እስኪመጣ ድረስ
ክርስቶስና የማዕድ ባልንጀሮቹ

ምዕራፍ 17 · 17 ደቂቃ ንባብ · 21 ደቂቃ ማዳመጥ

ክርስቶስና የማዕድ ባልንጀሮቹ

ክርስቶስና የማዕድ ባልንጀሮቹ «ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማዕድ ተቀመጠ።» —ሉቃስ 22:14።

ክርስቶስና የማዕድ ባልንጀሮቹ።

የክርስትና ሃይማኖት ውጫዊ ሥርዓቶች ሁለት ብቻ ናቸው፤ እነዚህም ሁለቱ እጅግ ቀላሎች ናቸው፤ ሆኖም አንዳቸውም ከሰው ለውጥ አላመለጡም፤ ወዮ! በእነዚህ ክፉ ጥመቶች ብዙ ጉዳት ደርሶአል፥ ብዙም የከበረ ትምህርት ተሠውቶአል። ለምሳሌ፥ ሐዋርያት ያከናወኑት የጥምቀት ሥርዓት አማኙ ከክርስቶስ ጋር መቀበሩንና ከጌታው ጋር በአዲስ ሕይወት መነሣቱን ያመለክት ነበር። ሰዎች ግን መጥለቅን በመርጨት፥ አስተዋዩንም አማኝ ምንም በማያውቅ ሕፃን መለወጥ ግድ አላቸው፤ እንዲህም ሥርዓቱ ተገደለ። ሁለተኛው የተቀደሰ ሥርዓት፥ የጌታ ራት፥ እንደ አማኞች ጥምቀት ፍጹም ቀላል ነው። በበዓል የሚበላ የተቈረሰ እንጀራና የሚጠጣ የፈሰሰ የወይን ጠጅ ነው፤ ይህም ክርስቶስ ስለ እኛ የተቀበለውን መከራ፥ ቅዱሳንም እርስ በርሳቸውና ከእርሱ ጋር ያላቸውን ኅብረት የሚያሳይ ደስ የሚያሰኝ ሥዕል ነው። ነገር ግን ይህም ሥርዓት በሰዎች እጅ ተበላሽቶአል። አንዳንዶች የወይኑን ጠጅ ፈጽመው አስወግደዋል፥ ወይም ለካህናት ወገን ብቻ አስቀርተዋል፤ ቀላሉም እንጀራ ወደ ተቀደሰ «ኅብስተ መሥዋዕት» ተለውጦአል። ማዕዱም፥ በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ የኅብረት ምልክት የሆነው—በአንድ ማዕድ ዙሪያ ተቀምጦ አብሮ ከመብላትና ከመጠጣት ይልቅ ኅብረትን የሚገልጥ ምን አለና?—ይህ፥ እንደ ሚሉት፥ መወገድ አለበት፤ መሠዊያም መቆም አለበት፤ ጌታ ኢየሱስን እንድናስብ ሊረዱን የተሰጡት እንጀራና የወይን ጠጅም ወደ «ደም የሌለበት መሥዋዕት» ይለወጣሉ፤ እንዲህም ነገሩ ሁሉ ለኅብረት ከተሰጠ ቅዱስ ሥርዓት ይልቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆነ ክብረ በዓል ይሆናል። እንግዲህ ከእግዚአብሔር ቃል አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ እንኳ እንዳንጨምርም እንዳናጎድልም በሌሎች በእነዚህ ስሕተቶች እንጠንቀቅ። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ላይ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በደኅና ትቆማላችሁ፥ ለሚጠይቋችሁም መልስ ይኖራችኋል፤ አዎን፥ በእግዚአብሔር ፍርድ ወንበር ፊት እንኳ ልትሰጡት የምትችሉት መልስ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቃል ፋንታ የገዛ ምኞታችሁ ወይም ሐሳባችሁ ወይም ጣዕማችሁ ወይም ተገቢና ትክክል ነው የምትሉት አስተሳሰባችሁ እንዲገዛችሁ አንድ ጊዜ ብትፈቅዱ፥ አደገኛ መንገድ ጀምራችኋል፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ ካልከለከለ፥ ወሰን የሌለው ጉዳት ሊከተል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ የሥልጣናችን መለኪያ ነው፤ ማንም ከእርሱ ፈቀቅ ሊል አይገባውም። ጠቢቡ ሰው በመክብብ፦ «የንጉሡን ትእዛዝ ጠብቅ እልሃለሁ» ይላል፤ እኛም ምክሩን እንደግማለን፤ የጌታችን እናት በቃና የተናገረችውን ጥበበኛ ትእዛዝም እንጨምርበታለን፤ እርስዋ፦ «የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ» አለች።

አሁንም የመጀመሪያውን የጌታ ራት በማሰላሰል እንድትመለከቱ እንለምናችኋለን። በዚያ ሰፊ ሰገነት ውስጥ መሠዊያ እንዳልነበረ ወዲያው ታስተውላላችሁ። ማዕድ ነበረ፥ እንጀራና የወይን ጠጅ ያለበት ማዕድ፥ ነገር ግን መሠዊያ አልነበረም፤ ኢየሱስም አልተንበረከከም፥—ለዚህ ምንም ምልክት የለም፥—ነገር ግን በምሥራቃውያን አቀማመጥ፥ ማለትም በከፊል ተደግፎ፥ እንደ ተቀመጠ አልጠራጠርም፤ ከሐዋርያቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ። ይህን ራት የሠራው እርሱ እንዴት ሊከበር እንደሚገባ ያውቅ ነበር፤ የመጀመሪያውም አከባበር ለሌሎቹ ሁሉ ምሳሌ ስለ ሆነ፥ ወደዚህ ቍርባን የምንቀርብበት ትክክለኛ መንገድ በማዕድ ዙሪያ ተሰብስበን፥ ጌታችንን እያሰብን እንጀራውንና የወይን ጠጁን አብረን ስንበላና ስንጠጣ ተቀምጠን ወይም ተደግፈን መሆኑን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።

መድኃኒቱ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያቱ ጋር ተቀምጦ ስናየው፥ በመጀመሪያ፦ ይህ ምን አደረጋቸው? ብለን እንጠይቅ። ሁለተኛ፦ ይህ ምን ያመለክት ነበር? ሦስተኛም፦ ከዚህ በትክክል ሌላ ምን ልንረዳ እንችላለን?

1ኛ. እንግዲህ በመጀመሪያ፥ ታላቁን መምህር፥ ጌታን፥ የጽዮንን ንጉሥ፥ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያቱ ጋር ሊበላና ሊጠጣ በማዕድ ተቀምጦ እናያለን፤—ይህ ምን አደረጋቸው?

