» በሌላም ስፍራ እንዲህ ብሎ ይመሰክራል፦ «የእግዚአብሔር እጅ ማዳን እንዳይችል አጠረችን? ወይስ ጆሮው መስማት እንዳይችል ከበደችን? ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይቷል፤ ስለ ኃጢአታችሁም እንዳይምራችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሯል።» ሥራችንንና የልባችንን ምሥጢር እያሰላሰልን ይልቁንም በደላችንን እንመርምር፤ የሕሊናችንን ዋጋ እንመዝን፤ በጌታ መንገድ እንዳልሄድን፥ የእግዚአብሔርንም ሕግ እንደ ጣልን፥ ትእዛዛቱንና የሚያድነውን ምክሩንም ልንጠብቅ ፈጽሞ እንዳልወደድን ወደ ልባችን ይመለስ።
22. ፍርሃት ሊያቀናው ስደትም ራሱ ሊያሻሽለው ያልቻለውን ሰው ምን መልካም ነገር ልታስብለት ትችላለህ? ምን ፍርሃት ወይስ ምን እምነት ከእርሱ ጋር ነበረ ብለህ ትገምታለህ? የኰራውና የደነደነው አንገቱ ወድቆም እንኳ አይታጠፍም፤ ያበጠችውና የታበየችው ነፍሱ ተሸንፋም እንኳ አትሰበርም። ወድቆ ሳለ የቆሙትን፥ ቈስሎም ሳለ ጤነኞቹን ያስፈራራል። በረከሱ እጆቹም የጌታን ሥጋ ወዲያውኑ ሊቀበል ስላልቻለ ያ ቅዱሳትን የሚያረክስ በካህናት ላይ ይቈጣል። ኦ፥ አንተ ያበድህ ሆይ፥ እብደትህ ምንኛ ከልክ ያለፈ ነው! የእግዚአብሔርን ቍጣ ከአንተ ሊመልስ በሚተጋው ላይ ትቈጣለህ፤ ስለ አንተ መለኮታዊውን ምሕረት የሚለምነውን፥ አንተ ራስህ የማይሰማህን ቍስልህን የሚሰማውን፥ ምናልባትም አንተ ራስህ ያላፈሰስኸውን እንባ ስለ አንተ የሚያፈሰውን ታስፈራራዋለህ። ገና ወንጀልህን ታከብዳለህ ታበዛማለህ፤ አንተ ራስህ በእግዚአብሔር አገልጋዮችና ካህናት ላይ የማትታረቅ ሆነህ ሳለ፥ ጌታ ስለ አንተ ሊታረቅ እንደሚችል ታስባለህን?
23. ይልቁንም የምንለውን ተቀበሉ፥ አስተውሉም። የምንመክራችሁን የሚያድኑ ትእዛዛት ደንቆሮ ጆሮአችሁ ስለ ምን አይሰማም? የምናሳያችሁን የንስሐ መንገድ ዕውር ዓይናችሁ ስለ ምን አያይም? ከሰማያዊ መጻሕፍት የምንማረውንና የምናስተምረውን ሕያው መድኃኒት የተመታውና የራቀው አእምሮአችሁ ስለ ምን አያስተውልም? ወይም አንዳንድ የማያምኑ በሚመጡት ነገሮች ላይ እምነታቸው ጥቂት ከሆነ፥ በአሁኖቹ ይደንግጡ። እነሆ፥ የካዱትን እንዴት ያሉ ቅጣቶችን በዓይናችን እናያለን! እንዴት ያለ የሚያሳዝን ሞታቸውን እናለቅሳለን! የቅጣት ቀን ገና ባይደርስም በዚህም እንኳ ያለ ቅጣት ሊሆኑ አይችሉም። ሌሎች እንዲታረሙ አንዳንዶች በዚያው መካከል ይቀጣሉ። የጥቂቶች ሥቃይ ለሁሉ ምሳሌ ነው።
