ምዕራፍ 20 · 15 ደቂቃ ንባብ · 20 ደቂቃ ማዳመጥ
የጠነከረው ጥሪ
«አንዳንድ ጊዜ ወንዶቹና ወንዶች ልጆቹ ሄደው ከሴቶቹ ጋር እንድንነጋገር አይተዉንም፤ በእንዲህ ያለ ጊዜ ከሁሉ የተሻለ መጠጊያ ሆኖ የማገኘው በዝምታ መጸለይ ነው። በሌሎች ስፍራዎች ሰዎቹ በደስታ ይቀበሉሃል፥ ነገር ግን ከኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት በቀር ማንኛውንም ነገር ያዳምጣሉ፤ ይህ ደግሞ ከማውቀው ከማንኛውም ነገር ይልቅ ለመሸከም የከበደ ነው።»
አና ጎርደን፥ ቻይና።
«በአገር ቤት ያሉ ሰዎች ስለ ስኬቶች ብቻ መስማትን አይውደዱ፤ በትግሉም ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ልናሠለጥናቸው ይገባናል።»
ቄስ ኤ. ሽራይበር፥ ሱማትራና ሕንድ።
«ይህ ከአካል፥ ከአእምሮና ከመንፈስ ኃይላት ብዙ የሚጠይቅ ውጊያ ነው፤ ተቃዋሚዎችም ብዙ ናቸው። የአሕዛብነት ከባድ ሸክም፥ የሰው ዓላማና ግብ በጥቂቱ ብቻ መታወቁ፥ የጨለማ ኃይላትም ትክክለኛና ብርቱ ተቃውሞ እውነተኛ ውጊያ ያደርጉታል፤ የሚያሸንፉትም ጽናት፥ ድፍረት፥ ታማኝነት፥ ወሰን የሌለው ትዕግሥትና መጽናት ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው።
ተስፋ የሚያስቆርጥ ሥዕል ሥዬ ይሆን? በፈቃዳቸው ቀርበው በመልካም ሊሠሩ ይችሉ የነበሩ መልካም ሰዎችን እያስፈራሁ ይሆን? አይመስለኝም። ትክክለኛዎቹ ሰዎች፥ በፈቃዳቸው ሊቀርቡ የሚገባቸው፥ በችግሮቹ ከመገፋት ይልቅ እንደሚሳቡ አስባለሁ።»
ቄስ ጄ. ላምፓርድ፥ ሕንድ።
ይህን ፎቶግራፍ ያገኘነው ወዳጅነት በሞላበት በብራህማኖች መንገድ ባሳለፍነው በዚያ የታኅሣሥ ቀን ነበር። ወደ ፊት ቀርባ፥ ፎቶ ለመነሣት ምንም ሳታስብ፥ ለአፍታ ከግድግዳው ጋር ቆማ ካሜራውን ትኩር ብላ ስትመለከት፥ ወንዶቹ «በዚህ ከተማ ለእናንተ እንዲህ የምትቆም ሌላ አንዲት ሴት የለችም!» አሉ። አብዛኞቹ ሴቶች ወደ ካሜራው ዓይናቸውን ለመጣል እንኳ ፈሩ፤ እርሷ ግን አልፈራችም። ይሁን እንጂ ከእኛ ጋር ለመነጋገር አልቆየችም፤ በዚያው ቈራጥ ሁኔታ ተራምዳ ሄደች። ብራህማን መበለቶች በአጠቃላይ በምንም ዓይነት በቀላሉ የሚቀረቡ ወገን አይደሉምና። አንዳንድ ጊዜ ልቧን የምትከፍትልንና እኛ በተጽናናንበት መጽናናት እንድንነግራት የምትፈቅድ አንዲት እናገኛለን፤ ብዙ ጊዜ ግን ደንዳኖች ሆነው ወይም በፍጥነት እየደነደኑ እናገኛቸዋለን።
ባለፉት ጥቂት ወራት ስላዳመጡት ስለ ማንኛቸውም ለመጻፍ ገና ጊዜው አልደረሰም፤ ነገር ግን ይህን ፎቶ ያስገባነው፥ የእርሱ ፍቅር የመሳብ ዕድል እንዲያገኝ ብቻ ቢፈቅዱለት፥ በሕንድ ካሉት ከአብዛኞቹ ሴቶች ይበልጥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል ነጻነት ያላቸውን እንድታስቡአቸው ለማሳሰብ ነው። በዚህኛውና በላይኛው የተራሮቹ ጥምዝ ወዳሉት ልዩ ልዩ ከተሞች ሄደናል፤ ነገር ግን በታችኛው ጥምዝ ወዳሉት ከተሞች፥ ወይም ከተራሮቹ ሥር ተጠግተው ከተበተኑት ብዙ መንደሮች ወደ ግማሹ እንኳ አልደረስንም፤ በድንኳን ሰፍረን ከወጣንበት ጊዜ በቀር፥ ራቅ ብለው ያሉትንማ በእርግጥ አልነካናቸውም።
