ምዕራፍ 18 · 8 ደቂቃ ንባብ · 10 ደቂቃ ማዳመጥ
በፈቃዳቸው የሚሰለፉ ይፈለጋሉ
«ታላቅና ግርማ ያለው የጦር ሚኒስቴር አለን፤ ሠራዊቱ ግን እጅግ ትንሽ ነው። . . . ሰፋፊ አህጉራት ፍጹም በሚባል ጨለማ ተሸፍነው ሳሉ፥ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩም የአሕዛብነትን ወይም የእስልምናን ሰቆቃ እየተቀበሉ ሳሉ፥ እግዚአብሔር ያስቀመጠህ ሁኔታ ከውጭ አገር የሚስዮን ሥራ መስክ እንድትርቅ በእርሱ የታሰበ መሆኑን የማስረዳት ሸክም በአንተ ላይ ነው።»
ኢየን ኪት ፋልኮነር፥ ዓረቢያ።
በጥር 1900 በለንደን በተደረገው ዓለም አቀፍ የተማሪዎች የሚስዮን ጉባኤ ከቀረቡት ንግግሮች በአንዱ፥ አንድ የደቡብ ሕንድ ሚስዮናዊ ስለ ብራህማን ዘር «የሕንድ አንጎል» ብሎ ተናገረ። «ቍጥራቸው በአንጻሩ ትንሽ ነው—ከአሥር እስከ አሥራ አምስት ሚሊዮን—ነገር ግን በቍጥር ጥቂቶች ቢሆኑም—ከሂንዱ ሕዝብ አምስት በመቶ ብቻ—ያንን ሕዝብ ሁሉ በእጃቸው መዳፍ ይዘውታል። በአገሪቱ ያለውን የተሰሚነት ቦታ ሁሉ ይዘዋል። የአገር መሪዎችና ፖለቲከኞች፥ ዳኞች፥ መሳፍንት፥ የመንግሥት ባለ ሥልጣናትና የየደረጃው ጸሐፊዎች እነርሱ ናቸው። በሰዎች ላይ ተሰሚነትን የሚያስገኝ ቦታ ካለ፥ የሚይዘው ብራህማን ነው። ከዚህም በላይ ቅዱስ ካስት ናቸው፤ ሕዝቡም በምድር ላይ ያሉ አማልክት እንደ ሆኑ ይቀበላቸዋል—ይህም ማዕረግ በብዙ የነፍስ ሽግግሮች በተጠበቀ ብቃት የተገኘ ነው ተብሎ ይታመናል።»
በዚህ አውራጃ ፔትራዎች መካከል ብራህማኖች አጽንተው የያዙአት የጥንት ልማድ ያላት ትንሽ የገጠር ከተማ አለች። ከዚያች ከተማ አንድም ተመላሽ ወጥቶ አያውቅም፤ ከተማይቱም ከቶ አይወጣም ብላ ትመካለች። ከቤቶቹ አንዱም ለትምህርት፥ ለጉብኝት እንኳ ገና አልተከፈተም፤ እኛ ግን ወዳጆችን እያፈራን ነው፤ በቅርቡም መግቢያ እንደምናገኝ ተስፋ እናደርጋለን። አንድ ጥዋት በመንገድ ላይ አሳለፍን፤ ይህን አልተቃወሙም፤ ነጻዎቹ ወጣት ብራህማኖች በዙሪያችን ሲሰበሰቡ፥ ወይም ፎቶ «እንዲነሡ» ለአፍታ ከግድግዳ ጋር ሲቆሙ፥ ይህን ለምናውቀው ለእኛ እንኳ ምን ያህል የታሰሩ እንደ ሆኑ መገንዘብ አስቸጋሪ ነበር። «ሊያሸንፉ ሲገባቸው የታሰሩ፤ ነገሥታት ሊሆኑ ሲገባቸው ባሮች።» በሥጋም በነፍስም፥ የእንግሊዝ አእምሮ ፈጽሞ ሊረዳው በማይችል ባርነት የታሰሩ።
ከዚያም በኋላ ፎቶግራፎቹን ስናይ፥ እንደ እነዚህ ወጣት ተማሪዎች በነበሩበት ጊዜ ከባርነታቸው ሊያመልጡ የደፈሩትን አንዱንና ሌላውን አሰብን፤ ነገር ግን ተጎትተው ተመለሱ፤ ሰንሰለቶቹም ከቀድሞው ይልቅ አጥብቀው ተቸነከሩ፤ እያንዳንዱም ቀለበት እንደ ገና ተፈትኖ በብርቱ ተመታ።