በመጀመሪያ ምን እንደ ነበሩ አስተውሉ። በመጀመሪያው ጥሪው ተከታዮቹ ሆኑ፤ «በኋላዬ ኑ» ብሎአቸዋልና። ይህም ማለት፥ እርሱ መሲሕ እንደ ሆነ በልዩ ልዩ ምልክቶችና ተአምራት ስለ ተረዱ ተከታዮቹ ሆኑ። ተከታዮች ከመሪያቸው እጅግ ርቀው ሊሆኑና ከእርሱ ጋር ጥቂት ወይም ምንም ግንኙነት ላይኖራቸው ይችላል፤ መሪው የሠራዊቱ ተራ አባላት ሊቀርቡት የማይችሉት ታላቅ ሊሆን ይችላልና። በደቀ መዛሙርቱ ረገድ ግን መከተላቸው በተለየ ሁኔታ የቀረበ ነበረ፤ መምህራቸው እጅግ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ነበረና፤ ቢሆንም ግንኙነታቸው በመጀመሪያ ሁልጊዜ እጅግ የጠበቀ አልነበረም፤ ስለዚህም እንደዚህ ራት ወዳለ በዓል የጠራቸው ገና በመጀመሪያ አልነበረም። በመከተል ጀመሩ፤ እኛም መጀመር ያለብን ከዚህ ነው። ገና ከጌታችን ጋር ወደሚቀርብ ኅብረት መግባት ባንችል፥ ቢያንስ ድምፁን በመንፈሱ ልናውቅና በጎች እረኛውን እንደሚከተሉ ልንከተለው እንችላለን። እርሱን የምንከተልበት ዋነኛው መንገድ በእርሱ መታመን፥ ከዚያም ምሳሌውን በትጋት መምሰል ነው። ይህ መልካም ጅማሬ ነው፤ ፍጻሜውም መልካም ይሆናል፤ ዛሬ ከእርሱ ጋር የሚሄዱ ወደ ፊት ከእርሱ ጋር ያርፋሉና፤ በእግሩ ፈለግ የሚሄዱም በዙፋኑ ላይ ይቀመጣሉ።

ተከታዮቹ ከሆኑ በኋላ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ሆኑ። ሰው ለጊዜው ተከታይ ሆኖ ገና ደቀ መዝሙር ላይሆን ይችላል። ተከታይ በጭፍን ሊከተልና የማያስተውለውን ብዙ ነገር ሊሰማ ይችላል፤ ደቀ መዝሙር በሆነ ጊዜ ግን መምህሩ ያስተምረዋል፥ ወደ እውነትም ይመራዋል። መተርጐም፥ ማብራራት፥ ችግሮችን መፍታት፥ ጥርጣሬዎችን ማስወገድና እውነትን የሚያስተውሉት ማድረግ በደቀ መዛሙርቱ መካከል የመምህር ተግባር ነው። ተከታዮቹ ደቀ መዛሙርት መሆናቸው እጅግ የተባረከ ነገር ነበረ፤ ነገር ግን ደቀ መዛሙርት ከመምህራቸው ጋር ተቀምጠው እስኪበሉ ድረስ የግድ የቀረቡ አይደሉም። ሶቅራጥስና ፕላቶ በአካዳሚያቸው ወደ ቤታቸው ያልጋበዙአቸውን ብዙ ሰዎች ያውቁ ነበር። ወንድሞቼ ሆይ፥ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንድንሆን ብቻ ጠርቶን ከዚያ በላይ ባይሆን ኖሮ፥ እጅግ የምናመሰግንበት ምክንያት በኖረን ነበር፤ በእግሩ ሥር እንድንቀመጥ ተፈቅዶልን በፊታችን ባለው በእንዲህ ያለ ግብዣ ፈጽሞ ባንካፈል ኖሮ እንኳ፥ በጥልቅ ልናመሰግን በተገባን ነበር፤ አሁን ግን ከዚያም የሚበልጥ ስፍራ ስለ ሰጠን፥ ለደቀ መዝሙርነታችን ፈጽሞ ታማኝነትን አናጕድል። ዕለት ዕለት ከኢየሱስ እንማር፤ ያስተማረንን ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስን እንመርምር፤ ከዚያም በመንፈስ ቅዱሱ እርዳታ በጥንቃቄ እንታዘዝ። ነገር ግን ከዚህ የሚያልፍ ገና አንድ ነገር አለ።

የጌታ ደቀ መዛሙርት ከሆኑ በኋላ፥ የተመረጡቱ ቀጥለው አገልጋዮቹ ለመሆን ከፍ አሉ፤ ይህም አንድ እርምጃ ወደ ፊት ነው፤ ደቀ መዝሙር ገና ሕፃን ሊሆን ይችላልና፤ አገልጋይ ግን ኃይል አለው፥ በመጠኑም ሥልጠና ተቀብሎአል፥ በምላሹም አንዳች ያበረክታል። መምህራቸው ወንጌልን እንዲሰብኩና የጸጋን ተልእኮ እንዲፈጽሙ ኃይል ሰጣቸው፤ እንደዚህ ያለውን መምህር ለማገልገልና መንግሥቱን ለማቋቋም ለመርዳት በመጠራታቸውም ደስተኞች ነበሩ። ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ ሆይ፥ ሁላችሁ የክርስቶስ አገልጋዮች መሆናችሁን በእርግጥ ታውቃላችሁን? እንዲህ ከሆነ፥ እምነታችሁ ደካማ ስለ ሆነ አገልግሎቱ አንዳንድ ጊዜ ከባድ መስሎ ቢታያችሁም፥ አገልጋዮች በመሆናችሁ ብቻ እጅግ አመስግኑ፤ በዚህ ዓለም መንግሥታት ሁሉ ላይ ከመንገሥ እግዚአብሔርን ማገልገል ይሻላልና። ከሰዎች ሁሉ ታላቅ ሆኖ የራስ ምኞት ባሪያ ከመሆን ወይም ሰውን ብቻ ደስ ከማሰኘት የክርስቶስ ታናሽ አገልጋይ መሆን ይሻላል። ቀንበሩ ልዝብ ሸክሙም ቀሊል ነው። የእንደዚህ ያለ መምህር አገልጋይ በጥሪው ደስ ሊለው ይገባል፤ ነገር ግን ከዚህ የሚያልፍ ገና አንድ ነገር አለ።