በሳምንት ውስጥ የሥራ ከሰዓት በኋላዎች አምስት ብቻ ናቸው፤ ቅዳሜ ለሌሎች ጉዳዮች ይሰጣልና፥ እሑድም የክርስቲያኖች ነው፤ ጥቂት ፍላጎት በታየ ጊዜም ወደዚያው መንደር እንደ ገና እንመለሳለን፤ ይህ ያዘገየናል፥ ነገር ግን በእርግጥ ዋጋ አለው። ከዚያም መቋረጦች አሉ—አንዳንድ ጊዜ በሂንዱዎቹ በኩል፤ ለምሳሌ ማንኛዪቱም ሴት ለመስማት ጊዜ የሌላት የበዓላት ጊዜ፤ በእኛም በኩል፥ በአየሩም በኩል ማለት ይቻላል፥ ብርቱ ሙቀት ወይም ብርቱ ዝናብ ከቤት ውጭ መሥራትን የማይቻል ሲያደርገው። በንድፈ ሐሳብ ደረጃ እየተዘዋወሩ ማገልገል በሚያስደስት ሁኔታ ፈጣን ነው፤ በተግባር ግን፥ እየተዘዋወረ የሚያገለግል ሚስዮናዊ ሁሉ እንደሚያውቀው፥ እጅግ ዘገምተኛ ነው። የሚሠሩ ሌሎች ነገሮች አሉ፤ ቀድሞ የገቡት ሊማሩ፥ ሊሠለጥኑና በእናትነት ሊያዙ ያስፈልጋል፤ ስለ ተጨማሪዎችም እግዚአብሔርን በመጠበቅ ብዙ ጊዜ ሊያልፍ ይገባል፤ ስለዚህ ወደ ኋላ ስንመለከት በዙሪያችን ላሉት ሺዎች እጅግ ጥቂት ያደረግን ይመስለናል፤ አሁንም ወደ አውራጃው ምሥራቃዊ ክፍል መመለስ አለብን፤ ከተመላሾቹ ወንዶች ልጆች አንዳንዶቹ በዚያ በትምህርት ቤት አሉና፥ ካለፈው ዓመት ዘርም በኋላ የሚሰበሰብ ፍሬ ሊኖር ይችላልና።
እኔ ግን ከምጽፈው ቀና ብዬ ሠላሳ ማይል የሚረዝም የተራራ ሰንሰለት አያለሁ፤ ይህም ሰንሰለት ሳይቋረጥ ወደ ሰሜን አንድ ሺህ ማይል ይዘረጋል። ከታች ባሉት ሜዳዎች ምን ያህል ጥቂት እየተሠራ እንዳለ አውቃለሁ፤ የእግዚአብሔር ሕዝብ መቼ እንደሚነቃ፥ የሚወረስ እጅግ ብዙ ምድር ገና እንደ ቀረ መቼ እንደሚያስተውል፥ ተነሥቶም መቼ እንደሚወርሰው እደነቃለሁ። ከእኔ ጋር ይህን የተራራ ቁራጭ ቍልቍል ተመልከቱ፤ ሥራ የሚሠራባቸው ከተሞች አሉ፥ ነገር ግን ክትትል ያስፈልጋቸዋል፤ ሚስዮናውያኑም በሚገባ ሊያደርጉት እጅግ ጥቂቶች ናቸው። ቢቻል በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ የወንዶች ተዘዋዋሪ ቡድን ከመምጣቱ በቀር ምንም ነገር ለመሞከር እንኳ ያልተደረገባቸው ከተሞችና ብዙ መንደሮች አሉ፤ ይህ ግን ሴቶቹን በሚገባ አይደርስም፤ ቢደርስም እንኳ፥ አንድ ምሳሌ ወይም አንድ ተአምር ወይም ከሕይወቱ ጥቂት ድርጊቶችን ወይም ከትምህርቱ ጥቂት ነጥቦችን የምትሰሙት በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ቢሆን ኖሮ ስለ ኢየሱስ ምን ያህል ታውቁ ነበር? ልብ የሚነኩ ልመናዎችን ለመጻፍ ወይም ከሌላ ከማንኛውም ስፍራ አንድን ሠራተኛ እንኳ ለመሳብ አልፈልግም፥—እግዚአብሔር እነዚህን ደብዳቤዎች አንድን ሰው ወደ ቻይና፥ ወይም ሠራተኞቹን ወደሚፈልግበት ወደ ማንኛውም ስፍራ ለመላክ እንደ ተጠቀመባቸው ባውቅ ደስታ በሆነልኝ ነበር፥—ነገር ግን ይህን የእርሻውን ቁራጭ ዙሪያዬን ስመለከት ሠራተኞቹ እስከ አሁን ድረስ እንዴት እንዲህ ጥቂቶች እንደ ሆኑ ከመደነቅ ልቆጠብ አልችልም።
በከተሞቹና በመንደሮቹ ያሉ ሰዎች ወደ ቤታቸው እንድንገባ በማይፈቅዱበት ጊዜ «የበረንዳ ሥራ» የምንለውን እንድንሠራ ፈቃደኞች ሆነው አግኝተናቸዋል። የበረንዳ ሥራ፥ እንደ ሜዳ ስብከት፥ ሴቶቹን በተመለከተ አጥጋቢ አይደለም፤ ነገር ግን ከምንም ይሻላል።
ይህ ፎቶ በሚያሳየው መንገድ አንድ ከሰዓት በኋላ አሳለፍን። መተላለፊያ መንገድ ነው፤ ስለዚህ አልተከለከልንም፤ እንዲያም ሆኖ በእርሱ ከመሄዳችን በፊት ሁልጊዜ ፈቃድ እንጠይቃለን። ለእናንተ እንዴት ያለ ተራና የተለመደ መንገድ ይመስላል፤ ተመልካቹን የሚያስፈራና የብራህማንነትን ግርማ የሚያሳድርበት የሕንጻ ታላቅነት የለውም፤ ቢሆንም ያ መንገድ፥ እንደ እርሱም ያለ መንገድ ሁሉ፥ ለእኛ እውነተኛ ፔትራ ነው፤ በዙሪያው ከተሠራለት የቤተ መቅደስ ቅጥር ይልቅ ከፍና ጠንካራ በሆኑ ቅጥሮች ተከቧልና፤ ቅጥሮቹ ከአንድ ዓይነት የብርሌ ዓለት የተሠሩ ይመስላሉ፤ እስክትደርሱባቸው ድረስ አይታወቁም፥ ያን ጊዜም እንኳ አይታዩም፥ ልታልፉት የማትችሉት ነገር እንደ ሆኑ ብቻ ይታወቃሉ።