ነገሮች እንደምናስበው አይደሉም ብሎ የሚያረጋግጥልንን ያንን ፈገግታ እነዚህ እውነታዎች የበለጠ እንዲመልሱት፥ ስለ እያንዳንዳቸው እውነታውን በእርግጥ ለማወቅ ፈለግን፤ ስለዚህ አይየር እነዚህን ልጆች በደንብ ያውቃቸው ለነበረ ለአንድ ወንድም ሚስዮናዊ ጽፎ በእያንዳንዳቸው ላይ የደረሰውን እንዲነግረው ጠየቀው። ዛሬ ጥዋት ለዚያ ደብዳቤ መልሱ መጣ፤ «ልሰጥሽ አልወድም ነበር፤ ነገር ግን የሚሆነውን እውነት ይናገራል» ተብሎ ተሰጠኝ። እነዚህ ልጆች በሲ.ኤም.ኤስ. ኮሌጃችን ተማሪዎች ነበሩ።
በደብዳቤው መጀመሪያ የተጠቀሰው ክርስቶስን በጥምቀት የመሰከረ ወጣት ብራህማን ነው፤ ለብዙ ሳምንታት በሕዝብ እየመጡ ወደ ሂንዱነት እንዲመለስ በማናቸውም ክርክር ሊያግባቡት የሞከሩት ወዳጆቹ ያስነሡበትን ታላቅ ተቃውሞ በጀግንነት ተቋቋመ፤ እርሱ ግን ክርስቶስን ሰበከላቸው። ወጣት ሚስቱን አመጡ፤ እርስዋም ጠጕርዋን ነጨች፥ ዋይ ዋይም አለች፤ የመበለትን ኑሮ ውርደት እንዳይፈርድባትም ለመነችው። ከሁሉ ይልቅ ይህን መቋቋም ከባድ ነበር፤ ወደ ሚስዮናዊውም ዘወር ብሎ፥ «አባቴ ሆይ፥ ውሰዳት! ልቤን እየነቀለች ነው!» አለ።
ቀጥሎም የሌላው ብራህማን ተማሪ፥ የወዳጁ፥ የጥምቀት ቀን መጣ፤ እርሱም ከዚህ በፊት በዘመዶቹ ተይዞ ተዘግቶበትና ተርቦ፥ ከዚያም የተመረዘ ምግብ ተሰጥቶት ነበር፤ ነገር ግን መርዙ ለመግደል በቂ አልነበረም፤ እርሱም አምልጦ አሁን በሰላም ለጥምቀት ተዘጋጅቶ ነበር።
የአዲሱ ተጠማቂ ወዳጅ እንዴት ቆሞ ደስ እንዳለውና እግዚአብሔርን እንዳመሰገነ በኋላ ታወሰ። ከዚያም ጥምቀቱ ካለቀ በኋላ፥ በቀን ብርሃን አደጋ ይደርሳል ብሎ ሳይፈራ፥ ሊታጠብ ወደ ኩሬው ሄደ። ከዚያ በኋላ ከቶ አልታየም።
በትክክል ምን እንደ ሆነ ማንም አያውቅም። እርሱን እንዲጠብቁ የተቀጠሩ ሰዎች አጋጣሚውን ተጠቅመው ይዘው ወሰዱት ተብሎ ይታሰባል። ከዚያም ምን እንዳደረጉ ፈጽሞ አልተነገረም። ስለ ልጁ እርስ በርሱ የሚጋጭ ወሬ ለሚስዮናውያኑ ደርሷል። አንዱ፥ አሁንም ጸንቶ እንዳለ፤ ሌላው፥ አሁን በደቡብ ሕንድ ካሉት ታላላቅ የሳይቫይት ቤተ መቅደሶች በአንዱ ካህን እንደ ሆነ። የትኛው እውነት እንደ ሆነ እግዚአብሔር ያውቃል።
