ምዕራፍ 20 · 14 ደቂቃ ንባብ · 18 ደቂቃ ማዳመጥ
ከክርስቶስና ከሕዝቡ ጋር ያለ ኅብረት
በሜንቶን በቍርባን አገልግሎት ላይ የቀረበ መልእክት። «የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? አንድ እንጀራ ስለ ሆነ፥ እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን፤ ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።»—1ኛ ቆሮንቶስ 10፥16፣17።
ከክርስቶስና ከሕዝቡ ጋር ያለ ኅብረት።
ጽሑፉን በተሻሻለው ትርጕም እንደ ተሰጠው አነብላችኋለሁ፤ «የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ያለ አንድ ኅብረት አይደለምን?» ይህም ማለት፥ የክርስቶስን ደም ኅብረት የምንገልጽበት አንዱ መንገድ አይደለምን? ማለት ነው። «እንጀራው»፥ ወይም በኅዳጉ እንዳለው «የምንቆርሰው ሙሉ ዳቦ፥ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ያለ አንድ ኅብረት አይደለምን? ብዙዎች የሆንን እኛ አንድ ዳቦ፥ አንድ ሥጋ ነንና፤ ሁላችን ያን አንዱን ዳቦ እንካፈላለንና።» «ሙሉ ዳቦ» የሚለው ቃል ሐዋርያው ሊገልጸው ያሰበውን የአንድነት አሳብ ይበልጥ ግልጽ አድርጎ ለማውጣት ይረዳል።
አንዳንዶች ይህ ቀላል የጌታ ራት ሥርዓት አንድ ዓይነት አስማታዊ፥ ወይም ቢያንስ ሥጋዊ ኃይል እንዳለው፥ ስለዚህም ይህን እንጀራና ወይን በመብላትና በመጠጣት ብቻ ሰዎች የክርስቶስ ሥጋና ደም ተካፋዮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰባቸው የሚያሳዝን እውነት ነው። እንዲህ ያለ ግልጽ ምልክት በስግደቶች፥ በጌጣጌጦችና በልዩ ልዩ የሙያ ቃላት እንዲህ መወሳሰቡ የሚያስደንቅ ነው። ጌታ ከአሥራ ሁለቱ ጋር በማዕድ በመቀመጡና በሮማ ማኅበር ቅዳሴ መካከል ትንሽ መመሳሰል እንኳ ማየት የሚችል ሰው አለን? የመጀመሪያው ሥርዓት በላዩ በተጫነው ሥርዓተ አምልኮ ውስጥ ጠፍቷል። ኢየሱስ ኅብረትን ባሰበበት ስፍራ አጉል እምነት ምሥጢረ ቍርባንን አስገኝቷል። እስከ ሮማ ድረስ መሄድ የማይፈልጉ ብዙዎችም እንኳ ስለዚህ ቀላል ግብዣ ጨለማና ስውር ምሥጢር እንደ ሆነ አድርገው ይናገራሉ። የልጆችን እንጀራ ወደ ድንጋይ ለመለወጥ ልዩ ልዩ አስቸጋሪ ቃላትን ይጠቀማሉ። የጌታ ራት ሳይሆን «ኤውካሪስት» ይሉታል፤ በፊታችን የምናየው ሳሕን ሳይሆን «ፓቴን» ነው፤ ጽዋው «ካሊስ»፥ ማዕዱም «መሠዊያ» ነው። እነዚህ የአጉል እምነት ቅርፊቶች ናቸው፤ በእነርሱም የተባረከው የክርስቶስ ሥርዓት እንደ ገና ተሸፍኖ ሊጣመም ይችላል።
ይህ ራት ምን ማለት ነው? ኅብረት ማለት ነው፤ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት፥ እርስ በርሳችንም ኅብረት።
ኅብረት ምንድር ነው? በእንግሊዝኛው «ኮሙኒየን» የሚለው ቃል በቀላሉ «ዩኒየን»፥ ማለትም አንድነት፥ እና «ጋር» ማለት ወደ ሆነው «ኮም» ወደሚለው ቅድመ ቅጥያ ይከፈላል፤ ትርጕሙም ከአንድ ነገር ጋር አንድነት ነው። ስለዚህ ኅብረትን ልንደሰትበት የምንችለው አስቀድመን ከክርስቶስና ከቤተ ክርስቲያኑ ጋር አንድነትን ስናገኝ ብቻ ነው። አንድነት የኅብረት መሠረት ነው። በልብ፥ በነፍስና በሕይወት ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆን አለብን፤ ወደ ሞቱ ተጠምቀን፥ በሕይወቱ ሕያዋን ሆነን፥ እንዲሁም የአካሉ ብልቶች ሆነን እርሱ ራስ ከሆነላት ከመላዋ ቤተ ክርስቲያን ጋር አንድ መሆን አለብን። ከክርስቶስ ጋር አንድ እስክንሆን ድረስ ከእርሱ ጋር ኅብረት ሊኖረን አይችልም፤ ከቤተ ክርስቲያንም ጋር ሕያው አንድነት እስኪኖረን ድረስ ከእርስዋ ጋር ኅብረት ሊኖረን አይችልም።
