ምዕራፍ 9 · 14 ደቂቃ ንባብ · 18 ደቂቃ ማዳመጥ
ወደ ኋላ ማፈግፈግ
«ክዳታቸውን እፈውሳለሁ፥ በፈቃዴም እወድዳቸዋለሁ፤ ቍጣዬ ተመልሶአልና።»—ሆሴዕ 14:4።
ወደ ኋላ ያፈገፈጉ ሰዎች ሁለት ዓይነት ናቸው። አንዳንዶቹ ከቶ አልተለወጡም፤ የክርስቲያን ማኅበር አባል የመሆንን ሥርዓት ብቻ ፈጽመው ያፈገፈጉ ነን ይላሉ፤ ነገር ግን አባባሉን ከፈቀዳችሁልኝ ከቶ «ወደ ፊት ተራምደው» አያውቁም። ስለ ማፈግፈግ ይናገሩ ይሆናል፤ ነገር ግን በእውነት ዳግመኛ ተወልደው አያውቁም። እነዚህ በእውነት ካፈገፈጉት ሰዎች — ከማይጠፋ ዘር ተወልደው ነገር ግን ፈቀቅ ካሉት — በተለየ መንገድ ሊያዙ ይገባቸዋል። እነዚህን የኋለኞቹን የቀደመውን ፍቅራቸውን ትተው በሄዱበት በዚያው መንገድ መልሰን ልናመጣቸው እንፈልጋለን።
መዝሙር 85:5ን ግለጥ። በዚያ እንዲህ ታነባለህ፦ «ለዘላለም ትቈጣናለህን? ቍጣህንስ ለትውልድ ሁሉ ታስረዝማለህን? ሕዝብህ በአንተ ደስ ይለው ዘንድ ተመልሰህ ሕያው አታደርገንምን? አቤቱ፥ ምሕረትህን አሳየን፥ ማዳንህንም ስጠን።» አሁንም ደግሞ ተመልከት፦ «አምላክ እግዚአብሔር የሚናገረውን እሰማለሁ፤ ለሕዝቡና ለቅዱሳኑ ሰላምን ይናገራልና፤ ነገር ግን ዳግመኛ ወደ ስንፍና አይመለሱ» (ቍጥር 8)።
ወደ ኋላ ያፈገፈጉ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ቃል ጋር እንደ መገናኘት የሚጠቅማቸው ምንም ነገር የለም፤ ለእነርሱም ብሉይ ኪዳን እንደ አዲስ ኪዳን በእርዳታ የተሞላ ነው። የኤርምያስ መጽሐፍ ለተቅበዘበዙ ሰዎች ድንቅ የሆኑ ክፍሎች አሉት። ልናደርገው የምንፈልገው ያፈገፈጉ ሰዎች አምላክ እግዚአብሔር የሚናገረውን እንዲሰሙ ማድረግ ነው።
ኤርምያስ 6:10ን ለጥቂት ጊዜ ተመልከት። «ይሰሙ ዘንድ ለማን እናገራለሁ? ለማንስ አስጠነቅቃለሁ? እነሆ፥ ጆሮአቸው ያልተገረዘ ነው፥ ሊያደምጡም አይችሉም፤ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቃል ለእነርሱ መሰደቢያ ሆኖአል፤ ደስም አያሰኛቸውም።» ያፈገፈጉ ሰዎች ሁኔታ ይህ ነው። በእግዚአብሔር ቃል ምንም ደስ አይላቸውም። እኛ ግን መልሰን ልናመጣቸውና እግዚአብሔር ጆሮአቸውን እንዲያገኝ ልንፈቅድለት እንፈልጋለን። ከቍጥር 14 ጀምረህ አንብብ፦ «ሰላም ሳይኖር፦ ‹ሰላም፥ ሰላም› እያሉ የሕዝቤን ሴት ልጅ ስብራት በቸልታ ፈወሱ። ርኵሰትን ባደረጉ ጊዜ አፈሩን? ፈጽሞ አላፈሩም፥ ማፈርንም አያውቁም፤ ስለዚህ ከሚወድቁት ጋር ይወድቃሉ፤ በምጐበኛቸውም ጊዜ ይዋረዳሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመንገድ ላይ ቁሙ፥ ተመልከቱም፥ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት ናት? በእርስዋም ላይ ሂዱ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ። እነርሱ ግን፦ ‹አንሄድባትም› አሉ። ደግሞም፦ ‹የመለከቱን ድምፅ አድምጡ› ብዬ ጠባቂዎችን በላያችሁ አቆምሁ። እነርሱ ግን፦ ‹አናደምጥም› አሉ።»
አይሁድ ወደ ኋላ ባፈገፈጉ ጊዜ ሁኔታቸው ይህ ነበር። ከቀደሙት መንገዶች ፈቀቅ ብለው ነበር። ያፈገፈጉ ሰዎችም ሁኔታ ይህ ነው። ከመልካሙ የጥንት መጽሐፍ ርቀዋል። አዳምና ሔዋን የወደቁት የእግዚአብሔርን ቃል ባለመስማታቸው ነው። የእግዚአብሔርን ቃል አላመኑም፤ ፈታኙን ግን አመኑ። ያፈገፈጉ ሰዎች የሚወድቁት በዚህ መንገድ ነው — ከእግዚአብሔር ቃል ፊታቸውን በማዞር።