እኛ ግን በእንግሊዝ መንግሥት ሥር ነን። አንዳች ሊደረግ አይቻልም ነበርን? ከቅርብ ዘመዶቹ አንዱ በአሁኑ ጊዜ ከሕንድ ከተሞቻችን በአንዲቱ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ ነው። በእነዚያም ሳምንታት ከመጡት ብራህማኖች ብዛት መካከል ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች፥ የኮሌጅ ምሩቃን፥ የሕግ ሙያ አባላት ነበሩ—ሕግ በሕንድ የተወደደ ሙያ ነው። ይህም ሆኖ ይህ ነገር ተደረገ።
ሌላም ነበረ፤ እርሱን ለመያዝ የተጠቀሙበት ዘዴ እዚህ ሊጻፍ አይችልም። እውነትን በእርግጥ እንዳለ ለመናገር ስንሞክር የሚገጥመን ችግር ይህ ነው። በፍጹም ሊነገር አይችልም። ትቢያው ሊታይ ይችላል—ወይም ከእርሱ ጥቂቱ፤ እውነተኛው ነገር ሁሉ ግን ከቶ አይታይም።
ለመንግሥቱ የቀረቡ ሌሎችም ነበሩ፤ ታሪኩ ግን ያው እንደ ገና ነው። ሁሉም ከኮሌጁ በስውር ተወሰዱ፤ ሚስዮናዊውም «እነርሱን፥ ከክርስቶስም ሊመልሷቸው የተፈጠሩትን የገሃነም ዘዴዎች ማሰብ ልብን ያሳምማል» ብሎ ይጽፋል። እነዚህ የስሜታዊ ምናብ ቃላት አይደሉም። እንደ ምስክር የሚመሰክር ሰው ቃላት ናቸው። ምስክርም ቢሆን ግን ሊሰማው ይችላል።
ስለ አንዱ ይነግረናል፤ ብሩህና ደስተኛ ልጅ ነበረ ይላል፤ ወዳጆቹ ከጥምቀቱ በኋላ ወደ ቤቱ መመለሱን አልተቃወሙም፤ እርሱም ከሚስቱ ጋር እንደ ክርስቲያን መኖር የሚችል መስሎት ተመለሰ። ምግቡን በዕፅ አደነዘዙት፤ ከዚያ ያደረጉት ግን እንደ ገና በዝምታ መሸፈን አለበት. . . . የከፋውን ሁሉ አደረጉ. . . . ከዚያ የኃጢአት ቅዠት በነቃ ጊዜ፥ ሚስዮናዊ ወዳጁን ፈልጎ አገኘው። ከሂንዱዎችም እንኳ አንዳንዶቹ እርሱን ለማሳሳትና ለማጥፋት «በተደረገው ርኩስ ዘዴ አፍረው» እንደ ገና እንደ ክርስቲያን እንዲቀበል በወደዱ ነበር፤ መንፈሱ ግን ተሰብሮ ነበር። ተመልሶ በመምጣት የክርስቶስን ዓላማ ሊያዋርድ እንደማይችል ተናገረ፤ ወደማይታወቅበት ስፍራ ይሄዳል። ሚስቱን ትቶ ሄደ። ከዚያ ወዲህ ስለ እርሱ ምንም አልተሰማም።
የሥራ ጓደኛችን ስለ ሌላው ይነግራል፤ እንደ ገናም ስንናገረው ግማሹን ሳንናገር መተው አለብን። ይህኛው ክርስቶስን በጥምቀት ለመመስከር ይጓጓ ነበር፤ በዚያን ጊዜ የኮሌጅ ተማሪ ነበረ፤ እጅግም ቀናተኛ ነበረ። አባቱ የልጁን ፍላጎት ያውቅ ነበር፤ ጥቂት የሂንዱ አባቶች የሚያደርጉትንም አደረገ፤ ልጁን ለማጥፋት ቤቱን ገሃነም አደረገው። የሲኦሉ ሤራ ተሳካ። አእምሮ በእነዚያ አስፈሪ ዕፆች ሲደነዝዝና ከዚያም ሲቀጣጠል ነፍስ እስከ ምን ድረስ ተጠያቂ እንደ ሆነች እግዚአብሔር ብቻ ያውቃል። ነገር ግን እርሱ እንድትነሣና እንድታበራ ያሰባት ነፍስ፥ በጨለመ አስከፊ ትዝታ በማይነገር ውርደት ተጭና፥ ውስጥ ለውስጥ እንደሚበክል ጥቁር ቀለም ተበክላ እንደምትሰጥም እናውቃለን።