በዚያ የነበረን የመጀመሪያ ቀን የሚያበረታታ ነበር። ከመንገዱ ሩቅ ጫፍ ጀመርን፤ ከጥቂት ማግባባትም በኋላ ወንዶቹ ወደ አንድ ወገን ዘወር ለማለትና ሌላውን ወገን ለሚመጡት ሴቶች ሁሉ ሊተዉልን ተስማሙ። የተለየ ነገር አልሆነም፤ ነገር ግን ለሴቶቹ በጸጥታ ለመናገር አንዲት መልካም ዕድል እንኳ ብናገኝ ቀኑን መልካም አድርገን እንቆጥረዋለን።
በሚቀጥለው ጊዜ ስንሄድ እንደዚያ መልካም አልነበረም። በመካከሉ ስለ እኛ ሁሉን ሰምተው ነበር፤ ከላይኛዎቹ ካስቶች የመጡ ልጃገረዶችም ከእኛ ጋር እንዳሉ ሰምተው ነበር፤ ይህም በዓይናቸው እጅግ አስከፊ ነበር። ብራህማኑ ከፍፁም የበላይነቱ ከፍታ ዝቅተኛ ካስት የሚላቸውን ሰዎች ነፍሳት እጅግ አሳንሶ ይቆጥራልና፤ ነገር ግን ከመካከለኛው ርቀት ያሉት (ለራሱ ቅርብ ናቸው አይላቸውም፤ ከሌሎቹ ይልቅ በአደገኛ ሁኔታ ቀረብ ያሉ ብቻ ናቸው) ማንኞቹም «በክርስትና ሃይማኖት ጕድጓድ ውስጥ ቢወድቁ»፥ በእነርሱ ላይ እንዲህ ያለ ውጤት ያመጣው ኃይል በእርሱ ላይ፥ ከሁሉም በላይ በሴቶቹ ላይ የመሥራት ዕድል እንዳያገኝ መጠንቀቅ የሚጀምርበት ጊዜ እንደ ደረሰ ያስባል። ስለዚህ በዚያ ቀን ማንም ለማዳመጥ ጊዜ እንደሌለው በትሕትና ተነገረን፤ አንዳንድ ሴቶች ሊመጡ በፈለጉ ጊዜም አንዲት ጡንቻማ መበለት አባረረቻቸው። ወደ እነዚያ ውድ ብራህማን ሴቶች በናፍቆት ወደ ኋላ ተመለከትን፤ ነገር ግን መለመን ከንቱ ነበር፤ ስለዚህ ሄድን።
ከሌሎቹ ካስቶች በአንዱ፥ ይህ የወንዶች ረድፍ በሚወክለው ካስት፥ የበለጠ ወዳጅነት አገኘን፤ በጠባቦቹ የበረንዳ ፊቶች በአንድ ጫፍ እንድንቀመጥ ፈቀዱልን፤ በሌላውም ጫፍ ብዙ ሴቶች ተሰበሰቡ። በዚያ መርከስን እጅግ ፈሩ፤ በጣም ቀርበውም አይመጡም ነበር። ስለ እኛም እጅግ እንግዳ የሆኑ አሳቦች ነበሯቸው። ቢያሸቱት ክርስቲያኖች እንዲሆኑ የሚያስገድዳቸው ዱቄት እንዳለን እርግጠኞች ነበሩ። «ልጆችን እየጠራን» እንዞራለን፥ ማለትም በእጃችን እየጠቀስን እንዲከተሉን እንስባቸዋለን፥ ስለ ተመላሾችም በራስ ይህን ያህል ይከፈለናል ብለው ሰምተው ነበር። እንዲህ ያሉትን የተሳሳቱ አሳቦች ከአእምሮአቸው ለማስወገድ ብቻ አንዳንድ ጊዜ አንድ ሙሉ ከሰዓት በኋላ ይወስዳል።
ይህ የነገሩ የንግድ ገጽታ፥ የሚያውቅ በሚመስል ሰው ሲብራራ ሰማሁ። አንዲት ደግ አሮጊት ብራህማን ሴት ከፀሐይ ተከልለን በደጃፏ እንድንቀመጥ ፈቅዳልን ነበር፤ እኛም ቀስ በቀስ ጥቂት ጥላ ወዳለው ወደ በረንዳው ጫፍ ተጠጋን፤ በዚያም መስማት የፈለገች የምትመስል አንዲት ልጃገረድ ብቻዋን ተቀምጣ ነበር። አሮጊቲቱ ከኋላችን ተቀመጠች፤ ከዚያም አንድ ሽማግሌ መጣ፤ ሁለቱም መነጋገር ጀመሩ። አሮጊቲቱ ሽማግሌውን፥ «ወደ መንገዷ እንድንገባ ልታደርገን እየሞከረች ነው» አለችው። (እኔ እንዲህ ያለውን አነጋገር በጥንቃቄ ተቆጥቤ ነበር።) ሽማግሌውም ዓላማዬ ምናልባት ይህ እንደ ሆነ ተስማማ። «ብንገባ ምን ታገኛለች? ታውቃለህ?» «አዎን፤ እንዴት አላውቅም! ከእኛ ለአንዱ አንድ ሺህ ሩፒ፥ ለአንድ ቬላላር ደግሞ አምስት መቶ። ለዝቅተኛ ካስት ልጅ እንኳ አንድ ነገር ታገኛለች፤ ለአንዱ ከእኛ ግን ሙሉ አንድ ሺህ ታገኛለች!»