በኤርምያስ ምዕራፍ 2 እግዚአብሔር አባት ልጁን እንደሚማጸን እነርሱን ሲማጸን እናገኘዋለን። «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከእኔ የራቁ፥ ከንቱነትንም የተከተሉ፥ ከንቱም የሆኑ አባቶቻችሁ በእኔ ዘንድ ምን በደል አገኙ? … ስለዚህ ገና እከራከራችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከልጆቻችሁም ልጆች ጋር እከራከራለሁ … ሕዝቤ ሁለት ክፉ ነገር አድርገዋልና፤ እኔን የሕይወትን ውኃ ምንጭ ትተዋል፥ ውኃንም ሊይዙ የማይችሉትን የተቀደዱትን ጕድጓዶች ለራሳቸው ቈፍረዋል።»
እንግዲህ ያፈገፈጉ ሰዎች እንዲያስተውሉት የምንፈልገው አንድ ነገር አለ፤ ይኸውም ጌታ ከቶ እንዳልተዋቸው፣ እነርሱ ግን እንደ ተዉት ነው! ጌታ ከቶ ትቶአቸው አልሄደም፤ እነርሱ ግን ትተውት ሄዱ! ደግሞም ይህን ያደረጉት ያለ አንዳች ምክንያት ነው! እርሱ «ከእኔ የራቁ አባቶቻችሁ በእኔ ዘንድ ምን በደል አገኙ?» ይላል። መጀመሪያ ወደ እርሱ በመጣህ ጊዜ እንደ ነበረው እግዚአብሔር ዛሬም ያው አይደለምን? እግዚአብሔር ተለውጦአልን? ሰዎች እግዚአብሔር የተለወጠ ይመስላቸዋል፤ ጥፋቱ ግን የእነርሱ ነው። አንተ ያፈገፈግህ ሰው ሆይ፣ «ትተኸው ከእርሱ የራቅኸው በእግዚአብሔር ዘንድ ምን በደል አግኝተህ ነው?» ብዬ እጠይቅሃለሁ። እርሱ እንደሚለው ውኃን ሊይዙ የማይችሉትን የተቀደዱትን ጕድጓዶች ለራስህ ቈፍረሃል። ዓለም አዲሱን ባሕርይ ሊያረካ አይችልም። ከሰማያዊው ባሕርይ ተካፋይ የሆነችውን ነፍስ ምንም ምድራዊ ጕድጓድ ሊያረካት አይችልም። የሕይወትን ውኃ ቀምሰው ከዚያ በኋላ ስተው በዓለም ምንጮች ዘንድ መታደስን የሚፈልጉትን ክብር፣ ሀብትና የዚህ ዓለም ተድላ አያረኳቸውም። ምድራዊ ጕድጓዶች ይደርቃሉ። መንፈሳዊ ጥምን ሊያረኩ አይችሉም።
ደግሞም በቍጥር 32፦ «ቈንጆ ጌጥዋን፥ ሙሽራም ልብስዋን ትረሳለችን? ሕዝቤ ግን ቍጥር የሌለው ዘመን ረስተውኛል።» እግዚአብሔር ባፈገፈገው ሰው ላይ የሚያቀርበው ክስ ይህ ነው። «ቍጥር የሌለው ዘመን ረስተውኛል።»
ብዙ ጊዜ ወጣት ሴቶችን «ወዳጄ ሆይ፣ ከጌታ ይልቅ ስለ ጕትቻሽ ታስቢያለሽ» ብዬ አስደንግጫቸዋለሁ። መልሱም «አይደለም፤ እንደዚያ አላደርግም» የሚል ነበር። ነገር ግን «አንዱ ቢጠፋብሽ አትጨነቂምን? ልትፈልጊውስ አትነሺምን?» ብዬ በጠየቅሁ ጊዜ መልሱ «እንግዲህ፣ አዎን፤ የምጨነቅ ይመስለኛል» የሚል ሆነ። ከጌታ ፊታቸውን ቢመልሱም ግን ይህ አንዳችም አላስጨነቃቸውም ነበር፤ ያገኙትም ዘንድ አልፈለጉትም።
በአንድ ወቅት ከጌታ ጋር በኅብረትና በዕለታዊ ግንኙነት የነበሩ ስንቶች ዛሬ ከክቡር ነፍሳቸው ይልቅ ስለ ልብሳቸውና ስለ ጌጣቸው ያስባሉ! ፍቅር መረሳትን አይወድም። ልጆቻቸው ትተዋቸው ሄደው አንዲት ቃል እንኳ ባይጽፉላቸው ወይም የፍቅራቸውን አንዳች መታሰቢያ ባይልኩላቸው እናቶች ልባቸው ይሰበር ነበር፤ እግዚአብሔርም ወላጅ በተሳሳቱ ውድ ልጆቹ ላይ እንደሚማጸን ወደ ኋላ ባፈገፈጉ ሰዎች ላይ ይማጸናል። መልሶ ሊማርካቸው ይሞክራል። «ትተውኝ የሄዳችሁት ምን አድርጌአችሁ ነው?» ብሎ ይጠይቃል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ ውስጥ የሚገኙት እጅግ ርኅሩኅና አፍቃሪ ቃላት ያለ ምክንያት ትተውት ለሄዱት ይሖዋ የተናገራቸው ናቸው። ኤርምያስ 2:19።
እንደዚህ ካሉት ጋር እንዴት እንደሚዋቀስ ስማ፦ (ኤርምያስ 2:19።) «ክፋትህ ይገሥጽሃል፥ ክዳትህም ይዘልፍሃል፤ አምላክህን እግዚአብሔርን መተውህ፥ እኔንም መፍራት በአንተ ዘንድ አለመኖሩ ክፉና መራራ ነገር እንደ ሆነ እወቅ፥ እይም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።»