24. ለመካድ በፈቃዱ ወደ ካፒቶል ከወጡት አንዱ ክርስቶስን ከካደ በኋላ ዲዳ ሆነ። ቅጣቱ ወንጀሉ ከጀመረበት ስፍራ ጀመረ፤ ስለዚህም ምሕረትን የሚለምንበት ቃል ስላልነበረው ከእንግዲህ መለመን አልቻለም። በመታጠቢያ ቤት የነበረች ሌላዪቱ (የሕይወትን መታጠቢያ ጸጋ ካጣች በኋላ ወዲያውኑ ወደ መታጠቢያ ቤት መሄዷ ለወንጀሏና ለመከራዋ የጐደለው ይህ ነበርና)፥ በዚያ ርኵስ ሆና ሳለች ርኵስ መንፈስ ያዛት፥ በክፋት የበላችበትን ወይም የተናገረችበትን ምላሷን በጥርሷ ቈረጠች። ክፉው መብል ከተበላ በኋላ የአፍ እብደት ለራሱ ጥፋት ታጠቀ። እርሷ ራሷ የራሷ ገዳይ ሆነች፥ ከዚያም በኋላ ብዙ አልኖረችም፤ በሆድና በአንጀት ምጥ ተሠቃይታ ሞተች።
25. እኔ ራሴ በዚያ ሳለሁና ምስክር ሆኜ የሆነውን ተማሩ። በአጋጣሚ የሚሸሹ አንዳንድ ወላጆች ከፍርሃታቸው የተነሣ ጥንቃቄ አጥተው ትንሽ ሴት ልጃቸውን በሞግዚት እጅ ትተዋት ሄዱ። ሞግዚቲቱም የተተወችውን ሕፃን ለገዢዎች አሳልፋ ሰጠች። እነርሱም ሕዝቡ በሚጐርፍበት ጣዖት ፊት (በዕድሜዋ ምክንያት ገና ሥጋ መብላት አትችልም ነበርና) ከወይን ጋር የተቀላቀለ እንጀራ ሰጧት፤ ይህም ራሱ የጠፉት ሰዎች በሠዉት መሥዋዕት የተረፈ ነበረ። ከዚያ በኋላ ግን እናቲቱ ልጇን መልሳ አገኘች። ነገር ግን ልጅቱ የተሠራውን ወንጀል ቀድሞ ልታስተውለው ወይም ልትከለክለው እንዳልቻለች ሁሉ፥ አሁንም ልትናገረው ወይም ልታመለክተው አልቻለችም። ስለዚህ እኛ መሥዋዕት በምናቀርብበት ጊዜ እናቲቱ ሳታውቅ ልጅቱን ይዛት ገባች። ደግሞም ልጅቱ ከቅዱሳን ጋር ተቀላቅላ ጸሎታችንንና ምልጃችንን መታገሥ አቃታት፤ አንድ ጊዜ በልቅሶ ትናወጥ፥ ሌላ ጊዜም ከአእምሮዋ ብርቱ መታወክ የተነሣ እንደ ባሕር ማዕበል ትንገላታ ነበር፤ ገና ለጋ የሆነችው የዚያች ሕፃን ነፍስ በአሠቃዪ እንደ ተገደደች ሆና በቻለችው ምልክት ሁሉ የድርጊቱን እውቀት ተናዘዘች። ሥርዓቱ በተፈጸመ ጊዜ ዲያቆኑ ለተገኙት ጽዋውን ማቅረብ በጀመረ ጊዜ፥ ሌሎቹም ሲቀበሉ ተራዋ በደረሰ ጊዜ፥ ሕፃኒቱ በመለኮታዊው ግርማ ግፊት ፊቷን መለሰች፥ በሚቃወሙ ከንፈሮቿም አፏን ጨፈነች፥ ጽዋውንም እምቢ አለች። ዲያቆኑ ግን አጥብቆ ቀጠለ፥ እርሷ ብትቃወምም ከጽዋው ምሥጢር ጥቂቱን በግድ አስገባላት። ከዚያም ወዲያውኑ ሳግና ማስታወክ ተከተለ። ቅዱስ ቁርባን በረከሰ ሥጋና አፍ ውስጥ ሊቆይ አልቻለም፤ በጌታ ደም የተቀደሰው መጠጥ ከረከሰው ሆድ ፈንድቶ ወጣ። የጌታ ኃይል እንዲህ ታላቅ ነው፥ ግርማውም እንዲህ ታላቅ ነው። የጨለማ ምሥጢሮች በብርሃኑ ተገለጡ፤ የተሰወሩ ወንጀሎችም እንኳ የእግዚአብሔርን ካህን አላታለሉም።
26. ገና ስለ ራስዋ ሌሎች የሠሩትን ወንጀል ለመናገር ዕድሜዋ ያልደረሰላትን ሕፃን በተመለከተ ይህን ያህል ይበቃል። ነገር ግን በዕድሜ የገፋችና በአካልም የበሰለች አንዲት ሴት እኛ መሥዋዕት በምናቀርብበት ጊዜ በስውር ሾልካ ወደ መካከላችን ገብታ ለራስዋ ምግብን ሳይሆን ሰይፍን ተቀበለች፤ ገዳይ መርዝን ወደ መንጋጋዋና ወደ ሰውነትዋ እንደ ወሰደች ያህልም ወዲያው መሠቃየት ጀመረች፥ በእብደትም ደነደነች፤ ከእንግዲህ የስደትን ሳይሆን የወንጀልዋን መከራ እየተቀበለች