1ኛ. የጌታ ራት ትምህርት ይህ ነው፤ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት የምናደርግባቸው ብዙ መንገዶች ቢኖሩንም፥ ክርስቶስን መድኃኒታችን አድርገን ወደ ነፍሳችን መቀበል ከእርሱ ጋር ኅብረት የምናደርግበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ነው።
ወዳጆች ሆይ፥ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት የምናደርግባቸው ብዙ መንገዶች አሉን አልሁ፤ እንዲህ መሆኑን ላሳያችሁ።
ከጌታ ኢየሱስ ጋር በግል በመነጋገር ኅብረት የእኛ ይሆናል። እኛ በጸሎት እናነጋግረዋለን፤ እርሱም በቃሉ በኩል ያነጋግረናል። አንዳንዶቻችን ከሚስታችን ወይም ከልጃችን ይልቅ ከክርስቶስ ጋር አዘውትረን እንነጋገራለን፤ ከኢየሱስ ጋር ያለን ኅብረትም ከቅርብ ወዳጃችን ጋር ካለን ወዳጅነት ይልቅ የጠለቀና የተሟላ ነው። በማሰላሰልና አብሮት በሚመጣው ምስጋና ከተነሣው ጌታችን ጋር እንነጋገራለን፤ እርሱም በመንፈስ ቅዱሱ በአእምሮአችን ውስጥ አዲስ አሳብና ስሜት በመፍጠር ይመልስልናል። አንዳንድ ጊዜ በጸሎት ውስጥ ምንም ልናገር እንደማልችል ሲሰማኝ፥ ዝም ብዬ ተቀምጬ ወደ ላይ መመልከት እወዳለሁ፤ ያን ጊዜ እምነት ውዴን በመንፈስ ታያለች፥ በአእምሮም ጥልቅ ጸጥታ ውስጥ ድምፁን ትሰማለች። በዚህ ዓይነት ማንኛውም ቃል ሊገልጸው ከሚችለው በላይ የቀረበ ግንኙነት ከኢየሱስ ጋር አለን። ነፍሳችን በኢየሱስ ፍቅር ሙቀት ሥር ትቀልጣለች፥ በምላሹም የራስዋን ፍቅር ወደ ላይ ትወረውራለች። የማልም ወይም ባልተለመደ የመንፈስ ተመስጦ ትዝታ የተወሰድሁ አይምሰላችሁ፤ አይደለም፤ ታማኝ ነፍስ ቀኑን ሙሉ ከጌታ ኢየሱስ ጋር ልትነጋገር እንደምትችል፥ እርሱም አሁንም በሰዎች መካከል በሥጋ የሚኖር ያህል ከእርሱ ጋር እውነተኛ ኅብረት ሊኖራት እንደሚችል አረጋግጣለሁ። ይህ ነገር የመጣልኝ በጆሮ መስማት ሳይሆን በራሴ የግል ተሞክሮ ነው፤ ኢየሱስ ለዓለም ሳይሆን ለሕዝቡ ራሱን እንደሚገልጥ በእርግጥ አውቃለሁ።
አቤት፥ በማዕዱ ላይ እንጀራና ወይን በሌለ ጊዜ እንኳ በቅዱሳን አማኝና በውዴ መካከል ምንኛ ጣፋጭ ኅብረት ብዙ ጊዜ ይኖራል! መንፈስ ራሱ የታደሰውን ሰው ልብ ይስባልና፥ ልቡም ኢየሱስን ተከትሎ ይሮጣል፤ ጌታ ራሱም ለናፋቂው መንፈስ ይገለጣል። በእውነትም ኅብረታችን ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው። ይህን ደስ የሚያሰኝ ንግግር ትደሰቱበታላችሁን?
ቀጥሎም በአሳቡ፥ በአመለካከቱና በዓላማው ከክርስቶስ ጋር ኅብረት አለን፤ እንደ አቅማችንና እንደ ቅድስናችን መጠን አሳቡ አሳባችን ነውና። አማኞች ነገሮችን ኢየሱስ እንደሚያያቸው ያያሉ፤ እርሱን ደስ የሚያሰኘው እነርሱን ደስ ያሰኛቸዋል፥ እርሱን የሚያሳዝነውም እነርሱንም ያሳዝናቸዋል። ለምሳሌ፥ ከአሳባችን ሁሉ የሚበልጠውን ርእስ ተመልከቱ፤ አሳባችን የክርስቶስን አሳብ የሚመስል እንደ ሆነ እዩ። እርሱ በአብ ደስ ይለዋል፥ አብንም ማክበር ይወዳል፤ እኛስ እንዲሁ አይደለንምን? አብ የነፍሳችን ደስታ ማእከል አይደለምን? የስሙን ድምፅ ብቻ ስንሰማ ደስ አይለንምን? መንፈሳችን «አባ አባት» ብሎ አይጮኽምን? እንግዲህ ኢየሱስ ወደ አብ የሚሰማውን እኛም እንደምንሰማው ግልጽ ነው፤ ስለዚህም ከእርሱ ጋር እጅግ እውነተኛ ኅብረት አለን። ይህ አንድ ምሳሌ ብቻ ነው፤ ማሰላሰላችሁ ከኢየሱስ ጋር አንድ ዓይነት አሳብ የምናስብባቸውን ብዙ ልዩ ልዩ ርእሶች ያመጣላችኋል። እንግዲህ የፍርድ፥ የአመለካከትና የዓላማ አንድነት የኅብረት አውራ ጎዳና ነው፤ አዎን፥ ራሱ ኅብረት ነው።