ሁለቱም በዚህ ጭውውት እጅግ ተመሰጡ፤ እኔም በእርግጥ ተመስጬ ነበር፤ ይበልጥ ላስረዳቸውም አሰብሁ፤ ነገር ግን አሮጊቲቱ በችኮላ ተነሥታ እያነከሰች ወደ ቤቱ ገባች። ከዚያ ወዲያ በአጠገቧ ባለፍን ቍጥር ራሷን እየነቀነቀችብን «ቺ፥ ቺ!» ትል ነበር። በደጃፏ እንደ ገና እንድንቀመጥ እንድትፈቅድልን ምንም ዓይነት ማግባባት ሊያሳምናት አልቻለም። ያን አንድ ሺህ ሩፒ እንደምንፈልግ ግልጽ ነበር፤ እርሷም ከእኛ ጋር ምንም ግንኙነት አልፈለገችም።
በዚያው መንደር ብዙ ጊዜ ልታነጋግረን የምትሞክር፥ ነገር ግን ፈጽሞ ያልተፈቀደላት አንዲት ትንሽ ብራህማን ልጅ ነበረች። አንድ ቀን መያዝንና የሚያስከትለውን ሁሉ ደፍራ፥ የብራህማኖችን መንገድ ከመንደሩ የሚለየውን ጠባብ ወንዝ ተሻግራ ሮጠች፤ ከቡድናችንም አንዷን በችኮላ በትንሽ ሹክሹክታ፥ «ኦ፥ ስለ ኢየሱስ መስማት እንዴት እፈልጋለሁ!» አለቻት። በገዛ ከተማዋ በትምህርት ቤት እንደ ተማረች፥ ከዚያም በዚህ የጫካ መንደር ወዳለው ወደ አማቷ ቤት እንደ ተላከች ነገረቻት፤ «ያኛው» አለች፥ ለእኛ ፈገግታ ፈጽሞ ወደማያሳዩበት ቤት እያመለከተች፤ አማቷ ግን ስብከቱን ተቃወመች፤ እኛንም ብታዳምጥ ወደ ጕድጓድ ውኃ ልትጥላት ዝታባት ነበር። በዚያን ጊዜ አንድ ጨካኝ ድምፅ ጠራት፤ እርሷም በረረች። በሚቀጥለው ጊዜ ወደዚያ መንደር ስንሄድ በውስጥ በአንድ ስፍራ ተዘግቶባት ነበር።
ብዙ ጊዜ በዚያ ሲያልፉ ሰው በረንዳዎቹን ከሚደግፉት ትንንሽ ዓምዶች በስተኋላ ሆነው የሚመለከቱ አፋር ፊቶችን ያያል፤ ይበልጥ ለመቅረብም ይናፍቃል። ነገር ግን ሰው በአቋሙ እርግጠኛ ካልሆነ በቀር አንዳች ቅርበት ለማድረግ መሞከር አይገባም። ውጤቱ በድንገት ደንግጠው በሩጫ ወደ ቤት መግባት ብቻ ነው፤ ወደዚያም ልትከተሏቸው አትችሉም። ይህን ለማድረግ መሞከር ከብልግና የበለጠ ነው—እንደ መርከስ ይቆጠራል።
ልክ ትናንት ከቤታችን በስተኋላ ባለው መንደር ታላቅ ቤት ውስጥ ወደሚኖሩት ሴቶች ለመድረስ እየሞከርን ነበር። ይህ ፎቶ አሥር ደቂቃ ወይም ከዚያ በላይ ፊት ለፊት ቆመን የነበርንበትን በር ያሳያችኋል፤ መጀመሪያ እየጠበቅን፥ ከዚያም ከበሩ በስተኋላ የአንዲት ሴት መልክ ተደብቆ ልታዩ ወደምትችሉበት ወደዚያች ትንሽ ጨለማ ክፍል እንድታስገባን አሮጊቲቱን አማት እየለመንን።
ነገር ግን እኛ ወደ እነርሱ መሄድ አልቻልንም፤ እነርሱም ወደ እኛ መምጣት አልቻሉም። በመካከል ሁለት ጠባብ ክፍሎች ብቻ ነበሩ፤ ነገር ግን ከሁለቱ ሁለተኛው የናስ የውኃ ዕቃዎች ነበሩበት። ብንገባ ኖሮ እነዚያ ዕቃዎችና በውስጣቸው ያለው ውኃ በረከሱ ነበር። ሴቶቹ እንዲወጡ አልተፈቀደላቸውም፤ አማቲቱ ይህን በሚገባ ተቆጣጠረች፤ ከእርሷ የበለጠ ንቁ ጠባቂ ፈጽሞ አልነበረም። እንደ አንዲት ታላቅ ወፍራም ዶሮ በበሩ ላይ ቆማ፥ ነጭ የመበለት ቀሚሷን እንደ ክንፍ ዘርግታ ጫጩቶቿን በሚገባ ጠበቀች። «ሂዱ! በመጣችሁበት መንገድ ሂዱ!» ለእኛ የነበራት ቃል ይህ ብቻ ነበር።
የቤቱ ወዳጅ ሽማግሌ ወጥቶ ነበር። አንድ ወዳጅ ወጣት ሩዝ ይዞ ገባና ይሰፍረው ጀመር። እንድንቀመጥ ጋበዘን፤ ተቀመጥንም፤ እርሱም ሩዙን በትንንሽ የብረት ጽዋዎች ሰፈረ፤ ሲሰፍርም በዜማ ቃና ጮክ ብሎ ይቈጥር ነበር። እንድንመለከተው ደስ አለው፤ መመልከቱም የሚያስደስት ነበር፤ ጥቅሱ እንደሚገልጸው በትክክል አደረገውና፤ ሩዙን እየተጫነ፥ የብረቱን መስፈሪያ እየነቀነቀ፥ እስኪፈስስ ድረስ ሩዙን እያከመረ፥ ቢሆንም ይህን የተትረፈረፈ ጽዋ እንደ አንድ ብቻ እየቈጠረ፤ ከዚያም የሩዙን ቅርጫት ቆሞ ይጠብቅ ለነበረ ልጅ ሰጠና ለእኛ ምን ሊያደርግልን እንደሚችል ጠየቀ። የቤቱን ሴቶች ለማየት ምን ያህል እንደምንፈልግ ነገርነው፤ እርሱ ግን ያችን ብርቱ አሮጊት አማት መጋፈጥ አልወደደም፤ ስለዚህ ሙከራውን ትተን ወጣን። የሴቶቹን መኖሪያ የሚከልለውን የኋላ ቅጥር ስናልፍ አንዲት ልጃገረድ ልታነጋግረን የፈለገች ይመስል ከቅጥሩ በላይ ስትመለከት አየን፤ ነገር ግን ያች አምባገነን እመቤት ወዲያውኑ ወደ ኋላ ጐተተቻት፤ አንድ ውሻም እጅግ በቍጣ እየጮኸ ዘሎ ወጣ፤ ይህም በዙሪያችን ሌሎች ደርዘን ውሾች እንዲያላዝኑ አደረገ፤ እንዲህ ታጅበንም ተመለስን።