በመቶዎች የሚቈጠሩ ያፈገፈጉ ሰዎች ሲመለሱ አይቻለሁ ብል አጋንኜ አይደለም፤ ጌታን መተው ክፉና መራራ ነገር ሆኖ እንዳላገኙት ጠይቄአቸዋለሁ። ጌታን ያወቀ እውነተኛ ያፈገፈገ ሰው ከእርሱ ፊትን መመለስ ክፉና መራራ ነገር እንደ ሆነ የማያምን አንድ እንኳ ልታገኝ አትችልም፤ የተቅበዘበዙትን ለመመለስ ከዚያው ቍጥር የበለጠ የሚጠቀሙበት አንድም ጥቅስ አላውቅም። ወደ ሩቅ አገር ተቅበዝብዘህ ብትሆን፣ ይህ ጥቅስ አንተንም ይመልስህ።
ሎጥን ተመልከት። ክፉና መራራ ነገር ሆኖ አላገኘውምን? በሰዶም ሃያ ዓመት ኖረ፤ አንድም ሰው ወደ እምነት አልመለሰም። በዓለም ዓይን ተሳክቶለት ነበር። ሰዎች በሰዶም ሁሉ ከሚገኙት እጅግ ተሰሚነት ካላቸውና ከተከበሩ ሰዎች አንዱ እንደ ሆነ ይነግሩህ ነበር። ነገር ግን ወዮ! ወዮ! ቤተሰቡን አጠፋ። ያ ሽማግሌ ያፈገፈገ ሰው ልጆቹን ካስጠነቀቀና እነርሱም ጆሮ ዳባ ልበስ ካሉት በኋላ በእኩለ ሌሊት በሰዶም መንገዶች ሲሄድ ማየት እጅግ የሚያሳዝን ትዕይንት ነው።
ባልና ሚስት ወደ ኋላ አፈግፍገው ልጆቻቸው ፈጽመው ያልጠፉበትን አንድም አላውቅም። በሃይማኖት ያላግጣሉ፤ በወላጆቻቸውም ይሣለቃሉ፦ «ክፋትህ ይገሥጽሃል፥ ክዳትህም ይዘልፍሃል!» ዳዊትስ እንዲሁ ሆኖ አላገኘውምን? «ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ፥ ልጄ አቤሴሎም ሆይ! በአንተ ፋንታ እኔ በሞትሁ ምነው! አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ፥ ልጄ ሆይ!» እያለ ሲጮኽ ተመልከተው። ይህን ጭንቀት ያመጣበት የልጁ ሞት ሳይሆን ጥፋቱ ይመስለኛል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ከአንድ ሽማግሌ ጋር እኩለ ሌሊት እስኪያልፍ ድረስ ስነጋገር እንደ ቆየሁ ትዝ ይለኛል። ለብዙ ዓመታት በኃጢአት ምድረ በዳ ተራሮች ላይ ሲቅበዘበዝ ኖሮ ነበር። በዚያች ሌሊት ሊመለስ ፈለገ። ጸለይን፤ ጸለይን፤ ደግሞም ጸለይን፤ ብርሃን እስኪበራለት ድረስ ጸለይን፤ እርሱም ደስ እያለው ሄደ። በማግሥቱ ሌሊት ስሰብክ ከፊቴ ተቀመጠ፤ በሕይወቴ ሁሉ ማንንም እንደዚያ አዝኖና ጐስቍሎ አይቼ የማላውቅ ይመስለኛል። ወደ ጠያቂዎች ክፍል ተከተለኝ። «ችግሩ ምንድን ነው?» ብዬ ጠየቅሁት። «ዓይንህ ከመድኃኒቱ ላይ ተነሥቶአልን? ጥርጣሬዎችህ ተመልሰዋልን?» እርሱም «አይደለም፤ ያ አይደለም» አለ። «ወደ ሥራዬ አልሄድሁም፤ ይህን ቀን ሁሉ ልጆቼን ስጐበኝ ዋልሁ። ሁሉም ያገቡ ናቸው፤ በዚህችም ከተማ ይኖራሉ። ከቤት ወደ ቤት ሄድሁ፤ ነገር ግን ያልተሣለቀብኝ አንድ እንኳ አልነበረም። ይህ የሕይወቴ እጅግ ጨለማ ቀን ነው። ያደረግሁትን አሁን ነቃሁበት። ልጆቼን ወደ ዓለም ወስጃቸዋለሁ፤ አሁንም ከዚያ ላወጣቸው አልችልም።» ጌታ የማዳኑን ደስታ መልሶለት ነበር፤ ነገር ግን የመተላለፉ መራራ ውጤት በዚያ ነበር። የራሳችሁን ተሞክሮ ብትቃኙ እንደዚህ ያሉ ምሳሌዎች ደጋግመው ሲከሰቱ ታገኛላችሁ። ከብዙ ዓመታት በፊት እግዚአብሔርን እያገለገሉ ወደ ከተማችሁ የመጡ ብዙዎች በብልጽግናቸው ረስተውታል፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውስ የት አሉ? ጌታን ትተው ወደ ዓለም ደካማና የሚናቅ መጀመሪያ ትምህርት የተመለሱትን አባትና እናት አሳዩኝ፤ ልጆቻቸው ወደ ጥፋት በሚወስደው አውራ መንገድ ላይ ካልሆኑ እኔ ተሳስቻለሁ።