በሕይወቱ ፍጻሜ አቅራቢያ መምህራችን ደቀ መዛሙርቱ ያላቸውን ይበልጥ የቀረበ ዝምድና ገለጠ፤ እንዲህም ያሉ ቃሎችን ተናገረ፦ «ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፥ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና።» ይህ ታላቅ እርምጃ ወደ ፊት ነው። ወዳጅ ምንም ዝቅተኛ ቢሆን ከወዳጁ ጋር ብዙ መቀራረብ አለው። አገልጋዩ ሊያውቀው የማያስፈልገው ነገር ለወዳጁ ይነገረዋል። ተራ አገልጋይ ወይም ደቀ መዝሙር ወይም ተከታይ ያልደረሰበትን ኅብረት ወዳጅ ይደሰትበታል። ይህን ከፍ ያለ ግንኙነት፥ ይህን የበለጠ ውድ የዝምድና ማሰሪያ እናውቅ ዘንድ ይሁንልን! የመምህራችንን ወዳጅነት ሳንደሰትበት አንርካ! «ወዳጆች ያሉት ሰው ራሱን ወዳጅ አድርጎ ያሳይ»፤ የክርስቶስንም ወዳጅነት ብንሻ፥ ለዓላማው፥ ለእውነቱና ለሕዝቡ ወዳጆች ልንሆን ይገባናል። እርሱ ሁልጊዜ የሚወድድ ወዳጅ ነው፤ ወዳጅነቱን ልትደሰቱበት ብትወድዱ፥ በእርሱ ለመኖር ተጠንቀቁ።

እንግዲህ ጌታችን ከሕማማቱ በፊት ባለው ሌሊት ወዳጆቹን ከተራ ወዳጅነት አንድ እርምጃ አልፎ እንደ መራቸው አስተውሉ። ተራ ተከታይ ከመሪው ጋር በማዕድ አይቀመጥም፤ ደቀ መዝሙር ከመምህሩ ጋር የማዕድ ተካፋይ ነኝ አይልም፤ አገልጋይ ከጌታው ጋር በአንድ ማዕድ የሚስተናገደው አልፎ አልፎ ነው፤ ወዳጅ የተደረገውም ሁልጊዜ እንግዳ እንዲሆን አይጋበዝም፤ እዚህ ግን ጌታ ኢየሱስ የተመረጡትን የማዕድ ባልንጀሮቹ አደረጋቸው፤ ከእርሱ ጋር በአንድ ማዕድ እንዲቀመጡ፥ ከአንዱ እንጀራ እንዲበሉ፥ ከአንዱም ጽዋ ከእርሱ ጋር እንዲጠጡ ከፍ ከፍ አደረጋቸው። ከዚያ ስፍራ ፈጽሞ አላወረዳቸውም፤ እነርሱ የሁሉ ወኪሎች ነበሩ፤ ጌታም እነርሱን ባኖረበት ስፍራ ቅዱሳኑን ሁሉ ለዘወትር አኑሮአቸዋል። የሚያምኑት የጌታ ሕዝብ ሁሉ በተቀደሰ መብትና ጥሪ ከኢየሱስ ጋር በአንድ ማዕድ ተቀምጠዋል፤ በእውነት ኅብረታችን ከአብ ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነውና። እርሱ ወደ ልባችን ገብቶአል፤ ከእኛም ጋር እራት ይበላል፥ እኛም ከእርሱ ጋር፤ የማዕድ ባልንጀሮቹ ነን፤ በእግዚአብሔርም መንግሥት ከእርሱ ጋር እንጀራ እንበላለን።

እንግዲህ፦ «ይህ በዓል ሐዋርያትን ምን አደረጋቸው?» ለሚለው ጥያቄ መልሱ የማዕድ ባልንጀሮች የሚል ነው። ይህ በዓል የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አባላት ሁሉ በመለኮታዊ ጸጋ እርስ በርሳቸውና ከጌታቸው ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር የማዕድ ባልንጀሮች መሆናቸውን ያሳያል።

2ኛ. እንግዲህ አሁን ወደ ሁለተኛው እንሻገርና፦ ይህ የማዕድ ባልንጀርነት ምን ያመለክት ነበር? ብለን እንጠይቅ።

ከሁሉ በፊት የእርስ በርስ ታማኝነትን ያመለክት ነበር። ይህ በክብር አብሮ መብላትና መጠጣት እርስ በርሳቸው ለመታመን የገቡት ቃል ነበረ። እንዲህ ተብሎ መታወቅ ነበረበት፤ አለዚያ፦ «እንጀራዬን የሚበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣብኝ» በሚለው አቤቱታ ምንም ኃይል ባልኖረ ነበር። ይሁዳ ከጌታው ጋር እንጀራ ስለ በላ፥ አሳልፎ እንዳይሰጠውና በእርሱም ላይ ተረከዙን እንዳያነሣ ግዴታ ነበረበት ማለት አይደለምን? ይህ የተሰወረ ቃል ኪዳን ማኅተም ነበረ፤ አብረው ስለ በሉ እርስ በርሳቸው ለመታመን ታስረው ነበር። እንግዲህ ከእናንተ በእውነት የክርስቶስ አገልጋዮችና ወዳጆች የሆናችሁ ሁሉ፥ ጌታ ኢየሱስ በማዕዱ ከእናንተ ጋር ሲበላ ለእናንተ ታማኝ ለመሆን ራሱን በቃል እንደሚያስር እወቁ። መምህሩ ፈጽሞ ይሁዳን አይሆንም፤—ይሁዳ ያለው በደቀ መዛሙርቱ መካከል ነው። በጌታ ዘንድ ምንም ክዳት የለም፤ በአደራ የሰጠነውን ሊጠብቅ የሚችል ብቻ ሳይሆን ታማኝ ነው፥ ያደርገውማል። በታላቁና በዋናው ነገር ብቻ ሳይሆን በሰጠው በተስፋ ቃል ሁሉ ታማኝ ይሆናል። እንግዲህ ሊተዋችሁ ቢያስብ ኖሮ መምህራችሁ ከእርሱ ጋር እንጀራ ልትበሉ ወደ ማዕዱ እንዳልጠራችሁ በእርግጥ እወቁ። እንደ ክቡራን እንግዶቹ ተቀብሎአችኋል፤ ከምርጥ መብሉም መግቦአችኋል፤ በዚህም እንዲህ እንደሚላችሁ ያህል ነው፦ «ምንም ቢመጣ ፈጽሞ አልተዋችሁም፤ በመከራና በጭንቀት በፈተናም ጊዜ ሁሉ በቀኛችሁ እሆናለሁ፤ እናንተም አትናወጡም፤ እስከ መጨረሻውም ድረስ ታማኝነቴንና እውነቴን ትፈትናላችሁ።»