ይህ ቤት ከበራችን አምስት ደቂቃ እንኳ በማይርቀው በነጋዴው መንደር ውስጥ ነው፤ በውስጡ ያሉት ሴቶች ግን ለመስማት ከሚያስችላቸው ከማንኛውም ዕድል እጅግ የራቁ ናቸው። በዚያ ቀን ወንዶቹ ፎቶግራፉን እንድናነሣ አስገቡን፤ በዚህም ወዳጅነት እንመሠርታለን ብለን ተስፋ አደረግን፤ ነገር ግን በዚያ ስድስት ቤተሰቦች የሚኖሩ ቢሆኑም (ቤቱ ትልቅ ነውና፤ ፎቶግራፉ የሚያሳየው በርዝመቱ ሁሉ የሚዘልቀውን የበረንዳውን አንድ ጫፍ ብቻ ነው)፥ ከሴቶቹ አንዷን ለማነጋገር አንድ ጊዜ እንኳ ተፈቅዶልን አያውቅም፤ የስድስቱ ሁሉ አማት ዕድሉን ፈጽሞ እንዳናገኝ ትጠነቀቃለች። ከልጆቹ አንዷ፥ አንዲት ውድ ትንሽ ልጃገረድ፥ አንዳንድ ጊዜ ወደ ውጭ ትከተለናለች፤ ነገር ግን ገና የሰባት ዓመት ልጅ ናት፥ እምብዛም ደፋርም አይደለችም፤ ስለዚህ የምንዘምራቸውን አዝማቾች አንዳንዶቹን እንደምትቀስም ግልጽ ቢሆንም፥ ስታዳምጥ እንዳትታይ ትፈራለች፤ በአንድ ጊዜም ብዙ አታገኝም።
ወደ ሴቶቹ ለመድረስ በመንገድ ላይ ካሉት ተግባራዊ ችግሮች አንዳንዶቹ እነዚህ ናቸው። ሌሎችም አሉ። ብትገቡ እንበል፤ ወይም በአቅኚ ሥራ ይበልጥ እንደሚሆነው፥ በረንዳ ብታገኙ እንበል፤ ያን ጊዜም እንኳ ነገሩ በምንም ዓይነት ቀላል አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ በአደገኛ ሁኔታ ሞቃት ነውና። ፀሐይ ከተቀመጣችሁበት የድንጋይ ደረጃ እስከ አንድ ወይም ሁለት ጫማ ድረስ በመንገዱ ወይም በግቢው ላይ ትመታለች፤ ተመልሳም ወደ ላይ ትነጸባረቃለች። የሚነጸባረቅ ብርሃን ትኩሳት ማለት ነው፤ ስለዚህ የማንንም ስሜት ሳትጎዱ ከእርሱ ትንሽ ራቅ ለማለት ትሞክራላችሁ፤ በስውር ልትነኳቸው ያሰባችሁ እንዳይመስላቸው ለምን እንዲህ እንደምታደርጉ በዝርዝር እያስረዳችሁ፤ ከዚያም እስከዚህ ድረስ አመኔታቸውን ካገኛችሁ በኋላ፥ ምናልባት በቃል አልባው መጽሐፍ፥ ወይም በሕንድ ዜማ በተቃኘ መዝሙር፥ ወይም በአንድ ምሳሌ ሥዕል—ፈጽሞ የጌታችንን አይደለም—ትጀምራላችሁ፤ ወይም ከዚህም ይበልጥ ብዙ ጊዜ፥ ከሁሉ የተሻለው መንገድ መጽሐፍ ቅዱሳችንን መክፈት ሆኖ እናገኘዋለን፤ ሁሉም ቅዱስ መጽሐፍን ያከብራሉና፤ ከእርሱም እንደሚያስተውሉት የምናውቀውን አንድ ነገር እናነባለን። ብዙውን ጊዜ በበረንዳዎቹ አካባቢ አንድ ወይም ሁለት ሴቶች እናገኛለን፤ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥም ሌሎች ሁለት ወይም ሦስት ይመጣሉ፤ ይህንንም አይተው ሌሎች ሁለት ወይም ሦስት። ነገር ግን እነርሱን ማግኘትና ይዞ ማቆየት ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ሰዎች ለመስማት የተለየ ፍላጎት የሌላቸውን ነገር እንዲሰሙ ይዞ ማቆየት ቀላል አይደለም። እኛ ግን እንረዳለን፤ ብቻችንን አይደለንም። ይህን ማስታወስ ሁልጊዜ ብርታት ነው።
በሚገባ ከተጀመረ በኋላ መቋረጦች ይጀምራሉ። ምናልባት በአንድ ተአምር ታሪክ መካከል ናችሁ፤ በዚህ ጊዜም ደርዘን ሴቶች ተሰብስበው በሚገባ በማዳመጥ ልባችሁን ደስ ያሰኛሉ፤ ያን ጊዜ ከመንገዱ ማዶ አንድ ሰው ዘና ብሎ መጥቶ ጥያቄ ሊጠይቅ ይችል እንደ ሆነ ይጠይቃል፤ ወይም ወዲያውኑ ይጠይቀዋል። መጽሐፋችን እምነት ቢኖራችሁ ተራራን አንሥታችሁ ወደ ባሕር ልትጥሉ ትችላላችሁ እንደሚል ሰምቷል። እነሆ፥ በዚያ ተራራ አለ፤ ብሎ በሜዳው ላይ ቀጥ ብሎ አምስት ሺህ ጫማ ወደ ላይ የቆመውን፥ የጠንካራ ዓለት ዓምድ የሆነውን ምሰሶ ያመለክታል። በሌላው ወገን ባሕር አለ ይላል፤ ጣሉትና እናምናለን! ሴቶቹም ይስቃሉ። ነገር ግን ይበልጥ አስተዋይ የሆነች አንዲት ወደ እናንተ ዞራ፥ «መጽሐፋችሁ በእርግጥ እንዲህ ይላልን?» ብላ ትጠይቃለች፤ «እንግዲያስ ለምን አድርጋችሁ አታሳዩንም?» ሰውዬውም ሌላ አስተያየት ጣልቃ ያስገባል፤ በዳር ያለች አንዲት ሴትም ትሄዳለች፤ እናንተም ሰውዬው ቢሄድ ብላችሁ ትመኛላችሁ።