ታማኞች መሆን ስለምንፈልግ እነዚህን ያፈገፈጉ ሰዎች እናስጠነቅቃቸዋለን። ስለ አደጋ ማስጠንቀቅ የፍቅር ምልክት ነው። ለጥቂት ጊዜ እንደ ጠላቶች እንታይ ይሆናል፤ ነገር ግን እውነተኞቹ ወዳጆች የማስጠንቀቂያ ድምፅን ከፍ የሚያደርጉት ናቸው። ለእስራኤል ከሙሴ የበለጠ እውነተኛ ወዳጅ አልነበረውም። በኤርምያስ እግዚአብሔር ሕዝቡን ወደ እርሱ እንዲመልሳቸው የሚያለቅስ ነቢይ ሰጣቸው፤ እነርሱ ግን እግዚአብሔርን ጣሉት። ከግብፅ ያወጣቸውን፣ በምድረ በዳም ወደ ተስፋይቱ ምድር የመራቸውን አምላክ ረሱ። በብልጽግናቸው ረሱት፤ ፊታቸውንም መለሱ። ጌታ የሚሆነውን ነግሮአቸው ነበር። (ዘዳግም 28።) የሆነውንም ተመልከቱ። የእግዚአብሔርን ቃል ያቃለለው ንጉሥ በናቡከደነፆር ተማረከ፤ ልጆቹም በፊቱ ቀርበው አንድም ሳይቀር ታረዱ፤ ዓይኖቹም ከራሱ ተነቅለው ወጡ፤ በናስ ሰንሰለትም ታስሮ በባቢሎን ወደ ወኅኒ ተጣለ። (2ኛ ነገሥት 25:7።) የዘራውን ያጨደው በዚህ መንገድ ነው። በእርግጥ ወደ ኋላ ማፈግፈግ ክፉና መራራ ነገር ነው፤ ጌታ ግን በቃሉ መልእክት አንተን መልሶ ሊማርክህ ይወዳል።
በኤርምያስ 8:5 እንዲህ እናነባለን፦ «ይህ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ስለ ምን በዘላለም ክዳት ከዳ? ተንኰልን አጥብቀው ይዘዋል፤ ይመለሱ ዘንድ እንቢ ብለዋል።» ጌታ በእነርሱ ላይ የሚያቀርበው ክስ ይህ ነው። «ይመለሱ ዘንድ እንቢ ብለዋል።» «አደመጥሁ ሰማሁም፤ ቅን ነገርን ግን አልተናገሩም፤ ‹ምን አደረግሁ?› ብሎ ከክፋቱ ንስሐ የገባ ሰው የለም፤ ፈረስ ወደ ሰልፍ እንደሚሮጥ እያንዳንዱ ወደ ሩጫው ተመለሰ። በሰማይ ያለ ሽመላ እንኳ የተወሰነላትን ጊዜ ታውቃለች፤ ዋኖስና ኵርኵም ጨረባም የመምጣታቸውን ጊዜ ይጠብቃሉ፤ ሕዝቤ ግን የእግዚአብሔርን ፍርድ አያውቁም።»
እንግዲህ ተመልከት፦ «አደመጥሁ ሰማሁም፤ ቅን ነገርን ግን አልተናገሩም።» የቤተሰብ መሠዊያ የለም! መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የለም! በእልፍኝ ውስጥ ማምለክ የለም! እግዚአብሔር ሊሰማ ዝቅ ይላል፤ ሕዝቡ ግን ፊታቸውን መልሰዋል! ይቅርታንና መመለስን አጥብቆ የሚፈልግ ንስሐ የገባ ያፈገፈገ ሰው ቢኖር፣ በኤርምያስ 3:12 ከሚገኙት ቃላት የበለጠ ርኅሩኅ ቃላት አታገኝም፦ «ሂድ፥ እነዚህንም ቃላት ወደ ሰሜን ተናገር፥ እንዲህም በል፦ ከዳተኛው እስራኤል ሆይ፥ ተመለስ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እኔ መሐሪ ነኝና ቍጣዬን በእናንተ ላይ አላወርድም፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ለዘላለምም አልቈጣም።» አሁንም አስተውል፦ «በአምላክህ በእግዚአብሔር ላይ እንደ ተላለፍህ፥ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች መንገድህን ለእንግዶች እንደ በተንህ፥ ቃሌንም እንዳልሰማችሁ በደልህን ብቻ እወቅ፥ ይላል እግዚአብሔር። እናንተ ከዳተኞች ልጆች፥ ተመለሱ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እኔ ባላችሁ ነኝና» — እግዚአብሔር መጥቶ «እኔ ባላችሁ ነኝ! — ከአንድ ከተማ አንድ፥ ከአንድ ወገን ሁለት እወስዳችኋለሁ፥ ወደ ጽዮንም አመጣችኋለሁ» ሲል አስበው።
«በደልህን ብቻ እወቅ።» ያንን ክፍል ስንት ጊዜ ላፈገፈገ ሰው አሳይቼዋለሁ! «እወቀው»፤ እግዚአብሔርም ይቅር እልሃለሁ ይላል። አንድ ሰው «ይህን ማን ተናገረ? በእውነት በዚያ ተጽፎአልን?» ብሎ እንደ ጠየቀ ትዝ ይለኛል። እኔም «በደልህን ብቻ እወቅ» የሚለውን ክፍል አሳየሁት፤ ሰውየውም በጕልበቱ ተንበርክኮ «አምላኬ ሆይ፣ በድያለሁ» ብሎ ጮኸ፤ ጌታም በዚያው ቅጽበት መለሰው። ተቅበዝብዘህ ብትሆን፣ እንድትመለስ ይፈልጋል።
በሌላ ስፍራም «ኤፍሬም ሆይ፥ ምን ላድርግልህ? ይሁዳ ሆይ፥ ምን ላድርግልህ? ቸርነታችሁ እንደ ማለዳ ደመና፥ ማልዶም እንደሚያልፍ ጠል ነውና» ይላል (ሆሴዕ 6:4)። ርኅራኄውና ፍቅሩ ድንቅ ነው!
በኤርምያስ 3:22፤ «እናንተ ከዳተኞች ልጆች፥ ተመለሱ፥ ክዳታችሁንም እፈውሳለሁ። እነሆ፥ አንተ አምላካችን እግዚአብሔር ነህና ወደ አንተ መጥተናል።» ወደ ኋላ ባፈገፈገው ሰው አፍ ውስጥ ቃላትን ያኖራል። ብቻ ና፤ ብትመጣም በቸርነት ይቀበልሃል፤ በፈቃዱም ይወድድሃል።
በሆሴዕ 14:1, 2, 4፦ «እስራኤል ሆይ፥ በኃጢአትህ ወድቀሃልና ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ተመለስ። ቃላትን ይዛችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ (በአፋችሁ ቃላትን ያኖራል)፤ እንዲህም በሉት፦ ‹ኃጢአትን ሁሉ አስወግድ፥ በቸርነትም ተቀበለን፤ እኛም የከንፈራችንን ወይፈኖች እናቀርባለን› … ክዳታቸውን እፈውሳለሁ፥ በፈቃዴም እወድዳቸዋለሁ፤ ቍጣዬ ከእርሱ ተመልሶአልና።» እስኪ ያንን ልብ በል፤ ተመለሱ! ተመለሱ!! ተመለሱ!!! የሚለው ቃል በእነዚህ ክፍሎች ሁሉ ውስጥ ያስተጋባል።
እንግዲህ ተቅበዝብዘህ ብትሆን፣ እርሱ አንተን ሳይሆን አንተ እርሱን እንደ ተውህ አስታውስ። ካፈገፈገ ሰው ጕድጓድ መውጣት ያለብህ በገባህበት በዚያው መንገድ ነው። ጌታን ትተህ በሄድህበት በዚያው መንገድ ብትመለስ፣ አሁን ባለህበት ስፍራ ታገኘዋለህ።
ክርስቶስን እንደ ማንኛውም ምድራዊ ወዳጅ ብንይዘው ኖሮ ከቶ ትተነው አንሄድም ነበር፤ ያፈገፈገ ሰውም ከቶ ባልኖረ ነበር። ለአንድ ሳምንት ብቻ በአንዲት ከተማ ብቆይ፣ ካፈራኋቸው ወዳጆች ጋር ሳልጨባበጥና «ደኅና ሁኑ» ሳልላቸው ጥዬ መሄድን አላስብም። ለማንም አንዲት ቃል ሳልናገር ባቡር ይዤ ብሄድ በትክክል እወቀሳለሁ። «ምን ሆነ?» የሚል ጩኸት ይሆናል። ነገር ግን ያፈገፈገ ሰው ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ «ደኅና ሁን» ሲል ሰምተህ ታውቃለህን? ወደ እልፍኙ ገብቶ «ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ አሥር፣ ሃያ ወይም ሠላሳ ዓመት አውቄሃለሁ፤ ነገር ግን አገልግሎትህ ሰልችቶኛል፤ ቀንበርህ ልዝብ፣ ሸክምህም ቀሊል አይደለም፤ ስለዚህ ወደ ዓለም፣ ወደ ግብፅ የሥጋ ምንቸቶች እመለሳለሁ። ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ ደኅና ሁን! በሰላም ቈይ» ሲል? ይህን ሰምተህ ታውቃለህን? አይደለም፤ ከቶ አልሰማህም፤ ከቶም አትሰማም። እልሃለሁ፣ ወደ እልፍኝህ ገብተህ ዓለምን ዘግተህ ከጌታ ጋር ኅብረት ብታደርግ ልትተወው አትችልም። የልብህ ቋንቋ «ወደ ማን እንሄዳለን?» ከአንተ በቀር? «አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ» (ዮሐንስ 6:68) የሚል ይሆናል። እንደዚያ አድርገህ ብትይዘው ወደ ዓለም ልትመለስ አትችልም ነበር። አንተ ግን ትተኸው ኰበለልህ። ቍጥር የሌለው ዘመን ረስተኸዋል። ዛሬ ተመለስ፤ ልክ እንዳለህ ሆነህ ና! እግዚአብሔር የማዳኑን ደስታ እስኪመልስልህ ድረስ እንዳታርፍ ቍርጥ ውሳኔ አድርግ።
በኮርንዋል የሚኖር አንድ ጨዋ ሰው በአንድ ወቅት ወደ ኋላ ያፈገፈገ እንደ ሆነ የሚያውቀውን አንድ ክርስቲያን በመንገድ ላይ አገኘው። ወደ እርሱ ቀርቦ «እስኪ ንገረኝ፣ በአንተና በጌታ ኢየሱስ መካከል አንዳች መቀያየም የለምን?» አለው። ሰውየው ራሱን ደፍቶ «አዎን» አለ። ጨዋው ሰውም «እንግዲያስ ምን አደረገህ?» አለው። መልሱ የእንባ ጎርፍ ነበር።