እየተንቀጠቀጠችና እየራደች ወደቀች። በግብዝነት የተሸሸገው የሕሊናዋ ወንጀል ሳይቀጣና ሳይገለጥ ብዙ ጊዜ አልቆየም። ሰውን ያታለለችው እርስዋ እግዚአብሔር ግን እንደሚበቀላት ተሰማት። ሌላይቱም ሴት የጌታ ቅዱስ (ሥጋ) የነበረበትን ሣጥንዋን በማይገባቸው እጆች ልትከፍት በሞከረች ጊዜ፥ ከውስጡ በተነሣ እሳት ልትነካው እንዳትደፍር ተከለከለች። ራሱ የረከሰ አንድ ሰውም ካህኑ ከፈጸመው መሥዋዕት ከሌሎቹ ጋር በስውር ድርሻ ሊቀበል በደፈረ ጊዜ፥ የጌታን ቅዱስ ነገር ሊበላውም በእጁ ሊዳስሰውም አልቻለም፤ እጆቹን ሲከፍትም አመድ ይዞ አገኘ። እንዲሁም ጌታ ሲካድ እንደሚርቅ፥ የተቀበሉትም ነገር ለማይገባቸው ለመዳን እንደማይጠቅም በዚህ በአንዱ ሰው ተሞክሮ ተገለጠ፤ ቅድስናው ሲለይ የሚያድነው ጸጋ ወደ አመድ ይለወጣልና። ንስሓ የማይገቡ፥ የወንጀላቸውንም ሕሊና የማይናዘዙ፥ በርኩሳን መናፍስት የተሞሉ ስንቶች በየዕለቱ አሉ! በእብደት ቁጣ እስከ አእምሮ መናወጥና እስከ ቂልነት ድረስ የሚናወጡ ስንቶች ናቸው! በዓለም ውስጥ በሚደርሱት ልዩ ልዩ ውድቀቶች ምክንያት የኃጢአተኞች ብዛት እንደ በዛ መጠን የኃጢአታቸው ቅጣትም ልዩ ልዩ ነውና የእያንዳንዱን ሰው ሞት አንድ በአንድ መዘርዘር አያስፈልግም። እያንዳንዱ ሰው ሌላው የደረሰበትን ሳይሆን ራሱ ሊቀበለው የሚገባውን ያስብ፤ ቅጣቱም ለጊዜው ቢዘገይ ያመለጠ አይምሰለው፤ ፈራጁ እግዚአብሔር በቁጣው ለራሱ አስቀምጦታልና አብልጦ ሊፈራው ይገባዋል።
27. በአስጸያፊ መሥዋዕቶች እጃቸውን ባያረክሱም ሕሊናቸውን በምስክር ወረቀቶች ያረከሱ ሰዎች ንስሓ የሚያስፈልጋቸው ያነሰ ነው ብለው ራሳቸውን አያታልሉ። ያ የሚክድ ሰው የሰጠው ያ ቃል ቀድሞ የነበረውን የሚክድ የክርስቲያን ምስክርነት ነው። ሌላው ሰው በእውነት የፈጸመውን እርሱ ራሱ እንደ ፈጸመው ይናገራል፤ «ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም» ተብሎ የተጻፈ ቢሆንም፥ አዋጁን በመታዘዙ ለምድራዊ ጌታ ተገዛ፤ ከእግዚአብሔር ይልቅ ለሰው ሥልጣን አብልጦ ታዘዘ። ያደረገውን ነገር በሰዎች ዘንድ ባነሰ ውርደት ወይም ባነሰ በደል ቢገልጠውም ምንም ልዩነት የለውም። ምንም ቢሆን ፈራጁን እግዚአብሔርን ማምለጥና መሸሽ አይችልም፤ መንፈስ ቅዱስ በመዝሙራት «ያልተፈጸመውን አካሌን ዓይኖችህ አዩ፤ ሰዎችም ሁሉ በመጽሐፍህ ይጻፋሉ» ይላልና። ደግሞም፦ «ሰው ፊትን ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል።» ጌታ ራሱም ደግሞ «አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ኵላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ» ብሎ በመናገር አስቀድሞ ያስጠነቅቀናል፤ ያዘጋጀናልም። እርሱ የተሰወረውንና የተሸሸገውን