ነገር ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ እናንተ ለጌታችሁ ልታሳዩት የሚገባችሁ ታማኝነት ካልታሰባችሁ ይህን ራት አላስተዋላችሁትም፤ ግብዣው የጋራ ነው፥ ቃሉም የሁለቱም ወገን ነውና። ከእርሱ ጋር ስትበሉ ለተሰቀለው ታማኝነታችሁን ቃል ትገባላችሁ። ወዳጆች ሆይ፥ ባለፈው ዓመት ቃላችሁን እንዴት ጠበቃችሁ? ከእርሱ ጋር እንጀራ በልታችኋል፤ በልባችሁም በእርሱ ላይ ተረከዝ እስከ ማንሣት ድረስ ፈጽሞ ፈቀቅ እንዳላላችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ነገር ግን እንደሚገባ ሁልጊዜ አክብራችሁታልን? እንግዶች ሊያደርጉ እንደሚገባ አድርጋችኋልን? ለእናንተ ያለውን ፍቅሩን አስባችሁ ለእርሱ ያላችሁን ፍቅር ጎን ለጎን አድርጋችሁ ሳታፍሩ ልታዩ ትችላላችሁን? ከዚህ ጊዜ ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ልባችን ከእርሱ እንዲርቅ ወይም ለክብሩ ያለን ቅንዓት እንዲቀዘቅዝ የማይፈቅድ ቀናተኛ ታማኝነትን ለውዴ በነፍሳችን ይሥራ!

ደግሞም በዚህ በክብር አብሮ መብላትና መጠጣት ውስጥ በደቀ መዛሙርቱና በጌታቸው መካከል ብቻ ሳይሆን በደቀ መዛሙርቱ በራሳቸው መካከልም የታማኝነት ቃል እንዳለ አስቡ። ይሁዳ ጴጥሮስን ወይም ዮሐንስን ወይም ያዕቆብን አሳልፎ ቢሰጥ ኖሮ ከሃዲ በሆነ ነበር፤ እንዲሁ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ ወደ አንዱ ማዕድ ስትመጡ ከእንግዲህ ወዲህ እርስ በርሳችሁ ታማኞች ልትሆኑ ይገባችኋል። ጭቅጭቅና ቅናት ሁሉ ይቁም፤ ለጋስና ፍቅር ያለበት መንፈስም በልብ ሁሉ ይንገሥ። ከእናንተ ጋር በቍርባን የተካፈሉትን ማንም ሲያማ ብትሰሙ፥ ከእነርሱ ጋር እንጀራ እንደ በላችሁ ስማቸውን ልትከላከሉ ግዴታ እንዳለባችሁ ቍጠሩ። በክርስቶስ በሆነ በማንም ወንድም ላይ የስድብ ክስ ቢነሣ፥ ስሙ እንደ ራሳችሁ ስም ውድ እንደ ሆነባችሁ ቍጠሩ። እጅግ የላቀውንና መንፈሳዊ የሆነውን አንድነት ከተራ ሕይወት ነገር ጋር ማመሳሰል ቢፈቀድልኝ፥ በመካከላችን እንደ ፍሪሜሶናውያን ያለ የተቀደሰ መተሳሰር ይጠበቅ። እርስ በርሳችሁ የአንዱ ብልቶች ናችሁ፤ በንጹሕ ልብ እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። ከአንዱ ጽዋ እየጠጣችሁ፥ ከአንዱ እንጀራ እየበላችሁ በዓለም ፊት ምልክት ታቀርባላችሁ፤ ይህም ሐሰት እንዲሆን ታስቦ እንዳልሆነ ተስፋ አደርጋለሁ። ይህ ክርስቶስ ለእናንተ ያለውን ታማኝነት በእውነት እንደሚያሳይ፥ እንዲሁ እናንተም ለክርስቶስና እርስ በርሳችሁ ያላችሁን ታማኝነት በእውነት ይግለጥ።

በሚቀጥለውም ስፍራ፥ አብሮ መብላትና መጠጣት የእርስ በርስ መተማመን ምልክት ነበረ። በዚያ አብረው በመቀመጣቸው እርስ በርሳቸው እንደሚተማመኑ በፈቃዳቸው ገለጡ። እነዚያ ደቀ መዛሙርት በመምህራቸው ታመኑ፤ እንደማያስታቸውና እንደማያታልላቸው ያውቁ ነበር። እርስ በርሳቸውም ተማመኑ፤ ከእነርሱ አንዱ ጌታቸውን አሳልፎ እንደሚሰጥ በተነገራቸው ጊዜ እርስ በርሳቸው አልተጠራጠሩም፤ ነገር ግን እያንዳንዱ፦ «ጌታ ሆይ፥ እኔ እሆንን?» አለ። እርስ በርሳቸው ብዙ መተማመን ነበራቸው፤ ጌታ ኢየሱስም፥ እንዳየነው፥ እንደ ወዳጆቹ በማድረግ በእነርሱ ታላቅ እምነት ጥሎ ነበር። ስለሚመጣው መከራውና ሞቱ ያለውን ታላቅ ምሥጢር እንኳ በአደራ ሰጥቶአቸው ነበር። በዚያ የራት ማዕድ የተቀመጡት የሚተማመኑ ማኅበር ነበሩ። እንግዲህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ በዚህ ማዕድ ዙሪያ ስትሰበሰቡ በጌታ ኢየሱስ ፍጹም በሆነ መታመን መንፈስ ኑ። መከራ ብትቀበሉ ፍቅሩን አትጠራጠሩ፤ ነገር ግን ሁሉን ለበጎ እንደሚሠራላችሁ እመኑ። በጭንቀት ብትታወኩ፥ ጭንቀታችሁን ፈጽማችሁ በቤዛችሁ እጅ በመተው መታመናችሁን አሳዩ። በመምህራችሁ ላይ ጥርጣሬ ይዛችሁ ወደዚህ ብትመጡ ለእናንተ የኅብረት በዓል አይሆንም። አይደለም፤ ከእርሱ ጋር እንጀራውን ስትበሉ መታመናችሁን አሳዩ። እርስ በርሳችሁም የወንድማማች መተማመን ይኑር። በመካከላችሁ የጥርጣሬና የአለመተማመን መንፈስ ማየት እጅግ የሚያሳዝን ይሆናል። ጥርጣሬ የኅብረት ሞት ነው። አንድ ክርስቲያን ሌላው ስለ እርሱ ክፉ ያስባል ብሎ ባሰበ ቅጽበት፥ በዚያ ሐሳብ ውስጥ ጥቂት እውነት እንኳ ባይኖር፥ ወዲያውኑ የምሬት ሥር ይተከላል። እርስ በርሳችን በቅንነታችን እንመን፤ እያንዳንዱ ወንድማችን ከእኛ ይልቅ ሊታመን እንደሚገባው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለንና። ጥርጣሬያችሁን ወደ ውስጥ መልሱ፤ መጠራጠር ግድ ቢሆንባችሁ የገዛ ልባችሁን ተጠራጠሩ፤ በዚህ ማዕድ ከእናንተ ጋር የተካፈሉትን ስታገኙ ግን በልባችሁ፦ «እንደነዚህ ያሉት ሊያታልሉኝ ቢችሉ፥ ወዮ! ሊያታልሉኝም ይችላሉ፥ በክርስቲያን ወንድሞቼ ላይ ዘወትር አለመተማመን ከማሳድር ይልቅ መታለልን እመርጣለሁ» በሉ።