በስሜታችንም ደግሞ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት አለን። በመንገድ ላይ የስድብ ቃል በሰማችሁ ጊዜ ቅዱስ ድንጋጤ ተሰምቷችሁ አያውቅምን? ኢየሱስ ኃጢአትን ባየ ጊዜና በራሱ ላይ በተሸከመው ጊዜ እንዲሁ ተሰምቶታል፤ ልዩነቱ እርሱ ከእናንተ ይልቅ ወሰን በሌለው መጠን መሰማቱ ብቻ ነው። ኃጢአተኞችን ስትመለከቱ ልታለቅሱላቸው እንደሚገባ ተሰምቷችሁ አያውቅምን? እነዚያ ቅዱስ እንባዎች ናቸው፤ ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌም ባዘነ ጊዜ ካፈሰሳቸው እንባዎች ጋር አንድ ዓይነት ይዘት አላቸው። አዎን፥ ለእግዚአብሔር ባለን ቅናት፥ ኃጢአትን በመጥላታችን፥ ሐሰትን በመጸየፋችን፥ ለሰዎችም በምናደርገው ርኅራኄ ከኢየሱስ ጋር እውነተኛ ኅብረት አለን።
ከዚህም በላይ በብዙ ሥራዎቻችን ከክርስቶስ ጋር ኅብረት አድርገናል። አላዋቂዎችን ለማስተማር ሞክራችሁ ታውቃላችሁን? ኢየሱስ ይህን አደረገ። አስቸጋሪ ሆኖ አገኛችሁትን? ኢየሱስም እንዲሁ አገኘው። ወደ ኋላ ያፈገፈገውን ለመመለስ ታግላችሁ ታውቃላችሁን? እንግዲያስ የጠፋውን አንድ በግ ለማግኘት ወደ ምድረ በዳ ከሚቸኵለው፥ ከሚያገኘው፥ በትከሻውም ላይ ከሚሸከመውና ደስ ብሎት ወደ ቤት ከሚያመጣው ከመልካሙ እረኛ ጋር ኅብረት ነበራችሁ። ስለ አንዲት ነፍስ ሌሊትና ቀን በእንባ ተግታችሁ ታውቃላችሁን? እንግዲያስ የሁላችንን ስም በተሰበረው ልቡ ላይ ከተሸከመው፥ መታሰቢያቸውንም በተወጉት እጆቹ ላይ ከያዘው ከእርሱ ጋር ኅብረት ነበራችሁ። አዎን፥ ራስን በመካድ፥ በልግስና፥ በበጎ አድራጎትና በአምልኮ ሥራዎች፥ መልካም እያደረገ ከዞረው ከእርሱ ጋር ወደ ኅብረት እንገባለን። የጠብን ውስብስብ ለመፍታትና በጠላትነት ባሉ ሰዎች መካከል ሰላምን ለማድረግ በምንሞክርበት ጊዜ ሁሉ ታላቁ ሰላም ፈጣሪ ያደረገውን እያደረግን ነን፤ ከሰላም ጌታና ሰጪ ጋርም ኅብረት አለን። በእርግጥም ለሰዎች ባለው የፍቅር ዕቅዱ ከጌታ ኢየሱስ ጋር በምንተባበርበት ስፍራ ሁሉ ከእርሱ ጋር እውነተኛና ሕያው ኅብረት አለን።
ከመከራችንም ጋር እንዲሁ ነው። አንዳንዶቻችን በመከራ ውስጥ ከጌታ ኢየሱስ ጋር ሰፊ ኅብረት ነበረን። «ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ»፤ ወዳጁን አጣ፥ እኛም እንዲሁ አጥተናል። ኢየሱስ በሰዎች ልብ ድንዳኔ አዘነ፤ ያን ኀዘን እናውቀዋለን። ተስፋ የሚጣልበት ጐበዝ ፊቱን አዙሮ ወደ ዓለም በተመለሰ ጊዜ ኢየሱስ እጅግ አዘነ፤ ያን ኀዘን እናውቀዋለን። ርኅሩኅ ልብ ያላቸውና ለሌሎች የሚኖሩ ሰዎች ወደ «የሕማም ሰው» ተሞክሮ በቀላሉ ይገባሉ። የሐሜትን ቍስል፥ የትዕቢተኞችን ነቀፋ፥ የጠባብ አክራሪዎችን መርዝ፥ የሐሰተኞችን ክሕደትና የእውነተኞችን ድካም በመጠናችን አውቀናል፤ በዚህም ከጌታችን ከኢየሱስ ጋር ኅብረት አድርገናል።