በራእይ 2:4-5 እንዲህ እናነባለን፦ «ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ነገር አለኝ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና። እንግዲህ ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፤ አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ።» «የቀደመውን ሥራ ማድረግ»ን በተመለከተ አንዳንድ ሰዎች ከሚሠሩት ስሕተት ልጠብቅህ እወዳለሁ። ብዙዎች ያንኑ ተሞክሮ እንደ ገና ሊያገኙ እንደሚገባቸው ያስባሉ። ይህ በሺህ የሚቈጠሩ ሰዎችን ለወራት ያለ ሰላም አቆይቶአቸዋል፤ የመጀመሪያው ተሞክሮአቸው እንዲታደስ ሲጠባበቁ ኖረዋልና። መጀመሪያ ወደ ጌታ በመጣህ ጊዜ የነበረህን ያንኑ ተሞክሮ ከቶ አታገኝም። እግዚአብሔር ራሱን ከቶ አይደግምም። ከምድር ሚሊዮኖች መካከል አንድ ዓይነት የሚመስሉ ወይም አንድ ዓይነት የሚያስቡ ሁለት ሰዎች የሉም። ሁለት ሰዎችን መለየት አልችልም ትል ይሆናል፤ ነገር ግን በሚገባ ስትተዋወቃቸው ልዩነታቸውን ቶሎ ልትለይ ትችላለህ። እንዲሁም ማንም ሰው ያንኑ ተሞክሮ ሁለተኛ ጊዜ አያገኝም። እግዚአብሔር ደስታውን ወደ ነፍስህ ቢመልስ በራሱ መንገድ ያድርገው። እግዚአብሔር እንዲባርክህ መንገድን አትቀድለት። ከሁለት ወይም ከሃያ ዓመት በፊት የነበረህን ያንኑ ተሞክሮ አትጠብቅ። አዲስ ተሞክሮ ይኖርሃል፤ እግዚአብሔርም በራሱ መንገድ ይይዝሃል። ኃጢአትህን ብትናዘዝና ከትእዛዛቱ መንገድ እንደ ተቅበዘበዝህ ብትነግረው የማዳኑን ደስታ ይመልስልሃል።
ጴጥሮስ የወደቀበትን ሁኔታ እንድታስተውል እወዳለሁ፤ ሁሉም የሚወድቁት በአብዛኛው በዚሁ መንገድ ይመስለኛል። ላልወደቁትም የማስጠንቀቂያ ድምፅ ከፍ ማድረግ እወዳለሁ። «እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።» (1ኛ ቆሮንቶስ 10:12)። ከሃያ አምስት ዓመት በፊት — ከተለወጥሁም በኋላ ለመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት — ለሃያ ዓመት ጸንቼ መቆም ብችል ከዚያ በኋላ መውደቅን መፍራት አያስፈልገኝም ብዬ አስብ ነበር። ነገር ግን ወደ መስቀሉ ይበልጥ በቀረብህ ቍጥር ውጊያው ይበልጥ ይጠነክራል። ሰይጣን ከፍ ብሎ ያነጣጥራል። ወደ አሥራ ሁለቱ መካከል ገባ፤ ገንዘብ ያዡን — የአስቆሮቱን ይሁዳን፣ የሐዋርያቱንም አለቃ — ጴጥሮስን — ለይቶ ያዘ። የወደቁ ሰዎች አብዛኞቹ የወደቁት በባሕርያቸው ብርቱ ጎን በኩል ነው። የኤድንበራ ምሽግ በተሳካ ሁኔታ የተደፈረበት ብቸኛው ጎን ዓለቶቹ እጅግ ገደላማ በሆኑበትና ጠባቂዎቹ ራሳቸውን በደኅና እንዳሉ በቈጠሩበት ስፍራ እንደ ሆነ ተነግሮኛል። ማንም ሰው በአንድ ነጥብ ላይ ዲያብሎስን ለመቃወም በቂ ብርታት እንዳለው ቢያስብ በዚያ ልዩ ጥበቃ ያስፈልገዋል፤ ፈታኙ የሚመጣው በዚያ በኩል ነውና።
አብርሃም በእምነት ቤተሰብ ራስ ላይ የቆመ ያህል ነው፤ የእምነት ልጆችም ትውልዳቸውን ወደ አብርሃም ይቈጥራሉ ሊባል ይችላል፤ ቢሆንም በግብፅ ሚስቱን ካደ። (ዘፍጥረት 12።) ሙሴ በየዋህነቱ የታወቀ ነበር፤ ቢሆንም ማኅበሩና እንስሶቻቸው የሚጠጡት ውኃ እንዲያገኙ ዓለቱን እንዲናገረው በጌታ በታዘዘ ጊዜ፣ በአንዲት የችኰላ ድርጊትና ንግግር ምክንያት ከተስፋይቱ ምድር ተከለከለ። «እናንተ ዓመፀኞች፥ ስሙ፤ ከዚህ ዓለት ውኃ እናወጣላችኋለንን?» (ዘኍልቍ 20:10)።
ኤልያስ በድፍረቱ የታወቀ ነበር፤ ቢሆንም ከአንዲት ሴት በደረሰው መልእክት ምክንያት እንደ ፈሪ የአንድ ቀን መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሄዶ በክትክታ ዛፍ ሥር ተሸሸገ፤ ይሞትም ዘንድ ለራሱ ለመነ። (1ኛ ነገሥት 19።) እንጠንቀቅ። ሰውየው ማንም ይሁን — በመድረክ ላይ የሚሰብክ ሊሆን ይችላል — በራሱ ቢታበይ መውደቁ አይቀርም። የክርስቶስ ተከታዮች የሆንን እኛ ትሑታን እንድንሆንና በትሕትና እንድንጠበቅ ዘወትር መጸለይ ያስፈልገናል። እግዚአብሔር የሙሴን ፊት ሌሎች ሰዎች እንዲያዩት አድርጎ አበራው፤ ሙሴ ራሱ ግን