የታደሰው እረኛ
የመግቢያ ማስታወሻ

ምዕራፍ 3 · 2 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ

የመግቢያ ማስታወሻ

«በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።» ሐዋርያት ሥራ 20:28

ጳውሎስ ለእነዚህ ሽማግሌዎች የሰጠው ምክር በእነርሱ ላይ ገዥ እንደ ነበረ ያረጋግጣል ብለው አንዳንዶች ቢያስቡም፣ ዛሬ ከጌታ ዘንድ የምንናገራችሁ እኛ እንዲህ ያለ መደምደሚያ ይወጣበታል ብለን ሳንሰጋ እንዲሁ በነጻነት ልናደርግ እንደምንችል ተስፋ እናደርጋለን። ሕዝባችንን በጌታ በላያቸው እንደ ተሾሙ ሹማምንት ሆነን የምናስተምር ብንሆንም፣ በእምነት ብቻ ሳይሆን በአገልግሎትም ወንድማማቾች እንደ መሆናችን አንዳችን ሌላውን ልናስተምር እንችላለን። በአደራ የተሰጡን ሕዝብ «እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ»፣ «በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ» ተብለው የታዘዙ ከሆነ፣ አስተማሪዎችም አንዱ ከሌላው በሥልጣን ወይም በማዕረግ ሳይበልጥ እርስ በርሳቸው እንዲሁ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም። እንደ ሕዝባችን ሁሉ እኛም የምንገድላቸው እነዚያው ኃጢአቶች፣ ሕያው ሊሆኑና ሊበረቱ የሚገባቸው እነዚያው ጸጋዎች አሉን፤ ከእነርሱ የሚበልጥ የምንሠራው ሥራ፣ የምናሸንፈውም የሚበልጥ ችግር አለብን፤ ስለዚህም ልንማር ባያስፈልገን እንኳ፣ እንደ እነርሱ ማስጠንቀቂያ ሊሰጠንና ልንነቃቃ ያስፈልገናል። ስለዚህ፣ ሌላ የምናደርገው ነገር ባይኖር እንኳ ለዚህ ብቻ ብለን እንዲህ ያሉ ስብሰባዎች ይበልጥ ደጋግመው ሊደረጉ ይገባል ብዬ እንደማስብ እመሰክራለሁ። ደግሞም ከእኛ መካከል እጅግ ትጉ የሆኑት ከመንጎቻቸው ጋር እንደሚያደርጉት፣ እኛም እርስ በርሳችን በግልጥና በቅርበት ልንነጋገር ይገባናል፤ አለዚያ የሰላ ምክርና ተግሣጽ የሚደርሳቸው እነርሱ ብቻ ቢሆኑ፣ በእምነት ጤናማና ሕያው የሚሆኑትም እነርሱ ብቻ ይሆናሉ። የጳውሎስ አሳብ ይህ እንደ ነበረ ለማረጋገጥ ለኤፌሶን ሽማግሌዎች ከሰጠው ከዚህ ቀስቃሽና ልብ የሚያቀልጥ ምክር ሌላ ማስረጃ አያስፈልገኝም። አጭር ስብከት ነው፤ ግን በቶሎ የሚማሩት አይደለም! የቤተ ክርስቲያን ጳጳሳትና አስተማሪዎች ጊዜያቸውን የወሰዱባቸውንና በዓለም ዘንድ የበለጠ ውዳሴ ያስገኙላቸውን ብዙ መጻሕፍት ቸል ብለውም ቢሆን ይህን አጭር ምክር በሚገባ ተምረውት ቢሆን ኖሮ፣ ለቤተ ክርስቲያንም ለራሳቸውም ምንኛ መልካም በሆነ ነበር! በዚህ ጥቅስ ላይ ንግግሬን በመቀጠል የሚከተለውን ቅደም ተከተል ለመከተል አስባለሁ፦

  • መጀመሪያ፣ ለራሳችን መጠንቀቅ ምን ማለት እንደ ሆነ እንመለከታለን።
  • ሁለተኛ፣ ለራሳችን ልንጠነቀቅ የሚገባን ስለ ምን እንደ ሆነ እናሳያለን።
  • ሦስተኛ፣ ለመንጋው ሁሉ መጠንቀቅ ምን ማለት እንደ ሆነ እንመረምራለን።
  • አራተኛ፣ ለመንጋው ሁሉ ልንጠነቀቅ የሚገባን በምን ሁኔታ እንደ ሆነ እናብራራለን።
  • አምስተኛ፣ ለመንጋው ሁሉ እንድንጠነቀቅ የሚያነሣሡንን አንዳንድ ምክንያቶች እናቀርባለን።
  • በመጨረሻ፣ ከጠቅላላው ነገር አንዳንድ ተግባራዊ ትምህርቶችን እናወጣለን።
ቀዳሚ ቀጣይ