ምናልባት ይሄዳል፤ ወይም ምናልባት ከሚታየው ነገር ልትለዩት ትችላላችሁ፤ እርሱንም እነዚያንም ሴቶች የማይታየውን ስለሚያንቀሳቅሰው ኃይል ለሚሰጥ አንድ የምስክርነት ቁራጭ እንዲያዳምጡ ታደርጋላችሁ፤ በልቡም መካከል ሳላችሁ ሌላ ተቃውሞ ይነሣል፦ «አንድ እውነተኛ አምላክ ብቻ አለ ትላላችሁ፤ እኛ ግን ሦስት እንደምታመልኩ ሰምተናል!» ወይም «አምላካችሁ ከኃጢአት ሊጠብቃችሁ ይችላልን?» እናንተም እግዚአብሔር እየረዳችሁ ክርክርን በሚያስወግድ መንገድ ለመመለስ ትሞክራላችሁ፤ ምናልባትም ደስ ብሏችሁ ይሳካላችኋል፤ አንዳንዶቹም እንደ ገና በትኩረት እያዳመጡ ሳሉ፥ አንዲት ሴት ከዚህ በፊት ስለ መለሳችሁት ስለ ዘመዶቻችሁ በጥያቄ ታቋርጣለች፤ እርሷ ግን ዘግይታ መጥታለችና ሁሉን እንደ ገና መስማት ትፈልጋለች። የቻላችሁትን ያህል ታረኳታላችሁ፤ ከዚያም ውድ ደቂቃዎቹ ምን ያህል በፍጥነት እያለፉ እንደ ሆኑ እየተሰማችሁ፥ እነርሱን ለመዋጀትና በዘላለማዊ ሥራ ለመሙላት፥ ኦ፥ እጅግ በትጋት ትሞክራላችሁ፤ ያን ጊዜ በድንገት ማኅበረሰቡ ሁሉ በታሚል እኅታችሁ ላይ ያተኩራል። እርሷ ማን ናት? ምን እንደሚከተለው አውቃችሁ ጥያቄውን ገና ከመጀመሪያው አልፋችሁት ነበር፤ እነርሱ ግን ጥቃቱን ያድሳሉ። «በትውልድ ክርስቲያን» ከሆነች፥ መርከስን ፈርተው ራቅ እያሉ ይጮኻሉ—«ዝቅተኛ ካስት፥ ዝቅተኛ ካስት!» ቃሉም በንቀት ከአፍ ወደ አፍ ይዛመታል። ተመላሽ ከሆነች ስለ ዘመዶቿ ይጠይቃሉ (ምናልባት ላለፉት አሥር ደቂቃዎች ስለ ካስቷ እርስ በርሳቸው ሲገምቱ ነበር)፤ ባትመልስላቸው አሳባቸውን ያለ ልክ ይለቁታል፤ ብትመልስ ደግሞ በቍጣ ይፈነዳሉ፥ «የገዛ እናትሽን ትተሻል! ካስትሽን አፍርሰሻል!» ለጆሮም በማይጣፍጡ ስሞች ይጠሯታል፤ ምናልባትም ሁሉም በአንድነት ተነሥተው ከእንዲህ ያለች አሳፋሪ ሰው ጋር ምንም ግንኙነት እንዳይኖራቸው እምቢ ይላሉ።
ወይም ምናልባት አንዳንዶቹን ማንበብ እንዲማሩ ለማግባባት እየሞከራችሁ ይሆናል፤ ብትሳካላችሁ እነርሱን የማስተማር ዕድል እጅግ እንደሚጨምር አውቃችሁ፤ እነርሱ ግን በዚያ መንደር ሴቶች ማንበብ ልማድ እንዳልሆነ ያረጋግጡላችኋል፤ ይህም በሚያሳዝን ሁኔታ እውነት ነው፤ ወይም ምናልባት ዳግመኛ ላታዩአቸው ለምትችሉት እንደምትነግሩ፥ ስለሚወዳቸው ፍቅር እየነገራችኋቸው ይሆናል፤ በንግግሩም መካከል አንድ ሕፃን ያለቅሳል፤ ትኩረቱም ሁሉ ወደ እርሱ ይሄዳል፤ ወይም አንዲት ሴት ወደ ቤት መግባት ትፈልጋለች፤ በብዙ መሰብሰብና ግርግርም መንገድ ሊከፈትላት ያስፈልጋል፤ ወይም አንድ ውሻ ድንጋይ ተረከዙን ተከትሎት፥ ከኋላውም የትንንሽ ወንዶች ልጆች መንጋ እያሳደደው እያላዘነ ከማዕዘኑ ዞሮ ይመጣል፤ ወይም ወንዶቹ የመሄጃ ጊዜ እንደ ደረሰ ይጮኻሉ፤ ወይም ሴቶቹ የምግብ ማብሰያ ጊዜ እንደ ደረሰ ይጠቁማሉ፤ ወይም አንድ ሰው የሚያናድድ ነገር ይናገራል ወይም ያደርጋል፤ ስብስቡም በቅጽበት ይበተናል፤ እያንዳንዱም ወደየራሱ ጕድጓድ ሄዶ በዚያ ቆሞ ወደ ውጭ ይመለከታል፤ እናንተም ወደ እነዚያ ትንንሽ ጨለማ በሮች ቀና ብላችሁ ትመለከታላችሁ፤ ወደ ውስጥ እንድትገቡ ቢፈቅዱላችሁ፥ ከእነዚያ ክፍሎች በአንዱ አጠገባቸው እንድትቀመጡና ያቋረጡትን ታሪክ መጨረሻ እንድትነግሯቸው ቢፈቅዱላችሁ የሚጠይቁትን ሁሉ ለመስጠት ፈቃደኞች እንደ ሆናችሁ ይሰማችኋል፤ እነርሱ ግን ይህን አያደርጉም። ኦ፥ ለአንድ ሰው እንዲህ ቅርብ ሆኖ ሳለ እንዲህ እጅግ መራቅ፥ አንዳንድ ጊዜ ከእነዚህ ሴቶች እንደሚራቅ፥ ሰውን ያሳዝናል። በደጃፋቸው ቆመው ሳሉ ትመለከቷቸዋላችሁ፤ በእጅ የሚደረሱ ናቸው፥ ነገር ግን የማይደረሱ ናቸው፤ በሺህ የሚቆጠሩ ማይሎች ርቀው እንዳሉ ያህል የማይደረሱ ናቸው። . . .