ስጽፍ ሌሎችን አስባለሁ፤ አንዱ በደንብ የምናውቀው ልጅ ነበረ፤ ለክርስቶስ ለመመስከር የሚጓጓ ድንቅና ትጉ ወጣት። እርሱን ለማጥፋት ከሚያሤሩት እንዴት እንደ ዳነ አንድ ምሽት ነገረን። ክርስቲያን ለመሆን ከወሰነ በኋላ ለብዙ ወራት በቤቱ ኖረ፤ ወገኖቹንም ሊማርክ ሞከረ፤ እነርሱ ግን ካስትን ለመስበር እንኳ በማሰቡ በእርሱ ላይ ተቈጥተው ነበርና አልሰሙትም። እርሱ ግን ምንም ሳይፈራ እየጠበቀ መሰከረላቸው። ከዚያም አንድ ቀን ድንገት ጥቂት ሰዎች ተቀምጦ ወደ ነበረበት ክፍል ሮጠው ገቡ፤ ያዙት፥ አሰሩት፥ አፉንም ለጐሙት። በእጃቸው ውስጥ ሆኖ መሬት ላይ ተጋድሞ ሳለ አንድ ነገር በግድ ወደ አፉ አስገቡ፤ ዕፅ መስሎት ፈራ፤ ነገር ግን ለሂንዱ የማይነገር ርኵሰት የሆነ የሚያስጸይፍ ነገር ብቻ ነበረ። ከዚያም ታስሮ ብቻውን ተዉት፤ በሌሊትም ማምለጥ ቻለ። ይህን ከነገረን ከጥቂት ወራት በኋላ እንደ ገና እንደ ተያዘ፥ በዚህ ጊዜም «በዕፅ ደንዝዞ እንደ ጠፋ» ሰማን።
በደቡብ ሕንድ ጥምቀት ካስቱ ተመላሹን ለመመለስ የሚቻለውን ዘዴ ሁሉ ከመጠቀም አይከለክለውም፤ ከተመለሰ በኋላ አንዳንድ ሥርዓቶች ይፈጸማሉ፤ ከዚያም እንደ ጸዳ ይቆጠራል፥ ወደ ካስቱም ይመለሳል። የመላው የካስት ኅብረት መመሪያ ይህ ነው፤ ከቻልክ ሳይጠመቅ መልሰው፤ ያም ሆነ ይህ ግን መልሰው። ከዚህ አውራጃ ከተለያዩ ክፍሎች የሆኑ ሁለት የብራህማን ልጆች ክርስቶስን መረጡ፤ በግልጽ መመስከር የሚያስከትለውን ሁሉ አልፈው ተጠመቁ። ከሁለቱ አንዱ ለደኅንነቱ ወደ ሰሜን ተላከ፤ ወገኖቹ ዱካውን ተከትለው ፈለጉት፤ በማዕከላዊ ሕንድ በአንድ የመንገድ ዳር ጣቢያ ሳይታሰብ ደረሱ፤ በደቡብ ወዳለው ቤቱም በግድ መለሱት። እዚያ ከደረሰ በኋላ ሊያቆዩት የራሳቸውን እርምጃ ወሰዱ። ሌላው ልጅ ወደ ማድራስ ተላከ። ብራህማኖች ያለበትን አግኝተው በሌሊት ቤቱን ሰብረው ገቡ፤ የልጁን ጠባቂዎች አሸንፈው ወሰዱት። እነርሱም በዚያ መልካም የመሰላቸውን አደረጉ፤ እነርሱም ተሳካላቸው። ከውጭ ማንም ጣልቃ ሊገባ አልቻለም። ካስቱ የራሱን ጉዳይ ይጠብቃል።
«ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ!» ብሎ ገና ሂንዱ የሆነ አንዱ ጻፈ፤ «በዙሪያችን በተሣለ አስማታዊ ክብ ውስጥ ያለን ያህል፥ ሰይጣንም በትሩን ይዞ ከውጭ ቆሞ በፍርሃት እንደሚያቆየን ያህል በአደጋ ውስጥ እንዳለን የምታውቀን ሆይ፥ የሰይጣንን አስማት ስበር፥ አንተንም እናገለግል ዘንድ ነጻ አውጣን!»