በማዕዱ ዙሪያ የመሰብሰቡ ሦስተኛ ትርጉም ይህ ነው፤ የልብ ወንድማማችነት። ጌታችን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ በመቀመጡ ከእነርሱ ጋር አንድ መሆኑን፥ በእውነትም ወንድም መሆኑን አሳየ። መቀመጫዎቻቸው በማዕረግ ቅደም ተከተል እንደ ተደረደሩ አናነብም። በሮም ያለው ታላቁ የቤተ መንግሥት አዛዥ ማዕዱን ቢያዘጋጅ ኖሮ፥ በእርግጥ ጴጥሮስን በክርስቶስ ቀኝ ባስቀመጠው ነበር፤ ሌሎቹንም ሐዋርያት እንደ ወደ ፊት ጵጵስናቸው ክብር በደረጃ ባስቀመጣቸው ነበር፤ ስለ አቀማመጣቸው የምናውቀው ግን ይህ ብቻ ነው፤ ዮሐንስ ከመድኃኒቱ አጠገብ ተቀምጦ በደረቱ ላይ ተጠጋ፥ ጴጥሮስም ራቅ ብሎ ተቀመጠ፤—እንዲህ እንደ ሆነ እርግጠኞች ነን፤ ዮሐንስን «ጠቀሰው» ተብሎአልና፤ አጠገቡ ተቀምጦ ቢሆን ኖሮ በጆሮው ባንሾካሾከለት ነበር፤ ነገር ግን ጠቀሰው፤ ስለዚህ በእንግዶቹ አቀማመጥ «ታች» ወይም «ላይ» የሚባል ቢኖር እንኳ፥ በማዕዱ ራቅ ብሎ ሳይቀመጥ አልቀረም። እውነቱ፥ እንደምናምነው፥ በዚያ በተቀደሰ እኩልነት መቀመጣቸው ነው፤ ጌታ ኢየሱስ ታላቁ ወንድም በመካከላቸው ነበረ፤ ሌሎቹም ሁሉ፦ «መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ» በሚለው ቃል መሠረት ነበሩ። እንግዲህ በዚህ ጊዜ እንደ ገና ወደ ማዕዱ ስንመጣ፥ በሰማይ ከፍ ካለው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በተቀደሰ ዝምድና እንደ ተሳሰርን፥ በእርሱም በኩል ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር ያለን ዝምድና እጅግ የቀረበና የጠበቀ እንደ ሆነ ይሰማን።

ወይ፥ የክርስቲያን ወንድማማችነት ይበልጥ እውነተኛ ቢሆን! «ወንድም» የሚለው ቃል እንኳ እንደ ግብዝነት መሣለቂያ ሆኖአል፤ ቢሆንም አይገርምም፤ በአብዛኛው እንደ ባዶ ልማዳዊ ቃል ይነገራልና፥ በብዙ ጊዜም ትርጉሙ እጅግ ጥቂት ነው። ነገር ግን አንዳች ትርጉም ሊኖረው ይገባል። በኢየሱስ ደም የታጠቡት በልባችሁ ፍቅርና በበጎ አድራጎታችሁ ትጋት ላይ መብት እንዳላቸው በእውነት ካልተሰማችሁ ወደዚያ ማዕድ ለመምጣት መብት የላችሁም። እንዴት! በሰማይ ለዘላለም አብራችሁ ልትኖሩ ሳላችሁ፥ እዚህ በምድር እርስ በርሳችሁ ፍቅር አታሳዩምን? እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ የመምህራችሁ አዲስ ትእዛዝ ነው፤ ቸል ትሉታላችሁን? የክርስቲያኖች ምልክት አድርጎ ይህን ሰጥቶአል፦ «ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ»፥—የወርቅ መስቀል ብታደርጉ አይደለም፥ ነገር ግን—«እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ።» ክርስቲያን በእውነት የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆኑ ምልክቱ ይህ ነው። እዚህ፥ በዚህ ማዕድ፥ ወንድማማችነትን እናገኛለን። ከዚህ ከተቀደሰ ራት የሚበላ ሁሉ በክርስቶስ የወንድማማች ማኅበር አባል መሆኑን ይገልጣል፤ ይህም ማኅበር ለአንድ ዓላማ የሚጋደል፥ እውነተኛ መተሳሰብ ያለው፥ እርስ በርሱ የአንዱ ብልቶች የሆነና ሁሉም የክርስቶስ አካል ብልቶች የሆኑበት ነው። እግዚአብሔር ይህን አሁንም በክርስትና ዓለም ሁሉ እውነት ያድርገው፤ ዓለምም፦ «እነዚህ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው እንዴት እንደሚዋደዱ እዩ!» እያለ እንዴት ይደነቃል!