እነዚያን ቃላት ልክ እንደ ጻፍኩ አንዲት ብራህማን ሴት ወደ በሩ መጥታ ወደ ውስጥ ተመለከተች። ከዚያም ገብታ ተቀመጠች፤ ነገር ግን አልተናገረችም። እንደዚህ ባለ ትንሽ ነገር እንኳ ልብ እንዴት እንደሚዘል ልታስቡ ትችላላችሁን? ብራህማን ሴቶች በየቀኑ ሊጠይቁን አይመጡም። ከዘንባባ ቅጠል ቁራጮች የተሠራ መጽሐፍ አወጣች፤ እኛም አነበብነው። ሁሉም ደንቆሮና ዲዳ ሆነው ከተወለዱ የሰባት ቤተሰብ አንዷ እንደ ሆነች፤ ራሳቸውን በጋንጀስ ለመስጠም እጅ ለእጅ ተያይዘው ወደ ቤናሬስ በእግር ለመሄድ እንዴት እንደ ተነሡ፤ አንድ ሴፖይ (ሕንዳዊ ወታደር) እንዴት እንዳስቆማቸውና ወደ አንድ እንግሊዛዊ ኮሌክተር (የአውራጃ አስተዳዳሪ) እንደ ወሰዳቸው፤ እርሱም ሰባቱን ለአንድ ዓመት እንዴት እንደ ረዳቸውና ከዚያም እንደ ለቀቃቸው፤ እንዴት እንደ ተበተኑና ልዩ ልዩ ቅዱሳት ስፍራዎችን እየጎበኙ በሄዱበት ሁሉ በደጋግ ሰዎች እየተረዱ እንደ ተንከራተቱ፤ ይህን የያዘችውም የምንሰጣትን ሁሉ በደስታ እንደምትቀበል ይናገር ነበር። . . . ሄዳለች፤ ምስኪን ደንቆሮና ዲዳ፥ ፈጽሞም አረማዊት የሆነች ሴት፤ ቆይታ እንድታርፍ ልናግባባት አልቻልንም። ባለ ትዳር እንደ ሆነች በምልክት ነገረችን፤ ባሏ ደንቆሮና ዲዳ ነው፤ አንድ ዕውር ልጅም አላት። ለጥቂት ደቂቃዎች ከአጠገባችን መሬት ላይ ተቀምጣ ጥያቄዎችን ጠየቀች—የተለመዱትን፥ ስለ እኔ፥ ሁሉንም በምልክት፤ ነገር ግን በምልክት ልናሳያት የቻልነው አንዳች ነገር ስለ አምላካችን ምንም ነገር በምንም መንገድ ሊያስረዳት አልቻለም። ቢሆንም ስለ ራሷ አምላክ ቢያንስ አንድ ነገር የምታውቅ ትመስላለች። ወደ አፏ አመለከተች፥ ከዚያም ወደ ላይ፥ ከዚያም የወንዝን መጠምዘዝ ለማሳየት ወደ ታችና ዙሪያውን፤ ከቅዱስ ወንዝ ወደ ቅዱስ ወንዝ እንዴት እንደ ሄደችና በእያንዳንዱ አጠገብ እንዴት እንደ ሰገደች በግልጽ በምልክት አሳየች፤ ወደ ላይም አመልክታ እጆቿን አጣመረች። እዚያ ነበርን፥ ልክ ስጽፍ እንደ ነበረው፥ ለእርሷ እንዲህ ቅርብ፥ ነገር ግን ከእርሷ እንዲህ ሩቅ።
ነገር ግን ወደ ሴቶቹ ለመድረስ ከሁሉ የሚበልጠው ችግር ሊደረስባቸው ምንም ፍላጎት የሌላቸው መሆኑ ነው። አንዳንድ ጊዜ፥ ልጅቱ መጥታ መስማት እንደ ፈለገችበት እንደዚያ ከሰዓት በኋላ፥ ፍላጎት ያላትን አንዲት እናገኛለን፤ አብዛኞቹ ግን ምንም ፍላጎት የላቸውም፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ሴት ጋር እንዲማሩ ከሚፈቀድላቸው ይበልጥ ከተራመዱ ከተሞችና መንደሮች በቀር፥ ይበልጥ ለመስማት እንዲፈልጉ የሚያደርጋቸውን ያህል ለመስማት ዕድል እምብዛም አያገኙም።
ከዚያም ጉዳዩን እጥፍ አስቸጋሪ ለማድረግ ያህል (ይህም ሕግ የየትኛውም ካስት ብትሆን በሴት ሁሉ ላይ ይሠራል)፥ እርሷ በሕግ ዓይን የባሏ ንብረት ናት፤ ክርስቲያን ሰው የሂንዱ ሚስቱን ከእርሱ ጋር እንድትኖር በሕግ ሊያስገድዳት ባይችልም፥ ሂንዱ ባል ግን ክርስቲያን ሚስቱን ከእርሱ ጋር እንድትኖር ሊያስገድዳት ይችላል፤ ስለዚህ ማንኛዪቱም ያገባች ሴት ክርስቲያን ለመሆን በሕግ ፈጽሞ ነጻ አይደለችም፤ ባሏ መልሶ ቢጠይቃት ልትጠበቅ አትችልምና፤ ማንኛዪቱም እንግሊዛዊት ሴት ልታስበው እንኳ ወደማትችለው ሕይወት አሳልፋ መሰጠት ይኖርባታል። ክርስቲያን ነኝ ልትል ትችላለች፤ እርሱ የምትለውን ከምንም አይቆጥረውም። እንዲህ በግድ ተመልሳ የምትወሰደውን ሴት እግዚአብሔር ይርዳት!
ነገር ግን ከዚህ እጅግ ዓመፀኛ ሕግ ኃይል የሚበልጥ ኃይል ጣልቃ እንደሚገባ አምነን፥ እንዲህ ያለች ሚስት ብትመጣ ማንኛውንም ቅጣት ደፍረን እንቀበላታለን። ብቻ፥ በሕንዳዊት ሴትና በነጻ ክርስቲያን ሕይወት መካከል ያሉትን ችግሮችና እንቅፋቶች ስንመለከት፥ ከችግሮች ሁሉ የመጨረሻውንና ከሁሉ ይበልጥ ለመረዳት የሚያስቸግረውን ይህን ችግር ዓይንን ጨፍኖ ማለፍ ከንቱ ነው፤ «ወደ ሕንድ የገባና በእስራት የሚያስፈጽም የእንግሊዝ ሕግ»፥ ጊዜው ያለፈበት የእንግሊዝ ሕግ!