ነገር ይመለከታል፤ የተደበቀውንም ያስተውላል፤ «እኔ በቅርብ ያለሁ አምላክ ነኝ እንጂ በሩቅ ያለሁ አምላክ አይደለሁም። ሰው በስውር ስፍራ ቢሸሸግ እኔ አላየውምን? ሰማይንና ምድርን የምሞላ እኔ አይደለሁምን?» ከሚለው ከጌታ ዓይን ማንም ሰው ሊያመልጥ አይችልም። እርሱ የእያንዳንዱን ሰው ልብና አሳብ ያያል፤ በሥራችን ብቻ ሳይሆን በቃላችንና በአሳባችንም ይፈርዳል። ገና በተዘጋው ልብ መሸሸጊያ ውስጥ ያለውን የሰዎችን ሁሉ አእምሮ፥ ፈቃድና አሳብ ይመረምራል።
28. ደግሞም ለጣዖታት በመሠዋት ወይም በምስክር ወረቀት ወንጀል ባይታሰሩም፥ እንዲህ ያለውን ነገር እንኳ ስላሰቡ ብቻ ይህንኑ በኀዘንና በቅንነት ለእግዚአብሔር ካህናት የሚናዘዙ፥ የሕሊናቸውንም ኑዛዜ የሚያቀርቡ፥ የአእምሮአቸውንም ሸክም የሚያራግፉ፥ «እግዚአብሔር አይዘበትበትም» ተብሎ እንደ ተጻፈ አውቀው ለቀላልና ለመጠነኛ ቁስሎች እንኳ የሚያድነውን መድኃኒት የሚሹ ሰዎች በእምነት ምንኛ የሚበልጡ፥ በፍርሃታቸውም ምንኛ የተሻሉ ናቸው! እግዚአብሔር በምንም አታላይ ብልሃት ሊዘበትበት፥ ሊታለልም፥ ሊሸነገልም አይችልም። እንዲያውም እግዚአብሔር እንደ ሰው እንደ ሆነ አስቦ ወንጀሉን በግልጥ ካልተናዘዘ የወንጀሉን ቅጣት የሚያመልጥ የሚመስለው ሰው አብልጦ ኃጢአትን ይሠራል። ክርስቶስ በትእዛዛቱ «በእኔ የሚያፍር ሁሉ የሰው ልጅ ያፍርበታል» ይላል። ክርስቲያን ለመሆን የሚያፍር ወይም የሚፈራ ሰው ክርስቲያን እንደ ሆነ ያስባልን? የክርስቶስ ለመሆን የሚያፍር ወይም የሚፈራ ሰው ከክርስቶስ ጋር እንዴት አንድ ሊሆን ይችላል? ጣዖታትን ባለማየቱ፥ በዙሪያው ቆሞ በሚሳደብ ሕዝብ ዓይን ፊት የእምነትን ቅድስና ባለማርከሱ፥ እጆቹንም በገዳይ መሥዋዕቶች ባለማርከሱ፥ ከንፈሮቹንም በክፉ ምግብ ባለማሳደፉ በእርግጥ ያነሰ ኃጢአት ሠርቶ ይሆናል። ይህም የሚጠቅመው እስከዚህ ድረስ ብቻ ነው፤ ይኸውም በደሉ እንዲያንስ እንጂ ሕሊናው ከበደል ንጹሕ እንዲሆን አይደለም። ለወንጀሉ ይቅርታን በቀላሉ ሊያገኝ ይችላል፤ ነገር ግን ከወንጀል ፈጽሞ ነጻ አይደለም፤ በበደሉ ዓይነት ያነሰ የሚመስለው ነገር ማስተስረያን ቸል በማለቱ እንዳይጨምር ንስሓውን መፈጸምና የጌታን ምሕረት መለመን አያቋርጥ።
29. የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፥ የበደለው ሰው ገና በዚህ ዓለም ሳለ፥ ኑዛዜውም ተቀባይነት ሊያገኝ በሚችልበት ጊዜ፥ በካህናትም የሚደረገው ካሣና ሥርየት በጌታ ዘንድ ተወዳጅ በሆነበት ጊዜ፥ እያንዳንዳችሁ የገዛ ራሱን ኃጢአት እንዲናዘዝ እለምናችኋለሁ። በፍጹም ልባችን ወደ ጌታ እንመለስ፤ ስለ ኃጢአታችንም ንስሓችንን በእውነተኛ ኀዘን እየገለጥን የእግዚአብሔርን ምሕረት እንለምን። ነፍሳችን በፊቱ ዝቅ ብላ ትዋረድ። ልቅሶአችን በእርሱ ዘንድ ያስተሰርይልን። ተስፋችን