ነገር ግን ይህ ማዕድ ከዚህ የበለጠ ትርጉም አለው፤ የጋራ ደስታን ያመለክታል። ኢየሱስ ይበላል፥ እነርሱም ይበላሉ፥ ያንኑ እንጀራ። እርሱ ይጠጣል፥ እነርሱም ከዚያው ጽዋ ይጠጣሉ። በመብሉ ልዩነት የለም። ይህ ምን ማለት ነው? የክርስቶስ ደስታ የሕዝቡ ደስታ እንደ ሆነ አይነግረንምን? «ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈጸም» ብሎአልና። ክርስቶስን ደስ የሚያሰኘው ያው ደስታ ለሕዝቡ የሚያዘጋጀው ነው። አንተ እውነተኛ አማኝ ብትሆን በክርስቶስ ደስታ ትካፈላለህ፤ መንግሥቱ ስትመጣ፥ እውነት ስትስፋፋ፥ ኃጢአተኞች ሲድኑ፥ ጸጋ ሲከበር፥ ቅድስና ሲበዛ፥ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ሲል ማየት ደስ ያሰኝሃል፤ ይህም የእርሱ ደስታ ነው። ነገር ግን ውድ ወንድሞቼና አብረን ሃይማኖተኛ ነን የምንል ሆይ፥ ዋናው ደስታችሁ የክርስቶስ ደስታ እንደ ሆነ እርግጠኞች ናችሁን? የሕይወታችሁ ዋና መደገፊያ የእርሱ መብልና መጠጥ የነበረው፥ ማለትም የሰማያዊውን አባት ፈቃድ ማድረግ፥ እንደ ሆነ እርግጠኞች ናችሁን? እንዲህ ካልሆነ በዚህ ማዕድ ምንም ጉዳይ የላችሁም ብዬ እፈራለሁ፤ እንዲህ ከሆነ ግን ወደ ማዕዱም ብትመጡ፥ የክርስቶስን ደስታ እንድትካፈሉ እጸልያለሁ። እርሱ በእናንተ ደስ እንደሚለው እናንተም በእርሱ ደስ ይበላችሁ፤ እንዲሁም ኅብረታችሁ ጣፋጭ ይሁን!

በዚህ ነጥብ በመጨረሻ፥ በአንዱ ማዕድ ያለው ግብዣ የቤተሰብ ፍቅርን ያመለክት ነበር። ከወላጆቹ ጋር በማዕድ መቀመጥ የልጅ ስፍራ ነው፤ በዚያ ፍቅር ይገዛልና። በማዕድ መቀመጥ የክብር ስፍራ ነው፤ «ማርታም ታገለግል ነበር፤ አልዓዛር ግን ከእርሱ ጋር ከተቀመጡት አንዱ ነበረ።» ነገር ግን ይህ ክብር ፍርሃት ሳይሆን ፍቅር የሚሰጠው ነው። ሰዎች በማዕድ ላይ ከሌላ ስፍራ ይልቅ ልባቸውን አብዝተው ይገልጣሉ። ሰውን ልታውቅ ብትወድድ በአክሲዮን ገበያ ልታየው አትሄድም፥ ወደ ገበያም አትከተለውም፤ በዚያ ልቡን ይሰውራልና፤ ነገር ግን ወደ ማዕዱ ትሄዳለህ፤ በዚያም ልቡን ይከፍትልሃል። እንግዲህ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ። መብል ነበረ፤ የቤት ውስጥ ቀላል መብል ነበረ፤ የቅርብ ኅብረት ያንን ሰዓት ገዛ። ወንድሞቼና እኅቶቼ ሆይ፥ አንዳንድ ጊዜ ወደዚህ ማዕድ መጥተን፥ ክርስቶስ ሳይገለጥልን፥ ባዶ ሥርዓት ብቻ ሆኖብን ከዚያ ያለፈ ምንም እንዳልሆነ እፈራለሁ። ከእኛ አንዳንዶቻችን እንደምናደርገውና ለብዙ ዓመታት እንዳደረግነው በየሰንበቱ ወደዚህ ማዕድ ስንመጣ፥ በአብዛኛው ካወቅነው ሁሉ የሚበልጥ የቀረበ ኅብረትን ከክርስቶስ ጋር እዚህ ስለ ተደሰትን፥ ስለዚህም ሥርዓት ስሙን ሺህ ጊዜ ስለ ባረክን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ቢሆንም፥ እንጀራውን ብቻ በልቶ የወይን ጠጁን ብቻ ጠጥቶ የተቀደሰ ትርጉሙን ሁሉ ማጣት የሚባል ነገር አለ። ጌታ ራሱን እንዲገልጥላችሁ እባካችሁ ለምኑት። ለእናንተ የሞተ ሥርዓት እንዳይሆን፥ ነገር ግን አሁን በእውነት ልባችሁን ለክርስቶስ እንድትሰጡ፥ እርሱም እጆቹንና ጎኑን እንዲያሳያችሁ፥ ከሚመጣውም ቍጣ የቤዣችሁን ሥቃዩንና ሞቱን እንዲገልጥላችሁ ለምኑ። ይህ ሁሉ፥ ከዚህም እጅግ የሚበልጥ፥ ኢየሱስ ከአሥራ ሁለቱ ጋር የተቀመጠበት ማዕድ ትምህርት ነው። የሮም ቤተ ክርስቲያን ከታወቁት ሠዓሊዎቿ አንዱ የሆነው ሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ ጌታችን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀምጦ የሣለውን ሥዕል ሁሉ ለምን ገዝታ እንደማታጠፋው ብዙ ጊዜ ተደንቄአለሁ፤ እነዚህ ሥዕሎች በዚህ ጉዳይ የጳጳሱን ተከታዮች ትምህርት ይቃወማሉና። ያ ሥዕል በግድግዳው ላይ እስካለ ድረስ፥ ቅጂዎቹም በየስፍራው እስከ ተሰራጩ ድረስ፥ የሮም ቤተ ክርስቲያን መሠዊያ በማቆም የቀደመችቱን ቤተ ክርስቲያን ትምህርት በመቃወም ተፈርዶባታል፤ ጌታ ያልተንበረከከበት፥ እንደ ሚያገለግል ካህንም ያልቆመበት፥ ነገር ግን እርሱና ደቀ መዛሙርቱ የተቀመጡበት የኅብረት ማዕድ እንጂ የመሥዋዕት መሠዊያ እንዳልተቈጠረ ራስዋ ታምናለችና። እኛ ግን ቢያንስ ከጥንቱ ዘመን የሚመጣ ተግሣጽ አንፈራም፤ የመጀመሪያውን ሥርዓት እንከተላለንና፥ ልንከተልም እንወስናለን። ጌታችን እስኪመጣ ድረስ ይህን እንድናደርግ አዝዞናል፤—እንድንለውጠው ሳይሆን እስኪመጣ ድረስ በዚያው ሁኔታ «ይህን» ብቻ እንድናደርግ፥ ሌላም ምንም እንዳናደርግ።

3ኛ. ፍጻሜ ስናደርግ፦ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ከመቀመጡ ሌላ ምን ሊረዳ ይቻላል? ብለን እንጠይቅ።