ይህ ብቻም አይደለም፤ በደስታውም ከመለኮታዊ ጌታችን ጋር ነበርን። ከጌታ ኢየሱስ የበለጠ ደስተኛ ሰው ፈጽሞ የኖረ አይመስለኝም። በትክክል «የሕማም ሰው» ተብሎ ተጠራ፤ ነገር ግን በማይነቀፍ እውነት «የደስታ ሰው» ተብሎ ሊጠራ ይችል ነበር። ደቀ መዛሙርቱን በጠራ ጊዜና እነርሱም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ፥ ፈውስንና እፎይታን በሰጠ ጊዜ፥ ለንስሐ ገቢዎች ይቅርታን በሰጠና በአማኞች ላይ ሰላምን እፍ ባለ ጊዜ ደስ ብሎት መሆን አለበት። በጉን የማግኘትና ብሩን ከትቢያ ውስጥ የማውጣት ደስታ የእርሱ ነበረ። ሥራው ደስታው ነበረ፤ ስለ እርሱም ውርደቱን ንቆ መስቀሉን የታገሠበት ታላቅ ደስታ ነበረ። በጎ ማድረግ ለአፍቃሪ ልቦች ደስታ ነው፤ ብዙ ሕመም ባስከፈለ መጠን ደስታው ይበልጣል። ደግ ሥራዎች ደስተኞች ያደርጉናል፤ በእንዲህ ያለ ደስታም ከኢየሱስ ታላቅ ልብ ጋር ኅብረትን እናገኛለን።
እንዲህ ወደ ጌታ የምትደርሱባቸውን የአጌት መስኮቶችና የቀይ ዕንቍ በሮች ዝርዝር ሰጥቻችኋለሁ፤ የጌታ ራት ሥርዓት ግን ከሁሉም የሚበልጥ መንገድ ያሳያል። ለኅብረት ከሁሉ ይበልጥ የሚቀርብና ከሁሉ ይበልጥ የሚሠራ ዘዴ ነው። ጌታ ኢየሱስን መድኃኒታችን አድርገን በመቀበል ከእርሱ ጋር ኅብረት የምናደርገው እዚህ ነው። በደለኞች የሆንን እኛ ማስተስረያውን የመሥዋዕት መንጻታችን አድርገን እንቀበላለን፤ ለዚህም ምልክት ይህን እንጀራ እንበላለን፥ ይህንም ጽዋ እንጠጣለን። አንድ ሰው «ኧረ፥ ወደ ክርስቶስ መቅረብ እንደምችል አይሰማኝም፤ እርሱ እጅግ ከፍ ያለና ቅዱስ ነው፥ እኔ ግን ምስኪን ኃጢአተኛ ብቻ ነኝ» ይላል። ልክ ነው። በዚያው ምክንያት ለልቡ እጅግ ቅርብ በሆነው ነገር ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ልታደርግ ትችላለህ፤ እርሱ መድኃኒት ነው፥ መድኃኒት ለመሆንም የሚድን ኃጢአተኛ መኖር አለበት። አንተ ያ ሰው ሁን፤ ክርስቶስና አንተም ወዲያውኑ በአንድነትና በኅብረት ትሆናላችሁ፤ እርሱ ያድናል፥ አንተም ትድናለህ፤ እርሱ ይቀድሳል፥ አንተም ትቀደሳለህ፤ ሁለቱም እንዲህ አንድ ይሆናሉ። ይህ ማዕድ ታላቁን መሥዋዕቱን በፊትህ ያቀርባል። ኢየሱስ አቅርቦታል፤ ትቀበለዋለህን? ምንም እንድታመጣ አይጠይቅህም፥ አንዲት የደም ጠብታ፥ አንዳች የሥጋ ሕመም አይጠይቅህም፤ ሁሉ እዚህ አለ፤ የአንተ ድርሻ መጥተህ መካፈል ነው፤ ልክ ጥንት መሥዋዕት አቅራቢው ካመጣው የደኅንነት መሥዋዕት ተካፍሎ ከእግዚአብሔርና ከካህኑ ጋር ግብዣ እንደ በላ። ለክርስቶስ ብትሠራ ያ በእርግጥ ከእርሱ ጋር አንድ ዓይነት ኅብረት ይሆናል፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ እርሱን ወደ ውስጣዊ ነፍሳችሁ የመቀበል ኅብረት ለሟች ሰው ሊገኝ ከሚችለው ኅብረት ሁሉ እጅግ የቀረበና የጠበቀ ነው። እኛና ክርስቶስ ለአንድ ዓላማ አብረን ስንሠራ የአገልግሎት ኅብረት እጅግ የተከበረ ነው፤ በክርስቶስ ልብ ላይ የተቀረጹት ፊደላት በልባችን ላይ ሲቀረጹ የመከራ ኅብረት እጅግ አስተማሪ ነው፤ ክርስቶስን የምትቀበልና በክርስቶስ የምትቀበል የነፍስ ኅብረት ግን ከማንኛውም ሌላ ኅብረት ይበልጥ የቀረበ፥ ይበልጥ ሕያው፥ ይበልጥም አስፈላጊ ነው።
እንዲህ ያለ ኅብረት ዘላለማዊ ነው። አሁን የበላሁትን ቍራሽ እንጀራ ከእንግዲህ ወዲህ በምድር ላይ ያለ ምንም ኃይል ከእኔ ሊወስደው አይችልም፤ ወደ ደም፥ ወደ ነርቭ፥ ወደ ጡንቻና ወደ አጥንት ወደሚለወጥበት ስፍራ ሄዷል። በውስጤ ነው፥ የእኔም ክፍል ሆኗል። ያቺ የወይን ጠብታ በደም ሥሮቼ ውስጥ ፈስሳለች፥ የሕልውናዬም ክፍል ሆናለች። እንዲሁም ኢየሱስን በእምነት መድኃኒቱ አድርጎ የሚቀበል ከእርሱ የማይወሰድበትን መልካም ዕድል መርጧል። ክርስቶስን ወደ ውስጣዊ ክፍሉ ተቀብሎታል፤ በምድር ያሉ ሰዎች ሁሉና በሲኦል ያሉ አጋንንት ሁሉ ክርስቶስን ከእርሱ ማውጣት አይችሉም። ኢየሱስ «የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል።» ይላል። ኢየሱስን በቅንነት ወደ ልባችን በመቀበላችን በእኛና በጌታ መካከል የማይፈታ አንድነት ይመሠረታል፤ ይህም በእርስ በርስ ኅብረት ይገለጣል። ለተቀበሉት ሁሉ፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ ይህን ኅብረት ሰጣቸው።
2ኛ. አሁን ደግሞ የኅብረትን ሌላ ገጽታ፥ ማለትም የእውነተኛ አማኞችን እርስ በርስ ኅብረት መመልከት አለብኝ። እርስ በርሳችን ኅብረት የምናደርግባቸው ብዙ መንገዶች አሉን፤ ነገር ግን አንዱን ክርስቶስ በአንድ መንገድ በጋራ እንደ መቀበል ያለ የእርስ በርስ ኅብረት መንገድ የለም። ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ኅብረት የሚያደርጉባቸው ብዙ መንገዶች አሉ አልሁ፤ እነዚህንም የኅብረት በሮች በሰፊው ልጠቅሳቸው እወዳለሁ።
በፊት የሄድንበትን መንገድ ያህል እንደ ገና ልሂድበት። በቅዱስ ንግግር ኅብረት እናደርጋለን። ከዚህ የበለጠ ቢኖረን እመኛለሁ። እግዚአብሔርን የሚፈሩ እርስ በርሳቸው አዘውትረው የሚነጋገሩበት ጊዜ ነበረ፤ አሁን ግን ይበልጥ የሚነጋገሩት እርስ በርሳቸው ላይ ይሆናል ብዬ እፈራለሁ። ብዙ ጊዜ ፍቅር በወንድም እጅ ቈስሎ ደም እየፈሰሰው መተኛቱ የሚያሳዝን ነገር ነው። ያን ያህል ባንከፋም እንኳ፥ ብዙ ጊዜ ወደ ኋላ የምንል ዝምተኞች ነን፤ በዚህም ጠቃሚ ንግግርን እናጣለን። የደሴት ሰዎች ዓይነት ቍጥብነታችን ብዙ ጊዜ አንዱ ክርስቲያን ከሌላው አጠገብ ፈጽሞ ተገልሎ እንዲቀመጥ አድርጎታል፤ ሁለቱም ግን አንዱ በሌላው ጓደኝነት ደስ ይሰኙ ነበር። የአንድ ቤተ ሰብ ልጆች እርስ በርሳቸው እስኪተዋወቁ መጠበቅ አያስፈልጋቸውም፤ ከዚህ አንድ እንጀራ በልተን የወንድማማችነትን ምልክት ሰጥተናል ተቀብለናልም፤ ስለዚህ ከዝምድናችን ጋር የሚስማማ ነገር እናድርግ፥ በሚቀጥለውም ጊዜ ስንገናኝ ወደ ቅዱስ ንግግር እንግባ። በብዙ ሁኔታዎች የክርስቲያን ወንድማማችነት በአምልኮ ስፍራ ውስጥ ጀምሮ እዚያው ያበቃል ብዬ እፈራለሁ። በእኛ መካከል እንዲህ አይሁን። ኢየሱስ ማእከሉ በሆነበት ክበብ ውስጥ ማኅበራችንን ማግኘት ደስታችን ይሁን፤ የኢየሱስ ወዳጆች የሆኑትንም ወዳጆቻችን እናድርግ። አዘውትረን በአንድነት በመጸለይና በማመስገን፥ በመንፈስም የተማርነውን እርስ በርሳችን በማካፈል፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እርስ በርሳችን ኅብረት ይኖረናል።
ክርስቲያኖች ሁሉ በአሳባቸው ኅብረት እንዳላቸው እርግጠኛ ነኝ። በወንጌል ዋና ዋና ነገሮች አንድ ዓይነት እናስባለን፤ ስለ እግዚአብሔር፥ ስለ ክርስቶስ፥ ስለ ኃጢአትና ስለ ቅድስና ባለን አሳብ እኩል እንራመዳለን፤ የጌታችንን መንግሥት ለማስፋፋት ባለን ብርቱ ምኞትም እንደ አንድ ነን። መንፈሳዊ ሕይወት ሁሉ አንድ ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ በሰዎች ነፍስ ውስጥ የሚያስነሣቸው አሳቦች እርስ በርሳቸው ፈጽሞ አይቃረኑም። ሃይማኖተኛ ነን ባዮች ሁሉ አሳብ ይስማማል አልልም፤ ነገር ግን በሁሉም ክፍሎችና በሁሉም ዘመናት በእውነት ዳግመኛ የተወለዱ ሰዎች አእምሮ እርስ በርሱ እንደሚስማማ አረጋግጣለሁ፤ ይህም ስምምነት የሚያስተውሉትን ብዙ ጊዜ በደስታ ያስገርማቸዋል። በስም ብቻ ክርስቲያን የሆኑትን አንዱን ወገን ከሌላው የሚለዩ ምልክቶች ከሃይማኖት ከስም በቀር ምንም ለሌላቸው እጅግ ጥልቅና ሰፊ ናቸው፤ ሕያዋን አማኞች ግን እምብዛም አያስተውሏቸውም። የሜዳ ከብቶችን የሚለዩ ድንበሮች ለሰማይ ወፎች መለያያ አይደሉም። አእምሮአችን፥ አሳባችን፥ ምኞታችንና ተስፋችን በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ነው፤ በዚህም ኅብረት አለን።