ፊቱ እንደሚያበራ አላወቀም ነበር፤ ሰውም በልቡ ይበልጥ ቅዱስ በሆነ ቍጥር ዕለታዊ ሕይወቱና አካሄዱ ለውጭው ዓለም ይበልጥ ይገለጣል። አንዳንድ ሰዎች ምን ያህል ትሑታን እንደ ሆኑ ያወራሉ፤ እውነተኛ ትሕትና ቢኖራቸው ግን ይህን ማስታወቅ ባላስፈለጋቸው ነበር። አስፈላጊ አይደለም። የመብራት ማማ በአቅራቢያ መኖሩን ለማስታወቅ ከበሮ እንዲመታለት ወይም መለከት እንዲነፋለት አያደርግም፤ ራሱ ምስክር ነው። እንዲሁም እውነተኛው ብርሃን በውስጣችን ካለ ራሱን ይገልጣል። ከሁሉ የበለጠ እግዚአብሔርን መምሰል ያላቸው ከሁሉ የበለጠ ጩኸት የሚያሰሙት አይደሉም። ከምኖርበት ብዙ ሳይርቅ አንድ ጅረት — ስኮትላንዳውያን እንደሚሉት ትንሽ «በርን» — አለ፤ ከብርቱ ዝናብ በኋላ የውኃውን ጩኸት ከሩቅ መስማት ትችላለህ፤ ነገር ግን ጥቂት ደስ የሚያሰኙ የአየር ቀናት ይምጡ፤ ጅረቱ ጸጥ ሊል ምንም አይቀረውም። ከቤቴ አጠገብ ግን ዓመቱን ሙሉ በጥልቅና ግርማ ባለው ጐዳናው ሲፈስስ ድምፁን በሕይወቴ ከቶ ሰምቼ የማላውቀው አንድ ወንዝ አለ። ጮኸን ሳናውጅ መገኘቱ ግልጽ እንዲሆን የእግዚአብሔር ፍቅር በውስጣችን እጅግ ሊበዛ ይገባዋል።
የጴጥሮስ ውድቀት የመጀመሪያው እርምጃ በራሱ መታመኑ ነበር። ጌታ አስጠነቀቀው። ጌታ እንዲህ አለ፦ «ስምዖን፥ ስምዖን ሆይ፥ እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ» (ሉቃስ 22:31-32)። ጴጥሮስ ግን «ወደ ወኅኒም ወደ ሞትም ከአንተ ጋር ለመሄድ የተዘጋጀሁ ነኝ» አለ። «ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም።» (ማቴዎስ 26:33።) «ያዕቆብና ዮሐንስ፣ ሌሎቹም ትተውህ ይሄዱ ይሆናል፤ በእኔ ግን ልትተማመን ትችላለህ!» ጌታ ግን አስጠነቀቀው፦ «ጴጥሮስ ሆይ፥ እልሃለሁ፥ እንዳታውቀኝ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዛሬ ዶሮ አይጮኽም።» (ሉቃስ 22:34።)
ጌታ ቢገሥጸውም ጴጥሮስ እስከ ሞት ድረስ ሊከተለው የተዘጋጀ እንደ ሆነ ተናገረ። ያ ትምክህት ብዙ ጊዜ የውድቀት ቀዳሚ ነው። በትሕትናና በዝግታ እንመላለስ። ታላቅ ፈታኝ አለብን፤ ባልተጠነቀቅንበትም ሰዓት ተሰናክለን ልንወድቅና በክርስቶስ ላይ ነቀፋ ልናመጣ እንችላለን።
የጴጥሮስ ውድቀት ቀጣዩ እርምጃ መተኛቱ ነበር። ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን አባብሎ ሊያስተኛት ከቻለ ሥራውን በእግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ በኩል ይሠራል። ጴጥሮስ በጌቴሴማኒ አንዲት አጭር ሰዓት ከመትጋት ይልቅ አንቀላፋ፤ ጌታም «እንዲሁም ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ ልትተጉ አልቻላችሁምን?» ብሎ ጠየቀው። (ማቴዎስ 26:40።) ቀጥሎ ያደረገው በሥጋ ብርታት መዋጋት ነበር። ጌታ ደግሞ ገሠጸውና «ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ» አለ። (ማቴዎስ 26:52።) ኢየሱስ ጴጥሮስ ያደረገውን ማረም ነበረበት። ቀጥሎ «ሩቅ ሆኖ ተከተለው»። እርምጃ በእርምጃ እየራቀ ይሄዳል። የእግዚአብሔር ልጅ ሩቅ ሆኖ ሲከተል የሚያሳዝን ነገር ነው። ከዓለማውያን ወዳጆች ጋር ሲወዳጅና ተጽዕኖውን በተሳሳተው ወገን ላይ ሲጥል ስታየው ሩቅ ሆኖ እየተከተለ ነው፤ በቤተሰቡ የቀድሞ ስም ላይ ውርደት ለመምጣቱ፣ ኢየሱስ ክርስቶስም በወዳጆቹ ቤት ለመቍሰሉ ብዙ ጊዜ አይቈይም። ሰውየው በምሳሌነቱ ሌሎችን ያሰናክላል፤ ያስወድቃልም።