እመልሳለሁ፤ በመጀመሪያ፥ ከዚህ የቅዱሳን ሁሉ እኩልነት ይረዳል። በዚህ አሥራ ሁለት ሐዋርያት ነበሩ። ነገር ግን ሐዋርያነታቸው በዚህ ጉዳይ አይመለከትም። ሐዋርያት ሁሉ ወደ ሰማይ ከሄዱ በኋላ የጌታ ራት በተከበረ ጊዜ፥ ሐዋርያት ስለ ሄዱ አንዳች ለውጥ ሊደረግ ነበረን? ፈጽሞ። አማኞች ጌታቸው እስኪመጣ ድረስ ለመታሰቢያው ይህን ሊያደርጉ ይገባቸዋል። የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ሁሉ ከቤተ ክርስቲያን በሄዱ ጊዜ እንዲለወጥ ትእዛዝ አልነበረም፤ አይደለም፥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ያው መሆን ነበረበት፤—እንጀራና የወይን ጠጅ በማዕድ ዙሪያም መሰብሰብ። እንግዲህ የቅዱሳንን ሁሉ እኩልነት እረዳለሁ። በሹመት ልዩነት አለ፥ በተአምራት ስጦታም ልዩነት ነበረ፥ በጸጋ እድገትም ታላቅ ልዩነት አለ፤ ቢሆንም በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ ቅዱሳን ሁሉ፥ ሐዋርያትም ቢሆኑ፥ እረኞች፥ መምህራን፥ ዲያቆናት፥ ሽማግሌዎች ወይም ተራ አባላት፥ ሁሉም እኩል ሆነው በአንድ ማዕድ ይበላሉ። እዚህ አንድ እንጀራ ብቻ፥ አንድ የወይን ፍሬም ብቻ አለ።

እነዚያ በፖለቲካ ዓለም እጅግ አደገኛ የሆኑት ቃላት፦ «ነጻነት፥ እኩልነትና ወንድማማችነት»፥ ከሕልም ያለፉ ሊሆኑ የሚችሉት በእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ብቻ ነው። ኢየሱስ ባለበት በዚያ ታገኙአቸዋላችሁ፤ በሪፐብሊክ ሳይሆን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት፥ ገዥነትና ሥልጣን ሁሉ በእርሱ ብቻ በሆነበት፥ ሁላችንም በፈቃዳችን እንደ ክቡር ራሳችን በምንቀበለው፥ ሁላችንም ወንድማማች በሆንንበት። የቀደሙት አማኞች ከእኛ የበለጠ ባሕርይ እንደ ነበራቸው ፈጽሞ አታስቡ። እዚያ ማዶ ተቀምጠው ስላሉት ስለ ቅዱስ ዊልያምና ስለ ቅዱሲት ጄን ለመናገር ካልተዘጋጃችሁ በቀር ስለ ቅዱስ ጳውሎስ፥ ስለ ቅዱስ ማቴዎስና ስለ ቅዱስ ማርቆስ አትናገሩ፤ እነዚህ በክርስቶስ ቢሆኑ እንደ እነዚያ የመጀመሪያ ቅዱሳን በእውነት ቅዱሳን ናቸውና፤ ወግ ቅዱሳን ብሎ ከሰየማቸው ከብዙዎቹ ይልቅ ከፍ ወዳለ ቅድስና የደረሱ አንዳንዶች ሊኖሩ እንደሚችሉም አስባለሁ። የቅድስና ከፍታዎች በጸጋ ለሁላችን ክፍት ናቸው፤ ጌታም እንድንወጣ ይጋብዘናል። ጌታ በቀደሙት ቅዱሳን የሠራው በእናንተ ሊሠራ አይችልም ብላችሁ አታስቡ። እንዲህ ስለምታስቡ ስለ እርሱ አትጸልዩም፤ ስለ እርሱም ስለማትጸልዩ አታገኙትም። የእግዚአብሔር ጸጋ ሐዋርያትን አጸናቸው፤ ያ ጸጋ ዛሬ ያኔ ከነበረው አያንስም። የጌታ ክንድ አላጠረችም፤ ኃይሉም አልተወሰነም። ብቻ ማመን ብንችል፥ እንደ እነዚያም የመጀመሪያ ቅዱሳን ትጉዎች ብንሆን፥ ገና መንግሥታትን እናስገዛለን፤ የግሪክና የሮም ጥንታዊ ፍልስፍናዎችና ጣዖታት በክርስቶስ የመጀመሪያ አገልጋዮች ትምህርት እንደ ተገለበጡ፥ እንዲሁ የሂንዱ አማልክትና የመሐመድ ሐሰት የሮምም ውሸቶች በእርግጥ የሚገለበጡበት ቀን ይመጣል። ያው ማዕድ ለእናንተ አለ፤ ያው መብልም በምሳሌ በዚያ አለ፤ ጸጋም እንደ እነዚያ ቅዱሳን ሰዎች ሊያደርጋችሁ ይችላል፤ በዚያው ደም ተገዝታችኋልና፥ በዚያውም መንፈስ ሕያዋን ሆናችኋልና። ብቻ እመኑ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላልና።

በጥቂቱ ብቻ የምጠቁመው ሌላው ነገር ይህ ነው፤ የቤተ ክርስቲያን ፍላጎት በዘመናት ሁሉ ያው ይሆናል፥ ለቤተ ክርስቲያንም ፍላጎት የሚቀርበው ፈጽሞ አይለወጥም። ማዕዱ ገና ይኖራል፤ ያንኑ መብል የያዘ ማዕድ፤—ለመብል አሁንም እንጀራ፥ ከእንጀራ የበለጠ ምንም አይደለም፤ ለመጠጥ አሁንም የወይን ጠጅ፥ ከወይን ጠጅ ያነሰ ምንም አይደለም። ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ ያንኑ መብል፥ ያንኑ ክርስቶስ፥ ያንኑ ወንጌል ትሻለች። ወንጌላችንን ለዚህ ለበራለት 19ኛው መቶ ዘመን እንዲስማማ እንድናስተካክል የምትነግሩን ከሃዲዎች ሆይ፥ ወዮላችሁ! ፀሐይንና ጨረቃን ከዋክብትንም የሚያልፈውን የዘላለም እውነት የምትመኩበት ግን የተቀባ ድንቁርና ብቻ ለሆነው ለባህላችሁ እንዲስማማ እንድናለዝበው የምትሹ ሐሰተኛ ልቦች ሆይ፥ ወዮላችሁ! አይደለም፤ በጥንት ምሽግን ለመስበር በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ የነበረው እውነት አሁንም ብርቱ ነው፤ እስከ ሞትም እንጠብቀዋለን፤ ጳውሎስ ወይም አውግስጢኖስ ወይም ካልቪን በሰበኩበት ጊዜ እንደ ነበረው ቤተ ክርስቲያን ዛሬም የጸጋን ትምህርቶች ትሻለች፤ በእምነት መጽደቅን፥ ምትክ የሆነውን ስርየት፥ ዳግመኛ መወለድንና የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት እንደ ጥንቱ ዘመን ከመድረኮችዋ እንዲሰበክ ትሻለች፤ በእግዚአብሔርም ጸጋ ታገኛቸዋለች።