የተወደዳችሁ ወዳጆች ሆይ፥ ስሜታችን ሌላው የንጉሥ የኅብረት ጎዳና ነው። ተቀምጣችሁ ተሞክሮአችሁን ትናገራላችሁ፤ እኔም የእኔን እየተናገራችሁ እንደ ሆነ አስቤ ፈገግ እላለሁ። አንዳንድ ጊዜ አንድ ወጣት አማኝ ማንም እንዲህ ያለ ታላቅ ውጊያ ታግሦ እንደማያውቅ እያሰበ ስለ ፈተናውና ስለ መከራው አሳዛኝ ታሪክ ያብራራል፤ እርሱ ግን የሚገልጸው በሐጅ መንገድ የሚሄዱትን ሰዎች የተለመደ ገጠመኝ ብቻ ነው፤ ሁላችንም ከእርሱ ጋር ኅብረት እያደረግን ነን። ስለ ጌታችን አብረን ስንነጋገር አንስማማምን? ስለ አባታችንና ከእኛ ጋር ስላደረገው ነገር ሁሉ ስንናገር አንድ አይደለንምን? ስናለቅስም፥ ስንቃትትም፥ ስንዘምርም፥ ደስ ሲለንም ሁላችን ዘመዳሞች አይደለንምን? ሰማያዊ ጣቶች በልባችን ውስጥ ያሉትን አውታሮች ሲነኩ አንድ ዓይነት ድምፅ ያወጣሉ፤ የአንዱ ሠሪ ሥራዎች ነንና፥ ለአንድ ምስጋናም ተቃኝተናል። በእግዚአብሔር እውነተኛ ሕዝብ ሁሉ መካከል እውነተኛ ስምምነት አለ፤ ክርስቲያኖች በክርስቶስ አንድ ናቸው።
በሥራዎቻችንም ደግሞ እርስ በርሳችን ኅብረት አለን። ሰዎችን ለማዳን በመሞከር አንድ እንሆናለን፤ እንደምንሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ኃጢአተኞችን በማስተማር፥ በማስጠንቀቅ፥ በመጋበዝና ወደ ኢየሱስ እንዲመጡ በማግባባት እንተባበራለን። የሕይወት አገልግሎታችን አንድ ነው፤ ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ ነን። አንዱን ምኞት እንኖራለን፤ «መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን።»
በእርግጥ በመከራችን እርስ በርሳችን ብዙ ኅብረት አለን። በዚህች ሰዓት የማንራራለት ድሀ፥ የታመመ ወይም ተስፋ የቈረጠ ቅዱስ በምድር ላይ የለም፤ የአንድ አካል ብልቶች ነንና፥ የክርስቶስም መከራ ተካፋዮች ነን። እንዲህ ማለት እንደምንችል ተስፋ አደርጋለሁ፤
«ከመንጋህ መካከል ልመግበው
የምንቀው ጠቦት አለን?
በፊቱ ቆሜ ጉዳይህን ለመሟገት
የምፈራው ጠላት አለን?»
የለም፤ አብረን መከራ እንቀበላለን፥ አንዳችን የሌላውን ሸክም እንሸከማለን፥ እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ እንፈጽማለን። ይህን ባናደርግ በገዛ እምነታችን የምንጠራጠርበት ምክንያት አለን፤ ብናደርገው ግን እርስ በርሳችን ኅብረት አለን።
በደስታችንም ኅብረት እንዳለን ተስፋ አደርጋለሁ። አንዱ ደስተኛ ነውን? አንቀናበትም፥ ይልቁንም ከእርሱ ጋር ደስ ይለናል። ምናልባት ይህ ሃይማኖተኛ ነን በሚሉት ዘንድ መሆን እንደሚገባው ያህል የተስፋፋ አይደለም። ሌላው ስለ ተሳካለት ወዲያውኑ ደስ ይለናልን? የሌላው ኮከብ ከእኛ ይልቅ ቢያበራ በብርሃኑ ደስ ይለናልን? አሥር መክሊት ያለውን ወንድም ስናገኝ እኛን እንዲረዳ እንዲህ ያለ ሰው ስለ ተሰጠን ራሳችንን እናመሰግናለን ወይስ የቻልነውን ያህል እናሳንሰዋለን? የባሕርያችን ብልሹነት እንዲህ ነውና ሌሎች ወደ ኋላ ቢተዉን በእድገታቸው በቀላሉ ደስ አይለንም፤ ነገር ግን ራሳችንን ለዚህ ማሠልጠን አለብን። ሰው ፈጥኖ ተቀምጦ በወዳጁ ኀዘን ይራራል፤ ተከብሮና ተወድሶ ቢያየው ግን እንደ ተቀናቃኝ ሊቈጥረው ይቀናዋል፥ ከእርሱም ጋር በቀላሉ ደስ አይለውም። ይህ ሊሆን አይገባም፤ ያለ ድካም በወንድማችን ደስታ ደስተኞች ልንሆን ይገባናል። ብንታመም፥ ብዙዎች በጽኑ ጤና ላይ መሆናቸው መጽናናታችን ይሁን፤ ብንዝል፥ ሌሎች በጌታ ብርቱዎች በመሆናቸው ደስ ይበለን። እንዲህም በላይ ፍጹማን እንደ ሆኑት ያለ ደስ የሚያሰኝ ኅብረትን እንደሰታለን።