ሁሉ በእርሱ ላይ ይደገፍ። በምን ዓይነት መንገድ መለመን እንደሚገባን እርሱ ራሱ ይነግረናል። «ተመለሱ» ይላል፥ «በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶም፥ በዋይታም ወደ እኔ ተመለሱ፤ ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ።» በፍጹም ልባችን ወደ ጌታ እንመለስ። ራሱ እንደሚመክረን ቁጣውንና መቅሠፍቱን በጾም፥ በልቅሶና በዋይታ እናብርድ።
30. ኃጢአትን ከሠራበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ በየዕለቱ ከሴቶች ጋር ወደ መታጠቢያ ቤቶች የሚመላለስ፥ በተትረፈረፉ ግብዣዎች ላይ እየተመገበና አብዝቶ በበላው ጣፋጭ ምግብ ተነፍቶ በማግሥቱ ያልተፈጨውን መብሉን የሚያገሳ፥ ከምግቡና ከመጠጡም የድሆችን ችግር ለመርዳት ምንም የማያካፍል ሰው በፍጹም ልቡ እንደሚያለቅስ፥ በጾምና በልቅሶ በዋይታም ጌታን እንደሚለምን እናምናለን? በደስታና በሐሴት እርምጃ የሚመላለስ ሰው ስለ ገዛ ሞቱ እንዴት አድርጎ ያለቅሳል? «የጢማችሁን ዳር አታበላሹ» ተብሎ የተጻፈ ቢሆንም እርሱ ግን ጢሙን ይነጫል፤ ጠጕሩንም ያሳምራል፤ ታዲያ እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ሰው አሁን ማንንም ደስ ለማሰኘት ይጥራልን? ወይስ የጠፋባትን የክርስቶስን ልብስ ሳታስብ ውድ የሆነ የከበረ ልብስ ለመልበስ ጊዜ የምታገኝ፥ የመለኮታዊውንና የሰማያዊውን ጌጥ መጥፋት ሳታለቅስ ውድ ጌጦችንና በብልሃት የተሠሩ ድሪሞችን ለመቀበል ጊዜ የምታገኝ ሴት ታቃስታለች፥ ታለቅሳለችን? የባዕድ አገር ልብስንና የሐር ቀሚስን ብትለብሺም ዕራቁትሽን ነሽ፤ በዕንቍም፥ በዕንቈ ባሕርይም፥ በወርቅም ከመጠን በላይ ብታጌጪም ያለ ክርስቶስ ጌጥ የማታምሪ ነሽ። እናንተ ጠጕራችሁን የምትቀቡ፥ ቢያንስ አሁን በኀዘን መካከል ሳላችሁ ይህን ተዉ፤ እናንተም በጥቁር ኵል በዙሪያቸው በተሰመረ መስመር የዓይኖቻችሁን ዳር የምትኳሉ፥ ቢያንስ አሁን ዓይኖቻችሁን በእንባ እጠቡ። ከወዳጆቻችሁ መካከል አንድ የምትወዱትን ሰው ሟች በሆነ ሰው ሁሉ በሚደርስ ሞት ብታጡ፥ እጅግ ባቃሰታችሁ፥ በተዘበራረቀ ፊትም ባለቀሳችሁ፥ በተለወጠ ልብስ፥ በተተወ ጠጕር፥ በጨለመ ፊት፥ በተዋረደ መልክ የኀዘንን ምልክቶች ባሳያችሁ ነበር። አንተ ምስኪን ፍጡር፥ ነፍስህን አጥተሃል፤ በዚህ በመንፈስ ሞተህ ለራስህ መኖርን ቀጥለሃል፤ ራስህም እየተመላለስህ የገዛ ሞትህን ተሸክመህ መዞር ጀምረሃል። ታዲያ መራራ ልቅሶ አታለቅስምን? ያለ ማቋረጥስ ዘወትር አታቃስትምን? ስለ ኃጢአትህ ኀፍረት ወይም ልቅሶህን ለመቀጠል ራስህን አትሰውርምን? እነሆ፥ እነዚህ ከኃጢአት ይልቅ የባሱ ቁስሎች ናቸው፤ እነሆ፥ እነዚህ የበለጡ ወንጀሎች ናቸው—ኃጢአትን ሠርቶ አለማስተስረይ—ወንጀልን ፈጽሞ ስለ ወንጀል አለማልቀስ።