በመጨረሻም፥ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ሁሉ ወደ ማዕድ ባልንጀርነት ስፍራ ባመጣበት በዚህ እውነት ውስጥ፥ ይህ ለሕዝቡ ሁሉ ለዘላለም ዕድል ፈንታቸው እንደሚሆን ትንቢት አለ። በሰማይ ከምድር ያነሰ መብት ሊኖር አይችልም። በሰማያዊው ሕይወት አማኞች በምድር ከነበሩበት ስፍራ ዝቅ ይደረጋሉ ማለት አይቻልም። እንግዲህ በምድር ምን ነበሩ? የማዕድ ባልንጀሮች። በላይ በሰማይስ ምን ይሆናሉ? አሁንም የማዕድ ባልንጀሮች፤ በእግዚአብሔርም መንግሥት እንጀራ የሚበላ ብፁዕ ነው። «ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር በእግዚአብሔር መንግሥት ይቀመጣሉ»፤ ጌታ ኢየሱስም በማዕዱ ራስ ይሆናል። እንግዲህ የደስታው ማዕድ ምን ይሆን? ምናባችሁን አሠሩ፤ ዋጋው ሁሉ በፊቱ በሆነ ጊዜ፥ ድሉም ሁሉ በተፈጸመ ጊዜ የነፍሱ በዓል ምን እንደሚሆን አስቡ። አስባችሁታልን? ልትገምቱትስ ትችላላችሁን? ምንም ቢሆን ትካፈሉበታላችሁ። እነዚያን ቃሎች እደግማለሁ፤ ምንም ቢሆን ከአማኞች ታናሹ ይካፈልበታል። አንቺ ድሀ ሠራተኛ ሴት ሆይ፥ ድካምሽና ችግርሽ ሁሉ ለዘላለም አብቅቶ በመሳፍንት መካከል በጌታሽ በኢየሱስ አጠገብ መቀመጥ ለአንቺ እንዴት ያለ ለውጥ ነው! አንተም የመከራ ልጅ የሆንህ አሳዛኝ ሆይ፥ ወደ እግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ ለመምጣት የማትችል ያህል የሆንህ፥ ምናልባትም ወደዚያ የሕማም አልጋ እንደ ገና የምትመለስ፥ በዚያ ምንም ሥቃይ አይኖርብህም፤ ነገር ግን ሁልጊዜ ከጌታ ጋር ትሆናለህ፤ የክርስቶስም ደስታ ለዘላለም ዓለም ደስታህ ይሆናል! ወይ፥ የዶክተር ዋትስን እነዚህን ቃሎች ልትረዱ አትችሉምን?—

«አዎን፥ ገና ሳንነሣ

ወደዚያ ወደማይሞተው ሕይወት፥

የዚያ የሚያስደንቅ ብፅዕና ሐሳብ

ዘወትር ደስታን ሊፈጥር ይገባል»?

የእናንተ የሚሆነውን ደስታ በመጠባበቅ የአሁኑን መከራችሁን እርሱ፤ ከዚህ ሰዓት ችግሮች በላይ ከፍ በሉ፤ በአሁኑ ጊዜ ደስ ሊላችሁ ባትችሉ እንኳ፥ ፈጥኖ የእናንተ በሚሆነው በሚመጣው ደስ ይበላችሁ።

በዚህ ጥልቅ የሐዘን ቃል እንፈጽማለን፤—እዚህ ያሉት ብዙዎች የተናገርነውን ሊያስተውሉ ስለማይችሉና በእርሱም ዕድል ስለሌላቸው ያለ ሐዘን። ከእናንተ አንዳንዶቻችሁ ክርስቶስን ስለማትወድዱ ወደ ቍርባን ማዕድ መምጣት የለባችሁም። በእርሱ አልታመናችሁም፤ በእርሱ ዕድል ፈንታ የላችሁም። በምሥጢራት ውስጥ መዳን የለም። እመኑኝ፥ በልባቸው ወደ ክርስቶስ ለማይመጡ እነዚህ ማታለያዎች ብቻ ናቸው። የተመሰለውን ነገር ሳይኖራችሁ ወደ ውጫዊው ምልክት መምጣት የለባችሁም። የመዳን መንገድ ይህ ነው፤ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን፥ ትድናለህም። በእርሱ ማመን በእርሱ መታመን ነው፤ የጥንት ቃል ብንጠቀም፥ መደገፍ ነው፤ በእርሱ መደገፍ፥ በእርሱ ማረፍ ነው። እዚህ እደገፋለሁ፤ በፊቴ ባለው በዚህ መደገፊያ ላይ ክብደቴን ሁሉ አሳርፋለሁ፤ በመንፈሳዊ ትርጉም በክርስቶስ እንዲሁ አድርጉ፤ በእርሱ ተደገፉ። የኃጢአት ሸክም አለባችሁ፤ ከኃጢአታችሁ ጋር በእርሱ ተደገፉ። ሁላችሁ የማትገቡ፥ ደካሞች፥ ምናልባትም ጐስቋሎች ናችሁ፤ እንግዲህ ድካሙን፥ አለመገባቱን፥ ጕስቍልናውንም ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉ። ሁሉ በሁሉ እንዲሆንላችሁ ተቀበሉት፤ እንዲህም በእርሱ በታመናችሁ ጊዜ ተከታዩ ትሆናላችሁ፤ ከዚያም በትሕትና ደቀ መዝሙሩ፥ በመታዘዝ አገልጋዩ፥ በፍቅር ወዳጁ፥ በኅብረትም የማዕድ ባልንጀራው ለመሆን ወደ ፊት ቀጥሉ።

ስለ ኢየሱስ ብሎ ጌታ እንዲህ ይምራችሁ! አሜን።

ጨርሰዋል፦ ክርስቶስና የማዕድ ባልንጀሮቹ

ቀዳሚ ቀጣይ