እነዚህን የክርስቲያን ኅብረት መንገዶች ሁሉ አንድ ላይ ባደርጋቸውም፥ አንዱን ክርስቶስ መድኃኒታችን አድርገን በመቀበልና ለዘላለም ሕይወት ለመንጻት በአንዱ ደም በመታመን እንደሚገኘው ኅብረት እርግጠኛ፥ ብርቱና ጥልቅ የሆነ ከእነርሱ አንዱም የለም። እዚህ በማዕዱ ላይ የሰፊውና የተሟላው ኅብረት ምልክቶች አሉላችሁ። ይህ እኔና እናንተ ልንመርጠው ወይም ልንጥለው የማንችለው ኅብረት ነው፤ በክርስቶስ ብንሆን የእኛ ነው፥ የእኛም መሆን አለበት። አንዳንድ ወንድሞች በውጫዊው ሥርዓት ኅብረታቸውን ይገድባሉ፥ ይህንም ለማድረግ በቂ ምክንያት እንዳላቸው ያስባሉ፤ እኔ ግን የአመክንዮአቸው ኃይል አይታየኝም፤ እነዚህ ወንድሞች በጸሎት፥ በምስጋና፥ ቃሉን በመስማትና በሌሎች መንገዶች ከሌሎች አማኞች ጋር ኅብረት ሲያደርጉ በደስታ አያለሁና፤ እውነቱ የእውነተኛ ኅብረት ጉዳይ በአብዛኛው ከሰው ቍጥጥር በላይ መሆኑ ነው፤ የደም ዝውውር ለተፈጥሮአዊው አካል እንደ ሆነ እንዲሁ ለመንፈሳዊው አካል ነው፤ በፈቃድ ላይ የማይመሠረት አስፈላጊ ሂደት ነው። እጅግ መንፈሳዊ የሆነ የአምልኮ መጽሐፍ ስታነቡ ተማርካችሁና ተጠቅማችሁ ይሆናል፤ ሆኖም የርእሱን ገጽ ስትመለከቱ ደራሲው የሮማ ቤተ ክርስቲያን አባል እንደ ነበረ አግኝታችሁ ይሆናል። ታዲያ ምን ይሁን? ያን ጊዜ ውስጣዊው ሕይወት ግድግዳዎችን ሁሉ አፍርሶአል፥ መንፈሶቻችሁም ኅብረት አድርገዋል። እኔ በበኩሌ አንዳንድ ውድ ሥራዎችን ሳነብ የሮማ ትምህርታቸውን ተጸይፌአለሁ፤ ሆኖም ስለ ኃጢአት በማልቀስ፥ በመስቀሉ እግር ሥር በመስገድና በጌታችን የክብር መንገሥ ደስ በመሰኘት ከጸሐፊዎቻቸው ጋር የቀረበ ኅብረት አድርጌአለሁ። ደም ከውኃ ይወፍራል፤ በክቡሩ ደምና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ ሕይወት ካለ ኅብረት የበለጠ የማይቀርና ቅን ኅብረት የለም። እዚህ አንዱን እንጀራ በጋራ በመቀበል አንድ መሆናችንን እንመሰክራለን፤ የተመረጡት ሁሉ በአንዱ ቤዛነት በእውነት ተካፋዮች በመሆናቸውም ያ አንድነት በእውነት ይገለጣል፥ እጅግ በጠነከረ መንገድም ይበስላል። በአንዱ ደም ታጥበን፥ ከአንዱ እንጀራ ተመግበን፥ በአንዱ ጽዋ ተጽናንተን፥ ልዩነቶች ሁሉ ያልፋሉ፤ «እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን።»
እንግዲህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህ ዓይነቱ ኅብረት ከሁሉ የተሻለ ከሆነ፥ እንድንደሰትበት እንጠንቀቅ። በዚህች ሰዓት እንጠቀምበት።
በዚህ ሥርዓት መስተዋት ውስጥ ክርስቶስን ለማየት እንጠንቀቅ። ከእናንተ እንጀራውን በልታችሁ ክርስቶስን ያላያችሁ አላችሁን? እንግዲያስ ምንም ጥቅም አላገኛችሁም። ወይኑን ጠጥታችሁ ጌታን ያላሰባችሁ አላችሁን? ወዮ! የጌታን ሥጋ ሳትለዩ ለራሳችሁ ፍርድ እንደ በላችሁና እንደ ጠጣችሁ እፈራለሁ። ነገር ግን ሽማግሌዎች በመነጽራቸው እንደሚያዩ በምልክቶቹ በኩል አይታችሁ ከሆነ፥ ለእንዲህ ያሉ የማየት ረዳቶች አመስጋኞች ሆናችኋል። ነገር ግን የሚታይ ነገር ከሌለ መነጽር ምን ይጠቅማል? ክርስቶስስ በአሳባችንና በልባችን ውስጥ ከሌለ ቍርባን ምን ይጠቅማል?