31. የከበሩትና ክቡራን ብላቴኖች አናንያ፥ አዛርያና ሚሳኤል በሚነድደው እቶን ነበልባልና ትኩሳት መካከል እንኳ ለእግዚአብሔር በግልጥ መናዘዝን አላቋረጡም። ምንም እንኳ በጎ ሕሊና የነበራቸውና በእምነትና በፍርሃት መታዘዝ ብዙ ጊዜ በጌታ ዘንድ መልካምን ያደረጉ ቢሆኑም፥ በበጎነታቸው የከበሩ ሰማዕትነቶች መካከል እንኳ ትሕትናቸውን መጠበቅንና ለጌታ ማስተስረይን አልተዉም። ቅዱሱ መጽሐፍ «አዛርያም ቆሞ ጸለየ፤ አፉንም ከፍቶ በእሳቱ መካከል ከባልንጀሮቹ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ተናዘዘ» ብሎ ይናገራል። ዳንኤልም ደግሞ ከእምነቱና ከንጽሕናው ብዙ ዓይነት ጸጋ በኋላ፥ ስለ በጎነቱና ስለ ምስጋናው ጌታ ብዙ ጊዜ ዝቅ ብሎ ከጐበኘው በኋላ፥ በጾም አብልጦ በእግዚአብሔር ዘንድ መልካም ለማድረግ ይጥራል፤ ማቅ ለብሶ አመድ ነስንሶ በኀዘን ይናዘዛል፤ እንዲህም ይላል፦ «አቤቱ፥ የሚወዱህንና ትእዛዛትህን የሚጠብቁትን ቃል ኪዳንህንና ምሕረትህን የምትጠብቅ ታላቅና ብርቱ የምትፈራም አምላክ ጌታ ሆይ፥ ኃጢአት ሠርተናል፥ በድለናል፥ ክፉም አድርገናል፤ ከትእዛዝህና ከፍርድህ ተላልፈን ራቅን፤ በስምህ ለንጉሦቻችንና ለአሕዛብ ሁሉ ለምድርም ሁሉ የተናገሩትን የባሪያዎችህን የነቢያትን ቃል አልሰማንም። አቤቱ፥ ጽድቅ ለአንተ ነው፤ ለእኛ ግን የፊት እፍረት ነው።»
32. እነዚህ ነገሮች በእግዚአብሔር ግርማ ዘንድ መልካም ለማድረግ በየዋሃን፥ በቅኖችና በንጹሓን ሰዎች ተደረጉ፤ አሁን ግን እነዚያ ጌታን የካዱት ሰዎች ለጌታ ማስተስረይንና እርሱን መለመንን እምቢ ይላሉ። ወንድሞች ሆይ፥ እለምናችኋለሁ፥ ለሚያድኑ መድኃኒቶች እሺ በሉ፤ የተሻለውን ምክር ታዘዙ፤ እንባችሁን ከእንባችን ጋር አንድ አድርጉ፤ ልቅሶአችሁን ከልቅሶአችን ጋር አጣምሩ፤ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን እንለምን ዘንድ እንለምናችኋለን፤ እንዲራራላችሁ እግዚአብሔርን ስለ እናንተ የምንለምንበትን ጸሎታችንን አስቀድመን ወደ እናንተ እናዞራለን። እጅግ አብዝታችሁ ንስሓ ግቡ፤ የሚያዝንና የሚያለቅስ ልቡና ያለውን ኀዘን በሥራ አሳዩ።
33. በዚህ ያህል ከባድ ወንጀል ተይዘው ሳሉ ኃጢአታቸውን እንዳያስተውሉና እንዳያለቅሱ በአእምሮ ዕውርነት የተመቱ የአንዳንዶች ያልተጠነቀቀ ስሕተት ወይም ከንቱ ድንዛዜ አያንቀሳቅሳችሁ። ይህ የተቈጣው እግዚአብሔር የሚያመጣው እጅግ የባሰ ቅጣት ነው፤ «እግዚአብሔርም የእንቅልፍ መንፈስን ሰጣቸው» ተብሎ እንደ ተጻፈ። ደግሞም፦ «እንዲድኑ የእውነትን ፍቅር አልተቀበሉምና። ስለዚህም ምክንያት ሐሰትን እንዲያምኑ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል፤ ይኸውም እውነትን ያላመኑ ዓመፃንም የወደዱ ሁሉ እንዲፈረድባቸው ነው።» በዓመፃ ራሳቸውን ደስ እያሰኙና በደነደነ ልብ መራቅ እያበዱ የጌታን ትእዛዛት ይንቃሉ፤ ለቁስላቸው የተሰጠውን መድኃኒት ቸል ይላሉ፤ ንስሓም አይገቡም። ኃጢአታቸው ከመታወቁ በፊት ግድ የለሾች ነበሩ፤ ከኃጢአታቸው በኋላ ግን እልከኞች ናቸው፤ በፊት አልጸኑም፥ በኋላም አይለምኑም፤ መቆም ሲገባቸው ወደቁ፤ በእግዚአብሔር ፊት ወድቀው መስገድ ሲገባቸው እንደ ቆሙ ያስባሉ። ማንም ሰው ሳይሰጣቸው በገዛ ራሳቸው ፈቃድ ሰላምን ለራሳቸው ወሰዱ፤ በሐሰተኛ የተስፋ ቃሎች ተታልለው ከከሐዲዎችና ከማያምኑ ጋር ተቈራኝተው ከእውነት ይልቅ ስሕተትን ይይዛሉ፤ ቍርባን ከማይቀበሉ ጋር ያለውን ኅብረት እንደ ተገቢ ይቈጥሩታል፤ እግዚአብሔርን በሰዎች ላይ ባያምኑም ሰዎችን በእግዚአብሔር ላይ ያምናሉ።
34. ከእንደዚህ ያሉ ሰዎች በተቻላችሁ መጠን ሽሹ፤ ከእነርሱ ጎጂ ግንኙነት ጋር የሚጣበቁትንም ሰዎች በሚያድን ጥንቃቄ ራቋቸው። ቃላቸው እንደ ጭንቁር ይባላል፤ ንግግራቸው እንደ ተላላፊ በሽታ ይሰፋል፤ ጎጂውና መርዘኛው ማባበላቸው ከስደት ራሱ የባሰ ይገድላል። በእንዲህ ያለ ሁኔታ ሊያስተሰርይ የሚችል ንስሓ ብቻ ነው የሚቀረው። ስለ ወንጀል የሚደረገውን ንስሓ የሚያስወግዱ ግን የማስተስረያን መንገድ ይዘጋሉ። ስለዚህ በአንዳንዶች ችኩልነት ሐሰተኛ ደኅንነት ሲሰጥ ወይም ሲታመንበት፥ የእውነተኛ ደኅንነት ተስፋ ይወሰዳል።
35. እናንተ ግን፥ የተወደዳችሁ ወንድሞች፥ ፍርሃታችሁ ወደ እግዚአብሔር ዘወትር የተዘጋጀ፥ አእምሮአችሁም በውድቀት መካከል ቢሆንም መከራውን የሚያስብ፥ በንስሓና በኀዘን ኃጢአታችሁን ተመልከቱ፤ የሕሊናችሁን እጅግ ከባድ ኃጢአት እወቁ፤ የጌታን ምሕረት ተስፋ ሳትቈርጡ፥ ይቅርታውንም ወዲያው ሳትጠይቁ፥ ኃጢአታችሁን ታስተውሉ ዘንድ የልባችሁን ዓይኖች ክፈቱ። እግዚአብሔር በአባት ፍቅር ሁልጊዜ ቸርና መሐሪ እንደ ሆነ መጠን፥ በዚያው መጠን በፈራጅ ግርማ ሊፈራ ይገባዋል። እጅግ እንደ በደልን እንዲሁ እጅግ እናልቅስ። ለጥልቅ ቁስል ረጅምና ጥንቁቅ ሕክምና አይጓደልበት፤ ንስሓው ከኃጢአቱ አያንስ። በማይታመን ቃል የካዳችሁት፥ ከእርሱ ይልቅ ዓለማዊ ሀብታችሁን የመረጣችሁበት፥ ቤተ መቅደሱንም በረከሰ መነካካት ያረከሳችሁበት ጌታ ቶሎ ብሎ የሚታረቅ ይመስላችኋልን? አምላካችሁ እንዳልሆነ የተናገራችሁለት እርሱ በቀላሉ የሚምራችሁ ይመስላችኋልን? አብልጣችሁ በትጋት መጸለይና መለመን ይገባችኋል፤ ቀኑን ሁሉ በኀዘን ልታሳልፉ፥ ሌሊቶችንም በትጋትና በልቅሶ ልታሳልፉ፥ ጊዜያችሁንም ሁሉ በዋይታ ልቅሶ ልትይዙ፥ በምድር ላይ በግንባራችሁ ተዘርግታችሁ ከአመድ ጋር ልትጣበቁ፥ በማቅና በጕድፍ ልትከበቡ ይገባችኋል፤ የክርስቶስን ልብስ ካጣችሁ በኋላ አሁን ያለ ልብስ ለመሆን ልትፈቅዱ፥ ከዲያብሎስ ምግብ በኋላ ጾምን ልትመርጡ፥ ኃጢአት በሚነጻበት በጽድቅ ሥራ ልትተጉ፥ ነፍሳት ከሞት በሚድኑበት ምጽዋት አዘውትራችሁ ልትሰጡ ይገባችኋል። ባላጋራው ከእናንተ የወሰደውን ክርስቶስ ይቀበለው፤ ያታለላችሁና ያሸነፋችሁ ሀብት አሁን ሊያዝም ሊወደድም አይገባውም። ስለዚህ ሀብት እንደ ጠላት ሊሸሽ፥ እንደ ወንበዴ ሊራቅ፥ ባለቤቶቹም እንደ ሰይፍና እንደ መርዝ ሊፈሩት ይገባል። የቀረውም ሀብት ወንጀሉና በደሉ የሚዋጅበት እንዲሆን ብቻ ይጠቅም። መልካም ሥራ ሳይዘገይ በብዛትም ይደረግ፤ ሀብታችሁ ሁሉ ቁስላችሁን ለመፈወስ ይዋል፤ ከሀብታችንና ከንብረታችን ለሚፈርድብን ለጌታ እናበድር። በሐዋርያት ዘመን እምነት እንዲሁ አበበ፤ የምእመናን የመጀመሪያው ሕዝብ የክርስቶስን ትእዛዛት እንዲሁ ጠበቀ፤ ፈጣኖች ነበሩ፥ ለጋሾችም ነበሩ፤ በሐዋርያት እንዲከፋፈል ያላቸውን ሁሉ ሰጡ፤ ይሁን እንጂ እንደዚህ ያሉትን ዓይነት ኃጢአቶች የሚዋጁ ሰዎች አልነበሩም።
36. ሰው በፍጹም ልቡ ቢጸልይ፥ በእውነተኛ የንስሓ ልቅሶና እንባ ቢያቃስት፥ በጽድቅና በማያቋርጥ ሥራ ጌታን ወደ ኃጢአቱ ይቅርታ ቢያዘነብል፥ ምሕረቱን በእነዚህ ቃላት የገለጠው እርሱ እንደነዚህ ላሉት ሊራራላቸው ይችላል፦ «ተመልሳችሁ ስታለቅሱ በዚያን ጊዜ ትድናላችሁ፥ የት እንደ ነበራችሁም ታውቃላችሁ።» ደግሞም፦ «የሚሞተው ሰው ሞት ደስ አያሰኘኝም፥ ይላል ጌታ፥ ነገር ግን ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ ነው።» ነቢዩ ኢዩኤልም በጌታ በራሱ ምክር የጌታን ምሕረት ሲገልጥ እንዲህ ይላል፦ «ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ እርሱ መሐሪና ይቅር ባይ፥ ታጋሽም፥ ምሕረቱም የበዛ ነውና፤ ባመጣውም ክፉ ነገር ይጸጸታል።» እርሱ ምሕረት ሊያደርግ ይችላል፤ ፍርዱን ሊመልስ ይችላል። ንስሓ የሚገባውን፥ የሚደክመውን፥ የሚለምነውን ኃጢአተኛ በምሕረቱ ይቅር ሊለው ይችላል። ስለ እንደነዚህ ያሉት ሰማዕታት የለመኑትን ወይም ካህናት ያደረጉትን ሁሉ እንደ ተቀባይነት ያለው ሊቈጥረው ይችላል። ወይም ማንም በገዛ ማስተስረያው አብልጦ ቢያነሣሣው፥ ቁጣውን ቢያበርድ፥ የተቈጣውን የእግዚአብሔርን መቅሠፍት በጽድቅ ልመና ቢያበርድ፥ የተሸነፉት ሰዎች እንደ ገና የሚታጠቁበትን የጦር ዕቃ እንደ ገና ይሰጣል፤ የታደሰው እምነት የሚበረታበትን ኃይል ይመልሳል፥ ያጸናልም። ወታደሩም ትግሉን እንደ ገና ይሻል፤ ውጊያውን ይደግማል፥ ጠላትን ይገጥማል፤ እንዲያውም በዚያው በደረሰበት መከራ ለጦርነት የበለጠ ደፋር ይሆናል። እንዲህ ለእግዚአብሔር ያስተሰረየ፥ ስለ ሥራው በንስሓ፥ ስለ ኃጢአቱም በኀፍረት ከውድቀቱ ኀዘን የተነሣ የበለጠ በጎነትንና እምነትን ያገኘ ሰው፥ በጌታ ተሰምቶና ተረድቶ በቅርቡ ያሳዘናትን ቤተ ክርስቲያን ደስ ያሰኛታል፤ አሁንም ከጌታ ዘንድ ይቅርታን ብቻ ሳይሆን አክሊልንም ያገኛል።