ቀጥሎ — ጴጥሮስ ከክርስቶስ ጠላቶች ጋር ይቀራረባል፤ ይወዳጃልም። አንዲት ገረድ ለዚህ ደፋር ጴጥሮስ «አንተ ደግሞ ከገሊላው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ» ትለዋለች። እርሱ ግን «የምትዪውን አላውቀውም» ብሎ በሁሉ ፊት ካደ። ወደ በሩም በወጣ ጊዜ ሌላይቱ ገረድ አየችውና በዚያ ላሉት «ይህ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበረ» አለች። ዳግመኛም በመሐላ ካደ። «ሰውየውን አላውቀውም።» ሌላ ሰዓት አለፈ፤ አሁንም ያለበትን ሁኔታ አላስተዋለም፤ ያን ጊዜ ሌላው አነጋገሩ ስለ ገለጠው ገሊላዊ እንደ ሆነ አስረግጦ ተናገረ። እርሱም ተቈጣ፤ ሊራገምና ሊምልም ጀመረ፤ ጌታውንም ዳግመኛ ካደ፤ «ወዲያውም ዶሮ ጮኸ።» (ማቴዎስ 26:69-74።)
ከራስ መታበይ ጫፍ ከፍ ብሎ ይጀምራል፤ እርምጃ በእርምጃም ወደ ታች ይወርዳል፤ በመጨረሻም መራገም ጀምሮ ጌታውን ከቶ እንዳላወቀው ይምላል።
ጌታ ዞር ብሎ እንዲህ ሊለው ይችል ነበር፦ «ጴጥሮስ ሆይ፣ እንዲህ ቶሎ ረስተኸኛል ማለት እውነት ነውን? አማትህ በንዳድ ታማ ተኝታ በነበረ ጊዜ በሽታውን እንደ ገሠጽሁትና እንደ ለቀቃት አታስታውስምን? ‹ጌታ ሆይ፥ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከኔ ተለይ› ብለህ እስክትጮኽ ድረስ በዓሣው ብዛት የተደነቅኸውን አታስታውስምን? ‹ጌታ ሆይ፥ አድነኝ፤ አለዚያ እጠፋለሁ› ብለህ ለጮኽኸው ጩኸት መልስ እጄን ዘርግቼ በውኃው ውስጥ እንዳትሰጥም እንደ ጠበቅሁህ ታስታውሳለህን? በተራራው ላይ ተለውጬ በታየሁ ጊዜ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ሆነህ ‹ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ በዚህ ሦስት ዳስ እንሥራ› ያልኸኝን ረስተሃልን? በእራት ማዕድ ላይና በጌቴሴማኒ ከእኔ ጋር የነበርኸውን ረስተሃልን? እንዲህ ቶሎ ረስተኸኛል ማለት እውነት ነውን?» ጌታ እንደነዚህ ባሉ ጥያቄዎች ሊወቅሰው ይችል ነበር፤ ነገር ግን እንዲህ ያለውን ምንም አላደረገም። ጴጥሮስን አንድ ጊዜ ተመለከተው፤ በዚያም እይታ ውስጥ እጅግ ብዙ ፍቅር ስለ ነበረ የዚያን ደፋር ደቀ መዝሙር ልብ ሰበረው፤ እርሱም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።
ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ በኋላም የተሳሳተውን ደቀ መዝሙር እንዴት በርኅራኄ እንደ ያዘው ተመልከት። በመቃብሩ ዘንድ የነበረው መልአክ «ለደቀ መዛሙርቱ ለጴጥሮስም … ንገሩአቸው» ይላል። (ማርቆስ 16:7።) ጴጥሮስ ሦስት ጊዜ ቢክደውም ጌታ ጴጥሮስን አልረሳውም፤ ስለዚህ ይህ የቸርነት ልዩ መልእክት ንስሐ ወደ ገባው ደቀ መዝሙር እንዲደርስ አደረገ። እንዴት ያለ ርኅሩኅና አፍቃሪ መድኃኒት አለን!
ወዳጄ ሆይ፣ አንተ ከተቅበዘበዙት አንዱ ብትሆን፣ የጌታ የፍቅር እይታ መልሶ ይማርክህ፤ የማዳኑንም ደስታ ይመልስልህ።
ከመደምደሜ በፊት፣ እግዚአብሔር እነዚህን ገጾች ከሚያነቡ ያፈገፈጉ ሰዎች አንዳንዶቹን እንደሚመልስና ወደ ፊትም ለኅብረተሰቡ ጠቃሚ አባል፣ ለቤተ ክርስቲያንም ደማቅ ጌጥ እንደሚሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ ልበል። ዳዊት ባይመለስ ኖሮ ሠላሳ ሁለተኛው መዝሙር ባልኖረን ነበር፦ «መተላለፉ የተሰረየለት ኃጢአቱም የተከደነለት ምስጉን ነው»፤ ወይም ተመልሶ በመጣው በዚያው ያፈገፈገ ሰው የተጻፈው ያ ውብ ሃምሳ አንደኛው መዝሙር ባልኖረን ነበር። ሦስት ሺህ ሰዎች በተለወጡበት በበዓለ ኀምሳ ቀን የተሰበከውም ያ ድንቅ ስብከት — ተመልሶ በመጣው በሌላው ያፈገፈገ ሰው የተሰበከው — ባልኖረን ነበር።
እግዚአብሔር ሌሎች ያፈገፈጉ ሰዎችንም ይመልስ፤ ከቀድሞው ይልቅ ሺህ ጊዜ አብልጦ ለክብሩ ይጠቀምባቸው።
ምዕራፍ 9 ተጠናቋል
ወደ ኋላ ማፈግፈግ