ጌታን ለይታችሁ ካያችሁ ደግሞ እንግዲያስ እርሱን መቀበላችሁን እርግጠኛ ሁኑ። ለራሳችሁ እንዲህ በሉ፤ «ክርስቶስ ለማንም የሆነውን ሁሉ ለእኔም ይሆናል። ኃጢአተኞችን ያድናልን? እኔንም ያድነኛል። የሰዎችን ልብ ይለውጣልን? የእኔንም ይለውጣል። በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ በሁሉ ነውን? ለእኔም ሁሉ በሁሉ ይሆናል።» ክርስቶስን እንዴት እንደሚቀበሉ እንደማያውቁ ሰዎች ሲናገሩ ሰምቻለሁ። ሐዋርያው ምን ይላል? «በአፍህ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል።» ልትበላው የምትፈልገው ነገር በአፍህ ውስጥ ቢኖር ከሁሉ የሚሻለው ምን ማድረግ ነው? አትውጠውምን? እምነት የሚያደርገው ልክ ያንን ነው። የክርስቶስ የጸጋ ቃል እጅግ ቀርቦልሃል፥ በምላስህ ላይ ነው፤ ወደ ውስጣዊ ነፍስህ ይውረድ። መድኃኒትህንም እንዲህ በለው፤ «ኢየሱስ ሆይ፥ አንተን ለመቀበል የማይገባኝ መሆኔን አውቃለሁ፤ ነገር ግን እንጀራ ወደ ተራበ እንደሚመጣ በጸጋህ ወደ እኔ ስለምትመጣ፥ በአንተ በመመገብ ደስ እያለኝ በምስጋና እቀበልሃለሁ! የወይን ፍሬ ወደ ተጠማ ሰው እንደሚመጣ ወደ እኔ ስለምትመጣ፥ ጌታ ሆይ፥ በፈቃዴ እወስድሃለሁ፤ ከእኔም የምትፈልገው ይህ መቀበል ብቻ ስለ ሆነ አመሰግንሃለሁ። መንፈስህ እንዲህ አላስቀመጠውምን፤ ‹ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው›?»
የተወደዳችሁ ወዳጆች ሆይ፥ ኢየሱስን እንዲህ ከተቀበላችሁት በኋላ እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ደስ መሰኘትን አትተዉ። ክርስቶስን ተቀብለው ሳሉ ፈጽሞ እንዳልተቀበሉት የሚናገሩና የሚያደርጉ ምንኛ ብዙዎች ናቸው! ሰው ከበላው በኋላ ያልበላ ያህል ይሰማኛል የሚለው ምግብ ደካማ ምግብ ነው፤ ማንም ሰው «ተቀብዬዋለሁ፤ ነገር ግን ምንም አልተደሰትሁም፥ ምንም ሰላም አላገኘሁም» ሊልበት የሚችለው ክርስቶስም ደካማ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስን ወደ ልባችሁ ከተቀበላችሁት ድናችኋል፥ ጸድቃችኋል። «እንደዚያ ተስፋ አደርጋለሁ» ብላችሁ ታንሾካሽካላችሁን? ያ ብቻ ነውን? አታውቁምን? የብዙዎች «ተስፋ አደርጋለሁ» ማለትና ማንከስ ደካማ አካሄድ ነው፤ ሁለቱንም እግሮቻችሁን አጽንታችሁ አኑሩና «ያመንሁትን አውቃለሁና፥ እርሱም አደራዬን እስከዚያ ቀን ድረስ ሊጠብቅ እንዲችል ተረድቼአለሁ» በሉ። ወይ ድናችኋል ወይ ጠፍታችኋል፤ በሁለቱ መካከል ሌላ ሁኔታ የለም። ወይ ይቅርታ አግኝታችኋል ወይ ተፈርዶባችኋል፤ ወይ ለታላቅ ደስታ መልካም ምክንያት አላችሁ፥ አለዚያም ለከባድ ጭንቀት ጽኑ ምክንያት አላችሁ። ማስተስረያውን ከተቀበላችሁ የቻላችሁትን ያህል ደስ ይበላችሁ፤ ገና የማታምኑ ከሆናችሁ ደግሞ ክርስቶስ የእናንተ እስኪሆን ድረስ አታርፉ።
አቤት፥ ኅብረቱን ፈጽሞ እንዳታጡ ሆናችሁ ከክርስቶስ ጋር ዘወትር ወደ ኅብረት የመግባት ደስታ! ወዳጆች ሆይ፥ ይህ በየቀኑና ቀኑን ሙሉ የእናንተ ይሁን! በፀሐይ ስታርፉ ወይም በአትክልት ስፍራዎች ስትመላለሱ ጥላው በላያችሁ ይውደቅ! በባሕር ዳር ተኝታችሁ የማዕበልን ማጕረምረም ስታዳምጡ ድምፁ ያበረታችሁ፤ ኮረብቶችን ስትወጡም መገኘቱ የተራራውን ብቸኝነት ያክብረው! ኢየሱስ በዙሪያችሁ ሁሉ ያለ መገኘት ይሁንላችሁ፤ ሌሊቱን የሚያበራ፥ ቀኑን መዓዛ የሚያለብስ፥ ስፍራዎችን ሁሉ ደስ የሚያሰኝ፥ ሥራዎችንም ሁሉ የሚቀድስ ይሁን! ውዳችን ለጌታ ቀን ብቻ ሳይሆን ለሳምንቱ ቀናትም ወዳጅ ነው፤ ለሚወዱት ደቀ መዛሙርቱ የማይለይ ባልንጀራ ነው። በዚህ ማዕድ ከሥጋውና ከደሙ ጋር ኅብረት ያደረጉ በገዛ ማዕዳቸው ጌታን የዘወትር እንግዳ አድርገው ሊያገኙት ይችላሉ፤ በዚህ የሰገነት ክፍል ከጌታቸው ጋር የተገናኙ የራሳቸውን እልፍኝ በንጉሣዊ መገኘቱ እንዲያበራላቸው ሊጠብቁት ይችላሉ። ከኢየሱስና ከተመረጡት ወንድማማቾች ጋር ያለ ኅብረት ከእንግዲህ ወዲህ የሕይወታችን አየር፥ የሕልውናችን ደስታ ይሁን። ይህ በምድር ሰማይን ይሰጠናል፥ በላይ ላለው ሰማይም ያዘጋጀናል።