በታሚል ሚስዮናችን ውስጥ ብራህማን ሴት ተመላሾች የሉንም። በትራቫንኮር ስለ ጥቂቶች እንሰማለን፤ ብራህማኖች በብዛት በሚገኙበትና ብዙም በማይገለሉበት በሰሜን ስለ ሌሎች እናውቃለን፤ ነገር ግን በዚህ አውራጃ ሁሉ ውስጥ እውነተኛ የሆነች አንዲት ብራህማን ተመላሽ ሴት ወይም ልጅ እንኳ የለችም። አንዲት እጅግ ያረጀች ሴት ነበረች፤ እርሷ ግን ከሁለት ዓመት በፊት ሞተች። ከሰሙት አንዳንዶቹ በእርግጥ በስውር የሚያምኑ ሆነዋል በሚለው አሳብ ራሳችንን ልናጽናና እንችላለን። ነገር ግን እውነተኛ አማኝ ሁልጊዜ በስውር ይኖራልን? ብዙ ውድ ትንሽ ልጅ ኢየሱስን እየወደደ በልጅነቱ ሞቶ ወደ እርሱ እንደ ሄደ ልንታመን እንችላለን። ነገር ግን በልጅነታቸው ያልሞቱትስ? የበለጠ ብሩህ አመለካከት ሊወሰድ እንደሚችል አውቃለሁ፤ በእነዚህ ደብዳቤዎች የሚያሳዝነው ጎን ጎልቶ ከተገለጸ፥ ይህ የሆነው ስለ እርሱ ያላችሁ እውቀት ያነሰ እንደ ሆነ ስለ ተሰማን ብቻ ነው።
ከውድቀቶቹ ይልቅ ስለ ስኬቶቹ ብዙ ተጽፏልና፤ ለእኛም ስለ ጦርነቱ ድሎች ከምታውቁ ይልቅ ስለ ሽንፈቶቹ ማወቃችሁ ይበልጥ አስፈላጊ መስሎ ይታየናል። ድሎቹን ለማክበር ዘላለም ሁሉ ይኖረናል፤ እነርሱን ለማሸነፍ ግን ከፀሐይ መጥለቅ በፊት ያሉት ጥቂት ሰዓታት ብቻ አሉን። እንደሚገባን እያሸነፍናቸው አይደለም፤ ምክንያቱም የሽንፈቶቹ እውነታ እጅግ በጥቂቱ ብቻ ይታወቃልና፤ የሚያስፈልጉት ተጨማሪ ኃይሎችም ሁኔታው በሚገባ ቢታወቅ ኖሮ እንደሚመጡት እየመጡ አይደሉም። የወንዶችና የሴቶች ተጨማሪ ኃይል ያስፈልጋል፤ ከሁሉ በላይ ግን የጸሎት ተጨማሪ ኃይል። ስለዚህ እውነቱን—የማይስበውንና ልብ ወለድነት የሌለውን እውነት—ስለ አሕዛብ እንደምናገኛቸው፥ ስለ ሥራውም እንዳለ ልንነግራችሁ ሞክረናል። ተጨማሪ ሠራተኞች ያስፈልጋሉ። ምን ያህል እንደሚያስፈልጉ፥ እዚህ ምን ያህል እንደሚፈለጉ ምንም ቃል ሊገልጽ አይችልም። ነገር ግን እውነታዎቹ ጥቁርና ነጭ ሆነው ሳሉ፥ በቀለማት ያሸበረቁ ሥዕሎችን በመሳል ማንንም ሰው ስለ መምጣት እንዲያስብ ለማማለል ፈጽሞ አንሞክርም። ጥቁርና ነጭ እንደ ቀለማት ፈጽሞ ባይስብስ? ስለዚህ ግድ የለንም፤ ሥራችን እውነቱን መናገር ነው። ሥራው የሚታይና የሚደነቅ ያማረ ነገር አይደለም። ውጊያ ነው። የጦር ሜዳዎችም ውብ አይደሉም።
ነገር ግን አንድ ሰው በእውነት በእግዚአብሔር ከተጠራ፥ ችግሮቹና ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ሁሉ ጥሪውን ይበልጥ ያጠነክሩታል እንጂ ሌላ አያደርጉም። ነገሮች ቀላል ቢሆኑ ኖሮ የሚያስፈልገው ያነሰ በሆነ ነበር። የሚያስፈልገው በበዛ ቍጥር ጥሪው በውስጥ ይበልጥ በግልጽ ይደውላል፤ እርግጠኝነቱም ይበልጥ ይጠልቃል፦ የእግዚአብሔር ጥሪ ነበር። ሰውም ሲታዘዘው፥ ከስኬት ደስታ ፍጹም ለየት ያለ የመታዘዝ ደስታ አለ። ወዳጆቹ ጥቂቶች በሆኑበት ስፍራ ከኢየሱስ ጋር በመሆን ደስታ አለ፤ አንዳንድ ጊዜም፥ ፈጽሞ ባልተጠበቀ ጊዜ፥ በሚቃወም ወይም ግድ በሌለው ከተማ ቀኑን ካሳለፋችሁ በኋላ ደክማችሁና ተስፋ ቆርጣችሁ ወደ ቤት ስትመለሱ፥ በድንገት—እንዴት እንደ ሆነ ልትናገሩ እንኳ አትችሉም—የኢየሱስ ደስታ ማዕበል በላያችሁና በውስጣችሁ ይፈስሳል፤ በፍጹም ደስታ ስሜትም ጸጥ ትላላችሁ። ከዚያም ነፍሳትን ሲያድን ስታዩት፥ ወይም የጓደኞቻችሁን ድሎች ስትሰሙ፥ ኦ! በውስጣችሁ ያለው ሁሉ፥ «ከሚገባኝ በላይ የተትረፈረፈ ደስታ አለኝ!» ብሎ ይዘምራል።