ይህ ሁሉ ከተፈጸመበት ስፍራ ርቀው ላሉት ቀላል ንባብ ሊሆን ይችላል። ርቀት እጅግ ግልጽ የሆነውን መስመር የማለስለስ ጠባይ አለው፤ ለመጻፍ ግን ቀላል አይደለም፤ ወደ እኛ እጅግ ይቀርባልና። ታዲያ ለምን ይጻፋል? የምንጽፈው የበለጠ ሊታወቅ የሚገባው ስለ መሰለን ነው፤ ይኸውም አምላካችንን የሚያውቁና እርሱን የመያዝን ምሥጢር የሚያውቁ ወንዶችና ሴቶች እርሱን እንዲይዙ፥ ካስቶችንም ለክርስቶስ ለመማረክ አጥብቀው እንዲይዙ ነው።
በእርግጥ የአንድ ሥራ ክብደት ራሱ፥ ወታደር «የጨለመ ተስፋ» ብሎ የሚጠራው መሆኑ ራሱ፥ ቀለል ካለ ነገር ከሚቀርበው ከማንኛውም ይልቅ የበረታ ጥሪና የበረታ ጥያቄ ነው። ወታደር ተስፋው «የጨለመ» ስለ ሆነ እጁን አይሰጥም። እጅግ አስጊ ቢሆንም እንኳ ተስፋ ነው። ለእርሱ በፈቃዱ ይሰለፋል፤ ቢያሸንፍም ባያሸንፍም ይዋጋል።
በዚህ ሥራ «የጨለመ» ተብሎ እንዲጠራ የሚያደርገው ነገር አለ። ለዘመናት ይህ ዘር ከተፈጥሮ ሕጎች አንዱን በዕውር ጽናት ሲጥስ ኖሯል፤ ውጤቱም የተወሰነ የሞራል ጥንካሬ፥ ጽናትና «ብርታት» ጕድለት ነው። ለዚህ ማንም ግለ ሰብ ተጠያቂ አይደለም፤ የጭካኔ ፍርድም ፈጽሞ ቦታ የለውም፤ ነገር ግን እውነታው እንዲህ መሆኑ ይቀራል፤ ከብራህማኖችና ከሌሎች በርካታ የሕንድ የላይኛ ካስቶች ጋር ሲሠራም ከግምት ውስጥ መግባት አለበት። ከዚህ የድካም ገጽታ ጎን ለጎን፥ የሚቃረን በሚመስል መንገድ፥ የካስት መንፈስ በመባል የሚታወቅ ያ እልኸኛ የብርታት ገጽታ አለ። ይህ መንፈስ ተመላሽ ሲመጣ ምን እንደሚሆን ባሳየኋችሁ ሁሉ ይታያል። የሚሊዮን የካስት ወንዶችና ሴቶች ሚሊዮን ፈቃዶች ሁሉ ተጨምቀው አንድ ብቸኛ ፈቃድ የሆኑ ያህል ነው፤ በአገር ቤት ከሚታወቅ ከማንኛውም ነገር ጋር የማይነጻጸር የፈቃድ ፍሬ ነገር ክምችት ነው።
ይህን ፊት ተመልከቱ—በፎቶ የተነሣ እውነታ ነው። ለመጽናት የሚያበረታውን ለመድፈርም የሚያነሣሣውን ያንን «አንዳች ነገር» አለመኖሩን አያሳያችሁምን? ከዚያም ይህን ስሙ፦—አንድ ክርስቲያን ሰው ሞቶ ተጋድሟል። ወደ መቃብር ስፍራው የሚወስደው መንገድ በዚህ አውራጃ ዋና ከተማ በብራህማኖች መንገድ በኩል ያልፋል፤ ሌላ መንገድ የለም። የብራህማኖች መንገድ የሕዝብ መተላለፊያ ነው፤ ለመተላለፊያ ሊዘጋ አይችልም፤ ብራህማኖች ግን ያ የሞተ ሰው በዚያ እንዲያልፍ ፈጽሞ እምቢ አሉ። ኤጲስ ቆጶሱ ተከራከረ። አይሆንም፤ ክርስቲያን ነበረ፤ በዚህ አያልፍም። ጊዜው እያለፈ ነው። በሐሩር አገሮች የሞተ ቶሎ መቀበር አለበት። ኤጲስ ቆጶሱ ለኮሌክተሩ (በዚህ የመንግሥት ተወካይ) አቤት አለ። ኮሌክተሩ ትእዛዝ ሰጠ። ብራህማኖች ለመታዘዝ እምቢ አሉ። የወታደሮች ጓድ እንዲወጣ አዘዘ። ብራህማኖች በጣራዎች ላይ ተሰብስበው ወታደሮቹን በድንጋይ ወገሩ። እንዲተኩሱ ትእዛዝ ተሰጠ። ከዚያ በኋላ፥ ከዚያ በፊት ግን አይደለም፥ ክርስቲያኖች ሙታናቸውን ማውጣት ቻሉ፤ በኋላም ብራህማኖች የራሳቸውን አወጡ። ይህ የሆነው ከጥቂት ዓመታት በፊት ነው፤ ከዚያ ወዲህም በዚያች ከተማ በውጭ ሲታይ ዘመኑ ተለውጧል። ነገር ግን ይህ የሚያሳየው መንፈስ እስከ ዛሬ ድረስ ይዞታውን አልለቀቀም፤ ትንንሽ ነገሮች ታላላቆችን እንደሚያሳዩ፥ ይህ የመንገድ ላይ ትዕይንትም ካስቶችን ለክርስቶስ የመማረክን ችግር የሚያጠነክረውን ያንን «አንዳች ነገር» መኖሩን ያሳያል። እያንዳንዱ ክፍል በራሱ ደካማ ነው፤ በኅብረት ግን ብርቱ ነው።
እንድናደርግ የታዘዝነውን ለማድረግ የምናደርገውን ሙከራ «የጨለመ ተስፋ» ብለን ጠራነው። ቃሉ የተሳሳተ ስያሜ ነው፤ አለቃችን መሪያችን ሲሆን አንድም ተስፋ ከቶ «የጨለመ» አይደለም! መሪያችን ግን ሰዎችን ይጠራል፤ እግዚአብሔርን ለመርዳት፥ በኃያላን ላይ እግዚአብሔርን ለመርዳት በመጡበት ቀን በሜዳው ከፍታዎች ላይ ነፍሳቸውን እስከ ሞት አሳልፈው እንደ ሰጡ እንደ ጥንቶቹ ጀግኖች ያሉ ሰዎችን። ለአደጋ የተሰጠ ሕይወት ሊጠፋ ይችላል።
አለቃችን ክርስቶስ በፈቃዳቸው የሚሰለፉትን ይጠራል፤ ውሉም ይህ ነው፦ «ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያድናታል።» ለኮሌጅ ልጆቹ የሚኖር የአስተማሪ ሕይወት «የጠፋ» ሊመስል ይችላል፤ በረጅሙ ሞቃት ቀናት ሰዓት በሰዓት በቤት ውስጥ በጸጥታ በሚደረግ ውይይት የሚያሳልፍ የተማሪ ሕይወት «የጠፋ» ሊመስል ይችላል። ይሁን፤ ይህን ማለት ሊሆን ይችላልና። ነገር ግን ስለ ስሙ የጠፋው ሕይወት፥ እርሱ እንደ ገና ይገኛል።